Saturday, 04 July 2020 00:00

“ሰው ከሞተ በኋላ ሬሳ እንደ ቅርጫ መቀራመትና በሬሳ ፖለቲካ መስራት ያስነውራል”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 - “ብዙ ነገሩ ከቦብ ማርሌይ ጋር ይመሳሰላል”
                           (አርቲስት ፀጋዬ ደንደአ)

          ሀጫሉን የማውቀው ከልጅነቱ ነው፤ አምቦ  አንድ አካባቢ ነው ኑሯችን፤ ከመተዋወቅ ባለፈ የቅርብ ዘመዴም ነው። በቤተሰብ ደረጃ ያሳደግነው ልጅ ነው።
ሰኞ ምሽት 3፡00 አካባቢ ነው የተደወለልን፤ ከዚያ በኋላ ወዲያውኑ ወደ ጳውሎስ ሆስፒታል ሄድን፡፡ እዛው አደርን፤ ነገር ግን ሊተርፍ ባለመቻሉ በነጋታው ከመንግሥትም በኩል፣ ከቤተ ዘመድም ከሁሉም የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ ቤተሰቦቹ አምቦ እንዲቀበር ስለፈለጉ አስክሬን ይዘን መሄድ ጀመርን።
የአርቲስት ሀጫሉን ባህሪ በተመለከተ በአርቱ በኩል የሚጫወተው ካራክተር ሌላ ነው። የቤተሰብ አስተዳደግና የግል ባህሪው የተለየ ነው። አርት ስትሰሪ የካራክተር ባህሪ ነው የምትሰራው የግልና የተፈጥሮ ባህሪሽ ሌላ ነው። ሀጫሉም ለምሳሌ የሚሰራው ካራክተር ቁጡ ከሆነ በስራው የሚያንፀባርቀው ያንኑ ነው። የልጁን የተፈጥሮ ባህሪ ስንመለከት ተጫዋች ነው። አኩርፎ አይተነው አናውቅም። ጨዋታ አዋቂ ነው፤ መድረክ ላይ እንደሚታየው አይደለም። የተፈጥሮ ባህሪው መድረክ ላይ ከሚታየው በጣም የተለየ ነው።
የሀጫሉ የሙዚቃ ተሰጥኦ “ፕሮፌሽናል” የሚያሰኘው ነው፡፡ በነገራችን ላይ ሙዚቃ በቋንቋ መለየት የሚጀምረው ኢትዮጵያ ላይ ሲደርስ ነው። ሙዚቃ ሲጀመር ቋንቋው ኖታ እንጂ ABCD፣ ሀሁ ወይም ቁቤ አይደለም። እኛ አገር ሙዚቃ ማለት ግጥሙ ነው ብሎ የሚያስበው ብዙ ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው ሰው በቋንቋው ያልተዘፈነን የጃማይካና የሕንድ ዘፈን ነው ሲያዳምጥ የሚውለው፡፡ ሌላው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ከሙዚቃነቱ ይልቅ ንግግር ነው የሚበዛው - መፎከር፣ መሸለል መቀስቀስ የሚባለው ግጥሙ ላይ ነው የሚያተኩረው፤ ለዚህ ነው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ከኢትዮጵያ መውጣት ያልቻለው።
ዞሮ ዞሮ ወደ ሀጫሉ ስንመለከት ፕሮፌሽናል አርቲስት ነው። በነገራችን ላይ ሀጫሉ በድምጽ ከመጫወቱ በፊት የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች ነበር። ብቃት ያለው ድራም ተጫዋች ነው። ልጁ የሙዚቃ ምት ስለሚችል የተፈጥሮ ተሰጥኦውን ድምፁን ወደ ምቱ አስገብቶ በደንብ የመቀመር ችሎታ አለው። አንድን አርቲስት ፕሮፌሽናል የሚያስብለው ጥሩ ድምፅ ብቻ ስላለው ሳይሆን ነገሮችን አዋህዶ አጣፍጦ የማቅረብ ችሎታው ነው። ሀጫሉ በዚህ የተዋጣለት ነው። ዋናው ነገር ይዞ የተነሳውን ካራክተር፤ በሙዚቃ ሕግና ሳይንስ ውስጥ ቀምሞ ማቅረብ መቻሉ ነው ብዬ አምናለሁ። ሀጫሉ ሲያነሳሳም ሲያስተክዝም እኩል ነው። ሥራዎቹን ልብ ብለሽ ከሆነ፣ ብዙዎቹ ልብ ውስጥ ገብተው የሚሰረስሩ የፍቅር ዘፈኖች ናቸው። የቅስቀሳ ዘፈኖቹም ደም የሚያሞቁ ናቸው። ሁለቱንም ዘውጎች በደንብ ይሰራቸዋል። በሙዚቃ በቆየባቸው 15 ዓመታት ውስጥ በጣም ብዙና ዘመን ተሻጋሪ ስራዎችን ነው የሰራው፡፡
የቀደመው ዘፈን የአዝማሪነት ባህሪ ስላለው “እኔን አወድሰኝ፤ መንግሥትን አወድስ” አይነት ነው፡፡ ይሄ አርት አይደለም፤ አርት የራሱ ሕግ ሳይንስና መሰረታዊ ነገር አለው፤ አርቲስቱ ይህንን ሲያሟላ አርቲስት ይባላል። ሀጫሉ ሁሉን ያሟላ አርቲስት ነው። እንዳልኩሽ ልጁ ድራም ተጫዋች ነው፤ መሳሪያ ተጫዋች ነው፤ መጀመሪያ ደሞዝ የበላው በድራም ተጫዋችነት ነው፤ ይህንን ብዙ ሰው አያውቅም። ስለዚህ ልጁ ሙዚቃ አዋቂ ነው አጠቃላይ ሰው ግን ልጁን ጎላ ባለ መልኩ የሚያውቀው በማነሳሳትና በቅስቀሳ ስራው ነው፡፡
ሀጫሉ በሙያው ብዙ አስተዋፅኦ አድርጓል፣ ህልፈቱ አያጎድልም አይደለም፤ ከሙያው ይልቅ ለቤተሰቡ ለልጆቹ ለቅርብ ጓደኞቹ ያጎድላል፤ የምትወጂውን ሰው ማጣት በጣም ይጎዳል ይከብዳል። በእኔ አስተሳሰብ አንድ ሰው ሲጠፋ ሙያው ይጎዳል ከሚለው በላይ አንድ ሰው ሲጠፋ ሰው ይጎዳል ነው የምለው፤ ከቤተሰብ ከአድናቂዎቹ ጀምሮ ሰው ይጎዳል። ያንን ሰው ባናደንቀው እንኳን እናውቀዋለን። ብዙ ሰው የሚያውቀው ሰው ሲሞት ባታደንቂው እንኳን ያሳዝናል። በአጠቃላይ የሰው ልጅ ያውም ከተፈጥሮ ሞት ውጪ ሆኖ ሲሞት በእጅጉ ያሳዝናል።
በቀጣይ የሙዚቀኞች ማህበር አለን፤ የማህበሩ አስተባባሪ ነኝ። ቴአትረኞች ቴአትር ሲሰሩ፤ ገጣሚያንና ፀሐፍት መጽሐፍ ሲያሳትሙ በሽፋናቸው ላይ በፖስተራቸው ላይ ፎቶውን እንዲጠቀሙ እናደርጋለን። በተጨማሪም ልጁ በአርቱ ላይ ያለው ጉልበት ትልቅ ነው። አፍሪካ ላይ ብዙ ችግሮች አሉ፤ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የፍትህ መጓደሎች አሉ። ቦብ ማርሌይ በዓለም ላይ ተወዳጅ የሆነው በድምፁ ብቻ አይደለም፤ የመብት ተሟጋች በመሆኑ ጭምር ነው።
እኛ አገር ብዙዎች የሕዝብ ድምፅ በመሆን ብዙ አይሳተፉም። ይሄ ልጅ ግን የሕዝቡን ብሶት ሲያንፀባርቅ ነው የኖረው፤ ስለዚህ ማንኛውም ሰው ፎቶው እንዲኖረው እናደርጋለን። በተለያዩ መስሪያ ቤቶችም ፎቶው እንዲቀመጥ የማድረግ ሀሳብ አለ። በሌላ በኩል፤ የአዲስ አበባ ከንቲባና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት የሚያደርጉትም ነገር አለ። በስሙም የሚሰሩ ነገሮች እንዳሉና የሙያ አጋሮቹም ሊያደርጉ ያሰቡት ነገር እንዳለ አውቃለሁ። ይሄ ልጅ ለሕዝብ ነፃነት የተሰዋ ነውና ብዙ ነገር ይገባዋል። አርቲስት የሕዝቡን ብሶትና ፍላጎት በተሰጠው ሙያ ማቀንቀን አለበት። ሀጫሉ ይህን በሚገባ አድርጎ በክብር ያለፈ የነፃነት ታጋይ ነው።
የሀጫሉ አሟሟት ቀጥታ ከነፃነት ታጋይነቱ ጋር የተያያዘ እንደሚሆን አልጠራጠርም። መጀመሪያውኑም ጋዜጠኞች፤ እሱ መጠየቅ የማይገባውን ነገር ነው ሲጠይቁት የነበረው። እሱ ፖለቲከኛ አይደለም። በአጠቃላይ የተሰራው ስራ ትክክል አይደለም። ካራክተር መስራትና ታሪክ ማወቅ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ለሞቱ መነሻም መጨረሻ ላይ ያደረገው የጋዜጠኞቹ ኢንተርቪው ነው። ጋዜጠኞቹ ስለሚመለከተው ስለ አርቱ ሳይሆን ስለማይመለከተው ፖለቲካ ነው የጠየቁት።  ልጁ ስለ ነፃነት ዘፈነ የሕዝብ ድምፅ አሰማ ይሄ ደግሞ ከሕዝብ ልጅ ከአርቲስት የሚጠበቅ ነው። መሳሪያ ታጥቆ አልተኮሰም ሕዝቡ ነፃነት ይፈልጋል ብሎ በመታገሉ የሚያኮርፍ አካል ይኖራል። ዞሮ ዞሮ ለዚህ ልጅ አሟሟት ተጠያቂውም ቃለ ምልልሱን ያደረገለት የሚዲያ ተቋምና ጋዜጠኞች ናቸው የሞቱ መንስኤም ያ ቃለ ምልልስ ነው ይሄ ነው።
ከሀጫሉ አሟሟት በበለጠ አቀነባበሩ ነው ያሳዘነኝ። በኢትዮጵያ ታሪክ አርቲስት በሰው እጅ ሲጠፋና ሲሰዋ አይቼም ሰምቼም አላውቅም። ለእኔ አርቲስት በሰው ሲገደል በውጭ አገር እንጂ የሰማሁት በእኛ አገር የመጀመሪያዬ ነው። የፈለገ ፖለቲካም ይሁን ተወዳጅ አርቲስትም ይሁን ምንም ይሁን በሕይወት እያለ ሲጠቀሙበት እንጂ አስክሬኑ ተይዞ ፖለቲካ ሲሰራበት ይሄ የመጀመሪያው ልጅ ነው፡፡ በእኔ እምነት ሰው ከሞተ በኋላ አስክሬኑን ይዞ እንደ ቅርጫ ለመከፋፈል መሯሯጥ በጣም የሚያሳዝን የሚያስነውር ነው። አስክሬን እስኪበላሽ ድረስ በሰላም እንዳያርፍ “አይቀበርም ቤተሰብ ከቀበረም አውጥተን እንወስዳለን” ብለው ትንቅንቅ ውስጥ መግባት ከኢትዮጵያ ባህልም አስተሳሰብም እምነትም ውጪ ነው። አይተንም ሰምተንም አናውቅም። እዚህ አገር ሰው ቋንቋው ይለያይ እንጂ ባህሉ አንድ ነው። ሰው ሲሞት እናት አባት አጠቃላይ ቤተሰብ ነው የሚወስነውም የሚቀብረውም። ሞትና ሰርግ በማህበረሰባችን በባህላችን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሥነ ሥርዓት ነው። “አስክሬኑ የእናንተ አይደለም” እስከመባል የደረሱበት አሳዛኝ ድርጊት ነው የተፈፀመው። ተቀበረ ማለትም አይቻልም። ይሄ በጣም አሳዝኖኛል፤ የምሬን ነው።
እንግዲህ በኦሮሞ ባህል በሰው እጅ ለሞተ ሰው ብዙ አይለቀስም ይባላል። ሀጫሉ በስጋ ቢለየንም አልሞተም፤ ልክ እንደ ቦብ ማርሌይ በሙዚቃ 15 ዓመት ኖሮ ብዙ ሰርቷል፤ ቦብ ማርሌይም የ15 ዓመት የሙዚቃ ሕይወት ነው የነበረው፡፡ ቦብ ማርሌይ በ36 ዓመቱ ነው የሞተው። ሀጫሉም በ36 ዓመቱ ነው ያለፈው፤ ቦብ የነፃነት የመብት የእኩልነት ታጋይ ነበር፤ ሀጫሉም እንደዛው ለሰው መብት መከበር ለነፃነት ለፍትህ ሲታገል ነው የተሰዋው፡፡ ብዙ ነገሩ ከቦብ ማርሌይ ጋር ይመሳሰላል። በመጨረሻም ለሀጫሉ ቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድና አድናቂዎቹ በርቱ ፅናቱን ይስጣችሁ እላለሁ።          


Read 1168 times