Saturday, 04 July 2020 00:00

የሃጫሉ የኪነጥበብ ወዳጆች ምን ይላሉ?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

   “ኪነጥበብ ትልቅ ሰው አጥታለች”
                               (አርቲስት ታደለ ገመቹ)

                ከሀጫሉ ጋር የተዋወቅነው የመጀመሪያ አልበሙን እንዳወጣ ነበር፡፡ የመጀመሪያ አልበሙን ስሰማ ባለ ትልቅ ተሰጥኦ መሆኑን ለማወቅ ችያለሁ፡፡ ከዚያ በኋላም ብዙ ሥራዎችን በብዙ መድረኮች ላይ አብረን ሰርተናል፡፡ አንድ ሰው ካለፈ በኋላ ብዙ ይባልለታል ይደጋገማልም፤ አሁንም ስናገር የተለመደው አይነት ሊመስል ይችላል፡፡ ግን ከልቤ ስነግርሽ ሀጫሉ በጣም ደግ ልጅ ነው:: ለችግር የሚደርስ ሩህሩህና አዛኝ ልጅ ነው፡፡ ከደፋርነቱ ውጪ ማለት ነው፡፡ ከሰዎች ጋር በቀላሉ የሚግባባ፣ ከማህበረሰቡ ጋር ጤናማ ግንኙነት ያለው ተጫዋችና ሳቂታ ነው፡፡
የሃጫሉን ሞት የሰማሁት ሰኞ ምሽት ወደ 5፡00 አካባቢ ነው፡፡ የደወለልኝም ጓደኛዬ ታደለ ሮባ ነው፡፡ ደውሎ “የምሰማው እውነት ነው?” አለኝ ምን ሰማህ?” ስለው “ሀጫሉን ገደሉት” እየተባለ ነው ብሎ ነገረኝ፤ በጣም ነው የደነገጥኩት ከዚያ በኋላ ብጮህ ብፈርጥ ምን አመጣለሁ፡፡ ብዙ ጓደኞቼ ጋር ስደውል ላገኛቸው አልቻልኩም የግማሾቹ ቢዝ ሆኗል፡፡ ግማሾቹ ስልካቸውን አጥፍተዋል፡፡ በዚህ መሃል ግራ ገባኝ፡፡ በኋላ ወደ ማህበራዊ ሚዲያው ሄድኩና ማየት ጀመርኩኝ፤ የሚፃፈውን የሚባለውን አየሁ፤ ግን ማመን አልቻልኩም፤ ለመቀበል ጊዜ ወሰደብኝ፡፡ ምክንያቱም አንዳንዴ እንደዚህ እገሌ ሞተ እያሉ እያስወሩ ውሸት ሆኖ ይገኛል፡፡ እኔም ውሸት እንዲሆን ተመኝቼ ነበር፤ ነገር ግን ውሸት አልሆነም፡፡ ከ6፡00 በኋላ የተወሰኑ ጓደኞቼ ጋር ስደውል ሁሉም ያለቅሳሉ፡፡ በኋላም ምስሉን ሶሻል ሚዲያ ላይ ሲለቁት ተመለከትኩ፤ በጣም በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡
በነጋታው ቀብር ለመሄድ ተነስቼ ነበር፤ ግን በነጋታው የሆነው ደግሞ የተለየ ነው፤ መንገድ ዝግ ነው፤ ምንም እንቅስቃሴ የለም:: እኔ ደግሞ ኦሮሚያ ጫፍ ፉሪ አካባቢ ነውና የምኖረው መንቀሳቀስ አልቻልኩም፡፡ አንድ የቅርብ ወዳጅን አልቅሶ አለመቅበር ደግሞ ሌላ ሀዘን ነው፡፡
በሀጫሉ መሞት ኪነ-ጥበብ ትልቅ ሰው አጥታለች ነው የምለው፡፡ እውነት ለመናገር ልጁ እስከ ዛሬ ከሰራው የበለጠ መስራት የሚችልበት ጊዜ ላይ ነበር፡፡ እድሜው በጣም ትንሽ ነው፤ 30ዎቹ አጋማሽ ላይ ነበር:: ያለማጋነን ብዙዎቻችን ሌላ ተጨማሪ 20 እና 30 ዓመት ዕድል ብናገኝ የማንሰራውን በዚህች አጭር ጊዜ ውስጥ የሰራ ልጅ ነው። በጣም ጥበበኛ የግጥምና ዜማ ደራሲ ነው፤ በጣም የተለየ ልጅ ነው። ለሀጫሉ አንድ ዘፈን ሰርቶ መነሳት፤ አንድና ሁለት ሰዓት ቢፈጅበት ነው። ነገሩን ቀድሞ በውስጡ አስቦ አሰላስሎ ነው የሚጨርሰው። በአጠቃላይ ሀጫሉ በጣም ትልቅ የኪነ ጥበብ ሰው፣ ገና ሮጦ ያልጠገበ፣ በስራው ነገር የማይረካ፣ ገና ምንም አልሰራሁም ብሎ የሚያስብና ለበለጠ ስራ የሚተጋ ልጅ ነው። ስለዚህ ለሙዚቃው ኢንዱስትሪ ትልቅ ጎደሎ ነው።
አሟሟቱን በተመለከተ ብዙ አስተያየት መስጠት አልፈልግም፤ አልችልምም፡፡ ይህን የሚመለከተው አካል እያጣራው ይገኛል። ነገር ግን ሀጫሉ የነፃነት ታጋይ መሆኑን አውቃለሁ። ሀጫሉ ለነፃነት፣ ለእኩልነት፣ ለፍትህና ለርትዕ የሚታገል ልጅ መሆኑን አውቃለሁ። ለመብት ለተጨቆኑ የሚታገል ልጅ መሆኑን ከመግለጽ ውጪ ምንም የምለው የለም። በመሞቱ ከልቤ አዝኛለሁ ምን እንደምሰራ ሁሉ አላውቅም።
ለአርቲስቱ መታሰቢያ የሚሆን አስባችኋል ወይ ላልሽው ያው ለእርሱ መታሰቢያ የሚሆን ሀውልት እዚህ አዲስ አበባ ይቆማል ተብሎ ሰምተናል፤ ከዚያ ውጪ ግን የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት ሊሆን ይችላል፣ እሱንና ሙያውን የምናስታውስበትና የምንዘክርበትን ሁኔታ በተመለከተ ከጓደኞቻችን ጋር እየተመካከርን ነው ያለነው፤ በቅርብ ጊዜ የሚከናወን ይሆናል።
በመጨረሻም ሀጫሉን አጥተነዋል፤ አዝነናል፡፡ እኛ የሙያ ጓደኞቹ እሱ የጀመራቸውን ነገሮች፤ ሲያደርግ የነበራቸውን ነገሮች ሞልቶ ለመስራት ጥረት ማድረግ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ቤተሰቦቹን፣ ወዳጅ ዘመዶቹንና አድናቂዎቹን እግዚአብሄር ያጽናችሁ ነው የምለው፡፡ የሱንም ነፍስ ይማር እላለሁ።     Read 376 times