Thursday, 16 July 2020 20:30

“የሀይሌ ሻሸመኔ ሆቴል መቶ በመቶ፤ ሀይሌ ዝዋይ ሪዞርት 80 በመቶ ወድመዋል”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

-  በሆቴሉ ግቢ ቆመው የነበሩ 10 መኪኖች ሙሉ በሙሉ ተቃጥለዋል
       - እንግዶቻችን ምንም ሳይሆኑ በሰላም በመውጣታቸው እንደ ትልቅ ዕድለኝነት ነው ያየነው

          ባለፈው ሰኔ 22 እውቁና ተወዳጁ የኦሮምኛ አቀንቃኝ ሀጫሉ ሁንዴሳ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በተተኮሰበት ጥይት ሕይወቱ ማለፉን ተከትሎ፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረው ረብሻና ግርግር መቶ የሚደርሱ ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ በርካቶች ለከፍተኛና አነስተኛ ጉዳት ተዳርገዋል። በርካታ የመንግሥትና የግለሰብ ንብረቶችም መውደማቸውን መንግሥት ገልጿል። ከወደሙት ንብረቶች መካከልም የእውቁ አትሌትና የቢዝነስ ሰው ሀይሌ ገብረስላሴ ንብረቶች የሆኑት ዝዋይ (ባቱ) ሀይሌ ሪዞርትና ሻሸመኔ ሀይሌ ሆቴል ይገኙበታል።  በሁለቱ ንብረቶች ላይ የደረሰው ጉዳት ምን ይመስላል ስትል የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በሀይሌ ሪዞርቶችና ሆቴሎች የኮርፖሬት ኦፊስ ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ መልካሙ መኮንን አነጋግራቸዋለች።

          እስኪ በዝዋይና በሻሸመኔ ሀይሌ ሆቴልና ሪዞርቶች ላይ ስለደረሰው የውድመት መጠን ያብራሩልኝ?
በመጀመሪያ በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ሞት በጣም ማዘናችንን መግለጽ እንወዳለን። የአርቲስቱ ሞት ሰኞ ምሽት 3፡30 ገደማ ከታወጀ በኋላ ከለሊት 9፡00 ጀምሮ ነው ንብረት መሰባበርና ማቃጠል የተጀመረው። ዋናው ጥፋት በተለይ በሻሸመኔ ንጋት 11፡00 አካባቢ ነው የተጀመረው። ይህን ያህል ነው ብሎ ለመግለጽ የሚያስቸግር ቁጥር ያላቸው ወጣቶች ነበር የመጡት። በየሆቴሉ ክፍል ሁሉ እየገቡ መስታወት አረገፉ። ከዚያ በኋላ ወደ ማቃጠል ነው የዞሩት። በዕለቱ ሥራ ላይ የነበሩትን የሆቴሉን ሰራተኞች አሯሩጠው አስወጧቸው፤ ከዚያ በኋላ የነበረው ነገር ከእኛ ቁጥጥር ውጪ ነው የነበረው። የምሽቱ ተረኛ የነበረው የሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ እዛ ለነበሩ እንግዶች ደዋወለ፤ ነገር ግን እሱንም ሲያባርሩት ነፍሱን ማትረፍ ነበረበትና ሮጦ አመለጠ። እንግዶቹም በራሳቸው መንገድ ነው የወጡት።
በሆቴሉ ውስጥ ምን ያህል እንግዶች ነበሩ?
በሆቴሉ ውስጥ 11 እንግዶች ነበሩ ሁሉም በሰላም ወጥተዋል። ነገር ግን በሆቴሉ ግቢ ውስጥ ቆመው የነበሩ 10 መኪናዎች ሙሉ በሙሉ ተቃጥለዋል።
የሻሸመኔው ሀይሌ ሆቴል ጉዳቱ በገንዘብ ሲሰላ ምን ያህል ይሆናል?
የሻሸመኔው ሆቴል መቶ በመቶ ወድሟል - Full Damage  ነው። ምክንያቱም አንድን ሆቴል ሆቴል የሚያሰኘው ሕንጻው ብቻ አይደለም። በሆቴሉ ውስጥ ብዙ ማሽነሪዎች የተለያዩ እቃዎች አሉ። በሆቴሉ ውስጥ የሚገኘው ዕቃ ነው በጣም ውዱ ነገር፤ ይሄ ሁሉ ነው ሙሉ በሙሉ የተቃጠለው።
የዝዋዩ ሀይሌ ሪዞርትስ?
የዝዋዩም ተመሳሳይ ጉዳት ደርሶበታል። በነገራችን ላይ በተመሳሳይ ሰዓት ነው ጥፋቱ የደረሰው። ከሻሸመኔው ትንሽ ቀደም ብሎ 10፡00 አካባቢ መጡ እሱንም ገብተው ሰባበሩ፤ አቃጠሉ፤ እዛ የነበሩ ሰራተኞችን አስወጥተው እየተመላለሱ የፈለጉትን አደረጉ። እነሱ ከወጡ በኋላ ሪዞርቱን ሄደን ስናየው፣ የተቃጠለው ተቃጥሎ የቀረው ንብረት በሙሉ ተዘርፏል።
ምን አይነት እቃዎች ናቸው  የተዘረፉት?
ቴሌቪዥኖች፣ ፍሪጆች፣ የኪችን ዕቃዎች በሙሉ ተወስደዋል። የሚቻለውን እየወሰዱ፣ የማይቻለውን እያቃጠሉ ነው ያወደሙት።
የዝዋዩ ሪዞርትም እንደ ሻሸመኔው ሙሉ በሙሉ ወድሟል ማለት ነው?
ከ70 - 80 በመቶ ወድሟል ማለት ይቻላል። ለምንድን ነው እንደ ሻሸመኔው መቶ በመቶ ወድሟል የማንለው፣ ዝዋይ ሀይሌ ሪዞርትን አይተሽው ከሆነ ቤቶቹ የተለያየ ቦታ ላይ ነው የተገነቡት። ወጥ የሆነ ሕንጻ አይደለም። አንዳንድ ቪላዎችን አልከፈት ሲላቸው በመስኮት ሰባብረው ገብተው ሙሉ በሙሉ ካወደሙ በኋላ ሳያቃጥሉ የተዋቸው አሉ። ይሄ ማለት በየቪላዎቹ እየገቡ እቃዎቹን፤ የሽንት ቤት መቀመጫ ሳይቀር ሰባብረው ቪላውን ሳያቃጥሉ የተውት አሉ። ውስጡ ምንም የማይጠቅም ሆኗል። ግን ቤቱ ሳይቃጠል የተረፈ አለ። ስለዚህ በእኛ ግምት ከ70-80 በመቶ ነው የወደመው።
በአጠቃላይ የደረሰው ኪሳራ በገንዘብ ምን ያህል ይገመታል?
እውነት ለመናገር እሱን ቁጭ ብለን አልሰራነውም። ገና መታየትና መጠናትም አለበት። አሁን በገንዘብ ይህን ያህል ኪሳራ ደርሶብናል ብለን መናገር አንችልም፤ በጣም ከባድ ነው።
ሻሸመኔ ሀይሌ ሆቴል ምን ያህል ሰራተኞች ነበሩት?  ምን አገልግሎቶች ነበር የሚሰጠው?
ዝዋይ ላይ 142፣ ሻሸመኔ 130 ቋሚ ሰራተኞች ነበሩን። ሻሸመኔ ሆቴላችን 52 የመኝታ ክፍሎች ነበሩት፣ ሳውና እና ስቲም የወንድም የሴትም ያሟላ ነበር። ጂምናዚየም የመዋኛ ገንዳ፣ 600 እና 1 ሺህ ሰዎች የሚይዝ የስብሰባ አዳራሽ ነበረው። ሁለት ሬስቶራንትም የያዘ ነበረ። ወደ ዝዋዩ ሪዞርት ስንመጣ፣ ወደ 70 አልጋ፣ የቤተሰብ ክፍል ሲሆን የአልጋ ቁጥሩ ከአንድ በላይ ስለሚሆን ነው 70 ያልነው እንጂ 52 የመኝታ ክፍል ነው ያለው፤ ሳውና ስቲም፣ ጂምናዚየም ሬስቶራንቶች፣ የስብሰባ አዳራሾችም ልክ ከሻሸመኔው ጋር ተመሳሳይ ነገሮችን ያሟላ ነው። በዚህ ሁሉ ላይ ነው ጉዳት የደረሰው።
ለምን ይመስላችኋል ንብረቶች ላይ ያነጣጠሩት?
እንግዲህ አንዱና ዋነኛው ሀይሌ ታዋቂና ዓለም አቀፍ ሰው ስለሆነ ትኩረት ለመሳብ ይሁን ከጀርባው ሌላ ነገር ይኑረው እኛ አናውቅም። ይሄ መጠናት አለበት። በእርግጥ በአሁኑ ችግር ምንም እንኳን በመጀመሪያ ወደኛ መጥተው ቢያወድሙም፣ በዝዋይም በሻሸመኔም ሌሎች በርካታ ሆቴሎችና ንብረቶችም ስለወደሙ የእኛ ብቻ ነው ለማለት ይከብዳል። ለምሳሌ በዝዋይ “ሼር” የሚባለውና 13 እና 14 ሺህ ሰራተኛ ያለው የአበባ ካምፓኒ በጣም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል። በአጠቃላይ አሁን ላይ ይሄ ነው፣ እንዲህ ነው ለማለት ይከብዳል።
ይሄ ሁሉ ጥፋት ሲደርስ የመንግሥት የፀጥታ አካላት አልደረሱላችሁም? የጥበቃ ሰራተኞች አልነበራችሁም?
ሻሸመኔ ላይ የምሽት ተረኛ የሆቴሉ ማናጀር፣ ተረኛ የሴኩሪቲ ሰራተኞቻችን… ሌሎችም ነበሩ። በእርግጥ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ቁጥራቸው ውስን ነው። ምን መሰለሽ… ለጥፋት የመጡት ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፣ ለቁጥር አዳጋች ነበሩ። ከእኛ ሰራተኞችም ቁጥጥር ውጪ ነው - ብዛታቸው። በዚህ ምክንያት የከተማውም ሆነ የእኛ የሴኩሪቲ ሰራተኞች ነገሩን መቆጣጠር አልቻሉም። እኛ እንዲያውም እስከ ዞን ድረስ ደውለን ነበር። በነጋታው በቀለ ሞላ ፊት ለፊት ቆሞ የነበረ መኪና አምጥተው ፊት ለፊታችን ሲያቃጥሉና ሌላም ጥፋት ሲያደርሱ ነው የዋሉት። በአጠቃላይ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ ነው የነበረው።
ንብረት ከማውደም ውጭ ሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት የለም?
እኛ ጋ ሰዎችን እያሯሯጡ ከማስወጣት ውጪ ያደረሱት ነገር የለም፤ ሰው ባለመግደላቸውና እንግዶቻችን በሰላም በመውጣታቸው እኛ እንደ ትልቅ እድለኝነት ያየነው።
ለደረሰባችሁ ውድመት ማንን ነው የምትጠይቁት?
እንግዲህ በቀጣይ በኢንሹራንስ በኩል ያለውን ወደ ኢንሹራንስ እንወስዳለን። በሌላ በኩል፤ ለኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ቢሮ፣ ለኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤትና ለተለያዩ ለሚመለከታቸው አካላት እናመለክታለን። የደረሰብንን መጠነ ሰፊ ጥፋትና ኪሳራም ሪፖርት እናደርጋለን። ያኔ ጉዳዩ ጥርት ብሎ የደረሰብን ኪሳራ መጠኑ ሲታወቅና ሁሉም ሲለይ ለሚዲያም መግለጽ ካለብን እንገልጻለን። ለጊዜው ማለት የምንችለው ግን ይሄንን ብቻ ነው።


Read 3744 times