Saturday, 04 July 2020 00:00

በኮሮና ወረርሽኝ የቆመው የኢትዮጵያ እግር ኳስ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  ስፖርት አድማስ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ ባህሩ ጥላሁን ጋር ያደረገው ልዩ ቃለ ምልልስ፡፡

     • የተጨዋቾችን ደሞዝ በሙሉ ለመክፈል ቀነ ገደቡ ሰኔ 30 ያበቃል
     • ክለቦች ችግር ላይ ናቸው፡፡ እስከ 577 ሚሊዮን ብር የመንግስት ድጋፍ ተጠይቋል፡፡ ከ200ሚሊዮን ብር በላይ ለደሞዝ ክፍያ የሚሆን ነው፡፡
     • አሰልጣኞች ተጨዋቾችን መብት ለማስከበር በአደባባይ መሟገት አለባቸው፡፡
     • ፌደሬሽኑ በጥናት ላይ የተመሰረተ መመርያ ያወጣል፡፡ እስከ ሐምሌ ወር አጋማሽ ተግባራዊ ያደርገዋል፡፡
     • ክለቦች በአህጉራዊ ውድድሮች ላይ እንዳይሳተፉ ሲወሰን ብዙ አማራጮችን ታይተዋል፡፡
     • 70ኛው የፊፋ ኮንግረስ አዲስ አበባ ላይ ሳይካሄድ በመቅረቱ 11 ቢሊዮን ብር አሳጥቷል፡፡ ፌዴሬሽን ቅሬታውን ለዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር
        ይገልፃል
     • በፌደሬሽኑ በኩል ቅድሚያ የተሰጣቸው ጉዳዮች፡- ለክለቦች የፕሮፌሽናል ፍቃድ አሰጣጥን በደንብ ከልሶ መመልከት፤ አዳዲስና የማስተካከሉ                    መመርያዎችን ማጽደቅና ወደ ስራ መግባት፤ ሁሉንም ውድድሮች መልሶ መጀመር እንዲሁም የካፍ ‹‹ሴንተር ኦፍ ኤክሰለንስ›› የምስራቅ አፍሪካ ትልቁ            ማዕከል ማድረግ፡፡


             በኢትዮጵያ እግር ኳስ በተለያዩ ደረጃዎች የሚወዳደሩ ክለቦች የተጨዋቾቻቸውን ደሞዝ በሙሉ እንዲከፍሉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ያወጣው ማሳሰቢያ ምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?
 ባወጣነው ማሳሰቢያ መሰረት ቀነ ገደቡ ሰኔ 30 ላይ ያበቃል፡፡ ክለቦች ለተጨዋቾቻቸው ሙሉ ክፍያ ለመፈፀም ከ1 ሳምንት ያነሰ ጊዜ ነው የቀራቸው፡፡  ከሁሉም ክለቦች የምንጠብቀው አጠቃላይ የደሞዝ ክፍያዎች መፈፀማቸውን ነው፡፡ እስከ ሐምሌ 5 ይህኑ ደግሞ  ተግባራዊ ስለማድረጋቸው በሪፖርት ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል:: ከየትኛውም ክለብ እስካሁን ለእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የደረሰ መረጃ የለም:: በየትኛውም ህግ ላይ አንድ ሰው ለሰራበት ክፍያውን ማግኘት አለበት፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ግን ከደሞዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ የ6 እና የ8 ወራት ክፍያ ያላገኙ ተጨዋቾች አሉ፡፡  የ4 ወራት ክፍያቸውን ያላገኙ ተጨዋቾች ደግሞ በብዙ ክለቦች  ይገኛሉ፡፡ የተወሰኑ ክለቦች የደሞዝ ክፍያዎችን እየፈፀሙ ቢሆንም እንደጠበቅነው አይደም፡፡
ፌደሬሽኑ ደሞዝ ለማስከፈል መስራቱ ሌሎች ወሳኝ ተግባራቱን እንዳያከናውን አድርጎታል፡፡ በየክለቡ ደሞዝን በተመለከተ ምሬት የሚያሰሙ ተጨዋቾች ጥቂት አይደሉም:: በተለይ በ1ኛ ሊግ በሚወዳደሩ ክለቦች ችግሩ ሰፊ ነው፡፡ በዋናው ፕሪሚዬር ሊግም አጣብቂኝ ውስጥ የገቡ ክለቦች ጥቂት አይደሉም፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ እንደሚለው ኮቪድ 19 ችግር ያመጣው በሁሉም ላይ ነው፡፡ ይህን በማመን የእግር ኳስ ባለድርሻ አካላት ምክክር ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ከውይይቶች መፍትሄዎች ይገኛሉ በማለትም ለክለቦች ይህንኑ አቅጣጫ ጠቁመናል፡፡ ለምሳሌ የፋይናንስ ችግር ውስጥ ገብቶ ደሞዝ ለመክፈል ያዳገተው ክለብ፤ ለተጨዋቾች ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥበት ሁኔታ ላይ የመጀመርያው ርምጃ ተጨዋቾቹን ማማከር መሆን አለበት፡፡  ተቀራርቦ ከሚደረግ ምክክርና ድርድር መፍትሄዎች ይገኛሉ፡፡ ይህን አይነት አሰራር በመከተል ምሳሌ ከሚሆኑ ክለቦች አንዱ ኢትዮጵያ ቡና ነው፤ ከተጨዋቾቻቸው ጋር ውይይት ማድረግ ችለዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ  ደግሞ ችግር የለብንም በሚል አስቀድሞ ክፍያውን በመፈፀም የተጨዋቾቹን ጥያቄ መልሷል፡፡
ከደሞዝ ክፍያዎች ባሻገር ፌደሬሽኑ ከክለቦች ሌላ ምን ይጠብቃል?
የዲስፕሊን ቅጣቶችን የሚመለከት ነው፡፡የፍትህ አካሉ ባስተላለፋቸው ውሳኔዎች ብዙ ክለቦች ባለዕዳዎች ናቸው፡፡ በዲስፕሊን ጉዳዮች ተካስሰው የተረቱ እና ቅጣት እንዲከፍሉ የተወሰነባቸው አሉ፡፡ ክፍያዎቹን የመፈፀም ግዴታ አለባቸው፡፡ ፌደሬሽኑ በየውድድር ዘመኑ የሚገጥሙት ከዲስፕሊን ጋር የተያያዙ ሁኔታዎች አሉ፡፡  በተለይ ደግሞ ክፍያዎችን በመሰብሰብ ብዙ ፈተናዎች ይገጥሙታል:: የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የዲስፕሊን ቅጣቶችን በተመለከተ ያወጣው ቀነ ገደብ 1 ሰሞን ቀርቶታል፡፡
በተለይ ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ አንዳንድ ክለቦች የተጣሉባቸውን የዲስፕሊን ቅጣቶች ለመክፈል ማመንታታቸው ያሳስበናል:: በቀደሙት የውድድር ዘመናት ፌዴሬሽኑ ይህን ለማስፈፀም የተለያዩ አስገዳጅ ሁኔታዎችን ይጠቀም ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን በኮቪድ 19 በተፈጠረው ሁኔታ ምንም አይነት አስገዳጅ ማሳሰቢያ ለመስጠት አልተቻለም:: በፕሪሚዬር ሊጉም በከፍተኛ ሊጉም ይህን ግዴታ መወጣት ያለባቸው ክለቦች አሉ:: ነገር ግን ኮቪድ 19 ከመጣ በኋላ  እንደ ግዜ መግዣ ተጠቅመውታል፡፡ ክፍያዎች ለመፈፀም እያመነቱ ናቸው፡፡ ውድድር ቢኖር ክለቦችን ከውድድር እናግዳችኋለን በሚል ክፍያውን እንዲፈፅሙ እናስገድድ ነበር፡፡ አንዳንድ ክለቦች ውድድር ስለሌለ ተዘናግተዋል፡፡ ፌደሬሽኑም የሚያስገድድበት ሁኔታ ስለማይኖረው ባንከፍልም ምንም አይመጣም በሚል እያሰቡም ይሆናል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ግን በዚህ ጉዳይ ላይ እስከ ቀነ ገደቡ ይጠባበቃል፡፡ ከዚያም በኋላ ምን አይነት ርምጃዎችን መውሰድ እንዳለበት ያውቃል፡፡
በአጠቃላይ የ2012 ዓም የውድድር ዘመን ስለተሰረዘ ብቻ ክለቦች ያሉባቸውን ግዴታዎች አለመወጣታቸው አግባብ አይደለም፡፡ ቸልተኝነቱንም አብዝተዋል፡፡ የደሞዝ ክፍያዎች መፈፀም አለባቸው፤ የዲስፕሊን ቅጣቶች ሊወራረዱ ይገባል፡፡ ከእነዚህ ሁኔታዎች በስተቀር እግር ኳስ ፌደሬሽኑንና ክለቦችን ሌላ የሚያገናኝ ነገር የለም፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ባሳለፈው ውሳኔ ክለቦች ባይከፍሉ ከሐምሌ 5 በኋላ ፌዴሬሽኑ ምን ማድረግ እንዳለበት አስታውቋል፡፡ በዚያ ቀነ ገደብ ውስጥ መክፈል ያለባቸውን ክፍያ እና መወጣት ያለባቸውን ሃላፊነት የመፈፀም ግዴታ አለባቸው፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ኮቪድ 19 ያደረሰውን ተፅእኖ በመቋቋም እና ወደፊትም ውድድሮችን ለማስቀጠል ምን እየሰራ ነው?
 በፌደሬሽኑ በኩል ብዙ ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው፡፡ ጥናትም እያደረግን ነው፡፡ ባለፈው ስራ አስፈፃሚው ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል ውድድር በምን መልኩ መጀመር ይቻላል የሚለውን ጥናት አድርጎ ለማቅረብ ነው፡፡ በዚያ መሰረት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶች እየተካሄዱ ናቸው፡፡  በተለያዩ ጊዜያት በቨርችዋል ግንኙነት እያደረግን ባካሄድናቸው ውይይቶች መረጃዎችን እየሰበሰብን ቆይተናል፡፡ ከተጨዋቾች ማህበር ጋር ሰፊ ውይይት አድርገናል፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ ከዳኞች ማህበር፤ ከየክለቦቹ አስተዳደርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የምናደርጋቸው ውይይቶች ነበሩ፡፡ በአገሪቱ ላይ በተፈጠሩ ድንገተኛ ክስተቶች ተስተጓጉለውብናል እንጂ፡፡ በቀጣይ ሳምንታት ውይይቶችን ለመቀጠል ነው የምናስበው፡፡
በኮቪድ 19 ሳቢያ በአገራችን እግር ኳስ ላይ አደጋዎች ተጋርጠዋል፡፡ስለዚህ ምን እየሰራችሁ? በተለይም  የክለቦችን ህልውና  ለመታደግ የከፋ ችግር ውስጥ ለወደቁ ተጨዋቾች ለመድረስ…
የእግር ኳስ ፌደሬሽን ውድድሮች መልሶ ለመጀመር ከሚያደርጋቸው ጥረቶች ባሻገር እንደአጠቃላይ ደግሞ ለመንግስት ጥናት አቅርቧል፡፡ በኮቪድ ሳቢያ ክለቦች  ችግር ላይ በመሆናቸው ከመንግስት በኩል የገንዘብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል የሚል ነው፡፡ ስለዚህም እስከ 577 ሚሊዮን ብር ከመንግስት ለማግኘት እንዲችሉ ጥያቄ አቅርበናል፡፡ የገንዘብ ድጋፉ በፌደሬሽኑ ስር ያሉ ሁሉንም ውድድሮች ይመለከታል፡፡  ለደሞዝ ለመክፈል ችግር ወስጥ የገቡ፤ የበጀት እጥረት ለገጠማቸው ክለቦች በሙሉ ነው፡፡ የደሞዝ ወጭን ለመሸፈን  እስከ 200 ሚሊዮን ብር ነው መንስትን የጠየቅነው:: ለአንደኛ ሊግ፤ ለከፍተኛ ሊግ፤ ለፕሪሚዬር ሊግ፤ ለሴቶች ሊግ ሁሉንም ሊጎች ይመለከታል:: ከመንግስት ቀና ምላሽ እናገኛለን ብለን እየጠበቅን ነው፡፡ ጥያቄው በአጠቃላይ በእግር ኳስ ስር ያሉ ሙያተኞችን የሚታደግ ነው:: በተለይ ግን ለተጨዋቾች ደህንነት ትኩረት ሰጥተን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ በየክለቡ ያሉ አመራሮችና አሰልጣኞች ይህን በተመለከተ ዝም ማለታቸው፤ ተፅእኖ አለመፍጠራቸው ግን ያሳዝናል፡፡ አሰልጣኞች በየክለቡ ለያዟቸው ተጨዋቾች ሲከራከሩ አይስተዋልም፡፡
ምናልባትም በተጨዋቾች ዝውውር ሂሳብ፤ እና  በደሞዝ ክፍያዎች ጋር በተያያዘ በጠረጴዛ ስር የሚካሄዱ ሙስናዎች የአሰልጣኞችን አንደበት ያሰረው ይመስላል፡፡ ደሞዝ ባለመክፈልና በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ክለቦች በሚያሳዩት ቸልተኝነት ላይ አሰልጣኞች በአደባባይ ሲሟገቱ አላስተዋልኩም?
ልክ ነህ፡፡ በተለያዩ የስፖርት ሚዲያዎች ተጨዋቾች ለወደቁበት ችግር አሰልጣኞቻቸው ያላቸውን አቋም ሲገልፁ እና ተፅእኖ ለማሳደር እየሞከሩ አይደለም፡፡ በክለቦች፤ በተጨዋቾችና በአሰልጣኞች መካከል በሚካሄዱ ምስጥራዊ ውሎች ሳቢያ ሊሆን ይችላል፡፡ አቋምን በነፃነት ለመግለፅ አሰልጣኞች አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል፡፡ በፌደሬሽን በኩል ያለው የደሞዝ ጣሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ በርካታ ተጨዋቾች ከደሞዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ጥያቄ ለእኛ እንዳያመለክቱ እንቅፋት ፈጥሮባቸዋል፡፡ መብታቸውን ለማስከበርም ተቸግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ የሚሰሩ አሰልጣኞች ለሚያሰሯቸው ተጨዋቾች ትኩረት አድርጎ ከመስራት አንፃር ክፍተቶች አሉባቸው:: አሰልጣኞች በደሞዛቸው ላይ ችግር ስለሌለባቸው ነው? በደሞዝ አለመከፈል ዙርያ አሁንም ድረስ በአደባባይ ቅሬታቸውን የሚያሰሙት ተጨዋቾች ናቸው፡፡ አሰልጣኞች ዝምታቸውን መስበር አለባቸው፡፡ አሰልጣኝ በሜዳ ላይ ባለው ሃላፊነት የተወሰነ አይደለም፡፡ አመራርም ጭምር ነው፡፡  አንዳንድ አሰልጣኞች የአስተዳደር ስራ እኛን አይመለከተንም በሚል ይናገራሉ፡፡ በየጊዜው ተጨዋቾቻቸውን ልጆቼ እያሉ እየጠሩ አስገዳጅ ሁኔታ በሚያጋጥምበት ወቅት ለተጨዋቾች አለመሟገት በምንም አይነት ተገቢ አይሆንም፡፡
በሌላ በኩል ከኮቪድ 19 በኋላ ስፖርቱን ለማስቀጠል ወሳኝ ተግባራት ይኖራሉ፡፡ በመጀመርያ ደረጃ መንግስት በግሩፕ ስለሚካሄዱ ስራዎች ለእግር ኳሱ የሚሰጠው ፍቃድ ያስፈልጋል፡፡ በፌደሬሽን በኩልም ውድድሮች ባይጀመሩም እንኳን ልምምዶችን በልዩ ሁኔታ ለማስቀጠል፤ ወደ ውድድር ለመመለስ የምናደርገው ጥናት መጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡ ጥናቱንም ከጤና ሚኒስቴር፤ ከህብረተሰብ ጤና ኢንስትትዩት እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንሰራበታለን፡፡ ክለቦች ወደ ልምምድ መቼ ይመለሱ? ውድድሮች እንዴት ይጀመሩ? እና ሌሎች ጥያቄዎችን ለመመለስ ጥናቱን መሰረት ያደረገ መመርያ በማውጣት መስራት ይገባል:: በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ በኩል ይህንን እስከ ሐምሌ ወር አጋማሽ ተግባራዊ ለማድረግ እቅድ አለን፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ሁሉንም ውድድሮች ከመሰረዙም በላይ ክለቦች በአህጉራዊ ውድድር እንዳይሳተፉም ይህን ትክክለኛ ውሳኔ ነው ብሎ ያምናል? ወደፊትስ ከአፍሪካ እግር ኳስ የበላይ አካል ተሳትፎውን በመሰረዝ የሚደርስ ጉዳት ይኖራል ወይ?
በፌደሬሽኑ በኩል የሁላችንም ፍላጎት ውድድር ለመቀጠል እንጅ ለማቋረጥ አልነበረም፡፡ ክለቦች በአህጉራዊ ውድድሮች ላይ እንዳይሳተፉ ያሳለፍነው ውሳኔ ብዙ አማራጮችን አይተን ነው፡፡ አንደኛ ውድድሮች የተካሄዱት በሁሉም ደረጃ 50 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይህን መነሻ አድርገን ነው ውሳኔ ላይ የደረስነው፡፡ ዓለም አቀፉ ህግም ውድድሮችን ባሉበት ደረጃ ማጠናቀቅ የሚቻለው 75 በመቶ ግጥሚያዎች ከተካሄዱ በኋላ ነው እንደሚል ይታወቃል፡፡ ይህ ደንብ ደግሞ በኢትዮጵያ እግር ኳስ የተካተተ አይደለም፡፡ በርግጥ ውድድሩን መሰረዙ በእግር ኳሳችን ላይ የሚያሳድራቸው ተፅእኖዎች ይኖራሉ፡፡ ከውሳኔው በፊት ግን ውድድሮችን ለማስቀጠል በተለይ ከመንግስት ጋር ሰፊ ጥረት ለማድረግ ሞክረናል፡፡ በአውሮፓ የሚገኙ ታላላቅ ሊጎች ውድድሮቻቸውን መልሰው የሚጀምሩበትን ሁኔታ ገና ሳያነሱ ነው፤ የእኛ ፌደሬሽን ከመንግስት ጋር ምክክር ያደርግ የነበረው፡፡
ውድድሮችን በተለይም የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግን በሁለት ከተሞችና ስታድዬሞች ለማከናወን በመጀመርያ አቅደን ነበር፡፡ ይህ አማራጭ ከፍተኛ በጀት እና የውድድር አመራር ስለሚጠይቅ እንዲሁም ከወረርሽኙ መዛመት ጋር እንደአገር ከፍተኛ ጫና ውስጥ ስለሚከት ነው የተውነው፡፡ በሌላ በኩል ካለንበት አስቸኳይ ጊዜ አንፃር ክለቦች በአህጉራዊ ውድድሮች መግባታቸው ከባድ ጫና ይፈጥርባቸዋል፡፡ እንደከዚህ ቀደሙ  በሚሳተፉበት ሁኔታ ላይ አዳዲስ አሰራሮች መኖራቸው በአግባቡ መወዳደር እንዳይችሉ ምክንያት መሆኑንም ተገንዝበናል፡፡
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ በአዲስ አበባ ሊያደርገው ከነበረው 70ኛው ጉባዔ ጋር በተገናኘ ምን ማለት ይቻላል? ኮቪድ 19 ይህ ታላቅ ስብሰባ በኢትዮጵያ እንዳይካሄድ ምክንያት ሆኗል፡፡ ምን አሳጥቶናል?
ፊፋ በኮቪድ 19 ሳቢያ በመጀመርያ ላይ  ስብሰባውን ወደ መስከረም ወር ማስተላለፉን አሳውቆ ነበር፡፡ ከዚያም ጉባኤውን በቪድዮ ኮንፍረንስ ለማካሄድ ወስኛለሁ ብሏል፡፡ የፊፋ ስብሰባ መስተንግዶ ከኢትዮጵያ ወጥቶ በቪድዮ ኮንፍረንስ እንዲካሄድ በመወሰኑ በቱሪዝሙ መስክ ላይ በቢሊዮኖች የሚተመን ገቢ አጥተናል:: ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር  የኮንግረስ ጉባኤዎችን ሲያዘጋጅ አገር ልዩ የበጀት ድጋፍ ይሰጣል፡፡ አሁን ለምሳሌ ከ70ኛው የኮንግረሱ ስብሰባ ጋር በተያያዘ እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር ለአፍሪካ አገራት ለመስጠት ማቀዱን የፊፋው ፕሬዝዳንት ኢንፋንቲኖ ተናግረው  ነበር፡፡ ከዚሁ ገንዘብ 33 በመቶው ለኮንግራሱ አስተናጋጅ አገር የሚሰጥ ነበር፡፡ ያ ማለት ደግሞ ከ350 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወይም  እስከ 11 ቢሊዮን ብር በመስተንግዶዋ ኢትዮጵያ ታገኝ ነበር፡፡ ይህን ከፍተኛ መዋዕለንዋይ ነው በስብሰባው መሰረዝ ያጣነው፤ ፌደሬሽኑ ቢሊዬነር የሚሆንበት አጋጣሚ ነው የተበላሸው፡፡
ታላላቅ ሆቴሎችም ከኮንግረሱ ጋር በተያያዘ ሊያገኙት የነበረው ከፍተኛ ገቢም ቀርቶባቸዋል፡፡ 69ኛው የፊፋ ኮንግረስ በፈረንሳይ  በተካሄደበት ወቅት ፓሪስ ጥቅሙን ማግኘቷን ምሳሌ ማድረግ ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ ይህን ኮንግረስ እንድታስተናግድ ስትመረጥ እንደዚህ ቀደሙ ከዓለም አቀፋዊ ውድድር አዘጋጅነት ጋር በተያያዘ አይደለም፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር በሚቀጥሉት ዓመታት የሚያካሂዳቸውን የኮንግረስ ስብሰባዎች ከውድድር አዘጋጅ አገራት ጋር አያይዟቸዋል፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ እድሉን በድጋሚ ማግኘቷ ያጠያይቃል፡፡እግር ኳስ ፌደሬሽኑ ይህን አስመልከቶ ከመቆጨትም በላይ ለዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ተገቢውን ቅሬታ በደብዳቤ ለማሳወቅ እየሰራ ነው፡፡ በሃምሌ ወር መጨረሻ ይህን አስመልክቶ ለፊፋ የምናሳውቅበት ሂደት ላይ ነን፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አሁን ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ሁኔታዎች በአጫጭሩ ብታስቀምጣቸው?
የኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ዙርያ ትኩረትና ቅድሚያ ሰጥተን ለምናከናውናቸው ተግባራት መንስኤ ሆኗል፡፡  በመጀመርያ ደረጃ የክለቦቻችን ፕሮፌሽናሊዝም ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ከክለብ ላይሰንሲንግ  ጋር ተያይዞ በጣም ብዙ ሁኔታዎች መስተካከል እንደሚኖርባቸው አምነናል፡፡ ክለቦቻችን አስፈላጊውን የፕሮፌሽናል ደረጃ ሳያሟሉ ነው ክለብ እያልን የምንጠራቸው፡፡ ለክለቦች የፕሮፌሽናል ፍቃድ አሰጣጣችንን በደንብ ከልሰን መመልከት ይኖርብናል፡፡ ክለቦች በፋይናንስ ያላቸውን የተረጋጋ ሁኔታ በቅርበት በመከታተል ለመስራት ነው፡፡ ሜዳዎቻችን በትክክል የእግር ኳስ ውድድሮችን ማካሄድ ይችላሉ የሚለውን ማረጋገጥም ይመለከታል:: በሁለተኛ ደረጃ በፌደሬሽን አሰራር ውስጥ አዳዲስና እያስተካከልናቸው ያሉትን መመርያዎች ማጽደቅና ወደ ስራ መግባት ነው፡፡ ይህም የተጨዋቾችች ዝውውር፤ የአካዳሚዎች አሰራር፤ ሌሎችንም ይመለከታል፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ሁሉንም ውድድሮቻችን እንዴት መልሶ መጀመር ይቻላል የሚለው ነው፡፡ የሌሎች አገራትን ተመክሮ በማየት፤ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ውድድሮችን ለመምራት ነው፡፡ በመጨረሻም  በአዲስ አበባ የሚገኘውን የካፍ ‹‹ሴንተር ኦፍ ኤክሰለንስ›› በተሻለ ገፅታ፤ ብሄራዊ ቡድንን የሚያስተናግድ እንዲሆንና የምስራቅ አፍሪካ ትልቁ ማዕከል ለማድረግ ነው፡፡

Read 2888 times