Sunday, 28 June 2020 00:00

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ካፒቴኑ በረኛ ተካበ ዘውዴና ድሬደዋ
የሀረርጌና የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን የምንጊዜም ምርጥ በረኛ ተካበ ዘውዴ በቀደመ ትውልድ አይረሳም። የአንድ እግር ኳስ ቡድን ካፒቴን በጨዋታው ህግ መሰረት ብዙ ኃላፊነቶች የተጣለበት ወሳኝ ተጨዋች ነው። በጨዋታው ወቅት የቡድኑን ባጅ በማድረግ ይለያል።
ካፒቴን በጨዋታ ጎበዝ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የአመራር ችሎታውም ለዚህ ቦታ ያስመርጠዋል። ካፒቴን ከእጣ አወጣጥ ተሳትፎ የዘለለ ግዙፍ ሚና እንዳለው የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ቡድኑን በመምራት፣ በማስተባበርና በማነቃቃት ድርሻዎች አሉት። ካፒቴኑ በእግር ኳስ ጨዋታ በተጨዋቾች መካከል መግባባት እንዲፈጠርና አለመግባባትም ከተፈጠረ በማስማማት ለአንድ ውጤት እንዲበቁ ኃላፊነት የተጣለበት ሲሆን፤ ቡድኑን በተመለከተ በማናጀሩ የሚነሱ ውዝግቦች መፍትሄ የሚሰጥ እንዲሁም ቡድኑን ወክሎ ከዳኛው ጋር የሚደራደር ቁልፍ ተጫዋች ነው።
ካፒቴኑ በአካል ብቃት ከሌሎች የተሻለ መሆኑ አይጠበቅም። በብስልቱ፣ አመዛዛኝነቱና ኃላፊነት የመሸከም ባህሪዎች ያስመርጡታል። ቡድኑ በግማሽ የጨዋታ አባላቱ ሞራላቸው ዝቅ ሲል ያነሳሳል፤ የማሸነፍ እልህ እንዲፈጠር ያደርጋል። በእግርኳስ ጨዋታ ካፒቴኑ በቡድኑ ማናጀር የሚመረጥበት በርካታ መስፈርቶች አሉ። የተጫዋቹ ልምድ፣ የአመራር ክህሎቱ፣ አንጋፋነቱ  እንዲሁም የጨዋታ ክህሎቱ ደረጃና የተፈጥሮ ተሰጥኦዎቹ ግምት ውስጥ ይገባሉ።
ይህን ያነሳሁት ስለ እግር ኳስ ለማውራት አይደለም። በልጅነቴ ግብ ጠባቂ ሆኖ ለድሬደዋ፣ ለሀረርጌና ኢትዮጵያ ምርጥ በረኛ የነበረው ተካበ ዘውዴ ጋር የመገናኘት እድሉ የፈጠረብኝ ደስታ ነው። ሞዴሊስት ፈቲሀ መሀመድ ከቤልጂየም ደውላ በውጭ የሚኖሩ የድሬደዋ ልጆችና ወዳጆች ማህበር፣ አረጋውያንንና አቅመ ደካማ የሚረዱበት እንቅስቃሴ መጀመሩን ነገረችኝ። ሙያዊ ድጋፍ መስጠት የምንችልበት ሁኔዎች ካሉ ለመሳተፍ Google Zoom Meeting ተጋበዝኩ። በልጅነት የማውቀው ከድሬደዋና ሀረርጌ እስከ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በረኛ ተካበ ዘውዴና አስተባባሪዎች በሚመሩት የኢንተርኔት ውይይት ተሳተፍኩ። ሰብሳቢው ተካበ ድሮ የሚያውቃት ያቺ የሁሉም ከተማና ሀገር፣ የቆዩና በዚህ ኮቪድ ወቅት የገጠማትን ፈተና ልጆቿ ያለ ምንም ልዩነት፣ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እገዛ እንዲያደርጉ፣ ከጓደኞቹ ጋር እያከናወኑ ያለው በጎ ተግባር ያስመሰግናቸዋል።
በጎግል ዙም ውይይታችን 24 ተሳታፊዎች የነበሩ ሲሆን ሁሉም ለሀገራቸው ፍሬያማ ተግባራት ያከናወኑና በሚኖሩበት ሀገር የተሳካላቸው የድሬደዋ ልጆችና ወዳጆች ነበሩ። በዚሁ ተሳትፎ ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገንም በፈትያ አመቻችነት፣ ለተካበ ዘውዴ ያለውን አድናቆት በመግለጽ፣ ለድሬደዋ የበኩሉን እገዛ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል።
በውይይቱ ቁምነገር ብቻ ሆነ እንጂ በ1980ዎቹ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድን፣ በምስራቅና መካከለኛ አፍሪካ ዋንጫ ድል በኋላ ከተሰጣቸው ሽልማቶች አንዱ “21ኢንች ቴሌቪዥን” በመሆኑ ቴሌቪዥኗ የት ደረሰች ብዬ ለመጠየቅ ፈልጌ ነበር። ለተካበና ለቡድኑ አባላት በወቅቱ መንግስት ለእያንዳንዳቸው አንድ ቴሌቪዥንና መሬት እንደሸለማቸው አይረሳም። ቴሌቪዥን ውድና ትልቅ እቃ በነበረበት ጊዜ የተሰጠ በመሆኑ የተጫዋቾቹ ደስታን እነሱ ያውቁታል። የወቅቱ መሪ በዚህ ድል ከመደሰታቸው የተነሳ በአፍሪካ ትልቁን ስታዲየም እንሰራለን ብለው በሚዲያ ቢያውጁም ፤ያሉትን ለመፈጸም ብዙ በስልጣን አልቆዩም።
(ከእስክንድር ከበደ)
የቀድሞ የሀረርጌ ምርጥ የእግር ኳስ ቡድን

Read 4190 times