Print this page
Saturday, 27 June 2020 13:26

"አብሲት እንዳላደርግህ!"

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

   “ውዝፍ እዳቸውን በጊዜ የማይከፍሉ ደንበኞች ላይ እርምጃ እንወስዳለን…” ማለት ግን ጠብ ነው፡፡ ልክ ነዋ…እዚህ ሀገር እኮ በ“እርምጃ ይወሰዳል” ስም ስንትና ስንት ነገር ተደርጓል፡፡ እናማ ካልጠፉ አነጋገሮች “እርምጃ ይወሰዳል” ማለት አሪፍ አይደለም፡፡--
        
             እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰኔም ይኸው ከአጋማሹ ተሻገረ አይደል! “ሰኔ ሠላሳ ጠብቀኝ” ነገር የቡቅሻ ቀጠሮ ለዘንድሮ አይሠራም፡፡ ‘ሠላሳ’ የምትለው ቁጥርማ አለች፤ ወሩ ተለወጠ እንጂ! ቂ…ቂ…ቂ…
ፍቅር ከእኛ እንዳይለየን
እንዲቃናልን ሥራችን
መጨቃጨቅ ይወገድና
ሰላም ይሁን ለሁላችን
የሚሏት ዘመን የማይሽራት ዜማ አለች፡፡
ከእንትናዬው ጋር ምግብ ቤት ገብቶ ለሀያ ሦስት ደቂቃ ሜኑውን ሲያይ ከቆየ በኋላ አስተናጋጇን… “አንድ በያይነቱ አምጪልን” ብሎ ወደ እንትናዬው ዘወር ብሎ “ካነሰ እንጨምራለን; የሚል ጋባዥ አይነት…“ቆጣቢ” ነው የሚባለው? ቢያንስ፣ ቢያንስ እዛ ቆማ ስትቆጥብ የነበረችው አሳላፊ እኮ ያቃጠለችው ካሎሪ የምግቡን ዋጋ እጥፍ ይሆናል!
መቼም… “ለአንተ የሀምሳ ምናምን ብር በያይነቱ ልጅቱ የሁለት መቶ ሀምሳ ብር ጉልበት የምታጠፋው በምን እዳዋ ነው!” ተብሎ ጠብ አይጀመር ነገር! ለነገሩ ከተፈለገ ሰበብ አይመጣም…አንዳንድ ምግብ ቤት ገና ሁለቴ እንደጎረሳችሁ ሀያ ምናምን ጊዜ የሚመላለሱት ‘ላቭ አት ፈርስት ሳይት’ ነገር ሆኖባቸው ሳይሆን፣…አለ አይደል… በተዘዋዋሪ “ምን ይጎልትሀል፤ ቶሎ በልተህ ወንበር ልቀቅ” አይነት ትንኮሳ ነው፡፡
ሀሳብ አለን… ከምግቡ አይነትና ዋጋ ጋር ልንቆይበት የምንችለው ጊዜ አብሮ ሜኑው ላይ ይጻፍልንማ! “ለጎድን ጥብስ ሠላሳ ሶስት ደቂቃ፣” “ለተጋቢኖ አስራ ሦስት ደቂቃ፣” ምናምን ይባልልንማ!  እርቦን ገብተን አታሳቁና!
አንዳንድ የዘፈን ክሊፖች ላይ የምናየው ዳንኪራ… አለ አይደል…የሆኑ ለእኛ በዓይን ያልታዩን ጠላቶችን በእርግጫና በጫማ ጥፊ የሚያተራምሱ ነው እኮ የሚመስለው! ዘፈኑ ላይ እንኳን ትንኮሳ ይጥፋበት! አሀ…የቀሺም አሰልጣኝ ‘ዉሹ’ ምናምን ይመስላላ! ተረጋጉ አንጂ…በ“እንዴነሽ ገዳዎ” የምን ‘ኩንግ ፉ ፋይቲንግ’ ምናምን ነገር ነው!
ጉልበተኛ በዛ…ፎካሪ በዛ…እንደ እኛ አይነቱ ሙሉ የነርቭ ስርአቱ በአደባባይ ቁልጭ ብሎ የሚታየው ሁሉ “ጡንቻዬ የአንበሳ መንጋ ያሳድራል” አይነት ነገር እያለ ግራ አጋባን እኮ! ደግሞ እኮ የጀግናው ቁጥር በዝቶ የፈሪዎቹ ቁጥር ሲቀንስ…አለ አይደል…አሪፍ አይደለም፡፡  መኪና ትንሽ በተነካካ ቁጥር የሚኖረውን ከበባና ግርግር ታዩልኛላችሁ! ‘ሲኒየር ሲቲዝን’ ሁሉ እኮ ለገላጋይ እያስቸገረ ነው!
ዘንድሮ ለጠብ ምክንያት የሚያስፈልገው አይመስልም፡፡ ‘ትዌንቲ ሰምቲንጉም’ ፎካሪ…‘ሰቨንቲ  ሰምቲንጉም’ ፎካሪ!
የጥል ነገር ሲነሳ ምን አለ መሰላችሁ… ገላጋይ በበዛ ቁጥር የተጣሉት ሰዎች ያዙኝ ልቀቁኝ እንዴት እንደሚባባስ ልብ ብላችሁልኛል!  በፊት ጊዜ እኮ ሲያስችግሩ “ተዉአቸው፣ ይዋጣላቸው፣” የሚባል ነገር ነበር፡፡ ሰዉ ሲሰለቸው ምን ያድርግ! ታዲያላችሁ ግማሽ ቀን ከምናምን ሰዓት ሲሰዳደቡ ይውሏታል እንጂ እንዲች ብለው ጫፋቸውን አይነካኩም፡፡ ምን አለፋችሁ…ማራቶን የሚባል አይነት የስድብ ፉክክር ነው የሚካሄደው፡፡
“ነግሬያለሁ፣ በእጄ ሰበብ እንዳትሆን…”
“ሰዉን ብዬ እንጂ፣ አሳይህ ነበር!”
“ምን እንዳትሆን ነው!”
“አንድ ቀን አብሲት ነው የማደርግህ!”
“ይኸው አሁን አጠገብህ ቆሜልህ የለ እንዴ! ምን ቀጠሮ ያስፈልጋል!”
“በእጄ ሰበብ ለመሆን ነው…”
የምን መነባንብ ቅብጥርስዮ ነው! ይዋጣላችሁ ተባላችሁ አይደለም እንዴ!
ስሙኝማ…አሁን ለምሳሌ በሰርጉ ማግስት አዲሱን ሙሽራ… “እንዴት ነው… ነገርዬውን በቦታው አገኘኸው ወይስ ተቀድመሀል?” ቢል ቅልጥ ያለ ጠብ የማይነሳሳ! ምን አገባው! ስሙኛማ የምር ግን እሱ ነገር፣ በፊት ጊዜም እኮ ሙሽራው “አግኝቸዋለሁ…” ቢል እንኳን አይታመንም ነበር ማለት ነው! ልክ ነዋ…. እንደዛ ካልሆነ፣ “እስቲ አምጣው የእንትኑን ሸማ፣ እንድንስማማ…” አይነት በሰው የውስጥ ጉዳይ መረጃ ሳይሆን ማስረጃ ጥየቃ ምን አመጣው? ያውም በዜማ! ለማጠናከሪያ ደግሞ “እስቲ አምጣው የእንትኑን ሻሽ እንዳንሸሽ” ብሎ ነገር አስቸጋሪ እኮ ነው:: ከተገኘ ተገኘ፣ ካልተገኘም ጠፋ ነው እንጂ…ሽሽትን ምን አመጣው! (ለነገሩማ ዘንድሮ እንኳን እንዲህ ተብሎ ሊዘፈን ቀርቶ የዚህ አይነት የሰርግ ማግስት ዘፈን እንዳለ  የሚያውቅ ሰው ለመኖሩ መጣራት አለበት!)
እናላችሁ…አንዳንዴ በደህናው ጊዜ እንኳን ጠብ፣ ጠብ የሚለን ለምንድነው አያሰኛችሁም! አሁን ለምሳሌ ድርጅቶች የሆነ ማሳሰቢያ ሲያወጡ እኮ አለ አይደል… “አብሲት እንዳላደርግህ!” አይነት ቃና አላቸው፡፡ “ውዝፍ እዳቸውን በጊዜ የማይከፍሉ ደንበኞችን በህግ እንደምንጠይቅ እናሳስባለን…” ማለት አንድ ነገር ነው፡፡ በቃ ግልጽ ነው… “ክፈል፣ አለበለዛ የክስ ፋይል እንከፍትብሃለን” ነው፡፡ “ውዝፍ እዳቸውን በጊዜ የማይከፍሉ ደንበኞች ላይ እርምጃ እንወስዳለን…” ማለት ግን ጠብ ነው፡፡ ልክ ነዋ…እዚህ ሀገር እኮ በ“እርምጃ ይወሰዳል” ስም ስንትና ስንት ነገር ተደርጓል፡፡ እናማ ካልጠፉ አነጋገሮች “እርምጃ ይወሰዳል” ማለት አሪፍ አይደለም፡፡
“እስቲ አሁን ያልካትን ድገማት!” ብለው ማፋጠጥ የማይችሉ ትውልዶች ላይ “አብሲት እንዳላደርግህ!” አይነት ጀግንነት ቅሽምና ነው፡፡
ባለ ሱቁ “ቀንስ እንጂ…” እያለ ለሩብ ሰዓት የሚከራከረውን ሰው “ወይ ግዛ ወይ ሱቁን ልቀቅ…” ቢል ንዝንዙ ሰልችቶት ነው ምናምን ነገር ይባላል፡፡ ግን ሌላ አረፍተ ነገር ጨምሮ  “ምን፣ እዚህ ባዶ ኪሳቸውን ይመጡና ይነጅሱናል!” ምናምን ካለ… በቃ ጠብ ነው፡፡  
ግማሽ ኪሎ ምስር ክከ መሸመቻ ገንዘብ ለመስጠት አንድ ሳምንት ሙሉ የሚፈጅበት ‘አባወራ’ መከራዋን የምትበላውን ሚስቱን… “ስሚ፣ የዶሮ አሮስቶ እንዳማረኝ ነገር…” በቃ ለእሷ ትንኮሳ ነው፡፡ መጀመሪያ ነገር…ቀምሶት የማያውቀው ነገር እንዴት ሊያምረው ይችላል! ቂ…ቂ…ቂ… ሁለተኛ ነገር እሱ ገንዘብ አልሰጥ እያለ፣ አንድ ድስት ምስር ወጥ አስር ቀን ሙሉ ፍሪጅ ውስጥ በ‘ጥገኝነት’ በሚቀመጥበት… የዶሮ አሮስቶ! (‘ፈረንጅ’ ግርም ሲለው “ሪሊ!” ለሚላት ነገር የአማርኛ እኩያዋን ፈልጉልኝማ!)
ትናንት አይደል እንዴ… “በየጊዜው ቲማቲም፣ ቲማቲም  የምትይው አንድ ኪሎ ለሁለት ወር አይበቃንምና ነው!” ብሎ ጠብ ሊጀምር አጥር ነቅንቆ ነበር፡፡
“ስማ፣ ይሄ ኮት ግን ኦርጂናል ነው?”
“እኛ በቀጥታ ከጣልያን ነው የምናስመጣው፡፡”
“እንደሱ ከሆነ በል ዋጋውን እቅጩን ተናገር…” ምናምን ማለት አንድ ነገር ነው፡፡
“እሱ እባክህ ተወው፣ ሳልቫጅ ከየትም፣ ከየትም እየሰበሰባችሁ ቦምብ ተራ ‘ሜድ ኢን ኢታሊ’ የሚል ምልክት እንደምታስለጥፉ የማናውቅ መሰለህ!” ማለት ግን ጠብ ነው፡፡
እሷዬዋ ዘመድ ጥየቃ ትሄዳለች፡፡
“ገና ምንም ወጥ ሳልሠራ መጣሽብኝ፡፡ ትንሽ ድርቆሽ ቢጤ በሚጥሚጣ ልስጥሽ?” ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ልክ ነዋ…መጀመሪያ ነገር ድርቆሽ በሚጥሚጣ ብሎ ነገር የምን ሀገር ሜኑ ላይ ነው ያለው? “በተዘዋዋሪ እንደ ድርቆሽ የደረቅሽ ሚጥሚጣ ነሽ እያለችኝ ነው እንዴ!” ብትል አይፈረድባትም፡፡
ፍቅር ከእኛ እንዳይለየን
እንዲቃናልን ሥራችን
መጨቃጨቅ ይወገድና
ሰላም ይሁን ለሁላችን
የሚሏት ዘመን የማይሽራት ዜማ አለች፡፡
“አብሲት እንዳላደርገህ!” አይነት ‘ጠብ ያለሽ በዳቦ’ በእግድ ይቋረጥልንና ላጣደፉን ነገሮች መፍትሄ ብንፈልግ ደግ ይሆናል፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1772 times