Monday, 29 June 2020 00:00

የሰዎች የብቃት ልዕልና - በኪነ ጥበብ፣ በጥንታዊ ትረካና በመጽሐፈ ሄኖክ፡፡

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(3 votes)

  የአንዳንድ ሰው ልዩ ብቃት፣  ግምታችንን የሚጥስ ደመናውን የሚሻገር “ሰማይ ጠቀስ” እየሆነ፤ ለእይታ ይጋረድብናል:: ከየት ተነስቶ፣ በየት በኩል፣ እንዴት ሽቅብ እንደመጠበቀ፣ በቅጡ ለመገንዘብ ያስቸግረናል፡፡ ከመሃላችን ሆኖም፣ በአንድ ክፍል አብሮን ተምሮ፣ ሰፈር መንደራችን ውስጥ አድጐ፣ በጉርብትና በስራ ቦታ ከአጠገባችን እያየነውም እንኳ፣ የብቃት ከፍታው፣ “ወለል ብሎ” ላይታየን ይችላል፡፡
የብቃቱ ምጥቀት፣ ወይም የብቃቷ ልዕልና…ጭላንጭሉ ቢታየን እንኳ፣ የብቃታቸውን ምንነትና የእድገታቸውን ጉዞ፣ በምልዓት መረዳት ቀላል አይደለም:: ለዚህም ነው፤ በዘመናችን ገናና ፊልሞች ውስጥ፣ ጀግና ሰዎች፣ እንደ ልዩ ፍጥረት የሚቆጠሩት (እንደ Superman, እንደ Demigod, Magical ወይም Mutant)። የብቃት ባለቤቶች፤ የብቃት ጌቶች፤ በአንዳች ተዓምር ከነሙሉ ብቃታቸው የተፈረጡ፣ ገና ከመነሻው ተሰርተው ተሟልተው የተወለዱ፣ ያለቀላቸው ወይም ከሌላ ዓለም የመጡ ፍጡራን (aliens) ሆነው ይታዩናል፡፡
ከዘመናችን ገናና ፊልሞች በተጨማሪ፣ ዋና ዋናዎቹ የጥንት ትረካዎችም፣ ይህንን እውነታ ይመሰክራሉ፡፡ ቀዳሚዎቹ ሁለት የአለማችን ስልጣኔዎች፣ ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር በቅርበት የተቆራኙ ስለሆኑ፣ በማስረጃነት ሳይጠቀሱ ሊታለፉ አይችሉም፡፡
የመጀመሪያው የስልጣኔ ታሪክ፣ ከዛሬዋ ኢራቅ፣ ከባግዳድ ከተማ አጠገብ ይነሳል:: የሱመር እና የባቢሎን የስልጣኔ ማዕከላትን ጨምሮ፤ እስከ ሶሪያና ኢራን፣ እስከ የመን እና ኢትዮጵያ፣ በሰፊው የተንሰራፋ ነው- የባቢሎን ስልጣኔ፡፡
የቋንቋ ጥናቶችም ይህንን ያረጋግጣሉ:: ለጥንታዊው የባቢሎን ቋንቋ እጅጉን የቀረቡ የዘመናችን ቋንቋዎች ጥቂት ናቸው:: ከነዚህም ውስጥ፣ አብዛኞቹ  የሚገኙት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ለካ፣ የባቢሎን ቋንቋ ተረት አይደለም፡፡ ለካ ውጥንቅጡ የወጣ የተሳከረ ቋንቋ አይደለም - የባቢሎን ቋንቋ፡፡  
እንደ ምናባዊ አፈታሪክ ሲቆጠር የነበረው የባቢሎን ቋንቋ፤ “በስነጽሑፍ እጅጉን የተራቀቀ፣ የመጀመሪያው የአለማችን ቋንቋ” እንደነበረ የታወቀው፣ ከ150 ዓመት ወዲህ ነው፡፡ ምን ተገኘ? ብዙ ጽሑፎች፣ ትልልቅ መዝገበ ቃላት ጭምር፣ በፍርስራሽ ቤተመፃሕፍት ውስጥ፤ ከአሸዋ ክምር ስር ተቀብረው ተገኙ፡፡ እናም፣ የባቢሎን ተረት ተቀይሮ ታሪክ ሆነ፡፡ ጥንታዊው ቋንቋ እንደ አዲስ ተጠና፡፡ ተተረጐመ፡፡
ከሺ ዓመታት በፊት የጠፋው የባቢሎን ቋንቋ፣ ከኢትዮጵያ የዘመናችን ቋንቋዎች ጋር ተቀራራቢ ይሆናል ብሎ ማን ገመተ? ከመቶ ቃላት መካከል 45 ተመሳሳይ ቃላት የያዙ ቋንቋዎች በጣም ተቀራራቢ ናቸው፡፡ የባቢሎንና የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የዚህን ያህል ይቀራረባሉ፡፡ “ዋናው ምንጭ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ወይስ ባቢሎን ግድም” የሚለው ጥያቄ፤ ገና ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልገው የሚገልፁ ምሁራን አሉ::
የሆነ ሆኖ፤ የጀግና ሰው ጀብዶችን የሚተርክ፤ የመጀመሪያው የስነጽሑፍ ድርሰት የተገኘው ከዚሁ የነባቢሎን ስልጣኔ ነው፡፡ የጊልጋሜሽ የጀብድ ገድል የተሰኘ ነው ትረካው:: ጊልጋሜሽ፣ በአእምሮና በእውቀት፣ በችሎታና በብርታት፣ ማንም አይስተካከለው፡፡ ወደር የሌለው የብቃት ጌታ ነው- ጊልጋሜሽ፡፡
እውቀትንና ጥበብን እያስተማረ፣ ባቢሎንን ወደ ስልጣኔና ብልጽግና የመራ፣ በዚያው ልክ ሃያል ተዋጊ እንደሆነ ድርሰቱ ይተርካል፡፡ ድንቅ ነው፡፡ በደልን አይቀበልም። ከሃያል አማልክትም ጋር ተዋግቶ ያሸንፋል፡፡ ለማመን ይከብዳል:: ግን፣ እንደማሳመኛ የቀረበ ማስረጃ አለ፡፡ ጊልጋሜሽ ልዩ ፍጡር ነው። በከፊል ሰው፣ በከፊል አምላክ ነው። በከፊል የምድር በከፊል የሌላ ዓለም ፍጡር እንደሆነ ትረካው ይገልፃል:: “ሁለት እጅ ከዚያ፣ አንድ እጅ ከዚያ” በማለት ጭምር በክፍልፋይ ያብራራል፡፡
ከኢትዮጵያ ጋር የተሳሰረ ሌላኛው የአለማችን ስልጣኔ፤ የግብጽ ስልጣኔ ነው:: ከበርካታ ድንቅ ታሪኮች መካከል፣ አንዱን ብቻ እንጥቀስ፡፡
የጽሑፍ ጥበብን፣ የቀን አቆጣጠርን፣ ህግና ስርዓትን ያስተማረ፤ የእውቀትና የጥበብ ፈርቀዳጅ ማን እንደሆነ የሚተርኩ ጽሑፎች አሉ፡፡ ጦጥ፣ ወይም ጦት ይሉታል:: ድንቅ ብቃት አይደል? ለዚያውም ለማመን የሚከብድ፡፡ በእርግጥ፤ ጦጥ እንደሰው በምድር ኖሯል፡፡ ግን እንደ አምላክም ነው ይላል - ጥንታዊው የግብፅ ትረካ፡፡ ከግሪክም ተመሳሳይ የልዩ ሰው ጥንታዊ ትረካዎችን እናገኛለን፡፡ ለምን?
የብቃት ሰዎች፣ ልዩ ፍጡር የሚሆኑብን ለምንድነው?
በአንድ በኩል፤ የድንቅ ሰዎች፣ አስገራሚ የብቃት ከፍታ፤ ከምግት ከሕልማችን የሚልቅ፤ የተዓምር ያህልም ብርቅ ይሆንና፣ እጅግ ያስደምመናል፤ የአድናቆት ማዕበል ያጥለቀልቀናል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፤ የሷ ወይም የሱ የብቃት ልዕልና፣ ለማመን ለመረዳት አልመች አልጨበጥ ይለናል፡፡ ማነፃፀሪያ፣ ማወዳደሪያ፣ ተቀራራቢ ምሳሌ፣ ተመሳሳይ መለኪያ አጥተን፣ ግራ እንጋባለን፡፡
ከታች ከትንሽ ተነስቶ፣ በዚህ አቅጣጫና ዘዴ፣ ወይም በዚያ መንገድና መሳሪያ፣ በምን ያህል ጥበብና ጥረት፣ የቱን ያህል እንደመጠቀ፣ ከብቃት ማማ እንዴት ወደ ተራራ አናት እንደደረሰ፣ ማሳየትም ማየትም እየተሳነን፤ “ወይ ተዓምር!” ያሰኘናል፡፡ ከማይታወቅ የምናብ ዓለም የመጣ፣ በሰው መልክ፣ ድንገት የተከሰተ፣ ልዩ “ተዓምር” ይሆንብናል፡፡
በዓለማቀፍ ደረጃ፣ በሰው ልጅ ታሪክ ያልታየ፣ “ወደር - የለሽ” አዲስ የብቃት ከፍታ ላይ የደረሱ ሰዎችን፣ በእውን እናውቃለን፡፡ ወደላቀ ብቃት የደረሱበትን መንገድ ባናውቅም፣ ዘዴና ጥረታቸው በዝርዝር ፍንትው ብሎ ባይታየንም፤ የመንስኤና የጉዞ ታሪካቸውን፣ በተሟላ በሚያረካ አሳማኝ ትረካ በእውን ማጣጣም ባንችልም፣…የተራራው ጫፍ ላይ ሲደርሱ ግን፣ ስኬታቸውን በእውን እናየዋለን:: መንስኤውንና ጉዞውን ሳይሆን፤ ውጤቱን ማየት አያቅተንም፡፡
ታሪከኛ አትሌቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከአበበ ቢቂላና ከማሞ ወልዴ ጀምሮ፣ ምሩጽ ይፍጠር፣ ከዚያም ኃይሌ ገብረሥላሴና ቀነኒሳ በቀለ…ልዩ ታሪክ ሰርተዋል፡፡ በዓለም የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ፣ ታይቶ የማይታወቅ አዲስ የብቃት ከፍታን፣ አዲስ የታሪክ እመርታን ያስመዘገቡ ልዩ ሰዎች ናቸው፡፡
ከደራርቱ ቱሉ ጀምሮ፣ ጥሩነሽ ዲባባና መሰረት ደፋር፤ አልማዝ አያናና ገንዘቤ ዲባባ…”በሰው ልጅ የድንቅ ብቃት መዝገብ” ውስጥ፣ ደማቅ ታሪክ ያሰፈሩ አስገራሚ ጀግኖች ናቸው፡፡
ከየት ተነስተው፣ በስንት ዓመት ጥረት፣ ምን ያህል አስቸጋሪ ውጣ ውረዶችን እንደተሻገሩ፣ ስንቱን ቁልቁለትና አቀበት እንደተጓዙ፣ …የጀግኖቹን ታሪክ እለት በእለት ስንከታተል አልነበረም፡፡ ከጀግኖቹ ጋር የምንተዋወቀው፤ በብቃት እጅግ ከመጠቁ በኋላ ነው - እንደ ድንገተኛ ተዓምር፡፡
የሼህ መሐመድ አልአሙዲ ዓለማቀፍ ኢንቨስትመንትን ያወቅነው፤ ቢሊዬነር ከሆኑ በኋላ አይደል? የሃዲስ አለማየሁ ልብወለድ፣ የፀጋዬ ገብረመድህን ትያትርና ግጥም፣ ለማመን የሚያስቸግሩ የመዝገቡ ተሰማ ስዕሎች…እነዚህ ተዓምረኛ የኪነጥበብ ከፍታዎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከነ ምርጥ ጥበባቸው ጋር የተፈጠሩና ከነብቃታቸው የተወለዱ ያህል፤ የኦሎምፒክ ውጤታቸውን፣ የስዕል ወይም የትያትር ጥበባቸውን ስናይ፣ ልብወለድና ግጥማቸውን ስናነብ ነው፤ እነዚያን ድንቅ ሰዎች የምናውቃቸው፡፡
ለነገሩ፤ ብቃታቸውንና የስራ ውጤታቸውን ለመገንዘብ ሳንችል፣ በስም ብቻ ሲጠቀሱ የምንሰማቸው ልዩ ሰዎችም ይኖራሉ - የሙዚቃ ጥበበኛው ያሬድና ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብ (ወርቄ) ምሳሌ ናቸው፡፡
የአክሱምና የሀረርን ምስረታ፣ የአስተዳደር ስርዓታቸውንና አለማቀፍ የንግድ ግንኙነታቸውን የቀረፁ የጥንት ሰዎችማ፣ በአብዛኛው በስም እንኳ አይታወቁም፡፡
ከፀሐይ ግርዶሽ ጋር ተያይዞ ሲጠቀስ የነበረውን የሄኖክ መጽሐፍ ተመልከቱ፡፡ ዝናው ሲነገር በተደጋጋሚ ሰምተን ይሆናል:: ግን ስለመጽሐፉ ምንነትና ይዘትስ? ስለ አፃፃፉ ታሪክ ወይም ስለተርጓሚዎቹስ፣ ኢምንት ይታወቃል? ታሪከኛ መጽሐፍ ቢሆንም ማለቴ ነው፡፡
ታሪከኛው መጽሐፍና “ልዩ ሰዎች”።
ታሪከኛነቱን አስቡት፡፡ በአንድ በኩል፤ “በመጽሐፈ ሄኖክ እንደተገለፀው” እየተባለ ከሁለት ሺ ዓመታት በላይ ተጽፎለታል:: ተነግሮለታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ “መጽሐፈ ሄኖክ የታለ?” ሲባል፣ የትም የለም፡፡ ጠፋ። ከእይታ እንደተሰወረ፣ ምዕተ ዓመታት ተቆጠሩ:: በየመሃሉ፣ “እዚያ ግድም ተገኘ”፣ “ወዲያ ማዶ ታየ” ተብሎ ይወራል፡፡ ግን በእውን አልታየም፡፡ የውሃ ሽታ ሆነ፡፡ መወራቱ  ግን አልተቋረጠም፡፡
ከምድረ ገጽ የጠፋና ለ1500 ዓመታት ተፈልጐ ያልተገኘ መጽሐፍ፤ “ኢትዮጵያ ውስጥ አለ” ተብሎ ወሬ መናፈሱም አይገርምም፡፡ ያው፣ አድራሻው የጠፋ መጽሐፍ፣ ብዙ ይወራለታል፡፡
ኢትዮጵያም ብዙ የሚነገርላት አገር ናት:: የሙሴ ጽላትና ታቦት፣ የዳዊት ዙፋንና የጠቢቡ ሰለሞን ቀለበት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኙ፤ ከሊቢያ እስከ ግብጽና ሶሪያ፣ ከእንግሊዝ እስከ ፈረንሳይና ጀርመን ተወርቷል፡፡ ሌላ ወሬ ተጨመረበትና፤ መጽሐፈ ሄኖክም ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ተባለ፡፡
“ወደ ምስራቅ በኩል ታይቷል”፤ “ወደ ደቡብ አቅጣጫ ተገኝቷል” እየተባለ ብዙ የተወራለት፤ ነገር ግን ለሺ ዓመታት ከሰው ዓይን የጠፋው የሔኖክ መጽሐፍ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለ ሲነገርለት፤ ምን ያህል ያሳምናል? “ብታምኑም ባታምኑም” ብለው የሚተርኩ መቼም አይጠፉም፡፡
ጄምስ ብሩስ፣ ኢትዮጵያን ዞሮ፣ ጥናቱንና አሰሳውን ጨርሶ ወደ አገሩ ሲመለስም፣ ተመሳሳይ ነገር ተናግሯል፡፡ መጽሐፈ ሄኖክን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳገኘ ገልጿል፡፡ ግን፤ በመናገር ብቻ አላበቃም፡፡  
በግዕዝ የተዘጋጀ የሄኖክ መጽሐፍ ይዞ ነው፤ ጀምስ ብሩስ ወደአገሩ የተመለሰው፡፡ ለዚያውም ሦስት መጽሐፍ፡፡ ለሺ ዓመታት ከምድረ ገጽ ጠፍቶ ያልተገኘው መጽሐፍ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት እንደልብ ይገኛል? አስገራሚ ነው፡፡
ተተርጉሞ ሲታይ ግን፤ የመጽሐፉ ትክክለኛነት፣ የጥርጣሬ አይን ውስጥ ገባ፡፡ አሳማኝ አይደለም ተባለ፡፡ ለምን? እንግዲህ፤ መጽሐፈ ሄኖክ ጥንታዊ እንደሆነ፣ ከ2ሺ ዓመት በፊት፣ ማለትም ከኢየሱስ በፊት የነበረ መጽሐፍ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
እንዴት? ምክንያቱም፣ በኢየሱስ ታሪክና በተከታዮቹ የሐይማኖት መፃሕፍት ውስጥ፣ በኦሪት ድርሳናት ውስጥም፤ በስም ሲጠቀስ የነበረ መጽሐፍ ነው- ትክክለኛው ጥንታዊ የሄኖክ መጽሐፍ፡፡ ቀዳሚና ጥንታዊ ከሆነ፣ የኢየሱስ ተከታዮች ባዘጋጇቸው መፃሕፍት ውስጥ የምናገኛቸው አዳዲስ አገላለፆችና አባባሎች፣  በጥንታዊው የሄኖክ መጽሐፍ ውስጥ መኖር የለባቸውም፡፡
የግዕዙ መጽሐፈ ሄኖክ ውስጥ ግን፤ የኢየሱስና የተከታዮቹ አዳዲስ አገላለፆችና አባባሎች ተካትተዋል - ለዚያውም በብዛት::
እንዴት መሰላችሁ? “ከሁለት መቶ ዓመት በፊት የታተመ ነው” የተባለለት መጽሐፍ ተገኘ እንበል፡፡ ገለጥ ተደርጐ ሲነበብ ግን፣ ስለ ሬዲዮ እና ስለ ኮምፒዩተር የሚተርክ ጽሑፍ ቢሆንብን አስቡት፡፡ “እነ ኮምፒተርማ መቶ ዓመት አልሞላቸውም” እንላለን፡፡ ስለኮምፒተር የሚያወራ ሆኖ ሳለ፣ “ከሁለት መቶ ዓመት በፊት የታተመ መጽሐፍ ነው” ተብሎ ቢመጣ፣ አሳማኝ ነው? “ፎርጅድ” እንደሚሆን አትጠረጥሩም? የግዕዙ መጽሐፈ ሄኖክም፤ ተጠረጠረ፡፡
ይሄ፣ “ኦሪጅናሉ”፣ ጥንታዊው የሄኖክ መጽሐፍ ሊሆን አይችልም ተባለ፡፡
ከኢየሱስ በኋላ፤ እየተዘወተሩ የመጡ አዳዲስ የሃይማኖት አገላለፆችና አባባሎች ቢኖሩም፤ ምናልባት፤ ከመጽሐፈ ሄኖክ የመነጩ አገላለፆች ቢሆኑስ? የግዕዙ መጽሐፈ ሄኖክ… ኦሪጅናሉ ጥንታዊ መጽሐፍ ቢሆንስ? በኢየሱስ ዘመን፤ ከፍተኛ ተወዳጅነትና ተነባቢነት የነበረው መፅሐፍ ቢሆንስ? ማመሳከሪያ ከሌለ እንዴት ይታወቃል?
የግዕዙ መጽሐፈ ሄኖክ፣ ጥንታዊውና ትክክለኛው መጽሐፍ እንደሆነ የተረጋገጠው፤ በ20ኛው ክፍለዘመን፣ ድንገት በዋሻ ውስጥ በርካታ ጥንታዊ መፃሕፍት በመገኘታቸው ነው - (the dead sea scrolls ይሏቸዋል)፡፡
ዋሻ ውስጥ የተገኙት ጥንታዊ መፃሕፍት፣ በጊዜ ብዛት ተጎሳቁለው ተጐድተዋል:: ተሸራርፈዋል፡፡ ቁርጥራጭ እንጂ የተሟሉ አይደሉም፡፡ ግን ሙሉ ለሙሉ አልተበላሹም፡፡ ተሸራርፈውም ቢሆን፣ ምንነታቸውን ለማወቅ አላስቸገረም፡፡
ከሁለት ሺ ዓመት በላይ እንዳስቆጠሩ ከተነገረላቸው ከነዚህ ጥንታዊ መፃሕፍት ውስጥ፤ ምን ቢገኝ ጥሩ ነው? መጽሐፈ ሄኖክ ተገኘ፡፡ ለዚያውም 10 መፃሕፍት:: ያኔ ጥንት፤ በጣም ተነባቢ መጽሐፍ ነበር ማለት ነው፡፡ በጊዜ ብዛት በከፊል የተጓደሉ መፃሕፍት ቢሆኑም፤ ማመሳከሪያ መሆን ይችላሉ፡፡ ለግዕዙ መጽሐፈ ሄኖክ፣ ጥሩ ማነፃፀሪያ ተገኘ፡፡
እውነትም፣ የግዕዙ መጽሐፈ ሄኖክ፣ ትክክለኛና ጥንታዊ እንደሆነ ተረጋገጠ፡፡ እስከዛሬም ሌላ የተሟላ የመጽሐፈ ሄኖክ ምንጭ የለም፡፡ ታሪከኛ መጽሐፍ መሆኑ ያከራክራል? አያከራክርም፡፡ ግን በይዘቱም ታሪከኛ ነው፡፡
“ተፈጥሮን ተመልከቱ፤ ከዘላለማዊ ስርዓታቸው ዝንፍ አይሉም” እያለ የእውቀትና የሳይንስ ዝንባሌን ይጠቁማል - የሄኖክ መጽሐፍ፡፡ አንድ ዓመት፤ 360 ቀናት ሳይሆን 364 ቀናት እንደሆነ፣ የፀሐይ ዓመታዊ ዑደትን እየተነተነ ያስረዳል፡፡ ያስተምራል፡፡ በሌላ በኩል ግን፣ እውቀትን፣ እርሻን፣ የብረታብረት ቴክኖሎጂን የሚያስተምሩና የሚያሰለጥኑ፣ ልዩ የብቃት ሰዎች መከሰታቸውንም ይተርካል፡፡
በባቢሎን፣ በግብጽ፣ በግሪክ ጥንታዊ ጽሑፎች ላይ እንዳየነው፤ በመጽሐፈ ሄኖክ ውስጥም፤ ልዩ የብቃት ሰዎች፣ በከፊል ሰው፣ በከፊል መልዓክ እንደሆኑ ተጠቅሷል::  
የብቃት ሰዎች፣ በዘመናችን ገናና ፊልሞች ብቻ ሳይሆን፣ በጥንታዊ ትረካዎችም ውስጥ፣ እንደ ልዩ ፍጡር ተደርገው የሚቆጠሩት፤ በተመሳሳይ ምክንያት ነው? ይመስላል። የጀግና ሰዎችን ጥረት ሳይሆን ውጤታው ብቻ ነው የሚታየን። 

Read 2625 times