Saturday, 27 June 2020 12:45

የአገራችን ፖለቲካና የሽምግልና ጥረቶች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

*የሽምግልና እሴታችንን ለምን አንጠቀምበትም ብለን ነው የተሰባሰብነው
  *አሉታዊ እሳቤዎችን እየቀነስን፤ አዎንታዊ እሳቤዎችን ማጎልበት አለብን
  *ሁላችንም በጥቂቱ ከራሳችን ጋር ሱባዔ መግባት ያስፈልገናል
  *መንግሥት የሽምግልናን ወጪ መቼም ሸፍኖ አያውቅም

           የኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት ላለፉት 15 ዓመታት የተለያዩ የሽምግልና ጥረቶችን አድርጓል፡፡ ምን ያህሉ ተሳክተውለታል!? ምን ያህሉስ ከሽፈውበታል? አሁን በህወኃትና በብልፅግና ፓርቲ መካከል የጀመረው የሽምግልና ጥረትስ ፍሬ ያፈራ ይሆን? ለመሆኑ ሽምግልና ማለት ምን ማለት ነው? ዓላማውስ ምንድን ነው? ዘለቄታዊ መፍትሄ ያመጣ ይሆን? ሽማግሌዎቹ ብዙ ጊዜ የሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው? በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአገር ሽማግሌዎች መማክርትና የብሔራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን አባል የሆኑትን ፕ/ር አህመድ ዘካሪያን፣ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ  አነጋግሯቸዋል። እነሆ፡-

                 ተሰሚነት ያላችሁ ግለሰቦች ተሰባስባችሁ አገራዊ የማሸማገል ጥረት ከጀመራችሁ ብዙ ጊዜ ሆኗችኋል። እስከ ዛሬ የተደረጉ የሽምግልና ጥረቶችን እንዴት ይገመግሟቸዋል?
በሽምግልናም ሆነ በእርቅ ችግሮች መፍትሄ የሚያገኙት ባጠቃላይ ፖለቲካውና ኢኮኖሚው መፍትሄ እያገኘ ሲመጣ ነው። ዝም ብሎ በጠራራ ፀሐይ “ሰላም ሰላም” እየተባለ ቢጮህ፣ የሚመጣ ለውጥ አይኖርም። የኛ የሽምግልና ጥረት ዓላማው፤ ጥፋትን ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ ሳይሆን መቀነስ መቻል ነው። ጥፋትን መቀነስ ከተቻለ ለሌላው በዛሬና በነገ መሀል የፈጣሪ ፀጋ ነው የሚሆነው። ለአንዳንዶች ጥረቱ ዝም ብሎ ውጤት አልባ ልፋት ይመስላቸዋል። ነገር ግን ለኔ በሽምግልና ጥረታችን፣ ለአንድም ቀን ቢሆን ችግርን ማስቀረት ወይም መቀነስ መቻል ስኬት ነው። ከዚያ በመለስ ላለው የፈጣሪ ፀጋን መለመን ነው። ብዙ ነገር እየሆነ ያለው በዚያ መንገድ ነው። ብዙ ነገር በአቀራረብ፣ በአነጋገር ይቀዘቅዛል። ሽምግልናውም መወሰድ ያለበት በዚህ ውጤቱ ነው። ማቀዝቀዝ መቻል በራሱ ውጤት ነው። የሰውን ልብ ለአንድ ደቂቃም ቢሆን፣ እርህሩህ ማድረግ ከተቻለ ሽምግልናው ሠርቷል ማለት ነው። ለምሳሌ ባለፈው ሁለት ዓመት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በትግራይ ክልል የጦርነት ጉሰማ ነበር። በቦታው ሄደህ ብታየው፣ በትክክልም የጦርነት ጉሰማው በተግባር ነበር። ወጣቱ ተዘጋጅቷል፤ ወታደሮች እየሰለጠኑ ነበር። በግልጽ የሚታይ የጦርነት ዝግጅት ነበር። ሁለቱም ዘንድ ሄደን፣ መሪዎቹን መሬት ላይ ተንከባለን ነው የለመንናቸው። እነሱም የኛን ሁኔታ ሲያዩ፣ ነገሩን በሩህሩህ ልብ ነበር ያዩት። እኛም የምንፈልገው ያንን ነበር። ለኛ ተሳካ አልተሳካ የምንለው ይሄን አይተን ነው። እንደ ሰው ለአንድ ደቂቃም ቢሆን ቆም ብለው ማሰብ መቻላቸው በቂያችን ነው። ቢያንስ ከመሞት መሰንበትን፣ ከመጠፋፋት መስከንን መርጠዋል። ያ ለኛ ስኬት ነው። ሌላው በፈለገው መንገድ እየተረጎመ ሊረዳው ይችላል። ለኛ ግን ስኬታችን ለደቂቃም ቢሆን እንደ ሰው እንዲያስቡ ማድረጋችን ነው። የእነሱን ልብ ማራስ መቻል ነው ጥበቡ። የእነሱ ልብ ረስርሶ ሕዝብ አንድ ቀን እንኳ እንቅልፍ መተኛቱ ስኬት ነው። ለኛ ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ባይፈታም ጊዜ ከተገዛበት ትልቅ ስኬት ነው።
የሀገር ሽማግሌዎች መማክርቱ "ወገንተኛ ነው፤ የሽምግልናን ባህል እያበላሸ ነው" የሚል ወቀሳ ይሰነዘርበታል… እርስዎ ምን ይላሉ?
አሁን በሽምግልናው ውስጥ ያለን ሰዎች በግለሰብ ደረጃ የተለያየ አመለካከት ሊኖረን ይችላል። ግን በሽምግልና ድምፅ ስንናገር ወገንተኛነት የለንም። እንሁን ብንልም የምንከተለው የሽምግልና አይነት አይፈቅድልንም። ምናልባት በግለሰብ ደረጃ ከተሸምጋዮቹ ጋር ሻይ ቡና የሚል ሊኖር ይችል ይሆናል። ግን ይሄ ሽምግልናው ላይ ምንም ተፅዕኖ አያመጣም። ስለ ሽምግልና ስናወራ ስለ አገር ሰላም ነው የምናወራው፤ ስለ ፖለቲካ ሴራ አይደለም። ያንን ለማድረግም ሁኔታው አይፈቅድም። ስለ አገር ሰላም ነው እንቅልፍ የምናጣው። የምናገኘው ገንዘብ ወይም የኢኮኖሚ አሊያም የሥልጣን ጥቅም የለም። እኔ ለምሳሌ በራሴ ገንዘብ ነው ይሄን የምሰራው። ጡረተኛ ነኝ። ከገንዘብ ባሻገር የራሴን ጊዜ ነው የምሰዋው። ሌላው ቁጭ ብሎ ሊያማ ይችላል። እሱ የራሱ ምርጫ ነው። እኔ ግን የምችለውን እጥራለሁ። እኛን የሚነቅፉ ወገኖች እስቲ የተሻለ አማራጭ ያምጡ። እኛ ፍላጎታችን ልጆቻችን እንዳይጎዱ፤ አገር ሰላም እንድትሆን ነው። ሌላ አላማ የለንም። ሽምግልና ስለ ሰላም ምን እናድርግ ተብሎ የሚመከርበት እንጂ የፖለቲካ ሴራ የሚጎነጎንበት አይደለም። እርካታው ሰላማዊ ሁኔታ ሲፈጠር ነው፤ ውጤቱ ያ ነው።
የሽምግልና ወጪያችሁን የሚሸፍነው ማን ነው?
በዚህ ሂደት ትልቁ ችግር ወጪን መሸፈን ነው። መንግሥት የኛን ወጪ አይሸፍንም፤ ሸፍኖም አያውቅም። ለጊዜው የሚረዳን አንድ ድርጅት አለ። ይሄ ድርጅት ባይኖር መሰብሰብም እንኳን አንችልም ነበር።
ወጪያችሁን የሚሸፍነው ድርጅት ማነው?
በፓስተር ዳንኤል የሚመራው “ጀስቲስ ፎር ኦል” ነው። እሱ ባይኖር ኖሮ ሽምግልና የሚባለውም ነገር አይኖርም ነበር። ብዙ የሽማግሌ ስብስቦች አቅም በማጣት ፈርሰዋል። ሽምግልና የጊዜና የገንዘብ አቅም ይፈልጋል። 10 ሰው ለመሰብሰብም ወጪ ይጠይቃል። ይሄ ወጪ የሚሸፈነው በዚህ ድርጅት ነው። የመንግሥት አምስት ሳንቲም የለበትም።
ምን አይነት የሽምግልና ሂደት ነው የምትከተሉት?
እኛ የምንሰራው ማደራደር አይደለም። ይሄን አድርጉ፣ ያንን አታድርጉ አንልም። እስካሁን ባለው እንቅስቃሴያችን ኢትዮጵያን በሙሉ አዳርሰናል። ሁሉም ጋ ስንሄድ የምንለው “እባካችሁ ሰላም አውርዱ!” ነው። እኛ ልመና ብቻ ነው የምናቀርበው። በዚያች ልመና ጠቡ ጥቂት ይቀዘቅዛል። ቀጣይነት ያለው ክትትል ካልተደረገ ደግሞ እንደገና ይግላል። አንዱ ችግራችን ይሄ ድጋሚ የመጋል ጉዳይ ነው። የፖለቲካ ሰዎችም ለሳምንት ያህል የታረቁ ይመስሉና እንደገና ጠቡ ይገነፍላል። እኛም እየሞከርን ነው የምንሄደው እንጂ ያለቀለት የሚባል ነገር የለም። ሽምግልናችን ደግሞ ወገንተኛ አይደለም። ወገንተኛ ነው የሚባለው ዳኝነት ብንሰጥ ነበር። እኛ ዳኝነት አንሰጥም፤ ማቀራረብ ተዉ ብሎ መለመን ብቻ ነው።
በሽምግልና ጥረታችሁ የሚገጥሟችሁ ፈተናዎች ምንድን ናቸው? ሽምግልናን በኢትዮጵያ አስቸጋሪ የሚያደርጉ ነገሮችን ሊነግሩን ይችላሉ?
አንደኛ፤ ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ እልኸኛ ነን። ሁለተኛ፤ የፖለቲካ የስልጣን ሂደታችን ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ችግር አለበት። ከጥንት ጀምሮ አገረ መንግሥት እናውቃለን እንላለን፤ ነገር ግን የሥልጣን ሽግግራችን ሁሌም ችግር ያለበት ነው። ሌላም አገር ይሄ ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ካለን የአገረ መንግሥት እድሜ ጋር ስናወዳድረው ከየትኛውም የባስን ነን። ክፋቱ ደግሞ ለወደፊትም በአጭር ጊዜ የሚስተካከል አይመስልም። ለዚህ ችግራችን ምክንያቱ፤ መሪ ከመረጥን በኋላ እንዲሰራ ብዙም እድል የምንሰጥ አለመሆናችን ነው። ሁሌም ለመረጥነው መሪ እንቅፋት የምንሆን ከሆነ የሚሰራ መሪ አናገኝም። ዘመናዊ ኢትዮጵያ ተመሰረተች ከሚባልበት ከቴዎድሮስ ዘመን አንስቶ ተመሳሳይ ችግር ይስተዋላል:: ለመሪዎች ጊዜ አንሰጥም። ስለዚህ ይሄን እንዴት እናስተናግድ የሚለው ነው በሂደት መልስ ማግኘት ያለበት። እልህንም እንዴት ማስተናገድ ይቻላል ለሚለውም መላ መሻት ይፈልጋል። እነዚህን ማስተካከል ለወደፊቱ  ብዙ ነገሮችን  ያቃልልናል።
በአገራችን በአጠቃላይ ጠብና ቅራኔዎችን እንዴት መቀነስ ይቻላል ብለው ያስባሉ?
ለኔ ጠላታችን ድንቁርና ነው። ችግርና ረሃብ ነው። እነዚህን ነገሮች እንዴት እንዋጋቸው ብለን፣ አስተሳሰባችንን አመለካከታችንን እነሱ ላይ ብናደርግ፣ ብዙ የአገር ችግር ይቃለል ነበር። ይሄ ደግሞ መሆን የሚችለው መሪ ሲኖር ነው። አሁን ያለው አካሄድ ግን መሪ እንዳይኖረን የሚያደርግ ነው። ለኔ ፍልስፍናውም ስነ ልቦናውም በራሳችን ልክ የተሰራ አይደለም። ለኛ የሚያስፈልገን ዲሞክራሲ ምን ዓይነት ነው? ቁጭ ብለን ተነጋግረን መወሰን አለብን። የሌላውን ኮፒ አድርገን አምጥተን ሞክረናል ግን ውጤታማ አልሆነም። በኛ ልክ ምኞታችንን ማስቀመጥ አለብን። የቅደም ተከተል ጉዳይ ነው ባልልም፣ በመጀመሪያ የኢኮኖሚ ችግራችንን መፍታት መቻል አለብን። ዲሞክራሲው በራሱ ጊዜ ተያይዞ ይመጣል። ኢኮኖሚ ሲዳብር ብልፅግና ሲመጣ፣ ግጭት በራሱ ጊዜ እየከሰመ እየመነመነ ይመጣል። ከማርክሲዝም በኋላ የትምህርት ሥርዓታችንም ሆነ ሥርዓተ መንግሥታችን ግራ የተጋባ ሆኗል። ግራ የተጋባ አካሄድና ውቅረ አዕምሮ (ማይንድ ሴት) ውስጥ ነው ያለነው። ያ መሆኑን ደግሞ መረዳት አቅቶናል። ሁሉም ስለ ሥልጣን ነው የሚያወራው ግን ወንበሩ አንድ ነው። ለስንት ሰው ነው የሚበቃው? በተራ እንቀመጥበት ስንል በየስንት ደቂቃ ነው የምንቀያየረው? በተለይ ተማርኩ ባዩ ብዙ አማራጮችን ማየት አለበት። እኔ ሁልጊዜ የስዊዘርላንድን ምሳሌ ነው የማነሳው። እነሱም እንደኛ እልኸኞች ናቸው። የተራራ ሕዝቦች ናቸው። ነገር ግን ከኛ የተሻለ ኢኮኖሚ ስለነበራቸው አገረ ግዛታቸውን (በኛ ክልል) አበዙ። 3 ሺህ አስተዳደሮች አሏቸው፤ ሶስት ቋንቋ አላቸው። ነገር ግን ዛሬም ድረስ በማንኛውም ጉዳይ በአመት ሁለት ሶስቴ ሕዝበ ውሳኔ ያደርጋሉ። ይሄን የሚያደርጉት ሀብታም ስለሆኑ ነው። እኛ ይሄን ለማድረግ አቅማችን አይፈቅድልንም። ነገር ግን ከነሱ የምንማረው ብዙ ነገር አለ።
የክልል አከፋፈል የመሪ አመጣጥና አካሄድ፣ የቋንቋ አጠቃቀም… እነዚህንና መሰል ነገሮችን መማር እንችላለን። እያፈረስን መገንባት ቆሞ ባለው ላይ መገንባቱ የተሻለ ነው። አሁን ያለነው አዙሪት ውስጥ ነን። ከዚህ አዙሪት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መውጣት አለብን። እልሃችንን መቀነስ ይገባናል:: ለኔ የችግሮች ሁሉ ምንጭ ግን ድንቁርናና ረሃብ ናቸው። ይሄን መረዳት አለብን።
ህወኃትና ብልፅግናን የማሸማገል ሂደት ላይ ናችሁ… ?
ለማስታረቅ ሳይሆን ለማቀራረብ ነው እየጣርን ያለነው። "ተው ተነጋገሩ" ነው እያልን ያለነው። እንዴት እንነጋገር የሚለው የነሱ ስራ ነው።    
እንዴት ነው ተስፋ አለው?
ቢያንስ አንነጋገርም ብሎ በር የዘጋብን የለም። ሁለቱም ለመነጋገር ፍላጎት አላቸው። ስለዚህ መንገድ ጀምሯል ማለት ነው። ሁሌም መጣላት በጣም ቀላል ነው፤ ፈታኙ በሰላም መኖር ነው። ከራስ ጋር በሰላም መኖር ራሱ ፈታኝ ነው። ከራስ ጋር መጣላት ቀላል ነው። እኛ እያልን ያለነው ከጠብና ቅራኔ ውጡና ተነጋገሩ ነው። ከዚያ በኋላ ያለው የእነሱ ድርሻ ነው። እኛ “ተው አትጣሉ፤ ተነጋገሩ” ነው  የምንለው። ይሄን ማድረጋችን ክፋት አይደለም። ክፋት ካልሆነ ደግሞ ሂደቱ ሕዝባዊ ንቅናቄ እንዲሆን እንፈልጋለን።  መታወቅ ያለበት እኛ ፖለቲከኞች አይደለንም።
አንዳንዶች ችግሩ የፖለቲካ ነው፤ ፖለቲካ ደግሞ በሽምግልና ሊታረቅ አይችልም ይላሉ?
አዎ ይሄን ሲሉ እሰማለሁ። እኛ ግን የፖለቲካን ልዩነት አይደለም የምናሸማግለው። እኛ የምንለው "ሰው አይሙት፤ ሰላም ይስፈን፤ ከሰላም በመለስ ችግራችሁን ፍቱ” ነው። ሥራችን የሚቻቻሉበትን መንገድ ማመላከት ነው። “120 ሚሊዮን ሕዝብ እንዳይጎዳ ምን እናድርግ ብላችሁ አስቡ ነው” ያልናቸው።
የሽምግልና ባህል በአገራችን ያጣውን ክብር መልሶ እያገኘ ነው ማለት ይቻላል?
በአገር ሽምግልናም ሆነ በሃይማኖት አማካኝነት ብዙ የተሻገርናቸው ችግሮች አሉ። በዚህ እሴት ብዙ ችግሮችን ተሻግረናል። እኛም ለምን በአገር ደረጃ የሽምግልና እሴታችንን አንጠቀምበትም ብለን ነው የተሰባሰብነው። በየአካባቢው ከፍርድ ቤቶችም በላይ ሽምግልናችን ነው ብዙ ችግሮችን እያቃለለ ያለው። ስለዚህ ይሄን እሴታችንን የአገርን ችግር ለመፍቻ ማዋል ጠቃሚ ነው። ይሄ እሴት ባይኖረን እኮ በየቦታው ደም አፋሳሽ ጦርነቶች ይከሰቱ ነበር። ነገር ግን በየቦታው ያሉ የሽምግልና እሴቶች ሚና ቀላል አልነበረም። ይሄን በቅጡ ማጤን ይገባናል።
በጀመራችሁት የሽምግልና ሂደት ውስጥ ሕዝቡ ሊገነዘበው የሚገባው ነገር ምንድን ነው ይላሉ?
ሰው ሁሉ ከራሱ ጋር መታረቅን ማሰብ አለበት። ንዴትና እልህ ቀውስን ነው የሚፈጥረው። ስለዚህ ሁላችንም በጥቂቱ ከራሳችን ጋር ሱባዔ መግባት ያስፈልገናል። ባለን ነገር ተመስገን ማለትን ከለመድን ፈጣሪም ይረዳናል። ከኮሮና በኋላ የኢትዮጵያውያን ልብ ትንሽ መለሳለስና መተሳሰብ ጀምሯል። በዚህ ላይ የበለጠ መስራት፣ ይሄን ስነ ልቦና የበለጠ ማጎልበት አለብን።
ከኮሮና በፊት የነበረው ሁኔታ ፈጽሞ ተመልሶ መምጣት የለበትም፤ እንዳይመጣ ተግተን መስራት ይገባናል። አሁን ያለው ሩህሩህነት የበለጠ ማደግና መበልፀግ አለበት። ከዚህ በኋላ ሽምግልናው ተሳክቷል፤ የሚጠበቅብን የፖለቲካ ሀይሎቹ ተነጋግረው እንዲስማሙ መፀለይ ነው። እንደ ማህበረሰብ፤ አሉታዊ ነገሮችንና እሳቤዎች እየቀነስን፣ አዎንታዊ ነገሮችንና እሳቤዎችን ማጎልበት ይኖርብናል። ልክ ዛፍ ለመትከል ንቅናቄ እንደፈጠርነው ሁሉ ለበጎ እሳቤም ሕዝባዊ ንቅናቄ መፍጠር አለብን። ሽማግሌዎችም ከጦርነት ሰላም እንደሚሻል ሁሌም መስበክ አለባቸው። የሃይማኖት አባቶች ይሄን ለመስበክ የሚያስችል ንቅናቄ ቢፈጥሩ መልካም ነው። ትምህርት ቋሚ መሆን አለበት። ባለፉት 30 እና 40 አመታት የታገልነውና የሰበክነው ስለ መብት ነው። አሁን ደግሞ ስለ ግዴታ ማውራት መጀመር አለብን። መብትና ግዴታን ማመጣጠን ይኖርብናል፡፡
የትምህርት ሥርዓታችንም፣ የማህበረሰብ ንቅናቄዎቻችንም በዚህ ላይ ቢያተኩሩ ጥሩ ለውጥ ልናመጣ እንችላለን። መገናኛ ብዙኃንም በዚህ ንቅናቄ ላይ ትልቅ ሚና መጫወት አለባቸው። ከአሉታዊ እሳቤ ወደ አዎንታዊ እሳቤ የሚደረገውን የሽግግር ንቅናቄ፣ መገናኛ ብዙኃን ትኩረት ሊሰጡት ይገባል።    


Read 3502 times