Saturday, 20 June 2020 12:52

“ቀለበታዊ የፀሃይ ግርዶሽ” ለ6 ሰዓታት በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ይታያል

Written by 
Rate this item
(6 votes)

  • ከጠዋቱ 3 ሰዓት ከ45 ላይ ለ38 ሴኮንድ  ጨለማ ይሆናል
         • በማያን የቀን አቆጣጠር “የዓለም ፍፃሜ” ነው

               ነገ እሁድ ማለዳ ‹‹ቀለበታዊ የፀሃይ ግርዶሽ›› በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ለ6 ሰዓታት እንደሚታይ ተገለፀ፡፡ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋም እንደጠቆመው፤ መሰል ክስተት በድጋሚ የሚያጋጥመው ከ18 ዓመታት በኋላ ሲሆን ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ የሚኖረው ደግሞ ከ146 ዓመታት በኋላ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፤ ነገ ሰኔ 14  ከምዕራብ እስከ ሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ ቀለበታዊ የፀሀይ ግርዶሽ እንደሚከሰት ያስታወቀው ከወራት በፊት ነበር፡፡ በተለይ ላሊበላ አካባቢ ግርዶሹ ከማለዳው 12 ሰዓት ከ45 ጀምሮ እስከ 6 ሰዓት ከ33 ድረስ እንደሚቆይ የተገለፀ ሲሆን፤ ግርዶሹ ለስድስት ሰዓታት ይቆያል ተብሏል። ዋናው ቀለበታዊ ግርዶሽ የሚከሰትበትና ቀኑ የሚጨልምበት ሰዓት በዕለቱ ከጠዋቱ 3፡45 ላይ እንደሚሆንና ለ38 ሰከንድ እንደሚቆይም ተነግሯል፡፡
ቀለበታዊ የፀሃይ ግርዶሽ ከላሊበላ ባሻገር ወለጋ፣ ከፊል ጎጃምና ጎንደርም የሚታይ ሲሆን ከኢትዮጵያ ውጭ በደቡብ ሱዳን፤ በኤርትራ፤ በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፤ በየመን፤ በኦማን፤ በፓኪስታን፤ በህንድ፤ በቲቤትና በቻይናም ይታያል ተብሎም ይጠበቃል፡፡
መጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ፣ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራርያ፤ ‹‹ጨረቃ ፀሐይን ሙሉ ለሙሉ መሸፈን ሳትችል ስትቀር፣ በጨረቃ ጠርዝ ዙሪያ ቀለበት ሠርታ ፀሐይ የምትታየን ከሆነ “ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ” (annular solar eclipse) ይባላል፡፡ ይህም ሊሆን የሚችለው ጨረቃ ከመሬት እርቃ ባለችበትና “አፖጊ” (apogee) ተብሎ በሚጠራው ርቀት ላይ ስትሆን ነው፡፡ በዚህ ወቅት የጨረቃ ጥቁሩ ጥላ (ጸሊም ጽላሎት) መሬት ላይ ላያርፍ ይችላል›› ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የነገውን ‹‹ቀለበታዊ የፀሃይ ግርዶሽ›› ከዓለም ፍፃሜ ጋር የሚያገናኙ ዘገባዎችም እየተሰራጩ ነው፡፡ በማያ ስልጣኔ ስለ ‹‹የዓለም መጨረሻ›› የተነገረው ትንቢት የሚፈፀመው በዚሁ ቀን (ጁን 21 ቀን 2020፤ ወይም ሰኔ 14 ቀን 2012 ዓ.ም ላይ) መሆኑን የእንግሊዙ ዘ ኤክስፕረስ ዘግቧል፡፡  የማያን የቀን መቁጠሪያ ከ5,126 ዓመታት በዚሁ ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ በሚከሰትበት ወቅት እንደሚጠናቀቅ ተመራማሪዎች መግለፃቸውን የጠቀሰው ዘ ኤክስፕረስ፤ ቀደም ሲል ዲሴምበር 21 ቀን 2012 እ.ኤ.አ የዓለም ፍፃሜ ይሆናል ተብሎ ሳይከሰት መቅረቱንም አስታውሷል፡፡
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፤ ክስተቱን ላቅ ያለ ሥነ ፈለካዊና ሀገር በቀል ዕውቀትን ከቴክኖሎጂ ጋር የሚያገናኝ ታሪካዊ አጋጣሚ ሲል ገልፆታል፡፡ በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በ1545 ዓ.ም፣ ሕዳር 5 ቀን 1661 ዓ.ም፣ መጋቢት 24 ቀን 1672 ዓ.ም እንዲሁም በ1720 ዓ.ም ፀሐይ ሙሉ በሙሉ ተጋርዳ እንደነበር ያስታወሰው ኢንስቲትዩቱ፤ ይህን ታሪካዊ ክስተት ሕዝብ ሳይደናገጥ በዕድለኛነት ስሜት በነጻነት፣ በንቃትና በጥንቃቄ ሊከታተለው እንደሚገባም መክሯል፡፡ ክስተቱ በተፈጥሮ ላይ ምንም ተፅዕኖ እንደማይኖረውና ምናልባትም የአየር ንብረት ለውጥ ሊኖር እንደሚችልም ጠቁሟል፡፡ ተማሪዎች፣ ተመራማሪዎችና ማኅበረሰቡ ክስተቱ ሊያመልጣቸው አይገባም ያለው ተቋሙ፤ በባዶ ዓይን ማየት ግን ለአደጋ በእጅጉ እንደሚያጋልጥ አስጠንቅቋል፡፡


Read 13767 times Last modified on Sunday, 21 June 2020 09:13