Saturday, 20 June 2020 12:41

የፈጠራ ስብሰባ

Written by  ከሞገስ ተከተል
Rate this item
(2 votes)

   ዩኒቨርሲቲ ከተዘጋ ጀምሮ እቤት ውስጥ ተቀርቅሬ ሰነበትኩ። የመቱ አንደኛ አመት ተማሪ የሆነው  ጓደኛዬ ወርቃለማሁም እንደዚሁ። ከወርቃለማሁ ጋር የምንወያይበት ሀሳብ ከተፈጠረ ቴሌግራም እንለዋወጣለን። ከዚህ ውጪ የምንገናኝበት ሌላ ዘዴ የለንም። ታዲያ! በእነዚህ ቀናት ውስጥ፣ባለሁበት ክፍል ሆኜ የማላሰላስለው ነገር የለም።
አንዳንድ ጊዜ ግራ ሲገባኝ “ኮረና እግዜር ይይልህ” እላለሁ። ሌላ ጊዜ ደግሞ  “ይህ ነገር ለበጎ ሊሆን ይችላል እኮ” በማለት እፅናናለሁ። አንድ ቀን ብቻዬን ቁጭ ብዬ ያለውን ሁኔታ ሳወጣ ሳወርድ፣ከአስራ አምስት ቀን በፊት ብሐ አካባቢ ባለው  የሸማቾች ማህበር ዳቦ መሸጫ ቅርንጫፍ ሃላፊ በሆነችውና በዳቦ ሸማቹ መካከል የተፈጠረው እሰጣ ገባ ትዝ አለኝ። የዳቦ መሸጫ ሹሟ ወ/ሮ ቀለሟ፤ ዳቦ ለመግዛት ለተሰለፉት የብሐ ሰፈር ነዋሪዎች ያሰማችው ቁጣ ያዘለ ንግግር ቁጭ ያልኩበት  እንዳለ ከፊቴ መጣ። “እናንተ ሰዎች! ዳቦ የለም አልተባላችሁም፤ደግሞም ስንዴ ከውጪ ሐገር በመርከብ ተጭኖ የውጪ ምንዛሪ እየተከፈለ  እንደሚመጣ አታውቁም! እንደገናስ ዳቦ ያለመኖሩን ለመግለፅ፣ እንደ እድራችሁ ጡሩንበኛ መንደራችሁ ድረስ እየመጣን መለፈፍ አለብን! በተጨምሪም ዳቦ በሌለበት ሸማቾች ሱቅ ድረስ እየመጡ ተጠጋግቶ መሰለፍ ኮረናን ያስፋፋል ስትባሉ አትሰሙም! ለመሆኑ መቼ ነው የሚነገራችሁን የምታዳምጡት” እያለች ባለበት ሁኔታ አንዷ በፊቷም በጀርባዋም ሁለት ሕፃናት  ያዘለችና ትዕግስቷ የተሟጠጠ ሰልፈኛ፤ “ወሮ ቀለሟ! ወሮ ቀለሟ!“ ስትል ተጣራች።
“አቤት”
“አንችም ስሚ! የምትይው ሁሉ አይገባንም። ለኛ ዳቦ ማጣትም ሆነ የኮረና መኖር ያው ነው፣ ሁለቱም የሞት ጎዳናዎች  ናቸው!” ብላ አንድ ዳቦ እንኳን ሳትሰንቅ ወደ ቤቷ ተመለሰች።
“እንዴት በዚህ በኮረና ወቅት፣ ሕፃን ያዘሉ ሴቶች ዳቦ ፍለጋ የሸማቾች ሱቅ ተደግፈው፣ ዳቦ ሳይዙ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ! በዚህስ ወቅት ማን ነው በየቤቱ ያሉትን ብዙ ሕፃናት የሚያሳድጉ ሴቶችን የሚታደገው! “ የሚለው ሀሳብ፣ ደግሞ ደጋግሞ በአዕምሮዬ ውስጥ አቃጨለብኝ።
እንደገና ደግሞ ትዝታዬ ወደ ሌላ ነገር ተሸጋገረ። አንድ ጋዜጠኛ ከብሐ ሰፈር መጥቶ በግብፅና በአባይ ጉዳይ ላይ የመንደሩን ነዋሪዎች ከጠየቀ በኋላ ባንድ ሬዲዮ  ጣቢያ ያስተላለፈው የመንደራችን ነዋሪዎች አስተያየት ትዝ አለኝ።
“አባይ ላንተ ወይም ላንቺ ምንድነው?”
አባይ ለኔ “መብራቴ፤ከማገዶ የሚያወጣኝ አሻራዬ፤ የእናቶችን በእንጨት ሸከማ የጎበጠ ወገብ  የሚያድን መድሐኒት፤ የሕይወት ስሬ፤ ወዘተ” እየተባለ የተሰጠው መልስ ስሜቴን ሰረሰረው።
በአባይ ጉዳይ የተማረውም ያልተማረውም፣ የወንዱም የሴቱም፣ የፖለቲከኛውም ከፖለቲካ ውጪ ያለውም፣ የፅንፈኛውም ከፅንፍ ውጭ ያለውም፣ የእስላሙም የክርስቲያኑም፣ የልጁም የሽማግሌውም፣ ሀሳብ ተመሳሳይነት አለው። የሁሉም አመለካከት የበሰለ ነው።”በአባይ እኛም እንጠቀም፤ ግብፅም ትጠቀም “ የሚል መንፈስ ያለው ነው።
“እንዴት ከራሳቸው አገር ነዋሪ ውጭ ለሌላ የሚያስቡ የአገሬ ልጆችን በዚህ በኮረና ወቅት የዳቦ እጥረት ያጋጥማቸው!” የሚል ሀሳብ እንደገና መጣና ጭንቅላቴን ሰቅዞ ያዘው። በዚህ አይነት አንድ ቀን ሳዝን ለምን እንዳዘንኩ ሳሰላስል፤ሌላ ቀን ደግሞ ተስፋ ስጭር፣ ለምን ተስፋ እንደጫርኩ እያሰላሰልኩ እያለ ወርቃለማሁ ደውሎ “ይባስ! ይባስ”ብሎ ጠራኝ። ቀጠለናም፤
“ኮረና ካለምም ከኢትዮጵያም ይጠፋል!  እኔ አጠፋዋለሁ” አለ።
“ምን ተፈጠረ?” ብዬ ጠየቅኩት ።
“ለማንኛውም የተከበሩ ወልደሃና መዝጊያው፤ ለመንደራችን ነዋሪዎች፣ በብሐ ልጆች ቴሌግራም ቻናል የላኩትን ማሳሰቢያ ልኬልሀለሁ፤ ተመልከተው፤ በተባለው ቀን ተገኝተን የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን” ብሎ ስልኩን ዘጋው።
አቶ ወልደሃና መዝጊያው፤ በብሐ መንደር አካባቢ ለብዙ ጊዜ የኖሩ፣ በዕቁብና በዕድር ዳኝነት መንደሩን እስካሁን ድረስ እያገለገሉ ያሉ በመሆናቸው የሠፈሩ ወጣት”የተከበሩ” እያለ ይጠራቸዋል።
እናም! የተከበሩ አቶ ወልደሃና መዝጊያው የላኩት ቴሌግራም እንዲህ ይላል፡- “ለውድ የብሐ ሰፈር ነዋሪዎች (በተለይ ለወጣቶች)፣ በቅድሚያ ቸሩ እግዚያብሔር  ይህንን መጥፎ ጊዜ በጥበብ እንድትሻገሩት መንገዱንና ዘዴውን እንዲያሳያችሁ እመኝላችኋለሁ። በመቀጠልም ጠቅላይ ሚኒሰቴር አብይ፣ በዚህ በኮረና ወቅት ሁሉም ኢትዮጵያዊ  እቤቱ ተቀምጦ አዕምሮውን እንዲያሰራና እምቅ አቅሙን እንዲመረምር ያስተላለፉትን መልዕክት ለማስታወስ እወዳለሁ። በመሆኑም የዚህ መንደር ነዋሪዎች፣ በቤታችን ለሃያ ስምንት ቀን እምቅ አቅማችንን እየመረመርን ተቀምጠን፣ ይኸው አቅማችን የሰጠንን የፈጠራ ሐሳብ ይዘን፣ የተሻለውን በመለየት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመስከረም ወር በጠሩት የፈጠራ ውድድር ለመቅረብ ፣ምልኬ ፍርጎ ከፍ ብሎ በሚገኘው ባዶ ሜዳ ላይ ሰኔ 1 ቀን 2012 ዓ. ም ከጧቱ 2:30 እንድትገኙ በትህትና አሳስባለሁ “አክባሪያችሁ ወልደሃና መዝጊያው የሚል ነው።
የጥራው ሀሳብ መሰጠኝ። እኔም የተከበሩ በጠሩት ስብሰባ ላይ ተገኝቼ ለውድድር የሚቀርብ የፈጠራ ሀሳብ ለማቅረብና ሰሞኑን ከወጠሩኝ ሐሳቦች ለመገላገል ለራሴ ቃል ገባሁ። “ስንዴን በልዩ ሁኔታ አምርቼ ዳቦን በሸማቾች ሱቅ አጥለቀልቀዋለሁ “ አልኩ።
የተከበሩ አቶ ወልደሃና መዝጊያው የጠሩት የስብሰባ ቀን እየተቃረበ ሲመጣ ፣ሰሞኑን ከሚሰማኝ ቁዘማ ጋር የተገናኙ አንዳንድ ሐሳቦች እንደ ጧት ጀንበር ብልጭ ማለት ጀመሩ። እነዚህ  ሐሳቦች ቀስ በቀስ እየጋሉ አዲስ የፈጠራ ሐሳብ በአዕምሮዬ ላይ አበራብኝና ይህንን ሐሳብ አውጥቶ ለመገላገል የስብሰባውን ቀን መናፈቅ ጀመርኩ። የስብሰባው ቀን ደረሰ።
የተከበሩ በጠሩት ስብሰባ የሰፈሩ ወጣቶች ልቅም ብለው ተገኝተዋል። በዚህ አመት ወደ ዩኒቨርሲቲ ከገቡት ውስጥ እኔና ጓደኛዬ ወርቅአለማሁን ግን ማንም የቀደመን የለም። ከወጣቶቹ በተጨማሪ አልፎ አልፎ ተለቅ ያሉ ሰዎች እዚያም እዚያም ይታያሉ። የተከበሩ አቶ ወልደሃና መዝጊያው ድምፃቸውን ካለሳለሱ በኋላ “ብሖች አንኳን ደህና መጣችሁ” አሉ። ቀጠሉናም “ጊዜው አስከፊ ስለሆነ ተራርቃችሁ እንድትቀመጡ በትህትና እጠይቃለሁ” አሉ። ተሰብሳቢውም በተጠየቀው መሠረት አደረገ። “እንግዲህ በዚህ ቀን እንድትሰበሰቡ የተደረገው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ላቀረቡት ጥሪ፣ የሠፈራችንን ወጣት (በተለይ የዩኒቨርስቲ ተማሪው) ባለፉት ሃያ ስምንት ቀናቶች ውስጥ ሲያብሰለስል የከረመውን ሀሳብ ለማድመጥና ጥሩ የሆነውን መርጠን በብሐ ሠፈር ስም፣ በመስከረም ወር ለሚደረገው የፈጠራ ውድድር ለማቅረብ ነው” በማለት የስብሰባውን አላማ ገለፁ።
እኔም ወዲያዉኑ “በዚህ አይነት ከእኛ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሚጠበቀው አስተዋጽኦ ብዙና የጠለቀ ነው” አልኩ በሆዴ።
ቀጠሉና “ውድ የሠፈሬ ሰዎች! አንድ ሰው አዲስ ነገር ከሰራ (ከፈጠረ ማለቴ ነው) ስሙ ለብዙ ጊዜ ይጠራል። ስሙ እንኳን ቢረሳም ሠፈሩን ያስጠራል። ወይም የሠራው ሥራ እስከ ዘለአለም ሲታወስና ሲነገር ይቆያል። እግዚአብሔርም ይህን ሰው ወደ ገሀነም አይጥለውም” አሉ።
“ለምሳሌ ከእናንተ መካከል ማንም ሃምሣ ክፍልን የማያውቅ አለ ብዬ አላምንም። አለ እንዴ?” ብለው ጠየቁ። ሁሉም “ማንም የለም “ ብሎ መለሰ።
ቀጥለውም “ሀምሣ ክፍል ባንድ ሰው ከስልሳ አመት በፊት የተሰራ የጠባብ ቤቶች ቅጥልጥል ነው። በዚያን ወቅት ብዙ መጠልያ ያጡ ድሖች በወር አንድ ብር ካምሣ እየከፈሉ ቤቶቹ በደርግ እስኪወረሱ ድረስ ይኖሩባቸው ነበር። አሁን ማንም ሰው ፒያሳ ላይ ቆሞ ወይም አዲሱ ገበያ ላይ ሆኖ ፣አምሳ ክፍል የት ነው ብሎ ቢጠይቅ ማንም ያሳየዋል። ሌላ ምሳሌ ልስጣችሁ ፣ከዛሬ አርባ አመት በፊት አቶ ስለወንድም ባንቻው የሚባሉ፣ በወቅቱ የነበረውን ነዋሪ የጠላ ፍቅር ያወቁ፣ ጠላን በተናጠል በጣሳ ከመጠጣት ይልቅ ተሰብስቦ በገንቦ እያስቀመጡ መጠጣት የነዋሪው ዝንባሌ መሆኑን የተረዱ፣ ከሌሎች የተለየ አዲስ ጠላ ጠመቁ። ስሙንም “ሾሊያ ነጭ ጠላ “ብለው ከጥላሁን ገሠሠ ተወዳጅ ዘፈን ጋር እንዲቀናጅ አደረጉት። ታዲያ! ይኸ ጠላ የሚሸጥበት አካባቢ እስካሁን በዚህ ስሙ እንደታወቀ ይገኛል። ከዚህም የተነሳ አንድ የአካባቢያችን ነዋሪ ቦሌ አየር መንገድ ወይም አየር ጤና ሆኖ አንድ ታክሲን፣ ሾሌ ነጭ ጠላ ውሰደኝ ቢለው፣ ያለ ምንም ችግር ቦታው ድረስ ያደርሰዋል።
የተከበሩ የስብሰባውን አላማ አስመልክቶ ባቀረቡት ምሳሌ፣ አንዳንድ ሰዎች ግራ የተጋቡ ይመስላል። በዚህ ጊዜ አንድ ወጣት ድንገት ብድግ አለና “ሃምሣ ክፍል እና ሾሌ ነጭ ጠላ እንዴት ከፈጠራ ሥራ ጋር ይገናኛሉ?” አለ። ቀጥሎም አንድ በዕድሜያቸው ፀና ያሉ ሰው ከመቀመጫቸው ተነስተው “ለምን ግልፅ በሆነ መንገድ ወደ ቁም ነገሩ አንገባም “ አሉ።
“ወደ ቁም ነገሩ ስንገባ፥ ፈጠራ አነሰ ሲባል የሠፈር ስም ሲበዛ፣ የሐገር ስም ሊያስጠራ ስለሚያስችል በነዚያ ሃያ ስምንት ቀናቶች ውስጥ ስታውጠነጥኑ የቆያችሁትን የፈጠራ ሀሳቦች ተራ በተራ በማቅረብ፣ አገራችሁን ወይም የሠፈራችሁን ስም ማስጠራት ትችላላችሁ” ብለው ንግግራቸውን ዘጉ።
ተሰብሳቢው ለጊዜው ፀጥ አለ። ማንም እጁን አውጥቶ በቅድሚያ ለመናገር የሚደፍር ጠፋ።
“ተናገሩ እንጂ! ዝም ተናገሩ እንጂ!” ዝም፥
እንግዲህ የሚናገር ከጠፋ አንድ ባንድ ስማችሁን እየጠራሁ እንድትናገሩ ላደርግ ነው” አሉና የተከበሩ ፊት ፊታችንን ማየት ጀመሩ።
እኔ ይህን ጊዜ በአዕምሮዬ ሲያቃጭል የነበረውን የፈጠራ ሀሳብ ለመዘርገፍ ቀና አልኩ። ትንፋሼን ወደ ውስጥ ሳብ ሳብ አደረኩና፣ ሰሞኑን ውስጤን ሲያወዛውዘው፣ ነፍሴንም ጭምር ሲያስጨንቃት የነበረውን ሐሳብ ለመግለፅ እጄን አወጣሁ። የተከበሩ “ጎበዝ ልጅ፣ ቀጥል” አሉኝ።
“ይባስ እባላለሁ፥ የመቱ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነኝ። እኔ ለውድድር ማቅረብ የፈለኩት “የስንዴ ዛፍ መፍጠርን” ይመለከታል።
ይህም ፈጠራ ስንዴን ከእርሻ ላይ ሳይሆን ጓሮ ከበቀለ ዛፍ ላይ እየለመለሙ (ወይም እያጨዱ ልበለው) ለመሰበሰብ የሚያስችል ስልት ነው። ይህ ዘዴ ስንዴን ካንድ ዛፍ በየሁለት ቀኑ ሃምሳ ኪሎ ለማምረት እንዲቻል  ታሳቢ ያደረገ ነው” አልኩ። ቀጠልኩና “ይህ የፈጠራ ሀሳብ እውን ከሆነ እያንዳንዱ ገበሬ ወይም ከገበሬ ውጭ ያለ ሰው፣ ሰፊ መሬት፤ የማረሻ በሬ ወይም ሰው ሰራሽ ማዳበርያ ሳያስፈልገው በጓሮው የስንዴ ዛፍ ተክሎ ስንዴን እንደ ልብ መልቀም ይችላል። በተጨማሪም ዛፉ የመስኖ ውሃ አያስፈልገውም። የጣሳ ውሃ እያጠጡ የፈለጉትን ያህል ሰብል ማፈስ ነው” ብዬ ፊቴን ወደ ተሰብሳቢው ቀና አደረኩ።
ተሰብሳቢው ግራ ተጋብቷል። ግማሹ አንገቱን ጎንበስ አድርጎ ማሽሟጠጥ የጀመረ ይመስላል። ሌላው ለቁም ነገር ሳይሆን ለቀልድ የመጣ ነው የመሰለው። በዚህን ጊዜ አንድ የሰፈሩ የለሊት የላዳ ታክሲዎች ጠባቂ ድንገት ተነሳና “እኛኮ እዚህ የመጣነው ስብሰባው ኮረናን ለመታደግ የሚያስችል ቁም ነገር የሚገኝበት መስሎን ነው። ወንድሞቼ! እህቶቼ! እስቲ አስቡት! እንዴት ስንዴ በዛፍ ላይ በጓሮ ይበቅላል? እባካችሁ አታጨናብሩን “ ብሎ ተቀመጠ።
ወዲያው “ይቻላል! ስንዴን ከስንዴ ዛፍ ለማብቀል እንዴት እንደሚቻል ሁሉም የፈጠራ ሀሳቡን ከገለፀ በኋላ ዕድሉ ከተሰጠኝ በስተመጨረሻ አብራራለሁ” ብዬ ተቀመጥኩ።
ቀጥለውም “እስቲ የተለየ ሀሳብ ያላችሁ እጃችሁን አውጡ” አሉ።  ጓደኛዬ ወርቃለማሁ ተሽቀዳድሞ  እጁን አወጣ። “ጎሽ ቀጥል”
“ዕድሉ ሰለተሰጠኝ አመሰግናለሁ፤ ወርቃለማሁ እባላለሁ። የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ አንደኛ አመት ተማሪ ነኝ። እኔ ለመፍጠር ያሰብኩት የኮረና አጥፊ ቦንብ ወይም በእንግሊዘኛው Covid 19 bomber የሚባል በጣም ትንሽ አንቴና መሰል  ዕቃ ነው። ይህንን ዕቃ ማንኛውም ሰው እንደ አርማ በደረቱ ላይ ለጥፎት የትም ቦታ መንቀሳቀስ ይችላል። ዕቃው ወይም አንቴናው ኮረናን ብቻ (እደግመዋለሁ ኮረናን ብቻ) ለይቶ ለማየት እንዲችል ፕሮግራም ሆኖ የተሰራ ካሜራ የያዘና በካሜራው ውስጥ የኮረና ምስል እንደታየ አስተካክሎ ወደ ታየው ኮረና ጨረር ልኮ ፥የታየውን ሁሉ እምሽክ የሚያደርግ ነው” ስል ተሰብሳቢው እንዳለ በሳቅ አስካካ።
አንድ በዕድሜ ጠና ያሉ ሰው ንዴት በተላበሰ መልክ ብድግ ብለው፤ “እኔ ወደዚህ አዳራሽ የመጣሁት አንድም የተከበሩን በማመን ቁም ነገር አገኛለሁ ብዬ፣ ሁለትም ኮረና በቤት ውስጥ አምቆ ላስቀረን በዕድሜ ለገፋን አዛውንቶች በአቶ ወልደሃና አስተባባሪነት፣ በመንደራችን ወጣቶች ተሳታፊነት የምግብ አሰባሰብ ፕሮግራም ይቀየሳል የሚል እሳቤ ኖሮኝ ነው። አሁን ግን የተያዘው ነገር ሁሉ ፌዝ መሆኑ ታየኝ። እንዴት በዚህ ክፉ የኮረና ጊዜ የሰው ልጅ በመሰሉ ያፌዛል” ብለው ሊሔዱ ሲሉ ሌላውም ተሰብሳቢ ከመቀመጫው ብድግ ብሎ፣ሰውዬውን በመከተል ከስብሰባው ለመውጣት አቆበቆበ።
ይህን  ጊዜ የተከበሩ ድንገት ብድግ አሉና “ሠፈራችን ውስጥ ራዕይ መታየት ሲጀምርና ተስፋ ሲፈነጥቅ፣ የት ነው የምትሸሹት! “ በማለት ተሰብሳቢውን እንዲቀመጥ አዘዙት። በታዘዘው መሠረት ተሰብሳቢው ተቀመጠ። እንደገና ተሰብሳቢው ከተቀመጠበት ብድግ እንዲልና የሚያሰሙትን መፈክር እንዲቀበል አዘዙት። ተሰብሳቢው እንደታዘዘው መፈክሮቹን እየተቀበለ ካሰማ በኋላ በሰላም ወደ መኖሪያው ተመለሰ። የተከበሩ እየመሩ፣ ነዋሪውም እየተቀበለ  ያስተጋባቸው መፈክሮች የሚከተሉት ነበሩ።
ወጣቶቹ ያቀረቡት ራዕይ ባጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር መለወጥ ይጀምራል! በዚህም የተነሳ የብሐ መንደር ነዋሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት የፈጠራ ውድድር ተሸላሚ ይሆናል! የቀረቡት የፈጠራ ሀሳቦች ወደ ተግባር ሲለወጡ ካላየን ወጣቶቹን አስጎመጁን ብለን እንከሳቸዋለን! -- የሚል ነው።
መንደርተኛው መፈክሩን አሰምቶ ወደ ቤቱ ቢመለስም፣ እኔና ጓደኛዬ ግን ራዕያችንን ወደ ተግባር ለመለወጥ እስካሁን  ዳገት እየወጣን ነው። እግዚአብሔር ይርዳችሁ በሉን።


Read 1546 times