Wednesday, 24 June 2020 00:00

“ሰኔ ነግ በኔ!”

Written by  አዲሱ ዘገየ
Rate this item
(0 votes)

      ““ሰኔ ነግ በኔ!” እና “አተላ በሰኔ፣ ሁሉም ለኔ ለኔ!” ሲል ያልተማረው ገበሬ ከእጅ ወዳፍ በሆነ የለት ኑሮው በቤቱና ባካባቢው የሚገጥሙትን የማምረቻ መሣሪያ ውስንነቶች እንዲሁም ሰኔን ተከትለው የሚመጡ ተፈጥሯዊ ገጸ በረከቶች በትብብርና በጋራ ለመሙላት ያለውን ብርቱ ጥረት የሚያሳይ ነው፡፡--”
     
              ሰኔ አወዛጋቢ ወር ናት፤ በሌላ በኩል ሠኔ ተብላ ትጻፋለች፡፡ በተለይ ዕድሜ ጠገብ በሆኑ ጥቂት ያገሪቱ ቋንቋዎች አንጻር የሆሄያቱ መለዋወጥ የትርጉም ልዩነትን ይፈጥርና አወዛጋቢነቱ ያይላል፡፡ ኢትዮጵያዊ የወራት ስሞችን ምንነትና ኬትነት (የቋንቋ ዘር ግንድ ሐረግ) ያጠኑ የውጭ ሀገራትና የሀገሬው ባለሙያዎች አሉ፡፡ እነዚህ ተመራማሪዎች ሰኔ የምትለው ቃል ከየትኛው ቋንቋ እንደተፈጠረች ርግጡን ማወቅ ባለመቻላቸው የየራሳቸውን አስተያየት ያስቀምጣሉ፡፡ ከእነዚህ አንደኛው፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ሲሆኑ “ሰኔን የወለደው የግእዝ ቃል ሞቷል” ይላሉ፡፡ ግርማ አውግቸው (ዶ/ር) እና አህመድ ዘካሪያ (ረ/ፕ) ደግሞ ሰኔ ከግእዝ ቋንቋ የዘር ግንድ መወለዷ አልታይ ስላላቸው “ሰኔ የሚለው ስያሜ በኢትዮ-ሴማዊ ቋንቋዎች ቅሪት/ነባር ቃል እንጂ በግእዝ ተፈጥሮ ወደ ሌሎች የተዛመተ አይመስልም፡፡” ሲሉ ይደመድማሉ፡፡
የቃላት ዘርን ፈልጎ ምንነቷንና ኬትመጣነቷን ማጥናት ላንድ የሙያ ዘርፍ ብቻ የተተወ ሥራ አይደለም፤ ይህ ያልሆነበት ምክንያት ራሱን ችሎ የቆመ፣ ቁርጥ ያለ ወሰንና ድንበር ያለው ብቸኛ የሙያ ዘርፍ አለመኖሩ አንዱ ነው፡፡ ስለዚህ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች አንጻር ማጥናት ተገቢና አዋጭነቱ የማያጠራጥር ጉድለትን፣ የሚመላ ሂደት ሆኖ ይመረጣል፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢም ወራትን ለመተንተን ሲጀምር አንድም፣ በሀገሬው አሰያየም ሥርዓት አንጻር የሚሰጡትን ፍቺና ትርጉም መነሻ ያደረገ ማመሳከሪያ መስጠት በማለም ሲሆን፣ አንድም፣ ከወራቱ ስያሜ አልፎ ከለት ተለት ሕይወት ጋር ተጣምረው ጥንት የኖሩበትን፣ አሁን እየኖሩ ያሉበትን ወደፊት ሊኖሩ የሚችሉበትን ማኅበረ-ባህላዊ፣ ታሪካዊና ፍልስፍናዊ ግጥምጥሞሾች/ተቃርኖዎች ፍንጭ መስጠት ነው፡፡ አንድም፣ ወራትና የሥነ ከዋክብት ጥናት ብሔራዊ ወሰንን አልፈው በአህጉራዊና ዓለማቀፋዊ ደረጃ የሚሰሩ ሁሉን አቀፍ ሰዋዊ ጉዳዮች በመያዛቸው የተለያዩ መልክዓ ምድራዊ ወሰኖችን “እንደ አቅሚቲ” አስተሳስሮ ማሳየት ታልሟል፡፡ በመጨረሻም፣ ከሥነፍጥረታት ወገን ሆኖ የመፈላሰፍ ዝንባሌ፣ እንደ ሀገሯ ከምትጮኸው ወፍ አንስቶ ዓለምን በወፍ በረር ለማካለል የሚበጅ ሀሳባዊ ጉዞ ነው፡፡
ስለዚህ ያቅሚቲ የተሰኘው ሥራ ውሱን በመሆኑ በሌሎች ትብብርና ጥረት ሊሞላ የሚችል ነው፡፡ አንዱን ወር ከሌላው ጋር በማነጻጽርበት ጊዜ ወላጅና ልጅ፣ እናትና አባት፣ እትማማችና ወንድማማች፣ ተባዕታይና አንስታይ፣ ታላቅና ታናሽ፣ የበኩርና ማሰሻ ወዘተ ማዕረጋት ሥር ማስቀመጤ እኩያ አለመሆናቸውን፣ ዙሮ ገብ/ገጠምነታቸውን፣ ተወራራሽ ባህርያቸውን በመዘንጋት አይደለም:: አንዱን ከሌላው በማዕረግ የማበላለጥ ሳይሆን የወግና የትረካ ስልቴ ስለሆነብኝ ነው፡፡
ወራትን ስተነትን፣ ስፈክር ሰኔ ላይ ደረስኩ፡፡ ሰኔ እና ሠኔ፣ ሰኔ እና ሰኞ፣ ሠኔ እና ሰኞ በመንታ መልኮቻቸው የተከሰቱበት አጋጣሚ ላይ እኛም ተገኘን፡፡ ሰኔን ለሕይወት ቅርብ በሆኑ ማስረጃዎች ማመሳከርን መርጫለሁ፡፡ የሀገሬው የዕውቀት ዘርፍ የከዋክብትን ትንታኔ በፊደላት ይወስናል:: የፊደላት ግድፈት ለስህተት ይዳርጋል፡፡ የፈረንጅኛው የኮከብ ትንታኔ፣ ዕለተ ልደትን ቆጥሮ ይነሳል፤ የቁጥር ልዩነት “ስሙን ለሰው አወረሰው!” ብሎ ያስነቅፋል፡፡ ሰኔ እና ሰኞ በሀገሬው የአኗኗር መልክ የክፉ ገጠመኝና ክስተት አመላካቾች ናቸው ብዬ አላምንም::  መልካም ዕድልን ተከትለው የሚመጡ በጎ በረከቶች አሏቸው፡፡ ሰኔ እና ሰኞ “ኮከባችሁ ገጥሟል” እንደሚባልላቸው ጥንዶች (ባልና ሚስቶች) አልሚና ለሚ ሆነው እንዲኖሩ፤ አልያም “ኮከባችሁ አይገጥምም!” እንደሚባልላቸው ጥንዶች አጥፊና ጠፊ የሚኳኋኑበትን አጋጣሚ አመላካች ናቸው፡፡
“ሰኔ መቃጠሪያ ኅዳር  መገናኛ!” የሚለው ብሒል፣ በሀገሬ አብዛኛው አርሶ አደር ዘንድ ሁነኛ ትርጉም አለው፤ በተለይም ክረምትን ጠብቆ ለሚያርሰው ገበሬ፡፡ የሰኔ ወር በዋናነት የእርሻና የዘር ወር ናት፡፡ ሠኔ ለገበሬው የፈተና ወሩ ናት ማለት ይቻላል:: ሰነፉና ጎበዙ፣ ጠንካራውና ደካማው የሚለይባት ወር ናትና፡፡ ሰኔ መዝሪያ፣ ኅዳር ማጨጃ/መሰብሰቢያ ወራት ስለሆኑ የአርሶ አደሩ ማኅበረሰብ ወሳኝ ዓመታዊ ዕለተ ምጽዓቶችን በብዛት የያዙ ወራት ሁለቱ ናቸው፡፡ ኅዳርና ሰኔ ያንዲት ሳንቲም አንድ እና/ወይም ሁለት ገጽታ/ዎች ማሳያ ናቸው:: መቃጠሪያ እና መገናኛነታቸው የሁለቱን ዝምድና ያሳያል፡፡ ይኸውም ኅዳርና ሰኔ እትማማች ወራት መሆናቸውን ኅዳር 1 ቀን በሚብትበት ዕለት ሠኔ 1 ቀን መርጣ መባቷ፣ ያንድ ሳንቲም አንድ ገጽታነታቸው ማስረጃ ነው፡፡ እንዲሁም ሁለቱ ወራት ተመሳሳይ ሃይማኖታዊ ክብረበዓላትን እንዲሁም ሀገር በቀል የአምልኮ ልማዶችን መሣ ለመሣ የሚያከብሩ መሆናቸው ያንድነት መልካቸውን ያሳያል፡፡ የኅዳርና ሰኔ ወርኀዊ በዓላት በኩታ ገጠምነት ለመከበራቸው አብነት የሚሆኑ (የተለመዱ ወርኀዊ በዓላትን ትተን)  ኅዳር 6 እና ሰኔ 16፣ ኅዳርና ሰኔ 12፣ 21፣ 26 ተጠቃሾች ናቸው፡፡
የተጠቀሱ የበዓል ቀናት ሰኔ እና ኅዳር ባንዲት ሳንቲም ያሉ ሁለት ገጽታዎችን ያስቃኛሉ፡፡ ለአብነት ያህል ሰኔ 16 ቀን የስደት ኑሮ የተጀመረባት፣ ኅዳር 6 ቀን ከስደት መልስና “ዞሮ ዞሮ ከቤት…” የተባለላት ቀን ናት፡፡ ስደተኞቹም በቤተልሔም የተወለደው ሕፃኑ፣ እናቱና ወገኖቹ ናቸው፡፡ ኅዳር 21 በአክሱም ጽዮን የምትገኘው የማርያም ታቦት የባዕድ አምልኮ መመለኪያ ጣዖትን የሰባበረችበት ቀን ስትሆን፣ ሰኔ 21 ቀን ደግሞ የማርያም ቅዳሴ ቤት (መመስገኛ መቅደስ) የተባረከበትና አገልግሎት የጀመረበት ቀን ናቸው፡፡
ኅዳር 26 ቀን የጸሐይ፣ የብርሃን፣ የዕውቀትና ጥበባት ተምሳሌታዊ አባት (በኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ.) አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ዜና ረፍቱ ሲሆን፣ ሰኔ 26 ቀን ወደ ክረምት መግባትን በምታውጀው ዕለት የጸሐይን ተፈጥሯዊ ባህርይ የገታው (ጸሐይን ያቆማት) ኢያሱ የሚከበርባት ዕለት ናት፡፡ ኅዳር 12 ውሃን ገስጾ ከተግባሩ በማገድ ከባርነት ነጻ የወጡ ወገኖችን ለሀገራቸው መሬት እንዲበቁ ለማድረግ ርዳታ ያደረገበት ቀን ሲሆን፣ በአንጻሩ የሰኔ አቻ ዕለት የንጉሥን (የዕውቀት፣ ጥበብ፣ ፍልስፍና) የምትወክል ደብዳቤን፣ ሥልጣን አልባ ያደረገና ሞትን ወደ ሕይወት የቀየረ አጋጣሚን ትወክላለች:: በዚህቺ ሰኔ 12 ቀን በሀገራችን የኪነ-ሕንፃ ታሪክ ፈር ቀዳጅ የሆነው፣ ንጉሥ፣ መሐንዲስ፣ ቅዱስ ላሊበላ ዕለተ ረፍቱ ናት፡፡
የወርኀ ሰኔ መጋቢ የሥነፍጥረታት አሃድ ውሃ ናት አልን፤ የመሬት ባህርይ ይመግብበት ከነበረው ወደ ውሃ ባህርይ ወይም ዘመነ-መንግሥት መሸጋገርን አመልካች ወርኀ ሰኔ ናት፡፡ ሰኔ 25 ቀን የጸደይ መውጫ፣ ሰኔ 26 ቀን የክረምት መግቢያ ናቸው፡፡ የሰኔ መጋቢ ኮከብ በሀገሬው ሸርጣን ወይም ጎርምጥ ናት:: ይህቺ የፍጥረት ተምሳሌት ውሃማ ቦታዎች ውስጥ ኑሮዋን ታደርጋለች፤ ስለታማ/መቀሳማ እግሮች አሏት፡፡ ጉርምጥ እግርን በመቀሳማ እጆችና እግሮቿ የምትቆርጥ ስትሆን በታማሚ ላይ የማይድን የቆላ ቁስልን (በእንግሊዝኛ ካንሰርን) ትፈጥራለች:: የሕመሟ ዓይነት በሀገሬው ዘንድ ጫዌ ተብላ ትጠራለች፤ ይህቺ በሽታ እግርን ጨው/አሻቦ ነጭ በማስመሰሏ የተሰጣት ስያሜ ነው፡፡  
የወርኀ ሰኔ የፈረንጅኛ ኮከቧ ካንሰር ትሰኛለች፡፡ ካንሰር በጨረቃ/በወርኅ ትመራለች ወይም ትመግባለች፡፡ (በዚህ ጊዜ ጸሐይ ሥልጣኗን መቀማቷን ልብ ይሏል) ወይም ከጸሐይ በላይ ጎላ ብላ እና ደምቃ ጨረቃ ትናኛለች፡፡ ተምሳሌታዊነቷም ዘር ከማፍራትና ከእንስታዊ፣ ስሜታዊ ባህርይ ጋር የተዋደደ ነው፡፡ ይህቺ ኮከብ የእናታዊ ክብካቤ ማሳየት እና “ማጀቴ፣ ቤቴ፣ ጓዳዬ” ባይነት መገለጫዋ ናቸው፡፡ ይህቺውም በሥነ-ፍጥረታት ወገኖች በሙሉ የሚገለጹ ተፈጥሯዊ ፍሬዎችን ለማፍራት የተፈጠረች፣ ሴቴ ጾታ መለያዋ የሆነላት ናት፡፡ ተፈጥሮ ፍሬዎቿን በተፈጥሮ የማዕድን ውጤቶች፣ በምድር ፍሬዎች (በልጅ፣ በሰብል፣ በአእምሮ የፈጠራ ውጤቶች ወዘተ) አማካይነት ማሳየት በካንሰር ጊዜ ይቻላል፡፡
“ሰኔን በዘራዘር፣ ሐምሌን በጎመን ዘር!” ሲባል አንድም ዘርን መዝራት፣ መበተን ማፍሰስ መዝራት የሰኔ ተግባራት መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ሰኔ ከዘር ጋር የተሳሰረች ወር መሆኗን ለማሳየት ዘራ እና ሸነ በሚሉ ቃላት ፍቺ መረዳት ይቻላል:: ዘርዐ ከሚለው ግስ የሚወለደው ቃል በተነ፣ ነሰነሰ፣ አንጠባጠበ፤ ሸነ የሩካቤ ሽንትን የሚል ፍቺ አለው፡፡ ሸነ፤ አጮረቀ፣ ረጨ፣ ፈነጠቀ፣ አፈሰሰ፣ አንዣረረ ማለት ነው፡፡ ሽንት ዘር፣ ልጅን ሲወክል የጉም ሽንትን/ካፊያ እና የጣይ ሽንት ርጥበት አዘል የአየር ጠባያትን ይወክላሉ፡፡ በነገራችን ላይ ከላይ የተጠቀሰውና የሰኔን ወላጅ ቋንቋ የሚያስሰው ጥናት፤ ሰኔ ሸነ ከሚለው ቃል ጋር ትስስር እንዳላት በመጠቆም፣ በወርኀ ሰኔ ከማረስ እና ዘር መዝራት ጋር የተገናኙ ተመሳሳይ ስያሜዎች በበርካታ የሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋዎች እንዳለ ይናገራል፡፡ እነዚህም  ስልጢ፣ ወለኔ፣ ዛይ፣ ሐረሪ፣ ኦሮሞ፣ ሶማሌ፣ ኮንሶ፣ ጌዴዖ፣ ናቸው፡፡ “አንድ ሰኔ የተከለው ካመት ዓመት አተረፈው፡፡ አንድ ሰኔ የጣለውን አምስት ሰኔ አያነሳውም!” የሚሉ ንግግሮች ወቅትን መሠረት ያደረገ ፍሬያማ ውጤት ማስመዝገብ ከሰው ልጆች የሚጠበቅ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ቀዳሚዋን ወርኀ ሰኔ ማክበር ማለት የሚፈለገውን የመኸር ውጤት በማዝመር፣ ካመት ዓመት በበጎ መሻገር (ያለ ችግር) እንደሚቻል፣ በአንጻሩ ደግሞ ያንድ ሰኔ መዘናጋት የሚያስከፍለውን ውድ ዋጋ የሚጠቁም ነው፡፡
“ሰኔ ነግ በኔ!” እና “አተላ በሰኔ፣ ሁሉም ለኔ ለኔ!” ሲል ያልተማረው ገበሬ ከእጅ ወዳፍ በሆነ የለት ኑሮው በቤቱና ባካባቢው የሚገጥሙትን የማምረቻ መሣሪያ ውስንነቶች እንዲሁም ሰኔን ተከትለው የሚመጡ ተፈጥሯዊ ገጸ በረከቶች በትብብርና በጋራ ለመሙላት ያለውን ብርቱ ጥረት የሚያሳይ ነው፡፡
በቀጣዩ ክፍል ሀገራችንን ከሌላው ዓለም የሚያገናኟት አብነቶች በዝርዝር ይቀርባሉ!

Read 6801 times