Monday, 22 June 2020 00:00

ምርጫና ጊዜ፤ የእባቡና የንስሩ እንቁላል

Written by  ምንያህል አሰፋ
Rate this item
(8 votes)

  በአንድ ወቅት እውነትን ከውሸት የሚለይበትን ጥበብ ለመማር ፅኑ ፍላጎት የነበረው ሰው፣ በአካባቢው ወደሚታወቁ አንድ መምህር ዘንድ መፍትሄ ፍለጋ ይሄዳል:: መምህሩም የአካባቢያቸው ማህበረሰብ በእውቀት ላይ የተመሰረተና ደስተኛ ህይወት እንዲኖረው ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ ቀን ከሌት በነፃ የሚያስተምሩ፣ ቅንና አዋቂ ሰው ናቸው፡፡ የዚህን ሰው ጥበብ የመማር ከፍተኛ ፍላጎቱን  ከተረዱ በኋላ ሁለት ተመሳሳይ እንቁላሎች ወደ ቤቱ ይዞ እንዲሄድ ይሰጡታል፡፡ እሱም እንዲህ ሲል ይጠይቃቸዋል፡- “መምህር ሆይ! እነዚህ  እንቁላሎች ምንድን ናቸው? ለምንስ ይጠቅሙኛል?”
መምህሩም፡- “አንዱ የንስር ሌላው ደግሞ የእባብ እንቁላል ነው፡፡ የመናገር እውቀት ያላቸው ሲሆን ከሶስት ቀን በኋላ ይፈለፈላሉ” ብለው መለሱለት፡፡
ሰውየውም ግራ በመጋባት፡- “መምህር ሆይ፤ የንስሩስ ይሁን፤ የእባቡ  እንቁላል ከተፈለፈለ እኔንም ሆነ ቤተሰቤን ነድፎ ይገድለናል” ሲል ስጋቱን ገለፀላቸው፡፡
 መምህሩም፡- “ልጄ ልክ ነህ፤ ነገር ግን እንቁላሎቹን ብትጠይቃቸው ማንነታቸውን ይነግሩሀል፡፡ አንተም የትኛው የእባብ እንቁላል እንደሆነ በለየህ ጊዜ፣ ከቤትህ አወጥተህ አርቀህ ጣለው፡፡ ንስሩም እውነትና ውሸትን የምትለይበትን ጥበብ ይገልፅልሀል፡፡ አንተና ቤተሰብህም ከንስሩ ጋር በደስታ ትኖራላችሁ፡፡ እባቡን የምትመርጥ ከሆነ ግን መከራህን ያበዛዋል፡፡ በዚህ ተስማምተህ እንቁላሎቹን ወደ ቤት ከወሰድክ፣ ከሁለቱ አንዱን መምረጥህ ግድ ነው፡፡ ካልሆነ ጥበብን አታገኛትም” በማለት ሰውየውን አስረዱት፡፡
ሰውየውም በመምህሩ ሀሳብ ተስማምቶና አመስግኖ እንቁላሎቹን ወደ ቤቱ ይዞ ተመለሰ:: እንቁላሎቹንም በጥንቃቄ አስቀምጦ፤ ማን እባብ እንደሆነ የመጀመርያውን እንቁላል ሲጠይቀው፤ “ጌታዬ፤ እኔ እውነትና ውሸትን የምትለይበትን ጥበብ የምገልፅልህ ንስር ነኝ” ሲል መለሰለት፡፡ ሰውየውም በመደሰት ሁለተኛውን እንቁላል አርቆ ለመጣል ሲያነሳው፣ እንቁላሉ ግን በታላቅ ድምጽ፤ “ጌታዬ እውነትና ውሸትን የምትለይበትን ጥበብ የምገልፅልህ እውነተኛው ንስር እኔ ነኝ” ሲል ጮኸ፡፡ ሰውየውም በድንጋጤ እንቁላሉን ወደ ነበረበት መልሶ አስቀመጠው፡፡
እንግዲህ ሁለቱም እንቁላሎች ንስር ነን እያሉ ነው፡፡ ሰውየውም በስህተት እባቡን ከመረጠ ህይወቱ አደጋ ላይ ትወድቃለች:: ስለዚህ ምርጫው የሞት ሽረት ጉዳይ ሆኖበታል፡፡
ሰውየው በረጅሙ ተንፍሶ፣ የመጀመሪያውን እንቁላል፤  “አንተ ንስር እንደሆንክ እንዴት ላምንህ እችላለሁ?” ሲል ጠየቀው፡፡ እንቁላሉም፤ “ጌታዬ ሁለት ቀን ታገስና እውነቱን ታውቃለህ” አለው፡፡
ሁለተኛው እንቁላል ጣልቃ ገብቶ እየተወራጨ፤ “ጌታዬ የመምህሩን ህግ ያክብሩ፡፡ ወደ ቤትዎ ወስደው ይምረጡ  እንጂ ሶስት ቀን እስኪፈለፈሉ ይጠብቁ አይልም፡፡ ስለዚህ ህጉን አክብረው ዛሬውኑ ይምረጡ፡፡ ተጨማሪ ቀን የሚሰጡ ከሆነ፤ እባቡ ተፈልፍሎ አደጋ ያደርስብዎታል:: ከዛም በላይ መምህሩ ያስቀመጡትን የጥበብ ህግ ይጥሳሉ፡፡ እባክዎ ጌታዬ አደጋ ከማድረሱ በፊት እባቡን ዛሬውኑ ያስወግዱት” በማለት በጩኸት ተናገረ፡፡
ውድ አንባቢያን፤ እናንተ ብትሆኑ የትኛውን ትመርጣላችሁ? ለምን? ለዛሬ የኔን እይታ እንደሚከተለው አስፍሬአለሁ፡፡
ለማንኛውም ችግር መፍትሄ ለመስጠት፣ የሂደቱ መጀመሪያ ሊሆን የሚገባው፣ ችግሩን መተንተንና ምክንያቶቹን ለይቶ ማወቅ ናቸው፡፡ የሰውየው ችግር በስህተት እባብን እንዳይመርጥ ነው፡፡ የችግሩ ዋና ምክንያት ደግሞ ሰውየው የእባብን እንቁላል ከንስር እንቁላል የሚለይበት እውቀት ማጣቱ ነው፡፡ ይህን ያወቀው እባብም “ንስር እኔ ነኝ” ብሎ ዋሽቶታል፡፡ ስለዚህ የችግሩ ምክንያቶች የእውቀት ማጣትና ውሸት ናቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የችግሩን ምክንያቶች ከለየን በኋላ ወደ መፍትሄው እንሄዳለን፡፡ የማንኛውም ችግር መነሻ ምክንያት ተቃራኒ፤ የችግሩ መፍትሄ ነው፡፡ የጥላቻ መፍትሄ ፍቅር ሊሆን አይችልም:: ግብ እንጂ፡፡ ስለፈለግን ብቻ ጥላቻን ወደ ፍቅር መቀየር አንችልም። ፍቅርም በትግል አይገኝም። ጥላቻ የቆመበትን የጠረጴዛ እግር፤ አንድ በአንድ በመስበር እንጂ።
ለምሳሌ በፍቅረኞች መካከል ለተፈጠረ ጥላቻ፣ ፍቅር በቀጥታ መፍትሄ አይደለም:: ጥላቻውን የፈጠረው ምክንያት አምሽቶ መግባት ከሆነ መፍትሄው በጊዜ መግባት፤ ገንዘብ ማባከን ከሆነ መፍትሄው ገንዘብ መቆጠብ፤ አለመተማመን ከሆነ መፍትሄው መተማመን መፍጠር ነው፡፡ ይህን ማድረግ ሲችሉ ብቻ ጥላቻን አስወግደው ፍቅር በልባቸው ማንገስ ይችላሉ፡፡
ወደ ጉዳያችን ስንመለስ፤ የሰውየውን እውቀት በቅፅበት መቀየር ስለማንችል መፍትሄ ሊሆን አይችልም፡፡ ለዛም ነው እባብ ለመዋሸት የደፈረው፡፡ ስለዚህ የችግሩ መፍትሄ የውሸት ተቃራኒ የሆነው እውነት ብቻ ነው፡፡
በመቀጠልም የችግሩን ተቃራኒ በመውሰድ፣ የሰውየውን ግብ ማስቀመጥ ይጠበቅብናል፡፡ ከላይ እንዳየነው የጥላቻ ተቃራኒ የሆነው ፍቅር፤ የመፍትሄው ግብ ይሆናል፡፡ በተመሳሳይ የእባብን እንቁላል በስህተት የመምረጥ ችግር ተቃራኒ፤ የንስርን እንቁላል መምረጥ ነው፡፡ ንስርን መምረጥን እንደ ግብ ካስቀመጥን፤ እውነትን በምን መልኩ ብንተረጉማት 100 ፐርስንት ንስርን ልንመርጥ እንችላለን፡፡ ይህን ለመመለስ ሁለቱ እንቁላሎች፣ እውነትን የገለፁበትን ጭብጥ መረዳት ያስፈልጋል፡፡
የመጀመሪያው እንቁላል እውነቱን ከጊዜ መራዘም ጋር ገልፆታል፡፡ በተቃራኒው፤ ሁለተኛው እንቁላል ተጨማሪ ጊዜን አምርሮ ተቃውሟል፡፡ ስለዚህ በጊዜና እውነት መካከል ያለውን ግንኙነት ካወቅን፤ ማን እንደዋሸ በቀላሉ መለየት ያስችለናል፡፡
ጊዜ ውሸትን ገፎ፣ እውነትን ይገልፃል:: ጊዜ የዋሾዎች ጠላት ነው፡፡ እነሱም አምርረውም ይታገሉታል፡፡ምክንያቱም ጊዜ ሲጨምር እውነትም አብሮ ይገለጣል፤ ውሸት ግን ደብዝዞ ይጠፋል፡፡
በመሆኑም ጊዜና እውነት በቀጥታ ይገናኛሉ፡፡ ለምሳሌ የጣሊያኑ ፈላስፋ ጊርዳን ብሩኖ፤  መሬት እንጂ ፀሀይን የምትዞረው፣ ፀሀይ መሬትን እንደማትዞር አረጋግጦ ነበር:: ነገር ግን በወቅቱ የነበሩ ልሂቃን “ውሸት አስተምረሀል፤ ህዝብንም አስተሀል”  በማለት በ1600 ከእነ ነብሱ በእሳት ተቃጥሎ አንዲገደል  አስፈርደውበታል፡፡ በተመሳሳይ ጋሊሊ ጋሊሊዎም  “መሬት ክብ ናት” በማለቱ እስከ ሞተበት ቀን 1642 ድረስ የቤት ውስጥ እስረኛ ነበር፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ጊዜ ሲጨምር እውነቱ፤ መሬትም ክብ መሆንዋ፤ ፀሀይ መሬትን ሳይሆን የሚልኪዌይ ጋላክሲ ማእከልን እንደምትዞር ተረጋገጠ፡፡ እዚህ ጋ በአለማወቅና በውሸት መካከል ያለውን ልዩነት መለየቱ ጠቃሚ ነው፡፡ አለማወቅ በራሱ ውሸት አይደለም፡፡ ነገር ግን አለማወቅ ግትርነትን፤ ግትርነትም ራስ ወዳድነትን፤ እራስ ወዳድነትም ውሸትን ይወልዳል፡፡
ይህ የጊዜ ንድፈ ሀሳብ፤ በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ  እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ዘርፎችም ይሰራል፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወቅት እየሱስ እንደ ወንበዴ፤ ማንዴላ እንደ ወንጀለኛ፤ የባርያ ንግድ እንደ ህጋዊ ስራ፤ ጥቁር እንደ እንስሳ፤ ዐባይ እንደ ግብፅ የግል ንብረት፤ ሕውኃት እንደ ኢትዮጵያ አለኝታ፤ ጀዋር እንደ ሕውኃት ጠላት ይታዩ ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሉም ራስ ወዳድነት የወለዳቸው ውሸቶች መሆናቸውን ጊዜ ገልጦ አሳየን፡፡
በመንፈሳዊ አለምም ብንመለከተው፤ አውቀንም ሆነ ሳናውቀው፤ ፈጣሪ  በየቀኑ ከሞት እየታደገን፣ በህይወታችን ሌላ ተጨማሪ ቀን ይሰጠናል፡፡ ምክንያቱም በተሰጠን ተጨማሪ ጊዜ፣ እውነቱን አውቀን በንስሀ እንድንድን ነው፡፡ ስለዚህ ጊዜ እውነት ነው፤ ጊዜ ህይወትም ነው፡፡
ለመምረጥ ግራ ወደተጋባው ሰው ስንመለስ፤ ተጨማሪ ጊዜን የተቃወመው እንቁላል መዋሸቱን እንረዳለን፡፡ ምክንያቱም ሰውየው በእለቱ ቢመርጥ፤ እባቡ 50 ፐርሰንት የመመረጥ እድል ያገኛል፡፡ ነገር ግን ምርጫው ለ3 ቀናት ተራዝሞ፣ እንቁላሎቹ ቢፈለፈሉ፤ የእባቡ የመመረጥ እድል ዜሮ ይሆናል፡፡ እባቡ ምርጫው እንዳይራዘም ሁለት የመከራከሪያ ምክንያቶች አቅርቧል:: አንደኛው የመምህሩን ህግ መጣስ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ እባቡ ተፈልፍሎ አደጋ ያደርሳል የሚል ነበር፡፡  ነገር ግን በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው የአዋቂው ሰው የህይወት መመሪያ እንደሚያሳየው ከሆነ፤ ሰዎች አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው  የተሳሳተ ምርጫ እንዲያደርጉ የሚፈቅዱ ሰው እንዳልሆነ ነው፡፡ ይልቁኑ ማህበረሰቡ በእውቀት ላይ ተመስርቶ የተሻለና ደስተኛ ህይወት እንዲመራ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ፣ ቀን ከሌት በነፃ የሚያገለግሉ ቅን ሰው መሆናቸውን ነው፡፡ በመሆኑም የምርጫውን ጊዜ ማራዘሙ በእውቀት ላይ ከተመሰረተና ለሚመርጠው ሰው እስከ ጠቀመው ድረስ የመምህሩ ህግ አይጣስም፡፡ ይከበራል እንጂ::
በንስሩና እባቡ መካከል ያለውን ተፈጥሯዊ ግንኙነት ካስተዋልን፣ ሁለተኛው ምክንያትም ቅጥፈት መሆኑን እንረዳለን፡፡  እባቡ ተፈልፍሎ አደጋ ከማድረሱ በፊት፤ ንስሩ እባቡን አናት፣ አናቱን ቀጥቅጦ ይገድለዋል፡፡ ይህ ነው እውነቱ፡፡
ስለዚህ ምርጫውን በማራዘም እባቡን ለንስሩ አሳልፎ መስጠት የችግሩ መፍትሄ ነው፡፡
ውድ አንባቢያን! ዛሬ እኛም እንደ ሀገር የገጠመን ችግር፤ ንስሩን ከእባቡ ለይቶ ለመምረጥ ግራ እንደተጋባው  ሰው አይነት ነው፡፡ አንዳንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ልኂቃን፤ የምርጫው ጊዜ መራዘም የሞት ሽረት ጉዳይ እንደሆነ ያስፈራራሉ፡፡ ይህ ሀሳብ ልክ ሊሆን ይችላል:: ነገር ግን በመራዘሙ ምክንያት ማን ይጠቀማል፤ ማን ደግሞ ይጎዳል  የሚለው ጥያቄ ማብራሪያ ያስፈልገዋል፡፡  
ምርጫ ቢራዘም  ተመራጩም፣ መራጩም፤ አስመራጩም  ተጨማሪ ጊዜ ያገኛሉ፡፡ ይህ ተጨማሪ ጊዜ ደግሞ እውነት የያዘውን ይጠቅማል፡፡ በተለይ የጉዳዩ ባለቤት ለሆነው መራጩ ህዝብ፤ ማን እውነትን እንደያዘ ለመለየት ሌላ እድል ይሰጠዋል፡፡ ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል ነውና፤ መንግስትም ተቋማቱን አጠናክሮ፣ ወንጀለኞችን ለፍርድ የሚያቀርብበት አፍታ ያገኛል፡፡ በተቃራኒው የምርጫው ጊዜ ሲራዘም፣ እራስ ወዳድ ፖለቲከኞች ይጋለጣሉ፡፡ ለዚህም ነው ልክ እንደ እባቡ በህግ ስም ጊዜን አሳጥረው፤ የራሳቸውን ህይወት አራዝመው  ንስር ለመሆን የሚቃጣቸው፡፡ ተሳክቶላቸው  እድሉን ካገኙ፤ የመረጣቸውን ህዝብ መልሰው መንደፋቸው አይቀርም፡፡  
እውነቱ ግን ህዝቡም ከምርጫው በፊት አሳልፎ ለንስሩ ይሰጣቸዋል፡፡ ሰሞኑን በትግራይ ክልል የታየው ህዝባዊ እንቢተኝነት ይህን እውነታ ያረጋግጣል፡፡ 110 ሚሊዮን የሚሆነውን የኢትዮጵያን ህዝብ  ሲያፍን የኖረው የህወኃት ቡድን፤ ዛሬ 10 ሚሊዮን በማይሞላው የትግራይ ህዝብ ላይ ተጭኖ ከ2 አመት በላይ መቆየት እንደማይችል እያየን ነው፡፡ ምክንያቱም ህዝቡ መተንፈስ ሲያቅተው፤ በህይወት ለመኖር ፈንቅሎ መውጣቱ  የግድ ነው፡፡
ስለዚህ የተራዘመው የምርጫ ጊዜ  ሞት የሚሆነው ለዛ ተጨማሪ ጊዜን ለሚፈራው፣ አምርሮም ለሚታገለው ነው፡: እሱ እንደ ነጋበት ጅብ ነው፡፡ ለሌላው ሲነጋ ለሱ ይጨልምበታል፡፡ እያንዳንዷን ተጨማሪ ደቂቃ ይታገላታል፡፡ ግን አይችልም፤ ይሸነፋል፡፡ በቃ ይሄ የጊዜ ህግ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ከላይ የተንጸባረቀው ሃሳብ የሚወክለው ጸሐፊውን ብቻ እንደሆነ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ ጸሃፊው በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የአካውንቲንግና ፋይናንስ መምህር ሲሆኑ በኢ-ሜይል አድራሻቸው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 3235 times