Tuesday, 23 June 2020 00:00

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ሰሚ ያለው ጆሮ ይስማ!!
ሩዝቬልት፣ የኒኳራጋው አምባገነን መሪ ሳሞዛ ዜጎቻቸው ላይ የሚፈጽሙትን ግፍ አስመልክቶ ሃገራቸው እንደዚህ አይነቱን አምባገንን ለምን እንደምትታገስ ሲጠየቁ፤ የሳሞዛ ውለታን ቆጥረው “May be Somoza is son of a bitch, but he is our son of a bitch” (በጨዋ አማርኛ “ሳሞዛ ግፈኛ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን እኛ የፈቀድንለት ግፈኛ ስለሆነ ግፉን አንቆጥርበትም፡፡”) እንዳሉ ይወሳል፡፡
ዛሬም ጭፍን ብሔረተኞችና የስልጣን ጥመኞች በተቋማትና በመንግስት መዋቅር ውስጥ ተሰግስገው ስማቸውን በመቀየር፣ በሕገ ወጥ መንገድ ሃብት ከማካበት፣ ሰልጣን ከመቀራመትና ግጭት ከመቀስቀስ ውጭ ሕዝባዊ ግብ እንደሌላቸው በድጋሚ እያየን ነው፡፡ እነዚህ ሃይሎች “ነገ” እንዳይኖር ተግተው የሚሰሩና ስለ ነገ የማይጨነቁ፣ የቀን ተቀን ሕልማቸውም፣ በጭቁን ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ስም እየማሉና እየተገዘቱ፣ በሙስናና በዘረፋ ለመክብር የሚጋጋጡ መሆናቸው እየተገለጠ ነው፡፡ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉንም እየጨፈላለቁ ወደሚቀጥለው የስልጣን እርከን መገስገሳቸው ፤ ለነሱ “የማንነታቸው መገለጫ መብት”፤ ለሌላው ዜጋ ደግሞ “የማንነቱ መገለጫ ግዴታ” አድርገው የደመደሙ ናቸው፡፡ ለራሳቸው እስከተመቻቸው ድረስ ቀጣይ ተረኛና ጉልበተኛ እስኪመጣ የወቅቱን ጉልበተኛ እያገነኑና እያነገሱ በስልጣን ላይ ስልጣን፣ በሃብት ላይ ሃብት ማካበትን ያቀዱ፤ የማንም ውክልና የሌላቸው ሃይሎች  ናቸው፡፡
ይህ ዓይነት መንገድ እንደ “ሳሞዛ” ቸል በመባሉ፣ አሸናፊና ተሸናፊ ወደ ማይኖርበትና የስርዓት አልበኞች ሀገርነት እየገፋን ነው፤ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ በየክልሉ በጠራራ ጸሃይ የሚገደለው፣ ንብረቱ የሚቃጠለው፣ የሚታጠረው፣ የሚሸጠው፣ የሚዘረፈው የሕዝብ መሬትና ሃብት ውድቀት እየደቀነ ነው፡፡ ለዘረፋና ለሹመት ተራውን እየጠበቀ ያለው ሃይል የመግነኑን ያክል፤ ከዛሬ ነገ እጣ ፈንታዬ ምን ይሆን በሚል ስጋት የሚሳቀቀው ዜጋ ቁጥር የትየለሌ እየሆነ ነው፡፡ አሳዛኙ ነገር ቀውሱን የሚያቀነባብሩት፣ የሚያስተባብሩትና ክስተቱን በፌስ ቡክና መገናኛ ብዙሃን እየተቀባበሉ የሚያሰራጩት ሃይሎች፣ በሰላማዊ ዜጎችና በመንግስት እምብርት ውስጥ ሆነው “ለራሳቸው የሰላም ደሴት” ፈጥረው ሌላውን ማተራመስ መቻላቸው ነው፡፡
ስርዓት የነገሰበትና የህግ የበላይነት የሰፈነበት ሀገር ላይ ስልጣን መቀዳጃና ሀብት ማፍሪያ መንገድ አንድ ብቻ ነው፡፡ ስልጣንን በምርጫ፤ ሃብትን በጉልበትህ በእውቀትህና በላብህ፡፡ ሌላ አማራጭ ፈጽሞ ሊፈቀድ አይገባም፡፡ የሕገ ወጥነት በር ለአንዱ ከተከፈተ፣ ሌላው በተከፈተው በር ዘው ማለቱ አይቀሬ ነው፡፡ እንደ ሀገርና ሕዝብ፣ ትናንት ላንመለስበት በጋራ የተሻገርነውን ድልድይ ዳግም እንድንሻገረው ቸል መባሉ ከማንወጣበት ማጥ ይከተናል። ሰሚ ያለው ጆሮ ይስማ!!!
(ከሙሼ ሰሙ ፌስቡክ)

እኛ እና ፖለቲካ
የሰው ህይወት በክብ ቅርጽ በተሰራ የድግግሞሽ ኡደት ይመሰላል። የድግግሞሽ ኡደቱ ግን የሰው ልጅ በተፈጥሮ ህጎች ውስጥ ሆኖ እንደሚያዘጋጀው ስርዓት የሚወሰን። የነገሮች ድግግሞሽ እንደ አዘጋጁ ስርዓት የሚለያይ። እራሳችንን ከነበርንበት በተደጋጋሚ የምናገኘው በአዘጋጀነው ስርዓት ምክንያት ነው። እዚህም ላይ ነው አሳቢያን ከማህበረሰብ ጋር የሚጋጩት፣ ኡደትን የሚወስነው ስርአት ይቀየር ወይስ ባለንበት እንቀጥል ሙግት። በነገራችን ላይ ማህበረሰብ ለውጥን ለመቃወም ፈጣን፣ ለመቀበል ዳተኛም ነው።
ይህች አለም የውድድር ናት። የወቅቱን የአለም ሁኔታ የተረዳ ቡድን በተሻለ የሚኖርባት። ሌላው ግን የሚጠፋባት፣ ካልጠፋም የበታች አገልጋይ የሚሆንባት። እናም ደካማ ከሆንን ለአለም ችግር ሁሉ የመጀመሪያ ተቋዳሽ እንሆናለን። የመብት እኩልነት ጥያቄ መልስ የለውም። እናም የበታች ሆነን ሳንፈጠር፣ በአለም ስርዓቱ ምክንያት የበታች እንሆናለን። ለዚህ መፍትሄው ትግልን በእውቀት መምራት፣ ለአገር ጠንክረን ሰርተን ጠንካራ አገር መገንባት መቻል ነው። አንድነት የሌለው አገር ይዘን፣ ተከፋፍለን ግን በተናጠል የጠነከርን ቢመስለንም፣ ደካማነታችንን ሌላው አገር ያሳየናል። የእኛም ነገር ይኸው ነው። ለዘላቂ መፍትሄ አለመስራት።
ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ለኢትዮጵያችን ጥሩ ነገር ይዞ መጥቷል። ወቅታዊው ትርምስም የሚያመለክተን በዚህ ሽግግር ውስጥ መሆናችንን ነው። ይህ ሽግግር እንዳይኖር የሚተጉ ደካሞች እያየን ቢሆንም። ይህንንም በሚጻፈው ሃሳብ ብዛት ማረጋገጥ ይቻላል። ማንኛውም የአገር ጉዳይ በትኩረትና በጥልቀት ሲተነተን እያየን ነው። ሃሳቦች የመንግስትን አቋም ሲያስቀይሩ አይተናል። ሁሉም ዜጋ የአገሩ ጉዳይ እንደሚያገባው አምኖ ተሳታፊ መሆን ጀምሯል። አሁን የሚጎድለው የተቋማት ግንባታ አለመቀላጠፍና ፖሊሲዎችን ማውጣቱና መተግበሩ መጓተቱ ነው። ለዚህም መንግስት የሚጠበቅበትን እንዲያደርግ፣ ሕዝቡ ግፊት ማድረግ አለበት። በዚሁ አጋጣሚ የሌብነት ጥቅማቸው በተነካባቸው ደካሞች የአገር ሰላም እንዳይናጋ፣ ወደ አልታሰበ የእርስ በርስ ጦርነት እንዳንገባ፣ የውጭ ጣልቃ ገቦች መጠቀሚያ እንዳንሆን ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል።
እንደ አገር ደሃ፣ ማይምነትና ድንቁርና የሰፈነብን የሆንንበት አንዱ ምክንያት የፖለቲካ ተቋማት የሆኑት ዘመናዊና በጥሩ ቢሮክራሲ የተዋቀረ አገረ መንግስት፣ የሕግ የበላይነት የሚከበርበት ሁኔታና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባለመገንባታችን ምክንያት ነው። የአገራችን የፖለቲካ ችግር ትልቁ ምክንያት፣ የግለሰብ ጥቅም ከአገርና ሕዝብ ጥቅም መቅደሙም ነው። ይህም እነዚህ ሆዳም ፖለቲከኞች፣ በተሳሳተ መረጃ ሕዝብ የእራሱን ጥቅም ለሌቦች አሳልፎ እንዲሰጥና የመደበቂያ ዋሻቸው እንዲሆን ያደርጉታል። ካልሆነም፣ በባንዳነታቸው የደህንነት ስጋት ይሆናሉ። ይህም ችግር የአገር ሰላም መጥፋት መንስኤዎች የሆኑትን ሥራ አጥ ወጣቶች፣ ሌባ ፖለቲከኞች፣ የማይጠግቡ ባለሃብቶች፣ ብልሹ የፍትህና የደህንነት አካላት፣ ደካማ የትምህርት ሥርዓት፣ እውቀቱና ተጠያቂነቱ የሌለው ሚዲያ፣ የሥነ-ምግባርና የሞራል እሴት መጥፋት፣ የውጭ መንግስታትና ባለሃብቶች ጣልቃገብነት፣ የውሸት ሃሳብ አቅራቢ ልሂቃን ይፈጥራል።
በሚገርም ሁኔታ ለአለፉት 50 አመታት እያስተዋልን ያለው ነገር፣ የዘውግ ፖለቲከኞች አገርን የማፍረስ ወይም አፍርሰው የመስራት ፍላጎት ነው። ችግሩ ማፍረስ እንጂ መስራት ምን እንደሆነ አለመረዳታቸው ነው። ለምን ለማፍረስና እንደ አዲስ መስራት አሰባችሁ ስትላቸው፣ የተወሰነ ቡድን የባህል የበላይነት ስላለው ይሉሃል። እንዴት ነው ይህ የሚስተካከለው ስትላቸው መልስ የላቸውም። ያላቸው ጥላቻ ብቻ ነው። የአለምም ታሪክ ይህ መሆኑን አይቀበሉም። የነበረውን ሁሉ ሲያፈርሱ ሌላው ዝም ብሎ የሚያያቸው ይመስላቸዋል። እንዲያውም፣ ሁሌም የሚደጋገምና የሚገርም ጉዳይ አለ። ህዝብ ሊወያይበትና ድምጽ ሊሰጥበት ይገባል የምትለዋ የልሂቃንና ፖለቲከኞች አባባል። ግን ከመቼ ጀምሮ ነው፣ ሕዝብ ወሳኝ ሆኖ የሚያውቀው? ለመሆኑ ከልሂቃንና ፖለቲከኞች ውጭ ሕዝብ ወሳኝ የሆነበት ሀገር በአለማችን ውስጥ አለ? የሕዝብ አመለካከትስ የሚቀረፀው በነዚሁ አካላት አይደለም ወይ? ስለዚህም ለሚታየው አዎንታዊም፣ አሉታዊም ውጤት ተጠያቂዎቹ እነዚሁ አካላት ናቸውና በሕዝብ ውስጥ መመሸጋቸውን ሊያቆሙ ይገባል። እናም የተሻለው መፍትሔ አቃፊ ስርዓት መመስረት፣ ችግሮችንም በፖሊሲ ቀስ በቀስ መፍታት እንጂ አገርንና የቆመበትን ባህል በአንዴ ማፍረስ አይደለም እላለሁ።
የፖለቲከኛ ስራ የአሳቢዎችን ሃሳብ ከቻለ በራሱ፣ ከአልቻለ በአማካሪ ታግዞ ወደ ተግባር መቀየር፣ አብዛኛው ሕዝብ ሃብትን እንዲያፈራ፣ ፖሊሲና ስትራቴጂ ማውጣት ነው። መሪዎች መስራት ያለባቸው ሕዝብ በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካውና በማህበራዊ ኑሮው ደስተኛ እንዲሆን ነው። የአንድ አገር መንግስት ትልቁ ሃላፊነት፣ የሰውን ሕይወትና ሃብቱን፣ የሰዎችን የስነ ምግባርና ግብረ ገብነት በሕግጋት እና የአገርን ደህንነት መጠበቅ ነው። ነገር ግን፣ ሁላችንም እያስተዋልነው ያለው የፖለቲከኞቻችን ትልቁ ስህተት፣ ዘላቂነት ያላቸውንና መሰረታዊ ችግሮቻችንን መፍታት ሳይሆን በተራና የአጭር ጊዜ የፖለቲካ ጥቅም በሚያስገኝ ጉዳይ ላይ ማተኮራቸውን ነው። በፖለቲከኝነት፣ በሃይማኖት መሪነት ተሸሽገው የሕዝብን ደህንነት የሚጎዱ፣ የባህል እሴቱን የሚንዱ በዝተዋል። የእኛ መሪዎች ከትናንት እስከ ዛሬ እየሰሩ ያሉት እራሳቸውንና ጭፍሮቻቸውን የማስደሰት ስራ ነው። ይህም የመንግስት አስተዳደሩ የሌቦች መናኸሪያ እንዲሆንና የሕዝብን የሞራል እሴት እንዲሸረሸር በማድረግ ሁሉን ሌባ አድርገውታል። ሕዝቡ ከእነሱ የተማረው ሌብነትን ነውና። እጅግ የሚገርም ሁኔታ፣ በእውቀት ሳንበስል መምህርና ተመራማሪ፣ ፖለቲካና አገር አስተዳደር ሳይገባን የፖለቲካ መሪ፣ የአገርን እድገት እየሰበክን እውቀቱም ሞራሉም ግን በተግባር የአለመኖር፣ የዛሬንና የቅርቡን እንጂ የሩቁን ነገ ያለማየት ችግር ተጠናውቶናል። እናም እላለሁ፤ እውቀትን መሠረት አድርገን፣ ለነገ ዛሬ ካልሰራን በአለንበት የምንዳክር ድሆች፣ የሆዳሞች ስብስብ መሆናችን ይቀጥላል። የችግር መፍትሄው እውቀትን ማካበትና መተግበር መቻል ነው። ለዚህ ደግሞ በጥሩ የትምህርት ስርዓት እየተመሩ ማስተማርን፣ የንባብ ባህልን ማዳበርን ይጠይቃል። የሚያስፈልገን ጥሩ ትምህርት፣ ብሎም ጥሩ አሳቢያንና የተግባር ሰዎች ነው። ምንም ኢንቨስት ያልተደረገበትን ሕዝብ ለችግራችን ተጠያቂ ማድረግ አይቻልምና።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሃመድ ኦሮሞ ነው፣ አይደለም? የሚል ክርክር አሳፋሪ ነው። በመጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያዊ፣ የሚመራው ፓርቲ ብሔራዊ ነው። እናም ጥያቄው መሆን ያለበት በትክክል እየመራ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ነው። በተጨማሪም፣ በእኛ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች የሚታየው ትልቁ ስህተት፤ አንዱ ብሔር ከሌላው የበለጠ ጀግናና አገር ወዳድ ለማድረግ የሚሄዱበት መንገድ ነው። እውነቱ፣ ሁሉም የእራሱ ጥንካሬም ድክመትም አለው። ማንም ብቻውን የመቆም አቅሙ የለውም። እናም የሕዝብን ትብብር ትልቅነት፣ ለሌብነት ለማዋል መጣሩ መቆምም አለበት። ሌላም ጉዳይ እዚሁ ላይ ላንሳ፣ ከሕወሓት የተነካካ ሁሉ አንገቱን ይድፋ አይነት አካሄድ ሊታረም ይገባል። ለምንመኛት ኢትዮጵያ ግንባታ እንቅፋት የሚሆን፣ የአገርን ጥቅምና አንድነት የሚጎዳ፣ ለሕወሓት ቅርብ የሆኑ የዜጎችን መብት የሚጋፋ፣ አጠፉ ከሚሏቸው ያለመሻልን የሚያመለክትም ነው። እብድ ፖለቲከኞችና ሌቦች እንጂ ሕዝብ በጀምላ የሚጠየቅበት አግባብ የለም። ምክንያቱም ሕዝብ እንደ ሕዝብ ሁሌም መልካም ነውና።
ምርጫው መራዘሙ ተገቢና ለአገር ደህንነት የተደረገ ጥሩ እርምጃ ነው። የሕወሓት ምርጫ አካሂዳለሁም አቋም፤ የአገርን ሰላም ከማወክ የዘለለ አላማ የለውም። እናም የፌዴራል መንግስቱ ማድረግ ያለበት፣ በመጀመሪያ በተቻለ መጠን ዴሞክራሲያዊ የሆነ የተቋማት አደረጃጀትን መከተልና እራሱ መንግስትም ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴን ማድረግ፣ ሁሉንም ዜጋ ያለ ብሔር ልዩነት በእኩል ሊያስተዳድሩ የሚችሉ የፖለቲካ መሪዎችን ማስመረጥና መሾም፣ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ የማያደርጉ ፓርቲዎች በህጉ መሠረት ተጠያቂ ማድረግ፣ ያልታሰበ ግጭት ተከስቶ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት እንዳንገባ ጥንቃቄ ማድረግ፣ የጦር ሃይል እርምጃን የመጨረሻ አማራጭ ማድረግ ነው። የምንፈልገው፣ የአማራ፣ የኦሮሞ ወይም የትግሬ መንግስት አይደለም። የምንፈልገው የኢትዮጵያ መንግስት ነው። የአማራ፣ ኦሮሞና ትግሬ የዘውግ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ግን አላማቸው ከዚህ በተቃራኒ ነው። ስልጣንን ለራስ ቡድን ማድረግና የአገር ሃብትን መቦጥቦጥ መቻል። ግን ደግሞ እነዚሁ ቡድኖች ስለ አገር እድገት፣ ስለ ሕዝብ ሰላምና ደህንነት ሲያወሩ ይሰማል። እንዳይመጡ መንገድ ዘግተው፣ እንዴት ነው ስለዚህ የሚያወሩት?
የዲሞክራሲና የእኩል ተጠቃሚነቱን ጥያቄ መመለስ እንዳለ ሆኖ፣ የጠሚ ዶ/ር ዐብይ መንግስት፣ ገበሬውንና ከኦሮሞ፣ አማራና ትግሬ ውጭ የሆነውንም በገጠርና በዳር የሚኖረውን ትኩረቱ ውስጥ አስገብቶ መስራት አለበት። 80% የሀገሪቱ ሕዝብ መተዳደሪያ፣ ዋናው የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ግብርና ወደ ጎን የተገፋ ይመስላልና። የዘውግ ፖለቲካው ከሕገ-መንግስቱና ከፌደሬሽኑ አወቃቀር ጋር ተዳምሮ ዋናው የችግራችን ምንጭ ሆኗል። እናም ምን ምን ተቋማት ያስፈልጉናል፣ ችግሮቻችን ምንድን ናቸው፣ የሕዝብ መንግስት እንዴት ይመስረት፣ ሕገ-መንግስቱ እንዴት ይሻሻል፣ ፌዴሬሽኑ እንዴት ይስተካከል፣ በአጠቃላይ ምን አይነት የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልገናል በሚለውም ላይ መስማማት ይጠይቃል። ለጥቃቅን ምሁራን የአገርን ሃብት በመርጨት ስልጣን ላይ ለመቆየት መሞከርም አገርንና እራስንም ይዞ እንደሚወድቅ ሊታወቅ ይገባል። የጋራ ርእዮት እንዲኖር መስራትም ያስፈልገናል። ለአገራችን የጋራ ራዕይና ርዕዮት ሆነው ሊያገለግሉ የሚችሉት፣ ድህነትንና ማይምነትን የጋራ ጠላቶች፣ ዜግነትን የጋራ ማንነት ማድረግ ወይስ ሌሎች እንደ ግብጽ ጠላትነት አይነት አማራጮች አሉ?
ወንጀል የሠራ አካልን፣ በስርዓቱ በፍትህ አካል መጠየቅ እንጂ በሕዝብ ሃብት የተቀጠረን የፀጥታ አካል ህግ አድርጎ መጠቀም ተገቢ አለመሆኑ ሊታወቅ፣ በስልጣን ያለ የፓርቲ አባልም ከሌላው የተለየ መብት የሌለው መሆኑን ሊያውቅ ይገባል። መንግስት ባንዳነቱ ለተረጋገጠ ማንም ግለሰብ ወይም ቡድን ትግስት ሊኖረው አይገባም። ሚዲያዎችም ጊዜያዊ ድርጊትን መዘገብ ብቻ ሳይሆን መንስኤና ውጤትን፣ ብሎም መፍትሔን መሰረት ያደረጉ ዝግጅቶችን፣ አዋቂዎችን በሚዲያዎች በማቅረብ ሕዝብን ሊያስተምሩ ይገባል። የተሻለ ስርዓት በማዘጋጀት፣ የድርጊትን ድግግሞሽ ባናቆመውም፣ የመጥፎ ድርጊት ድግግሞሽን ማቆም እንችላለን። እናም ለዘላቂ እድገት፣ ለጥሩ ስርዓት ግንባታ መጣር ይኖርብናል።
(ከመልካሙ አዳል ፌስቡክ)

ዲሞክራሲ ብሎ ነገር ምን ይሰራልናል?
ዲሞክራሲን እንፈልጋለን። ዳቦ ነው የሚያስፈልጋችሁ አትበሉን። እያንዳንዳችን የምንፈልገውን በራሳችን እንወቀው። የራሳችንን እድል በራሳችን እንወስን።
ዲሞክራሲ የሚያስፈልገን፤ እያንዳንዳችን በተናጥል የምንፈልገውን ነገር እንድናውቀው ነው። የምፈልገውን ነገር እንዳውቀው ነው። ፍላጎቶቼ የራሴው የግሌ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ነው። ግን እኮ ዲሞክራሲ የፖለቲካ ስርአት ነው። በፖለቲካ ስርአት ደሞ የሚወሰነው የግለሰብ ጥቅም ወይም ፍላጎት ሳይሆን የሀገር ጥቅም ወይም ፍላጎት ነው። እንዴት ነው ታዲያ ዲሞክራሲ የሚጠቅመው እያንዳንዱ ሰው የሚፈልገውን እንዲያውቀው ነው የምትለው? የሚል ጥያቄ ይሰማኛል ወይም እጠብቃለሁ። ይኸውልህ ወዳጄ፤ የተለመደውን የዲሞክራሲ ትርክት እንመልከተው። በተለመደው የዲሞክራሲ ትርክት መሰረት፤ ዲሞክራሲ የሚወልደው ሁለት ነገር ነው። የሀገር ጥቅም ወይም ፍላጎት የሚባለውን ነገር ይወልዳል። በሁለተኛ ደረጃ ደሞ ይህን የሃገር ጥቅም ወይም ፍላጎት የሚያገለግል መንግስት ይወለዳል። የሀገር ጥቅም ወይም ፍላጎት ማለት የዜጎች ጥቅም ወይም ፍላጎት ማለት ነው። እያንዳንዱ መራጭ ዜጋ የሚፈልገውን ነገር በምርጫና በተሳትፎው ይገልጣል። በዚህ ሂደት አብዛኛው ሰው በምርጫውና በተሳትፎው የገለጠው ፍላጎት፣ የሀገር ፍላጎት ወይም ጥቅም ተደርጎ ይወሰዳል። እኔ የምፈልገው ይሄን ነው እላለሁ። አንተም እንደዚሁ። እንዲህ እያለ ሃምሳ ሚሊዮን ወይም 200 ሺ ወይም 20 ሚሊዮን ሰው ፍላጎቱን ያሳውቃል። በብዙ ሰው የተገለጠው ፍላጎት የሀገር ወይም የህዝብ ፍላጎት እንደሆነ ይገመታል። በጥቂት ሰዎች የተንፀባረቀ ፍላጎት ሰሚ ያጣል። በእርግጥ እንዲህ አይነት ሰሚ ያጡ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ ያልተማከለ አስተዳደር፥ ገበያና መሰረታዊ የመብቶች ጥበቃ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
ልብ በል፤ የሀገር ፍላጎት ወይም ጥቅም መሰረቱ የዜጎች ፍላጎትና ጥቅም ነው። ሀገር ማለት የዜጎች ድምር እንደ ማለት ነው። እያንዳንዱ ሰው ፍላጎቱን ያውቃል፥ የሚበጀውን ያውቃል፥ ለጊዜያዊ እርካታ ሲል ቋሚ ጥቅሙን አሳልፎ አይሰጥም ተብሎ በመታሰቡ ነው። እውነት ግን እንደዚያ ነው? እውነት ፍላጎትህን ታውቀዋለህ? እውነት ግን የሚበጅህን ታውቀዋለህ?
እውነት ግን ራስህን መቆጣጠር ትችላለህ? በእነዚህ ጉዳዮች ላይ አያሌ ፅሁፎች ተፅፈዋልና ለማብራራት አልሞክርም። በእርግጥ እኔም በተለያዩ ጊዜያት በፉዣዥ የፃፍኩባቸው ናቸው። ላሁኑ ግን የሚከተለውን ልበል።
ፍላጎቶች የልምምድ ውጤቶች ናቸው። ከህፃንነት ጀምሮ በድግግሞሽና በሌሎች መንገዶች የተሞላሃቸው ናቸው። አብዛኛዎቹ የኔ የምትላቸው ፍላጎቶች ያንተ እንኳን አይደሉም። ሁሉም የወላጆችህ፥ የአስተማሪዎችህ፥ የአብሮ አዳጊዎችህ ናቸው ሊባሉም እንኳን አይችሉም። ምንጫቸው ሰባት ትውልድ ወደ ኋላ የሆነ ብዙ ፍላጎቶችን ነው የኔ ብለህ የምታስባቸው።
ካንተ የተለየ ሰባት ትውልድ የሚመዘዙና በተለያዩ ጊዜያት የተወለዱና ያደጉ ሰዎች ደሞ የተለያዩ ፍላጎቶቹን እንደ ራሳቸው ፍላጎቶች ይዘዋል። የኔ የምትለውን ፍላጎት የሆነ ኮሮጆ ውስጥ ከተህ በመመለስ ምን ያህል ሰዎች ተመሳሳይ ፍላጎት እንዳላቸውና ያንተ ፍላጎት በሀገር ፖሊሲ ውስጥ ምን ያህል እንደተንፀባረቀልህ ለማየት ውጤቱን መጠባበቅ አይደለም የዲሞክራሲ ዋናው ጥቅም። ቀዳሚው ጥቅምም ይህ አይደለም።
ፍላጎቶቻቸው፥ ጥቅሞቻቸው በሀገር ፍላጎት ወይም ጥቅም ያልተካተተላቸው ሰዎች ምን ይሆናሉ? ለነገሩ የተካተተላቸውም ቢሆን ሁሉም ፍላጎታቸው አይካተትላቸውም። እጅግ ጥቂት ፍላጎቶቻቸው እንጂ። ለምን? ምክንያቱም በሀገር ጥቅም ውስጥ የሚካተቱ ጥቅሞች በመንግስት የሚከወኑ ስራዎች ነው። በመንግስት የሚከወኑ ስራዎች የአብዛኛውን ጥቅም ማስጠበቃቸውን ለማረጋገጥ ነው የሀገር ጥቅም መነሻ የሚሆነው። ነገር ግን የዜጎች ጥቅም የሚከበረው ወይም የሚሰፋውና የሚበዛው በመንግስት ስራዎች ብቻ አይደለም። በዋናነት በዜጎች ስራና  ትብብር ነው። በመሆኑም አብዛኛው የዜጎች ጥቅም በሀገር ጥቅም ባይካተትም፣ በግለሰቦች ጥረትና ትብብር የሚስተናገድ ይሆናል።
ከዚህ አኳያ ስናየው የዲሞክራሲ ዋናውና ቀዳሚው ጥቅም፣ የሀገር ጥቅምንና ህዝባዊ መንግስት መውለድ አይደለም። ይልቅስ እያንዳንዱ ሰው የኔ ከሚለው ፍላጎት የተለዩ፥ አንዳንዴም የተቃረኑ ፍላጎቶች፣ ሌሎች ሰዎችም እንዳላቸው እንዲያውቅ ይረዳዋል። ማወቅ ብቻውን ግን ፋይዳ አልባ ነው። የሚልቀው ለምን እነዚህ ሰዎች ከኔ ተለዩ ብሎ እንዲጠይቅ ይረዳዋል። ለምን ተለየሁ ብሎ ራሱን እንዲጠይቅ ያደርገዋል። በመንግስት ስራዎች ከሚከወኑት ባሻገር ያሉ ፍላጎቶቹን ጥቅሞቹንም መልሶ እንዲፈትሻቸው እድል ይሰጠዋል።
ከዚህ በላይ እንደጠቀስኩት ፍላጎቶቻችን የኔ ወይም የእኛ ብንላቸውም በእርግጥም የኔ ወይም የእኛ አይደሉም። ከዚህ በፊት “የእንቁራሪት ጥብስ” በሚል ፅሁፍ ይህን ጉዳይ በፉዣዥ ለመመርመር ሞክሬ ነበር። ዲሞክራሲ ይህን እንድታውቅ እድል ይሰጥሃል። የሌሎች ሰዎችና ያንተ ጥቅሞችና ፍላጎቶች፥ ስጋቶችና፥ ፍርሃቶች ምንጫቸው ምን እንደሆነ እንድታውቅ ዲሞክራሲ እድል ይሰጥሃል። ይህን በሚገባ በመመርመር ከስዎች ጋር ያለህን ትብብር ማላቅ ትችላለህ። እድሜህን በሙሉ የኔ ያልከውን ነገር ግን ያልሆነውን ፍላጎት በማገልገል ከመባከን ትድናለህ።
ይህ ነው የዲሞክራሲ ተስፋ። ይህ ነው የዲሞክራሲ እድል። ይህን ተስፋና እድል የምትለማመደው ደሞ በምርጫ ወቅትና በፓርቲዎች የምርጫ ክርክርና የምረጡኝ ዘመቻ ወቅት ብቻ አይደለም። ከቤትህ ይጀምራል። ከትዳርህ ይጀምራል። ከልጆችህ ይጀምራል። የኔ የምትላቸውን ያልተሟሉ ፍላጎቶችና ምኞቶች እንዲሟሉልህና በውክልና ለመርካት በሚል ተስፋ ከሆነ ልጆችህን የምታሳድገው፤ ምርጫና የፓርቲዎች ክርክር ምን ሊጠቅምህ እንደሚችልም ግልፅ አይደለም ለኔ። እና የመሳሰሉት። የራሱን እድል በራሱ መወሰን ያልቻለ ዜጋ፤ በቡድን ሆኖ የቡድኑን የራስ እድል በራስ መወሰን ይችላል የሚለውን መቀበል ከባድ ይመስለኛል።
(ከሙሉጌታ መንግስት አያሌው ፌስቡክ)
ኤልያስና ኢዮብ አንድም ሁለትም.!
“እንደ ቃል” ፣ ሽሽት ነው፡፡ ከሥጋ ወደ መንፈስ የመመለስ ሩጫ፡፡ ከጨለማ ወጥቶ ወደ ብርሃን የመግባት ጥድፊያ፡፡ ገና ሲጀምር መንቃቱን ያውጃል፡፡ ተርፌአለሁ ብሎ ይለፍፋል ፡፡ ቃላቱ ተቃርኗዊ ውህድትን ያዘሉ ናቸው፡፡ መንቃት ከማንቀላፋት በኋላ የሚመጣ ነው፡፡ መትረፍም የአደጋ ተከታይ::
የአብዮቱ መባቻ ስንኞች ተቀበዝባዦች አይደሉም፡፡ ይሁነኝ ተብለው አሁንም አሁንም እየመጡ የሰርክ ህይወትን የሚፈትኑ እንጂ፡፡ “ነገን ላየው” የሚልን ሙዚቃ የሚሰማ ሰው፤ ግሩም የሬጌ ሐሳብን አገኘሁ ብሎ ሥጋውን ያስደስት ይሆናል፡፡ ግን አይደለም፡፡ ትርጉሙ ከመጀመሪያው ዜማ የቀጠለ ነው፡፡ መንቃት በትናንትና በዛሬ መካከል መቆም ብቻም ሳይሆን ወደ ነገም ለመሻገር ያንደረድራል፡፡ በዘፈን የማዘመር አብዮትንም ያስጀምራል፡፡
በከንቱ እየደከምኩ አይመስለኝም፡፡ “ነቅቻለሁ” ውስጥ ያሉት ተከታይ ስንኞች የፍርሃት ክንብንብን ወዲያ ጥለው ኢዮብ እየዘመረ መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡
“የተራበ ልብ ፍቅርን የጓጓ
ከእውነት ቤት ሄዶ የእውነት ያንኳኳ
ደጁን ለጠና እዛው ቆይቶ
የራሱን ያቅፋል በሩ ተከፍቶ”
ለአማኙ ኤልያስ መልካ፤ የእውነት ቤት ማለት የእግዚአብሔር ቃል መሆኑ የሚያከራክር አይደለም፡፡ መጽሐፉም እንዲህ ይላል፡- “ቃልህም እውነት ነው” (መዝሙረ ዳዊት 118 /119፡142 )
አላበቃንም፡፡ ተከታዮቹ ስንኞችም የሙዚቃውን ሰም አሽቀንጥረው ጥለው ወርቁን በግላጭ ይሰብካሉ፡፡ “ደጁን ለጠና እዛው ቆይቶ ፤ የራሱን ያቅፋል በሩ ተከፍቶ” እያሉ በማቴዎስና በሉቃስ ወንጌል የተነገረውን “መዝጊያውን ለሚያንኳኳው ይከፈትለታልን” ያጸናሉ፡፡
አንድምታው የእውነተኛ ፍቅር ባለቤት እግዚአብሔር መሆኑን ያስታውሳል፡፡ ሰዋዊው ፍቅርስ የአምላክን ቃል ዘንግቶ እንዴት ይሳካል? እያለ ይሰብካል፡፡ መዝሙረኛው ኤልያስ፤ ናፍቆቱም ምድራዊ አይመስልም፡፡ “ነገን ላየው” የሚለው ዜማው ሕይወትን በምድር ብቻ አይሰፍርም፤ መሻቱ ሰማያዊውን ዓለም ይመስላል፡፡
ለአፍታ “እንደ ቃልን” ተሰናብተን “ ከምን ነፃ ልውጣ ?” ወደ ሚለው የቤሪ አልበም እናምራ፡፡ የማይደበዝዘው ኮከብ ኢዮብ ያዜመውን “ነገን ላየው“ የተሰኘ ሙዚቃ በድጋሚ በቤሪ በኩል ያስደምጠናል:: በቀደመው አልበም ውስጥ ሊነግረን የፈለገውን ሐሳብ ፍንትው አድርጎ ያሳየናል::
ሕይወት የሩቅ እንጂ
የምድር መች አጭር ሆነች
የእውነቱ ነገ እንጂ
ዛሬን ስል ለምን ልጎምጅ፡፡
ስንኞቹን የትናንት ዜማውን ትርጉም ተናግረው የሚያቆሙ አይመስሉም:: ይልቁኑ የኢዮብ ህልፈት የወለደው መለያየት ስጋዊ እንጂ መንፈሳዊ አለመሆኑን ያሳያሉ፡፡ ምድራዊ ወዳጅነታቸው ተገታ እንጂ ሕይወት አለማብቃቷን ይጠቁማሉ፡፡ ኤልያስ እና ኢዮብ አንድም ሁለትም ነበሩ:: አንድነታቸው ከትናንት መፋታታቸው ነው፡፡ የቀደመውን ማንነታቸውን ገለዋል:: በራሳቸው ሰብዕና ላይ አምጸዋል፡፡ ባለፈ ታሪካቸው ተጸጽተው በደላቸውን ተናዘዋል፡፡ በእንጉርጉሮ ዜማም ቀድሞ የነበረውን የጥፋት ሕይወታቸውን ኮንነዋል፡፡ አምነውም “ንስሐ” ገብተዋል፡፡
እንዳጠፋሽ አጥፍቻለሁ
እንደሸፈትሽ ሸፍቻለሁ
ያየሽውን አይቻለሁ
ያለ ፅድቄ ያለ ፍርድ ቆሚያለሁ፡፡
ሐሳቡ ግላዊ ብቻ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው፡፡ በዮሐንስ ወንጌል 8፡7 ላይ “ከእናንተ ኃጥያት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት” ብሏልና፡፡ የዚህ ዜማ መልዕክት ሌላም ትርጉም አለው ብለው የሚሟገቱ አሉ፡፡ በኦሪት ዘመን ሚስቴ አመነዘረች ያለ ሰው ወደ ካህን ይወስዳታል፡፡ በዛም መራራ ውኃን እንድትጠጣ ይደረጋል:: አምንዝራ ስለነበረ ሆዷ ተነፋ ፡፡ እግሮቿም ሰለሉ፡፡
ባሏ የእጇን አገኘች አላለም፡፡ በእሷ ቅጣት ውስጥ እራሱን አሰበ፡፡ እሱም ንጹህ አይደለም፡፡ መጽሐፉ በዛ ሰው ውስጡ ያለውን መደበላለቅ አልነገረንም፡፡ ኤልያስ ግን የዛ ሰውን ህመም ሳይታመምለት የቀረ አይመስልም፡፡
ችኩል ቅጣቱ ከአንች የጀመረ
ሊታዘበኝ ነው የእኔን አሳደረ
ዋጋ ልክፈል ብሎ ካሰላው ጥፋቴን
ይደምርብኛል አንዴ ዳኝነቴን
“እንደ ቃል” የሙዚቀኞቹን “መንቃት” ሲያወጅ ተፈጥሯዊውን ከእንቅልፍ የመነሳት ገፅታ ተውሶ ነው፡፡ የጠዋት ብሩህ ወገግታ በአንድ በኩል፣ የትናንት ስንፍና በሌላ በኩል በኤልያስ ህሊና ውስጥ ግብግብ ይዘዋል፡፡ እጓለ ገብረዮሃንስ እንዲህ ያለውን ስሜት፣ የመንፈስ መከፈል ይሉታል፡፡ ነገሩን ሲያብራሩም፤ ሰው ከታች ከእንስሳዊ ከላይ ከአምላካዊ ነፍስ ጋር ተጎራብቷል ይላሉ፡፡ ሐሳቡ ፍልስፍናዊ በመሆኑ ጥቂት ሊብራራ ይገባዋል፡፡
የሰው ልጅ በሁለት ባሕሪያት መኻል የሚዋልል ፍጡር ነው፡፡ ሰብዓዊ እርቃኑ ሲገለጥ እንስሳዊ ገመናው ይታያል:: የፈጣሪውን መንገድ ሲከተል ቃሌን ብትሰሙ እኔን ትመስላላችሁን የሚለውን ጥቅስ ያስታውሳል፡፡ ሰው ህሊናን መታደሉ ደመነፍሳዊ ባህሪን እንዲጸየፍ ነው ፡፡
እሱ ብቻውን ግን እግዚአብሔርን ለመመስል አይረዳውም፡፡ ምድራዊ ሕይወት ላይ መሰልጠንም ያሻዋል፡፡ ኤልያስ በእንደ ቃል አልበም ውስጥ ከፍ ብሎ አምልካን ለመምሰል ቢጥርም፣ የመንፈስ መከፈሉ ግን ምድራዊ ኑሮን ሸሽቶ እንዳይሸሽው አደርጎታል፡፡
“የቋንቋ ፈላስፋ” ውስጥ የምንሰማው ኤልያስ የዚህ ነፀብራቅ ነው፡፡ ፉክክራችን የኢትዮጵያን ችግር በጥሩ ቋንቋ መግልጽ እንጂ ህመሟን ማከም አለመሆኑ ያብሰለስለዋል፡፡ መነሻው የሩቅ አይደለም:: በወቅቱ “50 ሎሚ” የተባለ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ነበር፡፡ ተሳታፊዎች ለማይክ ይሽቀዳደማሉ፡፡ የሀገራቸውን ችግር ውብ አድርገው ይተርካሉ፡፡ ግን ምን ይፈይዳል? ትናንትም እንዲህ ነበርን ዛሬም እንደዛ ፤ምናልባትም ነገ ይከተል ይሆናል፡፡ የማይደበዝዘው ኮከብ በዚህ ግጥሙ ውስጥ የአንድን ድሃ ገበሬ ስሜት ድንቅ አድርጎ የገለፀው ይመስለኛል፡፡
ተጠራርተን ከየቤቱ
ቃልን መርጠን መሻማቱ
ለእኛስ ነው ወይ መድኃኒቱ
ሃምሳ ሎሚ ከብዶት ይሸከም ጉልበቴ
አታግዙኝ ይቅር ጌጤ ነው ቅርጫቴ
“እንደ ቃል” የአብዮት መባቻ ነው፡፡ አልበሙ ሲጀምር የምንሰማው የመጀመሪያ ቃል “ነቅቻለሁ” ይላል፡፡ በእኔ ግምት ተከታዮቹ አስር ዜማዎችም ሆኑ ከዛ በኋላ የመጡት አልበሞቹ የዚህ ቃል እስረኞች ናቸው፡፡ ቁምነገሩ ግን እሱ አይደለም፡፡ መሰረታዊው ጉዳይ ኤልያስ ዘፈን ሀጥያት ነው ከሚሉት ጋር ጦርነት ሲጀምር አንዳችንም አልሰማንም፡፡ ነቅቻለሁ ብሎ በትናንት ትውፊት ላይ ሲያምፅም የነገረንም የለም፡፡
በህልፈቱ ሰሞን በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አንዲት ጽሑፍን አቅርቤ ነበር:: ከመድረክ እንደወረድኩ ከአድናቂዎቹ አንዱ እንዲህ አለኝ፡- “ሐሳቦቹ ጥሩ ናቸው፤ ግን ኤልያስን እሱ የማያውቀውን አብዮት መሪ አድረገነውስ ቢሆን?“ ጥያቄው የዋዛ አይደለም፡፡
የማይደበዝዘውን ኮከብ፤ ነፃነት የማያውቅ ነፃ አውጭ አድርገው የሚያስቡትም እንዳሉ አልዘነጋሁም፡፡ ግን አይደለም፡፡ የኤልያስ መልካ “ነቅቻለሁ” አልበም፤ “የንስሃ” ዘፈን ነው ፡፡ ትናንትን ተፀይፎ አዲስ ማንነትን መላበስ፡፡ የአብዮት መባቻ ላይም መድረስ::.........
(ከማዕረግ ጌታቸው ፌስቡክ)

Read 2388 times