Saturday, 20 June 2020 12:30

የወረርሽኝ ትንበያ ጠቃሚነቱ፣ መክሸፉ ነው።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

  • በየአገሩ፣ ምን ያህል ሰዎች፣ በምን ያህል ፍጥነት ለቫይረስ ይጋለጣሉ?
           • የትኞቹ ትንበያዎች ሰሩ? ምን ያህሉ ስህተት ሆኑ? አብዛኞቹ ከሽፈዋል።
                 
             የኮረና ቫይረስ ስርጭትን በተመለከተ የተዘጋጁ የትንበያ ቁጥሮች፤ “ምንም የጥንቃቄና የመከላከያ ጥረት ካልተደረገ” በሚል መነሻ ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ “እየተጠነቀቅን? እየተከላከልን? ጥረታችንን እንደ ከንቱ ከተቆጠረማ፤ ትንበያው ምን ይረባል?” እንል ይሆናል። ግን ደግሞ፤ ሌላ መነሻ የለም።
ስርጭቱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር፣ ምን ማድረግ እንደሚሻለን ማሰብና ዘዴ ቀይሰን መጣር የሚኖርብን፤ አደጋውን በሚመጥን መንገድ ነው፡፡ እናም፤ “ካልተጠነቀቅን፣ ካልተከላከልን፣…” በሚል ስሌት፣ የወረርሽኙን አደገኛነት ለመገንዘብ የሚረዳ ትንበያ ይዘጋጃል። ችግሩ ምንድን ነው?
በዚህ ስሌት የሚመጡ የትንበያ ቁጥሮች፤ “እጅግ የተጋነኑ” ሆነው ይታዩናል። የተተነበየው ያህል፣ ሚሊዮኖች ለቫይረስ አይጋለጡም። ትንበያው፤ በእውን አይከሰትም። “ይከሽፋል”። ለምን?
በአንድ በኩል፤ ትንበያው ያስፈልጋል- ቀድመን ለመዘጋጀትና ለመጣር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፤ ጥረታችን፤ ትንበያው በእውን እንዳይደርስ ለማስቀረት ነው፡፡ እንድናከሽፈው ነው፤ አገልግሎቱ።
ለቫይረሱ እንዳንጋለጥ ከተጠነቀቅን፣ በገፍ እንዳይሰራጭ ከተከላከልን፣ ...እንደ ብልሃታችንና እንደ ትጋታችን ልክ፤ ወረርሽኙን መግታት ባንችል እንኳ መግራት አያቅተንም፡፡ ከተሳካልን፤ “ትንበያው ከሸፈ” ማለት ነው፡፡ “ትንበያው ጠቀመን” ልንል የምንችለውም፤ በዚህ መንገድ እንጂ በሌላ አይደለም - አደጋውን ለማስቀረት፤ ትንበያውን ለማፍረስ፡፡
በእርግጥ፤ ከሁሉም በፊት፤ ትንበያው፣ “በእውቀትና በሳይንሳዊ መንገድ የተዘጋጀ ትንበያ” መሆን አለበት፡፡ ከእውነተኛ መረጃ፤ ከተጣራ ግንዛቤ፣ ከነጠረ ትንታኔ የመነጨ ካልሆነ፤ ከንቱ ልፋት ይሆናል፡፡ የትንበያ ልኩ፤ ቅጥ ከያዘ እውቀትና ከሳይንሳዊ አስተሳሰብ መገኘቱ ነው፡፡ “የዚህን ያህል ቀላል ነው” - ጉዳዩ፡፡ ያለ መረጃ፣ ያለ እውቀት፣ እና በዘፈቀደ የሚበተኑ የትንበያ ቁጥሮች፤ ጥቅም የላቸውም፡፡ የአላዋቂነትን ብክነት፣ የጭፍንነትን ጉዳት ለማስተማር ይጠቅማል ካልተባለ በቀር፤ የዘፈቀደ ትንበያ ምንም አይፈይድም፡፡
የትንበያ ፋይዳ የሚለካው፤ እንዲህ በቀላሉ ነው፡፡ “የእውቀትና የሳይንሳዊ አስተሳሰብ ውጤት” መሆን አለመሆኑ ነው ሚዛኑ፡፡ ነገሩ፤ “የዚህን ያህል ከባድ ነው”:: እውቀት፣ ያለ ብርቱ ጥረት፣ በዘፈቀደ አይገኝም፡፡ ለ“አዲስ እውቀት” መስራት ደግሞ፤ ከሁሉም የስራ አይነት ይከብዳል፡፡
የዘንድሮው አይነት የኮረና ቫይረስ ስርጭትና ወረርሽኝ፣ ካሁን በፊት አላጋጠመም፡፡ አዲስ ነው አይነቱ፡፡ የወረርሽኝ መከላከያ ጥንቃቄዎችና ዘዴዎች፤ እንደ ዘንድሮ፣ በፍጥነት የተስፋፉበት ታሪክ የለም፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ ብዙ አዳዲስ መረጃዎችን መሰበሰብ ቀላል አይደለም። መረጃዎችን አጣርቶና በትክክል አገናዝቦ፣ በቅጡ አዲስ እውቀት፣ ለማዳበር፣ ብዙ ጥረት ያስፈልጋል፤ ለዚያውም የጠቢባን ብርቱ ጥረት፡፡
ቫይረሱ፣ በፍጥነት የሚዛመት፤ የተወሰኑ ሰዎችን ደግሞ ለከፋ ስቃይና ለሞት እንደሚዳርግ ታውቋል። ግን፣ በምን ሁኔታ በምን ያህል ፍጥነት እንደሚዛመት በዝርዝር ተብጠርጥሮ ታውቋል? ይህም በቂ አይደለም፡፡ የመከላከያና የጥንቃቄ ጥረቶች፣ ምን ያህል ውጤታማ እንደሚሆኑ በዝርዝር ማጥናትም፤ ሌላ ከባድ ስራ ነው፡፡
እንግዲህ፤ በተሰበሰቡና በተጣሩ መረጃዎች መጠን፣ በተጨበጠ የግንዛቤ የእውቀት ልክ ነው፤ የትንበያ ቁጥሮች የሚዘጋጁት፡፡ እውቀት እየዳበረ በሄደ መጠን፤ የትንበያ ቁጥሮች የዚያኑ ያህል እየጠሩ፣ ከስህተት እየፀዱ፣ ፋይዳቸው ይጨምራል፡፡ እስከዚያው ግን፤ ከነጉድለታቸውም፤ በጥቂቱም ቢሆን፤ ይጠቅማሉ።
የዛሬ ሦስትና አራት ወር፣ ከየአገሩ ስንሰማቸው የነበሩ ትንበያዎች፤ ስህተታቸው በዝቶ፣ ጉድለታቸው ገዝፎ ቢታየን አይገርምም፡፡ የቫይረሱ ስርጭትና ጉዳት፤ ከተተነበየው በታች ነው። የተተነበየው አልደረሰም። ለምን?
አንደኛ ነገር፤ የያኔው መረጃና እውቀት አነስተኛ እንደመሆኑ መጠን፤ የያኔዎቹ ትንበያዎችም፣ ስህተታቸው ትልቅ፣ ፋይዳቸው ትንሽ እንደሚሆን አያከራክርም::
ሁለተኛ ነገር፣ ያ ሁሉ የወረርሽኝ መከላከያ ጥንቃቄና የመቆጣጠሪያ ጥረት፤ የቫይረሱን ስርጭትና ጉዳት ለመቀነስ እንደሆነ አንርሳ። የተተነበየው ያህል ብዙ ሰው ለቫይረሱ እንዳይጋለጥ፤ ትልቅ ጉዳት እንዳይደርስ ነው - የትንበያው አላማ፡፡
የጀርመን መራሔ መንግስት አንጌላ ሜርከል፤ ከአገሬው ህዝብ ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ ለኮሮና ቫይረስ ሊጋለጥ እንደሚችል ተናግረው ነበር፡፡ አሁን ሲታይ፣ ያ ቁጥር በጣም ሩቅ ሆኖ ቢታየን፣ ሜርከል ላይ ለመፍረድ መቸኮል የለብንም፡፡ በጣም በተጠቁት በጣሊያንና በስፔን እንኳ፤ የቫይረሱ ስርጭት 10 በመቶ አልደረሰም፡፡
ምንም እንኳ፤ እለታዊ ሪፖርት ከምናየው በላይ፣ ቫይረሱ በሰፊው የተዛመተ ቢሆንም፤ የተተነበየው ያህል አልከፋም። በተወሰኑ ከተሞች፤ 20 በመቶ ያህል ነዋሪዎች ለቫይረሱ ቢጋለጡም፤ በጥቅሉ ሲታይ ግን፣ የቫይረሱ ስርጭት ከተተነበየው በታች፣ 10% ሳይደርስ ረግቧል፡፡
ስዊድንን ማየት ይቻላል። ከሌሎች የአውሮፓ አገራት ተለይታ፤ “አገርን ዘጋግቶ፣ ፋብሪካዎችን ቆላልፎ ቤት መቀመጥ አያዋጣም፤ በጥንቃቄ መንቀሳቀስና መስራት ይሻላል” በሚል አቅጣጫ በተጓዘችው ስዊድን ውስጥም እንኳ፣ የቫይረሱ ስርጭት ተገርቷል፡፡
ደግሞስ፤ ከዚህ ውጭ ምን ሊሆን ይችላል? ቫይረሱ ያለ ልጓም አገር ምድሩን እንዳያጥለቀልቅ፤ በየአገሩ አነሰም በዛ፣ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር፤ ሰዎች የሚጠነቀቁትና የሚጥሩት ለምን ሆነና?
ጥረታችን፣ ከንቱ ልፋት አይደለም። የወረርሽኝ ከባድ አደጋ ሲመጣብን፣ ዝም አላልንም። የማስጠንቀቂያ ትንበያዎችን ሰምተን እንዳልሰማን ለመሆን አልሞከርንም። በብዥታ አልፈዘዝንም። አለበለዚያማ፤ የማስጠንቀቂያ ትንበያ ፋይዳ የቱ ላይ ነው?
ማስጠንቀቂያው በከንቱ ባክኖ፤ በአሳዛኝ ሁኔታ ትንበያው እውን ከሆነማ፤ የዮናስ መጽሐፍ፤ ምሳሌያዊ ትምህርትን ስተነዋል ማለት ነው፡፡ የትንበያ ፋይዳው፤ መልካም ውጤት በጥረት እንዲሳካ፤ አደገኛ መዘዝም በጥንቃቄና በብልሃት እንዲከሸፍ ነው:: ይህንን አትዘንጉ የሚል መልዕክት ያዘለ አይደለም እንዴ - የዮናስ አስገራሚ ትረካ፡፡ እንዲያውም፤ ዋነኛ መልዕክቱ ይሄው ነው፡፡
“በ10 ዓመት ውስጥ፤ የኢትዮጵያውያንን ኑሮ በእጥፍ ማሳደግ ይቻላል”፤ አልያም፤ “ለኮረና ቫይረስ ሚሊዮኖች ሊጋለጡ ይችላሉ” የሚሉ የእድገት ወይም የማስጠንቀቂያ ትንበያዎች፤ ፋይዳ የሚኖራቸው፤ ሁለት ነገሮችን ሲያሟሉ ነው። መነሻቸው ከእውቀት፤ መድረሻቸው ደግሞ በሰዎች እጅ ውስጥ መሆናቸው ነው - ፋይዳቸው፡፡
ማደግ ይቻላል፤ እድገት የሚሳካው ግን በሰዎች ጥረት ነው፡፡ ኮረና ቫይረስ በፍጥነት ይዛመታል፤ ግን በሰዎች ጥረት የቫይረሱን ስርጭት መግራት ይቻላል፡፡ መነሻቸው ከእውነትና ከእውቀት ነው። መድረሻቸው ደግሞ በሰዎች ጥረት ይወሰናል።
በሌላ በኩል፤  የዘፈቀደ ጭፍን መነሻ አለ።
አደጋዎችንና ፈተናዎችን አሳንሶ ማሳየት፤ ወይም ማጋነን፣… ከእውቀት ጋር መራራቅ፣  ከእውነት ጋር መጣላት ነው። ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን የማሳጣት አባዜ የተጠናወተው ሲኤንኤን፤ “አንድ ሚሊዮን አውቶማቲክ የትንፋሽ መሳሪያ (ቬንትሌተር)” ዛሬውኑ ካልወለዳችሁ እያለ ሲጮህ እንደነበረ አስታውሱ።
በአንድ ጊዜ አንድ ሚሊዮን ሰዎች ህመም የሚፀናባቸውና “ቬንትሌተር” የሚያስፈልጋቸው ከሆነ፤ … በዚያው ወር ስንት መቶ ሺ ሰው እንደሚሞት አስቡት። ከእውኑ ዓለም በእጅጉ የተራራቁ እንዲህ አይነት ትንበያዎች አሉ።
በአንድ ወር ውስጥ፤ ቢያንስ ቢያንስ ከ20 እስከ 30 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ ካልተያዙ በስተቀር፤ “ሚሊዮን ቬንትሌተር” እያሉ መጮህ… ትርጉም የለውም።
በዚያ ላይ፤ እጅን አዘውትሮ መታጠብ፣ የግል ርቀትን ማክበር፣ ሰው በሚበዛበት ቦታ አፍና አፍንጫን መሸፈን እና ሌሎች የወረርሽኝ መከላከያ ዘዴዎች፤ አንዱ ጥቅማቸው የታማሚ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ ነው።
ለማንኛውም፣ አደጋዎችን አሳንስ ወይም አግንኖ ለማሳየት መሞከር፣ ቀሽምነት ነው። ነገር ግን ሌሎች አይቀሬ የትንበያ ስህተቶች አሉ። ለቫይረሱ የመጋለጥና የማስተላለፍ አደጋ፤ ከቦታ ቦታ፣ ከእድሜ እድሜ፣ ከአየር ፀባይና ከወቅት ጋር ምን ያህል እንደሚለያይ፤ በወጉ ካልታወቀ፤ የትንበያ ቁጥሮች ላይ ስህተት ጎልቶ ይወጣል። ካሁን በፊት፣ ኢትዮጵያን በሚመለከት፤ የተዘገቡ ትንበያዎችን ማስታወስ ይቻላል። እስከ ግንቦት መጨረሻ ድረስ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለቫይረሱ እንደሚጋለጡ የሚገልጽ ትንበያ ወጥቶ ነበር።
በእርግጥ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ፤ ከተጨማሪ መረጃና ከእውቀት ጋር፤ የትንበያ ቀመሮች ከስህተት እየፀዱ ይመጣሉ። እንዲያም ሆኖ፣ “የተሟላ እውቀት ላይ ደርሰናል” ካልተባለ በስተቀር፤ የትንበያ ቀመሮች፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ ሙሉ ለሙሉ ከስህተት አይገላገሉም። ግን ደግሞ፤ ፋይዳ የሌላቸው ማስመሰል፤ ሌላ ከባድ ቀሽምነት ይሆናል።
“ይሄኛው የትንበያ ቁጥር ስህተት ነው፤ ያኛውም ስህተት ነው” ብሎ በደፈናው ማጣጣል ምን ማለት ነው? “ሌላ ትክክለኛ የትንበያ ቁጥር እኔ ጋ አለ!” ለማለት ነው? “ሌላ የተሻለና ደረጃ የወጣለት የትንበያ ቀመር አለኝ” ለማለት ነው? ቢኖርማ እሰየው ነበር። አለበለዚያ ግን፣ በደፈናው የትንበያ ቁጥሮችን ከማጣጣል ይልቅ፤ የቀመሮቹን ፋይዳና ጉድለት፤ የትንበያ ቁጥሮችን ትርጉም፣ አንደምታና የስህተት ወሰን በቅጡ ለማብራራትና ለማስረዳት መጣር ነው የሚሻለው።


Read 3303 times