Print this page
Monday, 22 June 2020 00:00

አሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ስለ ትግራይ ወቅታዊ ፖለቲካ ምን ይላል?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

     • ከወረርሽኙ ጎን ለጎን ምርጫ በጥንቃቄ ማካሄድ ይቻላል

        በትግራይ ክልል ገዢውን ፓርቲ በምርጫ ከሚፎካከሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ አንዱ ነው። የፓርቲው
ሊቀመንበር አቶ ዶሪ አስገዶም በክልሉ ስላለው ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ፣ የክልሉ መንግስት ለማካሄድ ስላቀደው ክልላዊ ምርጫ፣ በምርጫው መራዘም ዙሪያ ሀሳባቸውን ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አጋርተውታል።

                የአገራዊ ምርጫው መራዘምን በተመለከተ የፓርቲያችሁ አቋም ምንድን ነው?
ምርጫን በሚመለከት በመጀመሪያ ምርጫ ቦርድ፣ ምርጫን ማካሄድ አልችልም ብሎ የወሰነው በችኮላ ነበር። በጥናት ባልተደገፈበትና አሳማኝ ምክንያቶች ባልቀረቡበት ሁኔታ ነበር ውሳኔው የተላለፈው። ጉዳዩ ትንሽ ጊዜ ተሰጥቶት፣ ሁኔታው መገምገም ነበረበት። እርግጥ ነው ኮቪድ -19 እየጨመረ ነው። በዚህ ምክንያትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል። የምርጫው መራዘምም በፓርላማ ፀድቆ ህጋዊ ሆኗል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ላይ ግን ሁለት ነገሮች ለኛ ያሳስበናል፡፡ አንደኛው፤ ኮቪድ 19 ስጋት መሆኑ ከቀረ በኋላ ምርጫው እንደሚካሄድ ነው የሚያስቀምጠው። ይሄ ማለት ቁርጥ ያለ የሚታወቅ ቀን የለውም ማለት ነው። የአለም የጤና ድርጅትም ኮቪድ መቼ እንደሚቆም መገመት አልቻለም። ይህ በሆነበት ለማይታወቅ ጊዜ ምርጫው መራዘሙ ጥያቄ ይፈጥራል። ሕገ መንግሥቱን ለአደጋ የሚዳርግም ነው፤ ይህ እንዳይፈጠር በውሳኔው ላይ ገደብ መቀመጥ ነበረበት።
ወረርሽኙ የሚያበቃበት ጊዜ የማይታወቅ ከሆነ ምን አይነት ገደብ ሊቀመጥ ይችላል?
ወረርሽኙ የማይቋረጥ ከሆነ ቴክኖሎጂንም ቢሆን ተጠቅሞ ወረርሽኙ ሰዎችን እንዳያጠቃ አስፈላጊው ጥንቃቄ እየተደረገ ምርጫ ሊካሄድ የሚችልበት አማራጭ መቀመጥ ነበረበት። በዚህ መንገድ ገደብ ማስቀመጥ ይቻል ነበር። 6 ወር አይተን ከዚያ በኋላ በዚህ መልክ ምርጫው ይካሄዳል ሊባል ይችል ነበር። በሌላ በኩል፤ ምርጫው በሚካሄድበት ጉዳይ ላይ የፓርቲዎች ሀሳብ መደመጥ ነበረበት። ምክንያቱም ከመስከረም 30 በኋላ የገዥው ፓርቲ ስልጣን በሕገ መንግሥቱ ያበቃል። ይሄ በግልጽ የተቀመጠ፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም የማያሰጥ፣ ግልጽ የሆነ ጉዳይ ነው። ከመስከረም 30 በኋላ ምን ይሁን በሚለው ዙሪያ ከፓርቲዎች ጋር ተወያይቶ መወሰን ነበረበት።
ለምሳሌ የናንተ ፓርቲ አማራጭ ሃሳብ ምን ሊሆን ይችል ነበር?
በፓርቲዎች ውይይት የሚፈጠር የሽግግር መንግሥት መፍትሄ ነው ብለን እናምናለን። ሌላው አማራጫችን ደግሞ ከወረርሽኙ ጎን ለጎን፣ በጥንቃቄ ምርጫ መካሄድ ይቻላል የሚል ነው። ከእነዚህ ሁለቱ አማራጭ ውጪ ያለው ሌላው ነገር ሁሉ የሕገ መንግሥት መሰረት የለውም። አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከእነዚህ ውጪ ያሉትን እንደማይቀበሉ እንረዳለን።
ይህ በእንዲህ እንዳለ  የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የራሴን ምርጫ በነሐሴ አካሂዳለሁ ብሏል። ይሄን ውሳኔ ትክክል ነው ትላላችሁ?  
የትግራይ መንግሥት የወሰነው ውሳኔ ከሕጉ አንፃር ስናየው ክፍተት አለው ብለን አናስብም። በደንብ መታየት ያለበት ነገር ግን፣ የክልሉ ምርጫ ሲደረግ በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ፍቃድ ወይም አስፈጻሚነት መሆን አለበት። በሕገ መንግሥቱም ምርጫ በብቸኝነት የማስፈፀም ስልጣን የተሰጠው ምርጫ ቦርድ ነው። በቂ ዝግጅት ሲያደርግ እንደነበረም አስታውቋል። ስለዚህ የትግራይን ምርጫ ማስፈፀም አይከብደውም ማለት ነው። የክልሉ መንግሥትም ጥያቄውን ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ነው ማቅረብ ያለበት። ምርጫው በስምምነት ቢካሄድ የተሻለ ነው። እኛም ብንሆን ምርጫው ተራዝሞ ከሕገ መንግሥት ውጪ የሆነ መንግሥት በስልጣን እንዲቆይ አንፈልግም። ስለዚህ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የትግራይ ክልል ጥያቄን ተቀብሎ ምርጫ የሚካሄድበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለበት።
በትግራይ ክልል ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ አለ ብላችሁ ታምናላችሁ?
እርግጥ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠባብ ነው፡፡ ሚዲያውም የአንድ ወገን ነው፤ ነገር ግን እኛ ምርጫ ይካሄድ ስንል ያለ ምርጫ በሥልጣን ላይ የሚቆይ መንግሥት እንዳይኖር ነው። ምርጫው እንዲካሄድ የምንፈልገው ከዚህ አንፃር ነው።
ምርጫ ቦርድ፤ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተጣለበትና የኮሮና ወረርሽኝ እየተስፋፋ ባለበት ሁኔታ ምርጫውን ማድረግ አይቻልም በሚል ጥያቄውን ባይቀበልስ?
ክልሉ የራሱን ምርጫ አስፈፃሚ ማደራጀት ይችላል። ሕገ መንግሥቱም ይሄን አይነት የምርጫ አስፈጻሚ ማቋቋምን አይከለክልም።
ግን እኮ በአገሪቱ ምርጫን የማስፈፀም ብቸኛ ስልጣን በሕግ የተሰጠው ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ነው…
ትክክል ነው፤ ነገር ግን አንድ ክልል ምርጫ ማድረግ እፈልጋለሁ የሚል ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ ካጣ፣ የራሱን አስፈፃሚ ከማደራጀት የሚከለክለው ሕግም በሕገ መንግሥቱ አልተቀመጠም። በሌላ በኩል፤ በአሁኑ ወቅት ሁሉም ወገን ሕገ መንግሥቱን መሰረት አድርጎ አይደለም ያለው። ከዚህ አንፃር ላንዱ ሕገ መንግሥት መጣስ የሚፈቀድበት፣ ለሌላው የሚከለከልበት ሁኔታ አይኖርም። ሕገ መንግሥቱ ተጥሷል ብሎ ክልሉ ካመነ፣ የራሱን መብት ተጠቅሞ መወሰን ይችላል።
የክልሉ መንግሥት ራሱ እየመራው በሶስት ወር ውስጥ በትግራይ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል የሚል እምነት አላችሁ? በዚህ ምርጫስ ትሳተፋላችሁ?
እሱን የሚወስነው ሂደቱ ነው። መጀመሪያ መሰራት የሚገባቸው ብለን የምናስቀምጣቸው መስፈርቶች አሉ። እነሱ ከተሟሉ እንሳተፋለን። ምክንያቱም ምርጫ እየተካሄደ እኛ ወደ ኋላ የምንቀርበት ምክንያት አይኖርም። የተመሰረትነው በምርጫ ለመሳተፍና አሸንፈንም መንግስት ለመሆን ነው።
ምንድን ናቸው እነዚያ መስፈርቶቹ?
ምርጫው ነፃና ፍትሀዊ፣ በሕዝቡ ተአማኒ መሆኑን መጀመሪያ ማረጋገጥ እንፈልጋለን። ይሄን ለማረጋገጥ ደግሞ አንደኛ በምርጫ ቦርድ የሚመራ መሆኑ ነው። በምርጫ ቦርድ የሚመራ ከሆነ ችግር የለውም፤ ያለ ምንም ማቅማማት እንሳተፋለን። ቦርዱ ካልፈቀደና በክልል ደረጃ የሚቋቋም ቦርድ ካለ ደግሞ ገለልተኛና ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ መሆኑን ማረጋገጥ እንፈልጋለን።
ገለልተኝነቱን እንዴት ነው የምታረጋግጡት?
ሁሉም የፖለቲካ ሀይሎች ቦርዱን በማቋቋም በኩል በበቂ ውክልናና ድምፅ መሳተፍ አለባቸው። በዚህ መንገድ ወገንተኛ ያልሆነ የክልል ምርጫ ቦርድ ማቋቋም አይከብድም። ይሄ ቦርድ በሚዲያ አጠቃቀምና በምርጫው ሂደት ረገድ የሚያስቀምጣቸው ነገሮች ወሳኝ መስፈርቶቻችን ናቸው።
ህወኃት በክልሉ ድጋፍ ለማሰባሰብ የቻለው “የትግራይ ሕዝብ በጠላቶች የተከበበ የህልውና ስጋት እንደተደቀነበት በማስመሰል ነው” የሚሉ አስተያየቶች ይቀርባሉ፡፡ የእናንተ ፓርቲ የትግራይ ሕዝብ የሕልውና ስጋት ተደቅኖበታል የሚል እምነት አለው? በዚህ ላይ ያላችሁ አቋምስ ምንድን ነው?
ከፍተኛ ስጋት ውስጥ የሚያስገባ አደጋ ተደቅኖበታል ብለን አናስብም። ነገር ግን አንዳንድ ከፌደራል የማይጠበቁ ነገሮች ይሰነዘራሉ።
ለምሳሌ?
ለምሳሌ በቅርቡ ጠ/ሚኒስትሩም ሆኑ ሌሎች የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች፣ የትግራይ ክልል ምርጫ ካደረገ እርምጃ እንወስዳለን ብለዋል። ማን ላይ ነው እርምጃ የሚወስዱት? ይሄን ያሉት የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ መሪ ናቸው። ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይም ይሄን ሀሳብ የሚያጠናክር ነገር ብለዋል፡፡ ይሄ ህዝቡ ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገባ አድርጐታል።
እርምጃ መውሰድ ከሕዝቡ ጋር እንዴት ይገናኛል? ሕግን ለማስከበር በሚል ህወኃት ላይ እርምጃ ቢወሰድ ሕዝቡ ላይ እርምጃ ተወስዷል ማለት ነው?
ታዲያ ምን ማለታቸው ነው? ለምን ግልጽ አያደርጉትም? ዝም ብሎ እርምጃ እንወስዳለን ማለት ለሕዝቡ የሚሰጠው ትርጉም “ሊያጠፉን እየመጡ ነው እንዘጋጅ” የሚል ነው።
እናንተ ህወኃት እና ህዝቡ አንድ ነው ብላችሁ ነው የምታምኑት?
እኛ ህወኃትና ሕዝቡ የተለያዩ ናቸው ብለን ነው የምናምነው። ነገር ግን እርምጃ እንወስዳለን ሲባል ማን ላይ ነው የሚለው ግልጽ መሆን ነበረበት፡፡ የሚወሰደው እርምጃ ማን ላይ እንደሆነ ግልፅ ስላልሆነ ነው ጥርጣሬ የተፈጠረው። እርምጃ እንወስዳለን ሲባል፣ ሕዝቡ ላይ ነው ፓርቲው ላይ ነው የሚለው ግልጽ አይደለም።
አንድ መንግሥት በጅምላ ሕዝብ ላይ እርምጃ ይወስዳል ብላችሁ ታስባላችሁ?
እኛ እንደዚያ ብለን አናስብም። ግን በግልጽ ካልቀረበ ለፕሮፓጋንዳ ምቹ ነው። እዚህ ላለው ነገር ምቹ ይሆናል። እኛም የፌደራል መንግስቱ እንዲህ ያለ ነገር በተናገረ ቁጥር ምንድን ነው እያለ ያለው ብለን እናስባለን። እንዲያም ሆኖ መንግስት ወደ ሕዝቡ ይተኩሳል ብለን አናስብም። ነገር ግን እርምጃ ሲባል ምን አይነት? ማን ላይ? የሚለው በግልጽ መቀመጥ አለበት። በሌላ በኩል፤ የትግራይ ተወላጆች አሳማኝ ባልሆነ መንገድ መታሰር፣ እንዲህ ያለው ጥቃት ሊደርስብን ይችላል የሚል ጥርጣሬን ያጭራል። ስለዚህ ሕዝቡ ስጋት ላይ ሊወድቅ ይችላል። በሌላ በኩል ህወኃት አሁን በሚመራው ክልል ሰላም መኖሩን መዘንጋት የለብንም።
የዚህ የሰላም ምንጭ ምንድን ነው ትላላችሁ?
ሕዝቡ ነው። የትግራይ ሕዝብ ሰላም ይወዳል። እኛም የምናደንቀው ትግራይ ላይ ሰላም መሆኑን ነው። አንድ መንግሥት ከሁሉም በፊት በሚመራው ክልል ሰላምን ማስፈን አለበት። ሰዎች እንደ ልባቸው ወጥተው የሚገቡበትና የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ መፍጠር ይኖርበታል።
ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ደግሞ ሰላሙ “የተጠናከረ አፈና የፈጠረው ነው” ይላሉ…
እዚህና ሌላው ክልል ከዚህ አንፃር የአተያይ ልዩነት ይስተዋላል። የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ረገድ ምንም የተሰራ ነገር የለም። ህወኃትም “እኔ ብቻ ነኝ ስልጣን መያዝ ያለብኝ” የሚል አቋሙን አልቀየረም። በፓርቲዎች እንቅስቃሴ በኩል ብዙ የሚቀር ነገር አለ። ሕዝቡ ግን ለሰላም የቆመ ነው፤ የሰላሙ ምንጭ ራሱ  ሕዝቡ ነው፡፡ በገዥው ህወኃት በኩል የሚደረገው ነገር ግን ጥሩ አይደለም።
ሰሞኑን የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች የሽምግልና ጥረት ህወኃት ባስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች የተነሳ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ህወኃት ያስቀመጣቸውን ምክንያቶች እንዴት ታዩታላችሁ?
እንዲህ ያለው ጉዳይ በጋራ መድረክ ይፈጸም ማለቱ ተገቢ ነው። እኛም ስንጠይቀው የነበረ ነው። በአጠቃላይ የሁሉም አካላት የጋራ ድርድርና ውይይት ነው የሚያስፈልገው። በዚያው ልክ ግን ህወኃትና ብልፅግና ጠባቸውን ለብቻቸው መፍታትም አለባቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ሌሎቻችንም ያለንበት የጋራ ድርድርና ውይይት ነው መካሄድ ያለበት። ሌላው የኤርትራና ኢትዮጵያ ግንኙነት ጉዳይ ነው፤ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ብቻ መገናኘታቸው ብዙ ጥርጣሬን ያጭራል። እኛም በዚህ በኩል ጥርጣሬና ስጋት አለን። በሁለቱ አገራት መካከል የሚደረጉ ማናቸውም ግንኙነቶችም ሆኑ ስምምነቶች ለሕዝብ ይፋ መደረግ አለባቸው። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ እኛም ጥያቄ አለን።
በአጠቃላይ በክልሉ ለሚታየው ፖለቲካዊ ችግሮችና አለመግባባቶች መፍትሄው ምንድን ነው ትላላችሁ?
በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ችግሮች ስላሉ፣ ሁሉንም ያካተተ ውይይት ቢደረግና ብልጽግናም ሁሉንም በራሴ አደርጋለሁ የሚለውን ትቶ፣ ወደዚህ አይነቱ መድረክ ቢመጣ ጥሩ ነው። በፖለቲካ ሳቢያ የታሰሩ ሰዎችም መፈታት አለባቸው። በአጠቃላይ መፍትሄው የተደራጀ እውነተኛ የውይይት ሂደት መጀመር ነው።


Read 9405 times