Saturday, 20 June 2020 12:06

በተስፋና ተግዳሮቶች የተከበበው የሱማሌ ክልል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  የሶማሌ ክልላዊ መንግስት የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ሆነው ከተሾሙ ገና አንድ ወራቸው ነው፡፡ አቶ አሊ በደል መሐመድ ይባላሉ፡፡ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በአንትሮፖሎጂ ከጐንደር ዩኒቨርስቲ፣ ሁለተኛ ድግሪያቸውን በኢጁኬሽናል ሊደርሺፕና ማኔጅመንት ከሃሮማያ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል፡፡ ላለፉት 10 ዓመታት መንግስታዊ ባልሆኑ ዓለምአቀፍ ተቋማት ውስጥ ሰርተዋል፡ የአዲስ አድማሷ ናፍቆት ዮሴፍ ከኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው ጋር በክልሉ ፖለቲካዊ፣ ልማታዊና የኮቪድ ወረርሽኝ ዙሪያ እንዲህ አነጋግራቸዋለች፡፡


             እንዴት ነው ወደ ክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊነት የመጡት? አዲሱን ሃላፊነትስ እንዴት አገኙት?
እኔ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ፣ የአገሬን አጠቃላይ ሁኔታ በቅርበት እከታተላለሁ፡፡ በተለይ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በነበርኩበት ጊዜም፣ የሶማሌ ተማሪዎች ሀላፊም ነበርኩኝ። ከዚያ ደግሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ሕብረት የኮሚቴ አባልም ነበርኩ። የሶማሌ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ሶዴፓ) ውስጥም ተማሪ ሆኜ በአባልነት እንቀሳቀስ ነበር። ተመርቄ ወደ ጅግጂጋ ከተመለስኩ በኋላ በሶማሌ ክልል መንግሥት “የጎረቤት አገር የግጭት አፈታት ቢሮ” የመንግሥት ሰራተኛ ሆኜ ለዘጠኝ ወር አገልግያለሁ። ቢሮው በሶማሌና በኦሮሚያ እንዲሁም በሶማሌና በአፋር አካባቢ ድንበር ላይ የሚሰራ የመንግሥት ቢሮ ነው። ከዚያ ወጥቼ ነው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ የሰራሁት፡፡ DFID ውስጥ ሆኜም የአገሬን ፖለቲካና አጠቃላይ ሁኔታ በንቃት እከታተል ነበር።
በዚህ ሁኔታ ላይ እያለን የአገራችን ፖለቲካ ተለወጠና መልኩን ቀየረ። ከግጭት ወጥቶ የማያውቀው የሶማሌ ክልል ውስጥ በተለይ ለወጣት ምሁራን ማራኪ የሆነ ድባብ ተፈጠረ። የአገራችንም የክልላችንም ሁኔታ ሲለወጥና ተስፋ ሰጪ ሲሆን ፕሬዚዳንት ሙስጠፌም፤  የክልሉ ምሁራን ከያሉበት መጥተው ክልላቸውንና ሕዝባቸውን እንዲያገልግሉ ጥሪ አቀረቡ። ጥሪ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ሁኔታዎችንም አመቻቹ፡፡ እኔም እንደ ክልሉ ተወላጅ በዚያ አካባቢ ለበርካታ አመታት የነበረውን የክልሉንና የሕዝቡን አጠቃላይ ችግር ስለማውቅ፣ አቅም በፈቀደ ለማገልገል ከአንድ ወር በፊት የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ሆኜ ሥራዬን ጀምሬያለሁ። ገና በአንድ ወር ውስጥ እንዲህ ነው ለማለት ቢከብድም፣ ሀላፊነቱን ተቀብዬ እየሰራሁ ነው፤ ብዙ እንደሚጠበቅብኝም አምናለሁ።
ክልሉ ነዳጅን ጨምሮ እምቅ ሀብትና አቅም እንዳለው ቢታወቅም፣ በግጭትና በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ የሚጠበቅበት እድገት ላይ አልደረሰም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
እውነት ለመናገር እንዳልሽው ክልሉ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት አለው። በእርሻም በወንዞችም ሆነ በነዳጅ ሀብት ገና ያልተነካና ያልተጀመረ ሥራ አለ ብዬ አምናለሁ። ይህንን ሥራ ለመስራትና ክልሉንና ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተማረ የሰው ሀይል ያስፈልጋል። እንደሚታወቀው አገርን የሚለውጠው ሰው ነው፤ አገር ዝም ብሎ አይለወጥም። አሁን በክልሉ አመራር ላይ የሚገኙት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያየ ዘርፍ የተመረቁ፣ በውጭ አገር የነበሩ ምሁራንና እውቀት ያላቸው ሰዎች ናቸው:: እኔም  ከነዚህ ውስጥ አንዱ ነኝ ማለት እችላለሁ። ብቻዬን አገር እለውጣለሁ ባልልም፣ ከእነዚህ ጓደኞቼ ጋር ሆኜ የበኩሌንና የምችለውን በማድረግ በትብብር የክልሉን እድገትና የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የመስራት ዕቅድ አለኝ፡፡ አሁን ላይ በክልሉ ብዙ ተስፋም አለ፡፡ አንደኛው ተስፋ የሚሰጠው፤ የክልሉ ፖለቲካዊ መረጋጋት ነው። ሁለተኛው የተማረ ሰው በሀላፊነት ቦታ ላይ መቀመጡ ሲሆን ሶስተኛው፤ የክልሉ ተወላጅ ዲያስፖራዎች በአካባቢው ኢንቨስት ለማድረግ እየመጡ መሆናቸው ነው። ይህን ስመለከት በጣም ብዙ ተስፋና ለውጥ እንደሚመጣ እጠብቃለሁ፡፡ አሁን ሁሉም ነገር ጥሩ እየሆነ ነው።
እርስዎ በሀላፊነት በተመረጡበት የክልሉ 10ኛ መደበኛ የምክር ቤት ጉባኤ ላይ በሀሳብ ልዩነት ስብሰባውን ረግጠው የወጡ አባላት ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ገልፀዋል:: እርስዎ በቦታው ላይ ስለነበሩ እስኪ የተፈጠረውን ይንገሩኝ?
እንዳልሽው በዕለቱ በዚያ ስብሰባ ላይ ነበርኩኝ። እንደሚታውቀው፤ ብዙ ጊዜ ሰዎች የራሳቸውን ፍላጎት ለማስፈፀም መሰረት የሌለው ወሬ ይነዛሉ። በዕለቱ ስብሰባው በሰላም ነበር የተጀመረወ። አፈ ጉባዔዋ የእለቱን አጀንዳ ለታዳሚው ካቀረበች በኋላ አጀንዳው ተቀባይነት አገኘ። ሁለተኛ አጀንዳ ላይ ውይይት እየተደረገ ሳለ በቡድን የተሰበሰቡ ሰዎች መጮህ ጀመሩ። እነዚህ ቡድኖች መጀመሪያውኑ ችግር ለመፍጠር ሆን ብለው አንድ ቦታ ተቀምጠው የተዘጋጁ ነበሩ። ስለዚህ ስብሰባውን ረግጠው እየጮሁ ወጡ፤ በእርግጥ ጥቂት ሰዎች ነበሩ።
ምን ያህል ናቸው ስብሰባውን ረግጠው የወጡት?
27 ገደማ ናቸው። እንግዲህ በስብሰባው ከተሳተፉት ከ180 በላይ ሰዎች መካከል ነው እነዚህ ሰዎች ረብሸው የወጡት። እነዚህ ሰዎች ከዚህ ቀደም በክልሉ ፓርላማ ውስጥ የነበሩና ከአብዲ ኢሌ ጋር ሲሰሩ የነበሩ ናቸው። እነዚህ ሰዎች የወረዳ ኃላፊ እንዲሁም በምክትል ቢሮ ኃላፊነት ያገለገሉም ናቸው። ጥያቄ ካላቸው በዴሞክራሲያዊ መንገድ መጠየቅ ነበረባቸው። በረብሻና በጉልበት የሚሆን ነገር የለም። ጊዜው ያለፈበት አካሄድ ነው የተከተሉት። ስብሰባ ረግጠው ከወጡ በኋላ ሕዝቡን ለማነሳሳትና ለማሳመፅ ሙከራ አድርገው ነበር። ገና የመንግሥት አካላት በአካባቢው ሳይደርሱ፣ ከሕዝብ ጋር ነበር የተጣሉት። ፓርላማ እንዲህ እየተካሄደ ነው ብለው ሲጮሁ ሕዝቡ “እናንተ ውሸታሞች፤ ሰላም እንፈልጋለን ሂዱ ከዚህ” ብሎ ነው ያባረራቸው፡፡ የእነሱ አላማ ፓርላማውን ረብሸው ወጥተው ህዝብ በመቀስቀስ ስብሰባው እንዳይካሄድ ለማወክ ነበር፤ ግን አልተሳካላቸውም። ህዝብም አልተቀበላቸውም፡፡
ሰዎቹ ምን እንደሚፈልጉ በፓርላማው ገልፀው ነበር?
እነዚህ ሰዎች ካለፈው ስርዓት ተጠቃሚ ነበሩ፤ ያንን ጥቅም አሁን አጥተዋል፤ እውነታው ይሄው ነው፡፡ አሁን ሙስና የለም፤ ፓርላማው ግልጽ ውይይት ያደርጋል:: መነጋገር ይቻላል፡፡ አሁን አስፈፃሚው አካል ፓርላማውን ጠርቶ የሚጠይቅበት ግልጽ የሆነ አሰራር ተዘርግቷል፡፡ በፊት ይህ አይነት አሰራር አልነበረም፡፡ ከዚህ በላይ ምን ይምጣ፡፡ ስብሰባው ክፍት ነው፤ መወያየት መነጋገር ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፡፡ ረብሻንና ሁከትን ምን አመጣው?! ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ሌላ የግል ፍላጐትና አጀንዳ አላቸው ማለት ነው፡፡
ከነዚህ ሰዎች መካከል በዕለቱ ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳም እንዳለ ተነግሯል…
አዎ የ12 ሰዎች ያለመከሰስ መብት ተነስቷል፡፡ ህዝብን ለማነሳሳትና ረብሻ ለመፍጠር ሲሞክሩ እጅ ከፍንጅ የተያዙ ሰዎችም ታስረዋል፡፡ አንድ ሶስት ያህሉ ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ ነው ያለው፡፡ ሌሎቹ ከእስር ተፈትተዋል፡፡
አንዳንዶች፤ በክልሉ ከወሬ ያለፈ ለውጥ አልመጣም፤ አሁንም ሙስና አለ፤ እንደውም በክልሉ ከ36 ቢ. ብር በላይ በአዲሱ አመራር ተዘርፏል” እየተባለ ይወራል፡፡ እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
እንግዲህ አንድ ሰው ወይም አካል ለለውጥ ሲሰራ አደናቃፊና ስም አጥፊ አይጠፋም:: ይህንን አፋቸውን ሞልተው የሚናገሩ ሰዎች፤ በክልሉ እየተሰራ ያለውን ልማት በየወረዳው የሚሰራውንና የሚታየውን ለውጥ ሄደው አላዩም ወይም ስለ ለውጡ ማውራት አይፈልጉም፡፡ ብቻ የስም ማጥፋትና የመወንጀል ሥራ ሆን ተብሎ ይሰራል፡፡ እውነቱ ግን በጣም በሚገርም ሁኔታ፣ በየዞኑና በየወረዳው በርካታ መሰረተ ልማቶች ተገንብተዋል፡፡ ለምሳሌ ድልድይ፣ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ፣ መንገድና ሌሎችም በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ በመጀመሪያ እንደዚህ እያሉ ለሚያወሩትና ለሚያስወሩት ጥያቄ ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ ስለምታወሩት ነገር በደንብ ታውቃላችሁ ወይ? በክልል፣ ዞንና ወረዳ ደረጃ እየተሰራ ያለውን ልማት ተመልክታችኋል ወይ? ይህን ከማለታችሁ በፊት እስኪ ክልላችሁን ጐብኙ፣ እዩና ከዚያ ሙስና አለ ተዘረፈ በሉ፡፡ እኔ ለምሳሌ ጅግጅጋ ተቀምጬ፣ ጐንደር ተዘረፈ ካልኩ፣ ይሄ ትክክል አይደለም፡፡ ሰው ቢያወራልኝ እንኳን በአይኔ አይቼ በተጨባጭ ማስረጃ አስደግፌ ማውራት አለብኝ፡፡ እውነቱን ለመናገር አሁን በክልሉ ሙስና አለ እያሉ የሚያወሩ ሰዎች፣ ትላንት በስልጣን ላይ ሆነው እነሱ ሲያደርጉት የነበረውን ነው የሚያወሩት፡፡ ድክመታቸውን፣ የእነሱን ችግር ለመሸፈን፣ “ሙስና አለ” እያሉ እያወሩ፣ የክልሉን ሰላምና መረጋጋት ለማደፍረስ ቀን ከሌት ይተጋሉ፤ ግን በክልሉ ህዝብ ዘንድ በአይን የሚታይ በእጅ የሚዳሰስ ሰላም መረጋጋትና ልማት አለ፡፡ አሁን ላይ የክልሉን ሰላም መንግስት ብቻ አይደለም የሚጠብቀው፤ ራሱ ህዝቡ ከመንግስት ጋር በመሆን ይጠብቃል፡፡  ህዝቡ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ለመንግስት ያሳውቃል፡፡
ለምሳሌ ክልላችን ከፑንትላንድና ከሶማሌ ጋር ወደ 800 ኪ.ሜ ገደማ ድንበርተኛ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ድንበር ላይ ወታደር የለም፡፡ ህዝቡ ነው ሰላሙንና ድንበሩን የሚጠብቀው፡፡ የሱማሌ ህዝብ ባለፉት 27 አመታት በግጭትና በችግር ተዳክሟል:: ልማትም አላገኘም፡፡ ለውጡ ከመጣ ከሁለት ዓመት ወዲህ ህዝቡ የሰላምን ዋጋ በእጅጉ እያጣጣመና ሰላም በጣም ውድ ነገር መሆኑን ተገንዝቦ፣ ይህ ውድ ነገር ከእጁ እንዳይወጣ አጥብቆ እየሰራ ነው፡፡ እናንተም እንደ ሚዲያ የሚወራው ነገር እውነት ነው አይደለም ብላችሁ፣ መሬት ላይ ያለውን ነገር በቦታው ላይ ተገኝታችሁ ማየትና ማረጋገጥ አለባችሁ፡፡
በክልሉ በ2010 ዓ.ም መጨረሻ ላይ በተፈጠረ ግጭት በሰው ህይወት፣ በእምነት ተቋማትና ንብረት ላይ ጥፋት ደርሷል፡፡ በተለይ ችግሩ የደረሰው የክልሉ ተወላጅ ባልሆኑ ወገኖች ላይ ነበር፡፡ እነዚህን ዜጐች የክልሉ መንግስት ለመካስም 100ሚ. ብር መመደቡ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን አሁንም እነዚህ የክልሉ ተወላጅ ያልሆኑ ሰዎች ስጋት እንዳላቸው ይገልፃሉ፡፡ እነሱን የሚያጥላላ የጥላቻ ቪዳዮ እየተለቀቀ መሆኑንም ይገልፃሉ፡፡ ስለዚህ የሚያውቁት ነገር አለ?
እንደተባለው በተገለፀው ጊዜ የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፣ የሃይማኖት ተቋማትና ብዙ የንግድ መደብሮች ወድመዋል፡፡ የሃይማኖት አባቶች ሳይቀሩ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ የክልሉ መንግስትም በደረሰው ነገር በእጅጉ በማዘን የአቅሙን ድጋፍ አድርጓል፡፡ ከለውጥ በኋላ መንግስት ሁሉንም የሰላም ሁኔታ አረጋግጧል፡፡ ከዚያ በኋላ የክልሉ ተወላጅ ያልሆኑ ኢትዮጵያዊያን በሰላም እየሰሩ፤ ከተማዋንና ክልሉን የራሳቸው አድርገው፣ ያለ ችግር እየኖሩ እንደሆነ ነው የማውቀው፤ ተለቀቀ ስለተባለው ቪዲዮም የማውቀው ነገር የለም፡፡
የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፌ መሐመድን ጨምሮ ሌሎች አመራሮችም ህወሓት በእጅ አዙር በክልሉ ጉዳይ ጣልቃ ትገባለች ሲሉ ይደመጣል፡፡ እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
በሱማሌ አንድ አባባል አለ፡፡ ሱማሊኛ የምትችይ ቢሆን በደንብ ይገባሽ ነበር፤ ግን በአማርኛ ልሞክር፡፡ አንዲት እንስሳ አለች፤ ሁሌ እየሄደች እንደ ልቧ የምትመገበው ሳርና ቅጠል ቅጠል የምታገኝበት እሷ ብቻ የምታውቀው ቦታ አለ፡፡ ይህቺ እንስሳ እዛ ቦታ ሁሌ እየሄደች እንደ ልቧ ትበላለች:: በአጋጣሚ በአየር ንብረት ለውጥ፣ ያ የለመደችው እንደልቧ የምትበላው ሳርና ቅጠል ይደርቃል፡፡ ነገር ግን ተስፋ ሳትቆርጥ ከዛሬ ነገ ሳር አገኛለሁ እያለች ትመላለሳለች ትሄዳለች ግን ያ ሳር የለም፡፡ ይህንን ያነሳሁት ያለምክንያት አይደለም፡፡ ከዚህ በፊት ክልላችን የተወሰኑ ቡድኖች የሚጠቀሙበት ህዝብ የሚቸገርበት ነበር፡፡ አሁን እነዛ ቡድኖች ያ ጥቅም ዳግመኛ ይገኛል ብለው ይመላለሳሉ፤ በእጅ አዙር ክልሉን ለመበጥበጥ ይመላለሳሉ፤ ያ የሚዘረፍ ገንዘብ ተመልሶ አይገኝም፤ በትክክል ህወሓት እንዲህ አደረገ የሚባል ነገር ባይኖርም፤ በእጅ አዙር ክልሉን ለማወክ የሚሰሩ የቀድሞ ተጠቃሚ ሃይሎች እንዳሉና ያንን ጥቅም ለመመለስ እንደሚታትሩም እናውቃለን፡፡ ሴራውም ይገባናል፤ ነገር ግን ያ ሳር ዛሬ የለም፤ ደርቋል፤ እንደዛች እንስሳ ተስፋ ያለመቁረጥ መመላለሱ ግን ቀጥሏል፤ ይሄንን ነው ማለት የምችለው፡፡
ስለዚህ ባለፉት 27 ዓመታት ለህዝብ እንሰራለን ተብሎ የክልሉ ሀብት ከሰሜን እስከ ምስራቅ ሲዘረፍ ነበር፤ ይሄንን ማንም የሚያውቀው ነው፡፡ አሁን ላይ ለህዝብ የሚሰራ መንግስት፣ ለልማት ቆርጦ የተነሳ አመራር ሲመጣ፣ ያንን ለማደናቀፍና ችግር ለመፍጠር የሚሞክሩ አይሳካላቸውም:: ህዝቡም በቅቶታል፤ የሚጠቅመውን ያውቃል አለቀ፡፡ እኛ ቁርጠኝነት ስላለን ሁሉን ተቋቁመን እንሰራለን፡፡
የክልሉ መንግስት በአሁኑ ወቅት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ያለው በምን ጉዳይ ላይ ነው?
እንደ መንግስት አሁን ላይ ቅድሚያ ሰጥተን እየሰራን ያለነው ተቋማዊ ግንባታ ላይ ነው፡፡ ይሄ ምን ማለት መሰለሽ… የክልሉን መንግስትና አሰራሩን ለማጠንከር ተቋማዊ አሰራርና ሥርዓት ወሳኝ ነው ብለን እናምናለን፡፡ እንደነገርኩሽ ክልሉ ላይ በአመራር ደረጃ ያለን ሰዎች የተማርን ነን:: እያንዳንዱ አመራር አሰራሩን በማዘመን ተቋማዊ ቅርጽ ሰጥቶ ሥራውን አጠንክሮ መስራት ስላለበት፣ ተቋማዊ ልማትና ግንባታ ወሳኝ ነው፡፡ ስለዚህ ለዚያ ቅድሚያ ሰጥተን እየሰራን ነው፡፡ ተቋማዊ ግንባታው ሲጠናከር፣ የስራው ፍሰትና ሥርዓት ሁሉ ከግለሰቦች ትከሻ ላይ ይነሳና ተቋሙ ላይ ይሆናል፡፡ ከዚያ ለህዝቡ አገልግሎት በሚሰጥበት ጊዜ ቀልጣፋ ይሆናል፡፡ የውሃ፣ የጤና፣ የልማት ጥያቄው ምላሽ ያገኛል:: አሁን ክልሉ በፖለቲካው በኩል ከፍተኛ መረጋጋት ላይ ነው፡፡ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ከወረዳ ጀምሮ ያሉት ላይ የአቅም ግንባታ ሥራ እየሰራን ነው፡፡ በተጨማሪም ለሶማሌ ወጣቶች በስፋት የስራ እድል እየተፈጠረላቸው ነው፡፡ አሁን ላይ ብዙ የክልሉ ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
በሌላ በኩል ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፤ በርካታ መሰረተ ልማቶች ተሰርተዋል፡፡ በዚህ ዓመት ሰባት ያህል አዳሪ ት/ቤቶች ለአርብቶ አደር ልጆች ለመክፈት ግንባታ ተጀምሯል፡፡ ትልልቅ ፎቆች ናቸው፡፡ ብዙ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ተሰርተዋል:: በአጠቃላይ አሁን ክልሉ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ በልማቱም በፖለቲካ መረጋጋቱም በአመራሩም በንግድ እንቅስቃሴም ቢሆን፤ ሁሉም መስመር ይዞ እየሄደ ነው፡፡ ከአፋርና ከኦሮሚያ ጋር በፊት ግጭት ነበር፤ አሁን ሰላም ሰፍኖ ወንድማማች ህዝቦች እንደ ልብ እየተንቀሳቀሱ ይገበያያሉ፤ ይህንን ሁሉ ስንመለከት ተስፋችን ትልቅ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ባለፈው አንድ ወር ውስጥ እንኳን ሁለት ትልልቅ ዓለም አቀፍ ሆቴሎችና ነዳጅ ማደያዎችም ተከፍተዋል:: በጅግጅጋ ከተማ ውስጥ ዲያስፖራውም ኢንቨስት ማድረግ ጀምሯል፤ ይሄ ሁሉ ለውጡ ባመጣው ፖለቲካዊ መረጋጋት እውን የሆነ ነው፡፡ ሌላው ቢቀር እንደነ ኦብነግና ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ያለ ምንም ችግር እየተንቀሳቀሱ የሚገኙበት ሰላማዊ ክልል በመሆኑ ነው፤ አብዝቼ ተስፋ አለ የምልሽ፡፡
በክልላችሁ የኮሮና ወረርሽኝ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱና አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ እየተነገረ ነው፡፡ ስርጭቱን እንዴት መቆጣጠር አቃታችሁ? በምን ምክንያት ነው?
ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ እንግዲህ በአሁኑ ወቅት በክልላችን ብቻ ሳይሆን በአገርም በአህጉርም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ፈተና የሆነው የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ነው፡፡ በተለይ በሀገራችንም ብዙ ጫና እየፈጠረብን ያለ ወረርሽኝ ነው፡፡ በክልላችን በሽታውን ለመቆጣጠር ትልቅ ፈተና የሆነብን ከሶማሊያ ጋር ያለን ረጅም የድንበር ግንኙነት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሶማሊያ የሚመጡ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ከአቅም በላይ እየሆነብን ነው፡፡
አገራቸው ነው አትምጡ አይባልም። ነገር ግን ከክልሉ አቅም ጋር ሊመጣጠን አልቻለም፡፡ ሰዎች ሲመጡ ቦታ ሎጀስቲክ ያስፈልጋል። ውሃ፣ ምግብና መሰል አቅርቦቶች ያስፈልጋሉ። ላለፉት ሁለት ወራት ፈተና የሆነብን ይሄ ነው። በየቀኑ የሚገቡት ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ ነው።
ወደ ክልሉ ስንት የመግቢያ በሮች አሉ? ምን ያህል የለይቶ ማቆያና ሕክምና መስጫ ማዕከላት ተዘጋጅተዋል?
ወደ ክልሉ መግቢያ 21 ያህል በሮች አሉ:: ለይቶ ማቆያዎች ቶጎ ውጫሌ ላይ አለ፣ አውበሬ ወረዳ ላይ አለ። ዋርደር ዞን አለ:: ዋርደር ሶማሊያ ፑንትላንድ የሚገኝ ቦታ ነው።
ዶሎአዶ ላይ አለ፡፡ በጅቡቲ በኩል ደወሌ ላይ አዘጋጅተናል። በእነዚህ ሥፍራዎች ሰዎችን ለይተን እናቆያለን። የሕክምና ማዕከልም አለን። የሕክምና ማዕከሉ በክልሉ ጤና ቢሮና በፌደራል ጤና ሚኒስቴር በጋራ የተሰራ ነው። ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ናሙናውን መርምሮ ውጤት የሚሰጥ ማሽን አለን።
ይህን ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ለመቆጣጠር ከፌደራል መንግሥት ድጋፍ አልጠየቃችሁም?
በተለያየ ጊዜ ድጋፍ ጠይቀናል። ለዚሁ ጉዳይ በክልሉ የተቋቋመ ስትሪንግ ኮሚቴ አለ፡፡ ከዚህ ኮሚቴ ጋር በሳምንት ሁለት ጊዜ እንሰበሰባለን። በዋናው ኮሚቴ ስር የጤና ንዑስ ኮሚቴ፣ የሐብት አፈላላጊ ኮሚቴና ሌሎችም ኮሚቴዎች አሉ። ተሰብስበን ስራችንን በወረርሽኙ ዙሪያ ስንገመግም፣ አንዱና ዋናው ጫና በድንበር በኩል በብዛት እየገቡ ያሉ ሰዎች ብዛትና እኛ ያለን አቅም አለመመጣጠን ነው። ይህንን ጫና በተደጋጋሚ ለፌደራል መንግሥት አሳውቀን ድጋፍ ጠይቀናል።
ነገር ግን ማዕከላዊ መንግሥትም ባለበት ጫና ምክንያት ይመስለኛል ምላሽ አልሰጠንም:: እኛ ባለን አቅም እየተፍጨረጨርን ነው። የሀብትም የሰው ሀይልም ሆነ የቴክኒክ ድጋፍ ከፌደራል መንግሥት እየጠበቅን ነው። ከክልሉ ተወላጅ ባለሀብቶች፣ ዳያስፖራዎችና ከሌሎችም በሀብት አፈላላጊ ኮሚቴ በኩል እንቅስቃሴ ተደርጎ የተወሰነ ሀብት ማግኘት ተችሏል። ነገር ግን በቂ አይደለም። ለምሳሌ ቬንትሌተር የተገዛበት ገንዘብ ከሕዝበ ድጋፍ የተገኘ ነው።Read 859 times