Print this page
Saturday, 20 June 2020 11:58

በ700 ሚ.ብር የተገነባው አፍሪካ ውሃ ፋብሪካ ተመረቀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

ከአዲስ አበባ በ30 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ሆለታ ከተማ የተገነባውና 700 ሚ. ብር እንደወጣበት የተነገረለት አፍሪካ ውሃ ፋብሪካ፤ባለፈው ሳምንት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የሆለታ ከተማ ከንቲባ አቶ ኡቱካና ኦዳ እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተመርቋል።
 በሰዓት 66 ሺ ሊትር ውሃ የማምረት አቅም ያለውና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደራጀው ፋብሪካው፣ ለ200 ኤጀንቶችና ለ500 ቋሚ ሰራተኞች የሥራ እድል ፈጥሯል ተብሏል፡፡ የውሃ ፋብሪካው ፋብሪካው በአሁኑ ሰዓት በ0.3፣ በ0.5፣ በ1 እና በ2 ሊትር እንዲሁም በ20 ሊትር (ጃር) ለገበያ መቅረብ መጀመሩን የፋብሪካው ባለቤት አቶ ሰኢድ ዳምጤ በምርቃቱ ላይ ተናግረዋል። የፋብሪካው ግንባታ 1 ዓመት ከ8 ወር ብቻ መፍጀቱንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ፋብሪካው የተገነባባት ሆለታ ከተማ፣ ለአዲስ አበባ በጣም ቅርብና የ120 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ ብትሆንም፣ ማደግ የሚገባትን ያህል አለማደጓን የገለጹት አቶ ሰኢድ፤ከተማዋን የስብሰባና የመዝናኛ ማዕከል ለማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል። ባለሀብቱ ማህበራዊ ሀላፊነታቸውን ለመወጣትና ኮቪድ 19ን ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ 5 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ ሲለግሱ፣ 400 ለሚሆኑና በሆለታ ከተማ፣ በገላን፣ በሆለታ ወረዳና በቡሌ ሆራ ለሚገኙ 400 ያህል ቤተሰቦች 1.5 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የንጽህና መጠበቂያዎችን፣ ብርድ ልብስ፣ አልባሳትና ሌሎች ቁሳቁሶች መለገሳቸው ታውቋል፡፡ በተጨማሪም፤ በቡሌ ሆራ ከተማ በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት የሚያመጡ ተማሪዎች የሚማሩበት አዳሪ ት/ቤት በ20 ሚሊዮን ብር በጀት እያስገነቡ እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሏል፡፡    
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ፋብሪካውን መርቀው ከከፈቱ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ባለሀብቱ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች በሰሯቸው የኢንቨስትመንት ሥራዎች በአገራቸው ኢኮኖሚ ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ከማድረጋቸውም በላይ ለበርካቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር አገራዊ ግዴታቸውን እየተወጡ መሆኑን የገለጹ ሲሆን በሆለታ ከተማ የገነቡት አፍሪካ ውሃም ለአካባቢው ነዋሪ የስራ እድል ከመፍጠሩም ባሻገር ለከተማዋ እድገት መፋጠን ጉልህ ሚና ያለው በመሆኑ ባለሀብቱ ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።


Read 2833 times