Monday, 15 June 2020 00:00

ለብዝሐ ሕይወት ደህንነት ሕይወቱን የሰጠ ሣይንቲስት

Written by  ዘነበ ወላ
Rate this item
(2 votes)

 ባለፈው ሚያዝያ ወር መጨረሻ ላይ ከአዛውንቱ ሣይንቲስት ከሎሬት ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረእግዚአብሔር የተጻፈ አንድ ግልፅ ደብዳቤ በኢንተርኔት ላይ አነበብኩ::  በኢትዮጵያ  በዘረ-መል ምህንድስና የተለወጡ አዝርዕቶች እንዲመረቱ የኢትዮጵያ መንግሥት መፍቀዱን ሰምቶ ተቃውሞውን በጽሁፍ ከገለጸ በኋላ  ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወይም ቀልባቸውን የሚስበው ባለሙያዎች የሰጡትን  አስተያየትም ተመለከትኩኝ፡፡
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል 98 በመቶ ያህሉ የሣይንቲስቱን ሃሳብ ደግፈው ውሃ የሚያነሳ ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡ ይኸው ጉዳይ በአገራችን ከሚገኙት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መካከል በአሻምና ኢ.ቢ.ኤስ ሽፋን አግኝቷል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ፋና ወጊው አሻም ቴሌቪዥን፣ የሣይንቲስቱን ግልፅ ደብዳቤ ወደ አማርኛ በመተርጎም ለታዳሚው አድርሷል፡፡ ይህ ድርጊቱ ይበል የሚያሰኝ ሲሆን፤ በኋላም ጉዳዩን በጥልቀት የሚያውቁ  ወጣት ባለሙያዎችን በመጋበዝ ሙያዊ አስተያየታቸውን  አቅርቧል፡፡
ባለሙያዎቹ በጭብጥ ደረጃ ያነሷቸውን በተወሰነ ደረጃ ለመጥቀስ ያህል፤ ”ኩባንያዎቹ አውሮፓ ውስጥ በዘረመል ምህንድስና የተመረተን ምርት ለማምረት ሙከራ ተደርጎ ከፍተኛ ተቃውሞ  ተነስቶባቸዋል፡፡ ደቡብ አሜሪካ ውስጥም ተቃውሞ አለ፡፡ ስለዚህ አፍሪቃ ለዚህ  ምቹ  የሆነች ይመስላል፡፡ የምግብ እህል እጥረትን ለመቀነስ፣ ምርትን ለመጨመር፣  ለአረም ማጥፊያ የሚወጣ ኬሚካል ለማስቀረት፤ አረምን ለመቆጣጠር ወዘተ-- ይጠቅማል በሚል ሰበብ ወደ አህጉራችን እየተመሙ ነው፡፡ በሌላ አባባል የአፍሪቃን የሕያዋን ሀብትን /ብዝሐ ሕይወት/ ምንጩን /ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ነው  ግባቸው፡፡”
“የምግብ እጥረትን መቅረፍ ሳይሆን በአፍሪቃውያን ላይ የምግብ ጥገኝነት መፍጠር ነው የሚፈልጉት፡፡ እንዲያውም በዘር  ሰበብ ባሪያ ነው የሚያደርጉን” በማለት ጉዳዩን በጥልቀት የሚያውቁ አራት ባለሙያዎች ግንቦት 24 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽት፣ በአሻም ቲቪ “ሃሰሳ” ፕሮግራም ላይ ሐሳባቸውን አንፀባርቀዋል፡፡
ከሶስት ቀን ቀደም ብሎ ግንቦት 21 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽት ደግሞ በኢቢኤስ ‹ቴክቶክ› ፕሮግራም ላይ አዘጋጁ ሰለሞን ካሳ በዘርፉ ሣይንቲስት የሆኑትን ሎሬት ዶክተር መላኩ ወረደን በጉዳዩ ላይ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሣይንቲስቱ በሰጡት አስተያየትም፤ “የብዝሐ ሕይወት ሀብቱ ያለው እኛ እጅ ላይ ነው:: ቴክኖሎጂው ያለው ደግሞ ባዕድ እጅ ላይ ነው፡፡ መከራው የሚመጣው አንድ አይነት እንቅስቃሴ በተፈጠረ ጊዜ የተፈጥሮ ሀብቱ ላይ ብከላን ሊያስከትል ይችላል:: የተፈጥሮ ሀብት መበከል የአየር ንብረት ለውጥን ሲያስከትል፣ ያንን ለመተካት ወደ ደን በቀል /ዱር በቀል/ መሔድ ሊያሻን ነው:: የውጭ ኩባንያዎች እንከውን የሚሉት ኃላፊነት በጣም ከባድ ነው፡፡ ቢቻል ቢቻል እንዲህ አይነቱን ነገር ባንሞክረው መልካም ነው“ ብለዋል፡፡
ከ15 ዓመት በፊት በግንቦት ወር 1997 ዓ.ም ሪፖርተር ጋዜጣ አንድ ዜና ዘግቦ ነበር:: ዜናው “ካናዳ ለኢትዮጵያዊው ሣይንቲስት ቪዛ ከለከለች” የሚል ነው፡፡ ይህ ዜና በኢንተርኔት እንደተለቀቀ ዓለም አቀፍ ጩኸትን ቀሰቀሰ:: ጉዳዩ የሚያገባቸው አካላት ሁሉ በካናዳ መንግሥት ላይ ቅሬታቸውን አሰሙ፡፡ በቀናት ልዩነትም ስህተታቸውን አረሙ፡፡ ሣይንቲስቱንም ይቅርታ ጠየቁ፡፡ ቪዛቸውንም ሰጧቸው፡፡
ዶክተር ተወልደ ብርሃን ካናዳ የሚጓዘው እዚያ በሚካሄድ የዘረመል ምህንድስና ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ነበር፡፡ ካናዳዎች የጉዳዩ አውራ እሱ ስለሆነ ስብሰባውን ለማደናቀፍ፣ በተለያዩ ሰበቦች ሊያዘገዩት ሞክረው ነበር፡፡ የማታ ማታ ግን የሳይንቲስቱ ተፅዕኖ በማየሉ፣ ቪዛ ሰጥተውት በካናዳው ስብሰባ ላይ ተገኝቷል፡፡
ስለዚህ ጉዳይ ዶ/ር ተወልደ ሲያወጋኝ፤ “ካናዳዎች ያደናቀፉኝ  መስሏቸው ነበር፤ ነገር ግን ተሞኝተው ነው እንጂ ዕውቀቱ የእኔ ብቻ ሳይሆን በአያሌው በመልማት ላይ የሚገኙ አገሮች ሣይንቲስቶች ጭምር ነው፤” ነበር ያለኝ፡፡  አልተሳሳተም፡፡ በአሻም ቴሌቪዥንና በኢንተርኔት ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች፣ የብዝሐ ሕይወት ደህንነት ዕውቀት የአያሌ ወጣት ባለሙያዎች መሆኑን ተገንዝቤአለሁ፡፡
ሎሬት ዶክተር መላኩ ወረደ በሙያም ሆነ በዕድሜው አቻው ናቸው፡፡ የዶክተር ተወልደን አስተዋይነት፣ የዕውቀት ብቃትና ጉዳዩን የመረዳት አቅሙን ተገንዝበው፣ ለዓለም አቀፍ ድርድሩ ከመረጡት ባለሙያዎች መካከል ቀዳሚው ነበሩ፡፡
ዓለም አቀፍ ድርድሩ ላይ አሜሪካኖቹ መጀመሪያ አፍሪቃውያኑን በንቀት ነበር የተቀበሏቸው፡፡ ሊያቀርቡ ያሰቡትንም አጀንዳ አይተው “ይኼ ግሪን ፒስ የሰጣቸው ነው” ሲሉ ተሳልቀውባቸዋል፡፡ በሂደት ግን እውነታወን በቅጡ ተረድተውታል፡፡ ይህንን በአግባቡ ያልተረዱት አቶ መኮንን ተሾመ ቶሌራ የጠባሉ ግለሰብ፤ “የሣይንቲስቱ ሣይንሳዊ ያልሆነ  ሙግት” በሚል ርእስ  አንድ ጽሑፍ፣ ግንቦት 16 ቀን 2012 ዓ.ም በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ለንባብ  አብቅተዋል:: ጽሁፉ፤ “ባለቤት ላሜ ወለደች ቢል ጎረቤት አልወለደችም” አለ” እንደሚሉት የአገራችን ዘይቤያዊ አባባል ነው የሆነብኝ::  ከርዕሱ ጀምሮ ጸሃፊው፣ ሙሉ በሙሉ የሣይንቲስቱን ማንነትና አስተዋፅኦ ያልተገነዘበና ስሜትን ለመግለጽ ብቻ በጥድፊያ ብዕር ከአፎቱ እንደመዘዙ የሚያሳይ ነው፡፡
ከጽሁፋቸው ላይ እየነቀስኩ በጥቂቱ ላሳይ፤ “የዘረመል ምሕንድስና ሣይንስ  ልክ በብዙ አገሮች እየተስፋፋ እንዳለው በእኛም አገር  አቅም  በፈቀደ መጠንና ሁሉንም  የደህንነተ ሕይወት (ባዮሴፍቲ) ጥንቃቄዎችን በጠበቀ መልኩ እንዲደረግ የምንፈልግበት ምክንያት...” ሲሉ መልካም ፈቃደኝነታቸውን ያሳያሉ፡፡ የት አገር ተመረተ፣ ‹ዘርቶ መቃም፣ ወልዶ መሣምንም› አይጠቁሙንም፡፡
በዓለማችን ላይ 177 አገሮች ናቸው በዚህ በዘረመል ምህንድስና ዘር ድርድር ላይ ኮሎምቢያ በካርታጊና ፕሮቶኮል  ላይ የተሳተፉት፡፡ ከእነዚህ አገሮች ውስጥ አምስቱ አገሮች ሲቀሩ ሌሎቹ በሰነዱ ላይ ሕጋዊ ፊርማቸውን አኑረዋል::  በኢትዮጵያም  ይህ ፕሮቶኮል  የካቲት 2011 ዓ.ም ሕግ ሆኖ  ፀድቋል:: በዚህ ሰነድ ላይ ያልፈረመችው አሜሪካ  ነች። “ይህች አገር በየትኛውም የአካባቢ ጉዳይ ስምምነት ላይ ፊርማዋን አላኖረችም፡፡ ይሁን እንጂ  በዓለማችን ላይ ከሚመነጨው በካይ ጋዝ ¼ኛውን  የምታመነጭ  አገር ናት፡፡ ካናዳ፣ ቺሊ፣ አርጀንቲናና ኡራጋይን የያዘው ቡድን የሚያሚ ግሩፕ ይሰኛሉ፡፡ ምን አልባትም እነዚህን ይሆን ... አቶ መኮንን “...በብዙ አገሮች እየተስፋፋ…” እንደሆነ የሚነግሩን፡፡
አቶ መኮንን በመለጠቅም “…የዘረመል ምሕንድስናን ሣይንሣዊና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ከማየት ይልቅ  የራሳቸውን ፍላጎትና ምኞት  ብቻ ማየት ...” ይሉናል፡፡   የዶክተር ተወልደ የሙያ አጋር ሚስ ሊዝ ሆስኪን በበኩሏ፤ “…በአጠቃላይ የዓለማችንን ሕያዋን ደህንነት ለመጠበቅ የፈጠርነው ህቡዕ መንግሥት /ሕብረት/ መሪያችን ዶክተር ተወልደ ነው፡፡” ትላለች፡፡ ይህ ምስክርነት እርስዎ እንደሚሉት፣ በፍላጎትና በምኞት የመጣ ይመስልዎታል?... ሌሎች አያሌ ተመራማሪዎችም ለዶ/ር ተወልደ ምስክርነታቸውን ሰጥተውበታል፡፡
ወረድ ብለው ደግሞ ‘’...በተለያዩ የኮምፒውተር  ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ ቆየት ካለውና  እነ ዶክተር  ተወልደብርሃን ከተማሩበት ዘመን በተለየና በፈጠነ መልኩ እየዘመነ መጥቷል፡፡...’’ ይላሉ::  ከላይ እንደጠቀስነው በኢንዱስትሪ የበለፀጉት አገሮች አፍሪቃውያን እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ ለድርድር ሲቀርቡ በንቀት ዓይን አይተዋቸው፤ ነበር፡፡ በኋላ ግን አዋቂነታቸውን ተቀብለዋል:: አቶ መኮንን ተሾመ ቶሌራ፤ የዶክተር ተወልደን ማንነት፣ የሃሳቡ ጠንሳሽ መሆኑንና በመልማት ላይ የሚገኙ አገሮችን ድርድር መርቶ ተጨባጩን ውጤት ያስገኘ መሆኑን ያወቁ አይመስሉም:: ዶክተር ተወልደ ከልጅነት እስከ እውቀት የዕውቀትና የጥበብ ሰው ነው፡፡ ይህንንም ስለሚያውቁ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ሆነ ሌሎቹ ዩኒቨርሲቲዎች ዓመታዊ ዕቅዳቸውን ሲያወጡ ምክሩን ይጠይቁታል፡፡ ይህንን አሳምሬ አውቃለሁ፡፡ ከተማሪዎቹ ደግሞ እማኝ ልጥራ፡፡ ፕሮፌሰር እንደሻው በቀለ፣ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰውና ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነን ወደ ሳይንስ ፋኩሊቲ ብቅ ብለው ቢጠይቋቸው፣ “ማሰብን”  እንዳስተማራቸው ይነግሯችኋል፡፡
አንድ ዘና የምታደርግ ገጠመኝ ልጥቀስ፤ ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ ኬንያ ናይሮቢ ለሥራ ጉዳይ ሄዶ ከአንድ ኬንያዊ ምሑር ጋር ይጨዋወታሉ፡፡ ኬንያዊው ምሁር፣ ፕሮፌሰር ማስረሻ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ሲያውቅ አንድ ገጠመኙን አጫውቶታል፡፡ “ዶክተር ተወልደን ታውቀዋለህ? ይህ ሰው በአንድ ወቅት የአፍሪቃን የአካባቢ ችግር ከነመፍትሔው ነግሮን ነበር:: በዚህ ደስ ተሰኘሁና አጠገቤ ለተቀመጠች ነጭ ሴትዮ ‹ይሔውልሽ ወይዘሮ፤ሁለተኛ በእኛ ጉዳይ ጣልቃ አትግቡብን፡፡ እኛ አፍሪካውያን ችግራችንን ከነመፍትሔው እናውቀዋለን› ስላት፤ ሴትዮዋ ፈገግ ብላ “ይህ መድረኩ ላይ ወጥቶ ችግራችንን ከነመፍትሔው የሚነግረን ሰው ባለቤቴ እኮ ነው” ብላ አስገረመችው በማለት ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ አጫውቶኛል፡፡ በነገራችን ላይ ባለቤቱ ወይዘሮ ሱዛን ኤድዋርድ /194ዐ-2ዐ18/ በትውልድ እንግሊዛዊት፣ በዜግነት ኢትዮጵያዊት ስትሆን በሃይማኖቷም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ዳግም ተጠምቃ፣ የተዋህዶ እምነትን ተቀብላለች፡፡
ዶክተር ተወልደ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ በብዝሀ ሕይወት ሀብት፣ በዘረመል ምህንድስና እንዲሁም በማህበረሰብ መብት፣ በሶስት ግዙፍ አጀንዳዎች፣ በመልማት ላይ የሚገኙ አገሮችን ወክሎ በመምራት ድንቅ ውጤትን አስገኝቷል፡፡ ይህ ድርድር  ሕይወትንም የሚያስከፍል ነበር:: ይህንን ቀድማ የተረዳችው ባለቤቱ ወይዘሮ ሱዛን ኤድዋርድ ነበረች፡፡ ሁሉም ነገር በሰላም መጠናቀቁን ካስተዋለች በኋላ “እንኳን ደስ ያለህ፤ ይገሉሀል ብዬ ፈርቼ ነበር” ብላዋለች:: ይህንን ሃሳብ በአንድ ወቅት ከፕሮፌሰር እንደሻው በቀለ ጋር አንስተን ስንጨዋወት “እነዚህ ግዙፍ ኩባንያዎች አክብረው ዝም ያሉት እነሱም በሂደት ትርፋቸውን፤ እሱም የዓለም ደህንነትን ማክበር ግባቸው እንደሆነ ስለተረዱ ነው” ብሎኛል፡፡
አቶ መኮንን “ጠቢብ በአገሩ አይከበርም” እንዲሉ ሆኖ እንጂ ጉዳዩን ያገባኛል ብለው ካሰቡት ሳያነቡት፣ ሳይሰሙት የቀሩ አይመስለኝም፡፡ አሜሪካኖቹ በማስፈራራትም ሆነ በመደለል ለመያዝ ያደረጉት ጥረት አልሰምር ቢላቸው፤ አማላጅም ልከው ስላልተሳካላቸው ነው መጋተሩ ግድ የሆነባቸው፡፡ መጀመሪያ ሲንቁት የነበረውን ሣይንቲስት፣ ማንነቱን ካወቁ በኋላ ወደ አዳራሹ ሲገባ፤  “O he is coming!” ማለት ጀመሩ፡፡  
ዶክተር ተወልደ ንባቡ ጥልቅ ነው፡፡ ከእኔ ጋር ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት ባሳለፍነው የአስተማሪና የደቀመዝሙር ጊዜያት፣ በርካታ ዘመን አይሽሬ መጻሕፍትን አንብቧል፡፡ ባለፉት 46 ዓመታት ከሙያው ጋር የተያያዙ መጻሕፍትን ነው ያነበበው:: ይህንን ጥልቅ አሳቢ ነው አቶ መኮንን ትምህርቱ የድሮ ነው የሚሉት::
ሰብእናውን በተመለከተ እማኝ ልጥራ፤ ዶክተር ዓለማየሁ ዋሴ በቅርኑ ለንባብ በበቃ ”ሰበዝ’’ የተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ እኔና ዶክተር ተወልደ ብርሃን በሚል ርዕስ፣ ከገጽ 39 እስከ 45 ያሰፈሩትን ቢያነቡ የሣይንቲስቱን ሰብዕና ይረዱታል፡፡
አሜሪካ ረሃብ በዓለም ላይ ሲከሰት ከፍተኛዋ ምግብ ለጋሽ አገር ናት፡፡ ይህንን ማድነቅ ይኖርብናል፡፡ በአንድ ወቅት ግን “ምግብ ትፈልጋላችሁ? ያለው በቆሎ በዘረመል ምህንድስና የተለወጠ ነው፤ እሱን ነው ላቀርብላችሁ የምችለው’’ አለች፡፡
በወቅቱ ዛምቢያ ችግር ላይ ነበረች፡፡ ይህንን በዘረመል ምህንድስና የተመረተን ምግብ ለመቀበል ግን ፈቃደኛ አልሆነችም:: “አማራጭ የምግብ ምንጭ እፈልጋለሁ:: አሁን ይህንን በሣይንስ የተመረተን ዘር ብቀበል የበቆሎ ምርቴ ይበላሻል፤ አልቀበልም” ስትል አስቀርታዋለች፡፡ ሕዝቧ በቆሎን በስፋት የሚመገብ ሲሆን ይህንኑ እህል አምርታም ወደ አውሮፓ በመላክ 14ዐ ሚሊዮን ዶላር በየዓመቱ ታገኝበታለች፡፡
ይህ በቅጡ ያልተመረመረ፣ ተመርምሮም ውጤቱ ያልታወቀ የዘረመል ምህንድስና ውጤት፣ ሪፖርተር ጋዜጣ፣ ግንቦት 26 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም ባወጣው ዘገባ፤ “ዘረመል ምግቦች ለጤና ጠንቅ እንደሆኑና ኅብረተሰቡ እነዚህን ምግቦች መመገቡን እንዲያቆም” የአሜሪካን አካዳሚ ኦፍ ኢንቫይሮሜንታል ሜድስን  ጥናትን ጠቅሶ አስነብቧል።
ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር በግልጽ ደብዳቤውና አቋሙ “አይቆረጠም’ የብረት ቆሎ፣ አይወረወር የእሳት አሎሎ” ሆኖባቸ ነበር፡፡ ይኼኔ ፒሊፕ አይራኒ የተባለ ጸሃፊ፤ “ደርሶ ጀግና ልሁን ይላል’’ (Imagines himself as a hero) ሲል በእርግጥ የሳይንቲስቱ ጀግንነት ለእኛ ለመልማት ለምንዳክረውና የብዝሀ ሕይወት ሀብቱ በእጃችን ላይ ላለው አገሮች እንጂ፤ በኢንዱስትሪ ለበለፀጉትማ ጠላታቸው ነው፡፡ ሳይንቲስቱ፤ ማልኮለም ኤክስ “ብሬን ዎሽድ ፒ.ኤች.ዲ” እንደሚላቸው ባለመሆኑ የበሸቁበት ይመስላሉ፡፡
እንደዚያም ሆኖ የዘረመል ምህንድስና እርባና ቢስ ነው አላለም፡፡ ከእኔ ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ስናወጋ፤ “የአዲስ ፈጠራ መሞከሪያ ሆነን አደጋ ላይ እንዳንወድቅ ሥርዓት ይኑረው አልን እንጂ ፈጠራውን ሙሉ በሙሉ እየተቃወምን አይደለም” ብሎኛል፡፡
የሣይንቲስቱን ስጋት መቶ በመቶ እጋራዋለሁ፡፡ አገራችን በዓለማችን ላይ 12 የብዝሀ ሕይወት ሀብት ካላቸው አገራት አንዷ ነች፡፡ ይህ አይነቱ ልውጥ ሕያዋን አንዴ የተፈጥሮ ሀብታችንን ከበከለው ሀብቱ የእኛ መሆኑ ቀርቶ የፈብራኪዎቹ ኩባንያዎች ይሆናል፡፡ ዝርዝሩ ሰፊ ስለሆነ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ፡፡ ለአሁን ግን አንድ ምሳሌ ለማሳያነት ልጥቀስ፡፡
ምን አልባትም ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት በዓለም ላይ የገብስ ዘርን ብቻ የሚያጠቃ ‘’የሎ ዲዋርፍ ቫይረስ” የተባለ ሕመም ተከስቶ ነበር:: ይህ ለዓለማችን ሕዝብ እጅግ አስደንጋጭ ነበር:: ከሣይንቲስቱ ጋር ይህንን ጉዳይ አንስተን ስንጨዋወት “አውሮፓውያኑ ቢራቸውን እኛም በሶና ቆሏችንን አጥተን ነበር” ብሎኛል:: ይህንን ቫይረስ መቋቋም  የሚችል የገብስ ዘር ኢትዮጵያ ውስጥ ተገኘ፡፡ የአገራችን ፍቃድ  ሳይጠየቅ ቅርሳችንን ሠርቀው እንደሚወስዱት፣ ይህ ዘርም ከኢትዮጵያ ወጥቶ አሜሪካ ካሊፎርኒያ ገባ፡፡ ያንን አባዝተው የገብስ ዘርን ደህንነት ጠበቁበት:: በአሁኑ ጊዜ በዓመት እስከ 13ዐ ሚሊዮን ዶላር ይዝቁበታል፡፡  ከዚህ ገቢያቸው ላይ ለኢትዮጽያ አምስት ሣንቲም አይሰጧትም:: በዚህ ነውረኝነት ውስጥ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ሀብት አንድ ተአምር ፈጥሯል:: ይኸውም 12 የብዝሀ ሕይወት ሀብት ካላቸው አገሮች አንዷ በመሆንዋ ደህንነቱን ጠብቃለች:: አሁንም  በዘረመል ምህንድስና  የተመረተ ዘር አገራችን በ13ዐሺ ሔክታር መሬት ላይ ሞክራለች መባሉ፤ በነባሩና በጥንታዊው የብዝሀ ሕይወት ሀብት ላይ ብክለት ቢከተል የሚጠፋው የኢትዮጵያ ሀብት ብቻ ሳይሆን የዓለማችን ብዝሀ ሕይወት ሀብትም ጭምር ነው፡፡ ይህንን አገሪቱን የሚያስተዳድረው መንግሥትም ሆነ፣ ምርቴን ሞክሬ  ”ኢትዮጵያን ከረሃብ አወጣታለሁ’’ የሚለው ኩባንያ ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው::
ድሃ እንደ መሆን የከፋ ነገር የለም፡፡ ሰው የሚላስ የሚቀመስ ሲያጣ ምን እንደሚሆን ኖረነው፣ አንብበነው አስተውለናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አገር ሲደኸይ ደግሞ በብድር፣ በዕርዳታ ሰበብ አያሌ ‹የእጅ ጥምዘዛዎች› በታዳጊ አገሮች ላይ ይካሄድባቸዋል፡፡ ዳንቢሳ ሞዮ ‘DEAD AID’ በሚል ለንባብ ባበቃችው መጽሐፍ ገጽ 72 ላይ ኢትዮጵያና ጋቦን 97 በመቶ ያህል ዓመታዊ በጀታቸውን ለመሸፈን በዕርዳታ በሚገኝ ገቢያቸው ላይ ይተማመናሉ ትለናለች፡፡ ይህንን ያህል የባዕድ እገዛ ካሻን ደግሞ የተፅዕኖው ብዛት የትየለሌ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በተፅዕኖ የዕለት ችግር ለመወጣት ስንል፣ ዘለዓለማዊ ችግር በትውልድ ላይ እንዳንፈጥር ቆም ብለን ማሰቡ የግድ ነው፡፡
‘ለብልህ ይነግሯል እንጂ አይመክሩም’ እንዲሉ የታላላቆቹን ጥፋት አርሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰላም የኖቤል ሽልማት አሸናፊ የሆነ መንግሥት፣ የብዝሀ ሕይወት ሀብቱን የሚበክል ነገር ይሠራል ብዬ አላምንም፡፡ ‘ለንቁ ፈረስ ያለንጋው ጥላ ይበቃዋል’ እንዲሉ ልክ የምርጫውን ጉዳይ ለሕግ አዋቂዎች፣ ለሕክምና  ባለሙያዎችና ለምርጫ ቦርድ አዋቂዎች እንደተወው ሁሉ የውሃውን ጉዳይም ለሣይንቲስቶች፤ ከተቻለም ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ እንደሚለው፣ አንድ የሚያገባውን ተቋም መስርቶ ጉዳዩን ለዕድሜ ልክ ባለሙያዎቹ መተው ቢችል ማለፊያ ነው፡፡ የአካባቢውንም ጉዳይ ሣይንቲስቱም ሆነ ሌሎች የሥራ አጋሮቹ በጡረታም የተገለሉም ሆነ መሥሪያ ቤቱን የለቀቁ ጎልማሳ ባለሙያዎቹን ሰብስቦ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ትላላችሁ ቢል፣ የብልህ አካሄድን በጥሩ ሁኔታ አወቀበት፣ ለብዝሐ ሕይወት ዕድሜውን ሙሉ የሰጠው ሣይንቲስትም ልፋት ፍሬ አፈራ ብዬ አስባለሁ፡፡
በእኔ የሕይወት ዘመን ከአራት አስርት ዓመታት በላይ በዘለቀ ንባቤ፣ ዓለማችንን በቅጡ ልረዳት በአያሌው ጥሬያለሁ፡፡ አንድ ኩባንያ ዘርቶ፣ አጭዶና ከምሮ ሌላውን አገር አጠገበ ሲባል ሰምቼ አላውቅም፡፡ የኢትየጵያ ገበሬ እጆች 9ዐ በመቶ የሚሆነውን ሕዝቧን እየቀለበ ነው፡፡ ቀሪውን 1ዐ በመቶ የሚሆነውን እንዲቀልብ ተግቶ መሥራትና ጎረቤት አገሮችን ማስተዋሉ ማለፊያ ትምህርት ይገኝበታል፡፡ በቅርቡ ባነበብኩት የግርማ ባልቻ "የኢትዮጵያና የግብፅ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት”… የተሰኘ መጽሐፍ ላይ ግብፅና ሱዳን በምግብ እህል ራሳቸውን መቻላቸውን ተገንዝቤአለሁ:: በማን? በናይል!! ከእነዚህ አገራት ማለፊያ ትምህርት እንወስዳለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
አንዳርጋቸው ፅጌ “ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር” በሚለው መጽሐፋቸው፤ “12 የማይሞሉ በደንብ የተደራጁና ያቀዱ ሰዎች እንዴት በሺዎች የሚቆጠሩ የማይጠረጥሩ ሰዎችን እንደፈለጉ ማሽከርከር እንደሚችሉ በተግባር ተመልክተናል” ይሉናል፡፡ ዓለም አቀፍ ግዙፍ ኩባንያዎች አቅማቸው እንዲህ ነው፡፡ እሱን ለመመከት የጉዳዩን ባለቤቶች (ባለሙያዎች) በማሰባሰብ፣ ተደራጅቶ ማሰብ እንዲሁም ባለሙያን ማመን የአገር ደህንነትን ይታደጋል፡፡



Read 3137 times