Saturday, 13 June 2020 12:18

“የጊዜ መንኮራኩር”፤ ለፖለቲካ ምርጫና ለወረርሽኙ መጨረሻ!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

   • የህዳሴ ግድብንና የእለት ኑሮን፤ የክረምት እርሻንና የፀሐይ ግርዶሽን “በጊዜ ሰረገላ”።
      • ከ50 የዘመናችን ገናና ፊልሞች መካከል 45ቱ፣ በ“fantasy” እና በ“ተዓምር” የተንበሸበሹ፤ ምናባዊ “የሳይንስ፣ የሱፐርሄሮ እና የምትሃት” ፊልሞች    ናቸው። ከፊልሞቹ ዋና ዋና ምናባዊ ተዓምሮች ውስጥ፣ አንዱን ተመልከቱ - “የጊዜ መንኮራኩር”ን።
      • ዛሬ ላይ ሆኖ፣ በትንፋሽ ፍጥነት፣ ወደ ትናንት ወይም ወደ ነገ የሚያንሸራሽር “የጊዜ ሰረገላ”፤…. ባንዳፍታ አምናን አሳይቶ፣ የሚቀጥለውን ዓመት    አስጎብኝቶ የሚመልስ ምትሃት ብታገኙ አስቡት።
      • ከአመት በኋላ የሚካሄደውን ምርጫ ከነመዘዙ ታዝቦ መምጣት፣ የወረርሽኙን የወደፊት መከራ አይቶ መመለስ፣…. አጓጊ ባይሆንም፣ ከትናንትም
       ከነገም፣ ብዙ ድንቅ ነገሮችን መጎብኘት ቢቻል፣ ማለት ነው። ነገር ግን፣ ሽርሽር ብቻ አይደለም።
      • ትናንት የሰራኸውን፣ የሚቆጭ ስህተት አርመህ፣ ወደ ዛሬ መመለስ ከተቻለስ? ነገ ክፉ መዘዝ ሲፈጠር አይተሽ፣  ዛሬውኑ   ሰበቦችን ማጥፋትና
          ማስተካከልስ?
      • አንዱ ወሮበላ፣ “በሚቀጥለው ወር” ወንጀል ሲፈፅም ተመልክተሽ፣ “ከወዲሁ ዛሬውኑ” ማሰር፣ መክሰስና መቅጣትስ? ይሄ የተሳከረ ሀሳብ ነው። ግን፣  ወንጀልን ለመከላከል፣…. ተዘጋጅቶ መጠበቅስ?
      • “የጊዜ መንኮራኩር”፣ ከወር በኋላ ብቻ ሳይሆን፤ ከአስር ወይም ከመቶ ዓመት በኋላ ሊፈፀሙ የሚችሉ ወንጀሎችን ለማወቅ፤ አስቀድሞ መከላከያ    ለማበጀት፤ ወይም ሕግና ሥርዓትን ለማፅናት ይጠቅማል።
       • የአሜሪካ ህገ መንግሥት፣ ከ200 ዓመት በላይ የተጓዘ ድንቅ የጊዜ መንኮራኩር ነው ማለት ይቻላል? ሳይንስና ቴክኖሎጂም ተዓምረኛ ነው
          - በሚቀጥለው ሳምንት የሚከሰተውን የፀሐይ ግርዶሽ፣ ዛሬውኑ ማየት ከተቻለ።
                  
             “የጊዜ መንኮራኩር”ን እና ሌሎች ምናባዊ “ተዓምሮች”ን በመጠቀም፣ ተወዳጅ ልብወለድ ታሪኮችን መፍጠር፣ ከዚያም ቢሊዮን ዶላር የሚያስገኙ ፊልሞችን መስራት፣ ያስገርማል። የማይታመኑ ነገሮችን፣ “ቃል በቃል” ተአማኒ አድርጎ፣ መሳጭ ታሪክ ጽፎ ወይም በምስል አትሞ፤ በፊልም ቀርፆ ማሳየት፣ ትልቅ የፈጠራ ጥበብ ነው ለካ። ምን ይሄ ብቻ! “ከቃል በቃል” ትርጉም በተጨማሪ፣ ሌላ የላቀ ጥልቅ ትርጉም፤ ከፊልሞቹ ውስጥ እንደምናገኝ ነው፣ ጥበበኞቹ የሚነግሩን። እንዴት? እንደ ሰምና ወርቅ?
እስቲ እንየዋ። እንደ ሰምና ወርቅ፣ እንደ ዘይቤና ምሳሌ ስናገናዝበው፣… “የጊዜ መንኮራኩር” ጉዳይ፤ የፊልም ማድመቂያ፣ የልብወለድ ታሪክ ማሳመሪያ፣ ተራ “ተዓምር” አይደለም? “የጊዜ መንኮራኩር”፣ ገለጥ ተደርጎ ውስጡ ሲመረመር፣ ዘላለማዊ እውነትን እንደሚገልፅልን ያስረዱናል - ጥበበኞቹ። የጊዜ መንኮራኩር ተዓምረኛ መሳሪያ ነው። ውስጠ ሚስጥሩ ሲገለጥ ደግሞ፣ የእለተ ተእለት ሕይወታችንን ወለል አድርጎ ያስቃኘናል፤ ይሄውና ተመልከቱ ይሉናል - ተወዳጆቹ የዘመናችን ፊልሞች (“የድፍረታቸው ድፍረት”)።
“የጊዜ መንኮራኩር”… የዘወትር ሕይወትን የሚያንፀባርቅ ከሆነ፣… እንደ ምርጥ ዘይቤ፣ ጥልቅ ትርጉምን ያቀፈ ዘላለማዊ እውነት ከሆነ፤… ተሳፍረን እንሞክረው? ከዓመት በኋላ፣ የፖለቲካ ምርጫ እንዴት እንደሚካሄድ ከነውጤቱና ከነመዘዙ፣ ዛሬውኑ መቃኘትና በግላጭ ማየት ብንችል፤ ምን የምናገኝ ይመስላችኋል? የሚያስደስት ወይስ የሚያስፈራ? የተጋጋለ ወይስ የተረጋጋ?
መቼም ሰላማዊ ምርጫ ሊሆን አይችልም። ሰላማዊ እንዲሆን ካደረግን፤ ተዓምረኞች ነን - የጊዜ መንኮራኩርን የሚያስንቅ ትልቅ ተዓምር ሰራን ማለት ነው።
ደግሞስ፣ ከዓመት በኋላ ምን እንደሚከሰት፣ በትንሹና በጥቅሉ መገመት እንጂ፤ “እቅጩን” ማወቅ፤ እንደ “ትንቢት“ እንደ “ራዕይ”፣ ዛሬ ላይ ሆነን መጪውን ዓመት በገሃድ ማየት… ይሄ እንዴት ይሆናል?
የጊዜ መንኮራኩር ከሌለ፤ የሕዳሴ ግድብ ከየት ይመጣል?
በአንድ በኩል፣“የጊዜ መንኮራኩር” የሚሉት ተዓምር፤ “በምኞት ፈረስ”፣ የሕልም ዓለም ውስጥ የመንሳፈፍ ቀሽም ስሜት ሊሆን ይችላል። ሁለተኛ ነገር፤ “በስጋት በቅሎ”፣ የቅዠት ዓለም ውስጥ የመደናበር ድክመትን የሚያመለክት ምሳሌያዊ አባባል ይመስላል። ሦስተኛ ነገር፤… ሌላ ምን ጥልቅ ትርጉም አለው - የጊዜ መንኮራኩር? አለው።   
 “የጊዜ መንኮራኩር” የሚሉት ነገር፤ አንዳች ዘላለማዊ እውነትነት ከሌለው፤ የሰው ልጅ፣ እንዴት ለሚቀጥለው ወርና ዓመት፤ ለአስርና ለሃያ ዓመት በትክክል ማሰብና መስራት  ይችላል?
ባለ ሰላሳና ባለ አርባ ፎቅ ሕንፃ ለመገንባት፣ በቅድሚያ፣ ሕንፃው ለበርካታ አስርት ዓመታት እንደሚያገለግል እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል። ግን እንዴት? የሕዳሴ ግድብ፣ ከጣና ሀይቅ የሚበልጥ የውሃ መጠን መያዝ እንደሚችል፣ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ሀይል በእጥፍ አሳድጎ፣ ከሃምሳና ከመቶ ዓመታት በላይ እንደሚያገለግልስ እንዴት ይታወቃል?
በዓይነ ህሊና በርካታ ዓመታትን አሻግረን በማስተዋል፤ የሕዳሴ ግድብ ትልልቅ ፋይዳዎችን ማወቅ ካልቻልን፤… መጪውን ዘመን በጊዜ መንኮራኩር ከነውጤቱ ካልቃኘን፣ ግድብ ለመስራት ማን ይለፋል? ደግነቱ፣ አሳምረው የሚያውቁ ሰዎች አሉ። እውቀትና ሙያው ያላቸው፤ ጉዳዩን አብጠርጥረው ያጠኑ፣ ውጥኑን ከመነመላው የነደፉ፣ ስራውን የሚመሩና የሚያከናውኑ ሰዎች፣ የወደፊቱን ውጤትና ስኬት በተጨባጭ አይተዋል ማለት ይቻላል - ዛሬ ላይ ሆነው። “መዳፋቸው ውስጥ ጨብጠው የያዙትና በእውን የሚያዩት” ያህል፣ የሕዳሴ ግድብ የወደፊት ታሪክ፣ ምን እንደሚመስል ያውቃሉ - ዛሬ ላይ ሆነው።
ተዓምር ነው? ወይስ ተራ እውነት?
“የጊዜ መንኮራኩር” ማለት ይሄ ነው እንዴ? እንዲህ ከሆነማ፤ “ተዓምርነቱ” ምኑ ላይ ነው? ሰዎች፣ ትናንትን እየቃኙ፣ ነገን እያማተሩ፣ ዛሬ ይሰራሉ። ከትናንት ተምረው፣ የነገን ውጤት አስበው ይጥራሉ። ይሄ፤ አዲስ ነገር አይደለም፤ “ተራ እውነት ነው”። ይሄ፣ “ተራ የእለት ተእለት ሕይወት ነው” ብንል አይፈረድብንም።
ሁሉም ሰው፤ የእውቀቱና የአቅሙ ያህል፤ በየእለቱ ለነገ ማሰቡ፣ በየዓመቱ ለከርሞ ማረሱ፣ ከ10 ዓመት በኋላ ለመጪ ሕይወቱ እንዲጠቅመው አስቦ መማሩ… ድሮም የነበረ፣ ወደፊትም የሚኖር ዘላለማዊ እውነት ነው… እንል ይሆናል።
እንዲያውም፣ ዛሬ ላይ ሆነን፤ “ነገን ማየትና ማወቅ” ስለምንችል እንጂ፤ ባንችል ኖሮ፣ ጨርሶ በሕይወት የመቆየት እድል እንደማናገኝ ብናስብ፣ አልተሳሳትንም። “የጊዜ መንኮራኩር” ዘይቤያዊ ምሳሌነቱ ይሄው ነው? “ዘላለማዊ እውነትንና የዘወትር ሕይወትን ያቀፈ ጥልቅ ትርጉም” የሚኖረውስ በዚህ መልኩ ነው? ይሄ ገና ጭላንጭሉና ፍንጩ ብቻ ነው።
የገናናዎቹ ፊልሞች የስኬት ሚስጥር፤ ሰምና ወርቅ።
Harry potter, Dr. strange, x-men, wonderwoman, Ironman, Batman, Avengers…  The Lord of the Rings, star wars, እነዚህን የመሳሰሉ፣ ምናባዊ የሳይንስ፣ የሱፐር ሄሮ፣ እና የምትሃት ፊልሞች፤ በመላው ዓለም ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፉት በዋዛ አይደለም። ከፍተኛ ገቢ በማስገኘት፣ የቦክስ ኦፊስን ዘውድ የተቀዳጁት… እንዲሁ አለምክንያት አይደለም።
እንደ ንስር መብረር፣ እንደ ሮኬት መወንጨፍ፣ እንደ አነር መምዘግዘግ፣ ከእጃቸው መዳፍ የእሳትና የመብረቅ እሩምታ መልቀቅ፤ ተዓምር ነው። ግን፤ ተዓምር መስራት የሚችሉ ባለ ታሪኮችን ማሳየታቸው ነው የፊልሞቹ የስኬት ሚስጥር? አይደለም።
በእርግጥ፣ እንደ አውሎ ነፋስ ግንዳ ግንድን እየገነዳደሱ አለትን እየፈነቃቀሉ የሚያንሳፍፉ፤ እንደ ማግኔት ብረታ ብረትን ነቅለው፣ መኪናና ድልድዩን መንጭቀው የሚወረውሩ ተዓምረኛ ሰዎች ሞልተዋል - በገናናዎቹ ፊልሞች ውስጥ።
ዋናዎቹ ባለታሪኮች፣ በልዩ ብቃት እጅግ የላቁ፣ ድንቅ ሰዎች ናቸው ማለት ይቻላል። ወይም ደግሞ የድንቅ ሰዎችን የተለያየ ገፅታ አጉልተው፣ በዘይቤ የሚያሳዩ ምናባዊ ባለታሪኮችን ያሳያሉ - ገናናዎቹ ፊልሞች። ምትሃተኞች (Magicians)፣ የሌላ ዓለም መጤዎች (Eliens)፣ ፀጉረ ልውጦች (Mutants)፣ እና ሰውኛ ነገሮች  (እንደ Robot ወይም AI)፣… ዋነኛ ዘይቤያዊ ባለታሪኮች ሆነው ይጠቀሳሉ።
በአጭሩ፤ የብቃት ባለቤት ድንቅ ሰዎች አልያም ዘይቤያዊ ገፀባርያት ናቸው፤ የፊልሞቹ ዋና ዋና ባለታሪኮች። ነገር ግን፤ ገናናዎቹ ፊልሞች፣ በተዓምረኛ ሰዎችና ፍጡራን የተሞሉ ስለሆኑ ብቻ አይደለም ተወዳጅ የሆኑት።
የሰው ተፈጥሯዊ አቅም፣ ተራ እውነት የመሆኑ ያህል፤ ተዓምር የሚያሰኝ ድንቅ አቅም መሆኑን፣ በዘይቤ ማሳየት የቻሉ የመሳጭ ታሪክ  ፊልሞች ናቸው ስኬታማ የሚሆኑት።
“ተዓምረኛ ሰዎችና ምትሃተኛ መሳሪያዎች”፤ በሃያል ታሪክ፣ በውስጣዊ መልዕክት ይቃኛሉ፡፡
ተዓምረኞቹ ባለታሪኮች፣ ብርቅ ድንቅ መሳሪያዎችን፣ አስገራሚ የሀይል ምንጮችን እና የረቀቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የታጠቁ ናቸው፡፡  ወይም ደግሞ ምትሃታዊ ሃይል፣ ምትሃታዊ ዘዴና መሳሪያ ይኖራቸዋል። ግን እነዚህ አይደሉም የፊልሞቹ የስኬት ሚስጥር።
ቃል በቃል ወይም በጥሬው የማይታመኑ ምናባዊ ተዓምሮች፤ በሃያል የታሪክ ትልም ሲሰናሰሉ መሳጭ ይሆናሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፤ ዜይቤያዊ ምሳሌነታቸው እንደ ወርቅ ነጥሮና ጠርቶ፣ ዘላለማዊ እውነትን እንዲያንፀባርቅ በሚያደርግ ጥበባዊ ፈጠራ የተቃኙ ሲሆኑ ነው፤ ፊልሞቹ ተወዳጅነትን በሰፊው የሚያገኙት።
በሌላ አነጋገር፣ ምርጥ ድርሰቶችና ፊልሞች፣ እንደ ምርጥ ቅኔ ናቸው። ምርጥ ቅኔ፤ ቃል በቃል ሲነበብ፣ እንከን የለሽና ምንም የማይጎድለው ትልቅ ቁም ነገር ነው። ገለጥ አድርገው፣ በጥልቀት ምሳሌያዊ መልእክቱን ሲያጤኑት ደግሞ፤ እጅግ የላቀ ቁም ነገር ይሆናል። ምርጥ ቅኔ፣ ሰሙ እንደ ውድ እንቁ ነው፡፡ ወርቁ ሲታከልበት ደግሞ፣ እጅግ የከበረ፣ በጣምም የተዋበ ህያው እውነት ደምቆ ይታያችኋል።
የተሳካ፣ የመጠቀ የኪነ ጥበብ ስራ እንደዚህ ነው። ቅርፅና ይዘቱ፣ ላይና ውስጡ፣ ስያሜና ተግባሩ፣ መልክና ባህርይው፣ ድንቅ ታሪክና በውስጡ ያቀፈው የሀሳብ መልዕክት… አንዱም ሳይባክን፤ ሰምና ወርቁ፣ አንዱ ለሌላው መስዋዕት ሳይሆን፣ በልክ ተዋህዶ፣ በቅጥ ተቀናብሮ፤ በምልዓት የተፈጠረ “ምናባዊ እውነታና ህልውና” ነው - ሃያል የኪነ ጥበብ ሥራ።
“የጊዜ መንኮራኩር” ላይ ተሳፍሮ፣ 10 ዓመት ወደ ኋላ የሚጓዝ፣ 10 ዓመት ወደፊት ገስግሶ የሚመለስ ምናባዊ ተዓምረኛ ሰው አለ እንበል። መንኮራኩሩ፣ አራት ቀን የኋሊት የሚጓዝ ቴክኖሎጂ ነው - de Javu) በተሰኘው ፊልም ላይ። ወይም ደግሞ ዓመታትን የሚያሻግር የDr Strange ዓይነት ምትሃት ሊሆን ይችላል - Avangers endgame ላይ እንዳየነው።
ባለታሪክ ገፀ ባህሪያትና አላማቸው፣ ከነአቅማቸው ከነመሳሪያቸው፣ የልብወለድ ድርሰት አንድ ማጠንጠኛ ናቸው፡፡  ነገር ግን፣ ልብ ወለድ ድርሰት ወይም ፊልም፤ ሕይወት የሚኖረው፣ ለስኬት አልሞ፣ ፈተና እየከበደም፣ ታግሎ የሚጓዝ ታሪክ ሲኖረው ነው። ይሄም በቂ አይደለም። ሁሉንም ነገር፣ ድንቅ ባለታሪኮችንና መሳጭ ታሪካቸውን፣ ከመነሻ እስከ መድረሻ አዋህዶ በቅጡ የሚይዝ አቃፊ መልዕክት ያስፈልጋል። ከአርስቶትል እስከ አየንራንድ ድረስ፣ እነዚህን መሰረታዊ የኪነ ጥበብ ገፅታዎች አጉልተው አስረድተዋል፤
ገናናዎቹ ፊልሞች፣ መሳጭና ተዓምረኛ ልብ ወለድ ታሪኮችን በእውን ያሳዩናል -  ቃል በቃል ነው ትርጉም። የዚህኑ ያህል ደግሞ፤ ውስጣዊ  የሀሳብ መልዕክትንም የያዙ ናቸው - ፊልሞቹ። በውስጣዊ መልዕክት የተቃኙ ናቸው። እነዚህን ያላሟላ ስኬታማ የልብ ወለድ ፊልም የለም። ከባለታሪክ ገፀ ባህርያት በተጨማሪ፤ መሳጭ ታሪክና የሚጨበጥ መልዕክት… የኪነ ጥበባዊ ድርሰት መሰረታዊ መንታ ገፅታዎች ናቸው።
መሳጭ ታሪክ ከሌለው፤ ድርሰቱ፤ የኪነ ጥበብ ሥራ አይሆንም። ምናልባት፤ የደብዳቤ መልዕክት፣ የጉዞ ማስታወሻ፣ የምኞት መግለጫ፣ የግኝት ዘገባና ማስረጃ፣ የመርህ ማብራሪያና ማስተማሪያ ሊሆን ይችላል - ነገሩ። ኪነ ጥበብ ግን አይደለም።
አንዳች መጨበጫ መልዕክት የሌለው ታሪክም፤ ኪነ ጥበብነት ይጎድለዋል። ከመነሻ እስከ መድረሻ፤ እያንዳንዱን ክስተትና ክንውን፣ ውጥንና መላ፣ ተግባርና ፈተና፣ ስኬትና መዘዝ… ሁሉንም አስተሳስሮ ያዋሃደ፤ ምሉዕና ምናባዊ ታሪክ፣ በመጽሐፍ ካነበብን ወይም በፊልም ከተመለከትን፤… ሁሉንም በቅጡ አቅፎ የሚይዝ ማስተሳሰሪያ ቅኝት አለው ማለት ነው። ማስተሳሰሪያው ቅኝት፤ አንዳች የሚጨበጥ መልዕክት ነው።
መልዕክት አለው። ከላይ ባይታይም፤ ሁሉንም ይቃኛል።
“ንጉስ ሞተ፤ ንግስቲቱ ሞተች” የሚል አገላለፅ፣ በምሳሌነት ሲቀርብ አጋጥሟችሁ ይሆናል። እንዲህ አይነት የእለታዊ ክስተት የቅደም ተከተል ምዝገባ፤ አንድ ነገር ነው። በታሪክ ትልም የተሳሰረ ታሪክ ደግሞ ሌላ ነገር ነው።
“ንጉሱ ሞተ፤ ንግስቲቱ በድንጋጤ ሞተች” ከሚል አገላለጽ ጋር አነፃፅሩት። ምን ምን እንደተከሰተ በተናጠል አይዘረዝርም። የክስተቶቹን ትስስር ያሳያል። ምን፣ ምንን እንዳስከተለ ማመልከት ብቻ ሳይሆን፣ ስለ ሁለቱ ባለታሪኮች ባሕርይም፤ የሆነ ምስል ይጠቁመናል። ክስተቶችንና ተግባራትን፣ ሰዎችንና ባሕርያቸውን ማስተሳሰር የተቻለው ግን፤ ሁሉንም የሚያቅፍ አንዳች የመልዕክት ቅኝት በውስጡ ስላለ ነው።
ስለ ፍቅር ወይም ስለትዳር፣ ሌላ አይነት የሀሳብ ቅኝት እናገኛለን፤ “ንጉሱ በሞተ ማግስት፣ ንግስቲቱ መነነች” ከሚል ቅንጣት ትረካ ውስጥ።
የሃምሌትን ምሬት በማስታወስ፣ “ንጉሱ ሞተ። በማግስቱ ንግስቲቱ ተሞሸረች” ከሚል ቅንጭብ ትረካ ጋር በማነፃፀር፣ የቅኝት ልዩነታቸውን መመልከት ትችላላችሁ። “ንጉሱ በሴራ ሞተ። ንግስቲቱ ለበቀል ሴረኛውን አገባች” የሚል ሌላ የትረካ አቅጣጫም ጨምሩበት።
ከእያንዳንዱ የታሪክ አቅጣጫ፣ የንጉሱን ሞት ከንግስቲቱ ምርጫና ውሳኔ ጋር አስተሳስሮ የሚያቅፍ የየራሱ ውስጣዊ የመልዕክት ቅኝት፣ እናገኛለን። አቃፊ ውስጣዊ መልዕክት ከሌለ፤ እለታዊ የክስተት ምዝገባ እንጂ፣ ኪነ ጥበባዊ ትረካ መሆኑ ይቀራል።
ወደ ገናናዎቹ ፊልሞች እንመለስ።
ተዓምረኛ ሰዎች፣ በተዓምረኛ መሳሪያ የሚያከናውኑት ተዓምረኛ ተግባር፤ እርስ በርስ ተሰናስሎ መሳጭ ትረካ ሊሆንልን የሚችለው፤ አንድም፣ ቃል በቃል በታሪክ ትልም ስለተሳሰረ ነው (በአላማና በተግባር፣ በውጤትና በመዘዝ)።
ሁለትም፤ ቅጥ ባለው ውስጣዊ መልዕክት የተቃኘ ስለሆነ ነው።
የጊዜ መንኮራኩር ሽርሽርም ሆነ እሽቅድምድም፤ ከቃል በቃል ትረካ ባሻገር፣ ውስጣዊ ትርጉሙና የመልዕክት ቅኝቱ ታክሎበት ነው፤ ቁም ነገርነቱ።
“የጊዜ መንኮራኩር”፣ እንደ ሰምና ወርቅ።
“ያንና ይሄን ብናውቅ ኖሮ”፣ “ለዚህና በዚያ ብንሰራ ኖሮ”፣ “እንዲህና እንዲያ ብንሆን ኖሮ”… ለሚሉ ሀሳቦችና ስሜቶች እንግዳ አይደለንም። ዘወትር ያገጥሙናል። ከእነዚህ ይልቅ፤ “የጊዜ መንኮራኩር” ላይ ተሳፍረው ወዳለፈው ወርና ዓመት መሄድ፣ ከፈለጉም አስርና መቶ ዓመት የኋሊት መጓዝ ቢቻል ግን፣… ያልታወቀውን ተገንዝበው፣ ያልተሰራውን አከናውነው፣ ራስዎንም ከጉድለት አሟልተው፣… ወደ ዛሬ ይመለሳሉ።
ትናንትን በማየት ወይም የትናንትን ተግባርን በመቀየር ዛሬን ማሳመር… በአእምሮና በእውቀት፣ በኑሮና በንብረት፣ በሰብዕናና በሕይወት ጣዕም… እጅግ የበለፀገና ያማረ ሕልውና…. ዛሬ እውን ሆነ ማለት ነው። ድንቅ ተዓምር ነው - የጊዜ መንኮራኩር!
ግን አስቡት፤ ከእለት ተእለት ህይወት ጋር ይመሳሰላል። የትናንትን ታሪክ አይተን ትምህርት ካልቀሰምንና እውቀት ካልጨበጥን፣ ከትናንት ተግባር ተሞክሮ ካላገኘንና ልምድ ካልገበየን፣ ዛሬን እንዴት መኖርና ማሳመር እንችላለን?
ሌላ የጉዞ አቅጣጫም አለ።
ወደ ትናንት ወይም ወደ አምና እየተጓዙ ከመከለስ፣ ከማስተካከልና ከማሟላት ጎን ለጎን፣ ዛሬ ላይ ሆነን፤ ነገን ማየትና ማወቅ ብንችል ይታያችሁ። ከነባርና ከዘላለማዊ እውነታዎች በተጨማሪ፤ በሚቀጥሉት ወራትና ዓመታት የሚከሰቱ መልካም እድሎችን፣ ድንገት የሚፈነዱ አደጋዎችን በውን ለማየት፣ የጊዜ ሰረገላ ላይ ተሳፍሮ መጋለብ ቢቻል፣ ድንቅ ነው።
በእለት ተእለት ተግባር አማካኝነት ቀስ በቀስ የሚመነደጉ አስደናቂ ውጤቶችን፣… ወይም ውስጥ ለውስጥ የሚወሳሰቡ መዘዞችንም፤ ከወዲሁ አስቀድመን ማወቅ እንችላለን ማለት ነው። በዚህኛውና በዚያኛው አቅጣጫ፤ በደልዳላ መሰረት ላይ አስተማማኝ ብቃት እየገነቡ፣ ከ10 ዓመት በኋላ፣ የቱን ያህል እጅግ የላቀ መልካም የግል ማንነትን እንደሚቀዳጁ በእውን ማየትስ አያጓጓም? አልያም የትኛው ጠማማ አቅጣጫ፤ ምንኛ ብቃትን እያሳጣ፤ መነሻ መሰረትንም እየሸረሸረ፣ ከ10 ዓመት በኋላ፤ የቱን ያህል ወደ አቅመ ቢስ ሚስኪንነት እንደሚያወርድ ለማወቅም ያገለግላል - “የጊዜ መንኮራኩር”። በአጭሩ፣ አንድ ወይም ሁለት ወር፣ አስር ወይም ሀያ አመት ወደፊት መብረር ቢቻል፤…. መጪውን ጊዜ አይተን፤ ወደ ዛሬ መመለስ እንችላለን።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ምን ያህል ተከላክለን፣ ተቆጣጥረንና ተቋቁመን፤ ከምን ያህል ጉዳት አምልጠን፣ እስከ ምን ድረስ እንደሚሳካልን፣ ከወዲሁ ዛሬውኑ ማወቅ ቢቻል አስቡት።
የፖለቲካ ምርጫ፣ መቼ እንደሚካሄድ፣ በምን ጥበብና ጥረት ወይም በምን ሰበብና ስህተት፣ በምን ስንፍናና ክፋት፣ ምን አይነት ቀውስና ጥፋት እንደሚፈጠር፣ ወይም ምን አይነት ውጤትና ፋይዳ እንደሚገኝ፤… ዛሬ አሁኑኑ፣ በውን ብናይስ? ይቻላል። አቅማችንን በአግባቡ ከተጠቀምን።
ሳይንስና ቴክኖሎጂ፤ የጊዜ መንኮራኩር ናቸው?
ሁሉም ሰው፣ የነገንና የነገ ወዲያን ክስተት ማወቅ ባይችል እንኳ፤ የጊዜ መንኮራኩራቸውን እየነዱ፤ የጊዜ ፈረሳቸውን እየጋለቡ ነገንና ከነገ ወዲያን፣ ከዚያም አልፈው ወራትና ዓመታትን ወደፊት ተሻግረው ማየት ወይም አጥርተው ማወቅ የሚችሉ ሰዎች አሉ። ለምሳሌ? ከፀሐይ ግርዶሽ እስከ ፖለቲካ ድረስ፣ ምሳሌ ሞልቷል።
ባለፈው ሚያዝያ ወር ውስጥ የሰማነውን ዜና አስታውሱ። የፀሐይ ግርዶሽ ክስተትን በዝርዝር የዘገበ ነው፤ ዜናው። ክስተቱ በቦታ ብቻ ሳይሆን፣ በጊዜም ሰፊ ነው፤ ከጥዋት እስከ ረፋድ።
የፀሐይ ግርዶሹ ዘገባ፣ ሁለት ወር አልፎታል። በሌላ በኩል ደግሞ፤ የፀሐይ ግርዶሹ ገና አንድ ሳምንት ይቀረዋል - ሰኔ 14 ቀን ነው የሚከሰተው።
ወራትን ተሻግረው፣ የወደፊቱን ክስተት አስቀድመው ያወቁ ሰዎች ናቸው ፤ የፀሐይ ግርዶሽ እንደሚከሰት፤ ያስረዱን። ቀኑን ብቻ ሳይሆን፤ በአዲስ አበባ ከጥዋቱ 1 ሰዓት ላይ ምን ዓይነት ቅርፅ እንደሚታይ፤ ከዚያም ፀሐይ ቀጭን ጨረቃ እንደምትመስል፤ ለ3 ሰዓት ከሩብ የፀሐይ ግርዶሹ እንደሚያበቃ፤ ከሳምንታት በፊት አይተናል - “በአኒሜሽን”።
የሳይንስ አዋቂዎች በአኒሜሽን እንዳሳዩን ከሆነ፤ በላሊበላ አካባቢ፣ ለቅንጣት ደቂቃም ቢሆን፣ ጨረቃ ከሞላ ጎደል ፀሐይዋን “ጋርዳለች”። ወይም ከሳምንት በኋላ፤ በእውን “ትጋርዳለች”።
የሰው አእምሮ፤ እውኑን አለም በትኩረት እያስተዋለ፣ መረጃዎችን ከእውኑ ዓለም ጋር እያመሳከረ፣ እውነትነታቸውን እያረጋገጠ፤ በትክክል እያገናዘበ፤ በቅጡ እውቀትን እያዳበረና በስርዓት ሳይንሳዊ አስተሳሰብን እየተቀዳጀ መጓዝ ይችላል።
ረቂቅ አቶሞችንና ደቂቅ ህዋሳትን መገንዘብ፤ የፕላኔትና የከዋክብት ምህዋርን ማወቅ የምንችለው በአእምሯችን መነጽር ነው። ደቃቃውን አጉልቶ ወይም የሩቁን አቅርቦ የሚያሳይ መሳሪያ የሚፈጠረው፤ በአእምሮ ጥበብ ነውና። ይህም ብቻ አይደለም።
የትናንት ወይም የአምና ታሪክን፣ እንዲሁም የመጪውን ሳምንት እና የቀጣዩን ዓመት ክስተቶችን ለመቃኘት የሚቻለው በዚህ ድንቅ የሰው አእምሮ ነው። ይሄ፣ “ድንቅ የጊዜ መንኮራኩር” ቢባል ያንሰዋል እንጂ አይበዛበትም። ታዲያ የወረርሽኝ ፈተናንም ሆነ የፖለቲካ ምርጫ ግርዶሽን አስቀድመን ለማየት፣ በጊዜ መንኮራኩር መጓዝ ያቅተናል? አእምሯችንን በአግባቡ ከተጠቀምን፣ ከትናንት ተምረን፣ ለነገ መልካም ነገርን መስራት እንችላለን። ይሄ ነው ትልቁ መልእክት።Read 1916 times