Monday, 15 June 2020 00:00

በተለወጠ ዘመን፤ የተለወጠ አስተሳሰብ

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(2 votes)

     “ታላቁን የሕዳሴ ግድብ እየገነባን ያለነው ሃብታችንና መብታችን በመሆኑ ነው”
           
          ግብፅና ሱዳን እ.ኤ.አ በ1959 ባደረጉትና ካይሮ ላይ በተፈራረሙት ስምምነት፣ የአሁኖቹና የቆዩ መብቶች በሚለው አንደኛ ክፍል በተራ ቁጥር አንድ፤ “ይህ ስምምነት እስከ ተፈረመበት ድረስ የተባበረው አረብ ሪፑብሊክ ይጠቀምባቸው የነበሩት የናይል ውኃዎች መጠን የቆየ መብቱ እንደመሆኑ…የዚህ የቆየ መብት መጠን 48 ሚሊያርድ ኪዩቢክ ሜትር በዓመት ሲሆን፤ ይህም በአስዋን በሚደረግ ልኬት ይሆናል” የሚል ሃሳብ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ ከግብፅና ከሱዳን ጋር እስከ አሁን ባደረገችው ድርድር፣ ግብጽ አስዋን የልኬት ቦታ እንዲደረግላት ደጋግማ ሰትጠይቅ ቆይታለች:: ከዚህም አልፋ ሕዳሴው ግድብ ላይም አንድ የሷን ተወካይ ኡጋንዳ እንዳደረገችው የማስቀመጥና የግድቡን እንቅስቃሴ መከታተል እንደምትፈልግ በግልጽ አሳይታለች፡፡ በሕዳሴው ግድብ ላይ ልትተክለው የፈለገችውን ተቆጣጣሪ ውድቅ ያደረገው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ አስዋን ላይ የሚደረግ የልኬት ጥያቄንም መጣል ይኖርበታል፡፡ አብሮ ሊጥለው የሚገባው ድርቅና ተከታይ ድርቅ በሆነ ጊዜ አሁንም ልኬት አስዋን ግድብ ላይ ተወስዶ፣ ኢትዮጵያ ከያዘችው የውሃ ክምችት አንድ ትልቅ ግብጽ የምታነሳው የድርድር ሃሳብ ነው፡፡ ወትሮም የዝናብ ጠብታ የማያውቀው የግብጽ ምድር፤ የድርቅ መክፋትም ሆነ በተከታታይ መቀጠል፣ የመለኪያ ቦታ መሆን አይኖርበትም፡፡ ይህን ኢትዮጵያ በመሬቷ በግዛቷ ውስጥ ማድረግ ግድ ይላታል፡፡
“ከባልሽ ባሌ ይበልጣል” ብሎ ነገር ሊኖርም ስለማይገባው፣ ለአጭርም ሆነ ለረጅም ጊዜ በሚቆይና በሚደጋገም የድርቅ ወቅት፣ ግብጽ የጐደላትን ውኃ ማሟላት ያለባት አሁንም ግብጽ ራሷ ናት:: የከርሰ ምድር ውሃ በማውጣት ወይም ከቀይ ባህር ውሃ በማጣራት ወይም ደግሞ የውኃ አጠቃቀም መንገዷን በመለወጥ እራሷ ልትወጣው ይገባል እንጂ በኢትዮጵያ ኪሣራ መሆን የለበትም፡፡ በእኔ እምነት፤ አስዋን ግድብ ከሚጠበቀው በታች ውኃ መያዙ አይደለም ባዶውን ቢቀር፣ የማሟላት ኃላፊነት የኢትዮጵያ መሆን የለበትም፡፡  
እስከ ዛሬ ድረስ በልዩ ልዩ የውስጥ ችግሮቻችን የአባይን ውሃና ሌሎችንም የተፈጥሮ ሃብቶቻችንን ለማልማትና ለመጠቀም ኢትዮጵያ አልቻለችም:: ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን ግንባታ የጀመረችው፣ የቀጠለችውና እስከ ፍፃሜ ለማዳረስ የምትታገለው፣ ድሃ ስለሆነች፣ የሕዝቧ ቁጥር በየጊዜው እያደገ ስለሚሄድ ለአዲሱ ወጣት ትውልድ የሥራ እድል ለመፍጠር ወዘተ ሳይሆን የመጀመሪያውና የመጨረሻ ዋና ምክንያቷ የተፈጥሮ ሀብቱ ማንም የማያዝዝበት፣ የራስ ሃብትና መብቷም ስለሆነ ለግብጽና ለሱዳን ብቻ ሳይሆን፣ ለመላው ዓለም የሰው ልጅ ልትነግረው ልታሳውቀው የሚገባ እውነት ነው፡፡ እንዲያውም ኢትዮጵያ ለሱዳንና ለግብጽ ጥርት ባለ ቋንቋ ልትነግራቸውና ልታሳምናቸው የሚገባው እውነት “ፈጣሪ አባይን ለኢትዮጵያ እንደሰጠ ሁሉ፤ አባይ ደግሞ ሱዳንና ግብጽን ለኢትዮጵያ ሰጣቸው፡፡ ስለዚህም ሱዳንም ሆነች ግብጽ የአባይ ስጦታዎች ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ስጦታዎች ናቸው” እያለች ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከግብጽ ወይም ከሱዳን የሚመጣ አጀንዳ መቀበል የለባትም፤ እንዲያውም እሷ አጀንዳ ሰጪ መሆን አለባት የሚል ሃሳብ በግልጽ እየተነሳ ነው:: ተገቢና አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡ ለሁለቱም አገሮች ልትሰጣቸወ ከሚገቡ አጀንዳዎች አንዱ፣ እራሷ በምታዘጋጀው ዝርዝር የተግባር አፈፃጸም መመሪያ መሠረት፤በአባይ ተፋሰስ አካባቢ ለሚካሄድ የአካባቢ ጥበቃ ወጪ እንዲሸፍኑ ማድረግ ነው፡፡ ወጪውን በገንዘብ አስልቶ ማስቀመጥ፣ አፈፃፀሙን የሚከታተሉበት መንገድ መዘርጋት ይቻላል:: የሚዘረጋላቸው የክትትል መንገዶች ግን በምንም አይነት የሀገራችንን ብሔራዊ ደህንነት ለአደጋ የሚያጋልጡ ሊሆን አይገባም፡፡
ይህን ስል ዝም ብዬ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ለአመታት ባካሄደችው የአፈር ጥበቃና የችግኝ ተከላ በአንዳንድ አካባቢዎች የደረቁ ምንጮች ፈልቀዋል፡፡ የተራቆተ መሬት ለምልሟል:: የዚህ ውጤት ተጠቃሚ ደግሞ አባይ ነው:: የአባይ ፍሰት ጨመረ ወይም ባለበት ቆየ ሁለቱም የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት የድካም ውጤት ነው:: ሁለቱ አገሮች ያልዘሩትን እንዲያጭዱ እድል ሊሰጣቸው አይገባም፡፡ ስለዚህም ግብጽና ሱዳን በየዓመቱ ከመስከረም እስከ ግንቦት ባለው ጊዜ፣ የሚፈለግባቸውን የአካባቢ ጥበቃ ወጪ መክፈል አለባቸው:: ካልከፈሉ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከተጠየቀው ገንዘብ ጋር ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው ውሃ በግድቡ መያዝና ወደ ሌላ ልማት ማዛወር ይኖርባታል:: ይህን ማድረግ ደግሞ ችሮታ መጠየቅ ሳይሆን የድካምን ዋጋ መቀበል መሆኑን በድርብ መስመር ማስመር ያሻል፡፡
የውኃ መስኖና የኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ዶ/ር ስለሺ በቀለ፣ እሳቸው የሚመሩት የተዳዳሪዎች ቡድን፣ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ ውል እንደማይገባ ደጋግመው ተናግረዋል፡፡ እንደ የእለት ተእለት ፀሎት መደገም ያለበት፣ ከህሊና የማይጠፋ ሃሳብ ነው፡፡ ለተደራዳሪው ቡድንና አባላቱ ያለኝ አክብሮት ከፍ ያለ ነው፡፡ “ባትረዱንም ተውን፤ ተፍጨርጭረን እንልማበት” የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ንግግር፤ ለሃሳባቸው ሁሉ እንደ መነሻ ሊወስዱት የሚገባ መሆኑን መጠቆም እወዳለሁ፤ በመለማመጥ መንገድ ግን ፈጽሞ መሆን የለበትም፡፡
“ታላቁን የሕዳሴ ግድብ እየገነባን ያለነው ሃብታችንና መብታችን በመሆኑ ነው” የሚለው መሠረታዊ ሃሳብ ጐልቶ መውጣት አለበት:: እኛ ችግረኞች አይደለንም፡፡ አራት ነጥብ፡፡
ይህ ዘመን በፍትሕ መንፈሳዊ “የኢትዮጵያ ሰዎች ከአዋቂዎቻቸው መካከል ሊቀጳጳሳት አይሹሙ” ተብሎ በደባ በተፃፈ ሕግ ኢትዮጵያዊያን የሚሞኙበት ጊዜ አይደለም:: (የአፄ ኃይለሥላሴን ነፍስ ይማር) እሱ አልፏል:: ከአፄ ናዐኩቶ አምላክ ጀምሮ ብዙ የኢትዮጵያ ነገሥታት ዐባይን ለመገደብ አስበዋል፡፡ እስከ አቶ መለስ ዜናዊ ዘመን አልተቻለም ነበር፡፡ አሁን ግድቡ ተጀምሮ ግንባታውን እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ ከዚህ በኋላ የሚያቆመው የለም፡፡ ለግብጽና ለሱዳን የሚበጀው በተለወጠ ዘመን ላይ መሆናቸውን ማወቅና መቀበል ነው::  የኢትዮጵያ መንግሥትም በተለወጠ ዘመን፣ የተለወጠ ሕዝብ እንዳለው ማመን አለበት:: የሕዳሴው ግድብ የሕዝብና የመንግሥት አጀንዳ ነው፡፡ እያንዳንዱን እርምጃ በጥንቃቄ!!   

Read 8900 times