Sunday, 07 June 2020 00:00

“ፈንቅል”? - መንግስት በትግራይ ጉዳይ ቸልተኛ ሆኗል

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(4 votes)

  በየሳምንቱ ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ በምልካቸው ማስታወሻዎቼ አማካይነት በተለያዩ  ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያለኝን አስተያየት ለማንጸባረቅ ሞክሬያለሁ:: በተለይም፡- “የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ፣ ከአፋርና ከትግራይ ብንማርስ?፣ ህወሓት ሆይ በዴሞክራሲ ሂደት መሸነፍ የዓለም መጨረሻ አይደለም፣ ዲ`ፋክቶ መንግስት - የህወሓት ህልም?፣ በዓብይ ዘመን የታሰሩ ሰዎች ለፍርድ ይቅረቡ - ይለቀቁ - ካልሆነ የቁም እስርም መፍትሄ ነው፣…” በሚሉ ርእሶች ትግራይን የሚመለከቱ ሃሳቦችን በተለያዩ ጊዜያት በዚሁ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ጽፌያለሁ፡፡ በፌስቡክ ገጼም ላይ በርካታ ሃሳቦችን በዚሁ ጉዳይ ላይ በመጻፍ ስሜቴን ገልጫለሁ:: የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ መንግስት በትግራይ ጉዳይ ቸልተኛ ሆኗል የሚል ስሜት አድሮብኛል፡፡ የትግራይ ክልል ጉዳይ እልባት ከማግኘት ይልቅ ይበልጥ እየተወሳሰበና ወደ አደገኛ አቅጣጫ እየተገፋ በመሆኑ እነሆ ዛሬም በጉዳዩ ላይ ብእሬን አንስቻለሁ፡፡ ይህቺ ማስታወሻዬም በዚሁ መንፈስ እንድትነበብ ለማሳሰብ እወዳለሁ:: ስጋቴ እስኪወገድ ጩኸቴ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ እና የህወሓት መፋጠጥ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ስልጣን ከጨበጡ በኋላ የትግራይ ጎምቱ ፖለቲከኞች ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ መቀሌ መሄዳቸው በገሃድ የተስተዋለ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ግን መሆን ያልነበረበት የህወሓት ትልቁ ስህተት ሆኖ ይታየኛል፡፡ የቦክስ ስፖርተኛ ሽንፈትን የሚከናነበው ከ“ሪንጉ” (ከመጫወቻ መድረኩ) የወረደ እለት ነው እንደሚባለው፤ ፖለቲከኛ ሽንፈትን የሚከናነበው ከፖለቲካ መድረኩ ሲወርድ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ህወሓቶች አንዴ መድረኩን ከለቀቁ በኋላ ወደነበሩበት መመለስ አስቸጋሪ መሆኑን ማስተዋል ሲገባቸው፤ “እኛ ከሌለን ሀገር መምራት አይቻልም፤ ተለምነን እንመለሳለን” በሚል ስሌት ወደ ትግራይ በመሄድ መቀሌ የመሸጉ ይመስለኛል፡፡
በሌላ በኩል፤ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የሚመሩት ብልጽግና ፓርቲ፣ ህወሓቶች “እኛ ከሌለን ሀገር መምራት አይቻልም፤ ተለምነን እንመለሳለን” በሚል ስሌት ወደ ትግራይ ሲሄዱ “መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ” በሚል መንፈስ ከሸኛቸው በኋላ፤ ህወሓት ባትኖርም ሀገርን በተሻለ ደረጃ መምራት የሚቻል መሆኑን ማሳየት ላይ ያተኮረ ይመስላል፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ብዙዎቹ የብልጽግና ፓርቲ አመራር አባላት እንደ ኢህአዴግ በማእከላዊ መንግስት ደረጃ ለ27 ዓመታት ከህወሓት ጋር በጋራ ሲወስኑ እንዳልነበር ሁሉ፤ ቀደም ባሉት ዓመታት የተሰራውን “ስህተት” ሁሉ ጠቅልለው ለህወሃት የማሸከም አዝማሚያ አንጸባርቀዋል፡፡ ህወሃቶችም ቢሆኑ “ስህተቱ ሁሉ ተጠቅልሎ ለእኛ ተሰጠ” በሚል ሆደ-ባሻነት ማለቃቀሳቸው ተስተውሏል፡፡ በዚህም ምክንያት የሁለቱ ፓርቲዎች መራራቅና ፍጥጫ ከእለት ወደ እለት እየጨመረ መጥቶ ዛሬ በትግራይ “የመነጠል ስሜት” እየተስተዋለ ነው:: የክልሉ መስተዳድርና የፌዴራል መንግስት የአንድ ሉዓላዊ ሀገር አሀዶች አይመስሉም፤ አይናበቡም፡፡ አንዱ ሌላውን እንደ ባዕድ የሚያየው ይመስላል፡፡
በሌላ በኩል፤ በአሁኑ ወቅት በትግራይ መገንጠልን የሚያቀነቅኑ ፓርቲዎች ተፈጥረዋል:: በአንጻሩ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነት ጠንካራ አቋም ያላቸው ፓርቲዎችም ተቋቁመዋል፡፡ አረና ፓርቲም በክልሉ ጽናት ያላቸው በርካታ ታጋዮችን በመያዝ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ ነው:: እነዚህ ሁሉ የህወሓት ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ … ይህ ሁሉ ብዝሃነት የሚያሳየው “ህወሃትና የትግራይ ህዝብ አንድ ናቸው” የሚለው የህወሃት አመራሮች ተረት ተረት ውሃ የሚቋጥር አለመሆኑን ነው፡፡ በርግጥ በትጥቅ ትግሉ ወቅት የትግራይ ህዝብ ከህወሓት ጎን መሰለፉ እውነት ነው፡፡ ያ ሁኔታ ግን በአሁኑ ወቅት የለም ይላሉ የአካባቢውን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ አስተያየት ሰጪዎች፡፡
ፈንቅል?
ሰሞኑን ማህበራዊ ሚዲያውን እያጨናነቁ ካሉ የመነጋገሪያ አጀንዳዎች ዋነኛ ሆኖ የተስተዋለው በመላው የትግራይ ክልል “ፈንቅል” የሚል ስያሜ የተሰጠው “የወጣቶች ንቅናቄ” ተፈጥሮ የክልሉን መንግስትና ህወሓትን ከጫፍ እስከ ጫፍ እየናጠ መሆኑ ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ አንዳንዶች “በአማራ ክልል ፋኖ፣ በኦሮሚያ ቄሮ፣ በደቡብ ዘርማ፣ በሲዳማ ኤጀቶ…” የነበረው ዓይነት የወጣቶች ማእበል ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ እውነት የዚህ ዓይነት የወጣቶች ንቅናቄ በትግራይ አለ? ማን ነው ያደራጀው? ስያሜውንስ ማን አወጣው? ዓላማና ግቡ ምንድነው?... ለሚሉት ጥያቄዎች ተጨባጭ ምላሽ ማግኘት አስቸጋሪ ነው:: ከወደ ትግራይ የምንሰማው ግን “ፈንቅል የሚባል የህዝብ ንቅናቄ የለም፡፡ ያለው የወረዳ እንሁን ጥያቄ ነው” የሚል አስተያየት ነው፡፡
በመሰረቱ ህዝብ አንዴ አደባባይ መውጣት ከጀመረ ላነገባቸው ጥያቄዎቹ ምላሽ ሳያገኝ ወደ ቤቱ አይመለስም፡፡ “ከአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ሦስት በመቶ (3%) የሚሆነውን ማንቀሳቀስ ከተቻለ ለውጥ ማምጣት ይቻላል” የሚል የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ሣይንስ ንድፈ ሃሳብ በፖለቲካ ሊቃውንት ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ ማህበራዊ ሚዲያ እየተቀባበለው ያለው “ፈንቅል” የሚል ስያሜ የተሰጠው “ንቅናቄ”፤ ከፕሮፓጋንዳ ባለፈ ምን ያህል መጠንና ስፋት እንዳለው ለማወቅ አስቸጋሪ ነው፡፡
***
በኔ እምነት ፌዴራል መንግስት ትግራይን በተመለከተ የሚያራምደው ፖሊሲ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በማእከላዊ መንግስት የሚከናወኑ ተግባራትን ስናይ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ መንግስት ትግራይን በተመለከተ የሚያራምደው “ያልተጻፈ ፖሊሲ” ይኖረው ይሆን? የሚል ጥያቄን ያጭራል፡፡ ለዚህ አባባሌ ብዙ መገለጫዎችን መጠቃቀስ ይቻላል:: ወደ ትግራይ የሚጓጓዙ ተሸከርካሪዎች የትግራይ ህዝብ ጭምር አዋጥቶ፣ ታክስና ግብር ከፍሎ በተገነቡ በፌዴራል መንግስት የሚተዳደሩ ክልል ዘለል አውራ ጎዳናዎች እንዳይሄዱ በመንደር ፊታውራሪዎች መሰናክል ሲፈጠር፣ ፌዴራል መንግስት ምን እርምጃ ወሰደ? ወደ ትግራይ የሚጓጓዙ ንብረቶች በጠራራ ፀሐይ በወሮበሎች ሲዘረፉ ምን ተባለ፣ ምን ተደረገ? እነዚህ ሁኔታዎች ህዝብን አያስከፉም? የሚሉ ጥያቄዎችን እንድናነሳ ግድ ይለናል፡፡ እህልና ሸቀጥ እስከ አሁን ድረስ ወደ ትግራይ እንዳያልፍ መደረጉና የፌደራል መንግስት ይህንን እያየ እጁን አጣጥፎ መቀመጡ፤ በዚህ ላይ የህወሓት “ተከበሃል፣ ካለ እኔ ማንም ሊደርስልህ አይችልም…” የሚል ፕሮፓጋንዳና ማስፈራሪያ ሲታከልበት ህዝቡ ውስጥ የመጠቃት ስሜት ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ይቻላል። ፖለቲከኞች የሚያገኙትን የፖለቲካ ትርፍ አስልተው ምንም ዓይነት ውሳኔ ቢወስኑ የሚገርም አይደለም፡፡ እናም ሕወሓት ይህንን ፕሮፓጋንዳ ለራሷ የፖለቲካ ፍጆታ መጠቀሟ ግልጽ ነው፡፡ ይህ ግን ፍፁም ስህተት ነው፡፡ ፌዴራል መንግስትም ቢሆን ይህንን ሁኔታ ማስተባበል አሊያም አምኖ ተቀብሎ የእርምት እርምጃ ሲወስድ አለመታየቱ ተገቢ ሆኖ አይታየኝም፡፡
በኔ እምነት ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የተሰኘቺው የፖለቲካ ድርጅት ገና ካነሳሷ “ህዝባዊ” አልነበረቺም፡፡ ነገር ግን ደርግን በመደምሰስ ሂደት ህወሓት ትልቅ ሚና እንደነበራት ሊካድ የማይገባው ሀቅ ነው፡፡ ደርግን ታግለው ያሸነፉት የህወሓት ጎምቱዎች ዛሬ (ከዘመኑ ጋር በመዘመን) ራሳቸውን ታግለው ማሸነፍ አልቻሉም፡፡ ከፖለቲከኛነት ይልቅ የትጥቅ ትግሉን አሸናፊነት በማመንዠክ ተጠምደዋል፡፡ አኩራፊዎች ሆነዋል፡፡
እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ታግለው ማሸነፍ ያልቻሉበት ምክንያት፡- ተወልደው ያደጉት የፖለቲካ ችግሮች በጥይት እንጂ በውይይት በማይፈታበት የፊውዳሉ ስርዓተ ማህበር መሆኑ፣ የሰሜኑ ማህበረሰብ የአልሸነፍም ባይነት መንፈስ ያደረባቸው መሆኑና የጎምቱዎቹ የህወሓት መሪዎች እድሜ መግፋት መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው፡፡ የህወሃት ጎምቱዎች እንደ ፍቅር እስከ መቃብሮቹ ፊታውራሪ መሸሻ እና ፊታውራሪ አሰጌ የጦርነት ነጋሪት በመጎሰም “ይዋጣልን” የሚሉትም በዚሁ ፊውዳላዊ ግብዝነት ምክንያት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ በመሆኑም፤ ጎምቱዎቹ በ60 እና በ70 ዓመት እድሜያቸው የጦርነት ነጋሪት ስለጎሰሙ ሳይሆን እስከ ዛሬ ለሰሩት በጎ ነገር ሲባል “የወንድ በር” (Safe Exit) መስጠቱ አስፈላጊ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ራሳቸውን እንዲያሸንፉ ድጋፍና እገዛ ሊደረግላቸውም ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡
እንደ መውጫ …
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ መንግስት በትግራይ ክልል ላይ እየተከተለው ባለው ለዘብተኛ አቋም ምክንያት በክልሉ ስለመለያየት እየተቀነቀነ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ህዝቡ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል፡፡ አማራጭ በማጣቱ “ከማላውቀው መልአክ የማውቀው ጋኔን ይሻለኛል” ወደሚል ውሳኔ እየተገፋ መሆኑም ይነገራል፡፡ በመሆኑም፤ እንደ ፖለቲካ ኃይል (ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ) ብልጽግና ፓርቲ እና ህወሓት ለሀገራቸው ሲሉ በልዩነት ውስጥ አብሮ መስራት የውዴታ ግዴታ መሆኑን እየጎመዘዛቸውም ቢሆን ሊቀበሉት ይገባል፡፡
በመሀል ሀገር ያሉ አክቲቪስቶችም ቢሆኑ “ህወሓት በታሪኳ የሰራቺው ፋይዳ ያለው ነገር የለም” ከሚል ተገቢ ያልሆነ ድምዳሜና ነገር ማጋጋል መውጣት አለባቸው፡፡ ህወሓት ዴሞክራሲን በማምጣቱ ሂደት ባይዋጣላትም ደርግን በመጣሉ ሂደት የነበራት ሚናና የተግባር እንቅስቃሴ አክብሮት ሊቸረው የሚገባ መሆኑም መታወቅ አለበት፡፡ ሁሉንም ነገር በዜሮ ማባዛት ማንንም አይጠቅምም፡፡ ሊቢያን የበረሃ ገነት ያደረጋት ሙኣመር ጋዳፊ፣ አምባገነንነቱ ላይ ብቻ ትኩረት ተደርጎ፣ የአይጥ ሞት እንዲሞት መደረጉ ተገቢ እንዳልሆነው ሁሉ፤ እዚህም ሌላ ስህተት መስራት የለብንም:: በህግ መጠየቅ እንደተጠበቀ ሆኖ “የወንድ በር” (Safe Exit) የመስጠቱ አስፈላጊነት ሊሰመርበት ይገባል፡፡
በህወሓት በኩል (እውነትም “ህዝባዊ ነኝ” የምትል ከሆነ) የፖለቲካ ነጥብ ለማስቆጠር የምታደርገውን ሩጫና የማያወጣ የፕሮፓጋንዳ ቱማታ አቁማ፣ ለሀገርና ለህዝብ ስትል እያራመደቺው ያለውን ግትር አቋምና “ምንጊዜም ትክክል ነኝ፣ አልሳሳትም” የሚል ግብዝነት መመርመር ይጠበቅባታል:: ካለበለዚያ “ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው” እንዲሉ የተነሳው ማዕበል ባልተጠበቀ ሁኔታ የሚጠራርጋት መሆኑ ጥርጥር ያለው አይመስለኝም፡፡ እናም ለህዝብና ለሀገር ሲባል ስልጣንን ጭምር አሳልፎ መስጠት አስፈላጊ የሚሆንበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል መገንዘብም አስፈላጊ ነው፡፡ አንድ ኃላፊነት የሚሰማው የፖለቲካ ኃይል በአንድ ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ የፖለቲካ ውሳኔ የሚያሳልፈው፣ ውሳኔው ከሚያስገኘው ጥቅም አኳያ ብቻ በመመዘን ሊሆን አይገባውም፡፡ ይልቁንም በዚያ ውሳኔ ምክንያት በሌሎች ላይ ሊደርስ የሚችልን የጉዳት መጠን ጭምር ግምት ውስጥ በማስገባት ሚዛናዊ የሆነና ተጨባጭ ሁኔታውን ያገናዘበ (pragmatic) ውሳኔ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡
እንደ ሀገር መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይም ቢሆኑ 6 ሚሊዮን የሚሆነውን የትግራይ ህዝብ ቸል ሊሉት አይገባም፡፡ የትግራይ ህዝብ ለዚች ሀገር ከማንም በላይ ከፍ ያለ መስዋእትነት የከፈለ ህዝብ ነው፡፡ ኢትዮጵያን በመመስረቱ ሂደት ቀዳሚ ነበር:: የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ድንበር ሳያስደፍር ጠብቆ ኖሯል፡፡ ብዙ መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ እነዚህን ሁኔታዎች ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ትግራይን የረሷት የመሰሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ የተካረሩ ሁኔታዎች እንዲረግቡ በሆደ ሰፊነት አዎንታዊ እርምጃዎችን ሊወስዱ ይገባል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ከህወሓት ጎምቱዎች የተሻለ አርቀው ማሰብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ ህወሓትን ማባበልም ካለባቸው አባብለው፣ የሃይማኖት መሪዎችንና የሀገር ሽማግሌዎችን ልከው ወደ ትክክለኛው መስመር መመለስ ይጠበቅባቸዋል:: ከዚህ በተጨማሪ፣ በመሀል አገርና በውጪ ሀገር ለሚገኙ የትግራይ ተወላጆች፣ ምሁራን፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ባለሃብቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አክቲቪስቶች፣ ሴቶችና ወጣቶች ጥሪ በማድረግ ማሰባሰብ፣ ማወያየትና በልዩነት ውስጥ ሀገርን ለመገንባት የጋራ አቋም በመያዝ ነገሮችን ማለዘብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በትግራይ ምሁራን በኩል ደግሞ ብሔርተኝነት ሰዎች የፈጠሩት (construct) መሆኑ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል፡፡ የትግራይ ህዝብና ልሂቃኑ ብሄርተኛነትን በዴሞክራሲ አግባብ በመግራት ለሀገራዊ አንድነቱ ቅድሚያ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የትግራይ ህዝብ ደሙን ሲያፈስ፣ አጥንቱን ሲከሰክስ፣ ልጆቹን ሲገብር፣… የኖረው ትግራይን ለመነጠል ሳይሆን እንደ ሀገር ኢትዮጵያን ለመገንባት መሆኑን ልብ ሊሉት ይገባል፡፡ ገና ብዙ መስዋእትነት ይጠብቃችኋል፣ ይጠብቀናል፡፡ ልንሰለችም ተስፋ ልንቆርጥም አይገባም፡፡ ተስፋ ቆርጦ ማፈግፈግ፤ ቀደምት አያቶቻችን የከፈሉትን መስዋእትነት የትም ጥሎ መፈርጠጥ ነው::     
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድፋሻው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 4375 times