Wednesday, 10 June 2020 00:00

ከኮሮና ቫይረስ በኋላ የሚጎበኙ 7 የዓለማችን አገራት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ኢትዮጵያና ቱኒዝያ ይገኙበታል

               በኮሮና ቫይረስ ስርጭት እጅጉን ከተጎዱ ዘርፎች መካከል የጉዞና ቱሪዝም ዘርፍ መሆኑን ያስነበበው ፎርብስ መጽሔት፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ 7 መዳረሻዎች ግን ከኮሮና ቫይረስ ማገገም በኋላ ከፍተኛ የቱሪስት መዳረሻ እንደሚሆኑ ዘግቧል፡፡
የተመረጡት መዳረሻዎች በተፈጥሮ ሀብት፣ በታሪካዊ ቅርሶችና በባህል የከበሩ መሆናቸውን የጠቀሰ ሲሆን፣የአለማችን ተመራጭ መዳረሻዎች ይሆናሉም ብሏል፤ መጽሔቱ፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ ኢራን፣ ማያንማር (በርማ)፣ ጆርጅያ፣ ፊሊፕንስ፣ ስሎቬንያና ቱኒዝያ በፎርብስ መጽሔት የተካተቱ ሌሎች መዳረሻዎች ናቸው፡፡ ከአፍሪካ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር የተካተተችው ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ቱኒዝያ ስትሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2019 ከ9.4 ሚሊዮን በላይ ጎብኝዎችን አስተናግዳለች፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ቢሊዮን ብሮችን ለመዳረሻ ልማትና አዳዲስ መስህቦችን ለማልማት የመደበ ሲሆን፣ አንድነት ፓርክ፣ አብሮነት ፓርክ፣ የእንጦጦ መዝናኛ፣ የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎችና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡
ኢትዮጵያ የአለም ስልጣኔ ሀገር ናት ያለው ፎርብስ፤ ነፃ ሀገር፣ የሰው ዘር መገኛ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን የደን ሽፋንና ተፈጥሯዊ መስህቦች እንዲሁም ከሌላው ዓለም የተለየ የአመጋገብ ባህል ከሌሎች የዓለም አገራት ተመራጭ መዳረሻ ያደርጋታል ብሏል፡፡
 ኢትዮጵያ የዘርፉን ዕድገት ለማረጋገጥ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ሽርክና አሰራርን ለመተግበር እየተንቀሳቀሰች ሲሆን የኮሮና ወረርሽኝ በዘርፉ ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ ለመከላከል በቀጣይ በጤና፣ በንፅህና፣ የቱሪስቶችን ደህንነት በማስጠበቅ ሂደት ላይ በትኩረት እየሠራች ሲሆን የቱሪስት መዳረሻዎችና አካባቢያቸውን ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ነፃ ለማድረግም የፀረ-ተህዋስያን ስርጭት ለማከናወን ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑ ታውቋል፡፡
ፎርብስ መፅሔት፤ በየዓመቱ ተመራጭ የዓለማችን የቱሪዝም መዳረሻ አገራትን በተለያዩ መስፈርቶች  እየመዘነ ደረጃዎችን የሚሰጥ ሲሆን በአለም አቀፍ ደረጃም ከፍተኛ ተቀባይነት፣ተደራሽነትና ተከታዮች እንዳሉት ይታወቃል፡፡


Read 3519 times