Print this page
Saturday, 06 June 2020 15:21

የግብጽ ዘፈን - ሁሌም ”የኔ ናይል!”

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

    ለሺህ ዐመታት የሃይድሮ ፖለቲካ መናኸሪያ የሆነው ናይል፤ በግብጽ ምድር እንደ ውሃ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አምላክ፣ እንደ ውበት ምንጭ እንደ ሰውና አማልክት መስተጋብር ጣቢያ ሲታይና ሲዘመርለት፣ ሲዘፈንለትም የኖረ ነው፡፡ ስለዚህም በደረቅ አፍ የሚጠራ ሳይሆን ቅኔ የጠገበ፣ ቁጣው የሚያስፈራ ተደርጎ ሲነገር ዘልቋል፡፡ በርግጥም ናይል ለግብጽ ሁለንተናዊ ስልጣኔ ሚናው ታላቅ ነበር፡፡ ስለ ሰማይ ጥበብ፣ ስለ ጨረቃና ከዋክብት፣ ጥናት ስነ ክዋክብት መነሻ የሆነ፣ እስከ ዛሬም ድረስ ዕውቀት ጠገብ ያደረጋቸው ይኸው ተፋሰስ ነው፡፡
እስከ ዛሬ ቱሪስት ሳቢ የሆኑ ፒራሚዶችም፣ የናይልን ተፋሰስ ተከትሎ በመጣ የስልጣኔ ዳና የተፈጠረ ነው፡፡ ጸሐፍት እንደሚሉት፤ የቀደሙ ግብጻውያን ናይልን እንደ አንዳች ተዐምራዊ ክስተት ይቆጥሩት ነበር፡፡ የዐለም ስልጣኔ ላይ የተጻፈ መጽሐፍ ‹‹world civilization›› ይላል፡፡
በመሆኑም ለናይል ብቻ የሚቀኙት ቅኔ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይነግሩናል፡፡
Adoration to nile!
Hail to thee, O nile!
Who manifestth thyself over this land.
And comesth to give life to Egypt.
ይሁንና ይህ ግብጽ ላይ ዘውድ ደፍቶ የነገሰው ዐባይ መነሻና ምንጩ የሆነቺው ኢትዮጵያ ላይ ያን ያህል አግራሞትና አድናቆት አልፈጠረም፡፡ 86 ፐርሰንት ውሃው ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች እየሄደ፣ ያን ያህል ትኩረት ባለማግኘቱ ረሃብ ሲፈራረቅብንና ዘመን ቆጥሮ ሲቀጣን ኖሯል፡፡ የሚገርመው ደግሞ በአባይ ተፋሰስ አስሩ ሀገራት፣ በዐለማችን ላይ ካሉ ደሃ የሚባሉት ሀገራት አራቱን መያዛቸው ነው:: ከሀገራቸውና ከደጃቸው ያለውን ውሃ ባለመጠቀማቸው ድህነት እየገነነባቸው ኖረዋል፡፡ ኢኮኖሚያቸውም በግብርና፣ በዝናብ ውሃ ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡
ይሁንና የዐለማችን ውሃ ዐጠር ከሚባሉት የሰሜን አፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት አንዷ የሆነችው ግብጽ፤ ከሌሎች ምድር በሚፈስስላት ውሃ ገነት ሆና በናጠጠ ኢኮኖሚ ተቀናጥታ ትኖራለች፡፡ በኢኮኖሚ አቅሟም ጠንካራ ሆና በሌሎች ጥቅም ላይ ጫና በመፍጠር ቀጥላለች፡፡
ይሄ  ናይልን ከሌሎች ከልክሎ ለራሷ ብቻ ስትጠቀምበት የኖረችው የሞኝ መዝሙር፣ አሁንም መቀጠሉ የሚያስቅና የሚያስገርም ነው፡፡ ከ2 ሺህ ዐመት በፊት ሄሮዶቱስ የተባለው የግሪክ ጋዜጠኛ፤ “ናይል ማለት ግብጽ፤ ግብጽ ማለት ናይል ናት›› በማለት የጻፈውን ነገር ይዘው፣ዛሬም  በተለወጠና በተሻለ የኢኮኖሚ አቅም ውስጥ ሳሉ ሌሎች የተፋሰሱን ሀገራት ስነልቡናዊ ጫና ውስጥ ለመጣል ሰበብ አድርገው መጠቀማቸው ትዝብት ላይ የሚጥል ነው፡፡ ይህ የሄሮዱተስ አባባል ዘመን ቆጥሮ ሁኔታዎች ከተለወጡ በኋላ የግብጽን የኢኮኖሚ ሁኔታ ያጤነችው ፖርቱጋላዊት ጋዜጠኛ፤ የቀድሞው መዝሙር ዘመኑ ማለፉንና የግብጽ ኢኮኖሚ ከዐባይ መላቀቁን ጽፋለች:: በርግጥ በሄሮዶቱስ ዘመን ግብጽ የደሃ ገበሬዎች ሀገር፣ ኢኮኖሚዋም በግብርና ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ በኋላ ግን በተሻሻለ የኢኮኖሚ ስርዐት በመመራት ባመጣችው ዕድገት፣ ከናይል ጥገኝነት መውጣትዋ የዐደባባይ ምስጢር ነው፡፡
የግብጽ ኢኮኖሚ የናይል ጥገኛ ሆኖ ቢቆይም ወደ ተሻለ የኢኮኖሚ ስርዐት መግባት የጀመረው እንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር በነበረችበት በ1882 የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎችዋን ጥሬ ሀብት ለማሟላት ዘመናዊ የጥጥ እርሻ ተግባራዊ ስታደርግ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ በ1902 የተጠናቀቀው አነስተኛ ግድብ ሲሰራ ለቀጣዮቹ ትልልቅ ፕሮጀክቶች የሚሆን ልምድ አግኝተዋል:: በተለይ ከኢትዮጵያ የሚፈስሱት ወንዞች በሚሞሉበት ጊዜ የሚፈጠረውን መጥለቅለቅ ለመቀነስ በከንቱ ወደ ሜድትራንያን ባህር የሚፈሰውን ውሃ በመገደብ፣ ለተለያዩ ልማቶችና ለሐይድሮ ኤሌክትሪክ ሀይል መጠቀም ችለዋል፡፡
ከዚያም በኋላ በ1920 ራስዋን የቻለች ነጻ ሀገር ስትሆን፣ እንግሊዝ በሱዳን ለነበራት የጥጥ እርሻ ውሃ አጠቃቀም ላይ ግጭት ተፈጥሮ፣ ወደ ሌላ ስምምነት እንዲመጡ ግድ ብሏቸዋል፡፡ ስለዚህም በ1929 በግብጽና በእንግሊዝ መካከል ስምምነት ፈርመዋል:: ይህ ስምምነት ግብጽ በየጉባኤው ይዛው የምትመጣው የቅኝ ግዛት ስምምነት ውል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ያንን ውል የታችኛው ተፋሰስ ሀገሯ ሱዳን እንኳ ትተቸዋለች፡፡
ለምሳሌ በ1958 የሱዳን የመስኖና እርሻ ሚኒስተር ስለ 1929ኙ ስምምነት ሲናገሩ እንዲህ ብለው ነበር፡-የዐባይ ውሃ ስምምነት ድርድር በሚደረግበት ጊዜ፣ አስተያየቷን እንድትሰጥ ሱዳን አልተጠየቀችም:: መብቷም ግምት ውስጥ አልገባም፡፡ በተጨማሪም ስምምነቱ በተፈጸመበት ወቅት ፣ግብጽም ሳትቀር የተሳተፈችበት የቅኝ ግዛት ጫና በሰፈነበት ሁኔታ ነበር:: እንደ እውነቱ ከሆነ ስምምነቱ በቀጥታ በግብጽና በእንግሊዝ መንግስታት መካከል ደብዳቤ በመለዋወጥ የተፈጸመ ነው፡፡
ብለው ነበር፡፡
ግብጽ ከዚህ ስምምነት ሌላ አንጠልጥላው የምትዞረው ፋይል፣ የ1959 በሱዳንና በርሷ መካከል የተካሄደው ስምምነት ነው:: ይሁንና ለሱዳን ቀደም ካለው ስምምነት የተሻለና አንጻራዊ ፍትሃዊነት የነበረው ነው:: ግብጽን በኢኮኖሚ የበላይነት ወንበር ያፈናጠጣትና ብቻዋን ዘውድ ልጫን ያሰኛት በሶቪየት ህብረት እርዳታ የሰራችውና በ19706 የተጠናቀቀው የአስዋን ግድብ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የውጭ ምንዛሪን ሚዛን ለመጠበቅ የስዊዝ ካናል ገቢም የራሱን አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል፡፡ ካናሉ ሲከፈት እንግሊዝና ፈረንሳይ ለ100 ዐመታት በነጻ ይጠቀምበታል የሚል ውል ቢኖርም፣ ከግብጹ አብዮት በኋላ በ1954 በመንግስት ተወርሷል፡፡ በአካባቢው የነዳጅ ምርት መተላለፊያና ለሌሎች የምዕራቡ ሀገራት ጥሬ እቃ ማመላለሻ በመሆን ገቢው ከፍ እያለ ሄዷል፡፡ የግብጽ የኢኮኖሚ ሂደቶች በአጠቃላይ በአምስት እንደሚከፈሉ አቶ ግርማ ባልቻ በሚከተለው መልክ አስቀምጠውታል፡፡
1952-1967 ታላላቅ የማምረቻ ድርጅቶች፣ የብረታ ብረትና ኬሚካል ኢንዱስትሪዎች በመንግስት ቁጥጥር ስር የነበሩበት፤
1967—1963 የጦርነት ኢኮኖሚ የነበረበት፤
1974—1981 የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ነፍስ የዘራበት፣ ኢንቨስተሮች የገቡበት፤
1982—1990 የውጭ ብድር ጫና የነበረበት፣ የፓሪስ ክለብ ዕዳ ቅነሳ ያደረገበት፤
1991—2007 የዋጋ ቁጥጥርን ማላላት፣ ድጎማን መቀነስ፣ የዋጋ ግሽበትንና የታክስ መጠንን መቀነስ፣ ማክሮ ኢኮኖሚውን ማረጋጋት፣ የነጻ ገበያ እንቅስቃሴ፣ ከመንግስት ተጽዕኖ ነጻ መሆን፡፡
ግብጽ የአስዋንን ግድብ ከሰራች በኋላ ኢኮኖሚዋ ተስፈንጥሯል፡፡ ከዚህም በኋላም ትልልቅ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች፣ በተለይም የቶሽካ ፕሮጀክት፣ አምስት ፕሮጀክቶችን ገቢራዊ ለማድረግ ሰርታለች:: ከነዚህ አምስት የልማት ብሎኮች፣ አራቱ ብሎኮች 50 ፐርሰንት የውሃ አቅርቦት የሚያገኙት ከናይል ተፋሰስ ሀገራት ነው፡፡ ልማቱም የተከናወነው በሶስት የአስተዳደር ክልሎች፣ ማለትም በፖርት ሳይድ፣ ኢስማኤልና ሰሜናዊ ሲናይ ነበር፡፡
አምስተኛው ብሎክ ግን በግዛት ክልሉና በባህርይው የተለየ ነበር፡፡ ዐላማው የኢኮኖሚ ልማት ቢሆንም ሌላም የፖለቲካ ዐላማ ያፈናጠጠ ነበር፡፡ በዋናነት የእስራኤልንና የፍልስጤምን የውሃ ችግር የመፍታት ሃሳብ ያለው ቢሆንም፣ በሌላ ጎኑ የናይልን የውሃ ጥያቄና ግጭት ወደ መካከለኛው ምስራቅ ማዛመት እንደነበር ጸሐፍት ያወሳሉ፡፡
ይሁንና ለዚህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ያሰማችው ድምጽ ከምንም አልተቆጠረም:: ግብጽ በየትኛውም አጋጣሚ የድሮ ዘፈኗን ‹‹ናይል ማለት ግብጽ፣ ግብጽ ማለት ናይል›› እያለች መዝፈን ነው፡፡ ከዚያ ሲያልፍም ከግብጽ ላይ አንዲት ጠብታ ውሃ ቢነካ ጦር እንሰብቃለን!›› ወደ ሚል የማያዋጣ መንገድ መሮጧን አልተወችም፡፡
በየድርድሩም የተለመደውን የ1929 እና የ1959 ስምምነት ይዛ ትሮጣለች:: ካሉት ዘጠኝ ያህል ዐለም አቀፋዊ መርሆዎች በተለይ ‹‹ቀድሞ የመጠቀም መርህን›› በመጠቀም ከእኛ ያልተረፈ ውሃ ማንም ሊጠቀምበት አይችልም›› በሚል ያረጀና ያፈጀ ዘፈን ይዘፍናሉ፡፡ በመላው ዐለም የውሃ አጠቃቀምን በሚመለከት የላይኞቹ ሀገራት የታችኞቹን ይጨቁናሉ በሚል የተደረጉትን ስምምነቶች የግሪንቢጥ ዘቅዝቀው ጭራሽ በላይኞቹ ላይ ቀንበራቸውን መጫን ይፈልጋሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ብዙ ጊዜ የተፋሰሱን ሀገራት በጦርነት ዛቻ ለማሸማቀቅ ትፈልጋለች፡፡
በኢትዮጵያ ላይ እንኳ በተለያዩ ጊዜያት የዛቱትን ዛቻ ማስታወስ ይቻላል፡፡ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ለማሸማቀቅ ሞክራለች፡፡ ለምሳሌ በ1950ዎቹ ታላቁ የአስዋን ግድብ ሲገነባ ንጉስ ኃይለስላሴ ‹‹ስለ ጉዳዩ የመንግስታችን አስተያየት መጠየቅ ነበረበት›› ስላሉ፣ የጋማል አብዱል ናስር መንግስት ካይሮ ላይ በአማርኛ ቋንቋ አቋቁመው በንጉሱ ላይ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ መንዛት ጀመሩ፡፡ በተለይ የእስልምና እምነት ተከታዮችንና የዘውዱን መንግስት ተቃዋሚዎችን በማሰለፍ መንግስትን ለመገልበጥ ሴራ አሲረው ነበር:: በዘመነ ደርግም በ1977 ዓ.ም፣ ጥቁር ዐባይና ጣና ሀይቅን በሚመለከት መንግስት ጥናት እንዲደረግ ጠይቆ፣ በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ጥናት በመካሄዱ፣ የግብጽ ፕሬዚደንት አንዋር ሳዳት የጦርነት ቀረርቶ ለማሰማት ሞክረዋል፡፡ ሰኔ 5 ቀን 1980 ዓ.ም በሳዳት የሚታዘዝ ሁለተኛ ክፍለ ጦር ለውጊያ ዝግጁ እንደነበረም ተነግሯል::  ሳዳትም በንግግራቸው እንዲህ ብለው ነበር::
“ሕይወታችን መቶ በመቶ በዓባይ ውሃ ላይ ያረፈ ስለሆነ፣ ሕይወታችንን ለማጥፋት የሚሞክር ማንም ይሁን ማን በጦር ኃይል እንቋቋመዋለን፤ምክንያቱም ለእኛ የመኖር ወይም ያለመኖር ጥያቄ ነውና!›› ብለዋል፡፡
እውነት ለመናገር ግን ግብጽ ያለ አባይ አትኖርም የሚለው የጥንት ዜማ ይሰራል ወይ! ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ይሁንና ታሪክ ሲፈተሽ ነገሩ ውሃ የማያቁርና በተጨባጭ እንደ ተረት የሚቆጠር ነው:: ስለዚህ ጉዳይ አቶ ግርማ ባልቻ የተባሉ ጸሐፊ፤ ጉዳዩ ያረጀና ያፈጀ እንደሆነ በግልጽ አስቀምጠዋል፡፡ የውሃ ሀብትንም በሚመለከት በቂ የከርሰ ምድር ውሃ ክምችት እንዳላትና የኢኮኖሚ ሁኔታዋ ከቀድሞው ፈጽሞ የተሻሻለና ከናይል ውሃ ጥገኝነት የተላቀቀ ኢኮኖሚ እንዳላት በበቂ ማስረጃ አስፍረዋል፡፡
በመረጃቸውም መሰረት፣ የአገልግሎት ዘርፉ አንደኛ፣ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ሁለተኛ ሲሆን ግብርናው ከ14 ፐርሰንት ያልበለጠ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል:: አያይዘውም፤ ግብጽ በቀጣዩ ዘመናት የተፋሰሱን ሀገራት ድርሻ ጠቅልላ መኖር የማይቻልና የማያዋጣ መንገድ መሆኑን ማወቅና በሌላ ቅኝት መጠቀማቸው ግድ ይላል ባይ ናቸው፡፡ በተለይ ውሃ ቆጣቢና የተሻለ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ቀጣዩን ዘመን ከሌሎች ጋር ተግባብታ መሄድ ይገባታል፡፡ በግብርናው ምርትም ውሃ አባካኝ ያልሆኑ ምርቶችን በተለይ የሸንኮራ አገዳ፣ ሩዝ፣ የከብቶች መኖና የመሳሰሉትን በሌሎች ተክሎች በመተካት በሌሎች ድርሻ ላይ መንጠልጠልዋን ማቆም አለባት፡፡
አለዚያ የሕዝብ ቁጥራቸው እየጨመረ የሚመጣውን የተፋሰሱን ሀገራት ዕጣ ፈንታ በማሰብ፣ መስማማት እንጂ በተለመደው መንገድ መቀጠል እንደማይቻል ማወቅ ግድ ይላታል፡፡
ኢትዮጵያ የጀመረችውን የህዳሴ ግድብ፣ ከግብ ለማድረስ ከላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ጋር በመተባበር፣ በዐለም ዐቀፉ ህግና ስምምነት መሰረት፣ የሚገባት ድርሻ ላይ አደራዳሪ ሳትፈልግ ውሃ መሙላቱን መቀጠል ብቸኛው አማራጭዋ ነው፡፡ ሶስተኛ ወገን ከማስገባትና ቀዳዳ ከማስፋት ይልቅ ከዲፕሎማሲው ጎን ለጎን የተጀመረውን ስራ መቀጠል አለባት የሚለው ሃሳብ የሚያዋጣ ይመስላል፡፡
እንደ ሕዝብም ሁላችንም የፖለቲካ ልዩነታችንን ወደ ጎን ትተን፣ በአንድነት ግድባችንን አጠናቅቀን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባናል፡፡



Read 1528 times