Wednesday, 10 June 2020 00:00

የፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ሚዛናዊነት የጎደለው የአምነስቲ  ሪፖርት
የአምነስቲ ኢንተርናሽናልን ሪፖርት በጥሞና አነበብኩት። እጅግ ስሜት የሚነኩ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በሪፖርቱ ውስጥ ተካትቷል። ግፍ ለተፈጸመባቸው  አይደለም፣ ለሰማነው እንኳን ከባድ ጸጸት ጥሎብናል። የኢትዮጵያውያን እናትና አባቶች ሆይ፤ መጽናናቱን ይስጣችሁ እላለሁ!! የመረጃው ጥራትና ሚዛናዊነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የቀረበው ሪፖርት አሳሳቢ ስለሆነ፣ መንግስት ተገቢውን ማጣራት አድርጎ፣ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ አበክሬ እጠይቃለሁ።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ሪፖርቱን ጠለቅ ብለን ስንፈትሽ ግን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት አንድ ክልልን፣ ያውም አንድ የፖለቲካ መስመርን ብቻ ተከትሎ ለምን ተዘገበ የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል። ከታሪክና ከተሞክሮ እንደምንረዳው፤ አምነስቲ በአንግሎ ሳክሰን ነጮች የተሞላ፣ በግልጽ ከሚዘግበው ባልተናነሰ የሕቡዕ ዓላማና ግብ የተበጀለት፣ ከምዕራባውያን ውጭ ሌላው የዓለም ፍጡር ሁሉ ግፈኛና አረመኔ አስመስሎ ለማሳየት የተመሰረተ ተቋም ነው።
በዚህም የተነሳ በርካቶች፣ አምነስቲን ቀለም አምላኪ ነጮች፣ የኒዮ-ኮሎኒያል ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ ያለ ክብሩና ያለ ንጽህናው በማወደስ፣ በማሞገስና ተደማጭነት እንዲኖረው በማድረግ፤ ዓላማቸውን እንዲያሳካ የሚያሰማሩት ለስላሳ ሃይል (Soft Power) ነው። ይህ ብቻ አይደለም፤ አምነስቲ የገዢዎቹን ተልዕኮ ማስፈጸሙ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በተረፈው ሰዓት፣ ጊዜና እግረ መንገዱን የራሱን “ጥሪ” እና “ተልዕኮ” አንግቦ፣ የበለጠ ለቀረበውና ለከፈለው የሚተጋ የመፈንቅለ መንግስትና የብሔር ግጭት ሴራ መጠንሰሻና መቀፍቀፊያ ተቋም እንደሆነ በርካቶች የሚስማሙበት ነው።
ወደ ሀገራችን ጉዳይ ስንመለስ፣ ባለፈው ሶስት ዓመት፣ በመንግስት ሃይልም ሆነ በታጣቂ ቡድን፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ በጽንፈኛ ቡድኖች ቀጥተኛ ተሳትፎ በሺ የሚቆጠሩ ዜጎች በግፍና በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፣ ተፈናቅለዋል፤ እህቶቻችን፣ እናቶቻችን ተደፍረዋል። በፖለቲካ ሃይሎች የጥላቻ ፖለቲካ ምክንያት፣ ያለ ምክንያት በግፍ የፈሰሰው የሱማሌው፣ የጋሞው፣ የወላይታው፣ የኦሮሞው፣ የአማራው፣ የትግራዩና የጉራጌው ደም ከመቃብር በላይ እየጮኸ ነው። በዩኒቨርስቲዎቻችን ውስጥ ሞታቸው ከንቱ ሆኖ የቀሩ ልጆቻችን፣ እምጥ ይግቡ እስምጥ መላቸው ሳይታወቅ ደብዛቸው የጠፋ እህቶቻችን ጉዳይስ የታለ!?
አምነስቲ ሆይ፤ ዛሬ ኢትዮጽያ ውስጥ ያንድ ወገን ዘገባ፣ ያንድ ቡድን ትርክት በቂ ተጫዋችና ተዋናይ አለው። ኢትዮጵያውያን የቸገረንና ዘመኑ የደቀነብን ፈተና ግን ዘር ለይቶና ብሔር ቆጥሮ የሚሰራጭን የጥላቻ ዘገባ ሰበብ እያደረገ የሚፈጸመው ፍጅትና እልቂት ነው። ይህ አልበቃ ብሎ ግን ሚዛናዊነትና ርትዕ የጎደለው፣ የአንድ ፖለቲካ መስመር ተከትሎ የሚቀነቀን፣ አንዱን አቃፊ ሌላውን አግላይ ሪፖርት፣ “የሰውን” ዘር መሰረት አድርጊያለሁ ከሚል ተቋም ሲቀርብ ማየት ከአሳፋሪነትም በላይ ነውር ነው። ስለ ሰው ዘር ፍትህና ርትዕ ከቆማችሁ፣ የሌሎቻችን ሞት፣ ስደት፣ እርዛትና ግድያ ለምን አልተሰማችሁም? ለምንስ አልቆጫችሁም?!
ብትወዱትም ብትጠሉት፤ ሌሎቻችንም እንደ ሰው ልጅና እንደ ዜጋ የሚሳሳልን፣ የሚያለቅስልን በሕይወት እንድንኖርለት የሚፈልግና የምትፈልግ እናት፣ አባት፣ እህትና ዘመድ፤ ቢያንስ ደግሞ ወገን ያለን ፍጡሮች ነን። አምነስቲ ሆይ፤ ሁሉን አቀፍ የሆነ፣ የሰውን ዘር በእኩል የሚያይ፣ ግፍና ግፈኞችን የሚጸየፍና በስማቸው የሚጠራ፣ ለፍትህ እንዲቀርቡ ጥሪ የሚያስተላልፍ ሪፖርት አሁኑኑ እንዲወጣ እንጠይቃለን።
 (ከሙሼ ሰሙ ፌስቡክ)
***

Read 6529 times