Saturday, 06 June 2020 14:27

ለሕዳሴው ግድብ የተበረከቱ ቅኔዎች

Written by  ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)
Rate this item
(0 votes)

  በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ሲጎበኙ በሥራው ከመደነቃቸውና ከመደሰታቸው የተነሣ ፍጻሜውን ለማየት እንዲያበቃቸው እንደየ ዕምነታቸው ጸሎት ያደርጋሉ፤ ሙዚቃ ይደርሳሉ፤ ተውኔት ይጽፋሉ፤ ግጥም ይገጥማሉ፤ ቅኔም ይቀኛሉ፡፡ በዚህ ረገድ ከአቶ መለስ ዜናዊ ታሪካዊ ሥራና ከኢንጂነር ስመኘው በቀለ ጥረት፤ ከዶክተር ዐቢይ አህመድ ትኩረት ጋር ተያይዘው ከተደረሱ ቅኔዎች መካከል ጥቂቶቹን ላቀርብላችሁ ወደድኩ፡፡
የፍኖተ ሰላም ሀገረ ስብከት አስተዳዳሪና የቅኔ ሊቅ፣ ሊቀ ኀሩያን አዱኛ አበበ (ከምዕራብ ጎጃም)፤ የሕዳሴን ግድብ ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው ሲጎበኙ፣ የአቶ መለስ ዜናዊን መልካም ሥራ የሚያወድሱ የተለያዩ ቅኔዎችን በግዕዝ ተቀኝተው ነበር:: ቅኔዎቹን በአማርኛ ጭምር ተርጉሜ ለአንባቢዎች አቀርበዋለሁ፡፡ በሌላ በኩል፤ በምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ የጉንደ ወይን ማርያም የቅኔ መምህር የሆኑት ጌታ አስተርአየ ሔኖክ፤ አቶ መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት በተለዩበት ወቅት ኀዘናቸውን የገለጹበትን የአማርኛ መወድስም አስነብባችኋለሁ፡፡  
እኔም፤ በብሔራዊ የሕዳሴ ግድብ አስተባባሪ ኮሚቴ ጋባዥነት ግድቡን ከጎበኘኹ በኋላ የተሰማኝን ስሜት የገለጽኩባቸውን የተወሰኑ የቅኔ ዘለላዎች እነሆ ብያለሁ። በዚህ ረገድ ከተራ ቁጥር 1-4 ያሉት ቅኔዎች የሊቀ ኀሩያን አዱኛ አበበ ድርሰቶች ናቸው:: በተራ ቁጥር 5 ላይ የተመለከተው አማርኛ መወድስ የመምህር አስተርአየ ሔኖክ ሲሆን ከተራ ቁጥር 6-13 የተሰደሩት ስምንት ቅኔዎች ደግሞ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ሥራዎች ናቸው፡፡
1. ጉባኤ ቃና በበለስ ተዐወቀ ምጽዓቱ ለወልደ መለኮት መለስ፡፡ አምጣነ አውጽአ ቆጽለ ወአሕመልመለ በለስ፡፡
ሰም፡- ቅኔው በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 21 ቁጥር 29-31 ‹የጌታ መምጣት በበለስ ታወቀ› የሚለውን ቃል መሠረት ያደረገ ነው። ፍቺ፡- የመለኮት ልጅ የሆነው የመለስ መምጣት በበለስ ታወቀ:: በለስ ቅጠል አውጥቶ ለምልሟልና፡፡
ወርቅ፡- በመለስ ዜናዊ አማካይነት ዓባይ በመገደቡ የአካባቢው ዛፍ ሁሉ ለመለመ፤ ኢትዮጵያ ተለወጠች፤ አበበች፤ የሥነ ኑረት ለውጥ መጣ፡፡
2. ጉባኤ ቃና እምትንቢተ ነቢይ መለስ አቡሁ ለክብረ ቅዱሳን ሕዳሴ፡፡
ለወልዱ ዓባይ ጸውዖ እምነ ምድረ ግብጽ ድምሳሴ፡፡
ሰም፡- ቅኔው በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 2 ቁጥር 15 “ጸዋእክዎ ለወልድየ እም ግብጽ” ‹ልጄን ከግብጽ ጠራሁለት› ከሚለው ቃል ጋር የተያያዘ ነው። ፍቺ፡- ከነቢዩ ከአባቱ ሐሳብ በመነሣት፣ መለስ የቅዱሳን የሕዳሴ ክብር ይሆን ዘንድ ልጁን ዓባይን የጥፋት ምድር ከሆነቺው ግብጽ ጠራው።
ወርቅ፡- ያለ ምንም ጥቅም እስከ ሱዳንና ግብጽ ድረስ ይፈስስ የነበረው ዓባይ፤ በሕዳሴ ግድብ አማካይነት በሀገሩ ክብር እንዲያገኝ በመለስ ዜናዊ ተጠራ:: ዓባይ በመለስ አማካይነት ለሀገሩና ለሌሎች ሀገሮች ጭምር ጥቅም እንዲሰጥ፤ ልማት ላይ እንዲውል እየተደረገ ነው፡፡
3. ዘአምሰኪየ ኃያላነ ሱዳን ወግብጽ ዘኢተሀበሉ ቅጽራ፡፡
ለምድር ብሔረ አግዓዚ እስመ ማይ ሐፁራ፡፡
ወቅርብተ ገነት ኤዶም እንተ እደ ሰብእ ኢገብራ፡፡
ሰም፡- የግብጽና የሱዳን ኃያላን የኢትዮጵያን ቅጽር ያልደፈሩዋት የአግዓዚ ሀገር የሆነችው ኢትዮጵ፤ ቅጽርዋ ውኃ ስለሆነና በውኃ ስለታጠረ ነው። ይህችም ሀገር ለገነት ቅርብ ስትሆን በማንም የሰው እጅ ያልተሠራች ናት።
ወርቅ፡- በሕዳሴ ግድብ አማካይነት ኢትዮጵያ ወሰኗን እንደምታጥርና ግድቡም እንደ መከላከያ ሆኖ እንደሚያገለግላት ቅኔው ይገልጣል።
4. መወደስ ኦ፡ መለስ መኮንነ ኩሉ፤ ዘይሰግድ ለከ ብርከ ሰብእ ዘአሜሪካ፡፡
እመ አመድካ ለኢዮር ወአመ ለምድር ሰበካ፡፡ በደመ ዚአከ ተሀጺባ፤
ምድር ብሔረ አግዓዚ ትግብር ፋሲካ፡፡
መጋቤ ገነቱ ኢትዮጵያ፤ አዳም ዓባይ ተመይጠ እምሕርካ፡፡ ለዓለም፡፡
ኢያንቀልቅል መሠረታ ዲበ ማየ ግዮን አጽናአካ፡፡ ወእም ወሰና ኢትኅልፍ ለማየ ግዮን አዘዝካ፡፡ እስመ ኃይለ ሥልጣን ተውህበከ እም ኢትዮጵያ እስከ አፍሪካ፡፡
ሰም፡- የቅኔው መነሻ በትንሣኤ አደራረስ “ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሀጺባ በደመ ክርስቶስ” የሚል መዝሙር ነው። ትርጉሙ፡- እንኳን የሰው ልጅ ይቅርና ምድርም እንኳ በክርስቶስ ደም ታጥባ ፋሲካዋን ታደርጋለች ማለት ነው፡፡ ፍቺ፡- የአሜሪካ ሰው ሁሉ የሚሰግድልህ፤ የሁሉ መኰንን የሆንኸው መለስ፤ ምድርን በወሰንካትና በሰበክሃት ጊዜ በአንተ ደም ታጥባ የአግዓዚ ሀገር የሆነችው ምድር ፋሲካዋን ታደርጋለች፡፡ አዳም ዓባይም መጋቢው ወደ ሆነቺው ኢትዮጵያ ገነቱ ከምርኮ ተመለሰ፡፡ መሠረቷ እንዳይናወጥ በግዮን ውሀ አቁመሃታልና፡፡ ከወሰኗም እንዳታልፍ የግዮንን ውሀ አዘዝካት፡፡ ከኢትዮጵያ እስከ አፍሪካ ሥልጣን ተሰጥቶሃልና።
ወርቅ፡- የመጀመሪያው ሰው አዳም በክርስቶስ ደም ከሲዖል ወደ ገነት እንደገባ ሁሉ ግዮን እየተባለ የሚጠራውና የዘለዓለም ስደተኛ የሆነው የዓባይ ወንዝም፤ በአቶ መለስ ዜናዊ ጥረት መገደቡን ቅኔው ያመሠጥራል።
5. መወደስ ክፉ ሞት በረድ በበረታ ጊዜ፤ የሚያስደነግጥ ሁሉን በደጋም ሆነ በቆላ፡፡
የሔኖክ  ፍሬ  ሕይወት  ለሁሉ  የሚደርስ በኋላ፡፡
ምንም  ሊያፈራ  አልቻለም  መለስ  ዜናዊ  ማሽላ፡፡ ተስፋ እንዳልነበረ ለድሆች በመላ፡፡
ከቆረጠው ዘንድ በነሐሴ፤ ክፉ ሞት በረድ ገና በአበባው እንደቀላ፡፡ ለዓለም፡፡
ኢትዮጵያም ይህንን አይታ ገባች ከቤቷ ጉድ ብላ፡፡ ተረድታለችና አዝመራዋን መለስ እሸትን እንደማትበላ፡፡
ሊቃውንትና ወጣት እዚህ ያለነው በጅምላ:: እናረጋጋት እናታችንን በችጋር ብዛት እንዳትጉላላ።
ሰም፡- ገና በአበባ ላይ የሚገኘውን ሰብል ኃይለኛ የክረምት በረዶ ሲመታውና ያለ ፍሬ በአጭር ሲያስቀረው ባለ አስመራዎቹ በእጅጉ ያዝናሉ፤ ለሚመጣው ዓመት ምን እንበላ ይሆን ብለውም ይጨነቃሉ፡፡
ወርቅ፡- አቶ መለስ ዜናዊ ለሀገራቸው እድገትና ልማት ገና ብዙ እንደሚሠሩ ሲጠበቁ በአፍላነት ዘመናቸው ከዚህ ዓለም በሞት ስለተለዩ፣ ሕዝባቸው ከልብ አዘነ፡፡ በኢትዮጵያ ላይም ከባድ ኀዘን ወደቀባት፡፡
6. ጉባዔ ቃና ለኢትዮጵያ መርዓት ሕዝበ ኢሎፍሊ ይፈርህዋ እሙነ፡፡ በፍኖተ ኵሉ ዓባይ ኢትዮጵያ፤ አምጣነ ታነሥእ እብነ፡፡
ሰም፡- የአካባቢ አገሮች (አማሌቃውያን) ኢትዮጵያ ሴትን በእውነት ይፈርዋታል:: የሁሉም መመላለሻ በሆነው በዓባይ ጎዳና ድንጋይ ታነሣለችና፡፡
ወርቅ፡- አንዲት ሴት በመንገድ ላይ በድንገት ድንጋይ ብታነሣ መንገደኛ ሁሉ ይህች እብድ ሴትዮ ልትመታኝ፤ ልትፈነክተኝ ነው ብሎ እንደሚፈራት ሁሉ ኢትዮጵያም በሕዳሴው መንደር ዙሪያ ሌትም ቀንም ገደል ስትንድ፤ ድንጋይ ስትፈነቅልና ስትፈልጥ፤ ብረት ስታቀልጥ፤ ስትክብ፤ ስትገነባ ያዩዋት የጎረቤት ሀገሮች ሥጋት ላይ ወደቁ፤ ፈሩዋት ማለት ነው፡፡
7. እዝል ጉባዔ ቃና በእደ ስመኘው ዮሐንስ እራቆ ሶበ ተጠምቀ እኁኁ፡፡
ዮርዳኖስ ዓባይ እንዘ ይገብእ ድኀሬሁ፡፡
ሰም፡- የቅኔው መሠረት ካህናት የጌታን ጥምቀት ምክንያት አድርገው በባሕረ ጥምቀት ላይ  ባሕርኒ ርእየት ወጎየ፣ ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኀሬሁ። አድባር አንፈርዓጹ ከመ ኀራጊት ...ማለት ባሕር አይታ ሸሸች፡፡ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ፣ ተራሮች እንደ ጊደር ዘለሉ እያሉ የሚዘምሩት መዝሙር ነው፡፡ ፍቺ፡- ክርስቶስ ዓባይ በኢንጂነር ስመኘው ዮሐንስ እጅ ራቁቱን በተጠመቀ ጊዜ ውሀው ወደ ኋላው ሸሸ።
ወርቅ፡- በኢንጅነር ስመኘውና በሌሎች ባለሙያዎች እጅ ዓባይ ሲገደብ ወደ ኋላው፤ ወደ ሀገሩ የሚመለስ መሆኑን ቅኔው ያመሠጥራል።
8 እዝል ጉባዔ ቃና ለአዳም ሜይቴክ ይቤሎ ሕገ ፈጣሪ ዘሙሴ፡፡ ትመውት ሞተ እመ ትበልዕ ወርቀ ዕፀ በለስ ሕዳሴ፡፡
ሰም፡- የሙሴ ፈጣሪ ሕገ መንግሥት አንዳንዱን የሜይቴክ ሙሰኛ፣ አዳም የሕዳሴን ዕፀ በለስ ንዋይ ከበላህ የሞት ሞትን ትሞታለህ አለው፡፡
ወርቅ፡- የሙሴ ፈጣሪ ሕገ መንግሥት አንዳንዱን የሜይቴክ ሙሰኛ፣ ለሕዳሴ ከተዋጣው ገንዘብ አጉድለሃል (ዘርፈሃልና) በሕግ ትጠየቃለህ፤ ትዋረዳለህ አለው፡፡
9. ግእዝ ጉባዔ ቃና ወሬዛ ሜይቴክ ይመስለኒ ደብተራ፤ ለነዋይ ብእሲት እስመ በምትሐት ሰወራ፡፡
ሰም፡- ጎልማሳው ሜይቴክ ደብተራ ይመስለኛል፡፡ ቆንጆይቱን ንዋይ በምትሐት ሰውሯታል፡፡
ወርቅ፡- አንዳንድ የሜይቴክ ባለ ሥልጣን የሕዳሴይቱን ብር ቢሰውርም በሕግ ተጠያቂ ሆኗል፡፡
10. ዘአምላኪየ መምህረ ሕዳሴ መለስ ወሰባኬ ወንጌል ዘዖስሎ፡፡
ኢታውጽእ አፍኣ ለዓባይ ይቤሎ፡፡
ርኁብ ዘውግከ እንዘ በቤትክ ሀሎ፡፡
ሰም፡- ቅኔው በመጽሐፍ “ለእመ ሀሎ ርኁብ ውስተ ቤትከ ኢታውጽእ አፍአ::” ማለት የተራበ  የተቸገረ በቤትህ ውስጥ እያለ ለታይታ ብለህ ወደ ውጭ አታውጣ የሚለውን ቃል መሠረት ያደረገ ነው።
ፍቺ፡- የሕዳሴ መምህርና የዖስሎ ወንጌል ሰባኪ የሆነው መለስ፤ ዓባይ ባለጸጋን በቤትህ ውስጥ ረሀብተኛ፤ ችግረኛ እያለ ሀብትህን፣ ድግስህን ወደ ውጭ አውጥተህ አትስጥ አለው።
ወርቅ፡- በዴንማርክ ዋና ከተማ በዖስሎ ስለ ሥነ ኑረት አጥብቆ ተከራካሪ የሆነው መለስ፤ የሕዳሴው ግድብ ተግባራዊ እንዲሆንና የሥነ ኑረት ለውጥ እንዲመጣ ዓባይን ወደ ውጭ አትውጣ ብሎ አዘዘው፤ አስገደደው:: ለሀገር እንዲጠቅም አደረገው፡፡
11. ሣህልከ ይቤላ ዓባይ ዘእብነ ፔካ፡፡
ለኢትዮጵያ መርዓት እንተ ትሰመይ ዓይኑካ፡፡
ፄውውኒ በውስተ ቤትኪ እኩንኪ ምህርካ፡፡
ሰም፡- የቅኔው መነሻ በመልክዓ ማርያም:: “ጊዜ ስደቶሙ ለኃጥኣን እምዓፀደ ዓባይ ፋሲካ፡፡ ፄውውኒ መንገሌኪ እኩንኪ ምህርካ” የሚለው ነው፡፡
ፍቺ፡- እንደ ዕንቁ የሚያብረቀርቀው ዓባይ ወጣት በዓይን ፍቅር የተያዘባትን ኢትዮጵያ ልጃገረድን ምርኮኛሽ አድርጊኝና በቤትሽ ውስጥ አስቀምጭኝ አላት፡፡
ወርቅ፡- ዓባይ በሕዳሴ ግድብ አማካይነት ተማርኮና ኢትዮጵያ ውስጥ ቀርቶ ጥቅም ላይ ሊውል ነው።
12 ሣህልከ. እንዘ እንዘ ትቀድህ ማየ ባሕረ መርኅባ፤ ወለተ ዓባይ ሠሐቀት ወተፈስሐት እምልባ፤ ዓቢይ በዓይነ ዚአሁ አኮኑ ቀጸባ፡፡
ሰም፡- በራስዋ ወንዝ አካባቢ ልጃገረዲቱ ዓባይ ገምቦዋን አንሥታ ውኃ ስትቀዳ በጣም ደስ አላት፡፡ ጎረምሳው ዓቢይ በዓይኑ ጠቅሷታልና፡፡
ወርቅ፡- ልጃገረድ ውኃ ስትቀዳ ያገኛት ወንድ ሲያሽኮረምማት ደስ እንደሚላት፣ ዶክተር ዐቢይ አህመድ ግንባታው ቀዝቅዞ የነበረውን የሕዳሴ ግድብ ሥራ ሲያስጀምሩት፣ የህዳሴ ግድብ ደስ  አላት፤ ሀገራችን በተስፋ ተሞላች ማለት ነው፡፡
13. መወድስ፡- ሐዋሬ ፍኖት ዓባይ ዘኢትዮጵያ፤ ኢየሱስ ንዑድ ውስተ ቅድሜሁ ኢሖረ፡፡ ምስለ አብያጺሁ ማያት በውስተ ፍኖት ኀደረ፡፡ በፍኖተ ቃና ዘገሊላ፤ ከብካበ ሕዳሴ አኮኑ ነጸረ:: ወመልዖን ለጽኅርታት፤ በማይ ጽሩይ መስነቅተ ዚአሁ ከመ ጾረ፡፡
ለዓለም፡፡
በቃናሂ ሀገረ ጉባ ዘኢተገብረ ተገብረ።
በእደ ስመኘው ወይነ ቃና ተአምረ ወመንክረ፡፡
በብዝኃ ጣዕሙ ግሩም ዘያስተፌስሕ አህጉረ፡፡
ስብሐተ ውዳሴ ኢይበቁዖ ማየ ግዮን ዘሣረረ፡፡
ክብረ ዮሴፍ ይደልዎ ማየ ግዮን ዘፈጠረ፡፡
ሰም፡- የኢትዮጵያ መንገድ ተጓዥ የሆነው ዓባይ ክቡር ክርስቶስ ወደፊቱ ብዙ አልሄደም። ከሐዋርያት ውኃዎች ጋር በጎዳና ላይ አደረ። በቃና ዘገሊላ ጎዳና የሕዳሴን ሠርግ ቤት አይቷልና። ጋን ሸለቆዎችንም ጓዙን እንደ ተሸከመ በንጹህ ውኃ ሞላቸው። ሀገረ ጉባ በተባለው በቃናም ያልተደረገ ነገር ተደረገ፡፡ በጌታ በኢንጂነር ስመኘው ተገኘ እጅ የወይን ጠጅ ውኃ ተጠምቋልና፡፡ የወይን ጠጅ ውኃ ጣዕሙ አስደናቂና የሚጠጣውን ሀገር /ሕዝብ/ ሁሉ የሚያስደስት ነው።
እናም የግዮንን ወንዝ ለሠራው ፈጣሪ ኢንጂነር ምስጋና ሲያንሰው ነው። ይልቁንም በስደት ዘመኑ ግብጽ ላይ እንደከበረው ዮሴፍ ክብርና ሞገስ ይገባዋል፡፡
ወርቅ፡- አንድ መንገደኛ ወደ መንገድ ሲሄድ ሲርበው፤ ሲደክመውና የሠርግ ድግስ ሲያይ እዚያው እየበላ እየጠጣ በመንገድ ሊያድር ይችላል። ይህም ዓባይ በሕዳሴ ግድብ አማካይነት በቤቱ ውስጥ ለማደር መገደዱን ያሳያል።
ቅኔው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያውን ተአምር በቃና ዘገሊላ ሠርግ ቤት ተገኝቶ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅነት የቀየረ መሆኑን መነሻ አድርጎ የተዘረፈ ነው። “ጋን ሸለቆዎችን በወይን ጠጅ ሞላቸው” ማለትም በግድቡ አማካይነት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ዳር ድንበር የሚገኙ የኢትዮጵያ ሸለቆዎች በውኃ የሚሞሉ መሆናቸውን ያሳያል።
  በቃና ዘገሊላ ያልተደረገ ነገር ተደረገ፤ ሲባልም በጉባ (በጉሙዝኛ ብርሃን ማለት ነው) ለጎረቤት ሀገሮች ሁሉ የሚበቃ ታላቅ ታሪክ እየተሠራ መሆኑን ያስገነዝባል። ይኸውም በኢንጂነር ስመኘውና በሌሎች ባለሙያዎች ወርቃማ እጅ ታምርና ድንቅ ነገር መሠራቱን፤ እንደ ወይን ጠጅ የተቆጠረው ውኃም ከጣዕሙ ብዛት የተነሣ ሰውን /ጠጭውን፤ የአካባቢ ሀገሮችን ሁሉ) እንዳስደሰተ ይገልጻል። እናም ይህንን የዓባይን ውኃ ለፈጠረው ፈጣሪ፤ [ለአቆመው መንግሥት፤ ለገደበው ባለሙያ፤ በአጠቃላይ በግድቡ ላይ አሻራቸውን ለአስቀመጡ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ምስጋና ያንሳቸዋል፡፡ ይልቁንም በስደት ዘመኑ ግብጽ ላይ እንደከበረውና በፈርዖን ፊት ሞገስ አግኝቶ ወገኖቹን እንደጠቀመው ዕብራዊው ዮሴፍ ክብርና ሞገስ ይገባዋል ማለት ነው፡፡ እና ዓባይም በስደት ዘመኑ ለግብጽና ለሱዳን ታላቅ ጥቅም እንደሰጠ ሁሉ ዛሬ መገደቡ ለኢትዮጵያ ታላቅ ኩራት፤ አስተማማኝ የልማትና የብርሃን ተስፋ መሆኑን ቅኔው፡ ይገልጻል፡፡Read 613 times