Saturday, 06 June 2020 14:11

“ከ25 ሚ. በላይ ኢትዮጵያውያን እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከ25 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ለእርዳታ ጠባቂነት መዳረጋቸውን የአለም የምግብ ፕሮግራም አስታወቀ፡፡
ከዚህ ቀደም በድርቅና በተለያዩ ተፈጥሮአዊ ምክንያቶች 15 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን እርዳታ ጠባቂ እንደነበሩ ያወሳው ሪፖርቱ፤ ተጨማሪ 10 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት የሰው እጅ ጠባቂ ሆነዋል ብሏል፡፡
በከተማ በዋናነት የኮሮና ወረርሽኝ ስጋት የተረጂዎችን ቁጥር ማሳደጉን፣ በገጠር ደግሞ ከኮሮና በተጨማሪ የአንበጣ መንጋ በሰብል ላይ ያደረሰው ጉዳት ተደማምሮ ለችግሩ መባባስ አይነተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ተመልክቷል፡፡    
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የኮሮና ወረርሽኝ፣ የአንበጣ መንጋ እንዲሁም ድርቅና የጐርፍ አደጋዎች በመተባበር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን የሰው እጅ ጠባቂ እያደረጉ መሆኑን የገለፀው የተቋሙ ሪፖርት፤ የበለጠ ቀውስ እንዳይከተል መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስቧል፡፡
ባለፈው ሚያዚያ ወር ብቻ ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ 3 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ለእርዳታ ጠባቂነት ተዳርገው እንደነበር ያስታወሰው ሪፖርቱ፤ ይህ አሃዝ በየጊዜው እየጨመረ መሆኑንና በቀጣይም ሊጨምር እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡
ባለፈው ሣምንት የኮሮና ወረርሽኝ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተቋቋመው የፀረ ኮሮና የሚኒስትሮች ኮሚቴ ባካሄደው ስብሰባ ወቅት 30 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ለሰው እጅ ጠባቂነት ሊዳረጉ እንደሚችሉ ተገልፆ እንደነበር ይታወቃል፡፡


Read 8311 times