Saturday, 06 June 2020 14:08

በመጪዎቹ 2 ሳምንታት የበሽታው ስርጭት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል የሚል ስጋት አለ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

  - በአንድ ሣምንት ብቻ ከ900 በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል
       - 49 የጤና ባለሙያዎችና 16 የሆስፒታል ሠራተኞች በቫይረሱ ተይዘዋል
              
           በመጪዎቹ ሁለት ሣምንታት የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ስርጭት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል የሚል ስጋት መኖሩን የህክምና ባለሙያዎች ጠቁመዋል፡፡
ህብረተሰቡ በሽታውን ለመከላከል በሚወሰዱ እርምጃዎች ላይ የሚያሳየው ቸልተኝነት ከወቅቱ የአየር ሁኔታ ጋር ተዳምሮ የበሽታውን ስርጭት ሊያባብሰው እንደሚችልም ተሰግቷል፡፡
በአገራችን በቫይረሱ የተያዘው የመጀመሪያው ሰው መገኘቱ ሪፖርት ከተደረገበት ከመጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ወዲህ ያለፈው ሣምንት እጅግ ከፍተኛው የቫይረሱ ተጠቂዎች የተገኙበት ሣምንት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በትናንትናው ዕለት በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠው 169 ሰዎች ጋር በአንድ ሳምንት ብቻ 974 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ታውቋል፡፡ ከእነዚህ የኮረና ታማሚዎች መካከል አብዛኛዎቹ የውጪ አገር የጉዞ ታሪክም ሆነ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንኪኪ የሌላቸው እንደሆኑ ተረጋግጧል፡፡
በአገሪቱ እስከአሁን ድረስ በቫይረሱ ከተያዙት 1805 ሰዎች መካከል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ሲሆኑ፤ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ከፍተኛውን የስርጭት መጠን በመያዝ ቀዳሚ ሆኗል፡፡ ልደታ ክፍለከተማም ከኮረና ታማሚዎቹ ከ250 በላይ የኮሮና ታማሚዎችን በመያዝ ይከተለዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችም በቫይረሱ እየተያዙ ነው፡፡ እስከአሁን ድረስ 49 የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎችና 16 ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች በአጠቃላይ 65 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል፡፡ በቫይረሱ ከተያዙት በጥቁር አንበሳና በጳውሎስ ሆስፒታል ውስጥ የሚሰሩ ሃኪሞችና ነርሶች እንደሚገኙባቸው ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
ይህንኑ የጤና ባለሙያዎች ለበሽታው ያላቸውን ተጋላጭነት ለመቀነስ የጤና ሚኒስቴር የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጿል፡፡ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱን ተከትሎ የጤና ባለሙያዎች ለበሽታው ይበልጥ ተጋላጭ እየሆኑ መምጣታቸውን የገለፀው የጤና ሚኒስቴሩ መግለጫ ከዚህ በተጨማሪም የኮቪድ 19 ህሙማንን ለሚያክሙ 1750 የሚደርሱ የጤና ባለሙያዎች የሚያገለግሉ ጊዜያዊ የመኖሪያ ቤቶች ማዘጋጀቱንና ባለሙያዎቹ በቫይረሱ ቢያዙ ተጋላጭ ቢሆኑና ቢታመሙ ተለይተው የሚቆዩበትና የሚታከሙበት ሥፍራ መዘጋጀቱን ጠቁሟል፡፡ ህብረተሰቡ ራሱን በመጠበቅ የባለሙያዎችን ጫና እንዲቀንስ የጤና ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል፡፡
በአሁኑ ወቅት 24 የምርመራ ማዕከላት በስራ ላይ የሚገኙ ሲሆን አራት ተጨማሪ ደግሞ ሰሞኑን ሥራ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል:: 16 ላብራቶሪዎችም በዝግጅት ላይ ይገኛሉ ተብሏል፡፡
40 ጽኑ ህሙማንንና 1200 የኮሮና ታማሚዎችን ለማስተናገድ ይችላል የተባለው የሚሊኒየም አዳራሽም ህሙማንን ተቀብሎ ማስተናገድን ጀምሯል፡፡ በአዳራሹ ላብራቶሪ፣ መድሃኒት ቤት፣ የጤና ባለሙያዎች የልብስ መቀየሪያና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ቦታዎች የተዘጋጁ ሲሆን፤ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የአየር ስርዓት ፍሰቱን ለማስተካከል የሚረዱ መሳሪያዎችም ተገጥመውለታል፡፡
በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጦ በለይቶ ማከሚያ ስፍራዎች ህክምና እየተደረገላቸው  ከሚገኙ ህመምተኞች መካከል ከሆስፒታል እየጠፉ የሚሄዱ መኖራቸውን ምንጮች ጠቁመዋል:: ከደቡብ ክልል በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጦ ከማቆያ እየጠፉ የሚመጡ ሰዎች ኮሮናን የመከላከል ሥራችንን ከባድ አድርጐብናል ብሏል፡፡ የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አቀናው ቀውዛ፣ ግንቦት 21 ቀን 2012 ዓ.ም በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጠ 95 ሰዎች መካከል ሶስቱ ጠፍተው ወደ ደቡብ ክልል መግባታቸውንና በፍለጋ መያዛቸውን፣ በተመሳሳይ መንገድ የገቡ ሌሎች ሁለት ሰዎች አሁንም አለመገኘታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል::
የጤና ሚኒስቴር በሪፖርቶቹ ይፋ እንደሚያደርገው በኮረና ቫይረስ መያዛቸው ከሚረጋገጡ ሰዎች መካከል ለሌላ ህክምና ሄደው ምርመራ ሲደረግላቸው በቫይረሱ መያዛቸው የሚታወቅ ሰዎች ያሉ ሲሆን እስከአሁን በቫይረሱ ሳቢያ መሞታቸው ከተረጋገጡት 18 ሰዎች መካከል አምስት ያህሉ ከሞቱ በኋላ በተደረገላቸው ምርመራ ቫይረሱ እንዳለባቸው የታወቁ ናቸው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በደቡብ ክልል ካፋ ዞን በድንገት በተፈጠረ ፀብ ሳቢያ ህይወቱ ያለፈ አንድ ሰው ለአስከሬን ምርመራ ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ቫይረሱ እንደተገኘበት ታውቋል፡፡  

Read 9426 times