Monday, 01 June 2020 00:00

የፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

    የዜግነት አርአያ
አገሩ አሜሪካ ነው፤ ከተማው ሚኒአፖሊስ ነው፤ የተገደለው ጥቁር አሜሪካዊ ነው፤ ገዳዩ ነጭ የአሜሪካ ፖሊስ ነው፤
 አሜሪካ በሙሉ ተረበሸ፤ ግድያውን አደባባይ ወጥተው የተቃወሙት ነጮችም፣ ጥቁሮችም አሜሪካኖች ናቸው፡፡
በአንድ አገር ስሕተት ይፈጸማል፤ ጥፋት ይሠራል፤ ስሕተቱን ወይም ጥፋቱን ጎሣው፣ ወይ የቆዳው ቀለም፣ ወይ
 ቋንቋው፣ ወይ ሃይማኖቱ፣ ወይም ቁመቱ አይሸፍነውም፤ ዜጋ ሁሉ አብሮ ይቆማል፤ ዜጋ ሁሉ መንግሥቱን ያርማል፤
 ዳኛውም ትክክለኛውን ፍትሕ ለሁሉም ይሰጣል፡፡
(ከመስፍን ወልደ ማርያም ፌስቡክ)
ግንቦት 2012
 
ሕገ መንግሥትና ምርጫ
የመገለባበጥ ጨዋታ ውስጥ የሚገለባበጡት ሰዎች እርስበርሳቸው ሲተያዩ መገለባበጣቸውን ይመለከታሉ፤ በመመልከትም አእምሮአቸው አዙሪት ውስጥ ይገባል፤ ከመገለባበጡ ተመልሰው ሲቆሙ ወይም ሲያርፉ አዙሪቱ አይለቃቸውም፤ ዛሬም በመገለባበጥ ላይ ናቸው፤ ስለዚህ ከእነሱ ቁም-ነገር ለማግኘት መሞከር ሕዝብን ለማታለል ካልሆነ ሌላ ፋይዳ የለውም፡፡
በመሠረቱ የሚደንቀኝ ግን ሕግን ለመጣስና ሕግን ለማስጣስ መሣሪያ የነበሩ ሰዎች ተሰብስበው ስለ ሕገ መንግሥት መኖርና አለመኖር ሲከራከሩ ማየቱ ነው፤ አንዳንድ የላቀ አእምሮ ያላቸው ሰዎችም እዚህ ዶሮ ማታ፣ ዶሮ ማታ ጨዋታ ውስጥ መሳተፋቸው ነው፤ የግብዞችን ውይይት ስሰማ ረስቼው የነበረውን የሮማውያን ገዢ ማርከስ ኦሪልየስን ጽሑፍ አስታወሰኝ፤ ከሞት የሚያመልጥ የለም፤ የሕገ መንግሥቱ መሀንዲስ ሲፈልገው ፕሬዚደንት፣ ሲፈልገው ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆነው፣ ሲፈልገው ይህን አንቀጽ፣ ሲፈልገው ይህኛውን አንቀጽ ከሕገ መንግሥቱ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ የሚሰርዘው ዛሬ የለም፡፡
እግዚአብሔር ከመሸጦነትና ከኮሮና ይጠብቀን!
(ከመስፍን ወልደ ማርያም ፌስቡክ)
ግንቦት 2012
 
‹‹ህጋዊ›› ህገወጥነት
ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ መንግስት ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቷል፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ደግሞ ጫት ማስቃሚያ ቤቶችን እንዲዘጉ ይደነግጋል፡፡ ከዚህ በዘለለ ጫት ማምረትም ሆነ ለገበያ ማቅረብ አልተከለከለም፡፡ በደሴ ከተማ የሆነው ከዚህ ውጪ ነው፡፡ ጫትም ከማሳ ቆርጠው ወደ ገበያ ከሚወስዱና ከሚሸጡ ሰዎች ተሰብስቦ እንዲቃጠል ማድረግ በዜጎችም፣ በሀገርም ላይ ተጨማሪ ጫና መፍጠር ነው::
በወረርሽኙ የተነሳ፣ በተለይ በአዲስ አበባ እንደምናየው፣ በአነስተኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ ዜጎች፣ የእለት ጉርስ ገዷቸዋል፡፡ ይህ እንደ አዲስ አበባ ባይሆንም በሌሎች ከተሞችም እየታየ ነው፡፡ ወረርሽኙ ጦም ያሳደራቸውን መደገፍ ሲገባ ሌላ ተቸጋሪ፣ ጦም አዳሪ መፍጠር ምን የሚባል ነው?
‹‹የ150 ሺህ ብር ጫት አቃጠልን››ብሏል፣ የአማራ ክልል ኮምኒኬሽን ቢሮ፡፡ ከዚሁ ጋር የሚከተሉትን ጥያቄዎች ይመልስ፤ ‹‹ከተቃጠለባቸው ውስጥ ስንቱ የእለትና የሳምንት እቁቡን ሳይከፍል ቀረ? ስንቱ ማፍጠሪያ ሳንቡሳና ቴምር ሳይዝ ገባ? ስንቱ መነገጃውን አጣ? ተበድረው ለንግድ የወጡ ስንቶች ነበሩ? ቀን ከሚያተርፉት አመሻሽ ላይ እዳቸውን የሚከፍሉ ነበሩበት?...››
ሀገሪቷ ወደ ውጭ እየላከች የምትለማበትን ጫት፣ ዜጋው ሸጦ የእለት ጉርሱንና ያመት ልብሱን እንዳያገኝ ማድረግ ፍጹም ህገወጥነት ነው፡፡ ጫትን ማምረትም ሆነ መቃም በሀገሪቱ ህገወጥ ተግባር አይደለም፡፡ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች፣ ባለፉት አመታት ብዙ ገበሬዎች የአትክልት ጓሯቸውን፣ የሰብል ማሳቸውን ወደ ጫት ማሳ ቀይረዋል፤ የተሻለ ገቢ አግኝተው ኑሮአቸውን ለማሻሻል፡፡
ይህ ተግባር ሀገሪቱ ጫትን እንደ አደንዛዥ እጽ በህግ እስካላገደች ድረስ ህገወጥ ነው፡፡ ይህን ያደረጉ አካላት መጠየቅ አለባቸው:: ስልጣን፣ የፖሊስ ዩኒፎርም መልበስና ጠመንጃ ማንገት የህገወጥነት ሰርተፊኬት አይደለም፡፡ የተቃጠለባቸውም ዜጎች የንብረታቸው ዋጋ ሊከፈላቸው ይገባል፤ ከይቅርታ ጋር፡፡
በርግጥ ጫት ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ከፍተኛ ቢሆንም፣ በዜጎችና በሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው፡፡ መንግስት ይህን ችግር ለመቅረፍ፣ መጀመሪያ በጥናት ላይ ተመስርቶ፣ ጫትን በማምረትና በመሸጥ ላይ የተሰማሩ ዜጎች፣ በሌሎች የስራ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
(ከበድሉ ዋቅጅራ ፌስቡክ)
 ግንቦት 2012

የዲጂታል ዘመንና አዲሱ ትውልድ
የግንቦት 20 የደርግ አገዛዝ ውድቀት ለሁለት አስርት ዓመታት አንድ ሐሙስ ሲቀረው እውን የሆነ ክስተት ነው። ትግሉ የትውልዱን የሕይወት መስዋዕትነትን ብቻ ሳይሆን የጊዜንም መስዋዕትነት ጠይቋል።
ይኼኛውና መጪው የዲጂታል ዘመን ትውልድ ግን በዚህ ደረጃ የጊዜን መስዋዕትነት የሚፈልግ አይመስልም። በዲጂታል ዘመን “ጥራኝ ጫካው” በ”ጥራኝ ፌስቡክ” ተቀይሯል። በዲጂታል ዘመን መረጃን ፍለጋ አያሌ ኪሎ ሜትሮችን መኳተን አያስፈልግም፣ እኛ ወደ መረጃው ሳይሆን መረጃው ራሱ እስካለንበት ቦታ ድረስ ይመጣል። በዲጂታል ዘመን ስብሰባ ለማካሄድ የግድ ሰፋፊ አዳራሾች አያስፈልጉም፤ መረባዊ ትስስሮች የቪዲዮ ኮንፍረንሶች፣ የቴሌግራም ግሩፖች የስብሰባውን ሚና እየተኩ ከመጡ ሰነባብቷል።
የአሁኑና መጪው ትውልድ 20 እና 30 ዓመታት ጫካ ውስጥ ገብቶ ሽምቅ ውጊያ ለማድረግ ጊዜም የለውም፤ ሁሉንም ነገር በቶሎ ማግኘትን ኢንተርኔቱ አለማምዶታልና ሌላውም እንዲሁ እንዲሆንለት ይፈልጋል። ስለዚህም ከጫካው የደፈጣ ጦርነት ይልቅ የከተማ ውስጥ አመፆችን ማድረግ ምርጫው ነወ። ጉዞውን ከከተማ ወደ ደደቢት፣ ከዚያም ወደ ቤተ መንግስት ሳይሆን ከመኸል ከተማ በቀጥታ ወደ ቤተ መንግስት ማድረግም መንገዱ ነው። ትውልዱ ጠመዝማዛ መንገድን አይወድም፣ ዳገት መውጣት ጋራ ሸንተረሩን ማካለል አይፈልግም..የቀጥታ መስመር ጉዞ ሕልሙ ነው..በሂሳብ የተማርነው “The shortest path” እሱም አይደል? ለዚህም ከጥቂት ዓመታት በፊት በአረቡ ዓለም የተቀጣጠለውን የከተማ አመፆችን (The Arab Spring) በምሣሌነት ማንሳት ይቻላል፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት በሀገራችን የተቀጣጠለው የቄሮና ፋኖ አመፆችም በጥራኝ ጫካው ሳይሆን በጥራኝ ፌስቡክ ዘመቻ የተከሰቱ ነበሩ።
ስለዚህም መንግስታት ለወቅቱ ሁኔታ ወቅታዊና ዘመኑን የሚመጥን አመራር መስጠት ግድ ሊሆንባቸው ነው። ለምሣሌ በዚህ በሶሻል ሚዲያው ዘመን አያሌ “Informal” ማዘዣ ጣቢያዎች በየሰፈሩ እንደ አሸን ፈልተዋል። መንግስታትም ለ”Informal” ማዘዣ ጣቢያዎች “Informal” ዕወቅና የሰጡ ይመስላል።
በዚህ ዘመን የሶሻል ሚዲያን የመረጃ ሠራተኞቹን መድቦ የማይከታተል መንግስት ይኖራል ብሎ ማሰብ አይቻልም... በአደባባይ ለሶሻል ሚዲያ በተለይም ለፌስቡክ ያላቸው ትኩረት እምብዛም እንደሆነ ለማስመሰል የሚያደርጉት የይምሰል ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ። እናም ዛሬ መንግስታት ተቀናቃኞቻቸውን “መንገድህን ጨርቅ ያድርግልህ” የሚሉበት ሳይሆን ትውልዱ መንግስትን “መንገድህን ጨርቅ ያድርግልህ” የሚልበት ዘመን ነው። ይህን ስል ግን ካለፈው ዘመን እየተንጠባጠቡ የመጡ ሙሉ በሙሉ ለመክሰም ጊዜ የሚፈልጉ የ”ጥራኝ ጫካው” ርዝራዦች ዛሬም የሉም እያልኩ አይደለም፡፡ ዕውቁ ፈላስፋው ኢድመንድ በርክ..In what we improve we are never wholly new; in what we retain, we are never wholly obsolete” እንዲል! የድንበር ላይ መስመሩ ደማቅ ሳይሆን “Blurred” ነው እንደ ማለት።
(ከጌታሁን ሔራሞ ፌስቡክ)
 
ትንሽ ስለ “ግንቦት 20”
ስለ “የካቲት 11” ብዙ ስሜት የለኝም፤ ስለ “ግንቦት 20”ም እንዲሁ! ስለ ህወሓት ትግል ግን አንፀባራቂ ስሜት አለኝ።
የካቲት 11
ዘውዳዊው አገዛዝ ተገርስሶ መስከረም 2, 1967 ዓ.ም ደርግ (officially) ስልጣን ያዘ። የካቲት 11, 1967 ዓ.ም ተሓህት (ህወሓት) ጫካ ገባ። ደርግ ስልጣን ከያዘ ከ6 ወር በኋላ መሆኑ ነው። በ6 ወር ግዜ የደርግን ፖለቲካዊ ማንነት ለመገምገም (ለማወቅ) ያንሳል። ደርግ ጥሩ ይሁን መጥፎ  ለመገንዘብ... ! ከመስከረም 2 እስከ የካቲት 11, 1967 ዓ.ም ሽግግሩ “ሰላማዊ” ነበር ማለት ይቻላል።
ግን የደርግን ተፈጥሮ ጥሩም ይሁን መጥፎ በውል ሳይታወቅም የህወሓት መሪዎች በረኻ መውረዳቸው በራሱ ስህተት ሊሆን አይችልም። ደርግ የፈለገ ባህሪ ይኑረው ህወሓቶች የራሳቸውን ታሪክ ማስፃፍ፣ የራሳቸውን ጀግንነት መስራት ፈልገው ቢሆንስ!? መውጣታቸው ልክ ነበር።
የደርግ ጭካኔ
ትግሉ በሆነ አጋጣሚ ይጀመር፤ ከተጀመረ በኋላ ግን የደርግ አምባገነናዊ ባህሪ በግልፅ ወጥቷል። ትግራይ ውስጥ ግፍ ተፈፅሟል። አሰቃቂ ድርጊቶች ተከናውነዋል። ደርግ ፍፁም አረመናዊና መወገድ ያለበት ስርዓት መሆኑን ራሱን አጋልጧል።
የህወሓት ትግል
የታጋዮቹ ቆራጥነት፣ አሳቢነት፣ መስዋእትነት ፍፁም ተዓምራዊ ነበር። ለወደፊትም አይደገምም! ስንዘክረው እንኖራለን። ሁሉም የበረኻ ታጋዮች ክብርና አድናቆት ይገባቸዋል። ሦስት ሰዎች ግን በተለየ አደንቃለሁ። በቅደም ተከተል፡-
1. ሐየሎም አርአያ
ጀግንነቱን ለመግለፅ ቃላት ያጥሩኛል። ታግሎ ደርግን ከስልጣን አባረረ። ማንንም ሳይጎዳ፣ ሳይበድል፣ ሳይዘርፍ፣ ፍትሕ ሳያጓድል፣ በጓዶቹ እንደተወደደ አለፈ። ጀግናችን ነው።
2. ኢያሱ በርሀ
ስነ ጥበበኛ! ትግሉን በጥበብ ያነሳሳ፣ ያደራጀ፣ የመራ፣ ልዩ ፍጥረት!
3. መለስ ዜናዊ
የፖለቲካ አስተሳሰቡን አልደግፍም። እንደውም እቃወመዋለሁ። የፖለቲካ አረዳዱና ሁኔታዎችን የመገንዘብና የመግለፅ ዓቅሙ ግን እጅግ የሚገርም ነው፤ በዚሁ አደንቀዋለሁ።
ስለ አጠቃላይ ትግል
ወላጆቻችን የልጅነት ዕድሜያቸውን፣ ጊዜያቸውን፣ ውድ ህይወታቸውን መስዋእት አድርገውና አካላቸው ጎድሎ የደርግን ስርዓት ስላባረሩልን እናመሰግናቸዋለን። እነሱ ባያደርጉት ኖሮ ዕዳው ለኛ ይተርፍ ነበር። ግን ደርግን ከስልጣን ማባረር በራሱ ግብ ነበር? ደርግን ማባረር means እንጂ በራሱ ግብ (end) አልነበረም፤ ሊሆንም አይችልም። ደርግ ተባረረ። ከዛ ምን?
የትግሉ ዓላማ
የትግሉ ዓላማ የደርግን ስርዓት ከስልጣን አስወግዶ ሌላ የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ነበር፤ ወይም መሆን ነበረበት። በደርግና በህወሓት መካከል የነበረው ልዩነት የሰዎች ወይም የቋንቋ ወይም የሀይማኖት ሳይሆን የስርዓት ነው። የባለ ስልጣናት ለውጥ የስርዓት ለውጥ ላያሳይ ይችላልና። እናም የትግሉ ዓላማ ፍትሕ፣ ነፃነትና እኩልነት የሚያስሰፍን የፖለቲካ ስርዓት በመገንባት ጭቆናና የእርስ በርስ ጦርነት ስጋት ዳግም የማይፈጠርባት ሀገር ማየት ነበር።
ታድያ ትግሉ ግቡን መቷል? አልመታም!
ግንቦት 20
መገምገም ያለበት ከትግሉ ዓላማ መሳካትና ግብ መምታት አንፃር ነው። በትግሉ ጊዜ “እኔ ቀድሜ ልሰዋ፥ አንተ ትንሽ ቆይ” በሚል የአሳቢነት መንፈስ ጓዶች ፈንጂ የረገጡበት ዓላማ አሁን ላይ “እኔ ቀድሜ ልብላ፥ አንተ በረሃብ ሙት” ወደ ሚል የስግብግብነትና የጭካኔ ደረጃ ተሸጋግሯል። በዚሁ የስሕተት መንገድ የዴሞክራሲ ስርዓትም ሳይገነባ፣ ፍትሕ፣ ነፃነትና እኩልነትም ሳይሰፍን እነሆ ወደ ኋላ ተመልሰን የአዙሪት መንገድ ይዘናል።
አሁንም ሰላማዊ ዜጎች በጠራራ ፀሓይ በመንግስት የፀጥታ ሐይሎች የሚገደሉበት ጊዜ ላይ ነን።
አሁን ትግራይ ውስጥ በትጥቅ ትግል የሚፋለም፣ የተወሰነ መሬት በሐይል የተቆጣጠረ (ሓራ መሬት ያለው) ሕገ ወጥ ሽምቅ ተዋጊ በሌለበት ንፁሃን ዜጎች እየተገደሉ፤ ልክ በደርግ ዘመን እንደነበረ መንግስት፣ ሁሉንም አካባቢዎች ገና ሳይቆጣጠር፣ በጠመንጃ የሚፋለሙና የሚያስቸግሩ ሽምቅ ተዋጊዎች (እንደ ህወሓት ዓይነት) ቢኖሩ ኖሮ፣ የህወሓት መንግስት በቀን ስንት ንፁሃንን ይገድል ነበር?
ደርግ የህወሓት ታጋዮች ትግራይ ውስጥ ባይንቀሳቀሱ ኖሮ (በዚያ ጊዜ ትግራይ ውስጥ ዓማፂ ቡድን ባይኖር ኖሮ) የደርግ ወታደሮች ወደ ትግራይ ይመጡ ነበር? ምን ሊሰሩ? ሓውዜንና ሌሎች የትግራይ አካባቢዎችን ይደበድቡ ነበር? ለምን ሲባል? ሌላ ቢቀር የጦር መሳርያ ለማባከንስ ይፈልጉ ነበር?
ህወሓት መኖር አልነበረባትም አላልኩም። ነጥቡ፤ ህወሓት ደርግ የገጠመውን ፈተና ቢገጥማት ኖሮ ከደርግ ትብስ ነበር ነው።
ህወሓት ለውጥ ማምጣት ይጠበቅባት ነበር። ድሮ ወላጆቻችን የታገሉለት የፍትሕ፣ የነፃነትና የእኩልነት ጥያቄ አሁንም እንደራበን ነው። በቀጣይ ትግል ይረጋገጣል! የትግሉ ዓላማ ግቡን ስላልመታ ነው “ግንቦት 20” ስሜት የማይሰጠኝ!
(ከአብርሃ ደስታ ፌስቡክ)

ህወሓት 2 ምዕራፎች
በህወሓት ታሪክ ከግንቦት 20, 1983 ዓ.ም በፊት እና በኋላ ያለው ዘመን ለያይተን መገምገም ይኖርብናል። ከ1983 ዓ.ም በፊት የነበረው የትግራይ ህዝብ ትግል ሲሆን ለፍትሕ፣ ለነፃነትና ለእኩልነት የህይወት መስዋእነትነት የተከፈለበት ምዕራፍ ስለሆነ ለዘላለም ሊዘከር ይገባዋል።
ከ1983 ዓ.ም በኋላ ያለው ህወሓት ግን የህዝብ ሳይሆን በሕግ የተመዘገበ የፖለቲካ ድርጅት ነው። ስሙም መቀየር ይገባው ነበር። የህዝብ ታሪክና የፖለቲካ ድርጅት የስልጣን ጊዜ መቀላቀል የለባቸውም። የህዝብ ትግል ህወሓት እንደ ድርጅት ባጠፋው ልክ መመዘን የለበትም!
(ከአብርሃ ደስታ ፌስቡክ)

የጠ/ሚኒስትሩ የግንቦት 20 መልዕክት  
ግንቦት ሃያ የዘመናዊት ኢትዮጵያን ታሪክ ከቀየሩ ዕለታት መካከል አንዱ ነው:: ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ለማድረግ አያሌ ታጋዮች እጅግ ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ነፍስ ሠውተዋል፡፡ የግንቦት ሃያ ታጋዮች የነፍስ ዋጋ የከፈሉለት ዓላማ ግፍና ጭቆና፣ አድሎና ወገንተኝነት ቆሞ፤ እኩልነት ፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትና የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ነው፡፡
ግንቦት ሃያን ማክበር ያለብን እነዚህን ዓላማዎች እያሰብን መሆን አለበት፡፡ ቀኑን የምናስበው በግንቦት ሃያ ላይ ተቸክለን ሳይሆን ወደፊት እየሄድን የኋላውን እየገመገምን መሆን አለበት፡፡
ግንቦት ሃያን ያመጡ ታጋዮች ዓላማ ኢትዮጵያን ወደ ግንቦት ሃያ ሁለት መውሰድ እንጂ ወደ ግንቦት አሥራ ዘጠኝ መመለስ አልነበረም:: ሀገራቸው በሁሉም መመዘኛ ግንቦት ሃያን አልፋ፣ ግንቦት ሃያ አንድንም ተሻግራ፣ ወደ ግንቦት 22 መድረስ ነበር፡፡
የግንቦት ሃያ ታጋዮችን ዓላማ የምናሳካው በሁለመናዋ ከግንቦት 19 የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባት ከቻልን ብቻ ነው:: የብልጽግና ጎዳናችን ዓላማ ግንቦት ሃያ ላይ ቆሞ፣ ግንቦት አሥራ ዘጠኝን እያሰቡ መኩራራት ሳይሆን ሀገራችንን ወደ ግንቦት 22 ማስፈንጠር ነው፡፡
ይህ ማለትም ሀገራችን ከነበረችበት አስከፊ ሁኔታ ማላቀቅ ብቻ ሳይሆን መድረስ ወደነበረባት የላቀ ደረጃ ማድረስ ነው፡፡ የግንቦት ሃያ የድል መታሰቢያ በዓልን ስናከብር በተባበረ ክንድ ከግንቦት ሃያ የሚልቅ፣ ወደ ግንቦት 19 እንዳንመለስ የሚያደርግ ምጡቅ ሥርዓት ለመገንባት ቃላችንን የምናድስበትና ወደ ላቀ ውጤት ለመቀየር ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የምንገባበት መሆን ይገባዋል፡፡
ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ በአጥንትና ደማቸው ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ላቆዩ ሰማዕታት!
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

Read 9057 times