Sunday, 31 May 2020 00:00

የዐረብ ሊግ እና የእስላማዊ ትብብር ድርጅት አባል ብንሆንስ? ለምን ዓላማ?

Written by  ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(1 Vote)

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ውስብስብ ችግሮች እንዳሉበት በመስኩ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ በዚህ ሳምንት መጣጥፌ በዚሁ ጉዳይ ላይ የመወያያ ሃሳብ ለማቅረብ አሰብኩ፡፡ “ኢትዮጵያ የዐረብ ሊግ እና የእስላማዊ ትብብር ድርጅት አባል ለምን አትሆንም?” በሚለው ጥያቄ ዙሪያ ለመወያየት ስለ ሁለቱ ተቋማት አመሰራረት፣ አባላትና ዓላማ በቅድሚያ እናያለን፡፡ በመቀጠል የእነዚህ ተቋማት አባል ብንሆን ለኢትዮጵያ የሚያስገኘውን ጥቅም ለማመላከት እሞክራለሁ፡፡
የአረብ ሊግ አመሰራረት፣ ዓላማና አባላት
የዐረብ ሊግ አካባቢያዊ ድርጅት ነው፡፡ ይህ ድርጅት በዋናነት የምዕራብ አፍሪካ እና የምዕራብ ኢስያ ሀገራትን ያቀፈ ነው፡፡ ሊጉ እ.ኤ.አ ማርች 22 ቀን 1945 በካይሮ ከተማ መመስረቱ ይታወቃል፡፡ መስራቾቹ ስድስት ሀገሮች ሲሆኑ እነሱም፡- ግብጽ፣ ኢራቅ፣ ዮርዳኖስ፣ ሊባኖስ፣ ሣዑዲ ዓረቢያና ሶሪያ ሲሆኑ፤ የመንም በዚያው ዓመት በግንቦት ወር ሊጉን ተቀላቅላለች፡፡
የዐረብ ሊግ መሰረታዊ ዓላማ “በአባል አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ በማቀራረብና በመካከላቸው ያለውን ትብብር በማስተባበር፤ ነፃነታቸውን እና ሉዓላዊነታቸውን መጠበቅ እንዲሁም የአረብ አገሮችን ጉዳዮችና ፍላጎቶች ትኩረት እንዲያገኙ ማድረግ” ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የሊጉ ቀዳሚ ዓላማ የአረብ ሀገራትን ኢኮኖሚ በማሳደግ፣ አለመግባባቶችን በመፍታት እና የፖለቲካ አላማዎችን በማቀናጀት ላይ ያተኮረ ክፍለ አህጉራዊ ድርጅት መፍጠር ነበር፡፡ ሊጉ በተመሰረተ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከወሰዳቸው ቀዳሚ እርምጃዎች አንዱ እ.ኤ.አ በ1948 የእስራኤል መንግሥት ተመስርቶ ገና ብቅ ሲል ከስሩ መንቀል ነበር፡፡ ይህም እርምጃ በዚያ ወቅት እስራኤል እንደ ሀገር መመስረቷን በመቃወም በአረቡ ዓለም ለተቀሰቀሰው ሕዝባዊ አመፅ ምላሽ ለመስጠት የተወሰደ እርምጃ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህ እርምጃ አባል ሀገራቱ በመንሸራተታቸው ምክንያት ብዙ ርቀት አልሄደም፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ ማለትም  እ.ኤ.አ ሚያዚያ 13 ቀን 1950 በተደረገ ስምምነት መሰረት፤ ወታደራዊ እርምጃዎችን በጋራ ለማስተባበር “የጋራ መከላከያ ኃይል ማቋቋም” ተጨማሪ ዓላማ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ እ.ኤ.አ በ1965 ደግሞ አንድ የጋራ ገበያ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡
የአረብ ሊግ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት በዋነኛነት ያተኮረው በኢኮኖሚ፣ በባህል እና በማህበራዊ ፕሮግራሞች ላይ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት እ.ኤ.አ. በ1959 የመጀመሪያውን የአረብ ነዳጅ ኮንግረስ ያቋቋመ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ1964 የአረብ ሊግ የትምህርት፣ የባህል እና የሳይንስ ድርጅት (አሊስኮ) ተቋቋመ፡፡
በሦስተኛው ዋና ፀሐፊ (እ.ኤ.አ. 1972 - 1979) በመሐመድ ራድ አመራር የሊጉ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እየጨመረ ሄዷል፡፡ ሆኖም በፖለቲካ ጉዳዮች በተለይም እስራኤልንና ፍልስጤማውያንን በሚመለከት በተፈጠረ አለመግባባት ሂደቱ ተዳክሟል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1964 የፍልስጤም ነፃነት ድርጅት (PLO) የፍልስጤማውያን ተወካይ ሆኖ በታዛቢነት እንዲሳተፍ የተደረገ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ. በ1976 ወደ ሙሉ አባልነት ተሸጋግራል፡፡
እ.ኤ.አ. ማርች 26 ቀን 1979 ግብፅ ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት ከፈረመች በኋላ ሌሎች የአረብ ሊግ አባላት የግብፅን አባልነት ለማገድ እና የሊጉን ዋና መስሪያ ቤት ከካይሮ ወደ ቱኒስ ለመውሰድ ውሳኔ አሳለፉ:: ግብፅ እ.ኤ.አ. በ1989 የአረብ ሊግ አባል ሆና የተመለሰች ሲሆን የሊጉ ዋና መስሪያ ቤትም በ1990 ወደ ካይሮ ተመልሷል፡፡
የትምህርት፣ የባህልና የሳይንስ ድርጅት፣ የአረብ ኢኮኖሚያዊ አንድነት ምክር ቤት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ምክር ቤት በመሳሰሉ ተቋማቱ አማካይነት የአረብ ሊግ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህል፣ የሳይንስ እና ማህበራዊ ፕሮግራሞችን በመቀየስ የዓረቡን ዓለም ፍላጎቶች ለማሟላት ጥረት አድርጓል፡፡ የአረብ ሀገራት የፖሊሲ አቋማቸውን ለማስተባበር፣ በጋራ ጉዳዮች ላይ ለመምከር፣ አለመግባባቶችን እልባት ለመስጠትና ግጭቶችን ለመቆጣጠር ለአባል ሀገራት መድረክ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ማህበሩ ኢኮኖሚያዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ በርካታ ሰነዶችን ለማርቀቅ እና ከፍጻሜ ለማድረስ ጠቃሚ መድረክ ሆኖ አገልግሏል፡፡
እ.ኤ.አ ከማርች 2015 ጀምሮ አክራሪነትን እና ሌሎች በአረብ ሀገራት ላይ ያነጣጠሩ ስጋቶችን ለመቋቋም የሚያስችል የተቀናጀ የአረብ የመከላከያ ኃይል መቋቋሙ ይታወቃል፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ መሳተፍ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ሲሆን ሠራዊቱ ጣልቃ የሚገባው ከአባል አገራት በአንዱ ጥያቄ ሲቀርብ ብቻ ነው::
የተወሰኑ የአረብ ሊግ አባል አገራት እንደ ነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ ባሉ ሀብቶች የበለፀጉ ናቸው፡፡ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎትም እያደገ የመጣ ዘርፍ ነው፡፡ ከአስር ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ መወዳደር የቻሉ ኩባንያዎች ሊፈጠሩ ችለዋል፡፡ የአረብ ሊግ በደቡብ ሱዳን ደቡባዊ ክፍል የሚገኘውን ታላቅ ለም መሬትንም ያካትታል፡፡ ይህ መሬት የዓረቡ ዓለም የዳቦ ቅርጫት ተደርጎ ይወሳል፡፡ የደቡብ ሱዳን ነፃ መውጣት የአካባቢውን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ አልጎዳውም፡፡
አብዛኞቹ የዓረብ ሊግ አባል ሀገራት ዜጎች እስልምናን የሚከተሉ ሲሆን ክርስትና ሁለተኛው ትልቁ ሃይማኖት ነው፡፡ በግብፅ፣ በኢራቅ፣ በዮርዳኖስ፣ በሊባኖስ፣ በፍልስጤም፣ በሱዳን እና በሶሪያ በድምሩ 15 ሚሊዮን ክርስቲያኖች ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም፤ ቁጥራቸው አነስተኛ ግን ጉልህ የሆኑ የድሩዝ፣ ያዚዲ፣ ሻባክስ እና ማንዳውያን እምነት ተከታዮችም በሊጉ አባል ሀገራት ውስጥ አሉ።
የአረብ ሊግ ኦፊሴላዊ የሥራ ቋንቋ ዐረብኛ ነው፡፡ ሆኖም በርካታ የአረብ ሊግ አባል አገራት ሶማሊ፣ አፋር፣ ኮሞሮያን፣ ፈረንሣይኛ፣ እንግሊዘኛ፣ በርበር እና ኩርድ ያሉ ሌሎች ብሔራዊ ቋንቋዎች አሏቸው፡፡ በአብዛኞቹ አገራት ውስጥ ዓረብኛ ቀበሌኛዎች ይነገራሉ፡፡
“የአረብ ሊግ ስምምነት” ተብሎም የሚጠራው የአረብ ሊግ ቻርተር የአረብ ሊግ መመስረቻ ሰነድ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1945 ሊጉ ሲመሰረት በተደነገገው መሰረት የሊጉ አባላት በወቅቱ ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡ የአረብ ሀገሮችን የሚያጠቃልል መሆኑ በሰነዱ ላይ ተገልጿል:: ከላይ እንደተገለጸው ሊጉ ሲመሰረት ስድስት አባላት ብቻ ነበሩት፡፡ በአሁኑ ወቅት 22 አባላት አሉት፡፡ አምስት አገራት አስተያየትና ምክር የመስጠት መብት ኖሯቸው የታዛቢነት ደረጃ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ድምፅ የመስጠት መብት ግን የላቸውም፡፡
ሃያ ሁለቱ የዐረብ ሊግ አባላት፡- አልጀሪያ፣ ባህሬይን፣ ኮሞሮስ፣ ጂቡቲ፣ ግብፅ፣ ኢራቅ፣ ዮርዳኖስ፣ ኩዌት፣ ሊባኖስ፣ ሊቢያ፣ ሞሪታንያ፣ ሞሮኮ፣ ኦማን፣ ፍልስጤም፣ ኳታር፣ ሣዑዲ ዓረቢያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ሶሪያ፣ ቱኒዝያ፣ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬት እና የመን ናቸው:: በታዛቢነት ደግሞ አምስት ሀገሮች አሉ፡፡ እነሱም፡- አርሜኒያ፣ ብራዚል፣ ኤርትራ፣ ህንድ እና ቬንዙዌላ ናቸው፡፡
የአረብ ሊግ የአባልነት መስፈርት የመመስረቻ ሰነዱን መፈረም ብቻ ነው፡፡ የዐረብ ሊግ አባልነት ከእስልምና ሃይማኖት ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ አረብነትም መስፈርት አይደለም፡፡ እያንዳንዱ አባል ሀገር በሊጉ ጉባዔ እኩል አንድ ድምጽ አለው፡፡ የጉባዔው ውሳኔዎች ተፈጻሚ የሚሆኑት የድጋፍ ድምጽ በሰጡ ሀገሮች ላይ ብቻ ነው፡፡
የእስላማዊ ትብብር ድርጅት አመሰራረት፣ ዓላማና አባላት
የእስላማዊ ትብብር ድርጅት በእንግሊዝኛ “Organization of Islamic Cooperation - OIC” በመባል ይታወቃል፡፡ የእስላማዊ ትብብር ድርጅት እ.ኤ.አ. በ1969 የተቋቋመ ዓለም አቀፍ ድርጅት ሲሆን፣ በድምሩ 57 አባል ሀገራት ያሉት ነው፡፡ የዚህ ድርጅት አባል ሀገራት በድምሩ ከ1.9 ቢሊዮን በላይ ህዝብ አላቸው፡፡ ከ57ቱ ሀገራት በ53ቱ የእስልምና እምነት ተከታዮች በቁጥር ይበዛሉ፡፡ ድርጅቱ “የሙስሊሙ ዓለም የጋራ ድምፅ” እንደሆነና “ዓለም አቀፍ ሰላምና ፍቅርን” በማስፋፋት የሙስሊሙን ዓለም ጥቅም ለማስጠበቅ እና ለመጠበቅ እንደሚሰራ ይነገራል፡፡ የእስላማዊ ትብብር ድርጅት (OIC) በተባበሩት መንግስታት እና በአውሮፓ ህብረት ቋሚ ውክልና አለው፡፡ የድርጅቱ ኦፊሴላዊ ቋንቋዎች አረብኛ፣ እንግሊዝኛ እና ፈረንሣይኛ ናቸው፡፡
እ.ኤ.አ ነሐሴ 21 ቀን 1969 በኢየሩሳሌም በአል-አቅሷ መስጊድ እሳት ተቀጣጠለ፡፡ በወቅቱ የኢየሩሳሌም ሙፍቲ የነበሩት አሚር አል-ሁሴይኒ የተነሳውን ቃጠሎ “የአይሁድ ወንጀል” የሚል ስያሜ በመስጠት ሙስሊም የሃይማኖት መሪዎች ስብሰባ እንዲያካሂዱ ጥሪ አደረጉ፡፡ እሳቱ የ800 ዓመት እድሜ ያለውን የመስጂዱን የእንጨት ጣሪያና አጥር አወደመው፡፡ ይህንን ጥፋት የፈጸመው ዴኒስ ሚካኤል ሮሃን የተባለ አውስትራሊያዊ አክራሪ ክርስቲያን “የአእምሮ ህመምተኛ ነው” የሚል ማስተባበያ ተሰጠ፡፡
በዚህ ጥሪ መሰረት እ.ኤ.አ. መስከረም 25 ቀን 1969 ሃያ አራት የሙስሊም አገራት ተወካዮች የተገኙበት ጉባዔ በሞሮኮ ራባት ተካሄደ:: በዚህ ስብሰባም “ሙስሊም መንግስታት ህያው በሆነው የእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮ አማካይነት በኢኮኖሚያዊ፣ በሳይንስ፣ በባህላዊ እና በመንፈሳዊ መስኮች ትምህርትን ለማስፋፋት እና ትብብርና ድጋፍን ለማሳደግ መመካከር አለባቸው” የሚል ውሳኔ ተላለፈ:: ከስድስት ወር በኋላ ማለትም እ.ኤ.አ. በመጋቢት ወር 1970 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የመጀመሪያውን እስላማዊ ኮንፈረንስ በሳዑዲ አረቢያ፤ ጄዳ ከተማ አካሄዱ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1972 የእስላማዊ ትብብር ድርጅት ተቋቋመ፡፡
በአል-አቅሷ መስጊድ የተነሳው እሳት ለእስላማዊ ትብብር ድርጅት መመስረት ምክንያት ሲሆን፤ በርካታ ሙስሊሞች ይህ ድርጅት ሙስሊሞችን የሚያሰባስብና በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በማህበራዊ ጥቅሞቻቸው ዙሪያ እንዲመክሩ የሚረዳ ተቋም ሆኖ ያገለግላል የሚል እምነት አድሮባቸው ነበር፡፡ በተለይም በዚያ ወቅት የኦቶማን ኢምፓየርና የኸሊፋ አስተዳደር በመንኮታኮቱ የተፈጠረውን ክፍተት ይህ ድርጅት ይሞላዋል የሚል ተስፋ ተፈጥሮ ነበር፡፡  
በመመስረቻ ቻርተሩ መሰረት የእስላማዊ ትብብር ድርጅት ዓላማ የእስልምናን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እሴቶች ማስጠበቅ፤ በአባል አገራት መካከል ትብብርን ማስፋፋት፤ በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ፣ ሳይንሳዊ እና በፖለቲካዊ መስኮች ትብብርን ማሳደግ፤ ዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ የበኩሉን አስተዋፅዖ ማድረግ፤ እንዲሁም በሳይንስና ቴክኖሎጂ መስኮች ትምህርት እንዲስፋፋ ማገዝ ነው፡፡ ድርጅቱ በባህላዊ እና በማህበራዊ ፕሮጄክቶች የታወቀ ቢሆንም የፖለቲካ ተጽዕኖ ፈጣሪነቱ በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ ውስን ነው፡፡
እ.ኤ.አ. ማርች 2008 የእስላማዊ ትብብር ድርጅት ቻርተር ተሻሽሏል፡፡ በተሻሻለው ቻርተር ሰብአዊ መብቶችን፣ መሠረታዊ ነፃነቶችን እና መልካም አስተዳደርን በሁሉም አባል ሀገራት ተግባራዊ እንዲደረግ ተወስኗል፡፡ በተሻሻለው ሰነድ ውስጥ በደፈናው የተባበሩት መንግስታትን ቻርተር እና አለም አቀፍ ህግን እንደሚግፍ ገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅት የእስላማዊ ትብብር ድርጅት መሰረታዊ ዓላማዎች፡- “በአባል አገሮች መካከል የወንድማማችነትና የአንድነት ትስስር የበለጠ እንዲጠናከርና እንዲስፋፋ ማድረግ፣ የአባል ሀገራትን የጋራ ጥቅም ለማስጠበቅ እና ለመጠበቅ፤ አባል አገራት ለሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች በጋራ የሚያደርጉትን ጥረቶች መተባበርና ማቀናጀት፤በአባላት መካከል ፍትዊነትን፣ መከባበርንና መልካም ጉርብትናን ተግባራዊ በማድረግ ዓለም አቀፍ ሰላምን፣ ደህንነትን እና አንድነትን ማረጋገጥ፣ በተባበሩት መንግስታት ቻርተር እና በዓለም አቀፍ ሕግ በተደነገገው መሠረት፣ ለህዝቦች መብቶች መረጋገጥ ድጋፍ ማድረግ፣ ኢኮኖሚያዊና የንግድ ትብብርን ማጎልበት፣ የጋራ ገበያ ለመመስረት የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ ውህደትን ማሳደግ፣ ዘላቂና ሁሉን አቀፍ የሰብአዊ ልማት እና ኢኮኖሚያዊ ደህንነት ለማሳካት ጥረት ማድረግ፣ በመግባባትና በመቻቻል ላይ በመመስረት እስላማዊ ትምህርቶችን እና እሴቶችን ማስተዋወቅ እና መጠበቅ፣ የእስልምናን ትክክለኛ ገጽታ መጠበቅ፣ የእስልምናን ስም ማጉደፍ መከላከል፣ በስልጣኔዎችና በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይትን ማበረታታት፤ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ማስፋፋት፣ በአባል አገሮች መካከል ምርምርን እና ትብብርን ማበረታታት እና ማጎልበት፣ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የወጣቶች፣ አዛውንቶች እና ልዩ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች እንዲሁም የቤተሰብ እሴቶችን ማስጠበቅ፣ ሰብአዊ መብቶችንና ነፃነቶችን መጠበቅ፣ ማስፋፋት፣ ቤተሰብ ተፈጥሮአዊና መሰረታዊ የሕብረተሰብ አካል በመሆኑ አፅንዖት መስጠት፣ መጠበቅና ማሳደግ፣ ሽብርተኝነትን፣ የተቀናጀ ወንጀልን፣ በሕገ ወጥ ዕፅ አዘዋዋሪነትን፣ ሙስናን፣ የገንዘብ እጥበትን እና በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን መዋጋት፣…” የሚሉትን ዋና ዋና ጉዳዮች ያካተተ ነው፡፡
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ዓላማዎች ሙስሊም ሀገራትን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ለማካተት የሚያስችሉ መሆናቸውን ማስተዋል ይቻላል፡፡ እነዚህ ዓላማዎች ከግብ ለማድረስ አባል ሀገራቱ ሊከተሏቸው የሚገቡ መርሆዎችም በድርጅቱ ሰነድ ላይ ሰፍሯል፡፡ መርሆዎቹም፡- “ሁሉም አባል ሀገሮች ለተባበሩት መንግስታት ቻርተር ዓላማዎች እና መርሆዎች ተገዢ ይሆናሉ፣ አባል ሀገሮች ሉዓላዊና ነፃ ናቸው፤ እኩል መብቶች እና ግዴታዎች አላቸው፣ ሁሉም አባል ሀገሮች ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ይፈታሉ፣ ኃይልን ከመጠቀም ወይም ከማስፈራራት ይቆጠባሉ፣ ሁሉም አባል ሀገሮች ሀገራዊ ሉዓላዊነትን፣ ነፃነትና ዳር ድንበር ያከብራሉ፤ በውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ አይገቡም፣ አባል አገራት ለዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት የድርጅቱን ቻርተር፣ የተባበሩት መንግስታትን ቻርተር፣ ዓለም አቀፍ ህግን እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግን ያከብራሉ፣ አባል ሀገራት በሀገራቸውና እና በዓለም አቀፍ ደረጃ መልካም አስተዳደርን፣ ዲሞክራሲን፣ ሰብአዊ መብቶችና ነፃነትን፣ የሕግ የበላይነትን ያሰፍናሉ፣ ይደግፋሉ ያበረታታሉ፤ አባል ሀገሮች አካባቢን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ጥረት ያደርጋሉ” የሚሉ ናቸው፡፡
የእስላማዊ ትብብር ድርጅት አባልነት ከእስልምና ሃይማኖት ጋር ግንኙነት የለውም:: የእስላማዊ ትብብር ድርጅት የአባልነት መስፈርትም በቻርተሩ ላይ ሰፍሮ ይገኛል:: በዚህም መሰረት፤ “የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል የሆነ፣ ይህንን ቻርተር የተቀበለ፣ በሀገሩ በርከት ያሉ ሙስሊም ዜጎች ያሉት፣ የአባልነት ማመልከቻ ያቀረበ፣ ማንኛውም ሀገር የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት ባወጡት መስፈርት መሰረት ሁሉም የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከተስማሙ ድርጅቱን ሊቀላቀል ይችላል” ይላል፡፡ ድርጅቱ ቋሚ አባላት ብቻ ሳይሆኑ ሀገራትን በታዛቢነትም ይቀበላል፡፡ የታዛቢነት ደረጃ የሚወሰነው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት ስምምነት ነው፡፡ ለዚህም መመዘኛ መስፈርት አለው፡፡
የእስላማዊ ትብብር ድርጅት 57 አባላት ያሉት ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 56 ቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባላት ሲሆኑ፤ 57ኛዋ ፍልስጤም የተ.መ.ድ አባል አይደለቺም፡፡ ከአባላቱ ውስጥ 47ቱ ሀገራት ብዙ ሙስሊሞች የሚገኙባቸው ሀገሮች ናቸው፡፡ የእስላማዊ ትብብር ድርጅት አባል ሀገራት አጠቃላይ የህዝብ ቁጥር ከ1.9 ቢሊዮን በላይ ነው፡፡
አባል ሀገራቱ ከአፍሪካ፡- አልጀሪያ፣ ቤኒን፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ካሜሩን፣ ቻድ፣ ኮሞሮስ፣ ጂቡቲ፣ ግብጽ፣ ጋቦን፣ ጋምቢያ፣ ጊኒ፣ ጊኒ ቢሳው፣ አይቮሪ ኮስት፣ ሊቢያ፣ ማሊ፣ ሞሪኒያ፣ ሞሮኮ፣ ሞዛምቢክ፣ ኒጀር፣ ናጀሪያ፣ ሴኔጋል፣ ሴራሊዮን፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ቶጎ፣ ቱንዚያ እና ኡጋንዳ አባል ናቸው፡፡ ከኢስያ ደግሞ፡- አፍጋኒስታን፣ አዘርባጃን፣ ባህሬይን፣ ባንግላዴሽ፣ ብሩኒ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ኢራን፣ ኢራቅ፣ ዮርዳኖስ፣ ካዛኪስታን፣ ኩዌት፣ ኪርጊስታን፣ ሊባኖስ፣ ማሌዥያ፣ ማልዲቭስ፣ ኦማን፣ ፓኪስታን፣ ፍልስጤም፣ ኳታር፣ ሣዑዲ ዓረቢያ፣ ሶሪያ፣ ታጂኪስታን፣ ቱርክ፣ ቱርክሜንስታን፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬት፣ ኡዝቤኪስታን እና የመን ናቸው፡፡ ከአውሮፓ አልባንያ እንዲሁም ከደቡብ አሜሪካ ጉያና እና ሱሪኔም ይገኙበታል::
ብዙ ሙስሊም ካላቸው የዓለም ሀገራት አባል ያልሆኑት ህንድ፣ ኢትዮጵያ፣ ሩሲያ እና ታይላንድ ናቸው፡፡ ሩሲያ እና ታይላንድ ሙሉ አባላት ባይሆኑም የታዛቢነት ደረጃ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ህንድ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙት ሙስሊሞች መካከል 11 በመቶ የሚሆኑት ህንድ ውስጥ እንደሚኖሩ በመግለጽ የአባልነት ጥያቄ ብታቀርብም ፓኪስታን በካሽሚር ምክንያት የሕንድን ጥያቄ በመቃወሟ እስከ አሁን አባል መሆን አልቻለቺም፡፡ የኢትዮጵያ አባል አለመሆን ግን ምክንያቱ በግልጽ አይታወቅም፡፡
የአረብ ሊግንም ይሁን የእስላማዊ ትብብር ድርጅት አመሰራረት፣ ዓላማ፣ መርሆዎች፣ አባላት፣ የአባልነት መስፈርት በአጭሩ ለማየት ሞክረናል፡፡ የአባል ሀገሮቹን ስብጥር ስንመለከት የአባልነት መስፈርቱ ከእስልምና ሃይማኖት ጋር ግንኙነት የሌለው መሆኑንም ማስተዋል ይቻላል፡፡ የፖለቲካ ሣይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተማሪ እንደመሆኔ፤ በጉዳዩ ላይ የመወያያ ሀሳቦችን ማቅረብ አስፈለጊ ነው ብየ አምናለሁ፡፡ በዚህ ረገድ በመጀመሪያ ደረጃ ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ “ሀገራችን ኢትዮጵያ የእነዚህ ተቋማት አባል ለምን አልሆነቺም?” የሚል ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ መላምቶችን ከመደርደር በዘለለ ቁርጥ ያለ መልስ ሊኖረው የሚችለው የኢትዮጵያ መንግስት በተለይም የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ አንድ ሀገር ቀርቶ አንድ ግለሰብ የአንድ እድር አባል ከመሆኑ በፊት በዚያ አድር ውስጥ እነማን አሉ? እድሩ ምን ምን ግዴታዎችና ጥቅሞች አሉት? የእድሩ አባል በመሆኔ ምን አገኛለሁ፣ ምንስ አጣለሁ?... የሚሉትንና መሰል ጥያቄዎችን በማንሳት ከራሱና ከቤተሰቡ ጋር መምከሩ የሚጠበቅ ነው:: የኢትዮጵያ መንግስትም አባል የሚሆንበትን አካባቢያዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቋም ከመወሰኑ በፊት በርካታ ምዝናዎችን ማካሄዱ ተገቢም አስፈላጊም ነው፡፡ እኔ ባለኝ መረጃ፤ ኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ የገለልተኛነትን መንገድ የመከተል ፖሊሲ ታራምዳለች፡፡ ይህ ፖሊሲ ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የዘለቀ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ስልሳ እና ሰባ ዓመታት የቆየ ፖሊሲ ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር እንደገና መገምገም አስፈላጊ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ከኢስያ በተለይም ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት አካል ናት፡፡ የዘር ግንዳችንም፣ ሃይማኖታችንም፣ ባህላችንም፣ ቋንቋችንም፣ ንግዳችንም ከእነዚህ ሀገራት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ከእድገታችንም አኳያ  የዛሬ ስልሳ እና ሰባ ዓመታት በነበርንበት ደረጃና ሁኔታ ላይ አይደለንም፡፡ ስልሳ እና ሰባ ዓመታት ስለ ዓባይም ሆነ ስለ ግድብ አጀንዳ አልነበረንም፡፡ ዛሬ እነዚህ አጀንዳዎች ጠረጴዛችን ላይ የተቀመጡ ናቸው፡፡ ውይይትም ድርድርም ይፈልጋሉ፡፡ ትብብርም ይሻሉ፡፡
ከውሃ ጋር በተያያዘ ዋነኛዋ የኢትዮጵያ ተቀናቃኝ የሆነቺው ግብጽ፤ የአረብ ሊግም፣ የእስልምና ትብብር ድርጅትም አባል በመሆኗ የወዳጆቻችንን እጅ ጭምር ለመጠምዘዝ ችላለች፡፡ ዛሬ ከእኛ ጋር መሆናቸውን የነገሩን ወዳጆቻችን ከእኛ ሲለዩ ከግብጽ ጎን ተሰልፈው የምናገኛቸው በነዚያ ተቋማት ተጽእኖ ምክንያት መሆኑን ልብ ልንለው ይገባል፡፡ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ሀገራችን ከአረብ ሊግ ጋርም ይሁን ከእስላማዊ ትብብር ድርጅት ጋር ሊኖራት የሚገባውን ግንኙነት መመርመር የሚገባት ጊዜ ላይ ደርሳለች የሚል እምነት አለኝ፡፡
ከዚሁ ጋር የሚነሳው ጥያቄ “ሀገራችን የአረብ ሊግ እና የእስላማዊ ትብብር ድርጅት አባል በመሆኗ ምን ጥቅም ምንስ ጉዳት አለው?” የሚል ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠው መልስ በጥናት ላይ ሊመሰረት ይገባዋል፡፡ ስለሆነም የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፤ ነገ ዛሬ ሳይል ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር መታወቅ አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን ብዝሃ ሃይማኖት ያለባት አገር ናት፡፡ የአረብ ሊግ ወይም የእስላማዊ ትብብር ድርጅት አባል ሆነች ማለት የእስላም ሀገር ናት ማለት አይደለም፡፡ አሊያም አረብ ሆነች ማለት አይደለም፡፡ ግብጽ የኢጋድ አባል ለመሆን የማታደርገው ጥረት የለም:: ግብጽ ይህንን የምታደርገው በአፍሪካ ቀንድ ስለምትገኝ ሳይሆን የአፍሪካ ቀንድ (ኢጋድ) ሀገራት በዓባይ ዙሪያ የሚያደርጉትን ውይይት በቅርበት ለመከታተል ነው፡፡ እኛም ለሀገራችንና ለህዝባችን ጥቅም (በተለይም ለዓባይ) ስንል አባል መሆን ወይም መገኘት በሚገባን መድረክ ሁሉ መገኘት አስፈላጊ ነው፡፡ ኤርትራ የአረብ ሊግ አባል የሆነቺው አረብ ስለሆነች ወይም እስላም ሀገር ስለሆች አይደለም፡፡ ከነዚያ ሀገራት ጋር የሚያገናኝ ጥቅም ስላላት ነው:: እነ ብራዚልና ቬንዙዌላ የእስላማዊ ትብብር ድርጅት አባል የሆኑት የእስላም ሀገር ስለሆኑ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል አረብ ሁሉ እስላም አለመሆኑም መታወቅ አለበት፡፡
 ጸሐፊውን Email: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 4146 times