Sunday, 31 May 2020 00:00

እኛ ዳዊትን እንጂ ኢየሱስን አንፈልግም!!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

 ዐይሁድ እንደ ኢትዮጵያውያን አትንኩኝ ባይ፣ ባህላቸውንና እምነታቸውን የማያስደፍሩ ዐይነት ይመስሉኛል፡፡ ስለዚህም ዐለምን አሸንፎ በገዛው የሮማ መንግስት እንኳበቅኝ ለመገዛት አሻፈረኝ እያሉ ሕይወታቸውን እስከመስጠት ደርሰው ነበር፡፡ ለምሳሌ ባህላቸውን፣ እምነታቸውንና ትውፊታቸውን ለመጠበቅ ከማንም ዜጋ ይልቅ በእምቢታቸው መላውን ዐለም ሮማ ቀጥ አድርገው የገዙትን ሮማውያን አወዛግበዋል፡፡ በተቻላቸው መጠን ክብራቸውን ለመጠበቅ ተጋድለዋል:: በባቢሎን ምርኮ ዘመን የተማረኩት ግዞት ሄደው ኙሯቸውን ሲኖሩ፣ በምድራቸው የቀሩት ደግሞ የባቢሎን መንግስት ያስቀመጠላቸውንና ባንዳ ያሉትን ጎዶልያስን በሞት አሰናብተዋል፡፡ ሲጀመርም ኀይኞች ናቸው፤ አባታችን የሚሉት አብረሃም ሳይቀር ጥቃት አይወድድም፡፡ ስለዚህም ሎጥ ችግር ውስጥ በገባና በተዘረፈ ጊዜ በቁጣ ወጥቶ ነገስታትን መትቶ ተመልሷል፡፡
እንዲያውም ጸሐፍት እንደሚሉት ሮማውያን አይሁዳንን ጸጥ አድርጎ ለመግዛት ሰላሳ አንድ ዐመታት ወስዶባቸዋል፣ ይላሉ፡፡ከዚያ በኋላም አሻንጉሊታቸውን ሄሮድስን የአይሁድ ንጉስ ብለው ሾመው እንኳ በየገበያውና በየአደባባዩ ሳይቀር አይሁድን እያደኑ ሲገድሉ፣ ንጉስ ተብዬው ሕዝቡን ፈጅተው፣ የምድረበዳ ገዢ ሊያደርጉኝ ያስባሉ! ማለታቸውን አንድ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ በጻፉት መጽሐፍ አስፍረዋል::
አይሁድ በዚህ አልገዛም ባይነታቸው ምክንያት የደረሰባቸው ጣጣ ተቆጥሮ የሚያልቅ አይደለም፤ እምቢታቸው በቤተ መቅደሳቸው የሚጸየፉት የዐሳማ መስዋዕት ተደርጎ፣ ደሙ በቤተ መቅደሱ ግድግዳ እስኪቀባ ድረስ የመረረ ዋጋ ከፍለዋል፡፡
ይሁንና እምቢ ባይነታቸው ጀግና አፍቃሪና አትንኩን ባይ አክባሪነትንና አድናቂነትን አጎናጽፏቸዋል፡፡ ስለዚህም ንጉስ ዳዊትን የመሰለ ጦረኛ ንጉስ በዘፈን አጅበዋል፡፡
አንዴ ምድረ እስራኤልን በዛቻ የናጠውን ጎልያድን፣ ትንሹ እረኛ ዳዊት በወንጭፍ ጠጠር በአደባባይ ሲዘርረው ‹‹ዳዊት እልፍ ገደለ›› በማለት ከንጉስ ሳዖል የበለጠ ቁጥር በመስጠታቸው  ሳኦልን አስቆጥተዋል፡፡
ሕዝበ እስራኤል በሁለት ነገር ያከብራል፤ አንድ እንደ ሙሴ እግዚአብሄር አብሮት አለ ብሎ የሚያምነውን ሰው፤ ሁለት እንደ ኢያሱ ሰላሳ አንድ ነገስታትን በጦርነት ልክ የሚያስገባ ጀግና ሲያገኝ፡፡
ይሁን እንጂ እግዚአብሄርንም የሚያውቁት በጦረኝነቱ ስለሆነ የተለሳለሰ ነገር አይወድዱም:: ምክንያቱም ሕይወታቸውና ኑሯቸው ከጦርነት ጋር የተዛመደ በመሆኑ፡፡
የተባሉት ተዋግታችሁ ውረሱ እንጂ በነጻ ውሰዱ አይደለም፡፡
እናም ይህ ባህላቸውና ስነልቡናቸው  ምስኪን ሰው ሆኖ የመጣውንና ሁሉን ነገር በፍቅርና ትህትና ልፍታ የሚለውን ኢየሱስን እንዳይቀበሉ አድርጓቸዋል፡፡ በወንጭፍ ግንባር መትቶ የሚጥልለት ጀግና በበቀለበት ሀገር መስቀል ላይ እሞታለሁ›› ብሎ በጠላቶቹ ፊት እጁን የሚሰጥ መሲህ መቀበል ፈጽሞ ይከብዳቸዋል:: ስለዚህም ሊቤዣቸው የመጣውን መሲህ አሳደዱት፤  የሚያድናቸውን ጠሉት፡፡ ሃሳቡና ሃሳባቸው መንገዱና መንገዳቸው የተለያየ ሆነ፡፡ ከሮም ግዞት በፈጣን እርምጃ ነጻ የሚያወጣቸውን ሲፈልጉ ጭራሽ ‹‹የበደሏችሁን ይቅር በሉ›› ሲል ቀለዱበት፡፡
ከርሱ ይልቅ በአባቶቻቸው ዘመን የበደሏቸውን መሪዎች እያስታወሱ ቢቆዝሙ ይቀላቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የጀግንነትና የአትንኩኝ ባይ ባህላቸው ነው:: እያቅራራ የሚገድል እንጂ ምህረት እየለመነ የሚሞት ሰው ዕጣ ክፍላቸው አይደለም፡፡ያድነናል ያሉት መሲህ ራሱ ሞቶ አፈር ሲገባ ከማየት ደጋግሞ መሞት ይሻላል፡፡
ይህ ለእነርሱ ልፍስፍስነት ነው፤ ልፍስፍስ ደግሞ አይወዱም፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያንም የዚህ ዐይነቱ ነገር ይቸግረናል፡፡ ንጉሶቻችንን እያሰብን በኩራት የሚሞላውና በሽለላ የምንወጠረው፣ ጀግንነታቸው እያኮራን ነው፡፡ ቴዎድሮስን የምንወድደው፣ በርካታ ዘፈኖች የተዘፈኑለት፣ ቴአትሮች የተጻፉለት፣ መጠጥ ፉት ባልን ቁጥር መይሳው ካሳ ብለን ያዙን ልቀቁን ብለን የምንጋበዘው ለጠላቶቼ እጄን አልሰጥም ብሎ ራሱን በጥይት እሳት አቃጥሎ ስለሞተ ነው፡፡
ያ ባይሆን ግን እናፍርበታለን፡፡ እንኳን ስሙን ልናነሳ ሲያነሱብን እንከላከላለን፡፡ምክንያቱም ጀግና እንወድዳለንና!
ዐጼ ዮሃንስ መተማ ላይ ቢሞቱም በተደጋጋሚ ግብጽንና ሌሎች ጠላቶቻችንን ስለመቱልን በክብር እናነሳቸዋለን:: ኮሎኔል መንግስቱ ሳይቀሩ አንድ ኢትዮጵዊ በሃምሳ ባዕድ እቀይራለሁ ብለዋል እያልን እስከመኩራራት የደረስነው ከትሁት ይልቅ የሚታበይ ጀግና ስለምንወድድ ነው፡፡
ባልቻ አባነፍሶ፣ ገበየሁ አባጎራ፣ አሉላ አባነጋ ወዘተ እያልን ጀነራሎቻችን በየአደባባዩ የምንጠራው ወድደን አይደለም፤ ጀግንነት ባህላችን ሆኖ ጀግና ስለምንወድድ ነው፡፡
ምናልባት ኢየሱስ መሲህ ሆኖ እኛ ሀገር ቢመጣ የሚደርሰው ዕጣ ከአይሁድ የከፋ ሊሆን ይችል  ነበር፡፡ ለስላሳ ነገር አንወድም፤ አልጫ! ከመብላት በበርበሬና በሚጥሚጣ መቃጠል ይሻለናል፤ ስለዚህም በርበሬ የሌለው ሁሉ ለኛ አልጫ ነው፡፡ አልጫ ማለት ደግሞ ሃሞት የሌለው ነው፡፡
እኛ ይቅር በለው፤ ተወው፣ ከማለት ይልቅ ‹‹አቅምሰው! ድፋው! ዋጋውን ስጠው!›› ማለት እንወዳለን፡፡
ስለዚህም አሁን ካለው መንግስት አስተዳደር ጋር በሰላም መቀጠል ፈተና ሆኖብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቶች አሉን፡፡ ከመገደል፣ ከመታሰር፣ ከመገደል ያወጡናል ብለን አስበናቸው፣ ስንሞት ዝም፣ ስንታሰር ዝም፣ እያሉ ያንዳንዶቻችንን ቅስም ሰብረውታል:: በምን ምክንያት እንደሆነም እኛ መጠየቅ አንሻም፡፡ መንግስት የምናውቀው አናፍጦ ስርዐት የሚያስከብር እንጂ ለምኖ ማግባባት የሚቃጣው ቄስ ነገር አይደለም፡፡ ፖሊሱም ቢሆን ሰው ሲጋደል፣ ጠመንጃውን ብድግ አድርጎ፣ ዐይኑን አጉረጥርጦ ወንጀለኛውን ልክ የሚያስገባ እንጂ አብሮን ወንጀለኛውን የሚለማመን አልነበረም፡፡ አሁን ግን ፖሊሱ ወንጀል ሰራ የተባለውን አስሮ ዝም፡፡ ሕግ አስከባሪውም ዝም ሆኗል፡፡ ይሄ ለኛ የማይዋጥ ፈተና ነው:: ሰበቡም በቀላሉ አልገባንም፤ብቻ ዝም ብለን መላ እንመታለን፡፡ መንግስት ጠላት ስለበዛበት ነው፡፡ ወያኔና ተላላኪዎቹ ቀዳዳ እንዳያገኙ ነው፡፡ ሀገሪቱ በጥንቃቄ ካልተያዘች ትበተናለች፣ ወዘተ እያልን እንታገሳለን፡፡ ጥቃትን በጭፍኑ አንቀበልም ያሉት ደግሞ አሁንም የመንግስት ለውጥ ይሻሉ፡፡ ግርግሩ መሃል ሌቦችም አሻሮ ይዘው ወደነውጡና ለውጡ መዝሙር ይጠጋሉ፡፡
ለውጡ መነሻው ላይ ብዙ ጥፋት እንዳስቀረ የሚያስብ የጠፋ ይመስላል፡፡ኦቦ ለማ መገርሳና ዶክተር ዐቢይ ባይመጡ የትግራይ ተወላጆች ላይ በስሜት ይፈጸም የነበረውን ጥፋት አላሰብነውም፡፡ በወያኔና በህወሃት ካድሬዎች የተበሳጨ ሁሉ ለክፋት ቀን እየጠበቀ እንደነበር አንረሳውም፡፡
በየወረዳው ጥርስ የተናከሰው የመንደር ፖለቲከኛ ስጋው ከመዘልዘል የዳነው ለውጡ ሰላማዊና ጥንቃቄ የተሞላ በመሆኑ ነበር፡፡
ይሁንና ብዙዎቻችን ሳናደንቀው ለውጡ ወደ ሌላ ነውጥ ገብቷል፡፡ ይህንን ያለማመስገን ነገርና ባህል ሳስታውስ የሚዋኝ ውሻ የነበረው ሰው ታሪክ ትዝ ይለኛል፡፡
ይህ ሰው ውሻው ውሃ ላይ እንደ የብስ መሮጥና ዳክዬ ማደን ይችል ነበር፡፡ እናም አንድ ቀን ይህን አስደናቂ ውሻ ለጓደኞቹ ለማሳየት ወደ ሃይቅ ይዟቸው ሄደ፡፡ ከዚያም አስደናቂው ውሻ ተዐምር አሳያቸው:: ዳክየ አሳድዶ እያደነ አመጣ:: ይሁን እንጂ የቱም ሰው አስተያት አልሰጠም፡፡ይህ ሁኔታ ያስቆጨው የውሻው ባለቤት በሌላ ቀን ከጓደኞቹ አንዱን ስለውሻው አዳኝነትና የውሃ ላይ ጉዞ ጠየቀው፡፡ ይሄኔ ለባለውሻው የሰጠው አስተያየት ‹‹ውሻህ ዋና አይችልም!›› የሚል ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ የኛም ነገር እንዲህ ነው፡፡ መልካሙን ነገር ሳይሆን ጥፋቱ ላይ እናተኩራለን፡፡ ግን ሁልጊዜ ከበጎ ጎኑ መጀመር መልካም ነው:: ፍቅርና ይቅርታን መለማመድም ፍሬያማ የሚያደርገን ይመስለኛል፡፡  
ከላይ እንዳልኩት ጀግንነት ማድነቃችን ጥሩ ነው፡፡ ጠመንጃን ብቻ መፍትሄ አምጪ ማድረጋችን መሻሻል ያለበት ይመስለኛል:: ጠመንጃን እንደ ጥሩ ምርጫ መውሰድ ትክክል አይደለም፡፡ ሰሞኑን እንኳ አንድ አክቲቪስት ነገር ስለጦርነት የጻፈው ነገር አሳፍሮናል፡፡ አንድን ሕዝብ ጦርነት ባህላዊ ጨዋታው ነው›› ብሎ እንደጥሩ ነገር ማውራት አሸማቃቂ ነው:: ሁሉም ነገር ተቀባይነት የሚያገኝበት ዘመን አለው፤ አውድ አለው፡፡ ይሁን እንጂ የምግብና መጠጥ ውሃ ችግር ያጎሳቆለውን የሀገራችንን ሕዝብ ወደዚህ ሀሳብ መጎተት ከስንፍና ውጭ ምን ሊባል ይችላል!!
የአባቶቻችን ጀግንነት አልጠቀመንም አንልም፤ የማንም መጫወቻና ባሪያ አልሆንም:: እንኳን በሕይወት ያሉት የሞቱትን ወገኖቻችንን አስከሬን በጠላት እጅ ላለመጣል የከፈሉትን መስዋዕትነት በኮሪያው ዘመቻ የነበሩ የውጭ ሀገር ሰዎች ሳይቀሩ የሰጡትን እማኝነት ከመጻሕፍት ገጾች መፈተሸ ይቻላል:: ዐጼ ዮሃንስ መተማ ላይ በጥይት ከተመቱ በኋላ አስከሬናቸውን ላለማስነካት ብዙ ጀግኖች እንደወደቁም እናውቃለን፡፡ ጥቃት ያለመውደዳችን አንዱ ማሳያ ይህ ነው፡፡ ይህንን የክብር ስራ ለፈጸሙ አባቶች ምስጋናዬ ታላቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ያለ ዐውዱና ዘመኑ እንደ ትናንት እንኑር ካልን ጣጣው ብዙ ነው:: አሁን የመነጋገር፣ የመደማመጥና ከድህነት የመውጫ ጊዜ ነው፡፡ ነገሮችን ከጠመንጃ ይልቅ በውይይት የመፍታት ዘመን ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን መብታችን ሲነካና ቀኛችን ሲመታ ግራችንን ጨምረን እንስጥ ማለት አይደለም፡፡
ይሁንና እንደ ዕብራውያኑ ዛሬም የሚሞግተን ነገር አለ፡፡ ያም የሚሰቀልልንን ሳይሆን የሚሰቅልልና በወንጭፍ ጠጠር ከትቶ የጎልያድን ግንባር የሚያፈርስ ጀግና እንፈልጋለን:: እንደ ሳዖል ደረቱ ሰፋ ያለ፣ ጠላቶቹ በቁጣው መብረቅ የሚደነግጡለት ግዙፍ ሰው ያጓጓናል፡፡
እንደ ኢየሱስ ለስላሳና ጥይት የማያጮህ ያበሳጨናል፤ ወዲያው የሚበቀልልን እንፈልጋለን፡፡ ኢየሱስ በአይሁድ አይን ሲታይ የተናቀው ጎራዴ ስላልመዘዘ፣ ወዲያው ከሮማ ገዢዎች ስላልታደጋቸው ነበር፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ ለእስራኤል መንግስት ትመልሳለህ?›› የሚለው ጥያቄ የዚያ ማሳያ ነው፡፡ እርሱ ግን ‹‹ሕዝቡን እታደጋለሁ ››ብሎ ብዙ ካወራ በኋላ የፊጢኝ ታስሮ ወደ መግረፊያ ስፍራና ወደ ስቅላት ሲሄድ አሽሟጠጡበት፡፡ ይሁን እንጂ የራሱ የተለየ ምርጫ ና መንገድ ነበረው፡፡ በሞት መንገድ ማሸነፍ እንደሚቻል አምኗል፡፡መቃብር ውስጥ አልፎ ሕይወት እንደሚገኝ አስልቷል፡፡ ስለዚህም ዐለማችንን የቀየረውን ታሪክ ጽፏል፡፡
እኛም ያው ነን፡፡ ልባችን የሚኮራው ጦር መዝዞ ጠላታችንን አፈር በሚያስግጥ መሪ እንጂ እጆቹን ለፍቅር ዘርግቶ ‹‹ምህረት ያዋጣናል›› በሚል መሪ አይደለም፡፡ሚጥሚጣ የሚወድድ፣ በርበሬ ከሌለው አልጫ የሚያቅለሸልሸው፣ ያገሬ ሰው ኮስታራ ካልሆነ መሪ አይመስለውም:: ይህ ስነልቡና እስኪቀየር ድረስ ለስላሳ ነገር አልለመድንም፡፡ ቢራ ጠጥቶ በካቲከላ ኮስተር ማለት የምንፈልገውን እኛን በትዕግስት ይዞ መጓዝ ዋጋ ያስከፍላል፡፡የሚገርመው ደግሞ የኛ ነገር ጣጣው ብዙ መሆኑ ነው፡፡ ችግሮቻችን በየሰፈራችን የተፈተሉ ናቸው፤ ሁላችንም የምንማረርበት ነገር አለን፡፡ ሁላችንም በብሶት እንባችን ዐይናችን ላይ ተንጠልጥሏል፡፡ ችግሮቻችን የሚፈቱት ራሳችንን ስናደምጥ ግን አይደለም፡፡ ስንደማመጥ ነው፡፡
ወንጀለኛው እንኳ ምህረትን ገፍቶ ጦር በሚሰብቅበት ሀገር፣ ነገሮችን በሰላም መግፋት ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ለተቀመጭ ሰማይ ቅርቡ ሆኖ ‹‹ለምን እንዲህ አይደረግም?›› እያልን የምንነጫነጭባቸው ነገሮች ሀገር እስከማፍረስ ሊደርሱ እንደሚችሉና ነገሩን በየደረጃው መፍታት የተሸለ መሆኑን እንዴት ባለ መንፈስ ማስረዳት ይቻል ይሆን? እኛ ቁጡ ነን፤ጥቃት አንወድድም፡፡
የሀገሬ ሰው እንደዚህ ነው፡፡ ታንክ በጎራዴና በጦር የመለሱ አባቶቹን ገድል እየሰማ አድጎ ፍቅር ብቻ ስትለው ‹‹ይለይልን!›› ይልና ግጥም ያወጣል፡፡ ዘራፍ ብሎ ለሞት ይታጠቃል፡፡ ከጥቃት ይልቅ ሞት ክብሩ ነው፡፡ ይሄኔ እንደ እስራኤል ስለኛ የሚዋጋ መሪ ይኑረን!! ይላል:: እንደ ጓድ መንግስቱ ‹‹አብዮታዊት ኢትዮጵያ ወይም ሞት›› ሲባል ባንዲራው ላይ የዐይኖቹን የእንባ ጤዛ ያነብባል፡፡
አሁን ፈተናችን ይህ ነው አዲሱ መሪያችን ‹‹ፍቅር ያሸንፋል!›› በፈገግታ መታየታቸው ከሃሞተቢስነት ይቆጠራል፡፡ ያበሳጫልም:: ስለዚህ ይህቺን ሀገር ሰይፍ ሳትይዝ አትመራም፤ መስቀል ላይ ተንጠልጥለህ “አድንሃለሁ!” ብትል መጀመሪያ ከመስቀል ውረድ ይልሃል፡፡
በፈገግታ ሳይሆን በቁጣ ቴሌቪዥን ላይ መሪውን ሲያይ ኩራቱ አናቱ ላይ ይወጣል፡፡
ያሁኑ ችግራችን ይህንን ዐይነት ሰው ማጣት ነው፡፡ ከድህነት እንውጣ›› ቢባል ብዙም የሚሰማ ጆሮ ያለን አይመስለኝም:: ደህነት ከክብር አይበልጥም!! ሰሞኑን ዶክተር ዐቢይ እንደ ኮሎኔል መንግስቱ ቢሆን ግብጽን አናቷን ብሎ ልክ ስገባት ነበር፡፡ ወያኔን መቀለ ድረስ ሄዶ ወያኔን ድራሹን ቢያጠፋው ብሎ ይመኛል፡፡
ግን እውን ጦርነት መፍትሄ ይሆናል !መዋጋት ድል ያመጣል? ዱላ ዳቦ ይሆናል?
የሚያዋጣን አሁንም ፍቅርና አንድነት፣ ይቅርታና የሰለጠነ ችግር የመፍታት ስልት ነው:: ቢሆንም ግን በሰላም ወጥተን የምንገባባት፣ ሕግ የሚከበርባት ሀገር ታስፈልገናለች፡፡
ተስፋችንም ፍቅርና ሕግን ማስከበር በጣምራ ነው፡፡

Read 2858 times