Sunday, 31 May 2020 00:00

ዶ/ር አሸብር በኮቪድ - 19፣ በሽግግር መንግስትና በህገመንግስት ትርጓሜ ዙሪያ…

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

   - የኮሮና ወረርሽኝ የስፖርት ዘርፉን ክፉኛ ጐድቶታል
    - ሕገመንግስቱ ትርጉም አያስፈልገውም፤ ምንም ክፍተት የለውም
    - ያልመረጥኩት ሰው እንዲመራኝና እንዲያስተዳድረኝ አልፈልግም

           በደቡብ ክልል የተለያዩ ዞኖች የክልልነት ጥያቄ ማንሳታቸውን ተከትሎ ለችግሩ መፍትሔ የሚያፈላልግ ‹‹የደቡብ ክልል የሰላም አምባሳደሮች ቡድን” በጠ/ሚኒስትር ዐቢይ መመስረቱ ይታወቃል፡፡ አዲስ አድማስ ከሶስት ሳምንት በፊት ከሰላም አባሳደሮቹ ቡድን አባል ከአቶ ወንድሙ ሀይሌ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፣ የደቡብ ሕዝብ አፋጣኝ ምላሽ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚጠብቅም ገልፀው ነበር፡፡ ይህንን ተከትሎ ማክሰኞ ሚያዚያ 4 ቀን 2012 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ከክልሉ የዞን አመራሮች ጋር በጉዳዩ ዙሪያ መወያየታቸውን በፌስቡክ ገፃቸው አስታውቀዋል፡፡ ዛሬ ደግሞ እንግዳ ያደረግነው የደቡብ ክልል የሰላም አምባሳደሮች ቡድን አባል፣ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንትና የቀድሞው የአፍሪካ ፓርላማ ተቀዳሚ ምክትል አፈ ጉባዔ እንዲሁም የአፍሪካ ፓርላማ የክብር ም/ፕሬዚዳንት ከሆኑት ከዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ ጋር ነው፡፡ የአዲስ አድማሷ ናፍቆት ዮሴፍ በኮቪድ -19 እና ባስከተለው ዘርፈ ብዙ ቀውስ ዙሪያ፣ በተራዘመው አገራዊ ምርጫ እንዲሁም የሽግግር መንግስት ማቋቋም የሚል ሃሳብ ስለሚያራምድ ፓርቲዎች፣ ስለህገመንግስት ትርጓሜና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግራቸዋለች፡፡

          ራስዎን ከኮሮና ቫይረስ እንዴት እየተከላከሉ ነው?
እኔ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ ጤና ሚኒስቴር የሚያወጣውን ምክርና የጥንቃቄ መንገዶች እየተገበርኩ፣ እንደ ሞያተኛም አስፈላጊውን ጥንቃቄና አካላዊ እንቅስቃሴም እያደረኩ እያሳለፍኩ ነው፡፡   
የኮቪድ 19 በአገራችን የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ነው፡፡ ለመሆኑ ኮቪድ 19በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካውና በማህበራዊ መስተጋብሩ ላይ እያደረሰ ያለውን ጫና እንዴት ይገልፁታል?
ኮሮና ቫይረስ በአጠቃላይ በአለማችን ላይ እጅግ ያልተጠበቁና ትልልቅ ጉዳቶች እያደረሰ ያለ አደገኛ ወረርሽኝ ነው፡፡ ጉዳቱም የበርካቶችን ሕይወት በመንጠቅ፣ ኢኮኖሚውን በማድቀቅ፣ የስነ ልቦና ጫና በማድረስና በልማት ማደናቀፍ የሚገለጽ ነው፡፡ ወረርሽኙ በዋናነት ከጎዳቸው ዘርፎች አንዱ የስፖርቱ ዘርፍ  ነው። ስፖንሰርሽፑን ጎድቶታል፣ አትሌቶችን ጎድቷል፣ ሜዳዎች ዝግ ሆነዋል፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ተዘግተዋል፡፡ የተጀመሩ ግንባታዎች በየቦታው ቆመዋል፡፡ በአጠቃላይ ሁሉንም ዘርፍ የጎዳ ወረርሽኝ ቢሆንም፣ በስፖርቱ ዘርፍ የበለጠ ጉዳት አድርሷል፡፡ ጉዳቱ ለአሁን ብቻ ሳይሆን ለወደፊትም ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል ዕዳ ጭኖብን ነው የሚያልፈው። ይሁን እንጂ ከሁሉም ቀዳሚውና ሊተርፍ የሚገባው የሰው ሕይወት ነው፡፡ አሁን በእኛ አገር የዓለም ኦሊምፒክ የተራዘመውን ያህል፣ የኢትዮጵያ ምርጫም እየተራዘመ ነው ያለው፡፡ ምክንያቱም አሁን ባለው አስጨናቂ የወረርሽኝ ወቅት ሕዝቡን ሜዳ ላይ አውጥቶ ወደ ባሰ ችግር ከመክተት ችግሩን መቋቋምና ለደጉ ጊዜ መፀለይ ነው የሚሻለው፡፡ ስለዚህ ወረርሽኙ አገራችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው፡፡
በግልም የቢዝነስ ሰው ነዎትና በግል ቢዝነሱ ላይ ያሳረፈውን ጫና ቢነግሩን?
እንዳልኩሽ በአገር ደረጃም ስፖርቱ ላይ ለጃፓን ቶኪዮ ኦሎምፒክ ዝግጅታችንን አጠናቅቀን፣ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ነበርን:: ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴም ሆነ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የውድድሩን ጊዜ በጉጉት ሲጠብቅ ነበር፤ ሰፊ ዝግጅትም አድርገን ነበር፡፡ ለአትሌቶቻችንም የስኬትና የህልማቸው መዳረሻ ኦሎምፒክ ውድድር ነውና በጉጉት ሲጠብቁ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ድካምና ልፋት ቢፈስበትም ምንም ማድረግ ስለማይቻል ተራዝሟል ችግሩ በዚህ ደረጃ የገዘፈ በመሆኑ አትሌቶቻችን በሥነ ልቦናም በኢኮኖሚም ተጎድተዋል ሁላችንም ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ ገብተናል፡፡ በግል ስራችንም ቢሆን ሰው ከቤቱ ካልወጣና እንደ ልቡ መንቀሳቀስ ካልቻለ መገበያየት፣ መስራት መነገድ አይችልም፡፡ ከዚህ አኳያም የደረሰው ጉዳት ቀላል አይደለም፡፡ ነገር ግን ከምንም በላይ የሰው ሕይወት ይበልጣል:: እኛ ካለን በጤና ከቆየን የጠፋውን ሁሉ ሰርተን እንመልሰዋለን፡፡ እኛ ከጠፋን የሚተካም የሚስተካከልም ነገር የለም፡፡ ከዚህ አንፃር ቅድሚያ ለጤንነታችን በመስጠት፣ አገራችን ላይ መስመር የሳተ ችግር እንዳይፈጠር መጠንቀቅ አለብን፡፡ መዘናጋት ይብቃ፤ የተጠቂዎቹ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን እያየን ነው፡፡
በኮሮና የተነሳ ነሐሴ ላይ ሊካሄድ የነበረው አገር አቀፍ ምርጫ መራዘሙን ተከትሎ፣ አንዳንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ “መንግሥት ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ ያወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሥልጣን ማራዘሚያ እየተጠቀመበት ነው፤ ከመስከረም 30 በኋላ አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግሥት ስልጣኑ ያበቃል፣ የሽግግር መንግሥት ተቋቁሞና ሁሉም የመፍትሄው አካል ሆኖ ከአንድና ከሁለት ዓመት በኋላ ምርጫው መካሄድ አለበት” እያሉ ነው፡፡ እርስዎ ቀደም ሲል የፓርላማ አባልና የአፍሪካ ፓርላማ ተቀዳሚ ምክትል አፈ ጉባዔ እንደነበሩ የሚታወስ ነውና… እስኪ በዚህ ዙሪያ ያለዎትን ልምድ ያካፍሉን?
ሁሉንም በየፈርጁ ማየት ተገቢ ነው፡፡ እኔ በተለይ ምርጫን በተመለከተ ከሚያውቁት ሰዎች አንዱ ነኝ፡፡ እንደገለፅሽው የአፍሪካ ፓርላማ ምክትል አፈ ጉባዔ ሆኜ ሰርቻለሁ:: ብዙ ምርጫዎችንም አስፈጽሜያለሁ፡፡ በአፍሪካ ደረጃም ብዙ ፈተናዎችን አሳልፈናል:: ምርጫዎች ሲራዘሙም ሲሰረዙም ከእነ ምክንያታቸው አውቃለሁ፡፡ በአፍሪካ ደረጃ ያሉት አብዛኞቹ ሕገ መንግሥቶች ተመሳሳይና ተቀራራቢ ናቸው፡፡ ተቃዋሚዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል:: መንግሥትም ያስኬዳል ያለውን አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ በዚህ መሀል ምን ቢሆን ይበጃል የሚለውን ማየት ነው የሚሻለው:: የኢትዮጵያ መንግሥት ምርጫውን አሁን ቢያካሂድ ኖሮ ከእርሱ በላይ ተጠቃሚ የለም፡፡
እንዴት ማለት?
ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት ተቃዋሚዎች ለምርጫ የሚያበቃ በቂ ዝግጅት የላቸውም፡።
ይህን ለማለት ያበቃዎት መነሻ ምንድን ነው? እንዴትስ ለማረጋገጥ ይቻላል?
ይህን ስናገር በእርግጠኝነት ነው፤ መረጃውም ስላለኝ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች አብዛኞቹ በሚባል ደረጃ ዝግጅት የላቸውም፡፡ ከላይ አንስተሽ እስከ ታችኛው እርከን ድረስ ያለው የብልጽግና መዋቅር ነው፡፡ ሕዝቡን በቀላሉ የማግኘት እድሉ አለው:: ደግሞም እያገኘ ነበር፡፡ ምርጫው ይካሄዳል በሚል ከፍተኛ ዝግጅት አድርገዋል፡፡ ከዚህ አኳያ ምርጫው በታለመለት ጊዜ ባለመካሄዱ ከማንም በላይ ገዥውን ፓርቲ ነው የጎዳው፡፡ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች “ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት የለም፤ ሁላችንም እኩል ነን፤ የሽግግር መንግሥት አቋቁመን እንቀጥላለን” የሚሉት ነገር ተገቢ አይደለም፡፡
ተገቢ አይደለም ሲሉ ጥያቄያቸው ሕጋዊ መሰረት የለውም እያሉኝ ነው?
ለምንድነው ተገቢ የማይሆነው መሰለሽ? አንድ የተመረጠ መንግሥት ጊዜውን ሲጨርስ ማስረከብ ያለበት ለተመረጠ መንግሥት ነው:: ሁለተኛ የአገሪቱ ፓርላማ የመጨረሻው የአገሪቱ ሉአላዊ የስልጣን አካል ነው፡፡ ያ ፓርላማ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ማለት ነው:: ያ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ ሕገ መንግሥቱን የመከላከልና የመጠበቅ ሀላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ሕገ መንግሥቱን መከላከል ሲባል ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ገምግሞ፣ ለዚያ ችግር መፍትሄ ማስቀመጥ ማለት ነው፡፡ እኔ በግሌ ምክር ቤቱ እራሱ ሕገ መንግሥቱ ለምን ትርጉም ያስፈልገዋል እንደሚል አላውቅም፡፡ ምንም ትርጉም አያስፈልገውም፤ ግልጽና ግልጽ ሆኖ ነው የተቀመጠው፡፡ ሕገ መንግሥቱን ተከላከል ጠብቅ ነው የሚለው፡፡ ከምንድነው የሚከላከለው ከተባለ ከቀውስ፣ ከችግር ነው፡፡ አገርን ወደ አደጋ ከሚወስዱ አደገኛ ነገሮችና ሁኔታዎች ነው፡፡ አሁን መጥፎ ነገሩ ምንድን ነው? ምርጫ በወረርሽኝ ምክንያት መካሄድ አይችልም፤ ከዚያ ደግሞ መንግሥት መቀጠል አይችልም የሚባል ሁኔታ ሲፈጠር ሕገ መንግሥቱን ተከላከል የሚል ስልጣን ፓርላማው ሰጥቶታል፡፡ ሕገ መንግሥት ተከላከልና ጠብቅ ሲባል በእኔ እምነት፤ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓታችን፣ አለማቀፋዊ ግንኙነታችንና የዜጎቻችንን መብት ሊያናጉ ከሚችሉ ማናቸውም አደጋዎች ጠብቅ ማለት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በዚያ ስልጣኑ ተጠቅሞ ፓርላማው ለተከሰተው ችግር መፍትሄ በማምጣት፣ አገርና ሕዝብን ከቀውስና ከአደጋ መጠበቅ አለበት፡፡
ግን እኮ ተፎካካሪዎች እያሉ ያሉት ችግር ሲፈጠር ምርጫን ለማራዘም የተደነገገ የሕግ ማዕቀፍ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ አልተካተተም ነው….
እንደዚህ ከሆነማ ምርጫን ያለማካሄድ አይቻልም የሚል ሕግም አልተቀመጠም:: ፓርላማው ሕገ መንግሥቱን እንዲከላከል የተሰጠው ስልጣን እንደዚህ ዓይነቶቹን ችግሮችም ለመፍታት ያገለግላል፡፡ ሕገ መንግሥቱን ጠብቅ ብሎታል፡፡ ሕገ መንግሥቱን የሚጠብቀው’ኮ ከጦጣ ወይም ከዝንጀሮ አይደለም! ከቀውስ ወይም አገርን የከፋ አደጋ ውስጥ ከሚከት ችግር ነው፤ አይደለም እንዴ? አገር ላይ አደጋ ተጋርጧል፤ ምርጫውም ለተወሰነ ጊዜ ይራዘማል፤ መንግሥትም ትቀጥላለህ ብሎ የመወሰን መብት አለው፡፡ “ሕገ መንግሥቱ ክፍተት አለው፤ ትርጉም ያስፈልገዋል” ሲባል ይገርመኛል፡፡ ምንም አይነት ክፍተት’ኮ የለውም፡፡ ይሄ ማለት ምንም አይነት ችግርና እንከን የለውም ማለት ግን አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ በግልፅ ገዢው ፓርቲ ያራዝማል ተብሎ ያልተቀመጠው የሚያሳየው ዓለም አቀፍ ተቃውሞን በመፍራት ነው፡፡ ባይሆንማ በግልፅ ምርጫ ያላማካሄድ የሚያስከትለውን ሕጋዊ ድንጋጌ ያስቀምጡ ነበር፡፡  
ሕገ መንግሥቱን ስለ ማሻሻል የሚያነሱ ወገኖችም አሉ፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አሁን ህገመንግስት  ስለ ማሻሻልም አናወራም፡፡ ከዚህ አደጋ እንዴት እንውጣ ነው ዋናው ነገር፡፡ ከዚህ ቀውስ ለመውጣት ያለን አማራጭና ቀዳዳ የቱ ነው የሚለው ነው መታሰብና ትኩረት ማግኘት ያለበት:: ከቀውሱ መውጫ ቀዳዳችን ደግሞ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50 ንዑስ አንቀጽ 1 ነው፡፡ እሱም ሕገ መንግሥቱን መከላከልና መጠበቅ ነው፤ አራት ነጥብ፡፡ ይሄ ለፓርላማው የተሰጠ ስልጣን ነው፡፡ ሕገ መንግሥት ማለት አገር ነው፣ ሕዝብ ነው፣ ዜጋው ነው፤ ስለዚህ ፓርላማው በተሰጠው ስልጣን ልክ ሙሉ ሃላፊነት ወስዶ ኢትዮጵያን መከላከል ነው ያለበት፡፡ ኢትዮጵያን ሲከላከል ችግር አያጋጥምም ማለት አይደለም:: የሚደሰትም ሆነ የሚከፋ አካል አይኖርም ማለትም አይደለም፡፡ እሱን በልኩ ማየትና አገሪቱን መከላከልና መወሰን አለበት::  “ከዚህ ጊዜ በኋላ መንግሥት የለም” ብሎ መናገር በራሱ ለሕዝብና ለአገር አለማሰብ ነው፡፡ አዋቂዎች እንደሚሉት፤ ከመንግሥት አልባ አገር ይልቅ ጨቋኝ እንኳን ቢሆን መንግሥት ቢኖር ይሻላል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያም ሆነች ሕዝቦቿ መንግሥት አልባ ሊሆኑ አይገባም፡፡  በተቻለ መጠን ፓርላማው ይህን ከወሰነ በኋላ መንግሥት ደግሞ ቀጣይ ምርጫ ምን መምሰል አለበት? መቼ መካሄድ አለበት? በዚህ ሂደት ላይ ከተቃዋሚዎች ጋር እንዴት እንደራደር በሚለው ላይ የውይይት መድረክ ማዘጋጀት ይኖርበታል:: ንግግር ወሳኝ ነው፤ ሰጥቶ የመቀበል ባህል ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ሥርዓት አልበኝነት ተፈጥሮ ከምንተላለቅና ከምንጎዳ መንግሥት መቀጠል ነው  ያለበት፤ ሕገ መንግሥቱም ይፈቅድለታል፡፡
የሽግግር መንግስት መቋቋም አለበት የሚል ሃሳብ የሚያራምዱ ፓርቲዎችን በተመለከተ ምን  አስተያየት አለዎት?
እኔ እንደ አንድ ዜጋ እንዲሁም ምርጫን እንደመራና እንደሚያውቅ ሰው መናገር እችላለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ሰዓት መታመን ያለበት ሥልጣን የሚገኘው  ከምርጫ ኮሮጆ ብቻ ነው የሚለው ይመስለኛል፡፡ በግሌ በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ ጥረትን አልቀበለውም፡፡ እኔ ያልመረጥኩት ሰው እንዲመራኝና እንዲያስተዳድረኝ አልፈልግም፡፡ ማንኛውም ዜጋ በዚህ የሚስማማ ይመስለኛል:: ጥቂት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፍላጎታቸው ሳንመረጥ ስልጣን እንውሰድ ነው፡፡ ፓርቲ ማለት የተወሰኑ ግለሰቦች ስብስብ እንጂ የሕዝብ ተወካይ ማለት አይደለም፡፡
 የኢትዮጵያ መንግሥት ወረርሽኙን ለስልጣን ማራዘሚያ እየተጠቀመበት ነው እንጂ ምርጫው መካሄድ ይችል ነበር የሚሉ ፓርቲዎችም አሉ…?
እንግዲህ ይሄ የእምነት ጉዳይ ነው፡፡ የሰብዓዊነት የፍጡርነት ጉዳይም ነው፡፡ ከሰው ሕይወትና ኑሮ የኔ ስልጣን ይበልጣል የምትይ ከሆነ ምርጫ ልታካሂጂ ትችያለሽ፡፡ ምርጫ አካሂደሽ ሕዝብን በወረርሽኝ ካስጨረሽ፣ ብትመረጪስ ማንን ነው የምትመሪው?
የወቅቱን አጠቃላይ ሁኔታ በተመለከተ የሕዝቡ ስሜት ምን ይመስልዎታል?
አብላጫው ሕዝብ እኔን ጨምሮ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ የተናገሩትንና የሚወስኑትን የሚቀበል፣ የሚደግፍና የሚያምን ይመስለኛል፤ ምክንያቱም ሕዝቡ ደህንነቱን ይፈልጋል፤ ጠንካራ መንግሥት ይፈልጋል፣ ልማት ይፈልጋል፣ ምርጫም ቢሆን በአስተማማኝ ሁኔታ ተዘጋጅቶ ሕዝቡም በልበ ሙሉነት ወጥቶ የሚፈልገውን መምረጥ ይፈልጋል፡፡ እንዲህ አይነት ምርጫ የሚመጣው ደግሞ በሰላማዊ ጊዜ ነው። ምንም እንኳን ራሴን ወክዬ መናገር ቢኖርብኝም፣ ሕዝቡ በተደበላለቀና ባልመረጠው ፓርቲ መመራት ይፈልጋል ብዬ አላምንም፡፡ ቢያንስ ሕግ መጠበቅ ፓርላማም መከበር አለበት፡፡ ፓርላማ የሚወስነውን መቀበልም ያስፈልጋል፡፡ ቅድም ስለ ሕገ መንግሥት መሻሻል አንስተሻል:: ግዴለም ክፉው ቀን ይለፍና ያደርሰናል፡፡ እስከዚያው እንረጋጋ፡፡ ከዚያ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ይምከርበት፡፡ ሕገ መንግስቱን ለማሻሻል ቢያንስ 6 ክልሎች ይሻሻል የሚል ሃሳብ ማንሳት አለባቸው፡፡ ያንን ህጋዊ መንገድ ተከትሎ መላውን ኢትዮጵያዊ በማሳተፍ ማሳሻል ይቻላል፡፡ ህገ-መንግስቱ ብዙ የማይመቹ ነገሮች አሉት፡፡ በተለይ “እስከ መገንጠል” የሚለው አንቀጽ 39 አይመችም፡፡ እውነቱን ለመናገር ይሄ ሁሉ ጊዜውን ጠብቆ የሚደረግ ነው፡፡
እስኪ ወደ ደቡብ ክልል የሰላም አምባሳደሮች ቡድን እንምጣ፡፡ ቡድኑ የዞኖችን የክልል እንሁን ጥያቄ ተከትሎ የተነሳውን ቀውስ በመፍታት በኩል በጐ አስተዋጽኦ እያሳረፈ እንደሆነ የአምባሳደሮቹ ቡድን አባል አቶ ወንድሙ ሃይሌ በቅርቡ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልፀው ነበር፡፡ እርስዎ እንዴት የአምባሳደሮች ቡድን አባል ሊሆኑ ቻሉ? ሌላው ጥያቄ ደግሞ “ዶ/ር አሸብር የደቡብ ሰው ስለሆኑ ይመለከታቸዋል። አባዱላ ገመዳ ኦሮሞ ናቸው፤ እንዴት በዚህ ስራ ላይ ተሳታፊ ሆኑ” በሚል ጥያቄ ሲነሳ ሰምቻለሁ፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ የተሳተፍኩት በዞኖች የክልልነት ጥያቄ ምክንያት 1ለ55ቱ ሲወሰን፤ በአጠቃላይ በክልሉ ሰላም ጠፋ፤ የሰው ህይወት መጥፋት ንብረት መውደምና መፈናቀል በዛ፡፡ እኔ እንደ ዜጋም እንደ ደቡብ ተወላጅነቴም ነገሩ ሲያስጨንቀኝ፣ ዝም ብለን ከምናይ የምንችለውን እናድርግ በሚል ነው የሰላም አምባሳደር ቡድኑ የተቋቋመው፡፡ እንደኔ ጥሩ ስራ እየሰራ የሚገኝ ቡድንም ነው፡፡ ይበጃል ያለውን ሃሳብ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርቦ፣ ህዝቡን እንዲያወያዩ ለሰላም አምባሳደሮቹ ሃላፊነት ተሰጥቶ፣ በዞኖችና በልዩ ወረዳዎች ህዝባዊ ስብሰባዎችና ጥናቶች ተካሂደዋል፡፡ ውጤቱን ቡድኑ እያዘጋጀው ይመስለኛል፡፡
አባዱላን በተመለከተ ተናገር ካልሽኝ፣ እሱ ለአገር የተፈጠረ ሰው ነው፡፡ ለራሱና ለቤተሰቡ ሳይሆን ለአገር የተፈጠረ ነው፡፡ እንዳልሽው ኦሮሞ ነው፤ ግን ደግሞ ደቡብም ነው፡፡
እሱ ሁሌ የእኛ ችግር ይቆጨዋል፡፡ ደቡብ ላይ ያለውን እምቅ አቅም ያይና ህዝቡ ለምን እንደዚህ ይጐዳል፣ ለምን ይቸገራል ብሎ ያስባል፡፡ ይሄንን ችግር ለመቅረፍ፣ መፍትሔ ለማምጣትና ለማስተባበር በቁርጠኝነት ነው የተሳተፈው:: በዋነኝነት ይህንን ሚና የተጫወተው አባዱላ ነው፡፡ እኛም እዛ ሆነን ደገፍነው አስተባበርንለት እንጂ ዋናውን ሚና የተጫወተውና ትልቁን ሥራ የሰራው አባዱላ ነው፡፡
እኔ በበኩሌ አባዱላን በማወቄ ደስተኛ ነኝ:: ፓርላማም እያለሁ አውቀዋለሁ፤ አብረንም ብዙ ስራ ሰርተናል፡፡ የክልሉም ጉዳይ ላይ ሲሳተፍ የማንንም ሃሳብ ለማፈን ሳይሆን መፍትሔ ለማምጣት ነው፡፡ አባዱላ 55ቱ ክልል ቢሆንም አንድ ላይ ቢሆንም ግዴለውም፤ ሰላም እስካመጣ ድረስ፡፡ ክላስተር የተባለውም ቢሆን ሰላም እስካመጣ ድረስ ግዴለውም፡፡ ብቻ ሰላም ይምጣ፡፡ እኔ ለሰላሙ ሚና ልጫወት ላግዝ ልደግፍ ብሎ ነው የገባው፤ እየተሳካለትም ነው:: የሚኮራበት ትልቅ ሰውና ለአገር የሚጨነቅ ነው፡፡ እኔ እንደ ወንድም፣ እንደ ጓደኛና እንደ አለቃ ሆኖ ነው የማውቀው፡፡ በዚያ ደረጃ ከአባዱላ ጋር መስራት ለኔ ክብር ነው፡፡
የክልሉን ሰላም ለማምጣት እንቅስቃሴ የተጀመረው በታህሳስ መጨረሻ ነበር፡፡ በወቅቱ ኮሮና ቫይረስ ወሬውም የለም፤ ተደራጅተን ሄደን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ስናነጋግር “55ቱንም በማይፈልጉት መጠን አንድ ላይ መጨፍለቅ ተገቢ አይደለም፤ 56 ክልል ማድረግም እንኳን በደቡብ ክልል  በአገር አቀፍ ደረጃም አይሆንም፤ እናንተም ህዝቡን በማወያየት የመፍትሔ አካል ሁኑ” ብለው እውቅና ከሰጡን ጊዜ ጀምሮ ደቡብ ላይ ሰላም ወረደ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል በገቡት መሰረት እየተካሄደ ያለበት መንገድ በክልሉ ከፍተኛ መረጋጋትና ሰላም እያመጣ፣ ጥሩ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል፡፡ የደቡብ ጉዳይን በተመለከተ፤ ወደዚህ ተልዕኮ ስንገባ ያለ አድልዎ፣ በንጹህ ልቦና ሕዝባችንን ለማገልገል መሆኑን መግለጽ እፈልጋለሁ:: ከማንጠብቃቸውና ታላላቅ ከሚባሉ ሰዎች የደረሰብን ማብጠልጠልና ክብረ ነክ የሰብዕና ማንቋሸሽ አሳዝኖናል፡፡ የማደናቀፍ ስራም ተሰርቷል፡፡ ነገር ግን በቁርጠኝነት ስለተነሳን በጽናት ተወጥተነዋል፡፡ ሕዝባችን ጉጉቱንና ፍላጎቱን ፍፁም ኢትዮጵያዊ በሆነ ጨዋነት ገልጿል፡፡ እንደ ሰላም አምባሳደሮችም ሕዝቡ የተናገረውንና የፈለገውን ሳንጨምርና ሳንቀንስ ለመንግሥት ያቀረብን ስለሆነ በቀጣይም ሕዝቡ መፍትሔ እንደሚያገኝ በአእምሮው በመያዝ፣ ሰላምና ደህንነቱን የማስጠበቅ ስራ እየሰራ፣ በትዕግስት እንዲጠብቅ እፈልጋለሁ፡፡  
“ዶ/ር አሸብር ኢትዮጵያን በእግር ኳስ ለሁለት ዓመት አስቀጥቷል፤ አሁንም ደቡብን ለማተራመስ እየሰራ ነው” የሚሉ አንዳንድ አስተያየቶች ይሰማሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ?
በእውነቱ በእጅጉ አዝናለሁ፡፡ እኔ ዕድሜ ልኬን ለኢትዮጵያ ክብርና እድገት ከመስራት ውጪ አንድም ጊዜ አገሬን አስቀጥቼ አላውቅም:: እንደተባለው ዶ/ር አሸብር ኢትዮጵያን ለሁለት ዓመት አስቀጥቷል ሲባል እሰማለሁ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ በኔ ዘመን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት አልተቀጣችም፡፡ አንድ የማስታውሰው ግን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ጽ/ቤት ሰብረው በመግባት እስከ አለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሆነ የአገር ገጽታ የጠፋበት፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም ቢሮ ሰብረው ለገቡት እውቅና የከለከለበት ወቅት ነበር፡፡ ይህንን የፌዴሬሽን በር ሰብረው የገቡትን ሰዎች ድፍረትና ሕግን ለማስከበር ጉልበት ያለው መንግሥት ቢኖር ኖሮ፣ እስር ቤት ያስገባቸው ነበር፡፡ ይሁንና እነዚህ ሰዎች መንግሥትን በኪሳቸው የያዙ ሰዎች ነበሩ፡፡  ከቀድሞው ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በስተቀር ሌሎች ሚኒስትሮች እንኳን በራሳቸው ሊወስኑ ጠቅላዩ ያሉትንም ለመፈፀም ፈቃደኞች አልነበሩም፡፡ በመሆኑም ሰዎቹ በር የመስበርና ሰው የመደብደብ ወንጀል ፈፅመው ዝም ተብለው ታልፈዋል:: እኔንም ያለ ማሳሰራቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስላልተቀበሉት ይመስለኛል። ከእሳቸው በስተቀርም እነዚህ ሰዎች የማያዝዙት መ/ቤት አልነበረም፡፡ ሌላው ቀርቶ ቤተ መንግሥት እንኳን ሚኒስትሮችና የም/ቤት አባላት ቀበቶና ጫማ አውልቀውና ተፈትሸው በሚገቡበት ቦታ ላይ ሰልፉን ረግጠው ያለ ፍተሻ ነበር የሚገቡት፡፡ ያን ያክል ስልጣንና ጉልበት የነበራቸው ሰዎች፣ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑን በር መስበርና ስልጣን መውሰዳቸው ከሕግ በላይ ስለነበሩ ላይደንቅ ይችላል፡፡ ፊፋ ኢትዮጵያን ለሁለት ዓመት አልቀጣም እንጂ ቀጥቶም እንኳን ቢሆን ሀላፊነቱን መውሰድ የነበረበት ማን ነው? አስቀጣ ተብሎ መወቀስ ያለበትስ ማን ነው? ለዚህም ነበረ ተደብዳቢው ጋዜጠኛ አቶ አማረ አረጋዊ ‹‹ገንዘብ ሲናገር ፍትህ ዝም ይላል›› ብሎ የተናገረው፡፡ እንደዚህ አይነት ነገር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌላ የአፍሪካ አገርም ታይቶ ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ ላይ ‹‹ጉብታ ቤተሰቦች›› እንደዚህ አድርገው መጨረሻቸው በውርደት ነው የተጠናቀቀው፡፡ ዞሮ ዞሮ ኢትዮጵያ አልተቀጣችም እንጂ ተቀጥታ እንኳ ቢሆን አስቀጣ መባል ያለበት ከሕግ በላይ የሆነው፣ በር ሰብሮ የገባው ወንበዴ፣ ለአገርና ሕዝብ ክብር የነሳ ሰው እንጂ ወይስ ዶ/ር አሸብር ይሆናል? ጉዳዩ ‹‹አህያውን ፈርቶ ዳውላውን›› ይሉትን አባባል ያስታውሰኛል፡፡ በአጠቃላይ ያለው እውነታ ይሄ ነው፡፡ ወደፊትም እውነታው ይወጣል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እኔም ያለ ጥፋቴ ስሜ መብጠልጠሉ አንድ ቀን ይቆማል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡  Read 1175 times