Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 07 July 2012 12:00

ሦስት ባንኮች በጋራ የአሌክትሮኒክ ክፍያ ጀመሩ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አዋሽ፣ ንብና ሕብረት ባንኮች በጋራ ባቋቋሙት ፕሪምየር ስዊት ሶሉሽንስ (ፒኤስኤስ) አ.ማ ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክስ ባንኪንግ አገልግሎት መጀመራቸውን አስታወቁ፡፡ በተመሳሳይም በአገሪቷ ባሉ ሁሉም ባንኮች ዘመናዊና ብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት ይዘረጋል፡፡በመላ አገሪቱ ከ200 በላይ ቅርንጫፎችና ከአንድ ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያሏቸው አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ንብር ኢንተርናሽናል ባንክና ሕብረት ባንክ አ.ማ በመጀመሪያ ምዕራፍ በሚተከሉት 60 ኤ.ቲ.ኤም እና በ300 ፖይንት ኦፍ ሴል መሳሪያዎች በመጠቀም ደንበኞቻቸው ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ ባንክ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ የሕብረት ባንክ ፕሬዚዳንትና የፕሪምየር ስዊት ሶሉሽንስ አ.ማ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ብርሃኑ ጌታሁን ገልፀዋል፡፡

አቶ ብርሃኑ፣ ፒ አስ ኤስ ከትናንት ወዲያ ምሽት በተመረቀበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በየዓመቱ 40 የኤ.ቲ.ኤም እና 300 የፖይንት ኦፍ ሴል መሳሪያዎች እየተጨመሩ ለደንበኞች ምቹ የካርድ አገልግሎት የማቅረብ ሂደቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ገበያ ውስጥ በውድድር መንፈስ የሚሰሩ ድርጅቶች ለጋራ ዓላማ በትብብር መቆማቸው በተለይም በአገራችን የንግድ እሳቤ አስቸጋሪ ተደርጐ እንደሚገመት አቶ ብርሃኑ ጠቅሰው፣ ሦስቱም ባንኮች ባዋጡት ሀብት የጋራ መሰረተ ልማት መስርተው ለደንበኞቻቸው ዘመዊ የኤሌክትሮኒክ ክፍያ አገልግሎት ማቅረብ መቻላቸው ሁሉንም ወገን አሸናፊ መንበር (win win situation) ላይ ያስቀመጠ በመሆኑ ድርጅቱ (ፒኤስኤስ) የተቋቋመለትን ዓላማ ሙሉ በሙሉ አሳክቷል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ከአጭር ጊዜ ስልታዊ ትብብር በዘለለ ራሱን ችሎ በቆመ ድርጅት በኩል የተመሰረተ ስልታዊ ግንኙነት ለባንኮቹ ደንበኞች የተሻለ ምርጫ ያለው የኤሌክትሮኒክ ባንክ አገልግሎት መስጠትና የአገርን ሀብት በግል ሳይሆን በጋራ መጠቀም አስችሏል፤ እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ለሚደረገው ብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት ዝርጋታ በማገዝ ረገድ የራሱን ሚና ይጫወታል ብለዋል - አቶ ብርሃኑ፡፡

ፕሪምየር ስዊት ሶሉሽንስ በርካታ ዘመናዊ አገልግሎቶችን እንዲሰጥ ታስቦ በከፍተኛ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ውጤቶች የተደራጀ ስለሆነ ከኤቲኤም ገንዘብ ማውጣትና ማስገባት፣ በሂሳብዎ ያለዎትን ገንዘብ ማወቅና አጭር የሂሳብ መግለጫ (ሚኒ ስቴትመንት) ማግኘት፣ ቪዛና ማስተር ካርድ የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ካርዶችን መጠቀም፣ የሐዋላ አገልግሎት መስጠት፣ በክፍያ ካርድ በግብይት ስፍራ (ፖይንት ኦፍ ሴል) ግዢዎችን መፈፀም… ከማስቻሉም በላይ በቅርቡ ሞባይል ባንኪንግና ኢ-ኮሜርስ ክፍያዎችን መፈፀም እንደሚያስችል ተነግሯል፡፡

በኤሌክትሮኒክ የክፍያ አገልግሎት ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት ሱፐርቪዥን ምክትል ገዢ አቶ ጌታሁን ናና በበኩላቸው፣ ባንካቸው በአገሪቷ ያሉ የንግድ ባንኮች በራሳቸው ተነሳሽነት ዘመናዊ አሰራር ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት ከመደገፉም በላይ ዘመናዊ የብሔራዊ ክፍያ ሥርዓት መዘርጋቱንና በዕለቱ የተመረቀው ፒ ኤስ ኤስ አሰራርም የብሔራዊ ክፍያ ሥርዓቱን በማገዝ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ገልፀዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ በዘረጋው ብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት በአገሪቷ ያሉ ባንኮች በሙሉ ባለ አክሲዮን የሆኑበት፣ ደንበኞች በሙሉ የሁሉንም ባንክ መሰረተ ልማት ተጠቅመው በቀላሉ የኤሌክትሮኒክ ባንክ አገልግሎት እንዲያገኙ ኢትዮ ስዊት ሶሉሽንስ የተባለ ኩባንያ መቋቋሙን አቶ ጌታሁን ጠቅሰው ፒ ኤስ ኤስም ወደፊት ከኢትዮ ስዊች ሶሉሽንስ ጋር ተገናኝቶ የተቋቋመበትን ዓላማ በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚያሳካ እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡

በአሁኑ ወቅት እየተተገበረ ባለው የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ጥቅም ላይ የሚውልበት ታላቅ አገራዊ ንቅናቄ በመሆኑ የአገራችን ባንኮች ይህንን ሀብት በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል ዘመናዊ የአሠራር ዘዴ መተግበር እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

ይህ ዘመናዊ አሠራር አገሪቷ ያላትን ውሱን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም አጋዥ አቅም የሚሰጣት ነው ያሉት አቶ ጌታሁን፤ “የኤሌክትሮኒክ ክፍያ ሥርዓት በጋራ በማቋቋም በውድድር መኻል ለመተግበር የወሰኑት የአዋሽ፣ የንብና የሕብረት ባንኮች በጋራ አንድ መሰረተ ልማትና ሀብት መጠቀማቸው ከፍተኛ አዋጭ መሆኑን በመገንዘብ ለዚህ ልዩ ፕሮጀክት ስኬት ያደረጉት ጥረት ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው” ብለዋል፡፡

“በብሔራዊ ባንክ በኩል ከፕሪምየር ስዊች ሶሉሽንስ ምስረታ ጀምሮ እስከ ትግበራው ሂደት ድረስ መስጠት የምንችለውን ድጋፍ በሙሉ ለመስጠት ሞክረናል፡፡ ይህ ድጋፋችን ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በዚህ አጋጣሚ ለመግለፅ እወዳለሁ” በማለት ቃል ገብተዋል፡፡

ኢትዮ ስዊች ሶሉሽንስ ማለት በኢትዮጵያ ያሉ ባነኮች ሁሉ (አዋሽ፣ ንብና ሕብረትን ጨምሮ) በተመሳሳይ መልኩ አንድ የክፍያ መሰረተ ልማትን መጋራት የሚያስችል ብሔራዊ የክፍያ ስዊች በመቋቋም ላይ መሆኑን አንድ ከፍተኛ የባንክ ባለሙያ ገልፀዋል፡፡

ፕሪምየር ስዊች ሶሉሽንስ አ.ማ በ165 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመ ኩባንያ ሲሆን የሦስቱ ባንኮች ደንበኛ ያልሆነ ማንኛውም ሰው ቅድመ ክፍያ ካርድ በመግዛት መጠቀም እንደሚችል ሊቀመንበሩ አቶ ብርሃኑ ጌታሁን ተናግረዋል፡፡

 

 

Read 19172 times Last modified on Saturday, 07 July 2012 12:11