Saturday, 30 May 2020 13:13

“የአንድ አካባቢ መዘጋት የተለየ ቁጣና መርገምት ተደርጎ መታየት የለበትም፤ ስርጭቱን አፍኖ የማስቀረት ስትራቴጂ ነው”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

- አሁን ወደ ከፍተኛው ችግር የመግቢያ መንደርደርያ ላይ ነን፤ “ፒክ” ወደሚባለው ከፍተኛ ችግር በምን ያህል ፍጥነት ይደርሳል?
   - ማህበረሰቡም መንግስትም የሚወስደውን እርምጃ ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጥበቅ ያለብን ጊዜ ላይ ነን
   - ሰኔ መጨረሻ ድረስ ስርጭቱ እየጨመረ እንደሚመጣ ተገምቷል፤ ከፍተኛ አደጋ ወደሚያደርሰው መንገድ እየሄድን መሆኑን ጠቋሚ ነው
   - በክልል በተለመደው የኑሮ ዘይቤ መንቀሳቀስና መዘናጋት በስፋት ይታያል፤ የአገሪቱ የገጠር ክፍል በቫይረሱ ከተጎዱ ኢኮኖሚው በእጅጉ ይጎዳል

       የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከሁለት ሳምንት ወዲህ በስፋት እየታየሲሆን፤ ችግሩን የሚያከብደውና የከፋ የሚያደርገው ደግሞ በቫይረሱ ከተያዙት አብዛኞቹ የጉዞ ታሪክም ሆነ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸው አለመሆናቸው ነው:: የጤና ጥበቃ ሚ/ር በየቀኑ የሚያደርገውን የኮቪድ ምርመራ ከሞላ ጎደል ወደ 5 ሺ ገደማ ማድረሱ ትልቅ ስኬት ቢሆንም የዚያኑ ያህል በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በቀን ከ100 በላይ አልፎ 137 መድረሱ ግን በእጅጉ
የሚያሳስብ ነው፡፡ ለመሆኑ ይሄ አሃዝ ምን ትርጉም አለው? ወደ አስከፊውና አይቀሬው ሁኔታ እያመራን ይሆን? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የድንተኛና ጽኑ ህክምና ረዳት ፕሮፌሰርና በኮቪድ 19 የጤና ቴክኒክ አማካሪ የቡድን አስተባባሪ ከሆኑት ዶ/ር ወልደሰንበት
ዋጋነው ጋር በሰሞኑ የወረርሽኙ ሁኔታ ላይ ቆይታ አድርጋለች፡፡


              ከሰሞኑ የወረርሽኙ ተጠቂዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣ ሲሆን፤ መንግስት  አብነት አካባቢ 500 አባወራዎች የሚገኙበትን መንደር ለይቶ ዘግቷል፡፡ አካባቢው መዘጋት ፋይዳው ምንድን ነው?
ይሄ እንግዲህ ስርጭቱን አፍኖ ባለበት የማስቀረት የአሰራር ስትራቴጂ ነው፡፡ በአንድ የማህበረሰብ ስርጭት አለበት ተብሎ በሚታሰብበት አካባቢ ቫይረሱ ወደ ሌላው በስፋት እንዳይዛመት የሚደረግበት አሰራር ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን የመቆጣጠሪያ አንዱም መንገድ ነው፡፡
በተዘጋው መንደር ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች አይወጡም አይገቡም፤ ከወዳጅ ዘመድም አይገናኙም፡፡ እነዚህ ሰዎች ከህብረተሰቡ መገለል እንዳይደርስባቸው ስጋት አለ፡፡ መገደባቸውን ተከትሎ በዕለት ተዕለት ኑሯቸው ላይ ችግር እንዳይገጥማቸው ምን እየተደረገላቸው ነው?
እውነት ለመናገር ከባድ ነው፡፡ እዚያ አካባቢ ያለው ማህበረሰብ ስነ - ልቦናዊ ጫና ቀላል አይሆንም፡፡ አጠቃላይ የወረርሽኙ ባህሪ ስነ - ልቦናዊ ጉዳትን የሚያስከትል ነው፡፡ ይሄ በግልጽ ይታወቃል፡፡ የአካባቢውም እንቅስቃሴ ሌሎች መስተጋብሮች የሌሉት ሲሆን የራሱ ጫና ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን ጫናው አንድ ግለሰብ ኳራንቲን ገብቶ ሲወጣ ከሚፈጠርበት ጫና አይበልጥም፡፡ ለምን ካልሽኝ… በተዘጋው መንደር ቢያንስ እንደ ማህበረሰብ አንድ ላይ ነው ያሉት:: አንዱ አንዱን የማጽናናትና የማበረታታት እድሉ አላቸው፡፡ ግለሰብ ግን አስቢው… ከወዳጅ ዘመድና ከቤተሰብ ስለሚገለል ጫናው ትንሽ ይበረታበታል፡፡ መንደር ሲሆን ጫናው ይቀንሳል ለማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከ “ሎክዳውን” ሲወጡ የስነ ልቦናና በህክምናው “ሳይኮ ሶሻል ሰፖርት” የሚባለው ድጋፍ ዝግ ሆኖ ለቆየው አካባቢ ሰዎች በባለሙያ መሰጠት አለበት፡፡
አድልዎና ማግለልን በተመለከተ ወረርሽኙ አንድ መንደር ወይም አንድ አገር ላይ የተከሰተ ሳይሆን በመላው አለም ዘርና ቀለም፣ ሀብትና ድህነት ሳይለይ የተሰራጨና ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለ ነው፡፡ እነዛ ሰዎች እንደ ሌላው መንቀሳቀስና መስራት እየፈለጉ ለእኛ ሲሉ መስዋዕትነት እየከፈሉ እንደሆነ ነው ማህበረሰቡ ማሰብ ያለበት፡፡ ስለዚህ ስርጭቱን ለመግታት አንዴ ኳራንቲን ተደርገው፣ ያ ጊዜ ሲያልፍ እንደ ማንኛውም ማህበረሰብ ነፃ ይሆናሉ:: ሰዎችን ማግለል የለብንም፤ ይሄ ፈጽሞ ትክክል አይደለም፡፡ ማግለል ዋጋ ያስከፍለናል እንጂ አይጠቅመንም፡፡ ይሄ ክፉ ነገር ከእኛ ወጥቶ ለሌሎች አይትረፍ በሚል መስዋዕትነት እየከፈሉ ነው፡፡ ይሄ ነገር ሲያልፍ በእድር በዕቁብና በማንኛውም ማህበራዊ መስተጋብር እንደ ሌሎች ህይወታቸውን ይቀጥላሉ፡፡ እንደውም ከኳራንቲን ሲወጡ ከእነሱ ብዙ ልምድ እናገኛለን፡፡ በኳራንቲን ወቅት እንዴት እንዳሳለፉ፣ ምን እንደተማሩ፣ ጥንካሬያቸውን እንማርበታለን፡፡ ለሌሎች ማህበረሰቦችም ምሳሌና ትምህርት የሚሰጡንን ሰዎች ዛሬ ልናገላቸው አይገባም፡፡ ነገ ችግሩ ወደ ሁላችንም መንደር ሊመጣ ይችላል፡፡ ስለዚህ የዚህ መንደር መዘጋት የተለየ ቁጣና መርገምት ተደርጐ በፍፁም መታየት የለበትም፡፡ እዚህ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ይሄ መንደር የታጠረው ለቅሶ ላይ የተለመደው ማህበራዊ እንቅስቃሴ ሲደረግ በተፈጠረ የቫይረስ ስርጭት ነው፡፡ እዛ መንደር ላይ ማህበራዊ ስርጭት የሚመስል ነገር በላብራቶሪ ምርመራ በመገኘቱ ነው የተዘጋው፡፡ በሌላውም አካባቢ ማህበራዊ ስርጭት የሚመስል መልክ ከያዘና ስጋት ካስከተለ ወደ ሌላው እንዳይስፋፋ አካባቢው ይዘጋል፡፡
ሰሞኑን የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ ነው፡፡ የሟቾች ቁጥርም 8 ደርሷል፡፡ የወረርሽኙ ሥርጭት በምን ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው ማለት ይቻላል?
በሽታው የተለያዩ ደረጃዎች አሉት፡፡ አንድ አገር ላይ መጤ የሆነ የበሽታ ስርጭት መታየት፣ ከዚያም አልፎ “ክላስተር” የምንለው ውስን ቦታዎች ላይ ብልጭ ብልጭ ብሎ መታየትና በዚያው ማብቃት ሁኔታዎች ይታያሉ፡፡ ከዚያም አለፍ ሲል ደግሞ ከአካባቢው በዛ ያለ ግለሰብ፣ ከዚያም ማህበረሰብ ጋር እየደረሰ፣ ስርጭቱ ሶስተኛና አራተኛ ደረጃ እየተላለፈ በሚመጣበት ጊዜ ማህበረሰባዊ ስርጭት እንለዋለን፡፡ ወደ ከፍተኛው ችግር የመግቢያ መንደርደሪያ ላይ ነን የሚያስብለው ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡ በእርግጥ ጅምሩን መንግስት የወሰደው እርምጃ፣ የጤና ዘርፉም ላይ የተሰራው ስራ አዘገየው እንጂ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ይጠቃል ተብሎ ነበር የተገመተው ከዚህ ቀደም ብሎ ነበር፡፡
ማህበረሰቡም እጅ በመታጠብ፣ በመራራቅ፣ ባለመጨባበጥ… ለጥሪው የሰጠው ምላሽ፣ የወጡ የህግ ማዕቀፎችም ተደማምረው ፍጥነቱን አዘግይቶታል፡፡ እንግዲህ በመንግስት የሚወሰዱ እርምጃዎችም ሆነ ማህበረሰቡ የሚሰጠው ምላሽ ሙሉ በሙሉ አያስቀረውም፤ ነገር ግን ያዘገየዋል፡፡ እኛም አገር የሆነው ይሄው ነው፡፡ አሁን ያለንበትን ሁኔታ ስንመለከት፣ ከክላስተር ዝቅ ያለ ማህበረሰባዊ ሥርጭት ብልጭታ ታይቷል፤ ነገር ግን ይሄ ነገር “ፒክ” ወደሚባለው ከፍተኛ ችግር በምን ያህል ፍጥነት ይደርሳል የሚለውን በግልጽ ለማስቀመጥ ለእኛም ግራ የሚያጋባ ወቅት ላይ ነው ያለነው፡፡ ጠቅለል ስናደርገው፣ የሰሞኑ ውጤቶች፣ ማህበራዊ ሥርጭት ደረጃ ላይ እንደደረሰ ማሳያዎች ናቸው፡፡
በቀጣይ ሳምንታት የወረርሽኙ ሁኔታ ምን አይነት ደረጃ ላይ ይደርሳል ተብሎ ይገመታል?
እንግዲህ ከዚህ በኋላ ሰኔ መጨረሻ ድረስ እየጨመረ እንደሚመጣ ተገምቷል:: “ፕሮጀክሽን ሞዴል” የሚባል ነገር አለ፡፡ በርካታ አስተዋጽኦ ያላቸው ነገሮች ተደምረው በቀጣይ ምን ይፈጠራል የሚል መላ ምት ነው:: ያ የሚያሳየን ከዚህ በኋላ ስርጭቱ እየጨመረ መንደርደሪያው ከፍ እንደሚልና ከፍተኛ አደጋ ወደ ሚያደርሰው መንገድ እየሄደ መሆኑን ነው:: አሁን ያለንበት ሰሞን ጥሩ ያልሆነ ጊዜ ነው፡፡ ማህበረሰቡም መንግስትም እየወሰደ ያለውን እርምጃ ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጥበቅ ያለብን ጊዜ ላይ ነን፡፡
አብነት አካባቢ የተዘጋው መንደር እስከ ምን ያህል ጊዜ ነው የሚቆየው?
ምን ያህል ጊዜ ተዘግቶ ይቆያል ለሚለው ስርጭቱ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ ወይም ባለበት እንደተገደበ እስኪረጋገጥ እስከ ሁለት ሳምንት ጊዜ ይፈጃል፡፡ እዚያ አካባቢ ናሙና ይወሰድና ውጤቱ ታይቶ ምንም አይነት ስርጭት ከሌለ፣ ነፃ ይሆናሉ፡፡ በጥቂቱ እስከ ሁለት ሳምንት ይወስዳል፡፡ ያ ካልሆነ እስከ ወራትም ሊቆይ ይችላል፡፡ ይህን የሚወስነው የአካባቢው የእንቅስቃሴ ሁኔታ ነው፡፡
የታጠረው መንደር ኗሪዎች በተገደቡበት ወቅት ምን የሚከናወኑ ነገሮች አሉ?
አንድ አካባቢ ከተዘጋ የሚከወኑ ነገሮች፡- ከአንዱ ግለሰብ ወደ ሌላኛው ግለሰብ በሽታው እንዳይሰራጭ እንቅስቃሴዎች ይገደባሉ፡፡ አስፈላጊና መሰረታዊ ግብአቶች ከመንግስት እንዲቀርብላቸው ይጠበቃል፡፡ ከዚያም ባለፈ የህክምና እርዳታዎች “ሳይኮ ሶሻል ሰፖርት”  የስነ - ልቦና እርዳታዎች ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አስፈላጊ የሆኑ ናሙናዎች በየጊዜው መውሰድና በአካባቢው ምልክት ያለው ሰው ካለ፣ ያንን አካባቢ እየፈለጉ አሰሳ ማድረግ ይጠበቃል፡፡ አሁንም ይሄ እየተደረገ ያለው ይሄ ነው፡፡
የኮቪድ -19 ወረርሽኝ በክልሎች ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
ሰሞኑን በክልል ቅኝታችን እንደተመለከትነው፣ ከክልል ይልቅ በአዲስ አበባ የተሻለ ግንዛቤ እንዳለ ተረድተናል፡፡ በክልል አካላዊ መራራቅን ጨምሮ እስከ የፊት ጭምብል አጠቃቀም ድረስ ክፍተቶች ተመልክተናል፡፡ በተለመደው የኑሮ ዘይቤ መንቀሳቀስና መዘናጋት በስፋት ይታያል:: በአብዛኛው ክልሎች ወደ ገጠርም ወጣ ስንል የሚታየው ይሄው ነው፡፡ ይሄ አይነት ቸልተኝነት ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍለናል:: አዲስ አበባ ላይ አብዛኛው ማህበረሰብ ጥሩ ምላሽ ሰጥቷል:: ይሄ ወደ ክልሎች እስከ ጫፍ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ድረስ መውረድና በአፋጣኝ መተግበር አለበት፡፡ ከአዲስ አበባ ጋር ተመሳሳይ ስራ ካልተሰራ፣ በተለይ በአገሪቱ የገጠር ክፍል የመሠረተ ልማትና በርካታ ችግሮች ስላሉ በቂ የህክምና ድጋፍ ለመስጠት ተግዳሮት ይገጥማቸዋል፡፡ የጤና ስርዓቱንም ከከተማው ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ልዩነት ነው ያለው፡፡ ይሄ ደግሞ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ የአገሪቱ የገጠር ክፍል ሲጐዳ ኢኮኖሚውም በእጅጉ ይጐዳል፡፡ ስለዚህ የምግብ ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ ችግር ስለሚፈጠር ገጠሩ የአገራችን ክፍል ከፍተኛ ትኩረትና ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው ተገንዝበናል፡፡ ሁሉንም አዳርሰን አላየንም፡፡ ሌሎችም የመንግስት አካላት እየዞሩ እያዩ ነው:: የምላሽ ሁኔታውን በክልል ማጠናከር፣ በአዲስ አበባ ላይ የሚደረገው ጥንቃቄና ትጋት በገጠር አካባቢዎች እንዲሰራና እንዲጠናከር እርዳታም እየተደረገ ነው፡፡ አዲስ አበባ የሚደረገው ሁሉ በክልሎችም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
ወደ አማራም ክልል ስንመጣ፣ አካባቢው የንግድ ቀጠናና ድንበር አካባቢ ከመሆኑ አንፃር፣ ከሱዳን ጋር ያለውን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ነው፡፡ “ማንዳቶሪ ኳራንቲን” አድርጐ ለመቆጣጠር መግቢያና መውጫው አንድ ወጥ ባለመሆኑ በእጅጉ ያስቸግራል፡፡ ለዚህ ደግሞ የጤና ዘርፉ ብቻ ሳይሆን የደህንነትና የተለያዩ የህግ አስከባሪ አካላት በሙሉ ዋጋ እየከፈሉ ነው፡፡ ድንበር አካባቢ ስንል መተማ ብቻ ሳይሆን አፋር፣ ጋምቤላና ሶማሌም አካባቢ በእግር የመግባትና የመውጣት ሁኔታዎች ይታያሉ፡፡ ይሄን ለመቆጣጠር ማህበራዊ ግብረ -መልስና የተጠናከረ ግብረ ሃይል ያስፈልጋል:: እንግዲህ  አትገባም መባል የለበትም፡፡ የሰው እንቅስቃሴ ካለ ህጋዊ የሆኑ መግቢያዎችን ፈቅዶ ኳራንቲን ማድረግ ነው የሚበጀው:: በድንበር አካባቢ ያለውን ማህበረሰብ እውቀት መገንባትና ግንዛቤውን ማሳደግ፣ ሰው በሽታውን ከመከላከል አንፃር ለራሱና ለሌሎችም እንዲጠነቀቅ ማድረግ ያስፈልጋል:: ሚዲያውም ችግሮች ባሉባቸው አካባቢዎች ሁሉ ግንዛቤ የመፍጠር ሃላፊነት አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡   


Read 1471 times