Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 07 July 2012 12:00

በጫት ላይ ኤክሳይዝ ታክስ የሚጥል ረቂቅ አዋጅ ወጣ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የጫት ነጋዴ ቫት እንዲሰበስብ ይገደዳል

ለአገር ውስጥ ገበያ በሚቀርበው ጫት ላይ በኪ.ግ 5 ብር ቀረጥ ያስከፍላል

የአገር ውስጥ የጫት ፍጆታ በከፍተኛ መጠን እያደገ በመሄዱ ለአገር ውስጥ ፍጆታ በሚውለው ጫት ላይ የሚጣለውን ታክስ በማሻሻል የአገር ውስጥ ፍጆታን ለመቀነስና ወደ ውጭ የሚላከውን ምርት ለማሳደግ ያስችላል የተባለ የጫት ኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ወጣ፡፡የጫት ምርት ቀረጥ የሚሰበሰበው በቢሮ ውስጥ ሳይሆን ጫት በሚጓጓዝባቸው መንገዶችና ምርቱ በሚነሳባቸው ቦታዎች ላይ በተቋቋሙ የመቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ወይም ኬላዎች ሲሆን ይህ ደግሞ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ካልተደረገበት በስተቀር ለሥነ ምግባር ችግር የሚያጋልጥ ከመሆኑም በላይ ሊሰበሰብ የሚገባውን ገቢ ያስቀራል  በረቂቅ አዋጁ ላይ እንደተገለፀው፡፡

 

 

አሁን በአገሪቱ ያለው የጫት ቀረጥ እና አሰባሰብ ሥርዓት እየተስፋፋ ያለውን የአገር ውስጥ የጫት ፍጆታ ከመግታት ይልቅ የበለጠ የሚያበረታታ እና ኤክስፖርቱን የሚያዳክም እንደሆነ የሚገልፀው ረቂቅ አዋጁ፤ ይህንን ችግር ለማቃለል ተገቢውን የቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋት ኤክሳይዝ ታክሱ በተወሰኑ ስትራቴጂካዊ ቦታዎች ላይ ብቻ እንዲሰበሰብ ማድረጉ ተገቢ መሆኑን ያመለክታል፡፡

ለአገር ውስጥ ፍጆታ በሚውለው ጫት ላይ በኪሎ ግራም 5 ብር የኤክሳይዝ ታክስ እንዲከፈልበት መደረጉን ረቂቅ አዋጁ በግልፅ አስቀምጦታል፡፡ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ከሚመለከታቸው የክልልና የከተማ አስተዳደር አካላት ጋር በመነጋገር ታክሱን ጫት በሚመረትባቸውና አመቺ በሆኑ ውስን ቦታዎች ላይ ብቻ ጣቢያዎችን በማቋቋም ሰብስቦ በየወሩ የገቢው ባለቤት ለሆነው ክልል ያስተላልፋል፡፡

በጫት ላይ ከሚጣለው ኤክሳይዝ ታክስ በተጨማሪ ማንኛውም በጫት ንግድ ሥራ ላይ የተሰማራ ነጋዴ አመታዊ የሽያጭ ገቢውን መሰረት በማድረግ፤የተጨማሪ እሴት ታክስ ወይም ተርን ኦቨር ታክስ ከተጠቃሚው እንዲሰበሰብ፤ እንዲሁም ከተጣራ አመታዊ ገቢው ላይ የንግድ ትርፍ ግብር እንዲከፍል የሚያስገድድ ልዩ ድንጋጌ በረቂቅ ህጉ ላይ ተካትቷል፡፡

ለውጪ ንግድ የሚውለውን ጫት ለማበረታታት ለኤክስፖርት የሚውል የጫት ምርት በኬላ በኩል ሲያልፍ ላኪው ታክሱን በገንዘብ ሳይሆን በቫውቸር እንዲከፍል በማድረግ ወደ ውጪ ለተላከው ምርት የጉምሩክ ዴክላራሲዮን በማቅረብ፤ ወደ ውጪ ሳይላክ ቀርቶ አገር ውስጥ ለተሸጠው ደግሞ ታክሱን በመክፈል ቫውቸሩን የሚያወራርድበት ሥርዓት ሥራ ላይ ይውላል፡፡ ረቂቅ አዋጁ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውይይት በቀረበበት ወቅት የመድረክ ተወካዩ አቶ ግርማ ሰይፉ እድሜአቸው ከ18 አመት በታች የሆኑ ህጻናት በጫት ንግድ ስራ ላይ ለመሰማራት እንዳይችሉ የሚከለክል አንቀፅ በአዋጁ ላይ እንዲካተት ጠይቀዋል፡፡ ሰዎች በቀላሉ መዝናኛ የለንም ብለው የሚያርፉበት እንዳይሆንና የጫት ተጠቃሚውን ቁጥር ለመቀነስ ይቻል ዘንድ ቆንጠጥ የሚያደርግ አዋጅ ሊወጣ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ ሀሰን አብዲ በአቶ ግርማ ሰይፉ የቀረበውን ሀሳብ በመቃወም በጫት ላይ ከልካይ ሕጎች ሊወጡ አይገባም ጫት ቅሞ ስራውን የማይሰራ ሰው የለም፡፡ ጫት ለአገሪቱ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ መሆኑ ሊታይ ይገባል ብለዋል፡፡

የጫት ግብርን ለማስከፈል በወጣው አዋጅ መሰረት፤ መከፈል ሲገባው ይህ አዋጅ ፀድቆ በሥራ ላይ እስከዋለበት ቀን ድረስ ያልተከፈለ ታክስ በዚያው አዋጅ መሰረት ገቢ እንዲሆን እንደሚደረግም ረቂቅ አዋጁ ደንግጓል፡፡

 

 

Read 20509 times Last modified on Saturday, 07 July 2012 12:12