Print this page
Saturday, 30 May 2020 12:55

የትግራይ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ወዴት ያመራል?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

    የ”ፈንቅል” እንቅስቃሴ ዓላማና ግብ ምንድን ነው?
                     - ህወኃት እንዴት ያስተናግደው ይሆን?

          በትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች ከ8 ቀናት በፊት ጀምሮ ተቃውሞና ሰላማዊ ሰልፍ እየተካሄደ መሆኑን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተገለፀ ሲሆን የክልሉ መንግሥት ደግሞ ምንም ችግር የለም ውሸት ነው እያለ ይገኛል፡፡ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው አረና ትግራይ በበኩሉ የችግሩን ስፋትና መጠን የሚተነትኑ መረጃዎችን እያጋራ ቆይቷል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በትግራይ ክልል ባሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች
ዙሪያ ከአረና የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ተክለዝጊ ወ/ገብርኤል ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጓል፡፡

                 ትግራይ ክልል ላይ ምንድን ነው እየሆነ ያለው?
በትግራይ ክልል ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ከበድ ያለ ነው:: ሁሉም እንደሚያውቀው የትግራይ ሕዝብ እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ በህወኃት ሥርዓት ታፍኖ ነው የቆየው:: ሕዝቡ ብዙ ጥያቄዎች አሉት የአስተዳደር ጥያቄ አለ፡፡ የስራ አጥነት ጥያቄ አለ፡፡ የፍትህ ጥያቄ አለ፡፡ ለእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ የመንግሥት አካል የለም፡፡ ያለው የክልሉ መንግሥት ከወሬና ከፕሮፖጋንዳ የዘለለ ነገር የለውም:: አሁን ደግሞ ከወትሮው በባሰ የሕዝብ ጥያቄ ታፍኖ ነው ነው:: ሕዝቡ ደግሞ አሁን ይበቃል አልታፈንም እያለ ነው ትልቅ እንቅስቃሴ እያደረገ ያለው፡፡
ምን አይነት እንቅስቃሴ ነው እያደረገ ያለው?
መንገድ ዘግቶ ተቃውሞውን እያሰማ ነበር የቆየው፡፡ ሕዝቡ በሰላማዊ መንገድ ነው ተቃውሞውን ጥያቄውን እያቀረበ ያለው የክልሉ መንግሥት ደግሞ ይሄን ጥያቄ የበለጠ ለማፈን ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው፡፡ ሕዝቡ ደግሞ እኛ በመረጥነው አካል ነው መተዳደር ያለብን:: የትግራይ ሕዝብ ከላይ እስከ ታች ያለው አስተዳደር  በራሱ በመረጠው ሀይል እንዲመራ ነው ፍላጎቱ፡፡ ይሄን ነው በዋናነት እየጠየቀ ያለው:: ሁለተኛው ትልቅ ጥያቄ ደግሞ የአስተዳደር አወቃቀር ነው፡፡ ሕዝቡ አንድ የወረዳ ጽ/ቤት ሄዶ አገልግሎት ለማግኘት እስከ 50 ኪ.ሜትር በትንሹ ይጓዛል፡፡ ይሄ አመቺ አይደለም፡፡ የትግራይ ሕዝብ ዋጋ የከፈለው በቅርብ ርቀት ያለብዙ ውጣ ውረድ እንዲተዳደር ነው፡፡ ስለዚህ አደረጃጀቱ ይስተካከልልን በቅርበት ነው አስተዳደር አገልግሎት ማግኘት ያለብን የሚል ጥያቄ ነው ያለው ከዚህ በፊት ወረዳ የነበሩ ነገር ግን አሁን ከሌላ ጋር የተጨፈለቁ አሉ፡፡ እነሱ በቅርበት አስተዳደር ይዋቀርልን የሚል ጥያቄ ጠንከር ብለው እያቀረቡ ነው፡፡ በአጠቃላይ የአስተዳደርና የአፈና ሥርዓት ተቃውሞ ነው እየተካሄደ ያለው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ አሁን ካለው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተገናኘ ሰዎች እየተገደሉ ነው፡፡ ወጣቶች ትንሽ ሰብሰብ ብለው ሻይ ቡና ሲሉ ከተገኙ ይገደላሉ፡፡ በዚህ አዋጅ መነሻ እስካሁን 3 ወጣቶች ተገድለዋል፡፡ ሁለቱ መቀሌ ላይ አንድ አክሱም አካባቢ ነው:: ምንም ሳያጠፉ ነው፡፡ ወጣቶች ለምን ሶስት አራት ሆነው ቆሙ ተብለው በቀጥታ ይገደላሉ፡፡ እነሱ ግን በየጊዜው በአዳራሽ በመቶዎች ሆነው ስብሰባ እየተቀመጡ ነው፡፡ አሁን እንኳ በአንድ አዳራሽ እስከ 150 ሰው ነው እየሰበሰቡ ከንቲባ የሚመርጡት ካድሬ የሚያወያዩት፡፡ ወጣቶችን ግን ተሰበሰባችሁ ብለው እያደኑ ይገድላሉ፡፡ ሁለት ሶስት ሆናችሁ ጠላ ጠጥታችኋል ብለው ነው መቀሌ በገዛ ቀዬአቸው ላይ ወጣቶች ላይ ተኩሰው የገደሉት፡፡ ሕግ ጥሰዋል ቢባል እንኳ እንዴት በቀጥታ በጥይት ይገደላል? ይሄ የክልሉን ገዥ ፓርቲ ለሕዝቡ ያለውን ንቀትና አመለካከት ያሳያል፡፡ ይሄ ሁሉ ተደማምሮ ሕዝቡ ጫፍ የደረሰ ብሶት ውስጥ ነው ያለው፡፡ ለምሳሌ ሽረ በተደረገው ሰልፍ መንገድ ተዘግቶ ነው ጥያቄያችን ይመለስልን በመረጥናቸው አካላት ነው መመራት ያለብን በሚል ከ8 ቀን በላይ ተቃውሞ ሲያደርግ የነበረው፡፡ በደቡብ ትግራይ አካባቢ በተለይ ወጅራት ሰላማዊ ሰልፎች ተደርገዋል፡፡ ነገር ግን ትግራይ ውስጥ ያሉ ሚዲያዎች የራሱ የህወኃት ልሳን ናቸው:: ስለዚህ ሁኔታውን እየደበቁ ነው፡፡ የሕዝብ ድምፅ እያፈኑ ነው፡፡ እነ ዋልታ፣ ፋና ጉዳዩን ይፋ ያወጡት እኛ ነገሩን ለማሳወቅ ጥረት ስናደርግ ከሰነበተ ከ8 ቀን በኋላ ነው፡፡ እነሱ እንደውም መረጃውን በማቅረብ በኩል አልፈጠኑም:: በትግራይ ውስጥ ያለው አፈና እንዲህ ቀላል አይደለም፡፡ ሕዝቡም በዚያው ልክ የመጣው ይመጣ ብሎ ለመብቱ ትግል እያደረገ መብቱን እየጠየቀ ነው፡፡
ጥያቄዎቹን ሕዝቡ በግልጽ ማቅረብ የጀመረው መቼ ነው?
ሕዝቡ ከዚህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በፊትም በተለያየ መንገድ ሲያቀርብ ነበር፡፡ ከዶ/ር ደብረ ፂዮን አስተዳደር በፊት ጀምሮ ነበር ጥያቄው ሲቀርብ የነበረው፡፡ እንደውም በዶ/ር ደብረ ፂዮን አስተዳደር የተሻለ ተስፋ ይኖራል የሚል እምነት ነበረው ሕዝቡ፡፡ ነገር ግን ያ አልሆነም:: መሬት ላይ ዶ/ር ደብረ ፂዮን አስተዳደር ሲፈተሽ ምንም የፈጠረው አዲስ ነገር የለም፡፡ በዚህ ሕዝቡ አሁን በእጅጉ ተስፋ ቆርጧል፡፡ ስለዚህ ያለው አማራጭ ተቃውሞ ማቅረብ ነበር፡፡ ይሄ አዝማሚያም ሁኔታውን ወደ አመፅ እንቅስቃሴ ሊወስደው ይችላል፡፡ ሕዝቡ በጣም የተበደለ ነው፡፤ አሁን ጥያቄውን የሚፈታለት ስላጣ ነው ጎዳና ላይ ወጥቶ ተቃውሞ ማሰማት የጀመረው:: ነገር ግን በዚህ ጥያቄውም ምላሽ የሚሰጥ አካል የለም፡፡ ለመመለስም ፍላጎት ያለው የክልል መንግሥት አይደለም ያለው፡፡ ሕዝቡ አመፁን አይወድም ሰላማዊ ነው ነገር ግን አፈናው ስለበረታበት ነው ወደዚህ እየተገፋፋ ያለው፡፡ አሁን ሁኔታውን ስናየው ሕዝቡ የሰላማዊ ትግሉ ጫፍ ላይ የደረሰ ትግል ለማካሄድ የተዘጋጀ ይመስላል፡፡
‹‹ፈንቅል›› የሚል እንቅስቃሴ አለ የሚል ነገር ነው በብዛት በማህበራዊ ሚዲያዎች የምንመለከተው በእርግጥስ እንዲህ ያለ የተደራጀ እንቅስቃሴ ነው ያለው? እንቅስቃሴውስ የፖለቲካ ድርጅቶች ነው ወይስ የሕዝቡ?
ፈንቅል የሚል እንቅስቃሴ በእርግጥም ተፈጥሯል፡፡ ነገር ግን ፈንቅል የሚለው ስያሜ በፊት ጀምሮ የነበረ የታጋይ ሀየሎም አርአያ የትግል እንቅስቃሴ ስም ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ጭቆና አፈናን አልቀበልም በሚለው እንቅስቃሴ ውስጥ የሃየሎምን ጀግንነት መነሻ ያደረገ ስያሜ ነው፡፡ ፈንቅል የሚለው ነገር ጭቆናን አፈናን ለመቃወም የሚደረግ እንቅስቃሴ መጠሪያ ነው:: አሁን በዚህ ሰሞን የነበረ እንቅስቃሴ ነው በድጋሚ እየተፈጠረ ያለው፡፡ ይሄን እንቅስቃሴ የሚመሩት ሰዎችም በግልጽ ራሳቸውን አሳውቀዋል፡፡ ግን ሕዝቡ ጋ ምን ያህል እንቅስቃሴያቸውን እያሰረፁ ነው የሚለውን በቀጣይ የምናየው ነው የሚሆነው፡፡ እኛ እንደ አረና በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ የለንበትም፡፡ ነገር ግን የሕዝቡን ትግል እንከተላለን እንደግፋለን ከፈንቅል እንቅስቃሴ ጋር ግን እንደ ድርጅት እኛ ግንኙነት የለንም፡፡ እኛ ትኩረታችን የሕዝቡን ድምፅ ማስተጋባትና የሚመለከተው አካል እንዲሰማ ማድረግ ነው፡፡ ጉዳዩ አሁን ከህወኃት መፍትሄ ያገኛል ብለን ግን አናምንም:: ምክንያቱም ህወኃት ይሄን ጥያቄ ለመመለስ ብቁ አቋም ላይ አይገኝም፡፡ ውስጡ በራሱ ጥሩ አይደለም፡፡ በቡድን ተከፋፍሏል፡፡ የእነ ደብረ ፂዮን ቡድን የእነ አለም ገ/ዋህድ የሚባል ቡድን አለ፡፡ በቡድን የተከፋፈለ ድርጅት ሆኗል:: በዚህ ሁኔታው እንኳን ክልል ሊመራ ይቅርና ይሄ ድርጅት የመቆየቱ ጉዳይ ራሱ ጥያቄ ውስጥ ነው ያለው፡፡  
ህወኃት በቡድን የተከፋፈለ ነው ሲሉ ማስረጃዎ ምንድን ነው?  ምን ያህል እርግጠኛ ኖት?  ህወኃት ይበልጥ ተጠናክሬያለሁ እያለ ነው?
እሱ ተጠናክሬያለሁ የሚለው የተለመደው ማጭበርበር ነው፡፡ ይሄን ማጭበርበር ወደ ጎን እንተወውና ህወኃት በቡድን የተከፋፈለ መሆኑ በራሳቸውም ሰዎች እየተገለፀ ያለ ጉዳይ ነው:: ከበፊት ጀምሮ ያለ ችግር ነው:: የእነ አባይ ወልዱ፣ የእነ አዜብ፣ የእነ ሳሞራ የኑስ የሚባሉ ቡድኖች በየጊዜው ነበሩ እነዚህ ሁሉ ቡድኖች ተመትተው አሁን የቀሩት የእነ ደብረ ፂዮንና የእነ ጌታቸው ረዳ ቡድን በአንድ በኩል በሌላ በኩል ደግሞ እነ አለም ገ/ዋህድ፣ እነ ፈትለወርቅ ያሉበት የእነ ስብሃት ቡድን አለ፡፡ እነ አባይ ወልዱ ቡድን ሲመታ ታስቦ የነበረው የእነ ስብሃት ቡድን ፈትለ ወርቅን ወደፊት ለማምጣት ፈልገው ነበር ግን አልተቻለም ነበር የእነ ደብረ ፂዮን ወደፊት መጣ፡፤ አሁንም እነዚህ ሁለት ቡድኖች በህወኃት ውስጥ አሉ፡፡ ለእነ ዶ/ር ደብረ ፂዮን ቡድን ከባድ የሆነ በእነ አለም ገ/ዋህድ የተሰራ ኔትዎርክ በትግራይ ውስጥ አለ፡፡ ስለዚህ እነ ዶ/ር ደብረ ፂዮን አሁን ያንን ኔት ዎርክ ማፍረስ አልቻሉም፡፡ ያ ቡድን በጣም ከባድ ኔት ዎርክ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ እነ ዶ/ር ደብረ ፂዮን ነገሮችን ማስተካከል አልተቻላቸውም፡፡ አንዳንዴ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ሕዝብ ጠላቶች እኛው ነን ሲል ይደመጣል፡፡ ይሄን ሲል ዝም ብሎ አይደለም:: አንድ ከፊታቸው የተጋረጠ ፈታኝ ነገር እንዳለ አመላካች ነው፡፡
የክልሉ መንግሥት ግን በክልሉ ምንም ችግር የለም እንደውም መገናኛ ብዙሃንን ተጠያቂ አደርጋለሁ እያለ ነው?
ይሄ ያው የተለመደ ማስተባበል ነው፡፡ ይሄን መግለጫ የክልሉ መንግሥት ከሰጠ በኋላ ግን የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ሃላፊ ወ/ሮ ሊያ ካሳ በመገናኛ ብዙሃን ቀርበው ሕዝቡ ተቃውሞ ማቅረቡን አምነዋል፡፡ ህዝቡ ይሄን ማድረጉ ሕገ መንግሥታዊ መብቱ ነው በማለት ሸፈንፈን አድርጎ ለማለፍ መሞከር በሚመስል መልኩ ችግሩን ይፋ አድርገውታል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን አጭበርብሮ ነገሩን ለመሸፋፈን የሚቻል አይሆንም፡፡ ይሄ አይነት ማጭበርበር ደግሞ አዲስ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን እየመሩ በነበረበት ጊዜ ራሱ ሲክዱት የነበረ ሃቅ ነው፡፡ ነገር ግን ወ/ሮ ሊያ ካሳ ሁኔታውን አምነዋል፡፡ ግን ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ነው በሚል ነው ለመሸፋፈን ሙከራ ሲያደርጉ የነበረው፡፡
ከዚህ እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ የእናንተ አመራሮች ላይ ወከባ መፈፀሙን ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው መሆኑን ከራሳቸው የማህበራዊ ሚዲያዎች ተመልክተናል… በእርግጥስ እንዲህ ያሉ ችግሮች ተፈጥረዋል?  በቀጣይስ ፓርቲያችሁ ይሄን ጉዳይ እንዴት ያስተናግደዋል?
እኛ ከ12 ዓመት በፊት ስንመሰረት ሕገ መንግሥቱን አክብረን፣ ለምርጫ ቦርድ መመሪያዎች ተገዥ ሆነን ሰላማዊ ትግል የምናደርግ ነን፡፡ በዚህ ትግል ውስጥ ብንቆይም አባሎቻችን የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር ከፍለዋል፡፡ እየተከፈለ የመጣነው መስዋዕትነት ቀላል አይደለም፡፡ አባላት ተገድለውብናል፣ የታሰሩ አባሎቻችን እንኳ እስከ ዛሬ አልተፈቱም:: ስንመታ፣ ስንገላታ፣ ስንገደል ነው የቆየነው:: አሁን ደግሞ አመጣጣቸው ትንሽ ከረር ያለ ነው፡፡ የሕዝቡ እንቅስቃሴም ከረረ ያለ ነው፡፡ እነሱም ምላሽ ሊሰጡበት ወይም አፈና ሊፈፅሙበት የሚሄዱበት መንገድ ከረር እያለ ነው የመጣው፡፡ አሁን አረናን በሚያንቀሳቅሱ ጠንካራ አመራር ግለሰቦች ላይ ትኩረት ተደርጓል፡፡ ተከራይተው ከሚኖሩበት በካድሬ ኔትዎርካቸው ማስፈራራት በመፈፀም አከራዮች እንዲያስወጧቸው ማድረግ፣ በየመንገዱ ወከባ መፈፀም እየተጠናከረ መጥቷል፡፡ አሁን ከሰሞኑ በሕዝብ ግንኙነት ሃላፊያችን አምዶም ገ/ስላሴ ላይም ተመሳሳይ ድርጊት ተፈጽሟል፡፡ ምንም በማያውቀው ሁኔታ ልጆቹና ባለቤቱን ጨምሮ በምሽት ከተከራየበት ቤት ለማስወጣት ሙከራ ተደርጓል፡፡ ይሄ ሁሉ ቢፈፀምብንም ትግላችንን ወደፊት እንቀጥላለን፡፡ ወደኋላ የሚመልሰን ነገር የለም፡፡ አቋማችን በሰላማዊ ትግል ላይ የፀና ነው፡፡ ይሄ ሁሉ በሆነበት እኛን ከብልፅግና ጋር ይሰራሉ እየተገናኙ ነው ከሚለው ወሬ አልፈው አሁን ላይ ከሻዕቢያ ጋርም ይገናኛሉ ይሰራሉ እያሉ እየወነጀሉን ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ውንጀላዎች ደግሞ ወዴት ሊያመሩ እንደሚችሉ ይገባናል፡፡
አሁን በክልሉ ያሉ የፖለቲካ ውጥረቶች ወዴት ሊያመሩ ይችላሉ? ሴናሪዮ (የቢሆን ግምት) ማስቀመጥ ይቻል ይሆን?
በአሁን ሰዓት ሃላፊነት ያለው ሀይል በየትኛውም ወገን ያስፈልገናል፡፡ እንደምናየው ከውስጥም ሆነ ከተለያዩ የውጭ አቅጣጫዎች የተደቀኑብን አደጋዎች አሉ፡፡ ስለዚህ አገራችን ቀጣይ ሆና እንድትኖር አርቆ አሳቢነት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ በኩል ደግሞ ዋነኛ ተዋናዮች የሚሆኑት ስልጣን ላይ ያሉ ሃይሎች ናቸው፡፡ ነገር ግን በእነሱ መሀል ያለው ግንኙነት ደግሞ በጣም የሚያሰጋ ነው፡፡ ምክንያቱም ትናንት አብረው የነበሩ ናቸው፡፡ አሁን ግን የተለያየ መስመር ላይ ናቸው ያሉት፡፡ ይሄን ልዩነታቸውን ደግሞ አስማምተው እየሄዱ አይደለም፡፡ ስለዚህ የሚያሰጋ ነገር አለ ማለት እንችላለን፡፡ ህወኃት ይሄን አደርጋለሁ ሲል አቅም እንኳ ባይኖረው ትርምስና ግርግር ሊፈጥር ይችላል፡፡ በተለይ የህወኃት አመራሮች በስልጣን በነበሩ ሰዓት ብዙ ጥፋት አጥፍተዋል፡፡ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል፡፡ ስለዚህ ለውጥ ከመጣ ያበቃልናል የሚል ስጋት ስላላቸው ሕዝብን አነሳስተው ወደ ጦርነት ሊገቡ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ፡፡ ነገር ግን የሕዝብ ተቃውሞ እየበረታ ሲሄድ ከህወኃት ጋር የሚሰለፈው ሀይል እየተመናመነ ይሄዳል አሁንም ተመናምኗል የሚል ግምገማ አለን፡፡ ስለዚህ እኔ የሚታየኝ ተስፋ ነው፡፡ የብልፅግና ፓርቲ አንዳንድ ወጣ ያሉ ሕዝብን የሚነካኩ አካሄዶች መታረም አለባቸው:: ጥንቃቄ ሊደረግባቸው ይገባል ቃላቶች ከዚያ ወጥተው ሲመጡ እዚህ ሌላ ትርጉም ተሰጥቷቸው ነው ለሕዝቡ የሚባዙት:: ስለዚህ የቃላትና አመለካከት ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ በመለስ ግን የትግራይ ሕዝብ እንደ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለውጥን ይፈልጋል፡፡ በዚያው ልክ ግን የሕወኃትን አቋም የሚደግፉና የመገንጠልን ሐሳብ የሚያቀነቅኑ ድርጅቶች በትግራይ አሉ:: ተቃዋሚ መስለው የህወኃት ጋሻ ጃግሬ የሆኑ አሉ፡፡
ከዚሁ ጋር አያይዘው በትግራይ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች አሰላለፍ ምን ይመስላል ቢያስረዱን?
አሁን ያለው አሰላለፍ በቅርብ ጊዜ የተፈጠሩትን አጠቃሎ የሚታይ ነው፡፡ ህወኃት በኢትዮጵያ ደረጃ የነበረው የፖለቲካ ፓርቲዎች የተንኮል አካሄድ ነው አሁን በትግራይ እየተተገበረ ያለው፡፡ ህወኃት ከፌዴራል ሲባረር ትግራይ መጥቶ ያደረገው የመጀመሪያ ተግባሩ እሱን በውስጥ የሚደግፉ ተቃዋሚ መሳዮችን ነው ያፈራው፡፡ በሀሳብ የህወኃት ልጆች የሆኑ ፓርቲዎች ነው የፈለፈለው፡፡ ባይቶና፣ ሳልሳዊ ወያኔ፣ እውነት የሚባል አለ ይሄ እንደውም እስከ መገንጠልን አጥብቆ የሚያቀነቅን ነው:: ሁሉም ተደማምረው የህወኃት ደጋፊ ብቻ ሳይሆኑ ህወኃት ራሱ ናቸው፡፡ እንደውም ከህወኃት በላይ ህወኃት እንሁን እያሉ ነው ያሉት፡፡ በአንድ በኩል ይሄ አሰላለፍ ነው ያለው:: ሌላኛው ደግሞ አረና፣ የእነ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ትዴፓ፣ አሲምባ ንቅናቄ፣ ብልፅግና የመሳሰሉት ደግሞ ለውጥ መምጣት አለበት፤ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ተደማምጠን የሚስተካከለው ተስተካክሎ በሰላማዊ መንገድ ለውጥ መምጣት አለበት የሚል ነው፡፡ ይሄ ቡድን መገንጠልን የሚኮንን ፌደራላዊት ኢትዮጵያን የበለጠ ስለማጠናከር የሚያስብ ሀይል ነው:: እንግዲህ በትግራይ ፓርቲዎች አሰላለፋቸው ለውጥ ፈላጊና ከህወኃት ጎን ተሰልፎ ለውጥ አያስፈልግም የሚል ብሎ መመደብ ይቻላል፡፡ እነዚያ የተፈጠሩ የህወኃት አጃቢዎች ሲጀመር ህወኃትን ለማዳን ተብለው የተፈጠሩ ናቸው:: እነዚህ በብዛት ለትግራይ ሕዝብ ተቆርቋሪ መስለው ነው የውሸት የሚዘምሩት በሕዝብ ላይ የሚፈፀምን አፈና ግን መናገር አይፈልጉም:: ስለዚህ ህወኃትን ለማዳን የተደራጁ በአንድ በኩል ህወኃትን ይበቃሃል የሚለው በሌላ በኩል ሆኖ ተሰልፏል ማለት ነው፡፡
በየጎራው የተሰለፉ ሀይሎች ለሕዝቡ ስጋት የሆኑ የፖለቲካ ችግሮችን ሊፈጥሩ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ ይሄ ስጋት እንዴት ነው ሊቀየር የሚችለው ምን ቢደረግ የተሻለ ይሆናል?
እንደኛ ሀሳብ ከሆነ ህወኃትና የትግራይ ሕዝብ የተራራቀ ነው፡፡ አንድ አይደለም የሚል በሚገባ መታወቅ አለበት፡፡ ህወኃት ደግሞ ሆን ብለው ሕዝቡን መሸሸጊያ፣ ጥፋታቸው መሸፈኛ ለማድረግ እኛና ሕዝቡ አንድ ነን ሲሉ ሲዘምሩ ነበር፡፡ ይሄ አሁንም ድረስ በጣም አደገኛ ነው፡፡ ሕዝቡ ደግሞ ፈፅሞ ጦርነት አይፈልግም ከምንም በላይ ጦርነትን ያውቀዋል፡፡ አሁን ሰላም ነው የሚፈልገው እኛም እንደ ድርጅት ነገሮች በሰላም ነው መቋጨት ያለባቸው እንጂ ጦርነት አያስፈልግም የሚል አቋም አለን፡፡ ጦርነትም እንደ ከዚህ ቀደሙ አማራጭ መሆን የሚችልበት እድል የለም፡፡ ለጥቂቶች ተብሎ ወደ ጦርነት አይገባም፡፡ አሁንም እኛ ነገሩን የምናየው በዚህ መልኩ ነው፡፡ ሕዝቡ ፈፅሞ ጦርነቱን አይፈልገውም ጦርነት የሚያስገባ ምክንያት እንደ ሌለ ጠንቅቆ ይረዳል፡፡ ከፕሮፖጋንዳ በፀዳ መልኩ በፌደራል መንግሥቱ ያሉ ለውጦችን ህዝቡ በአስተውሎት ይረዳል፡፡ ለጥቂቶች ምቾት ብሎ በጦርነት የሚማገድ የትግራይ ወጣት አይኖርም፡፡ ሕዝቡ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር ያለውን እኩል በመራራ ትግል አስቀድሞ አረጋግጧል፡፡ ይሄን መብቱን ወደኋላ የሚመልስ ሀይልም ፈፅሞ የለም፡፡ ያንን ማድረግ የሚቻልበት እድልም አሁን የለም:: ነገሮች በሰላም ማለቅ እንዳለባቸው ነው እኛ የምናስበው፡፡
እንዴት ነው ነገሮች በሰላም ሊቋጩ የሚችሉት መፍትሄ ሊገኝ የሚችለው እንዴት ነው?
የመጨረሻ መፍትሄ እንኳ ባይገኝ እንኳ የሁሉም ነገር መፍትሄ መወያየት ነው፡፡ ከዚያ ውጪ በጉልበት የሚደረግ ነገር መዘዝ አለው:: በቀላሉ የሚያልቅም አይሆንም:: ትልቁ አማራጭ መወያየት ከእልህ መለስ ብሎ መነጋገር ነው፡፡ የፌደራል መንግሥት ጥሩ ነገር ላይ ነው፡፡ ይሄ ቀጥሎ ይሄም ችግር በዚህ መልኩ የሚፈታበት የሰከነ መንገድ ነው መፈለግ ያለበት:: ሕዝብ ተሳትፎው በበዛ ቁጥር ጽንፈኞች ቦታ አይኖራቸውም፡፡ ስለዚህ በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሆደ ሰፊ ሆኖ ነገሮችን በእርጋታ እያየ መወያየትን እያስቀደመ ችግሩን ለመፍታት ጥረት መደረግ አለበት፡፡ ነገሩ ሲታሰብ አድካሚ ይሆናል ነገር ግን ውጤቱ መልካም ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን እነዚህ ጥቂት ሀይሎች ሕዝቡ ውስጥ ሆነው የሚዘምሩት ጦርነት እነሱንና ልጆቻቸውን አይነካም፡፡ ልጆቻቸው ውጭ አገር ነው ያሉት፡፡ ሕዝብን ነው ወደ ጦርነት የሚማግዱት፡፡ ስለዚህ ውይይትን ማስቀደም ለሁሉም ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ሕግ አላግባብ ሲጣስ ግን የፌደራል መንግሥት ሕጉ በሚፈቅድበት አግባብ ነገሮችን ማስተካከል አለበት፡፡ ከዚህ በመለስ የድሃ ልጅ በማስፈጀት እየተዘጋጁበት ባለው ጦርነት መፍትሄው ውይይት ነው መሆን ያለበት፡፡ የፌደራል መንግሥት ሆደ ሰፊ ሆኖ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ተቀራርቦ ነገሩን በእርጋታ ማካሄድ አለበት፡፡


Read 2352 times