Sunday, 24 May 2020 00:00

እንዲህም አለ፤ እንዲያም አለ ኮቪድ-19 እና ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣቶች

Written by 
Rate this item
(0 votes)


   *ፓርቲ ደግሶ የተገኘ ከ100ሺ ብር በላይ ይቀጣል
   *የፊት ጭምብል ያላደረገ 80ሺ ብር ይቆነደዳል
   *ርቀትን አለመጠበቅ በ30ሺ ብር ያስቀጣል  

 በአገራችን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚያስደነግጥ ሁኔታ እያሻቀበ መምጣቱን እየሰማን ነው፡፡ በአንጻሩ የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት በሚወሰዱ የጥንቃቄ እርምጃዎች ላይ ከፍተኛ መዘናጋት እየተስተዋለ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ሃላፊዎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ እየተናገሩ ነው - ልመናን ጭምር በሉት፡፡ ለራሳችንና ለቤተሰቦቻችን ህይወትና ደህንነት እንዴት እንለመናለን? በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ፣ በጣሊያን በስፔን፣ በብራዚል ወዘተ -- በኮቪድ 19 እየረገፈ ያለውን የህዝብ ብዛት እየሰማን አለመደንገጥና በቸልታ አዙሪት ውስጥ መግባት የጤና አይመስልም፡፡ እንግዲህ ዋናዎቹ የጥንቃቄ እርምጃዎች የሚባሉት እጅን በውሃና ሳሙና መታጠብ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ ሰዎች በሚበዙባቸው ሥፍራዎች አለመገኘት፣ የፊት ጭምብል ማድረግና የግድ ካልሆነ ከቤት አለመውጣት የሚሉ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሁሉም ይልቅ የተሻለ ተፈጻሚ የሆነው የፊት ጭምብል ማድረግ ነው - ብለዋል የጤና ባለሙያዎች፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ባለፉት ሳምንታት ፖሊስ አስቸኳይ አዋጁን ለማስፈጸም ማስክ ባላደረጉ ሰዎች ላይ የወሰደው እርምጃ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ማስክ ሳያደርጉ በህዝብ ትራንስፖርት ላይ መሳፈር አለመፈቀዱም ሌላው ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
 የሚያሳዝነው ግን መጀመርያ ገደማ ላይ እንደ ፋሽን ተይዞ ጥቂት የዘለቀው እጅን የመታጠብ ልማድ እየቀረ  መምጣቱ ነው ይላሉ፤ታዛቢዎች፡፡ ይሄ የሆነው ደግሞ የቫይረሱ ስርጭት እያሻቀበ በመጣበት ወቅት ላይ መሆኑ ችግሩን ያወሳስበዋል፡፡ እጃችንንም ለመታጠብ የፖሊስ ቁጥጥርና ቅጣት ያስፈልገናል ማለት ነው?  በአንዳንድ ግለሰቦች የሚፈጸሙ ሃላፊነት የጎደላቸው እንቅስቃሴዎች በብዙሃኑ ላይ የድንጋጤና ተስፋ መቁረጥ ስሜት ይፈጥራሉ፡፡ ቫይረሱ በአገራችን ላይ የሚያደርሰውን የአደጋ መጠን ልንቀንስ የምንችለው በግል በምናደርገው ጥንቃቄ ብቻ አይደለም፤የሁላችንንም ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ ና፡፡ የምንሞተውም የምንተርፈውም በአንድ ላይ ነው፡፡ ለዚህ ነው በዓለም ዙሪያ የሚገኙ  መንግስታት ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደቦችን በመጣልና ጥሰት በሚፈጽሙ ላይ ቅጣቶችን በመበየን የተጠመዱት፡፡ የጥቂት ግለሰቦች ሃላፊነት የጎደለው እንቅስቃሴ የቤተሰቦችን ብሎም የማህበረሰብን ደህንነት ለአደጋ ያጋልጣል፡፡ ከዚህ አንጻር መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማስፈጸም ረገድ ጠበቅ ማለት ሳይኖርበት አይቀርም፡፡ ለማንኛውም ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ ከሰሞኑ አዳዲስ ገደቦችንና ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣቶች የጣለችውን የባህረ ሰላጤዋን አገር በጨረፍታ ላስቃኛችሁ፡፡ ቢያንስ ለጠቅላላ ዕውቀት፡፡
 
የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ፣ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የጣላቸውን ገደቦች፣ የዛሬ ወር ገደማ በጥቂቱ ማላላት ጀምሮ ነበር፡፡ ነገር ግን በቅርቡ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን  ተከትሎ፣ አዳዲስ የተጠናከሩ ገደቦችንና እርምጃዎችን መተግበር የጀመረ ሲሆን ጥሰት በሚፈጽሙ ግለሰቦችም ላይ የኢኮኖሚ አቅምን የሚፈታተኑ  የገንዘብ ቅጣቶች የሚጥል አዲስ መመሪያ ደንግጓል፡፡
   
በአዲሱ መመሪያ መሰረት፤ በአገሪቱ ፓርቲ ደግሰው የተገኙ ግለሰቦች 10 ሺ ድርሃምስ (ከ100ሺ ብር በላይ) የገንዘብ ቅጣት የሚጣልባቸው ሲሆን የፓርቲው ታዳሚዎች ደግሞ በነፍስ ወከፍ 5 ሺ ድርሃምስ (50ሺ ብር ገደማ) እንዲከፍሉ ይገደዳሉ፡፡ አስገዳጅ የመዝጋት ወይም የተገደበ የሥራ ሰዓት ደንቦችን የሚጥሱ የቢዝነስ ተቋማት በበኩላቸው፤50 ሺ ድርሃም (ከ500 ሺ ብር በላይ) የገንዘብ ቅጣት ይጣልባቸዋል ተብሏል፡፡ የቤትና የጤና ተቋም የኳራንታይን ትዕዛዞችን የሚጥሱ ግለሰቦችም በተመሳሳይ ከ500ሺ ብር በላይ ይቀጣሉ፡፡ አካላዊ ርቀታቸውን የማይጠብቁስ? 30 ሺ ብር ገደማ ይከፍላሉ፡፡ ተደጋጋሚ ጥሰቶችን የፈጸሙ ደግሞ የ100 ሺ ድርሃም ቅጣትና የ6 ወር እስራት ይጠብቃቸዋል፡፡  
  የተባበሩት አረብ ኢምሬት ባለሥልጣናት እንደገለጹት፤ እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ  አንዳንድ ግለሰቦች በሚያደርጉት ሃላፊነት የጎደለው እንቅስቃሴ ሳቢያ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመር በማሳየቱ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ 24,190 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 224 ግለሰቦች በቫይረሱ ሳቢያ ለሞት ተዳርገዋል ተብሏል -እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ  መረጃ፡፡

‹‹የመፀዳጃ ቤት ወረቀት አለቀብን ብላችሁ እንዳትደውሉ››

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ፣ በዓለም ዙሪያ ብዙዎች ለክፉ ቀን እያሉ የተለያዩ ሸቀጦችን በገፍ እየሸመቱ በየቤታቸው ሲያከማቹ እንደነበረ የሚታወቅ ሲሆን በዚህም የተነሳ የሱፐርማርኬት መደርደርያዎች ኦናቸውን ቀርተው ነበር፡፡ በተለይም ራስን ከወረርሽኙ ለመከላከል የሚጠቅሙ የሳኒታይዘርና የማስክ እጥረት መከሰቱ  አይዘነጋም፡፡ ለብዙዎች አግራሞትን የፈጠረው ግን የመፀዳጃ ቤት ወረቀት እጥረት በከፍተኛ ደረጃ መከሰቱ ነው፡፡ በተለይ አሜሪካውያን የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ፣ ከሌሎች ሸቀጦች በተለየ የመፀዳጃ ቤት ወረቀት በብዛት ነበር የሚገዙት፡፡ ምክንያቱ በትክክል ባይታወቅም፡፡ (በነገራችን ላይ ወረርሽኙ ተባብሶ ምናልባት ሥርዓት አልበኝነት ቢፈጠር በሚል፣ የሽጉጥና የጠብመንጃ ሽያጩም ደርቶ ነበር)
ከኮቪድ-19 መከሰት ጋር ተያይዞ የተስተዋለውን የመጸዳጃ ቤት ወረቀት ከፍተኛ ፍላጎት የተገነዘበው በአሜሪካ የኦሪገን ፖሊስ መምሪያ፣ ባለፈው መጋቢት ወር መባቻ ላይ በፌስቡክ ያሰፈረው መልዕክት ፈገግታን የሚያጭር ነው፡፡ (ለፖሊስ መምሪያው ጭንቀት የወለደው ቢሆንም)
በኦሪገን የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉን ተከትሎ፣ ፖሊስ ለነዋሪዎች ያስተላለፈው መልዕክት እንዲህ ይላል፡-‹‹የመፀዳጃ ቤት ወረቀት አለቀብን ብላችሁ ብቻ 9-1-1 እንዳትደውሉ፡፡ ችግሩን ያለ እኛ እርዳታ ልትወጡት ትችላላችሁ፡፡››
 ፖሊስ ይህን መሰሉን መልዕክት በፌስቡክ ላይ ማስፈሩ ምቾት እንዳልሰጠውም ሳይገልጽ አላለፈም፤ግን ሌላ ምርጫ አልነበረኝም ባይ ነው፡፡
 በመጨረሻም ‹‹ይህም ያልፋል›› ሲል ለነዋሪዎች የመጽናኛ ቃል ያስተላለፈው የኦሪገን ፖሊስ መምሪያ፤ ‹‹አደራ የመጸዳጃ ቤት ወረቀት አልቆብናል ብላችሁ እንዳትደውሉ፤ እኛ ልናመጣላችሁ አንችልም፡፡›› በማለት እቅጯን ተናግሯል፡፡


Read 1631 times