Tuesday, 26 May 2020 00:00

ወረርሽኝን ከመከላከልና ከመቆጣጠር፤ ወደ “መቋቋም” እንደርሳለን?

Written by  ዮሃንስ. ሰ
Rate this item
(1 Vote)

- “ወረርሽኝን በመከላከል” ብቻ፣ ከኮሮና ቫይረስ ነፃ የምንወጣ ከመሰለን፣ የቫይረሱንና የበሽታውን አደገኛነት ገና በቅጡ አልተገነዘብነውም ማለት ነው፡፡
    - ስራንና ኑሮን በግማሽ በሩብ መቀነስ፣ ጊዜያዊ የወረርሽኝ መከላከያ ዘዴ እንጂ፣ ቫይረሱን የሚያጠፋ ወይም ለሳምንታት የሚቀጥል መፍትሔ አይደለም፡፡
    - “ቫይረሱን ማጥፋትና በሽታውን ማስወገድ ይቻላል ወይ?” የሚለውን ጥያቄ መጋፈጥ የግድ ነው፡፡ ፍቱን ክትባት ወይም መድሃኒት ገና አልተገኘም፡፡               ስለዚህ…
    - “በሽታውን ተቋቁመን፤ ኢኮኖሚንና ኑሮን ማሻሻል” እንዴት እንደምንችል ማሰብ ይኖርብናል - ወረርሽኙን ከመከላከልና ከመቆጣጠር በተጨማሪ፡፡
       
           ወረርሽኙን በስኬት መከላከል ማለት፣ ‹‹ማሸነፍ››ና ቫይረሱን ማጥፋት ማለት አይደለም፡፡ ደቡብ ኮሪያ፣ ዋናዋ የስኬት ምሳሌ ናት፤ ቫይረሱ ግን አልጠፋም፡፡ ከሁለት ሳምንት እፎይታ በኋላ፤ ደቡብ ኮሪያ እንደገና የቫይረስ ስርጭት አጋጥሟታል፡፡ በአንድ ጊዜ፣ ከአንድ ቦታ፣ ቫይረሱ ወደ መቶ ሰዎች የተዛመበት ፍጥነት አስደንጋጭ ነው፡፡ ደግነቱ፣ በፈጣን የምርመራና የቁጥጥር አሰራር አማካኝነት፣ የቫይረሱን ስርጭት ለመገደብ ችለዋል - የደቡብ ኮሪያ የጤና ባለሙያዎች፡፡
ድንገተኛውን ወረርሽኝ በመከላከል፤ ከደራሽ የጥፋት ጎርፍ ለማምለጥ የቻሉ አገራት፣ “እድለኛ” ወይም ስኬታማ ናቸው፡፡ ቫይረሱን ያሸነፉ ከመሰላቸው ግን፣ የሚያስቆጭ ስህተትና ጥፋት ላይ ይወድቃሉ፡፡ ታዲያ፤ “ወረርሽኝን መከላከል” ምን ፋይዳ አለው?
የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር፣ ደህና አቅም ለመገንባትና ጥንቁቅ አሰራር ለማጠናከር፣ በቂ የዝግጅት ጊዜ የምናገኘው፣ ወረርሽኝን በመከላከል ነው፡፡ ቢሆንም ግን፣ ቫይረሱ አይጠፋም፡፡ እዚህና እዚያ፣ እያሰለሰና እየሰነበተ፣ በየቦታውና በየጊዜው የቫይረስ ስርጭት ማገርሸቱና መበራከቱ አይቀሬ ነው፡፡
የቫይረስ ስርጭት ሲያገረሽ፤ ቶሎ ቶሎ እየተከታተሉ፤ እየመረመሩና እያወቁ፤ ስርጭቱን መገደብ ነው “ወረርሽኝን መቆጣጠር” ማለት:: ግን፣ ወረርሽኝን መከላከልና መቆጣጠርስ እስከ መቼ? እዚህ ላይ፣ ‹‹የስዊድን መንገድ›› እና ‹‹የክትባት ተስፋ›› ዋናዎቹ ርዕሶች ይሆናሉ፡፡
“ስራንና ኑሮን መቀነስ” እስከ መቼ?
ጥያቄው፤‹‹አደገኛውን ኮሮና ቫይረስ ማጥፋት ወይም በሽታውን ማስወገድ ይቻላል ወይ?›› የሚል ነው፡፡ እስካሁን፣ ከተስፋ በስተቀር፣ ከቫይረሱና ከወረርሽኙ ነፃ የሚያወጣ አንዳች የተጨበጠ ዘዴ አልተገኘም፡፡ አይገኝም ማለት ግን አይደለም፡፡ ፍቱንና ቀላል የህክምና ዘዴ ከተፈጠረ፤ ወይም ደግሞ፣ አስተማማኝ መከላከያ ክትባት ከተሰራ፣ ቫይረሱንና በሽታውን አሸንፎ ማስወገድ ይቻላል፡፡ እስከዚያ ድረስስ?
ክትባት እስከሚገኝ ድረስ፤ አመት ሙሉና ከዚያ በላይ፣ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ይቀጥላሉ? ፍርድ ቤቶችን ዘግቶስ እስከ መቼ መዝለቅ ይቻላል? የገሚሱ ዜጋ የእለት ሥራ ተስተጓጉሎ፣ መተዳደሪያ ገቢም ተቋርጦ፣ የገሚሱ ዜጋ ኑሮ በግማሽና በሩብ ጨልሞ፣ ለምን ያህል ጊዜ መቆየት ይቻላል?
እንደኢትዮጵያ የመሳሰሉ ደሀ አገራት ቀርተው፤ ወደ ብልፅግና የገሰገሱት አገራትም ክፉኛ ተቸግረዋል፡፡ እነ አውሮፓ እንኳ፤ ‹‹ስራን እና ኑሮን በመቀነስ›› ከአንድ ከሁለት ወር በላይ፣ በሰላም በደህና መሻገር እንደማይችሉ ታይቷል። በ80 ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የስራ አጥነትና የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡
በስራ አጥነትና በኢኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ ቅሬታና ምሬት እየተበራከተ፤ ነባር የፖለቲካ ችግሮች ይባባሳሉ፡፡ የተመሳቀለ ኢኮኖሚና የታወከ ፖለቲካ፤ ብዙዎቹን አገራት እንደሚያናጋና እንደሚያቃውስ አትጠራጠሩ፡፡ ቀውሱ፣ ለበርካታ ዓመታት የማይሽር ተጨማሪ በሽታ ይሆንባቸዋል፡፡
 “ተሟሙቶ፣ ገደል ገብቶ፣ አገርን ዘግቶ ወረርሽኝን መከላከል” በሚል ጭፍን ስሜት መነዳት፣ ለጊዜው ካልሆነ በቀር ከቫይረሱ ነፃ አያወጣንም፤ ኢኮኖሚን እየናደ ተጨማሪ የኑሮ በሽታ ይሆንብናል፡፡
ከዚህ ይልቅ፤ ከአገር አቅምና ከመተዳደሪያ ሥራ ጋር የተገናዘበ፤ የዛሬ ተግባርን ከዘላቂ የአላማ ስኬት ጋርና ከሚያስከትለው መዘዝ ጋር ያመዛዘነ የጥበብ መንገድ ያስፈልጋል፡፡
“ኑሮን በሥራ የመጠገን ጉዳይ”፣ በእንጥልጥል ሊከርም አይችልም፡፡
የቫይረሱ ስርጭት ያለ ተመልካች እንደ ጉድ እንዳይዛመትና አገሬውን በበሽታ ጎርፍ እንዳያጥለቀልቅ፤… ጊዜያዊ የመከላከያ ውሳኔዎችና ተግባራት ያስፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን ወረርሽኝን የመከላከል ምዕራፍ፣ በስኬት፣ ደረጃ በደረጃና በተቻለ ፍጥነት ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ መራመድ ካልቻለ፣ ነገሩ ሁሉ ከንቱ ሆኖ ይቀራል፡፡ ከቫይረሱ ለማምለጥ መንፈቅና ዓመት ቤት ዘግቶ መቀመጥ ይቅርና፤ ስራን በሩብ ቀንሶ በሰላም መክረምም አይቻልም፡፡
የቫይረሱን ስርጭት ከመከላከል በተጨማሪ፣ በየጊዜው የሚያገረሹ ስርጭቶችን ለመቀነስ የሚያስችል የወረርሽኝ መቆጣጠሪያ ዘዴ መፍጠር ይኖርብናል፡፡ ዜጐች ኑሮን ወደሚጠግን ስራቸው ይበልጥ የሚያተኩሩበት እድል መክፈት ይገባናል፡፡
ይሄ ወረርሽኝን የመቆጣጠርና ኢኮኖሚን የመጠገን ምዕራፍ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው፤ በጥንቃቄ ስራውን ለማነቃቃት፣ ኑሮውንም በትጋት ለማቃናት እንዲጥር፣ በአጠቃላይ የአገሬው ኢኮኖሚ እንዲያገግም የሚረዱ አመቺ ዘዴዎች ከተፈጠሩ፤ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ ተሸጋግረናል ማለት ነው፡፡
በቀዳሚው “የወረርሽኝ መከላከያ ምዕራፍ” ላይ ስኬታማ የሆኑ እንደ ደቡብ ኮሪያ የመሳሰሉ አገራት፣ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ ተሸጋግረዋል - “የወረርሽኝ መቆጣጠሪያና የኢኮኖሚ ማገገሚያ ምዕራፍ” እንዲሉ፡፡ ወረርሽኙን ከመከላከል በተጨማሪ የስርጭት ፍጥነቱን ወደ መቆጣጠር መሸጋገር ያልቻሉ አገራት ግን፤ “ኢኮኖሚንና ኑሮን የሚጠግን አላማ” ላይ ለማተኮር ቅንጣት እድል አያገኙም፡፡
ወረርሽኝን መቆጣጠር ስንችልና፤ እያንዳንዱ ዜጋ የመተዳደሪያ ስራውን እንደገና እያነቃቃ ኑሮውን ለማቃናት ሲተጋ ነው፤ ኢኮኖሚው የሚያገግመው፡፡ ይሄን ቸል ማለትና “ወረርሽኝን የመከላከል ዘመቻ” ላይ ብቻ ተጠምዶ መቅረት፤ መዘዙ ብዙ ነው፡፡  “ለሀብታም አገራትም” እንኳ ይከብዳል፡፡ “የስራና የኑሮ ጉዳይ”፣ እንዲሁ በእንጥልጥል ለሳምንታት “በእግድ” እና “በቀጠሮ” ሊከርም የሚችል ጉዳይ አይደለም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ አገራት ደግሞ፤ “ለስራ የመትጋትና ኑሮን የመጠገን ጉዳይ”፣ በይደር ሊሰነብት አይችልም፡፡
የክትባት ተስፋና ወረርሸኝን ጉዳት የመቋቋም ፈተና፡፡
የመጀመሪያው ምዕራፍ፤ “ኢኮኖሚን የማይንድ፣ ከወረርሽኝ የሚያድን”፣ አፋጣኝ የመከላከያ መፍትሔና ዘመቻ የገነነበት፣ ቀዳሚ “የዝግጅት ምዕራፍ” ነው፡፡ ነገር ግን፣ “መከላከል” ብቻ በቂ አይደለም፡፡  
ሁለተኛው ምዕራፍ፤ “ኢኮኖሚን የሚጠግን፣ ወረርሽኝን የሚቆጣጠር”፣ ጥንቁቅ አሰራር የሚጠናከርበት የመሸጋገሪያ ምዕራፍ ነው፡፡
ነገር ግን፣ “መከላከል” ና “መቆጣጠር” ም በቂ አይደሉም፡፡ ክትባት ተሰርቶ ለአገር ካልተዳረሰ በቀር፤ የቫይረሱ ስርጭትና የወረርሽኙ አደጋ፣ በሳምንትና በወር ብን ብሎ አይጠፋልንም::  አንደኛ ነገር፣ “በወረርሽኝ መከላከያና መቆጣጠሪያ” መንገዶች አማካኝነት የቫይረሱን ስርጭት መቀነስና ማዘግየት እንጂ፤ ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት አይቻልም፡፡ ሁለተኛ ነገር፣ አንዳንዶቹ የወረርሽኝ መከላከያና መቆጣጠሪያ ዘዴዎች፤ ለተወሰነ ጊዜ በተወሰነ መጠን ብቻ የሚያገለግሉ ናቸው፡፡
የኑሮና የስራ እንቅስቃሴን በግማሽም ሆነ በሩብ ማገድ የሚቻለው፣ ከጥቂት ቀናት ብቻ ነው፡፡ “ለይቶ የማቆየት ዘዴም” የራሱ ልክ አለው፡፡
አንድ ሺ፣ ከዚያም በላይ 10ሺ፣ 20ሺ…ሰዎችን “ኳረንቲን” ማድረግ ይቻላል - ለተወሰነ ጊዜ፡፡ ነገር ግን፤ በቫይረሱ ከተያዙ ሁለት መቶ ሰዎች ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሰዎችን በሙሉ አፈላልጐ ወደ ማቆያ ተቋም ማስገባት ቀላል አይሆንም፡፡ …በመኖሪያ መንደር፣ በስራ ቦታ፣ በመገበያያ ስፍራ፣ እያንዳንዱ ሰው ከመቶ ሰዎች ጋር ሊቀራረብና ሊነካካ ይችላል፡፡ ይሄን ሁሉ ማጣራትና 20ሺ ሰዎችን በአንዴ ወደ ኳረንቲን ማስገባት አይቻልም፡፡ ከተቻለም፣ ከጥቅሙ ጉዳቱ እየበዛ መሄዱ አይቀርም - በቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ሲበረክት፡፡
ስለዚህ፣ ወረርሽኝን ከመከላከል፣ እንዲሁም ከመቆጣጠር ባሻገር፤ ወረርሽኝን ተቋቁሞ ወደ ማሸነፍ የሚያደርስ ሦስተኛ ምዕራፍ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ እጅግ ወሳኝ ብቻ ሳይሆን፣ እጅግ ከባድ ምዕራፍ ነው፡፡ በአንድ ጐን፣ በበርካታ አገራት ክትባት ለመስራት የሚካሄዱ ጥናቶችና ሙከራዎችን በተስፋ መጠበቅ፤ በሌላ ጐን ደግሞ፤ “የስዊድን መንገድ” ተብሎ የሚታወቀው ዘዴ፣…በየእለቱ የምንሰማቸው የሦስተኛው ምዕራፍ ተጠቃሽ ገጽታዎች ናቸው::
ደቡብ ኮሪያ፣ “ወረርሽኝን የመከላከል ምዕራፍ” ላይ በምሳሌነት የምትወደስ አገር የመሆኗ ያህል፤ ስዊድን ደግሞ፤ “ወረርሽኝን የመቋቋም ምዕራፍ” ላይ ያተኮረች ዋና ተጠቃሽ አገር ሆናለች፡፡ በስኬትም ሆነ በአርአያነት የሚጠቀሱ አገራትን ማግኘት፣ መታደል ነው፡፡ በጭፍን ለመኮረጅ ሳይሆን አስተውሎ ለመማር ያገለግላሉ፡፡
ሳምንትንና ወርን ከማየት ባሻገር፣  መንፈቅንና አመትን መቃኘት፤ ወረርሽኝን ከመከላከልና ከመቆጣጠር በተጨማሪም አደገኛነቱንና ከባድነቱንም ተቋቁመን እንዴት በሽታውን ወደማሸነፍ፣ ኢኮኖሚን ወደማሳደግና ኑሮን ወደማሻሻል መሸጋገር እንደምንችል ማሰብ የግድ ነው፡፡Read 7280 times