Tuesday, 26 May 2020 00:00

ኢ/ር ይልቃልና የሽግግር መንግስት ሀሳባቸው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምፈልገውን መስፈርት አላሟሉም ብሎ ከሰሞኑ ከሰረዛቸው 27 የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ የኢትዮጵያውያን አገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) ነው፡፡ ኢሃን አባል በሆነበት አብሮነት በኩል የሽግግር መንግሥት ጥያቄን ሲያነሳ መቆየቱም ይታወቃል:: በፓርቲው የመሰረዝ ጉዳይ፣ በሚያነሳው የሽግግር መንግሥት ጥያቄና ተያያዥ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የንቅናቄው ሊቀመንበር የሆኑት ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል፡፡

          ፓርቲያችሁ ምርጫ ቦርድ የጠየቃቸውን መስፈርቶች ባለሟሟላቱ መሰረቁ ተገልጿል፡፡ ምን ተፈጥሮ ነው?
አልተሰረዘም! ውሳኔው ፖለቲካዊ ነው:: “ኢሃንን” ለማጥፋት ታስቦ የተደረገ ነው:: በተለይ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳው ትክክል አለመሆኑን አስመልክተን፣ የፓርቲዎች ድጋሚ ምዝገባ ማከናወን ላይ አዳጋች ሁኔታዎች አሉ፤ ይሄን የጊዜ ሰሌዳ ድጋሚ ያስብበት” ብለን ለቦርዱ ደብዳቤ አስገብተን ነበር፡፡ ለዚያ ደብዳቤ ምንም መልስ ሳይሰጠን ቆየ፡፡ በዚህ መሃል እኛ ያልነው ትክክል ሆነና ምርጫው ተራዘመ፤ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ገባን፤ በወረርሽኝ ምክንያትም እንቅስቃሴ ተገታ፡፡ በዚህ መሃል እኛ (ፓርቲያችን) ያለብን ጉድለት አልተነገረንም፡፡ ይሄን አሟሉ የሚል ደብዳቤም አልደረሰንም፡፡ ሌላው ቀርቶ “ህልውናችሁን አጥፍተናል” ስንባልም በደብዳቤ አልተነገረንም:: እንደ ማንኛውም ሰው ባለፈው አርብ ማታ ከማህበራዊ ሚዲያ ላይ ነው መረጃ ያገኘነው:: በአጭሩ የተፈጸመው በሕግም በሞራልም ተቀባይነት የሌለው ነገር ነው፡፡
የመስራች አባላት ዝርዝር ማቅረብ ባለመቻላችሁ ነው መሰረዙ የተገለፀው፡፡ ምንድን ነው የቸገራችሁ?
10 ሺህ ፊርማ ለማሟላት ጊዜ ይጠይቃል፤ ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ አባላት በጥንቃቄ ነው መመልመል ያለባቸው፡፡ አሁን ያለንበት ጊዜ ደግሞ ይሄን ለመፈፀም አመቺ አይደለም። የምርጫ የጊዜ ሰሌዳውም ምርጫ ማካሄድ የማይቻልበት ሁኔታ በመፈጠሩ ነው የተሰረዘው:: በዚህ ሁኔታ 10 ሺህ ፊርማ ለማሰባሰብ ጊዜ መስጠት ሲገባ “ህልውናን ሰርዣለሁ” ማለት ምን አመጣው? ቦርዱ፤ አመራሩን ያልመረጠው “ብልፅግና ፓርቲ” እያለ፣ እንዴት በኛ ህልውና ላይ ውሳኔ ለመስጠት ተጣደፈ? ብልፅግና መቼ ነው ጠቅላላ ጉባዔ ያደረገው? አመራሩንስ መቼ ነው የመረጠው? ለምን እሱን አይጠይቁትም? ጉዳዩ የእውነት ሕግ ማስከበር ከሆነ፣ ለምን ስልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ አይጠይቁትም? ትልቁ መነሻ የተሰረዝንበት ዋና ምክንያት ግን ለምን የሽግግር መንግሥት ጥያቄ አነሳችሁ በሚል ነው፡፡ የኛ መሰረዝ ከጥንካሬያችን የመነጨ እንጂ ደካማ በመሆናችን አይደለም፡፡
አሁን ምን አሰባችሁ? ህልውናችሁን አጥታችኋል?
ህልውናችንን አላጣንም አልኩህ፡፡ ለኛ የደረሰን ነገር የለም። በደብዳቤ አልተገለፀልንም:: እኛ መሰረዛችንን አናውቅም፡፡ ሰርተፊኬቱም ማህተማችንም በእጃችን አለ፡፡ በደብዳቤ ማሳወቅ አለባቸው፤ ያንን አላደረጉም፡፡ ስለዚህ እኛ ህልውና አላጣንም፡፡
በፖለቲካ እንቅስቃሴያችን እንቀጥላለን እያሉኝ ነው?
አዎ! እንቀጥላለን፡፡ “ኢሃን” አባል የሆነበት “አብሮነት” ተመስርቷል፡፡ “አብሮነት”ን የፈጠርነው እኮ በጋራ ለምርጫ ለመቅረብና የፖለቲካ ተግባሮችን ለማከናወን ነው፡፡ የኮሮና ጉዳይ ካለቀና በእርግጥም ምርጫ ቦርድ ከኛ የሚፈልገው ካለ፣ አባሎቻችን ተመካክረው አሟልተን እንቀጥል ሊሉ ይችላሉ፡፡ ከአባላት ጋር እንወያይበታለን፡፡ ተወያይተን እንቀጥላለን:: ምርጫ ቦርድ ሰርተፊኬት ሰርዣለሁ የምናቆመው ትግል አይኖርም፡፡ ይሄ የበለጠ እንድንታገላቸው ያደርጋል እንጂ ከትግል አያስወጣንም፡፡
“ጥንካሬ ስላለን ነው እኛን ለማስወገድ ጥረት የሚደረገው” ብለዋል፡፡ ጥንካሬያችሁ ምን ላይ ነው? የትኛው የጎላ እንቅስቃሴያችሁ ነው ጠንካራ የሚያሰኛችሁ?
በአሁኑ ወቅት የኛ ሀሳብ በኢትዮጵያ ውስጥ የበለጠ ተደማጭ ሆኗል፡፡ እኛ ሀሳባችንን በሰነድ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ነው እያቀረብን ያለነው። ስለዚህ ኢትዮጵያውያን በሙሉ የኛን ሀሳብ መስማት ይፈልጋሉ፡፡ በምርጫ ወረዳ ደረጃ ካስፈለገም ጎጃም ውስጥ እንኳ ተንቀሳቅሼ ሳነጋግር፣ ለሕዝቡ አዳራሽ አልበቃ ብሎት በስታዲየም እየተሰበሰበ ነበር ሲያዳምጠኝ የነበረው፡፡ ደብረ ማርቆስና ባህር ዳርን ጨምሮ ሌሎች ወረዳዎችም ላይ በተመሳሳይ መንገድ ነበር ከሕዝብ ጋር ስወያይ የነበረው። በዚህ ደረጃ ካየነው በሚዲያ ላይ ካለን ተፅዕኖ፣ መንግሥት በኛ ሀሳብ ተረብሾ በሚወስደው አቋም፣ የኢትዮጵያን ችግሮችና መፍትሄውን በሰነድም ዘርዝሮ በማስቀመጥ… ወዘተ እኛ ለዚህ በሚሆን የአመራር ብቃት ላይ ነን፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በ “አብሮነት”  ደረጃ የኢትዮጵያን የፖለቲካ መድረክ የተቆጣጠረ ሀይል የለም:: እውነቱን ለመናገር የሚወዳደርው የለም፡፡ በሀሳብ ከአብሮነት ጋር ተወዳዳሪ ሆኖ የሚቀርብ የለም፡፡ እንኳንስ በጥንካሬ ሊወዳደሩን ይቅርና አጠገባችንም የሚቆሙ አይመስለኝም፡፡
ሌሎቹ ሀሳብ የላቸውም እያሉ ነው?
ሀሳብም የላቸውም፤ ያላቸውንም በምክንያት በማስረዳት የሕዝቡንም ሆነ የሚዲያውን ቀልብ መግዛት የቻለ እንደኛ የለም። አሁን በአገሪቱ ገዥ ሆኖ ተፅዕኖ እየፈጠረ ያለው የኛ ሀሳብ ነው፡፡ የገዥው ፓርቲም ቢሆን አሁን እየሟሟ ነው፡፡ የኛ የሽግግር መንግሥት ሀሳብ ነው አስፈሪና ገዥ እየሆነ የመጣው፡፡ መንግሥትም ይሄን ሀሳባችንን እንደ ጦር እንደፈራው መረዳት ይቻላል፡፡
“በኢትዮጵያ ፖለቲካ እንደኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ የለም” እያሉኝ ነው፡፡ ግን ደግሞ ለፓርቲያችሁ 10 ሺህ አባላት እንኳ ማሟላት አልቻላችሁም...?  
አሁን ባለው ሁኔታ በተለያየ ቦታ ተንቀሳቅሶ አባላት ለማፍራት፣ ቢሮ ለመክፈት አይቻልም:: የኢትዮጵያ ፖለቲካ እርቅ ይፈልጋል ብለንም ስለምናስብም፣ አባላትን ለመመዝገብና አደረጃጀቶችን ለማስፋት ሁኔታው አይፈቅድም፡፡  በዚህ የተነሳ ግንኙነታችንን በአጀንዳዎች ነው እያደረግን ያለነው። በአቋሞች ነው  ግንኙነቶችን የምንፈጥረው አሁን የቢሮ ፖለቲካ እያደረግን አይደለም፡፡ በንቅናቄ ደረጃ ለሚመራው የኢትዮጵያ ፖለቲካ፤ በየቦታው ቢሮ መክፈት ትክክለኛ አካሄድ ነው ብለን አናምንም፡፡ እንደዚያ ማድረግ የሚቻለው ፖለቲካው የተረጋጋ ሆኖ፣ የጋራ ተቋማትና የጋራ ራዕይ ተፈጥሮ፣ ሕግና ሥርዓት ተከብሮ፣ የምርጫ ውድድር ቢደረግ ነበር፡፡ አሁን ነገሮች ባልጠሩበት፣ ሕዝብን በሀሳብ መርቶ ከጎን የማሰለፍ ንቅናቄ ነው የምናደርገው። የድርጅት ፖለቲካና ግብግብ አያስፈልግም፡፡ የኛ የትግል ስልት ይሄ ነው፡፡
በአገሪቱ ሕግ ተመዝግባችሁ ነው የምትንቀሳቀሱት፡፡ የአገሪቱ የፓርቲዎች ሕግ ደግሞ ለምሥረታ ቢያንስ 10 ሺህ አባላት እንዲኖራችሁ ይጠይቃል፡፡ ይሄ ከአገሪቱ ሕግ ጋር ግጭት ውስጥ አያስገባችሁም?
እኛ ጽ/ቤቶች በአዲስ አበባም በክልልም አለን፡፡ ሕጉንም በቀጥታ አልተቃወንም፡፡ ነገር ግን አሁን አገሪቱ ለምርጫ አልተዘጋጀችም ነው ያልነው፡፡ የኢትዮጵያ ችግር ከምርጫ በላይ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ድርድር ያስፈልጋል፡፡ አሁን የኛ አቋም ትክክል መሆኑ ታይቷል፡፡ ምርጫ ቦርድም የጊዜ ሰሌዳውን አጥፏል፡፡
የምርጫ ጊዜው የተላለፈው በወረርሽኝ ነው:: እናንተ  እንደምትሉት  በፖለቲካዊ ምክንያቶች ሳይሆን በኮሮና ቫይረስ ነው?  
ኮሮና ድንገታዊ ክስተት ነው፤ አለማቀፋዊ ነው፤ ግን የኢትዮጵያ ችግር መጀመሪያውኑ የተፈጠረ ነው፡፡ እኔ ራሴ ወረቀት አቅራቢ ሆኜ በተሳተፍኩበት የፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ስብሰባ ላይ፤ “ኢትዮጵያ አሁን ምርጫ ማካሄድ አትችልም” የሚለውን ከ95 በመቶ በላይ ፓርቲዎች ተስማምተውበት ነበር፡፡ ከብልግናና ከኢዜማ ፓርቲ ውጪ ሁሉም፣ ምርጫውን ማካሄድ እንደማይቻል ተቀብለው ነበር፡፡ ኮሮና ባይኖርም እኮ ምርጫው ሊካሄድ አይችልም ነበር፡፡ እኛ ነን ትክክል ያልኩት ከዚህ አንፃር ነው፡፡
ምርጫውን ለማካሄድማ መንግሥት ዝግጁ ነኝ ብሎ ሂደቱ ተጀምሮ ነበር፡፡ የኦሮሞ ብሄርተኛ ድርጅቶች፣ ሕወኃትና ሌሎችም ምርጫው መደረግ አለበት የሚል አቋም ነበራቸው… በዚህ መሃል ነው ኮሮና የተከሰተው፡፡ ለምርጫው መራዘም ብቸኛው ምክንያትም፣ የወረርሽኝ ስጋት መሆኑን ቦርዱ አስታውቋል…?
መቼም በፊት ሲያስሩን “ሽብርተኛ” እያሉ ነው የኖሩት፡፡ አሁንም የእነሱ ኮሮናን ሰበብ ማድረግ የሚደንቅ አይደለም፡፡ ግን ለኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታና ኢትዮጵያ ውስጥ ለምንኖር ሰዎች “አይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ” ዓይነት ነው፡፡ እውነታውን ካየን የኦሮሞ ብሄርተኛ ድርጅቶችና ህወኃት ምርጫ እንዲደረግ የሚፈልጉት ሌጋሲያቸው እንዳይነካ ነው:: ብልፅግና ደግሞ ጉልበት ስላለኝ አሸንፋለሁ በሚል ነው፡፡  ኢዜማ ያው የብልጽግና ደጋፊ ነው፡፡ እኛ ደግሞ “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ድርድርና ውይይት ያስፈልገዋል፣ ከሕገ መንግሥቱ የላቁ አማራጮች ያስፈልጉታል” የሚል አቋም ነው የያዝነው፡፡ ይሄ አቋማችን ከሁለት ዓመት በፊት የያዝነው ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ከተመዘነ ኮሮና ዝም ብሎ ሰበብ ነው ማለት ነው፡፡ እነ ፕ/ር መረራ እኮ “መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ነው” ሲሉ ነው የገለፁት፡፡ ስለዚህ ኮሮና ጣልቃ የገባ ምክንያት ነው፡፡
“አብሮነት” የሽግግር መንግሥት ይቋቋም  የሚል አቋም ላይ ፀንቻለሁ ብሏል፡፡ ሌሎች ደግሞ “እርስ በእርስ እንኳ መስማማት ያልቻሉ ፓርቲዎች እንዴት ነው ተነጋግረው የሽግግር መንግሥት ሊያቆሙ የሚችሉት ትርፉ አገርን ለትርምስና ለከፋ ብጥብጥ መዳረግ ነው” ብለው ይሰጋሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
ይሄ አንተ የምትለው --- ግልብና ያልታሰበበት ሃሳብ ነው፡፡  
እንዴት?
ይሄ ማለት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሀይል “እየተሳሳበ እየተገዳደለ እንኑር” ማለት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ይቃጠል፤ ህወኃትም ልገንጠል ይበል፤ አዲስ አበባንም ልውሰድ ከሚለው ጋር ሳንነጋገር እንዲሁ እየተጨቃጨቅን እንኑር ማለት ነው። ሰው እየሞተ፣ ንብረት እየወደመ እንቀጥል እንደ ማለት ነው፡፡ እኛ እኮ “ተወያይተን የሽግግር መንግሥት እናቋቁም” የምንለው የተጣላና  የተራራቀው እንዲቀራረብ ነው፡፡
እውነት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተስማምተው የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ይችላሉ ብለው ያምናሉ?
አዎ! ሲጀመር ያንን የማያምን ሰው፤ ፖለቲካ ውስጥ ምን ያደርጋል!
ለኔ የሚታየኝ ስጋት በተቃራኒው አንነጋገር መባሉ ነው፡፡  መነጋገር አለመቻላችን ነው ስጋት የሚሆነው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሊያፈርሰን ሊያጫርሰን ካልሆነ፣ ተነጋግረን በሚያቆስል ሁኔታም ቢሆን የኢትዮጵያን ጉዳይ አንድ መላ እናበጅለት ነው የምንለው። ሌላው ደግሞ ችግሩን ዝም ብለን እያየን እንኑር ነው የሚለው:: እኔ ሰው እየሞተ፣ አገር ወደ ቁልቁለት እየሄደች፣ ሳንነጋገር ዝም ብለን እንኑር የሚለውን አልቀበልም። አለመነጋገር ያፈርሰናል፡። የኛ ችግር ቀላልና በንግግር መፈታት የሚችል ነው:: ይሄን ሃሳብ ስናቀርብ “ተነጋገሩ፤ አገራችሁን አታፍርሱ” በሚል ድጋፍ ሊሰጠን ይገባ ነበር፡፡  
የሽግግር መንግሥት የሚለውን ሃሳብ የሙጥኝ ብላችሁ የያዛችሁት እናንተ ብቻ ናችሁ፡፡ የሌሎችን ድጋፍ ካላገኛችሁ ሀሳባችሁ እንዴት ሊሳካ ይችላል?
ሁሉም የየራሱን ስሌት ይዞ ነው የቆመው:: አንድ የማረጋግጠው ነገር፣ ከሁሉም በላይ አስታራቂውንና ደፋሩን ሀሳብ የያዝነው እኛ ብቻ ነን። መንግሥት “የሽግግር መንግሥት ጥያቄ ስልጣኔን ያሳጣል”፣ ሌሎች ደግሞ “ያስጠቃናል ያስበላናል” በሚል ስሌት ውስጥ ነው የገቡት፡፡ ስለዚህ እኛ ነን የሚበጀውንና ደፋሩን ሀሳብ የያዝነው። “አብሮነት” ብቻውን ይሄን ሀሳብ ሲያዝ፤ “ማንም ከማንም ጋር መፈራራት አያስፈልግም፤ ሁሉም ያለውን ሀሳብ ወደ ጠረጴዛ ያምጣና ተነጋግረን የኢትዮጵያን የወደፊት እጣ ፈንታ እንወስን” በሚል አቋም ነው፡፡ በጓዳ እየሄዱ “ሕገ መንግሥት ይሻሻል፣ ህወኃት አይምጣብኝ” እያሉ የት ድረስ ይዘለቃል? ሁሉም አሁን ከየራሱ አንፃር እያሰላ፣ አሸናፊ የሚሆንበትን ሃሳብ ነው እያቀረበ ያለው:: እኛ ደግሞ አገር አሸናፊ ልትሆን የምትችልበትን ሀሳብ ነው ያቀረብነው፡፡
አሁን ወደ ሕገ መንግሥት ትርጉም ተገብቷል:: በሂደቱ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
ያው ጠ/ሚኒስትሩ የሚፈልጓቸውን ምሁራን መርጠው፣ እሳቸው የሚፈልጉትን ሀሳብ ለሕዝብ ፕሮፓጋንዳ ሰርተው በማቅረብ፣ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ በማለት በስልጣን ለመቆየትና፣ ያንን ደግሞ ስጋ ለማልበስ የሚደረግ ሂደት ነው፡፡ ሌላ ምንም የተለየ ነገር የለም፡፡ ከዚህ በኋላ ምን ይመጣል ከተባለ፣ ያው ብሄራዊ የሉዓላዊነት ስጋት አለ፡፡ ስለዚህ ዶ/ር ዐቢይ በሥልጣን ይቆዩ ነው የሚባለው፡፡ ይሄ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግር ጋር ተዳምሮ፣ በሂደት ደካማ መንግሥት ይፈጠራል፡፡ የሕዝብ ድጋፍንም በሂደት እያጣ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ውጤቱ ደካማ መንግሥት ነው፡፡ ለዚህ ነው አስቀድመን እንነጋገር የምንለው፡፡  


Read 1143 times