Sunday, 24 May 2020 00:00

የማንነት ፖለቲካና የሀገራዊ አርበኝነት እርቅ

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(2 votes)

    “-ዳግም የሚወለደው ኢትዮጵያዊነት፤ በዜግነት የማንሸማቀቅበት፣ እርስ በርሳችን የተጋመድንበትን የትሥሥር ወሽመጥ የሚያበረታ፣ ባህላዊ እሴቶቻችንን እንደ ሸክም ሳይሆን እንደ ብሔራዊ ሀብት የምንቆጥርበት ይሆናል፡፡--”
         
             ጥቅል እውነታ
ጠባብ ብሔርተኝነት የሚበቅለው የብሔራዊው ዳቦ ሲያንስና የበላተኛው ቁጥር ሲበዛ ነው፡፡ አውሮጳና አሜሪካ የገጠማቸውን ግሽበት ተከትሎ፣ ወደ ሥልጣን የመጡት ትራምፕና የትራምፕ አምሳያ ቀኝ ዘመሞች፤ በስደተኞችና በጥቁሮች ላይ የወሰዱትን ከፋፋይ ፖሊስን ታሳቢ ማድረግ ይቻላል፡፡ ተሰፋ መቁረጥና ሥራ አጥነት አለቅጥ በአንድ ሀገር ሲስፋፋ፣ ዞሮ ዞሮ ውስን የሆነውን ሀብት ለመቀራመት፣ ሁሉም ወገን በየአቅጣጫው ባለ በሌለ ኃይሉ መረባረቡ የማይቀር ይሆናል፡፡
ፍኩያማ “Identity፡ The Demand for Dignity and the Politics of Resentment” በሚለው ግሩም መጽሐፉ፤ ማንነት ላይ ያጠነጠነ ፖለቲካ፣ ለዓለም ምን ያህል ጠንቅ እንደሚሆን በስፋት አትቷል፡፡ ከመጽሐፉ አንድ ሰበዝ ልምዘዝ፤ “ማንነትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ቅኝት ለዘመናዊው የሊብራል ዴሞክራሲ ፈተና ሆኗል፡፡ በሁሉም የዓለም ጥግ ተቀባይነት ያለው፣ ላቅ ያለ ሰዋዊ ሰብእናን መሠረት ባደረገ የፖለቲካ ማእቀፍ ውስጥ መግባት ካልተቻለ፣ እርስ በርሳችን የምንተላለቅበት የጥፋት  አውድ ገሀድ መሆኑ የማይቀር  ነው፡፡” (The rise of identity politics in modern liberal democracies is one of the chief threats that they face, and unless we can work our way back to more universal understandings of human dignity, we will doom ourselves to continuing conflict.)
በማንነት ዙሪያ የሚሽከረከር የፖለቲካ ንቅናቄ፣ ዓለም አቀፋዊ ድባብን እየተላበሰ እየመጣ እንደሆነ በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንዲህ አይነት፣ ከአምክንዮ የተራቆተ ፖለቲካዊ ውቅር፣ ዳፋው የሚከፋው ከሰለጠነው ዓለም ይልቅ፤ እንደ አፍሪቃ ባሉ በሁሉም ነገር ወደ ኋላ በቀሩ ሀገሮች ላይ ነው፡፡ ምእራብዊያን፤ የማንነት ፖለቲካ የአብራክ ክፋይ የሆኑትን መሪዎች ወይም ዘረኛ ኃይሎችን፣ አደብ የሚያስገዙበት መጠበቂያ ግምብ አላቸው፡፡ በዳበረ የሊብራል ዴሞክራሲ አማካኝነት የተቀለሱት ተቋማት፣ የዘረኞቹን መወራጨት በልክ እንዲሆን ዋንኛ መሸበቢያ ኹነኛ መሣሪያዎች ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ከማንነት ጋር የተያያዘ ትግል ከተጀመረ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የዘለለ ቢሆንም፤ ሕገ መንግሥት ተቀርጾለት፣ ሥልጣን በያዘው አካል መዋቅራዊ በሆነ መልኩ፣ በብርቱ ሲሰራበት የቆየው ባለፉት ሁለት ዐሥርተ ዓመታት ነው፡፡ በርግጥ፤ በሀገራችን ተንሰራፍቶ የኖረው አገዛዝ የዘውግ ማኅበረሰቦችን መብት አልደፈጠጠም ብሎ የሚከራከር የዋህ የታሪክ አዋቂ አይኖርም፡፡ ትልቁ ነጥብ፣ ጭቆናው የሚፈርጅበት ማእቀፍ ነው፡፡ የዘውጌ ፖለቲካ አራማጆች እንደ ማታጊያ ስልት የሚጠቀሙበት “የብሔር ጭቆና ትርክት”፣ ሀገራዊ ትስስርን በመበጣጠስ፣ ሌጣቸውን ለመቆም በሚውተረተሩት ኃይሎች ምናብ ውስጥ ብቻ ነው የሚገኘው፡፡ በጥንታዊው የጉልት ሥርዓት ውስጥ፣ የጎንደር ባላባትን ከጅማ ባላባት ጋር የሚያግባባቸው ቋንቋ፣ የዘውግ ማንነት ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ መደብ ነበር፡፡ በሁለቱም ዘንድ ያለው ሰፊው ማኅበረሰብ፣ በባላባታዊው አገዛዝ በእኩል ደረጃ ተጨቁኗል፡፡ በየትኛውም የታሪክ ሒደት፣ አንድ የዘውግ ማኅበረሰብ ተሰባስቦ፣ ሌሎችን የጨቆነበት አጋጣሚ የለም፡፡ በሀገሪቱ አራቱም ጥግ ያለው ሁሉም ማኅብረሰብ፤ ከኢኮኖሚ፣ከፖለቲካዊና ከማኅበራዊ እኩልነት ተነፍጎ ነው የኖረው፡፡
የማንነት ፖለቲካ አራማጅ ድርጅቶች
የወል ጠባይ
የጽንፈኛ ማንነት ፖለቲካ አቀንቃኞች፣ የመወዳደሪያ ምህዳሩ በተዘጋ ቁጥር ተጽዕኗቸው ይበረታል፡፡ ጽንፈኛ ኃይሎቹ ከሐሳብ ይልቅ የስሜት ኃብታም ናቸው:: የሕዝብን ቁስል እየነካኩ ተቀባይነትን ማሳደግ ተቀዳሚ ዓላማቸው ነው፡፡ ሀገር የምትገነባበትን ጡብ በማኖር ፈንታ፣ በሻሞ ፖለቲካ ውስጥ የሚቃርሙት ሲሳይ ነው ግድ የሚላቸው:: የዘውግ ድርጅቶች ሕዝባቸውን ከገባበት አዘቅጥ ለማውጣት በሚረዱ ፖሊሲዎች ላይ ጊዜ አያጠፉም፤ በተቃራኒው ብሶትን እንደ ቤንዚን እያርከፈከፉ ለፖለቲካ ትርፍ ይባትታሉ:: በከበባ ሥነልቦና ወይም “siege mentality” ቅርቃር ውስጥ ሕዝባቸውን በመክተት፣ በሥጋትና በሽብር እንዲኖር ይፈርዱበታል:: ድርጅቶቹ እንወክለዋለን የሚሉትን ሕዝብ እንደ ግል ርስታቸው ነው የሚቆጥሩት፡፡ የተለየ ሐሳብን መሠረት አድርጎ የተሰባሰበ የፖለቲካ ኃይል ድንገት በምህዳሩ ላይ ቢከሰት፣ ርስታቸውን ሊቀናቀን እንደመጣ ጣውንት ስለሚቆጥሩት፣ በምክንያት በመሟገት ፈንታ  ስም ማጥፋት ይቀናቸዋል::  
አንዳንድ የሐሳብ ወይም የዜግነት ፖለቲካን የሚደግፉ ምሁራን፣ የዘውግ ድርጅቶች በፖለቲካ ፓርቲ ስም ተመዝግበው ከሚታገሉ፣ በሲቪክ ማኅበራት ስምና አላማ ተወስነው ቢደራጁ የተሻለ ይሆናል፤ ይላሉ:: ማኅበራቱ ለተወሰነ ማኅብረሰብ መብት የሚቆረቆሩ ስለሆነ፣ ልክ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ፣ የፖለቲካ ሥልጣንን ለመያዝ አይወዳደሩም:: በመሆኑም እነዚህ ድርጀቶች ለሚወክሉት ማኅበረሰብ መብትና ጥቅም ለመቆርቆር ብሎም ለተገብራዊነቱ ለመንቀሳቀስ በሲቪክ ማኅበራት ስም ተደራጅተው ቢታገሉ ለሀገር የሚበጅ ይሆናል፡፡ ካልሆነ ምህዳሩን በተመጠነ መንገድ በመክፈት የሐሳብ ሙግት አውድን በማፋፋት፣ ድርጅቶቹ ጠውልገው እንዲከስሙ ማድረግ ሌላ አማራጭ መሆን ይችላል፡፡ ከዚህ ውጭ ድርጅቶቹን በሕግ ማገድ ግን ይበልጥ ተሰሚነታቸውንና ድጋፋቸውን እንደሚያበራክትላቸው የፖለቲካ ተንታኞች ያምናሉ፡፡
ኢትዮጵያዊነት ወይም ሞት
የኢትዮጵያዊ አርበኝነት እስትንፋስ የቆመው፣ በትላንት የጋራ የታሪካችንና ሥልጣኔያችን መደላደል ላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በተለይ፤ እንደ ሕዝብ አንድ ሆነን፣ ቀዬአችን ድረስ ዘልቆ የመጣውን ፀጉረ ልውጥ ወራሪ ኃይልን አይቀጡ ቅጣት የቀጣንበት ገድላችን፣ የታሪካችን ጉልላት ነው፡፡
ኢትዮጵያዊነት የሚለው የአልበገር ባይነት መንፈስ፣ እንደ ነጻነት ንቅናቄ (movement) ሆኖ ለበርካታ ጭቁን ሕዝቦች የተስፋ ውጋጋን ፈንጥቋል፡፡ የፓን አፍሪቃኒዝም፣ የፀረ ቅኝ ግዛትና የፀረ-አፓርታይድ ንቅናቄዎች መራራ ትግል የቆመበት መሠረት፣ የኢትዮጵያዊነት ርዕዮተ ዓለም ነበር፡፡ “ኢትዮጵያዊነት ወይም ሞት” ለጥቁር አፍሪቃዊያን ሕዝቦች የወኔ ስንቅ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ውለታው ብዙ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊነት ወይም ሞት ከቀያችን አድባር ጋር ግን  ጠበኛ ሆኖ ነው የኖረው:: በየጎጡ የሚስተጋቡትን ጉራማይሌ ድምጾች በመድፈቅ ሌጣውን ለመቆም ተውተርትሯል፡፡ ደርግ ይህን መፈክር አንግቦ ለቅራኔያችን እልባት ከመስጠት ይልቅ ሆድና ጀርባ የምንሆንበትን ዓለም ሲያወድል ኖረ፡፡ ለጥቆ የመጣው ሕወሓት መራሹ መንግሥት፣ በኢትዮጵያዊነት መቃብር ላይ ቁርሾአችንን እንደ ጥሪት ቋጥረን፣ ዐይንና ናጫ የምንሆንበትን የፖለቲካ ክኒና እያዋጠን፣ ለሁለት ዐሥርተ ዓመታት ጌታ ሆኖ ከረመ፡፡
የኢትዮጵያዊነትና የዘውጌ ማንነት ጠብ
ይህንን ነጥብ በታዋቂው የድህረ-ዘመናዊነት/ ፖስት ሞደርኒዝም/ አቀንቃኝ ፉኮ ንድፈ-ሐሳብ ማእቀፉ ውስጥ ብንገመግመው፤ የበለጠ ትርጉም ይኖረዋል:: እንደ ፈላስፋው አባባል፣ ጥቅልና አካባቢያዊ ማንነቶች በፍጹም አብረው ታርቀው ሊሄዱ አይችሉም፡፡ በባህል፣ በቋንቋና በአካባቢ ያልተቀነበበ አንድ ወጥ እውነት፣ ከውጥንቅጥ ነባራዊ ኹነቶች ጋር ይላተማል:: በዘመናት መፈራረቅ፣ በቦታ ልዩነትና በባህል ጉራማይሌነት የማትዛነፍ አንዲት እውነት እንዳለች ከሚያትት አስተምህሮት ጋር ፈላስፋው ጠበኛ ነው፡፡ ጥቅል (grand concept) እና አካባቢያዊ እውነታ (fragmented reality) በአንድነት ተቀይጠው ሊኖሩ አይችሉም የሚል አቋም አለው፡፡ ንድፈ-ሐሳቡን ወደ መሬት በምናወርድበት ጊዜ ከሀገራችን የፖለቲካ አውድ ጋር ፊት ለፊት ለመጋጨት እንገደዳለን፡፡
በሕወሓት/ኢሕአዴግ ፊታውራሪነት እውን የሆነው የ1987ቱ አራተኛው ሕገ መንግሥት የታነጸው ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች በሚለው አካባቢያዊ ማንነት (fragmented reality) ላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያዊ ዜግነት ለሚገኝ ጥቅል ሰብእና (grand concept) ሕገ መንግሥቱ የሚተወው ኩርማን ቦታ የለውም፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት ከፍ ብሎ ሲዘመር  የኖረው “እኛ ብሔር፣ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች”  እንጂ “እኛ ኢትዮጵያዊያን” የሚል አልነበረም፡፡
በፉኮዋዊ አስተምህሮት የተቃኘው ሕገመንግሥት፣ ቅራኔያችንን በብርቱ እንዳባባሰው ዘውግ ተኮር የሆኑት የአካባቢያዊ ግጭቶችን ዋቢ ማድረግ ይቻላል፡፡ አሰባሳቢው ኢትዮጵያዊ ማንነት ወደ ጎን ተገፍቷል፡፡ በርግጥ፤ አብዛኛዎቹ የዘውጌ ፖለቲካ አቀንቃኞች “ኢትዮጵያዊ ጥቅል ማንነት” በጎሳ ማንነት ኪሳራ እውን የሚሆን ጨፍላቂ ትርክት ነው፤ ብለው ያምናሉ፡፡ ከተማሪዎች ንቅናቄ አንስቶ ከፖለቲካ ልሂቃኖቻችን አንደበት የማይጠፋው ስብከት፤ “ኢትዮጵያዊ ማንነት” በሰሜን ባህልና ትውፊት ተለንቅጦ የተበጀ አግላይ ርዕዮት እንደሆነ ነው፡፡
እርቁን እንዴት እናውርደው?  
ሀገራችን ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች እስር ቤት እንደሆነች በማወጅ፤ የእልቂት መቀመቅን ሲምስ የኖረው አገዛዝ፤ ወደ ዳር በመገፋቱ ችግሮቻችንን በንግግር ለመፍታት ትልቅ እድል ተከፍቶልናል:: ይህ ዕድል፣ ከእጃችን ካመለጠ ግን ታሪክን እጀ ሰበራ እንደምናደርገው ጥርጥር የለውም:: ኢትዮጵያዊ አርበኝነትን ወደ ጎን የገፋ፣ የዘውጌ ማንነትን የደፈጠጠ ሥርዓት፤ አንዲት ጋት ፈቀቅ ሳይል አፈር እንደሚለብስ፤ የትላንት ገጠመኞቻችን ትምህርት ሰጥተውን አልፈዋል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከዘውጌ ማንነት  ጋር መሳ ለመሳ ሆነው እርስ በርስ ተደጋግፈው የሚሄዱበትን ፖለቲካዊ ሥርዓት ለዐይነ ሥጋ የምናበቃ ከሆነ፣ ሲያባንነን የኖረውን ቅዠታችንን እንደሚፈታ አያጠራጥርም፡፡   
ወደ ፊት የምንቀልሰው ሥርዓት፣ በጋራ ለተሻገርናቸው የታሪክ ጉድባዎች እውቅና የሚሰጥ መሆን አለበት፡፡ በተመሳሳይም ተዝቆ የማያልቀውን ባህላዊ እሴቶቻችን፣ ለብሽሽቅ ሳይሆን እንደ ሀገራዊ ሀብቶቻችን ቆጥረን፣ እርስ በርስ የምንዋሃድበት ቋንቋ መጎልበት ይኖርበታል፡፡
ኢትዮጵያዊ አርበኝነት ለዘውጌ ማንነት ጥላ ከለላ መሆን ይችላል፡፡ ጥቃቅን እውነታዎች (fragmented realties) ለመኖራቸው ዋስትና መሆን የሚችል፣ በዴሞክራሲያዊ ባህል የዳበረ ፍትሐዊና አቃፊ ኢትዮጵያዊነት መጎምራት አለበት:: ዳግም የሚወለደው ኢትዮጵያዊነት፤ በዜግነት የማንሸማቀቅበት፣ እርስ በርሳችን የተጋመድንበትን የትሥሥር ወሽመጥ የሚያበረታ፣ ባህላዊ እሴቶቻችንን እንደ ሸክም ሳይሆን እንደ ብሔራዊ ሀብት የምንቆጥርበት ይሆናል፡፡Read 4246 times