Saturday, 23 May 2020 15:34

በ“ኳራንቲን” የታጀበ ሁዳዴ - ወትንሣዔ - ወኢደል ፊጥር

Written by  ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(2 votes)

 በዚህ ሳምንት ለየት ያለች ማስታወሻ መጻፍ አሰብኩ፡፡ ዛሬ (ቅዳሜ) ወይም ነገ (ዕሑድ) የሮመዳን ፆም ፍቺ በዓል ይከበራል፡፡ ይህ በዓል በሙስሊሞች ዘንድ “የረመዳን ፆም ፍቺ በዓል” (ኢደል ፊጥር) በመባል ይታወቃል፡፡ በዓረብኛ “ዒድ” ማለት “በዓል” ማለት ነው፡፡
በእስልምና ሃይማኖት በየዓመቱ ሦስት በዓላት ይከበራሉ፡፡ እነዚህ በዓላት በሀገራችን በካላንደር ሥራ ተዘግቶ መከበር የጀመረው በደርግ ዘመነ መንግስት ሲሆን፤ ጊዜውም ከ1968 ዓ.ል ጀምሮ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ሙስሊሞች እነዚህን በዓላት በራሳቸው ፈቃድ በአደባባይና በየቤታቸው ቢያከብሯቸውም፣ እንደ ሌሎች ሃይማኖቶች በዓላት በመንግስት ደረጃ እውቅና የተሰጣቸው አልነበሩም፡፡
ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ ለሁሉም ሃይማኖታዊ በዓላት መንግስታዊ እውቅና ተሰጥቷቸው፣ ሥራ ተዘግቶ እንዲከበሩ ተደርጎ እስከ አሁን ድረስ የዘለቀ ቢሆንም፤ ዘንድሮ ግን ለየት ያለ ሁኔታ ተከስቷል፡፡ በዚህም መሰረት በክርስትና ሃይማኖት በኩል ታላቁ የፆም ወቅት (ማለትም የሁዳዴ ፆም) እና እለተ ትንሣዔ እንዲሁም በእስልምና ሃይማኖት ታላቁ የሮመዳን ፆም እና የዒደል ፊጥር በዓል ሁሉም አማኞች በቤታቸው ውስጥ ሆነው እንዲያከብሯቸው ግድ ሆኗል፡፡ ግዴታውን ያመጣው ደግሞ ዓለምን እያስጨነቀ ያለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ነው፡፡ ለዚህም ነው የመጣጥፌን ርእስ በ“ኳራንቲን የታጀበ ሁዳዴ ወትንሣዔ ወዒደል ፊጥር” ያልኩት፡፡
“ፆም” የሚለው ቃል የመዝገበ ቃላት ትርጉም፡-“መተው፣ መታቀብ፣ መታረም” ማለትነው፡፡በዚህ ትርጉም መሰረት “ፆም ማለት የሰው ልጅ የሕይወትን መመሪያ ላዘጋጀለት ፈጣሪው እየታዘዘ ኃጢዓትን ለማስተሰረይ (እንደየሃይማኖቱ) በሕገ-ሃይማኖት ለታወቁ ጊዜ ያት ከምግብ፣ ከመጠጥና ከመንፈሳዊ ፍላጎቶች በመከልከል፣ ጊዜን በጸሎትና በጎ ነገሮችን በማከናወን የመንፈስ ብርታትና እርካታ ማግኛ መንገድ” መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ:: “ፆም ማለት ሰውነት ከሚያስፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ መከልከል መወሰን ወይም ለሰውነት የሚያምረውን፣ የሚያስጎመጀውን ነገር መተው ማለት ነው” የሚሉ ወገኖችም አሉ። ፆም ከሃይማኖት ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ስላለው ሃይማኖት ባለበት ሁሉ ፆም አለ። ፆም አምላካዊ ግዴታ በመሆኑ፤ የፆሙ ወቅት፣ የፆሙ ጊዜ እና የአጿጿሙ ሁኔታ ቢለያይም በሁሉም ሃይማኖቶች ተግባራዊ ይደረጋል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በርካታ የፆም ዓይነቶች እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን “ዐብይፆም” ወይምየሁዳዴ ፆምዘለግ ላለ ጊዜ የሚከናወን ነው፡፡ በዐብይ ፆም የእምነቱ ተከታዮች በቤተ ክርስቲያን በመገኘት ጸሎት ያደርጋሉ፡ ፡በዘንድሮው የዐብይ ፆም በቤተክርስቲያን የሚደረገው ሥርዓተ አምልኮ ግን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በተሟላ መንፈሳዊ ተግባራትአልተጠናቀቀም፡፡
“ዐቢይ ፆም መንፈሳዊ ጉዞ ነው፤ መድረሻውም ትንሣኤ ነው” ይላሉ የክርስትና እምነት ተከታዮች፡፡ የትንሣኤ በዓል (በዓለ ፋሲካ)  ደስታ ነው፡፡ የዘንድሮው የትንሣኤ በዓል ግን ወዳጅ ዘመድን እየጠየቅን፣ አብረን እየበላንና እየጠጣን ሳይሆን በትካዜ ተወሽበን ነበር ያሳለፍነው፡፡ ዓብይ ፆምን እና እለተ ፋሲካን በኮሮና ውስጥ ሆነው፣ ከእንቅስቃሴ ታቅበው፣ ቀሳ ውስጥ ገብተው ያሳለፉ የክርስትና እምነት ተከታዮች ፆምና ፀሎታቸውን ሲያጠናቅቁ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ “ታላቅ” የተሰኘው የረመዳን ፆም ተተካ፡፡ ፆምና ፀሎቱ ቀጠለ…
በሂጅራ የዘመን አቆጣጠር ረመዳን የዘጠነኛው ወር ስም ነው፡፡ በረመዳን ወር ጧት ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት ጀምሮ ፀሐይ እስከምትጠልቅ ድረስ ለ30 ወይም ለ29 አልፎ አልፎ (በዘመናት መካከል) ለ28 ቀናት ያህል ሙስሊሞች ከምግብና ከውሃ ራሳቸውን ያቅባሉ፡፡ ይህንን የሚያደርጉት ግን ምንም ዓይነት አካላዊና መንፈሳዊ ችግር የሌለባቸው እንደሆነ ነው፡፡ በዚህ ወር ሙስሊሞች ራሳቸውን የሚያቅቡት ከምግብና ከውሃ ብቻ አይደለም፡፡ አንደበታቸውን ከሃሜት፣ ምላሳቸውን ከቁጣ፣ ዓይናቸውን መጥፎ ነገር ከማየት እንዲርቅ ያደርጋሉ፡፡ በአጠቃላይ ከመጥፎ ተግባራት ርቀው ሶላት በመስገድ፣ ፈጣሪን በመለመን፣ ምፅዋት በመስጠትና የመሳሰሉትን በጎ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይተጋሉ፡፡
በረመዳን ወር ሙስሊሞች መጥፎና አስጸያፈ ተግባራትን ይርቃሉ፡፡ ድክመታቸውን ለማረም ይጥራሉ፡፡ ይህ ራስን የመቅጣት ተግባር “ጅሐድ አል-ነፍስ” ወይም “ራስን መታገል” ይባላል፡፡ ነብዩ (ሰዐወ) ባስተማሩት መሰረት፤ ይህ ራስን የማጥራት ትግል ትልቁ “ጅሐድ” ነው፡፡ ራስን ከማንጻት በተጨማሪ ሙስሊሞች ከፈጣሪያቸው ጋር በፀሎት የሚያደርጉትን ግንኙነት በጥልቀት ያከናውናሉ፡፡ በዚህ ወቅት ሙስሊሞች ባለፉት ጊዜያት ያከናወኗቸውን መንፈሳዊ ተግባራት ይገመግማሉ፡፡ ለሰሩት ኃጢያት ፈጣሪያቸው ምህረት እንዲያደርግላቸው ይለምናሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ሙስሊሞች የርሃብን ምንነት በተጨባጭ ስለሚገነዘቡ ለድሃዎች ያዝናሉ፣ ያላቸውን ያካፍላሉ፣ ይለግሳሉ፡፡
በረመዳን ወር የሙስሊሞች አንዱ ግዴታ ምግብ በማዘጋጀት ድሃ ፆመኞችን ምግብና መጠጥ በማቅረብ ማስፈጠር (ፆም ማስገደፍ - ማብላት) ነው፡፡ የረመዳን ወር የመተዛዘንና የበጎ ተግባራት ማከናወኛ ጊዜ ነው፡፡ ከረመዳን ወር ውጪ ሙስሊሞች ጤነኛ ከሆኑ ዓመቱን ሙሉ ባሉት ጊዜያት በሳምንት የተወሰኑ ቀናትን እንዲፆሙ ይበረታታሉ፡፡ በዚህም በጎ ተግባራቸው ራሳቸውን ለዲሲፕሊን ተገዢ ማድረግ ይችላሉ፡፡
የበጎ አድራጎት ሥራ (ሰደቃ) በቁርኣን በተደጋጋሚ ትኩረት የተሰጠው ተግባር ነው:: ሙስሊሞች በረመዳን ፆም ወቅት የበጎ አድራጎት ተግባራት (ሰደቃ) እንዲያደርጉ በላቀ ደረጃ ይበረታታሉ፡፡ የበጎ አድራጎት ስራው እንደሰውየው ሃብትና ችሎታ ሊለያይ ይችላል:: ሃብት ያለው ካለው ላይ ቀንሶ ይሰጣል፡፡ የሌለው ሰው በአቅሙ የሚያከናውናቸው የበጎ አድራጎት ተግባራት (ሰደቃ) አሉ፡፡ ለምሳሌ፤ መንገድ ላይ እንቅፋት የሚሆንን ድንጋይ ወይም እሾህ ወይም ጋሬጣ አንስቶ መንገዱን ማጽዳት ሰደቃ ነው:: የእንጨት መፋቂያ ከዛፍ ላይ ቆርጦ ለሰዎች መስጠት ሰደቃ ነው፡፡ አንድ መፋቂያ መስጠትና አንድ ሚሊዮን ብር መስጠት አላህ ፊት እኩል ዋጋ አላቸው ተብሎ ይታመናል፡፡
ቁርኣን እንደሚለው የበጎ አድራጎት ልገሳ ሊደረግላቸው የሚገቡት የህብረተሰብ ክፍሎች የሚላስ የሚቀመስ የሌላቸው ድሃዎች፣ ወላጅ የሌላቸው ህፃናት፣ ድሃ ዘመዶች፣ መንገደኞችና እንግዶች፣ የውጪ ሀገር ስደተኞች፣ የጦር ምርኮኞች፣… ናቸው፡፡ በርካታ ሙስሊም ምሁራን የበጎ አድራጎት ስጦታ ሙስሊም ለሆነም ሙስሊም ላልሆነም መስጠት እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡
ሙስሊሞች የረመዳንን ወር በፆምና ምጽዋት በመስጠት ብቻ ሳይሆን በአካባቢያቸው መስጊድ በመገኘት ለፈጣሪ የሚያደርጉትን ሶላትና ጸሎታቸውን በጋራ እንዲያከናውኑ ግዴታ አለባቸው፡፡ ዘንድሮ ግን በኮሮና ቫይረስ ምክንየት ይህንን ማድረግ አልተቻለም:: በሁዳዴ ፆም ወቅት ቤተ ክርስቲያኖች እንደተዘጉት ሁሉ በረመዳን ፆምም መስጂዶች ተዘግተዋል፡፡
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው “ዒድ” ማለት “በዓል” ማለት ነው፡፡ ከረመዳን ፆም በኋላ የሚከበረው በዓል “ኢደል ፊጥር” (የፆም ፍቺ) ይባላል፡፡ የዚህ በዓል አከባበር የሚጀምረው በበዓሉ እለት ማለዳ ላይ በአንድ ከተማ ወይም በአጎራባች መንደሮች አካባቢ ያሉ ሙስሊሞች ሰፋ ባለ ሜዳ አንድ ላይ ተሰባስበው ሶላት በመስገድ ነው፡፡ ከሶላቱ በኋላ ወደየቤታቸው በመመለስ ከወዳጅ፣ ከዘመድ፣ ከጎረቤት፣… ጋር አብሮ በመብላትና በመጠጣት፣ በስልክና በአካል በመጠያየቅ ያሳልፋሉ፡፡ ዘንድሮ ግን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት አደባባይ ወጥቶ የኢደል ፊጥር ሶላትን በጋራ መስገድ የሚቻልበት ሁኔታ የለም::
ጽሁፌን ከማጠቃለሌ በፊት አንዳንድ ነጥቦችን በማንሳት ትኩረት እንዲሰጣቸው ማድረግ ወደድሁ፡፡ ላለፉት ሦስት ወራት መላው የዓለም ህዝብ ትኩረት ያረፈው ትልቅ አደጋ ሆኖ በተጋረጠበት የኮሮና ቫይረስ ላይ ነው፡፡ የኮሮና ቫይረስ የዓለም ኃያላን ጭምር ሊቋቋሙት ያልቻሉት ገዳይ ወረርሺኝ ነው፡፡ የኮሮና ቫይረስ በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ ቤተ ክርስቲኖች፣ መስጊዶችና ቤተ እምነቶች እንዲዘጉ አድርጓል፡፡ የኮሮና ቫይረስ የዓለምን ህዝብ እንቅስቃሴ ገትቷል፡፡ የኮሮና ቫይረስ የዓለም ህዝብ ፊቱን ወደ ፈጣሪው እንዲያዞር፣ እንደየእምነቱ በፆምና በፀሎት እንዲተጋ፣ መንፈሳዊነቱ እንዲነሳሳ ያደረገ ውጤትንም አስገኝቷል፡፡ ይህ ሁኔታ በእኛም ሀገር እውን ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት በጋራ ባሳለፉት ውሳኔ መሰረት ከሁዳዴ ፆም አጋማሽ ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል በየእምቱ ጸሎት እንዲደረግና ይህም ሂደት በቴሌቪዥን አማካይነት ለህዝብ እንዲደርስ ተደርጓል፡፡ የሂደቱ ማጠናቀቂያና ማሳረጊያ የረመዳን ፆም ፍቺ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
በኮሮና ውስጥ ሆነን ሁዳዴን ፆምን፡፡ በኮሮና ውስጥ ሆነን በዓለ ትንሣዔን አከበርን፡፡ በኮሮና ውስጥ ሆነን ረመዳንን ፆምን፡፡ ሁሉም በፈጣሪ ፈቃድ የሆነ ነው፡፡ አበው “እዬዬም ሲዳላ ነው” እንዲሉ ፆምም፣ ትንሣዔም፣ ኢድም በእምነታችን የአምልኮ ስርዓት መሰረት በጋራ ሊከናወን የሚችለው ምቹ ሁኔታ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ማንኛውንም ነገር በምንፈልገው መልኩ ማድረግ የምንችለው የፈጣሪ ፈቃድና ይሁንታ ሲታከልበት መሆኑንም ልብ ልንለው ይገባል፡፡ እነሆ አሁን ደግሞ በኮሮና ውስጥ ሆነን የረመዳን ፆም ፍቺን (ኢደል ፊጥርን) ማክበር ግድ ነው፡፡ መልካም ኢድ!
ጸሐፊውን በEmail: ahayder2000@gmail.Error! Hyperlink reference not valid. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 3842 times