Tuesday, 26 May 2020 00:00

ፌስቡክን በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 የኦቦ ዳውድ “ሰበር ዜና!”
ኦቦ ዳውድ ኢብሳ በአርትስ ቲቪ በነበራቸው ቆይታ ለኢትዮጵያ የአሃዳዊና ፌዴራላዊ ቅይጥ አወቃቀር ይሻላል የሚል ሐሳብ ሰነዘሩ!! “ሰበር ዜና!” “ዩኬን ውሰደው አሁን፤ ዩናይትድ ኪንግደም፤ ዌልስ፤ አየርላንድ፤ ስኮትላንድ እና ዋናኛው ኢንግላንድ፡፡ ይሔ ነው ዩኬን የፈጠረው፤ ፌዴሬሽን ነው፡፡ መንግስታት ናቸው እነዚያ፤ ራሳቸውን የቻሉ፤ ፓርላማ አላቸው፤ ካቢኔ አላቸው፡፤ አካባቢያቸውን የሚያስተዳድሩበት፡፡”
(ኦቦ ዳውድ ኢብሳ)
እንግዲህ በኦቦ ዳውድ ኢብሳ ገለጻ መሠረት፤ ዩናይትድ ኪንግደም ፌዴራል መንግስት መሆኗ ነው፡፡ አወቃቀሩን ለኢትዮጵያ የተመኙትም ዩኬ የምታራምደው የፌዴራል ሥርዓት ነው ከሚለው መነሻ ስለ መሆኑም መገመት ይቻላል:: እውነታው ግን ምን ይሆን?
በአጭር ቃል ዩኬ ፌዴራሊስትም አሃዳዊም አይደለችም፡፡ ኦቦ ዳውድ “ፌዴሬሽን” የሚለውን ቃል ከየት አምጥተው እንደተጠቀሙት ግራ ያጋባል:: ይልቁን በዩናይትድ ኪንግደም ሕገ መንግስትና አወቃቀር ላይ ጥናት የሚደርጉ አያሌ ምሁራን ለዩኬ መንግስታዊ አወቃቀር የአንድነት መንግስት (...Union State...) የሚለው ስያሜ ሥርዓቷን የበለጠ ይገልፃዋል ብለው ያስባሉ፤ እናም ዩኬ “Union state” ነች፡፡
በዚህ ዙሪያ  ከሁለት መፅሐፍት ያገኘሁትን መረጃ እንደወረደ ላስቀምጥላችሁ፦
እንግሊዛዊው Colin Turpin እና ስኮትላንዳዊው Adam Tomkins ከላይ በጠቀስኩት መፅሐፋቸው በአራተኛው ምዕራፍ፣ በ“Devolution and the structure of the UK” ንዑስ ርዕስ ሥር ያስቀመጡት ይህን ይመስላል፦
“It is used to be generally thought that the UK has a unitary constitution, like those of France, Italy, and Japan,The Netherlands, Sweden and New Zealand and unlike the federal constitutions of Germany, Switzerland, the US, Australia, Brazil, Canada, India, Nigeria and the Russian Federation. However, it may be that the better view is that the UK has a Union constitution that is neither straightforwardly unitary nor systematically federal in character…”
ፕሮፈሰር Robert Schutze ደግም ገና በመጽሐፋቸው መግቢያ ላይ፤ ባነሳነው ርዕሰ ጉዳይ ላይ እንደዚህ ይላሉ፦
“The United Kingdom is decidedly not a federal State. Centered on one –sovereign—Parliament, its legal structure is that of a unitary state; yet unlike classic ‘Unitary States’, it houses not just one but ‘four nations’ within its constitutional borders. The United kingdom is therefore sometimes described as a ‘Union’ or more often it is characterized as a ‘Union State’”
ዝርዝሩን በቀጣዩ ፅሑፌ የማነሳው ቢሆንም ‘Union State’ ሲባል መዋቅሩ የአሃዳዊውና የፌዴራል ቅይጥ ስለመሆኑ ከወዲሁ መገመት ይቻላል፡፡
ፕሮፈሰር Stephen Terney “The Paradox of Federalism, 2012” መፅሐፍ ምዕራፍ 4 ላይ “Union State” የሚለውን ስያሜ ያገኘውን ቅይጡን የዩኬ መንግስታዊ አወቃቀር “Fedralism in a Unitary State” በማለት ይጠራዋል፡፡ እዚያው መፅሐፍ ውስጥ በሌላ ሥፍራ ደግሞ ሉአላዊ ሥልጣንን ሳያጎናፅፍ፣ ራስን በራስ የማስተዳደር ሥልጣንን ከማዕከላዊው ከዩኬ መንግስት ወደ ንዑስ መንግስታት የሚሸነሽነውን “ዲቮሉሽን”ን ፕሮፈሰሩ “The poor cousin of Federalism” በማለት ይገልፀዋል፡፡ “Devolution” የፌዴራሊዝም የአጎት ልጅ መሆኑ ነው:: ለመሆኑ ዩናይትድ ኪንግደም ለምን ከሁለት የወጣች “Union State” ሀገር ተብለ ልትጠራ ቻለች? ኦቦ ዳውድም በምላሻቸው የጠቀሱት “Devolution” ምንን ያመለክታል? እውን የዩኬው “Devolution” ኦቦ ዳውድ እንደተነተኑት፣ ለአራቱ የዩናይትድ አባል ኔሽንስ ዘላቂ ሉዓላዊነትን (sovereignty) ያጎናፀፈ ነው? የቀጣዩ ፅሑፍ ይዘት የሚያተኩርበት አንኳር ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡
በመጨረሻም በኦቦ ደውድ ኢብሳን ቃለ ምልልስ ላይ ተንተርሰን “ኦቦ ደውድ ኢብሳ ለኢትዮጵያ “የአሃዳዊና ፌዴራላዊ ቅይጥ አወቃቀር ይሻላል” አሉ!! የሚል ሰበር ዜና ብንሰራ ጥፋተኞች አይደለንም ማለት ነው። ነገር ግን ኦቦ ዳውድ ኢብሳ ሌሎችን በአሃዳዊነት “እየፈረጁ”፣ በተቃራኒው አያሌ የአሃዳዊ አላባዎችን የያዘውን የዩኬ አወቃቀርን ኢትዮጵያ ውስጥ አምጥተን እንተግብር ማለታቸው የዓመቱ ምርጥ ተቃርኖ (Paradox) ተብሎ ሊመዘገብ ይችላል:: በእኔ እምነት፤ ይህ አለማንበብ የወለደው ስህተት በፖለቲካው ዓለም ለ50 ዓመትት ከቆዩ ፖለቲከኞች የሚጠበቅ አልነበረም፤ እሳቸውም ብቻ ሳይሆኑ ሌሎቹም የሀገራችን ፖለቲከኞች የንባብ ባሕል ላይ ብዙ መስራት ይጠበቅባቸዋል:: በነገራችን ላይ ይህ የንባቡ ጉዳይ ጋዜጠኞቻችንንም የሚመለከት ነው፡፡ የማደንቀው ጋዜጠኛ ደረጃ ኃይሌ በሚጠይቃቸው ጥያቄዎች ዙሪያ በቂ የዕውቀት ትጥቅ ይዞ ቢገባ ኖሮ፣ ልክ ያልነበረውን የኦቦ ዳውድን መግለጫ፣ ከሥር ከሥሩ እየተከተለ “ሉዓላዊ..ምናምን” እያለ ባላፀደቀላቸውም ነበር..ቢያንስ የዩኬውን!
(ከጌታሁን ሔራሞ ፌስቡክ)
“መሬት ይቅርታ መሆናችንን ሳናረጋግጥ፣ እውነት አለትን አንፈንቅል”
ጠዋት ነው፤ ትናንት፡፡ ውብ ነበር ማለዳው፡፡ አሮጌ መኪናዬን አሞቃለሁ፤ በሩን ከፈት አድርጌ ጸሀይ እየሞቅኩ:: ሁለት ወጣት ባለትዳሮች ከአንድ ልጅ (በግምት የ7 ወይም የ8 አመት ይሆናል) ከግቢ ሊወጡ፣ ወደ እኔ እየመጡ ነው:: አባትና ልጅ ወደ ኋላ ቀረት ብለዋል፤ ይጨቃጨቃሉ (ልጁን ይጨቀጭቀዋል):: ጆሮዬን ጥዬ አዳመጥኳቸው፡፡
‹‹እንዲያውም እውነቱን ካልተናገርክ አትሄድም፤›› አለና አባት ዞር ብሎ፣ ተረከዙ ላይ ተቀምጦ ልጁን ፊት ለፊት አፈጠጠበት::
‹‹ገብቶሀል! እውነቱን ንገረኝ፤
እግዚአብሄር የሚወደው አውነት የሚናገር ነው፡፡ አይደለም?››
ልጁ በመስማማት ጭንቅላቱን ነቀነቀ:: እናት ራቅ ብላ ትመለከታለች፤ ጨንቋታል:: ከፍቷታል፡፡
‹‹እውነቱን ተናገር! ምንም አትሆንም:: ካልተናገርክ ግን ነግሬሀለሁ፤ ቀደሀል አልቀደድክም?››
‹‹ቀድጃለሁ፡፡››
ልጁ ለመጀመሪያ ጊዜ ተናገረ፤ እጆቹን እያፋተገ፡፡
አባትየው፣ የልጁን ሁለት መዳፎች ከክንዱ የሚያረግፍ ጥፊ እጆቹ ላይ አሳረፈበት፡፡
ደነገጥኩ፡፡ አናገርኩት፡፡
ገላመጠኝና የልጁን እጅ ‹‹በፍቅር›› አንጠልጥሎ ከግቢ ወጣ፡፡
ቀኑን ሙሉ የልጁ ጭንቀት የአይኔ ብሌን ላይ እንደተሳለ ዋለ፡፡
ከዚህ በኋላ ይህ ልጅ እውነት ይናገራል?
አባትየው እውነቱን የፈለገው ለምንድነው?
እኛስ፣ ብዙዎቻችን፣ ‹‹ግዴለም፤ እውነቱን ንገረኝ/ንገሪኝ እና..›› የምንለው፣ እውነቱን የምንፈልገው ለምንድነው?
እንግዲህ እንዲህ ነው፣‹‹እውነት ተናገር እያልን፣ እውነት የፈጣሪ ናት እያልን፣ እውነት ሲናገሩ እየኮረኮምን፣ እውነትን ለልጆቻችን ባላጋራ አድርገን፣ ብዙዎቻችን ባደግንበት መንገድ ልጆቻችንን እያሳደግን ያለነው፡፡ በዚህ ዘመን ከተማ መሀል፣ በወጣት አባት ይህን ማየት ያሳዝናል፡፡ ውሻ እንኳን አድርግ የተባለውን፣ የታዘዘወን ሲያደርግ ለአፉ ሊጥ እንጂ ለወገቡ ፍልጥ አይቸረውም! ይህ እውነትን ማስተማር ሳይሆን፣ ከእውነት ማራቅ ነው፡፡ ልጆች ጥሩ ባህርያትን ሲያሳዩ መሸለም፣ መበረታታት፣ ቢያንስ በፈገግታ መታጀብ አለባቸው፡፡
ይህ ልጅ እዚህ የደረሰው እንዴት እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡ ደጋግሞ እውነት ተናግሮ ተቀጥቷል፤ መዋሸት ብቻ ሳይሆን፣ እውነት መናገርም አስቀጥቶታል፤ ስለዚህ ለእሱ ዋናው ጉዳይ ቅጣቱን፣ ቁጣውን ... የሚያቀልለትን መምረጥ ነው:: እውነትንና ሀሰትን ከሚያስከትሉበት ቅጣት አንጻር እየመዘነ ይከውናቸዋል፤ ከፍ ሲል ደግሞ ከሚያስገኙለት ጥቅም አንጻር:: እንዲህ ነው አድርባይ፣ መዋሸት እንቅልፍ የማይነሳው ትውልድ የተፈጠረው፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ፣ አባትየው እውነቱን የፈለገው ለምንድነው? ልጁን ለማስተማር ነው? ወይስ የእሱን ቅጣትና ፈር የሌለው ጩኸት ተጠየቃዊ ለማድረግ? የጎበጠ አባትነቱን በምክንያት ለመደገፍ? ... ማናችንም ብንሆን፣ ‹‹ግዴለም፣ እውነቱን ንገረኝ/ንገሪኝ...›› ብለን እውነቱን ለማወቅ ከመቆፈራችን አስቀድሞ እውነቱን ለምን እንደምንፈልገው ማወቅ አለብን:: እውነቱን መሸከም እንደምንችል፤ ለበጎ እንደምናውለው እርግጠኛ መሆን ያሻል፡፡
ሚስት ባሏን፣ ‹‹ማግጠሀል፣ አልማገጥክም? ብቻ እውነቱን ንገረኝ›› የምትለው በስጋ መቀረጣጠፊያዋ ልትቀረጣጥፈው ከሆነ፣ ባልም እንዲሁ የተቀባበለ ሽጉጥ ትራሱ ስር ደብቆ፣ ፍቅረኛም አሲድ በጀሪካን በረንዳ ላይ አስቀምጦ ከሆነ፣ . . . እውነቱ ያሉበትን ህይወት በበጎ ለመለወጥ ካልተጠቀሙበት፣ የሚፈልጉት ያሰቡትን መጥፎ ለመፈጸም ስሜታዊ ብርታት እንዲሰጣቸው ከሆነ፣ ውሸቱ ነው ከእውነቱ በላይ የሚጠቅማቸው፡፡ እውነቱ ጠቃሚ የሚሆነው ይቅርታ አውርደው በፍቅር ለመሞከር፣ ወይንም በቃን ብለው በሰላም ለመለያየት ካደረጋቸው ብቻ ነው፡፡
መንግስትም እንዲሁ ነው፤ ጥፋተኛ ሲናዘዝ ዶኩመንተሪ ሰርቶ፣ በየቲቪው አስጥቶ፣ በማህበረሰብ ዘንድ አሳጥቶ፣ ... ትንሽ አስሮ ወይ ነጻ ብሎ ይለቃል (አሁን ይህ እየቀነሰ ቢሆንም):: በሰጠኸው የእውነት ቃል በማህበረሰብ አስነውሮ፣ . . . ይለቃል፡፡
ይህም ከተነሳንበት አባት ድርጊት አይለይም:: እውነት እፎይታና ነጻነትን ይዞ የሚመጣ ይመስለናል፡፡ እውነት ብቻውን ነጻ አያወጣም:: እውነት ድንጋይ ነው፣ አለት፡፡ አለት ሆነን ከተቀበልነው ለውጥ አያመጣም፣ ‹‹አህያ ለአህያ ቢራገጥ፣...›› አይነት፡፡ መስታወት ሆነን ከጠበቅነው ይሰብረናል፡፡ መሬት ሆነን ከጠበቅነው አይጎዳንም፤ ያረፈበት ጎድጓዳም ሰነባብቶ ይሞላል፡፡ መሬትነት ይቅርታ ነው፡፡ መሬት ይቅርታ መሆናችንን ሳናረጋግጥ፣ እውነት አለትን አንፈንቅል፡፡
(ከበድሉ ዋቅጅራ ፌስቡክ)

የፖለቲከኞቻችን የስልጣን ጥማት?
የተከናወኑ በጎ ነገሮቹ እንደተጠበቁ ሆነው፣ ሃገራችንና ሕዝቦቿ ሶስት ተከታታይ ዓመታትን በማያቋርጥ ማዕበልና መናወጥ ውስጥ ሆነው አሳልፈውታል:: ሞትን፣ ስደትንና መፈናቀልን እንደ አመጣጡ ከነጠባሳውም ቢሆን በጽናት በማስተናገዳችንና እንደ ሃገር ሳንበታተን በመቀጠላችን የከፋውን ጊዜ አልፈናል ብዬ እገምታለሁ። አልፈናል ስል ግን፣ እስከ አሁን ማለቴ ነው? አሁንስ፣ አሁንማ መልካቸውንና ቅርጻቸውን የሚለዋውጡና ለብሶታቸውም ሆነ ለራዕያቸው ትናንትና ብቻ መኖር የሚፈልጉ የፖለቲካ ሃይሎች፤ በሀገራችን ጉዳይ ላለመግባባታችን መሰረታዊ ችግርነታቸው እያገረሸ ስለሆነ፣ መነጋገር አለብን ባይ ነኝ፡፡
ለችግራችን መፍትሔው በእጃችን ለመሆኑ ብዙ ምሳሌዎችን ማቅረብ ይቻላል። እስቲ፣ የሰሞኑን ገጠመኝ እናጢን። ለወራት ያህል የፖለቲከኞቻችን ኡኡታ ጋብ ብሎ በነቂስ መተሳሰብ፣ መተጋገዝና መረዳዳት ስንጀምር፣ እንደ ሃገር ሳንፈርስ የቆየነውና አስፈሪውን ማዕበል የተሻገርነው ሕዝብ ከሕዝብ ጋር በመጋጨቱ ሳይሆን በፖለቲከኞቻችን አቀጣጣይነትና፣ አዋሻኪነት እንደነበረ ለመገንዘብ እንችላለን። ከጥቂት የጥሞናና የእፎይታ ጊዜ በኋላ እንደገና ወደ መድረክ ሲመለሱ ደግሞ፣ የምረዳው ነገር ቢኖር የከፋፋይነትና የማወክ አቅማቸውን ይሆናል።
የአደረ አፋሽ ፖለቲከኞቻችን የስልጣን ጥማቸውን እንዲያረኩና ትንንሽ ዘውድ እንዲጭኑ ለማገዝ ሲባል፣ ሃገሩን ለማፍረስ ሕዝብ ፈቃደኛ አልሆንም አለ እንጂ፣ እነዚህ ሃይሎች ቀደም ሲል በሕዝብ የተቀሰቀሰውን የሰብአዊ መብት፣ የእኩልነትና የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ በመቀልበስ፣ ትንንሽ ሀገር ፈጥረው፣ ስልጣን ለመረከብ ተዘጋጅተው ነበር። ዛሬ ደግሞ ሕገ መንግስታዊ ክፍተትን በምርጫ ስም በማራገብ፣ መላውን ሀገር ለማንበርከክና በሽግግር ስም ስልጣን ለመጋራት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡
ፖለቲከኞቻችን በሕዝባቸው ላይ በዚህ ደረጃ ለምን ይጨክናሉ? ለሚለው ጥያቄ የብዙዎች መልስ እንደ ግንዛቢያቸው ፈርጀ ብዙ ሆኖ እናገኘዋለን። በርካታዎቹ የስልጣን ጥማት የፈጠረው መታወር ሲሉት፣ ሌሎች ስር የሰደደ ሃገርን የመክዳት አባዜ፣ ቀሪዎች ደግሞ የተረኝነት እብደት፣ ቀላል የማይባሉት ደግሞ በገዢ መደብነት ሂሳብና በቀልን የማወራረድ እብደት ያናወዛቸው ናቸው ይሏቸዋል፣ ብዙዎች ደግሞ ታሪክን እንደገና የመጻፍ ኋላ ቀርነት ያሰከራቸው እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
ዛሬ ሀገራችን በታሪካችን ከምናውቀውና ካሳለፍነው በእጅጉ የከፋ፣ ባልተለመደ ሁኔታ የገነነና ሁሉንም ዓይነት እብደቶች፣ ቅዠቶችና ልክፍቶችን አካታ በማስተናገድ ላይ ነች፣ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ፖለቲከኞችም ተቀዳሚ ተግባራቸው፣ ፖለቲካ መተንተንና ምድራዊ መፍትሔ መሻት ሳይሆን በሃይማኖት ማተራመስ፣ ትንቢትና ራዕይ መቀመር፣ ለሕዝብ ንቀትን፣ ዛቻና እብሪት ማከፋፈል ሆኗል፡፡
ለ29 ዓመት በሕገ መንግስታዊ ማነቆ፣ በአስተዳደራዊና በፖለቲካዊ አፈና እንዳይመረመርና እንዳይፈተሽ እድል ነፍገውት፣ ከዘመኑ ርቆና ቀንጭሮ የቀረ ሕገ መንግስት ላይ የሰፈረ “አንድ” አንቀጽ ክፍተት መስሎ ስለታየ ብቻ በሽግግር መንግስት ስም ስልጣን ካልተጋራን፣ በኮሮና ሕዝብ እየተጨነቀም ቢሆን ምርጫ ካላደረግን ጦር እናወርዳለ፣ እንገነጠላለን፣ ሀገር እናፈርሳለን የሚል አማራጭ ማቅረብ ከስልጣን ጥማት፣ ሕዝብ ላይ ከማቄምና ሕዝብን ለመበቀል ከሚነሳ ልክፍት ውጭ፣ ጠዋትና ማታ በስሙ ለሚለፈፍለት ሀገርና ሕዝብ ታስቦ እንዳልሆነ ግልጽ ነው።
በዚህ ዓይነት የፕሮፓጋናዳና የውዥንብር ማዕበል ውስጥ ተዘፍቆ የሚኖር ሕዝብ፤እስከ መቼ ድረስ ሳይወናበድ የሀገሩን ሕልውና አስከብሮ፣ የትውልድ አደራውን ይወጣል የሚል አሳሳቢ ጥያቄ አለኝ፡፡
ከሀገር ህልውና ቀጥሎ የሚመጡ የፖለቲካ ልዩነቶቻችን እንደተጠበቁ ሆነው፣ በእኩልነት ላይ ለተመሰረተች ሀገራችን እንደ ሕዝብ ምን ማድረግ አለብን? ያደረ አፋሽ ፖለቲከኞች እንዲያፈርሱን እንፍቀድ ወይስ በአንድ ቃል ፖለቲካ በሕዝብ ይሁንታ ወደ ስልጣን መወጣጫ መድረክ እንጂ ሃገር ማፍረሻ መሳርያ አይደለም እንበል?
(ከሙሼ ሰሙ ፌስቡክ )

የዶ/ር ቦሎድያ ሰቃይ ቀልዶች!
እስቲ በዶ/ር ጌታቸው ቦሎድያ አድክም እይታና ቀልዶች ዘና በሉ ፥ ቀልድ አእምሮን ያፍታታል፤ ፕሊስ ቀልድ ውደዱ፤ በተለይ ቁምነገር አዘል ቀልድ ከሆነ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደ ማለት ነው፤ ምክንያቱም ቁምነገርም እናገኝበታለን እንዝናናበትማለን።
...ዶ/ር ጌታቸው ቦሎድያ በAAU የባዮኬሚስትሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ነበር። አሁን ተረት ሆኑዋል። የሳይንስ ፋካልቲ ተማሪ ዶ/ር ጌታቸውን በአባቱ ስም ‘ቦሎድያ ‘ማለት ይቀናዋል።እኛ ቦሎዲያ ላይ አልደረስንበትም። ቀልዶቹ ላይ ነበር የደረስነው።እናም ስራ ከምንፈታ ውስጥ አዋቂዎች የነገሩንን እናካፍላችሁ።
•አንድ፦
...ሁሌም ኮርሱን ማስተማር ሊጀምር ሲል እንዲህ ይላል፤
“Come and drink from the fountain of knowledge. Here it is... in front of you...one of the best Biochemist in the world and also the only one in the horn of Africa...”
•ሁለት፦
...በደርግ ጊዜ ነው። አንዴ ወደ አውሮፓ ሊያቀና ሲል ዳጎስ ያለ ብር አስይዝ ይባላል። ይሄኔ “ለምን ሲባል?”ይላል ቦሎዲያ፤
“በዚያው እንዳትጠፋ ነው” ሲሉት፤
“እኔ ጌታቸው ቦሎዲያ ነኝ አገሬን ለማንም መቶ አለቃና ሻለቃ ጥዬ የምጠፋ! ወይ አለመተዋወቅ።”
•ሶስት፦
...ዶ/ር ቦሎድያ አንድ ተማሪውን ጸሃፊው ብራዲ የሆነውን “ጄኔራል ኬሚስትሪ” የሚባል መጽሐፍ ይዞ ያገኘዋል። (ያን ጊዜ ያ መጽሐፍ ለፍሬሽ ማን ቴክስት ቡክ ነበር።) ይቀበለውና አገላብጦ ካየው በኋላ፤
“እንዴ ብራዲ መፃፍ አሳተመች!?...አብረን ስንማር እኮ ጥያቄ ፈርታ ከኋላ ነበር የምትቀመጠው።”
•አራት፦
...አራት ኪሎ ሳይንስ ፋካልቲ ውስጥ አንድ ኤሊ አለች። ዩኒቨርስቲው ሲመሰረት ጀምሮ እዚያው ግቢው ውስጥ ነው የነበረችው። ያው ኤሊዎች የእድሜ ባለፀጋ ስለሆኑ ነው። ጌታቸው ቦሎዲያ ኤሊዋን ሲያያት እየሳቀ፤
“ጉድ ሞርኒንግ ፕሮፌሰር ኤሊ!...
“ጉድ አፍተርኑን ፕሮፌሰር ኤሊ!” እያለ ነበር አሉ የሚጠራት
“ለምንድን ነው?” ሲሉት፤
“እንኳን እሷ ... እነ እከሌ ፣እነ እከሊትም አስር አመት ዩኒቨርስቲ ስለቆዩ ብቻ ረዳት ፕሮፌሰር ተብለው የለ እንዴ!”ይላል።
•አምስት፦
...እንግዲህ በደርግ ወቅት ማታ ላይ በሬዲዮ በሰማው ዜና ጠዋት ክፍል ገብቶ ያላግጣል። የሰማውን እየደገመ፤
“ፐ! ትናንት የአርባጉጉ ገበሬዎች ...የሬገን አስተዳደርን ተቃውመው ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ!!...
...Dear students...Do you think that the Arbagugu peasants know whether the Ragen administration is a human being or a computer machine?”
•ስድስት፦
....እንደ ራሱ በጣም የሚመካባት ሴት ልጁ ማትሪክ ወስዳ አንድ “ቢ”ተቀላቀለባት።
“ጂኒየስ ናት ስትል አልነበር እንዴ?”አሉት ፍሬንድስ
“ምን ላድርግ...የእናቱዋ ጂን ጉድ ሰራኝ!”
•ሰባት፦
...ቦሎዲያ ከአንድ ተማሪ ጋር ተደባደበ አሉ ፥ ይህን የሰማው የዩኒቨርስቲው አመራር ለማባረር ፈጣን ነውና የተማሪውን መባረር የማስታወቂያ ሰሌዳው ላይ ለጠፈ። ቦሎዲያ ሲሰማ ወረቀቱን ገንጥሎ፣ ፕሬዚዳንቱ ዶ/ር አብይ ክፍሌ ዘንድ ሄደለት ፤
“አብይ ምን አግብቶህ ነው ይህን ምስኪን የምታባርረው?...እኔን እንጂ ዩኒቨርስቲውን አልደበደበም!...እኔን ለመታኝ ደጅ ሳገኘው በቡጢ አቀምሰውና ብድሬን እመልሳለሁ። ልጁን አሁን በፍጥነት ወደ ትምህርቱ መልሰው።”
•ስምንት፦
...አንዴ ከስድስት ኪሎ ወደ አራት ኪሎ በመኪናው ሲመጣ ተማሪውን ያገኘዋል።
“አንቺ! ነይ ግቢ” ይለዋል።አብሮት የነበረ ሌላ ተማሪም ይገባል...
“አንቺን አላቅሽም...የምን ተማሪ ነሽ?”
“የፖለቲካል ሳይንስ“ ይላል ልጁ።. ..አራት ኪሎ ደርሰው ሲወርዱ እንዲህ አለው ልጁን፤
“...Keep the politics to yourself ...but leave the science to me “ ...
(ፖለቲክሱን ራስሽ እዛው ያዢው፤ ሳይንሱን ግን ለኛ ተይልን እሺ!”)
(ከመልዕክተ ስንታየሁ ቴሌግራም)

Read 8427 times