Monday, 25 May 2020 00:00

ግንቦት - የመንታዎች እናት!

Written by  በአዲሱ ዘገየ
Rate this item
(0 votes)

   ወርኀ ግንቦትን ስንፈክር አንደኛ የግንቦት ስያሜ ምንነት፣ ሁለተኛ ግንቦትን ልዩ የሚያደርጉ ቀዬአዊ፣ ሀገራዊ፣ አሕጉራዊና ዓለማቀፋዊ በረከተ-መርገማትን በወፍ በረር እንቃኛለን፡፡ ግንቦት የሚለው ወርኀ ስም ገነበ ከሚለው ግሥ የወጣ ሲሆን ግንብን፣ ቤትን፣ ጎጆን የማቆም፣ የማነጽና የመገንባት ሂደት ገላጭ ነው፡፡ እንዲሁም ግንብን፣ አጥርን ቤትን ማፍረስ፣ መቆፈር፣ መማስና መሰርሰር ማለት ነው፡፡ ስለሆነም በግብሩ የሚያመለክተውን ግንባታ እና ጸረ-ግንባታ (ለልማት ተነሺ የሚል ስያሜ ለፈራሽ ቤቶች እንደሚቀጸልላቸው ሁሉ) እንቅስቃሴዎች መታወቂያ የሆነላት/ለት ወር ናት/ነው፡፡
በሌላ ቦታ ደግሞ የስሙ አወጣጥ ገቦ/ጎን/ጎረ + ክረምት ከሚሉ ቃላት ኅብረት ተመስርቶ፣ በሂደት ለውጥ አሳይቶ ግንቦት በሚለው ቃል መጽናቱን ምንጮች ይገልጻሉ:: ፍቺዋም የክረምት ወቅት ለሚብትባት ለወርኀ ሰኔ ተጎራባችነቷን ለማመልከት ነው፡፡ ማክሰኞ የሰኞ ማግሥት እንደምትባል ሁሉ፡፡ በዚህ የጉርብትና ቤት ገብተን ግንቦትን የክረምት ዋዜማ ወይም የቅርብ ታላቅ እህት ማድረግ እንችላለን:: በአብዛኛው የሀገሬው አርሶ አደሮች ዘንድ ግንቦት እና ሰኔ ወሳኝ ርምጃ የሚከወንባቸው ወራት በመሆናቸው በንቃትና ጉጉት ይጠበቃሉ:: ስለዚህም ከቤት፣ ከድግስ ድንኳን፣ አዳራሽና ሰቀላ መውጣትንና በማሣዎች ላይ ጥማድ በሬዎችን እየተከተሉ መዋል ግዴታ እንደሆነ በኑሯቸው መረዳት ይቻላል፡፡  
የሀገሬው አርሶ አደር፡-
ግንቦት ሰኔ መጣ ሸተተኝ አፈሩ፣
አንሳኝ አንሳኝ አለኝ ሞፈሩ ቀንበሩ፡፡
(የሕዝብ ሥነቃል)
ብሎ ወደ ማሳው ይሰማራል፡፡ ስለዚህ ወርኀ ግንቦት አርሶ አደሮች የመሬት/ማሳ/እርሻ/ምድር ፍንቀላ፣ አረሳ፣ ጭፍለቃ የሚከውኑባት ምርጥ ወር ናት፡፡ ወቅቱን ርጉው የመሬት ባህርይ እንደሚነግሥበት በጸደይ ትንታኔ አይተናል፡፡ አርሶ አደሩ ሞፈርና ቀንበሩን አንስቶ ሲያበቃ ወዲያውኑም የሚጠምዳቸው ጥማድ በሬዎችን ለሥራ ሲያነሳሳ፣ ሲያሞካሽና ሲያወድስ ይውላል፡፡ ግንቦትን ስያሜው ካደረገ የአዝመራ ዓይነት አንዱ ግንቦቴ የሚል ስም የተሰጠው የገብስ ዓይነት ነው:: “አትኩራ ገብስ ጎመን ባወጣው ነፍስ!” ቢባልበትም ጎመንን የሚያስከነዳ የምግብ ግብዓቶችን የያዘው ግንቦቴ ገብስ፣ በግንቦት ተዘርቶ በጳጉሜ ይደርሳል፡፡
ግንቦት በወዲያ ማዶ ካሉት ወራት መካከል ጥቅምትን በወዳጅነት ትመርጣለች:: ጥቅምትን በአቻነት የመምረጫ መስፈርቷ የሁለቱም ወራት መባቻዎች በተመሳሳይ ቀን መዋላቸው ነው፡፡ ስለዚህ “ቁርጥ እትማማቾች” ብሎ መደምደም አይቻልም፤ የየራሳቸው የልዩነት መልኮች አላቸው እንጂ:: ለምሳሌም ጥቅምት ወር ከክረምት/ከመከራ /ድንቁርና/ጨለማ/ አታካች የኑሮ መልክ መሰናበቻ ወር ናት፡፡ ግንቦት ደግሞ በተቃራኒው ወደዚያ አታካች ወቅት መግቢያ ዋዜማ ናት፡፡ ጥቅምት ብርዳም፣ ግንቦት ንዳዳም ወራት ሲሆኑ፣ ሁለቱም የሚተዳደሩት በነፋስ አማካይነት መሆኑ ያመሳስላቸዋል፡፡
ግንቦት ከታኅሣሥ፣ የካቲት እና ጳጉሜ ወራት የምትዛመድበት የቅርበት መልክ አላት:: የተጠቀሱ ወራት ግንቦትን ጨምረው ሰማይ ተከፍቶ የሚታይባቸው ዕለታትን ይዘዋል:: ሰማይ ሲከፈት (በኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ. የትርጓሜ መጻሕፍት አንጻር) ደግሞ በምድር ያሉ ሰዎች የሚያገኙት አንዳች ረቂቅ ሀብት አለ፡፡ ጥበብ፣ ዕውቀት፣ ምክር፣ ፍልስፍና ወዘተ ይገለጣሉ ተብሎ የሚጠበቅባቸው ልዩ ወራት ናቸው፡፡ በዚህ ዕለት ዕውቀት፣ ፈጠራ፣ ግኝት፣ ጥበብ፣ ፍልስፍና ወዘተ የሚፈልቁበትና የሚመነጩበት በር በሰማይ ይከፈታል ማለት ነው፡፡ አራቱንም ወቅቶች እንዲያዳርሱ የተለዩ ወራት እና ቀናት አሉ:: ስለዚህም ዕውቀትና ጥበብማ የክረምት፣ ወይም የመፀው፣ ወይም የበጋ፣ ወይም የጸደይ፣ ካንዱ ወቅት ሌላው፣ ከቀዳሚው ወር ኋለኛው ይበልጣል/ያንሳል እንዳይባል የዕውቀት መገለጫ አጋጣሚው በአራቱም ሁሉ እንዳለ ያመላክታሉ፡፡
ወርኀ ግንቦትን በልደታ አለመጀመር አይቻልም፡፡ ወይም ልደታን ዘሎ ሌሎችን ማውሳት ያጎድላል፡፡ የግንቦት ልደታ በዓል አከባበር ምንነትና ለምንነት መግለጫ የሚሰጡ ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች ቢኖሩም፤ ከሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በተጨማሪ የሚተገበሩ (በእምነቱ መሪና ተከታዮች ዘንድ እንደ ባዕድ አምልኮ የሚቆጠሩ) ሀገረሰባዊ የአምልኮ ልማዶች አሉ፡፡ ቅድመ ኦሪት፣ ድኅረ ኦሪት፣ ቅድመ ክርስትና ድኅረ ክርስትና እምነቶችን የሚወክሉ አሻራዎች ባንድነት የሚቀነቀንባት ቻይ፣ አካታች ወር ግንቦት ናት፡፡ የዛሬን አያድርገውና (በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት) የሃይማኖት መለያ ክርን/ማተብን፣ ወይም ቆብን፣ ወይም የአመጋገብ ልማድን መስፈርት ያላደረገ፣ አንድ አድራጊ የጋራ ማዕድ በግንቦት መባቻ ይቆረሳል፡፡ ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ የየአካባቢው ማኅበረሰብ ዘርና እምነት ምክንያት ሳያደርግ፣ አዳሜ እና ሔዋኔ ባንድነት ተሰባስበው ይለማመኑባታል፤ ይሳሉባታል፤ የቀደመ ስዕለታቸውን ያስገቡባታል:: ልዩ እና ባዕድ መሆን በዚህ ከበራ ላይ ባለመሳተፍ የሚገለጽ ጸረ-አንድነትን ይወክላል፡፡
ይህን በተመለከተ ፈቃደ አዘዘ (ዶ/ር) የጻፉትን መጥቀስ ግድ አለኝ፡፡ አንደኛ ክርስትና፣ እስልምና ይሁዲና፣ እንዲሁም ማርክሲዝም፣ ኮምዩኒዝም፣ ዴሞክራሲ፣ ፌዴራሊዝም ወዘተ ከላይ በገዥ ሥርዓታት በኩል የገቡ ናቸው፡፡ ባንድ በኩል ደግሞ ሀገር በቀል ሃይማኖቶችና እምነቶች ደግሞ ከጥንት ጀምሮ የነበሩና ዛሬም ድረስ ደረታቸውን ነፍተው ያሉና ከታች ከተጠቃሚው ማኅበረሰብ ውስጥ የተወለዱ ናቸው፡፡ እነዚህም ስለ እኛ እና ስለ ሀገራችን የሚነግሩን ብዙ እውነት መያዛቸው አያጠራጥርም፡፡ ሁለተኛ፣ ሰው የሚያደርገውን የሚያደርገው፣ ለሰርካዊ የኑሮ ችግሮቹ ሰርካዊ መፍትሄ ፈልጎ ቀኖናዊ ሃይማኖቶቹ፣ ብዙ ጊዜ፣ መልስ ለመስጠት ረዥም ጊዜ ስለሚፈጁ፣ ሀገር በቀሎቹ ደግሞ በየጊዜው፣ ሰሩም አልሰሩም፣ የወዲያው መልስና ተስፋ ስለሚሰጡ ሊሆን ይችላል:: (ጠቅለል አድርጌ ጠቅሻለሁ)፡፡
በግንቦትና ሰኔ ወራት ዘመናዊ እምነቶች እና የሀገር በቀል ልማዶች ባንድነት የሚከወኑባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ:: እነዚህም ጊዜያዊና ወቅታዊ መፍትሔዎችን ለማግኘት ሀገሬው የሚመርጣቸው ናቸው፡፡ ቀናቱ መንታና ከዚያ በላይ እምነቶች ባንድ መድረክ ላይ እንዲከወኑ ለማድረግ ሲመረጡ ይታያል፤ በተለይም የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ. ዓመታዊ የታቦታት ንግስ ክብረ በዓላትን ተገን ያደረጉ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል መስከረም/ግንቦት አንድ፣ መስቀል፣ ጥቅምት/መጋቢት/ሐምሌ አምስት፣ ኅዳር/ጥር/ሰኔ አስራ ሁለት፣ እንዲሁም የልደት፣ ጥምቀትና የፋሲካ በዓላት ተጠቃሾች ናቸው፡፡
የሀበሻዋ ወርኀ ግንቦት በጎርጎርሣውያኑ አጠራር የወርኀ ሜይ/May ሃያ ሶስት፣ እና የጁን/June ሰባት ቀናትን ደባልቃ ትይዛለች፡፡ በሀበሻዊ የኑሮ ዘዬ ግንቦት ለጋብቻ እንደማትመረጥ ሁሉ፣ የፈረንጆቹ ሜይ ለጋብቻ የማትመረጥ ዕድለ-ቢስ ወር ናት፡፡ ስለዚህ ጋብቻ መፈጸም የመጥፎ ምልኪ ምልክት ሆኖ ይቆጠራል፡፡ የግንቦት ተምሳሌታዊ ፋይዳ ብርሃነ-ጸሐይ፣ ሙቀተ-ጸሐይ፣ ኃይልን የተመላች ወር ናት፤ ይህቺውም ፍቅርን ታጠነክራለች፤ ዕውቀት /ብርሃን/ጥበብ/ ፍልስፍና፤ የፈጠራ ግኝቶች ካለመኖር ወደ መኖር የሚመጡባት ወር መሆኗ የውስጥና የውጭ ምስክሮች ይናገራሉ፡፡
ግንቦትን ስንፈትሽ ትኩረት ከምናደርግባቸው አላባዎች መካከል የወሯ መጋቢ ኮከብ አንዷ ናት:: ወርኀ ግንቦት ከአራቱ የሥነፍጥረታት መገኛ አሃዶች መካከል መሬት የምትነግሥበትና መጋቢ ኮከቧም ነፋስ (ነገር ግን ጥንድ/መንታ/ሁለት) የሆነችላት ናት፡፡ የኮከቧ ስም በዐረቢ (ዐረብኛ) አልጀውዛ፣ በግእዝ ገውዛ፣ በእንግሊዝኛ ጄሚኒ/Gemini ትሰኛለች፡፡ ገውዝ፤ የተክል ስም ስትሆን ፍሬዋ የምትበላ፣ መንታነት ያላት የዕጽዋትና አታክልት ወገን ናት፡፡ ይህቺ ኮከብ መለያዋ መንታነት/ጥንድነት ሲሆን ትእምርታዊ ፋይዳዋ ሸሪክነት (በንግድ፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ ኑሮ ወዘተ) የሚታይባት፣ የደባልነት ኑሮ መጀመሪያ፤ የዝምድና/ግንኙነት ማጠንከሪያ፤ ሁለትዮሻዊነት (የመንቶዎች ሕግ) እና ሚዛናዊ የሀብት ክፍፍል (የጾታ) ግብሮችን ታስተናግዳለች፡፡
ግንቦት ኅጸጽ/ጉድለት የምታስተናግድ ወር መሆኗ በአዋቂዎች ይነገራል። ይህ ጉድለቷም በአርነት ጉዞ ላይ የነበሩ እስራኤላውያን በሰሩት ጥፋት በመቅሰፍት የተቀጡባት ወር ናት:: ግንቦት ላይ ጋብቻ የማይከወነው “አየሩ ተስማሚ ስላልሆነ!” የሚል ሰበብ ይቀርባል:: በሌላ በኩል ደግሞ የኮከቧ ምስል ባልና-ሚስትን ወይም ወንድና-ሴትን ስለምትወክል ወሩ በኮከቧ በመያዙ በግንቦት መጋባት እንዳልተፈቀደ ምሳሌ ይሰጥባታል፡፡ በግንቦት ወር ውስጥ ጋብቻ የሚከለከልበት ምክንያት የግንቦት ቁስል ባለመዳኑ ነው፡፡ ሙሽራውና ሙሽሪት ራሳቸውን ወይም ቁስላቸውን በፍጥነት ለማሻር ይረዳቸው ዘንድ የጋብቻ ቀናቸውን ከግንቦት ውጭ ባሉ ወራት ቢያደርጉ ይመከራሉ፡፡
በግንቦት ትዳር መመስረት ብቻ አይደለም የሚከለከለው፣ ቤት መሥራት ጭምር እንጂ:: ለዚህ ምክንያት ከሚጠቀሱት አንደኛው የሰሎሞን ቤተ መቅደስና የባቢሎን ግንብ መሰራት የጀመሩት በዚሁ ወር በመሆኑ፣ ሁለቱም ቆይተው በመፍረሳቸው ግንቦት ቤትን ታፈርሳለች ይባልባታል፡፡ “ከሰው መርጦ ለሹመት፣ ከእንጨት መርጦ ለታቦት” እንዲል ዕጽዋትና አትክልት የተቆረጡበት ወቅትና ወር ማንነት ለተፈለጉበት ዓላማ መዋል አለመዋላቸውን ይወስነዋል፡፡ ስለዚህ በሚያዝያና ግንቦት የተቆረጠ እንጨት የሚነቅዝ በመሆኑ፣ የታነጸው ቤት ለምስጥ እንደሚዳረግና ቆይቶም እንደሚፈርስ ይገመታል:: በግንቦት የተቆረጠ ዛፍ ጉቶውም ቢሆን ዳግም አያቆጠቁጥምና በግንቦት ቤት አይሰራም የሚል የሀገሬው እምነት አለ፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ከእንጨት የሚመረጡትን የያዘችው ወር ጥቅምት ናት:: ምክንያቱም በጥቅምት ወር የተቆረጠ ዛፍ አይነቅዝም፡፡
የሰው የሥራው ዓይነት “ስሙ ማን ነው?” የሚል ጥያቄ እንዲቀርብበትና የሰውየውን፣ የሀገሩን፣ የቋንቋውን፣ የወላጆቹን ወዘተ ማንነትና ከየትነት ለማወቅ ያነሳሳል፡፡ ስለዚህም የወራትን ስያሜዎች ከውስጥ/በሀገሬው እና ከውጭ /በምዕራባውያን ስያሜ፣ ብያኔ፣ የጽንሰ ሀሳብ ማዕቀፍ ወዘተ አንጻር ትንታኔና ፍካሬ መስጠት አያጎድልም:: ይህም አንድነት ልዩነትን ለመረዳት፤ አንድም ሰው ድንበርና ጠፈር፣ ጊዜና ወቅት የማይወስነው አእምሯዊ አቅም እንዳለው ለማሳየት፤ አንድም የተለያዩ የሕይወት ልምድ ያላቸው አካላትን ለማናበብ ለማመሳከር፣ አእምሮና ልብን ብሩህ የሚያደርግ የዕውቀት ማብሪያ መሣሪያ በሁሉም ዘንድ መኖሩን ለመረዳት ያግዛል:: በጎርጎርዮሳውያኑ አቆጣጠር ከሜይ 9 እስከ ጁን 23፣ በእኛ ከግንቦት 1-30 ቀናት ድረስ የሚከበሩ በዓላትን በዓይነት፣ በግብር፣ በባህርይና መልክ በማስተሳሰር ወርኅ ግንቦትን እንቃኛለን፡፡
፩. ፈጠራና ግኝት፡- የከዋክብት ፍካሬ ሰነዶች የግንቦት ኮከብ የሚወልደውና የሚያሳድገውን ሰው መለያ ባህርይ ፍንጭ ይሰጣሉ፡፡ ይኸውም ብልሕ፣ ጥዑመ ልሳን/ድምጻዊ፣ ራሱን ጠባቂና ርጋታ ያልተለየው፣ ቀልድና ዋዛ ዐዋቂ ሲሆን፣ ነገር ሁሉ በቶሎ ይገለጽለታል፡፡ ለነገሩ የፀሐይ ኃይል መጠንከርና ማየል ተምሳሌታዊ ፋይዳ ልብን በማብራት ነገር ሁሉ እንዲገለጽላትና እንድትባንን ያደርጋታል፡፡ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በዓለም መድረክ እንዲተዋወቅ ያደረገውና ፋና ወጊ ሥራውን የቅዱስ ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤትን በመክፈት በመምህርነት፣ በተመራማሪነትና በደራሲነት ያገለገለው ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ነው፡፡ ፕሮፌሰር አሸናፊ “የጥቁሮች ሙዚቃ ምንጭ/ሥር” በሚል ጥናቱ፤ ኢትዮጵያዊውን የዜማ ሊቅ የቅዱስ ያሬድን የዜማ ውጤቶች ያስተዋወቀበትን ሥራ አሳትሟል፡፡ የቅዱስ ያሬድ መንፈስ ሳይጋባበት አልቀረምና የተወለደበት ወር በ1930 (በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የተጠቀሱ የዘመን መግለጫ ቁጥሮች ሁሉም ዓመት ምሕረትን የሚወክሉ ናቸው!) ሲሆን፣ ያረፈበት ወርም (1990) ቅዱስ ያሬድ ካረፈበት ወርኀ ግንቦት ጋር አንድ ነው፡፡ “ጻድቃን ሳይቀጣጠሩ ይገናኛሉ” አያስብልም?
ግንቦት 1945 በታላቋ ብሪታንያ የተካሄደ የንጉሳዊ ዘውድ ውርርስ (ወደ ንግሥት ዳግማዊት ኤልሳቤጥ) ሲዘዋወር ይህንን ዘውዳዊ ሥርዓተ-ሲመት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጥታ ስርጭት የቴሌቪዥን መስኮት ማስተላለፍ ተችሏል:: እንዲሁም ግንቦት ወር 1972 ላይ የአሜሪካው ሲ.ኤን.ኤን. የቴሌቪዥን ጣቢያ ስርጭት የጀመረባት ከመሆኗ በላይ፣ የተንቀሳቃሽ ምስል መቅረጫ (ቪዲዮ ካሴት ሪከርዲንግ/ቪካሪ) ለመጀመሪያ ጊዜ ባገልግሎት የዋለባት ወር ናት፡፡
የበለጸጉ የዓለም ሀገራት ያላቸውን አቅም፣ ጉልበትና ኃይል ከሚገልጹባቸው ሀብቶች መካከል ሃይድሮጅን እና ኒኩሌር ቦምብ ተጠቃሾች ናቸው:: ስለሆነም እነዚህን የኃይል ክምችቶች በስኬታማ መልኩ ማስወንጨፍና ማፈንዳት ከጉልበተኛ ሀገራት ተርታ ያሰልፋል:: ስለዚህ በ1949 ታላቋ ብሪታንያ፣ በ1966 እና 1990 ሀገረ ሕንድ ስኬታማ ሙከራዎችን በማድረግ፣ በኒኩሌር ኃይል ባለቤትነት ከሚታወቁ ጥቂት ሀገራት ዝርዝር መካከል ገብተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በግንቦት ወር ማገባደጃ ቀናት የሚከበር የወታደራዊ በዓል አለ፤ ይህ በዓል በአሜሪካ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ አሳሳቢነት መከበር የጀመረ ቢሆንም ፋይዳው በውትድርና ሙያ የሚያገለግሉ ዜጎችን በሥራቸው ማወደስና ዕውቅና መስጠት ነው:: በሌሎች የአውሮፓ ሀገራትም የሁለተኛው የዓለም ጦርነትን ተከትሎ በዓሉ የሚከበር ሲሆን፣ ዓላማውም አውሮፓውያኑ ወይም መላው ዓለም አንዳች ወሳኝ የለውጥ ንቅናቄ መጀመራቸውን በማስመልከት ትከበራለች፡፡ አብዛኞች የግኝትና የፈጠራ ውጤቶች ከውትድርና የሙያ ዘርፍ የፈለቁ እንደመሆናቸው ቀኑ ሲከበር አንድ መታሰቢያ በዓልን ከማክበር ባሻገር ወደዚህ ወሳኝ የለውጥ ምዕራፍ መሻገርን ምክንያት ማድረጉ ተገቢ ይመስላል፡፡ የዓለማቀፉ የተባበሩት ድርጅት፣ የሰላም አስጠባቂዎች ቀን በሚል፣ የወታደሮችን ሚና ማድነቅ እንደሚገባ ያወሳል፡፡ ወታደር ከተነሳ አይቀር በሀገራችንም ወታደራዊውን የአገዛዝ ሥርዓት ፈንቅሎ ያስወገደው ኢሕአዴግ ግንቦት 20ን እንድናከብር አስችሎናል:: በዚህ የወታደር ዱካ በሚበዛበት ወር፤ የደርግ መንግሥት “መፈንቅለ መንግስት ሲያካሂዱብኝ ደርሸባቸዋለሁ!” ብሎ በእስር ቤት ያስገባቸውን ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች በሞት መገላገል ሲመርጥ የታየበት ወር ናት፡፡ የወታደራዊ ጦሩ ዋና አዛዥ ደግሞ የስደት ሕይወትን እንዲመርጡ ያደረገ ነበር::
በዚህ ዘመን የኮሮና ወረርሽኝን ተከትሎ፣ ታዋቂ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በዓለማቀፍ ደረጃ ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ:: እኒህ ባለሙያዎች በየሥራዎቻቸው ኮሮናን ለመዋጋት የሚረዱ የባለሙያዎችን ምክር ሁሉ እያስደመጡ ነው፡፡ በሙዚቃ፣ ማስታወቂያ፣ አጫጭር የቴሌቪዥን ድራማ ወዘተ ዘውጎች አማካይነት ታዳሚዎቻቸውን ከማዝናናት፣ ከማስተማር፣ ከመምከር አልፈው ያካበቱትን ሀብት በልግስና እያበረከቱ፣ የገንዘብ ድጋፍ ሰብስበው የተቸገሩ ሰዎችን መሠረታዊ ፍላጎት ለማሟላት እየባዘኑ አሉ፡፡ የዓለሙ ማኅበረሰብም በያለበት በቤት ውስጥ በጽሙና እንዲቆይ በተመከረው መሠረት፣ በቤቱ ተወስኖ መዋልና ማደሩን ለምዶታል:: በዚህ ወሳኝ ወቅት የአደባባይ፣ የአዳራሽ፣ የመስክ፣ የማዘውተሪያ ስፍራ ወዘተ ትዕይንቶች ሁሉ ተገድበዋል፡፡
ይህ የቤት ሰው ተገድዶ የቴሊቪዥን መስኮቶች ላይ ማፍጠጥ፣ ወይም ከእጁ በማይጠፉ የተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ አይ ፓዶች፣ የተለያዩ መጠንና ቅርጽ ያላቸው ኮምፒውተሮች፣ ኤሌክትሮኒክስ ማጫወቻዎች ላይ ጥገኛ እንዲሆን ዘመን አብቅቶታል፡፡ በእነዚህ ቁሶች አማካይነት የቢሮ ሥራዎችን በቤት ውስጥ ሆኖ መሥራት፣ ትምህርትን መማር፣ መረጃዎችን መለዋወጥ፣ መገበያየት፣ ጊዜን ማሳለፍ፣ የራስን የቤት ውስጥ እንቅስቃሴዎች፣ ውሎና አዳሮች ቀርጾ “እዩልኝ! ቅመሱልኝ!” ብሎ እስከ መጋበዝ አድርሷል:: ይህ መሆኑ በተለያዩ ዘመናት ግንቦትን ተገን አድርገው የታሰቡ፣ የፈለቁ፣ የተወለዱ፣ የተፈጠሩ፣ የተፈበረኩ፣ መሣሪያዎች፣ መሣሪያዎችን ያስገኙ ረቂቅ አእምሯዊ ሀብቶች፣ ገናን የዕውቀት ዘርፎች፣ ዘመን ያፈራቸው ግብዓቶች፣ ወዘተ ተጠቃሚ ዓይንና ትኩረት ወደነርሱ እንዲማረክ ሳያደርጉ አልቀረም፡፡ ለዚህ ይመስላል አብዛኛው የዓለም ሕዝብ ባሁኑ ጊዜ ከሰው ለሰው የርስ በርስ ግንኙነት ራሱን ገድቦ ቴክኖሎጂው ባፈራቸው ረቂቅ የሕልም ዓለም ምናባዊ ሕይወትን ለጊዜ ማሳለፊያ መርጦ እንዲተገን ያደረገው፡፡
በግንቦት ወር ከሚከበሩ ዓለማቀፋዊ ይዘት ካላቸው በዓላት አንዱ የዓለም በመረጃ የበለጸገ ማኅበረሰብ ቀን ይጠቀሳል:: ይህን በዓል ለማክበር በመረጃዎች ክምችት ብቻ መጥለቅለቅ አይበጅም:: መረጃዎች የሚፈሱባቸው ዥረቶችን በአግባቡ የመጠቀም ክሂል ያሻል እንጂ፡፡ ስለዚህ ከላይ በተጠቀሱ የግንኙነት ማሳለጫ መሣሪያዎች አማካይነት መግባባት፣ መረዳዳት፣ ሀሳብ መለዋወጥ፣ እንዲቻል ግንቦት ወስናለች፡፡
፪. የሽርክና ማኅበር፡- ወርኀ ግንቦት ግለሰቦችን፣ ቡድንን፣ ተቋማትንና ሀገራትን በማሻረክ ትታወቃለች፡፡ በዚህ የሽርክና ሂደት አትራፊና አጉዳዮች የሚታዩ ሲሆን፣ የተጀመረው ሽርክና ጸንቶ የሚቀጥልበት ወይም የሚቋረጥበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ አንዳንዶቹ የመሰረቱት ሽርክና እስከ ዕድሜ ልክ እንዲኖሩ ሲያደርጋቸው፣ አንዳንዶቹን ደግሞ መልሰው በፍቺና በመለያየት ታሪካቸውን እንዲደመድሙ ሆነዋል፡፡ ከነዚህ ምሳሌዎች መካከል የዓለም እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) በፓሪስ ከተማ ላይ በ1896 ተቋቋመ:: የአፍሪቃ/ካ አንድነት ድርጅት በ32 ነጻ የአፍሪካ ሀገራት መካከል በተደረገ ስምምነት የተመሰረተው በ1955 በአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ የአውሮፓ ኅብረት ሰንደቅ ዓላማ በ1978 በኅብረቱ አባላት ጉባኤ የጸደቀው በወርኀ ግንቦት ነበር፡፡ በዕድሜ አንጋፋውና በእንግሊዟ የለንደን ከተማ የተቋቋመው የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር በ1836 ግንቦት ተመሠረተ፡፡
ሀገረ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ባንድ መንግሥት ለመተዳደር እንዲሁም ለመገንጠል ስምምነት ያደረገችባቸው አጋጣሚዎች የግንቦት ታሪኮች ናቸው:: መጀመሪያ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን በ1952 ከኤርትራ መንግሥት ወደ ኤርትራ አስተዳደር ወርዳ የኢትዮጵያ አካል ለመሆን ወሰነች፡፡ ከ31 ዓመታት በኋላ ደግሞ በ1983 ከኢትዮጵያ ተገንጥላ ነጻ ሀገር መሆኗ የታወጀው በግንቦት ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ፤ ሰሜናዊና ደቡባዊ የመን ሀገራት ተዋሕደው አንዲት የመን ሪፐብሊክን የመሠረቱት በ1982 ሲሆን ከአራት ዓመታት በኋላ “ጨዋታው ፈረሰ ዳቦው ተቆረሰ!” ብለው የተለያዩበትን አጋጣሚ ግንቦት ይዛለች፡፡ የናይጄሪያ ምሥራቃዊ ግዛት ቢያፍራ መገንጠሏን ያወጀችበትና ወዲያውኑም ወደ እርስ በርስ ጦርነት ያስገባት የፍቺ ክስተት በ1959 ግንቦት ላይ አስተናገደች፡፡ ወደ ምሥራቅ አውሮፓ ስንጓዝም፣ በ1998 ወርኀ ግንቦት ላይ የቀድሞዋ የዩጎዝላቪያ አካላት የነበሩ ሰርቢያ እና ሞንቴኔግሮ የውሕደት ስምምነታቸውን ሽረው በፍቺ ለመደምደም በቅተዋል፡፡
ሽርክናን በትዳር የጀመረው እንዲሁም አባቱን በሁለት ሸሪክ/ጎረቤታም ሀገሮች (ንጉሥ ወሎ ወትግሬ) ብሎ ሾሞ ከትዳሩና ከንጉሥ አባቱ ጋር ሳይቀጥል በለጋነት የዕድሜ ዘመኑ የተቀጨው ልጅ ኢያሱ፤ ጋብቻውና ሹመቱ የግንቦት ውጤቶች ነበሩ፡፡
(ይቀጥላል)

Read 2262 times