Saturday, 23 May 2020 15:20

የረመዳን ጾምና ኢድ አልፈጥር

Written by  ታደለ ገድሌ (ዶ/ር)
Rate this item
(1 Vote)

    “ ኢድ በዓል የም ሥጋና፣ የምሕረት፣ የይቅርታ፣ የሥነ ምግባራ ዊ ድል አድራ ጊነት ቀን ነው። የመልካም ውጤትና የብሩህ ግኝቶች ቀን ነው።--”
                 
             የረመዳን ጾም
ከእስልምና ሃይማኖት መሠረታዊ ሕግጋት ውስጥ ከፍተኛ ደረጃና የላቀ ከበሬታ ያለው  የረመዳን ወር ጾም ነው። ጾሙ በሙስሊሙ ኅብረተሰብ  ዘንድ ሲጾም  ቆይቷል፡፡ መንፈሳዊና ተግባራዊ መስተንግዶ ሲደረግለት የቆየው የጾም ወቅት ተጠናቅቆ፣ በታላቅ ድምቀት ይከበራል:: ስለ ረመዳን ወቅት ምንነት፣ ስለ ታሪካዊ አመጣጡና ባህላዊ ይዘቱ የእስልምና እምነት አባቶችና መጻሕፍት እንደሚያስረዱት፤  በመጀመሪያ ደረጃ የረመዳን  ወር የሚገባው  በዐረብኛው አቆጣጠር  በ4ኛው ወር ነው። ረመዳን ማለት ትርጉሙ፡- ረመደ ከሚለው ከዐረብኛ ቃል  የመጣ ነው። ረመደ ማለት ዐመድ ሆነ ማለት ነው። ...ለአሥራ አንድ ወር  ሙሉ የሰው ልጅ የሠራውን ኃጢአት  በዚህ የረመዳን ወር ውስጥ በጾም  ሲያሳልፈውና በንስሐ  ወደ አምላኩ  ገብቶ ፀሎት ሲያደርግ፣ ወንጀሉን በሙሉ ስለሚፍቀውና ስለሚያጠፋው ዐመድም አድርጎ  ስለሚበትነው፣ ረመዳን የሚል ስያሜ ሊያገኝ ችሏል፡፡ ይህ  የረመዳን ወር ጾም የተጀመረው  በነቢዩ መሐመድ  አሊቱርቱ ሰላም፣ ከመካ ወደ መዲና በሄዱ በሁለተኛው ዓመት ነው።
በእስልምና እምነት  አሹራ ማለት የሙሐረም በዐረብኛው አቆጣጠር  የመጀመሪያው  ወደ አሥረኛው ቀን ነቢዩ ላሂሙሳ በሥራው ላይ በውኃ አጥለቅልቆ፣ አላህ ከጨረሳቸው በኋላ ነቢዩ ላሂሙሳ፣ ይህንን ጾም ይጾሙ ስለነበረ ለጌታ ምሥጋና ለማድረስ፣ የጾም ግዳጅ ከመሆኑ በፊት እንደ ግዳጅ አድርገው ነቢዩ መሐመድ የአንድ ቀን ጾም ይጾሙ ነበር። ከዚያ በኋላ ስደት በሄዱ በሁለተኛው ዓመት መዲና እያሉ፣ ይህንን የረመዳን ወር እንዲጾሙ አላህ በቁርዓኑ አዝዟቸዋል፡፡ የረመዳንን  ጾም መጾምም ግዴታ  ነው፡፡ በእርጅና ምክንያት አንድ ሽማግሌ  ወይም አንዲት ባልቴት ለመጾም የማይችሉ ከሆነ፣ እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ አንዳንድ  ድሀ በቀን እያበሉ እነዚያ አዛውንቶች (ሽማግሌዎችና ባልቴቶች) መብላት ይችላሉ። በተፈጥሮ ሰው ሲያረጅ እንደ ሕፃን አሁንም አሁንም መብላት መጠጣት ስለሚያስፈልገው ተፈቅዶላቸዋል። “በጤና ምክንያት የስኳር በሽታ ያለው ወይም በተለያየ ምክንያት የተጎዳ ካለ፣ ቃሉ የሚታመን ዶክተር፤ “አንተ ጾምን ብትጾም ትጎዳለህ፤ እስከ ሕይወትህ ፍጻሜ ድረስ ጾም አካባቢ መድረስ የለብህም፤ ብትጾም የባሰ በሽታ ላይ ትወድቃለህ - ወይም ሕይወትህን ታጣለህ” ካለው በቀን አንዳንድ ድሀ እያበላ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ሳይጾም ሊቀመጥ ይችላል። ይኸ ለነዚህ ሰዎች ይሰራል። ለተቀረው ግን አይሠራም፡፡
ጾም መጾም ግዳጅ የሚሆንበት ሙስሊም በሆነ ሰው ላይ ነው። ሙስሊም ባልሆነ ላይ ግዳጅ የለም። በሁለተኛ  ደረጃ ሕፃናት ልጆች ላይ የጾም ግዴታ የለም (ለዐቅመ አዳምና ለዐቅመ ሔዋን እስኪደርሱ ድረስ) ማለት ወንድ አሥራ አምስት ዓመት እስኪሞላው፣ ሴት ልጅ ደግሞ የወር አበባ ማየት እስክትጀምር ድረስ መጾም የለባቸውም። ሴቷ የወር አበባ ባታይም አሥራ አምስት ዓመት  ከሞላትና ወንዱም እንደዚሁ በዚህ የዕድሜ ገደብ ከደረሰ የመጾም ግዴታ አለባቸው። የታመመ፣ የአዕምሮ በሽተኛ (ዕብደት ያለበት ሰውም) ከበሽታው እስኪድን ድረስ ለመጾም አይገደድም፤ ሲድን ግን መጾም ይገባዋል:: አንድ የሩቅ መንገደኛ /ሙሳትር/ የሆነ ሰው ከቤቱ እስከወጣበትና ወደ ቤቱም እስከተመለሰበት ጊዜ ድረስ ጠኔና በሽታ እንዳይገድለው መብላት ይፈቀድለታል:: በመንገደኝነት የሚበላው የረመዳን ወር ካለቀ በኋላ፣  ያንን የጾም ቀን ቀጠሮ መመለስ ግዴታው ነው። የአንድን ሙስሊም ሕይወት አደጋ ላይ  የሚያደርስ ኃይለኛ የውኃ ጥምና ረኃብ ከገጠመም፣ ይህ እንደ ሕመም ስለሚቆጠር ጾሙን መፍታት ይችላል። ይህ  በጋራ ለወንድም ለሴትም ይሆናል። በወር አበባ ላይ የምትገኝ ሴትም  ጾም መፍታት በእርሷ ላይ ግዴታ ነው፤ መብላት አለባት። አላህ ይህን ያደረገበት ምክንያት አንዲት ሴት በወር አበባ ላይ እያለች ብትጾም፣ (ጾም ደግሞ በተፈጥሮው ደም ስለሚቀንስ) ልትጐዳ ትችላለች። ከዚያ ውጪ ቀኑን ቆጥራ መክፈል አለባት። በተጨማሪም ወልዳ የተኛች  ሴትም  ከደሟ እስክትጠራ ድረስ እርሷም እንድትበላ ትገደዳለች። ጾም በነዚህ በሁለቱ ላይ ሐራም ነው። አይፈቀድላቸውም። አንዳንዶቹ ግን “በዚህ ወር ውስጥ መብላት ደስ አይለንም” እያሉ በወር አበባም ላይ እያሉ የሚጾሙ አሉ።  ወልደውም (ተኝተው) የሚጾሙ አሉ። ይኸ ግን በራሱ ወንጀል  እንደሆነ መጻሕፍቱም የእምነቱ አባቶችም ይመክራሉ፡፡
የምታጠባ  እናትንና  ነፍሰጡር ሴትን  በተመለከተም የጦም ትእዛዝ አለ፡፡  እናት ራሷ እያጠባሁ ከጾምኩ እጎዳለሁ ካለች፣ ጾም መፍታት ትችላለች። ነፍሰጡር የሆነች እናትም ለራሷ አስባ እጎዳለሁኝ  ካለች ወይም ፅንሱ ስለሚመገብ እጎዳለሁ ብላ ካሰበች፣ እርሷም ረመዳንን መፍታት (መብላት ትችላለች)፤  እንዲሁም  “እኔ በመጾሜ ሕፃኑ ልጅ ወተት ያጣል” ብላ ሰግታም ከሆነ ወይም ሆዷ ውሰጥ ያለውም ሕፃን “በመጾሜ ይጎዳል” ብላ ካሰበች ለልጆቿ  ስትል ጾሙን መፍታት ትችላለች። ችግሩ እንደተወገደላቸው ሴቶቹ መጾምና  ቀኑን ቆጥረው መመለስ ግዴታቸው ነው። ልዩነት ያለው ለራሷ ብላ ሰግታ የምትፈታው መፍታትና በሆዷ ውስጥ ላለው ወይም ለምታጠባው ልጅ ብላ ሰግታ የምትፈታው መፍታት ግን በሁኔታው ይለያያል። ለራስዋ እጎዳለሁ ብላ ፈትታ ከሆነ፣ ያንኑ ቀን ብቻ ጾማ መመለስ ነው የሚኖርባት። ለልጁ (ሆዷ ውስጥ ላለውም ሆነ ለምታጠባው) ብላ ፈትታ እንደሆነ ግን ያንን ቀን ጾማ በቀን ደግሞ አንድ ድሀ ማብላት አለባት። ለልጁ (ለሁለተኛ አካል ስትል ነውና የፈታችው)።  
“ለድሀ ማብላት ሲባል አንዳንድ እፍኝ ስንዴ ወይም እህል ለድሀ መስጠት ማለት ነው። ወይም አንድን ድሀ እስኪጠግብ ድረስ ማብላት ማለት ነው። ይህ እንደ ባለቤቱ ችሎታ ይታያል። እንደዚህ ዓይነት የጾም ዕዳ ያለባቸው ሰዎች የረመዳን ጾም ከመምጣቱ በፊት ጾሙን መመለስ ግዴታቸው ነው። ድንገት ካሣለፉ ወይም አንድ ዓመት ካለፈ በቀን አንድ ድሀ ያበላሉ። ወይም አንድ እፍኝ እህል ይሰጣሉ። ሁለት ዓመት ካለፈ ሁለት ድሀ ያበላሉ። ሁለት እፍኝ እህል  ይሰጣሉ:: ሦስትና አራት ዓመትም ካለፈ እንደዚሁ ስሌቱ ተግባራዊ ይሆናል።
በጾም  ቀን ከባለቤቱ ጋር የተገናኘ ቅጣቱ ከፍተኛ ነው። ይህን ያደረገ በአንድ ቀን ፋንታ ሁለት ወር ሙሉ በተከታታይ መጾም አለበት። ይህንን ማድረግ የማይችል ከሆነ በቀን ስድሳ ድሀ ማብላት ይኖርበታል። ሁለት ቀን ከሆነ የዚያኑ ያህል እጥፍ መሆን አለበት። በተረፈ ረስቶ ቢበላ፣ ቢጠጣ፣ ረስቶ ከባለቤቱ ጋር ቢገናኝ፣ ባስታወሰ ጊዜ ምግብና መጠጡን... አቁሞ ጾሙን መቀጠል ይኖርበታል። መንገደኛ በሽተኛ ሆኖ ወይም በእርጅና ምክንያት ሳይችል ቀርቶ ካልሆነ በስተቀር፣ ጾሙን ከመሬት ተነሥቶ ያለ አግባብ ያበላሸ ሰው  ዓመቱን በሙሉ ቢጾም ያችን ያንዷን ቀን የረመዳን ጾም ሊመልሳትና በእግዚአብሔርም ዘንድ ሞንዳ ሊያገኝባት አይችልም።
የዒድ  አልፈጥር በዓል አከባበር
ዛሬ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ሁሉም አማኝ በቤቱ ውስጥ ተገድቦ ቢገኝም፣ በሰላሙ ጊዜ  የኢድ አልፈጥርን  በዓል የሙስሊሙ ኅብረተሰብ የሚያከብረውና “አላህ ትልቅ ነው’’ እያለ ሶላቱን የሚሰግደው በአዲስ አበባ ስታዲየምና በዙሪያው በመሰባሰብ ነው፡፡ ኢድ አልፈጥር ማለት የረመዳን ጾፍ ፍቺ በዓል  ማለት ነው። ፈጥር ማለት ጾም መገደፍ፤ መመገብ  ማለት ሲሆን ኢድ ደግሞ በዓል ማለት ነው። ዒድ አልፈጥር (የጾም ፍቺ በዓል) የጾም ወር ከሆነውና ቁርዓን  ከወረደበት የረመዳን ወር በኋላ በእስላም ጨረቃዊ አቆጣጠር አስረኛው ወር በሆነው  በሸዋል  ወር የመጀመሪያው ቀን  ላይ ይውላል።
ይህ ቀን ለአንድ ሙስሊም ግለሰብ በአላህ አገልጋይነት ላስመዘገበው ከፍተኛ ክንውን አጠቃላይ የሆነ ክብረ በዓሉ ነው። እንዲሁም ተወዳጅ በሆነው ወንድማዊ መንፈስ ከበዓሉ በፊት ከነበሩባቸው መንፈሳዊ ግዴታዎች ለመውጣት ላበቃው አላህ ምስጋናውን ለማቅረብ የሚሰበሰብበት የአላህ ማወደሻና ማመስገኛ ቀን ነው። የረመዳንን ጾም የፈጸሙ ሙስሊሞች በኢድ አልፈጥር በዓል ቀን፣ ለደሆችና ለችግረኞች ዘካትን (ምጽዋትን) በማከፋፈል አላህን ማመስገናቸውን፣ ደስታቸውን ይገልጻሉ። ለድሆች መስጠት ችሎታ ባለው ሰው ላይ በአካባቢው ከሚበላው የምግብ ዓይነት ለአንድ ጊዜ የተሟላ የምግብ መጠን መስጠት ግዴታው ነው።  የሚያስተዳድረው ቤተሰብ ካለውም በእያንዳንዳቸው ቁጥር ልክ ተመሳሳይ መጠን መክፈል በሙስሊሙ ላይ ግዴታ ይሆንበታል። በዒድ በዓል ቀን አላህን ለማወደስ ራሳቸውን የሚያጠሩበት፣  ባለፀጋዎቹ የሚያመሰግኑበት፣ ለዚያው ቀን ሙታኖችን በማስታወስ ምሕረት  የሚለምኑበት፣ ችግረኞችን ለማስታወስ የእርዳታ እጃቸውን የሚዘረጉበት ሀብታሞችና ድሆች ሁሉም ለአላህ ውዴታ የሚረኩበት ቀን ነው። ዓርብ ሶላት እንደሚደረገው ሁሉ በዚሁ ቀን ለዒዓድ (በዓል)  ስግደት የሚሄድ ንጽህናውን ጠብቆ፣ ንጹህ ልብስ ለብሶ በመስጊድ ወይም  ሰጋጆች በሚሰበሰቡበት ስፍራ ከስግደቱ በፊት ጸሎት (ውዳሴ) ተክቢራ ያደርጋል።
“አሏህ አክበር፣ አሏሁ አክበር፣ አሏሁ አክበር ወሊል ላህል-ሀምዱ” ትርጉሙም፤ “አላህ ከሁሉም በላይ ኃያል ነው፡፡ አላህ ከሁሉም በላይ ኃያል ነው፡፡ ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ አላህ ከሁሉ በላይ ነው፡፡”
 ምስጋናም  “ለአላህ ይድረስ’’ ይላል።
ማንኛውም በዓል  ይቅርታ የሚተላለፍበት ለመሆኑ ሙስሊም ለዒዓድ ስግደት በሚሰባሰብበት ቀን ጌታውን ይቅርታ፣ ምሕረትንና የእምነት ልምላሜ እድገትን ይለምናል። አላህ (ሰ.ወ) ፍ/ፈም ለሆነ አገልጋዮች ምሕረትን ለመስጠት ቃል ገብቷል።
በስግደቱ ልቡን ወደ አላህ ለመመለስ እንዲህ ባለ ስብሰባ ውስጥ አንዳች የወንድም  ጥላቻ ወይም ምሬት በልቡ ውስጥ ካኖረ ማንኛውም አማኝ ሙስሊም፣ አላህ ፊት  ማፈሩ አይቀርም። በዚሁ ሁኔታ ላይ ሁሉ ምሕረትን ለመፈለግ አቅሙ የቻለውን ያህል በማድረግ፤ ፊቱን ወደ አላህ ከመለሰ ለበደለው ሁሉ ምሕረትን ያደርጋል። ከብዙኃኑ የፍፁምነት መንፈስ ከሌሎች  በይቅርታ ላለፈ ሰው ይቅርታ እንደሚደረግለት ይማራል። እሱ ይቅርታ ሲያደርግ፣ አላህ ደግሞ ለሱ ይቅርታ ያደርግለታል።
በእስልምና እምነት መሰረት፤ የዒድ በዓል የሰላም ቀን ነው። በሙስሊም ልብ ውስጥ ሰላም  ሥር ሲሰድ ከአላህ ጋር የማይፈርስ የሰላም ቃል ያስራል። የሰው ልጅ ከአላህ ጋር ሰላም ከሆነ ከራሱና ከተቀሩት ፍጥረታት ጋር ሁሉ ሰላም ይሆናል። ኢድ  በዓል የምሥጋና፣ የምሕረት፣ የይቅርታ የሥነ ምግባራዊ ድል አድራጊነት  ቀን ነው። የመልካም ውጤትና የብሩህ ግኝቶች ቀን ነው። መታሰቢያ (ማስታወሻ) ቀንም ነው። የዒድ አልፈጥር ሶላት አዛን (ኢቃማ) የለውም። ሁለት (ረኮዓ) የሚሰገድ ሲሆን ከሶላቱ በኋላ ሰጋጆቹ አላህን እንዲፈሩ፤ ቁርዓንን፤ የነቢዩን፤ እነሱ እንደሚሉት፤ (ሰ.ዐ.ወ) ፈለግ እንዲከተሉ በማሳሰብ መሪው (ኢማሙ) ዲስኩር ያደርጋሉ። የበዓሉ ሥነ ሥርዓት ካበቃ በኋላ ሰው ወደየ ዘመዱ፣ ወደየ ጓደኞቹና ቤተሰቡ ዘንድ በመሄድ ይዘያየራል። ከሙስሊም ጓደኛውም ጋር ሲገናኝ፡-
    “ምነል-ዐይዲን’’
    (እንኳን አደረሰህ)
    “ሚነል ፋኢዚን’’
    (እንኳን ድል አደረክ) ይባባላል።
ለመንፈሳዊ ግዴታዎች ዋስትና በመስጠት ግዴታውን በፍጹምነት የፈፀመ ከሆነና እንዲሁም ከኃጢአት፣ ከፍርሐት፣ ከርካሽ ጠባይና ከብልግና፣ ከምቀኝነትና ከክፋት፣ ከውርደትና ከሌሎችም የተገዢነት  (ባርነት) ምክንያት ሁሉ በመላቀቁና  በተግባር ድል በማድረጉ፣ የበዓሉ ቀን የድሉ ቀን ስለሆነ  “ሚነፋ-ፋኢዚን’’ ‘እንኳን ድል አደረክ’ ይባላል።
ለእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ፤“ዒዱ-ል ሙባረክ’’ ብያለሁ፡፡

Read 914 times