Saturday, 23 May 2020 15:16

በዓለም የኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር ከ5.1 ሚሊዮን አልፏል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

   ረቡዕ ብቻ ከ106 ሺህ በላይ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ተገኝተዋል

                  ባለፈው ሐሙስ ማለዳ…
ኮሮና ቫይረስ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ተሰምቶ የማይታወቅ አስደንጋጭ ቁጥር ተሰማ - “ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በመላው ዓለም ከ106 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው በምርመራ ተረጋግጧል፤ ይህም ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ወዲህ በአለማችን በአንድ ቀን የተመዘገበ ከፍተኛው የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ሆኗል” ብሏል - የአለም የጤና ድርጅት፡፡
ባለፈው ረቡዕ የተመዘገበውን ከፍተኛ ዕለታዊ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ጨምሮ፣ ኮሮና ቫይረስ እስከ ትናንት በስቲያ አመሻሽ ድረስ በመላው አለም ከ5,127,431በላይ ሰዎችን ማጥቃቱንና 331 ሺህ የሚሆኑትንም ለሞት መዳረጉን ያመለከተው ወርልዶ ሜተር ድረገጽ፤2,044,153 ያህል ሰዎችም ከቫይረሱ ማገገማቸውን አስታውቋል፡፡
በአለማችን ከፍተኛ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር የተመዘገበባቸው ቀዳሚዎቹ አምስት አገራት፡- አሜሪካ-1,593,297፣ ሩስያ-317,554፣ ብራዚል- 294,152፣ ስፔን - 279,524፣ እንግሊዝ- 248,293 መሆናቸውንም መረጃው አመልክቷል፡፡
እስከ ትናንት በስቲያ ከ95 ሺ በላይ ሰዎች የሞቱባት አሜሪካ፤ ከአለም አገራት በሟቾች ቁጥር የመጀመሪያውን ደረጃ ይዛ የቀጠለች ሲሆንእንግሊዝ ከ36 ሺህ በላይ፣ ጣሊያን በ32,330፣ ፈረንሳይ በ28,132፣ ስፔን በ27,888 ሟቾች እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸው የተነገረ ሲሆን ኮሮና  ካስከተላቸው ሞቶች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑትበአውሮፓ አገራት የተከሰቱ እንደሆኑ ኤቢሲ ኒውስ ዘግቧል፡፡ በመላው አለም በየሁለት ሳምንቱ 1 ሚሊዮን ያህል አዳዲስ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች እየተገኙ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፤ በሳምንቱ ከተመዘገቡ አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች መካከል ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት የተመዘገቡባቸው አራቱ አገራት፡- አሜሪካ፣ ሩስያ፣ ብራዚልና ህንድ መሆናቸውንም አመልክቷል፡፡

60 ሚሊዮን ሰዎች ለከፋ ድህነት ይዳረጋሉ
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሚያስከትለው ሁሉን አቀፍ ቀውስ ሳቢያ በመላው አለም 60 ሚሊየን ሰዎች ለከፋ ድህነት እንደሚጋለጡ የዓለም ባንክ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ አስጠንቅቋል።ኮሮና ቫይረስ የበርካታ አገራትን ኢኮኖሚ ክፉኛ መጉዳቱን ቀጥሏል ያሉት የባንኩ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ማልፓስ፤ በወረርሽኙ ሳቢያ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ለስራ አጥነት መዳረጋቸውን እንደተናገሩም ቢቢሲ ባወጣው ዘገባ አመልክቷል፡፡
ወረርሽኙ በተለይ በታዳጊና ድህነት ውስጥ ባሉ አገራት የሚገኙ ዜጎችን ክፉኛ መጉዳቱን የተናገሩት የባንኩ ፕሬዚዳንት፤ በዚህ አመት የዓለም ኢኮኖሚ በ5 በመቶ ያህል እንደሚያሽቆለቁል ጠቁመው፤ ባንኩ ድሃ ሃገራት የቫይረሱን ተፅዕኖ መቋቋም እንዲችሉ 160 ቢሊየን ዶላር በእርዳታና በአነስተኛ ወለድ ብድር መልክ ማቅረቡንም አመልክተዋል።

አፍሪካ በሳምንቱ
የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤የአፍሪካ መንግስታት ቀጠናዊ ትብብርን በማጠናከር፣ የጤና ባለሙያዎችን በማሰማራት፣ ለይቶ ማቆያዎችን በማዘጋጀት፣ እንቅስቃሴን በመገደብና ድንበሮችን በመዝጋት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሰጡትን ፈጣን ምላሽ አድንቀው “የሰለጠነው ዓለም ከአፍሪካ ብዙ ሊማር ይችላል” ብለው በተናገሩበትና የተቀረው አለም አፍሪካን ከመቼውም ጊዜ በላይ  ለመርዳት እንዲዘጋጅ ጥሪ ባቀረቡበት በዚህ ሳምንት፤ እንደተፈራው ባይሆንም ኮሮና በአህጉሪቷ መስፋፋቱን ቀጥሏል፡፡ሁሉንም የአፍሪካ አገራት ያዳረሰው ኮሮና ቫይረስ እስካለፈው ሐሙስ አመሻሽ ድረስ በአህጉሪቱ ከ95 ሺህ በላይ ሰዎችን በማጥቃት፣ 3 ሺህ ያህል ሰዎችን ለሞት የዳረገ ሲሆን ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥርም 39 ሺህ ያህል መድረሱ ተነግሯል፡፡
ደቡብ አፍሪካ በ18 ሺህ፣ ግብጽ ከ14 ሺህ በላይ፣ አልጀሪያ ከ7 ሺህ 500 በላይ፣ ሞሮኮ ከ7 ሺህ 100 በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁባቸው ሲሆን 680 ሰዎች የሞቱባት ግብጽ፤ በሟቾች ቁጥር ከአፍሪካ አገራት ቀዳሚነቱን መያዟን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በአህጉሪቱ በኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር ቀዳሚነቱን በያዘችው ደቡብ አፍሪካ፤ እስከ 2020 መጨረሻ ድረስ 50 ሺህ ያህል ሰዎች በቫይረሱ ሊያዙ እንደሚችሉ የአገሪቱ ተመራማሪዎች ማስጠንቀቃቸውን የዘገበው አልጀዚራ፤ የአገሪቱ የትምህርት ሚኒስቴር፣ በወረርሽኙ ስጋት ተዘግተው የቆዩ ት/ቤቶች ከሰሞኑ እንደሚከፈቱ ማስታወቁን ተከትሎ፣ በርካታ የአገሪቱ ዜጎች በውሳኔው ቅር በመሰኘት ስጋታቸውን እየገለፁ እንደሚገኙም አክሎ ገልጧል፡፡
መንግስታት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ያስችሉናል ያሏቸውን የተለያዩ ገደቦች፣ ማዕቀቦች፣ ህጎችና መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረጋቸውን በቀጠሉባት አፍሪካ፤ ከሰሞኑ ደግሞ ከወደ ኡጋንዳ ለየት ያለ ነገር ተሰምቷል፡፡
የአገሪቱ መንግስት የንግድ ቤቶች በራፋቸው ላይ የእጅ መታጠቢያ እንዲያዘጋጁ ያወጣውን መመሪያ መሰረት በማድረግ የካምፓላ ፖሊስ፣  የእጅ መታጠቢያ ያላስቀመጡ የንግድ ቤቶችን መዝጋት መጀመሩን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡በሌላ ዜና ደግሞ፣ የደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር እና   የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር የሆኑት ባለቤታቸው ቀዳማዊት አመቤት አንጀሊና ተኒና፤ በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸው በምርመራ መረጋገጡን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በአገሪቱ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር የተቋቋመው ግብረ ሃይል አባል የሆኑ አንድ ግለሰብ በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን ተከትሎ፣ በተደረገላቸው ምርመራ፤ ከጥንዶቹ በተጨማሪ የሪክ ማቻር የግል ጥበቃዎች፣ ሁለት ሚኒስትሮችና ሌሎች ባለስልጣናትም በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የክትባት ተስፋ…
ከትናንት በስቲያ ማለዳ…
በአገረ አሜሪካ ስማቸው ጎልቶ ከሚጠቀስ የህክምናው ዘርፍ ሳይንቲስቶች አንዱ የሆኑትና በካንሰርና በኤች አይቪ ኤድስ ፈርቀዳጅ ጥናትና ምርምር በማድረግ የሚታወቁት ዊሊያም ሃሴልታይን፤ ብዙዎችን ያስደነገጠ ነገር ተናገሩ፡፡
“ክትባቱ መቼ ይገኝ ይሆን እያላችሁ ቀን የምትቆጥሩ ሰዎች፣ እሱን ትታችሁ የፊት ጭንብል አድርጉ፤ እጆቻችሁን ታጠቡ፤ ርቀታችሁን ጠብቁ!...  የእንቅስቃሴ ገደቦችን እያነሳችሁ ወይም እያላላችሁ ያላችሁ መንግስታት ሆይ፣ እናንተም ክትባት ከዛሬ ነገ ይገኛል እያላችሁ ቀን መቁጠር አይበጃችሁም፤ ይልቁንም የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ጠንካራ የክትትልና የመለየት እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ትኩረት አድርጉ፡፡ የኮሮና ቫይረስ ክትባት እስከወዲያኛው ላይገኝ ይችላል!...”  በማለት ምክራቸውን ለግሰዋል -ታላቁ ሳይንቲስት፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ክሎሮኪን የተባለውን የወባ መድሃኒት ለኮሮና መከላከያነት እየወሰዱ እንደሚገኙ ተናግረ፣ው ብዙዎችን ባነጋገሩበት በዚሁ ሳምንት፣ ብራዚል ለኮሮና ፍቱን መሆኑ ገና በሳይንስ ያልተረጋገጠውን ይህን መድሃኒት በስፋት ለዜጎቿ ለማዳረስ ጥረት መጀመሯን ኤቢሲ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ ክሎሮኪንን ጨምሮ መሰል የወባ በሽታ መድሐኒቶች፤ ኮሮና ቫይረስን ይከላከላሉ እንደሆን ለማረጋገጥ በእንግሊዝ ኦክስፎርድ እና ብራይተን ዩኒቨርሲቲዎች ሙከራ ሊደረግ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ከአሜሪካ መንግሥት ብሔራዊ የጤና ኢንስቲትዩትና ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ ተመራማሪዎች ያዘጋጁት የኮሮና መከላከያ ክትባት፣ በዝንጀሮዎች ላይ ተሞክሮ ተስፋ ሰጪ ውጤት ማሳየቱንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
"ባለፈው ሳምንት በአይጦች ላይ የሞከርኩትንና ጥሩ ውጤት ያገኘሁበትን ሜሴንጀር አርኤንኤ የተሰኘ ክትባት፤ በቅርቡ በዝንጀሮዎች ላይ እሞክራለሁ" ያለው የታይላንድ መንግስት በበኩሉ፤ በሰባት ወራት ጊዜ ውስጥ የክትባቱን ምርምር አጠናቅቆ ይፋ እንደሚያደርግ ማስታወቁን የዘገበው ደግሞ ሮይተርስ ነው፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ የአገራት መሪዎች፣ ዝነኞችና ባለሙያዎችን ጨምሮ ከ140 በላይ ሰዎች፣ የኮሮና ቫይረስ ክትባትና መድሐኒት በምርምር በሚገኝበት ወቅት ለሁሉም የዓለም ሕዝብ፣ በፍትሃዊነትና በነጻ እንዲዳረስ በጻፉት የጋራ ደብዳቤ መጠየቃቸውን ቢቢሲ ከሰሞኑ አስነብቧል፡፡
ውዝግቡ ቀጥሏል
አሜሪካ እና የአለም የጤና ድርጅት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዙሪያ የጀመሩትን ውዝግብ አጠናክረው የገፉበት ሲሆን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሞኑ ለአለም የጤና ድርጅት በላኩት ደብዳቤ፤ ዶ/ር ቴዎድሮስ በ30 ቀናት ውስጥ በድርጅታቸው ላይ “መሰረታዊ ለውጥ” እንዲያመጡ ያሳሰቡ ሲሆን ካልሆነ ግን አሜሪካ ለድርጅቱ የምታደርገውን ድጋፍ ሙሉ ለሙሉ እንደምታቋርጥና ከአባልነት እንደምትወጣ አስጠንቅቀዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ቫይረሱ ከቻይናዋ ዉሃን በተነሳበት ወቅት ስለ ቫይረሱ ስርጭት በተደጋጋሚ ይቀርቡ የነበሩ ተጨባጭ መረጃዎችን ችላ ሲል ነበር በሚል የወቀሱት ትራምፕ፤ በተሳሳተ አካሄድ ብዙዎችን ለቫይረሱ የዳረገ  የቻይና አሻንጉሊት ሲሉ ያጣጣሉት ድርጅቱ፣ በአፋጣኝ መሰረታዊ የሆነ ማሻሻያ ተግባራዊ ካላደረገ በጊዜያዊነት ያቋረጡትን ድጋፍ በቋሚነት እንደሚያቋርጡት ማስጠንቀቃቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ኮሮናን ለመከላከል ሲሉ ለወባ በሽታ ህክምና የሚውለውን ክሎሮኪን የተባለ መድሃኒት ለሳምንታት መውሰዳቸውን በይፋ መናገራቸውን ተከትሎ፣ የአለም የጤና ድርጅት ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ፣እንደ ትራምፕ በሳይንስ ያልተረጋገጠ መድሃኒት ከመውሰድ ተቆጠቡ ሲል አስጠንቅቋል፡፡በሌላ በኩል ደግሞ ቻይና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመዋጋት 2 ቢሊዮን ዶላር መመደቧን ይፋ ማድረጓን ተከትሎ፣ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ፤ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት ከዳረገውና በትሪሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር ጥፋት ካስከተለው የገዛ ስህተቷ ጋር ሲነጻጸር ኢምንት ነው ሲሉ የመደበችው ገንዘብ በቂ አለመሆኑን በስላቅ ተችተዋል፡፡
የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂፒንግ፣ አገራቸው ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ግልጸኝነት፣ ሃላፊነትና ተጠያቂነት ባለው መንገድ እንቅስቃሴ ስታደርግ መቆየቷን መናገራቸው ያልተዋጠላቸው ፖምፒዮ፤"ወንድ ከሆነ ጋዜጣዊ መግለጫ አዘጋጅቶ፣ ከሪፖርተሮች የሚሰነዘሩለትን ጥያቄዎች በሙሉ ሳያማርጥ ፊትለፊት ይመልስ" ሲሉ ፕሬዚዳንቱን መወረፋቸውም ተዘግቧል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ከሰሞኑ ለሁለት ቀናት ባካሄደው 73ኛ አመታዊ ጉባዔ፣በተጠያቂነት እንደሚያምንና በጉዳዩ ዙሪያ ምርመራ እንዲደረግ እንደሚፈልግ ያስታወቀ ሲሆንትራምፕ ባልተሳተፉበት በዚሁ ጉባኤ ላይ የተሳተፉ አባል ሃገራትም ድርጅቱና በስሩ ያሉ ኤጀንሲዎች ለኮሮና ወረርሽኝ የሰጡት ምላሽ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ መስማማታቸው ተነግሯል፡፡
ተዘግቶ መቆየት ወይስ መከፈት?
የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኮሮና ሳቢያ በአገሪቱ ተጥሎ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለአምስተኛ ጊዜ እንዲያራዝምላቸው ከሰሞኑ ጥያቄ ማቅረባቸው የተነገረ ሲሆን፣ የአገሪቱ  ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን አዋጁ መራዘሙን እንደተቃወሙት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ከአለማችን ዝነኛ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የሆነው ካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ፤ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለአንድ አመት ያህል በክፍል ውስጥ ትምህርት እንደማይሰጥና ትምህርቱ በኢንተርኔት ታግዞ በርቀት እንዲሰጥ መወሰኑን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡ተዘግቶ መቀጠልም፣ ሙሉ ለሙሉ መክፈትም አደጋ እንዳለው የተገነዘቡት የኒው ዚላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደን፤ የአገሪቱ ሰራተኞች በሳምንት አራት ቀናት ብቻ ቢሰሩ መልካም ነው የሚል ሃሳብ ማቅረባቸው ተነግሯል፡፡
ሲንጋፖር በበኩሏ፤ ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር በተያያዘ ተግባራዊ ስታደርገው የቆየችውን የእንቅስቃሴ ማዕቀብ በሚቀጥለው ሳምንት እንደምታነሳ ብታስታውቅም፣ በአገሪቱ የሚገኙ የውጭ አገራት ዜግነት ያላቸው የቤት ሠራተኞች ግን ከቤት መውጣት እንደማይፈቀድላቸው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የታንዛንያው ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ፣ የዩኒቨርሲቲና የሁለተኛ ደረጃ ብሔራዊ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ከቀናት በኋላ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱና በኮሮና ለሁለት ወራት ያህል ተቋርጠው የነበሩ ስፖርታዊ ጨዋታዎችም እንዲጀመሩ መወሰናቸው ተነግሯል።በደቡብ ኮርያ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከረቡዕ ጀምሮ መከፈታቸው የተነገረ ሲሆን የዩክሬን መንግስት በበኩሉ፤ ተዘግተው የነበሩ ሆቴሎችና አጸደ ህጻናት እንዲከፈቱ፣ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲጀምር መወሰኑም ተዘግቧል፡፡
አብዛኞቹ አገራት ማዕቀብና እገዳዎችን ማላላትና ማንሳታቸውን ቢቀጥሉም፣ ፖላንድን የመሳሰሉ አገራት ግን ትምህርት ቤቶች ተዘግተው እንዲቆዩ መወሰናቸውን፤ እንደ ስፔን ያሉ አገራት ደግሞ የፊት ጭንብል ማድረግን የመሳሰሉ ግዴታዎችን በመጣል ላይ እንደሚገኙ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡
ከወደ አሜሪካ…
ከኮሮና ጋር በተያያዘ አነጋጋሪ ንግግሮችን ማድረጋቸውን የቀጠሉት የአሜሪካው ፕሬዚዳነት ዶናልድ ትራምፕ፣ ከሰሞኑ ደግሞ አገራቸው ብዛት ያላቸው ሰዎች በኮሮና ቫይረስ የተጠቁባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር መሆኗን በምርመራ ማረጋገጧ "ክብር" ሊያሰጣት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
"ብዙ ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ ማረጋገጣችንን እንደ መልካም ውጤት ነው የማየው፡፡ ይህ የሚያሳየው የምናደርገው ምርመራ ከሁሉም አገራት የተሻለ መሆኑን ነው" ብለዋል፤ ትራምፕ ከሰሞኑ በዋይት ሃውስ በሰጡት መግለጫ።
"የተገኘውን ውጤት እንደ ክብር ምልክት ነው የማየው። በአውነትም የከብር ምልክት ነው። በአገራችን በምርመራና በተለያዩ የህክምና ስራዎች ላይ የተሰማሩት ባለሙያዎች፣ ባከናወኑት የላቀ ሥራ የተገኘ ትልቅ ውጤት ነው" ሲሉም አክለዋል ትራምፕ፡፡
በቤላ በኩል ደግሞ፣ አሜሪካ ኮሮና ቫይረስ በስፋት ከመሰራጨቱ አስቀድማ በሰዎች እንቅስቃሴ ላይ ማዕቀብ ብትጥል ኖሮ 36 ሺህ ያህል ሰዎች ከሞት ይተርፉ እንደነበርበኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የተሠራው አንድ ጥናት ማመልከቱን ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡፡
አሜሪካ በበርካታ አካባቢዎች የእንቅስቃሴ ማዕቀብ የተጣለው ባለፈው መጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ እንደነበር ያስታወሰው ጥናቱ፤ የአገሪቱ መንግሥት ከዚያ አንድ ሳምንት ቀድሞ ማሕበራዊ ርቀት እንዲጠበቅና እንቅስቃሴ እንዲገታ ቢያደርግ ኖሮ በቫይረሱ ሳቢያ ለሞት ከተዳረጉት ሰዎች መካከል 83 በመቶ የሚሆኑትን ማዳን ይችል እንደነበር ይገልጻል፡፡
ኩባንያዎች ሰራተኛ መቀነሳቸውን ቀጥለዋል
ታላላቅ የአለማችን ኩባንያዎች ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ሰራተኞቻቸውን በጊዜያዊነትና በቋሚነት መቀነሳቸውን እንደገፉበት መረጃዎቸ ይጠቁማሉ፡፡
ዝነኛው የእንግሊዝ የሞተር አምራች ኩባንያ ሮልስ ሮይስ፣ 9 ሺህ ሰራተኞችን ከስራ ገበታቸው ሊያሰናብት ማቀዱን ከሰሞኑ ይፋ ያደረገ ሲሆን በዚህም 700 ሚሊዮን ዩሮ ያህል ወጪ ሊቀንስ እንደሚችል ተነግሯል፡፡በተመሳሳይ ዜና ደግሞ ከኮሮና ቫይረስ ቀውስ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ያጋጠመው ኦክስፋም የተባለው አለማቀፍ ግብረ ሰናይ ተቋም፤ ላለፉት 50 አመታት የሰራበትን አፍጋኒስታን ጨምሮ በ18 የአለማችን አገራት የነበሩትን ቢሮዎችን እንደሚዘጋና 1 ሺህ 500 ሰራተኞቹን እንደሚያሰናብት ማስታወቁ ተነግሯል፡፡
ውሃን፤“አውሬ”ማርባትና መብላት ከለከለች
አለምን እያስጨነቀ ያለው የኮሮና ቫይረስ መነሻ የሆነችው የቻይናዋ ውሃን ከተማ፤ ነዋሪዎቿ የተለያዩ የምድርና የባሕር ውስጥ እንስሳትንና አውሬዎችን ማደን፣ ማርባትና ለምግብነት ማዋል እንዲያቆሙ በማሳሰብ፤ ይህን ሲያደርጉ በተገኙት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ማስጠንቀቋን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የከተማዋ አስተዳደር በርካታ የምድርና የባሕር እንስሳትን ያካተተበትን ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው፤ የኮሮና ቫይረስ ከሌሊት ወፎች ተነስቶ፣ በሌሎች እንስሳት አማካኝነት ወደ ሰው ልጆች ሳይዛመት እንዳልቀረ የሚጠቁሙ ጥናቶችን መሠረት በማድረግ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፤ በተከለከሉት እንስሳት ንግድ ላይ ተሰማርተው ለቆዩ ነዋሪዎች የማቋቋሚያ ገንዘብ ድጋፍእንደሚደረግላቸው ቃል መገባቱንም አመልክቷል፡፡

Read 11449 times