Saturday, 16 May 2020 14:29

"በቀጣዩ ምርጫ ብልጽግና የማሸነፍ ዕድል የለውም" -አቶ ልደቱ አያሌው-

Written by 
Rate this item
(16 votes)

የኢዴፓ አመራርና አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው፤ የኮቪድ ወረርሽኝ ከተጋታ በኋላ በኢትዮጵያ እንደሚካሄድ በሚጠበቀው 6ኛው አገራዊ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ የማሸነፍ እድል እንደሌለው ባዘጋጁት የቅድመ ምርጫ ውጤት ግምትና ትንተና ሰነድ ላይ ጠቁመዋል፡፡
 ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም በኋላ የሚፈጠረውን የሥልጣን ክፍተት ለመሙላት መፍትሄው ለ2 ዓመት የሚዘልቅ  የሽግግር መንግስት ማቋቋም መሆኑን ሽንጣቸውን ገትረው የሚሟገቱት አቶ ልደቱ፤ ሃሳባቸው ውድቅ ተደርጎ ምርጫው የሚካሄድ ከሆነና በተዐምራዊ ምክንያት ሰላማዊ፣ ነጻና ፍትሐዊ መሆን ቢችል፣ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ካለው የፖለቲካ የኀይል አሰላለፍ አንጻር፣ ምርጫውን የትኛው የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ጎራ ሊያሸንፍ ይችላል? ለሚለው ጥያቄ፤ ‹‹የቅድመ -ምርጫ ውጤት ግምትና ትንተና›› መስጠት ጠቃሚ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡   
ከሁሉም ክልሎች በቀጣዩ  ምርጫ የሚመጣውን ውጤት ወደ እርግጠኝነት በተጠጋ መጠን አስቀድሞ ለመገመት የሚቻለው በትግራይ ክልል ነው የሚሉት አቶ ልደቱ፤ በክልሉ ዋናው (ምናልባትም ብቸኛው) የምርጫ አጀንዳ የትግራይ ክልል ሉዓላዊነትና የህወሓት ህልውና መቀጠል እንደሚሆን ይጠቁማሉ፡፡
"ይህንን አጀንዳ ደግሞ ከህወሓት በተሻለ መጠን በአሁኑ ወቅት ሊያሳካ የሚችል ድርጅት አለ ተብሎ በአብዛኛው የትግራይ ሕዝብ ዘንድ ስለማይታሰብ፣ ህወሓት ምርጫውን መቶ በመቶ ሊያሸንፍ ይችላል።" ይላሉ፤ በግምታዊ ትንተናቸው፡፡
 በኦሮሚያ ክልል አብዛኛው ሕዝብ ድምጽ የሚሰጠው ለፖለቲካና ለኢኮኖሚ አጀንዳዎች ሳይሆን በዋናነት “ለነጻ አውጭነት ትግል” ውለታ መክፈያነት ይሆናል የሚል ጠንካራ ግምት እንዳለ የሚገልጹት አቶ ልደቱ፤ በዚህ መሠረትም፣ ላለፉት 40 ዓመታት፣ “የነጻ አውጭነት” ትግል ያካሄደው ኦነግና ከኦነግ ጋር ተባብረው ወደ ምርጫው ለመግባት የወሰኑት እነ ኦፌኮ፥ ከ75 በመቶ ያላነሰ መቀመጫ በማሸነፍ፣ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤትንና በፌደራሉ ፓርላማ 96 መቀመጫዎችን ሊያሸንፉ ይችላሉ ብለዋል፡፡ ቀሪውን 20 % ወይም 26 መቀመጫዎች ደግሞ ብልጽግና- ተኮር  ጎራው፣  ቀሪውን 5 % ወይም 6 መቀመጫዎች ደግሞ የአንድነት- ተኮር ጎራው ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ተገምቷል፡፡ ብልጽግና ፓርቲ በአብዛኛዎቹ የኦሮሚያ ምርጫ ወረዳዎች፣ በአማካይ ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆነውን የሕዝብ ድጋፍ ሊያገኝ የሚችል  ቢሆንም፣ ይህ ድጋፍ ግን  በተሟላ ሁኔታ ወደ መቀመጫ አሸናፊነት የመቀየር ዕድል አይኖረውም፤ይላል የአቶ ልደቱ ትንተና።
 እንደ ኦሮሚያ ሁሉ በሶማሌ ክልልም፣ አብዛኛው ሕዝብ በመጪው ምርጫ ድምጽ የሚሰጠው “ለነጻ አውጭነት ትግል” ውለታ መክፈያነት ይሆናል የሚል ጠንካራ ግምት መኖሩን የሚጠቁመው ሰነዱ፤ ከዚህ አንጻርም ኦብነግ ከ60 በመቶ ያላነሰ መቀመጫ በማሸነፍ፣ የሱማሌ ክልል ምክር ቤትን እንደሚረከብ፣ ለፌደራሉ ፓርላማ ደግሞ 14 መቀመጫዎችን ሊያሸንፍ እንደሚችል ያመለክታል፡፡  ቀሪውን 40 በመቶ ወይም 10 መቀመጫዎችን ደግሞ ብልጽግና ፓርቲ ሊያሸንፍ ይችላል ይላል - ትንተናው፡፡  
በአማራ ክልል አብንን፣ አብሮነትንና መኢአድን የመሳሰሉ ፓርቲዎች ቢያንስ እርስ በርስ ከመፎካከር ከተቆጠቡና መስማማት ከቻሉ፣ የአንድነት- ተኮር ጎራው፣ በአነስተኛ ግምት፣ ከ90 በመቶ ያላነሰ መቀመጫ በማሸነፍ የአማራ ክልል ምክር ቤትንና ለፌደራሉ ፓርላማ 124 መቀመጫዎችን ሊያሸንፉ ይችላሉ። ከቀረው 10% ውስጥ ብልጽግና ፓርቲ 13 መቀመጫ፣ ብሔር ተኮር የሆነው ጎራ (ኦሮሚያ ልዩ ዞን) 1 መቀመጫ ሊያሸንፉ ይችላሉ ተብሏል።
"ይህንን ውጤት ለማስጠበቅ ግን ቢያንስ አብንና አብሮነት እርስ በርስ ላለመፎካከር ሊስማሙ ይገባል። ምክንያቱም የክልሉ ሕዝብ በአሁኑ ወቅት በአዲሱ የአማራ ብሔርተኝነትና በነባሩ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ለሁለት የተከፈለ አመለካከት ያለው በመሆኑ፣ በምርጫው የሕዝቡ ድምጽ በእነዚህ ሁለት አመለካከቶች እንዳይከፋፈል የሚያደርግ የፓርቲዎች ጥምረት መፍጠር የግድ ያስፈልጋል። ቢያንስ አብንና አብሮነት ወደዚህ ዓይነቱ ስምምነት መምጣት ከተሳናቸው ግን የሚያገኙት ውጤት ከ90 በመቶ ወደ 50 በመቶ ገደማ ዝቅ ሊል ይችላል፤ በአንጻሩ በክልሉ የሚገኙ አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እርስ በርስ ላለመፎካከር መስማማት ከቻሉ ደግሞ ውጤቱ ምናልባትም ከ90 በመቶ ወደ 95 በመቶ ሊያድግ ይችላል።" ብለዋል አቶ ልደቱ፤ በግምታዊ ትንተናቸው፡፡

"ብልጽግና ፓርቲ በአማራ ክልል እስከ 35 በመቶ የሚደርስ የሕዝብ ድጋፍ ሊኖረው ይችላል። የአንድነት ኀይሉ ድምጽ እንዳይከፋፈል የሚያስችል ስምምነት ውስጥ እስከገባ ድረስ ግን ይህ የብልጽግና ፓርቲ ድጋፍ በሀገሪቱ የምርጫ ሥርዓት ምክንያት ወደ ወንበር አሸናፊነት የመቀየር ዕድል የለውም።" ሲሉም ያብራራሉ፡፡
በአዲስ አበባ ላይ በቀረበው  የቅድመ ምርጫ ግምትና ትንተና፤ አብሮነት፣ አብንና ባልደራስን የመሳሰሉ ፓርቲዎች እርስ በርስ ላለመፎካከር ከተስማሙ፣ የአንድነት ጎራው፣ ከ80 በመቶ ያላነሰ መቀመጫ በማሸነፍ፣ የከተማዋን አስተዳደር ሊረከቡና 18 የፌደራል ፓርላማ መቀመጫ ሊያሸንፉ እንደሚችሉ የተገመተ ሲሆን ቀሪውን 20 በመቶ  ወይም 5 መቀመጫ ብልጽግና ፓርቲና የርሱ ደጋፊ የሆኑ ፓርቲዎች የማሸነፍ ዕድል ሊኖራቸው እንደሚችሉ ተገምቷል፡፡ "ብልጽግና ፓርቲና ኢዜማን የመሰሉ ፓርቲዎች በየወረዳው በድምሩ 25 በመቶ የሚሆን የሕዝብ ድጋፍ ሊኖራቸው ቢችልም፣ ይህ ድጋፍ በብዙዎቹ ወረዳዎች በምርጫ ሥርዓቱ ምክንያት ወደ ወንበር አሸናፊነት የሚቀየርበት ዕድል በጣም ጠባብ ነው።" ይላል ትንተናው፡፡  
"የብልጽግና ፓርቲ የገንዘብ ኀይል በአዲስ አበባ ቀላል የማይባል ተጽዕኖ ይኖረዋል። ነገር ግን ብልጽግና ፓርቲ ኦዴፓ በነበረበት ወቅት “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ናት” በማለት የወሰነው ውሳኔና የአዲስ አበባን ሕዝብ ስብጥር ለመቀየር አደረገው የተባለው ሙከራ፣ በምርጫው ሊደርስበት የሚችለውን ሽንፈት በማንኛውም ሌላ ምክንያት እንዳይቀለበስ  ያደርገዋል።" ሲሉ ያስረዳሉ አቶ ልደቱ፡፡
በዘንድሮው ምርጫ፣ በደቡብ ክልል፣ ዋና ዋና የመፎካከሪያ አጀንዳዎች ሦስት መሆናቸውን ይጠቁማል፤ የትንተና ሰነዱ፡፡ እነዚህም  የዞኖች ክልል የመሆን ጥያቄ፣ በኢትዮጵያ አንድነት መቀጠልና በብሔር ብሔረሰቦች መብት መከበር ዙሪያ ሚዛናዊ አቋም መኖር፣ ከሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ፣ በተለይም ከመሬት ጥበትና ከወጣቶች ሥራ አጥነት ጋር የተያያዙ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ናቸው የሚለው ትንተናው፤ለእነዚህ ጉዳዮች አሳማኝ አማራጭ የሚያቀርብ ጎራ የመመረጥ ዕድሉ ሰፊ እንደሚሆን ያስቀምጣል፡፡
 "ከዚህ አንጻር፥አብዛኛዎቹ የአንድነት ኀይሎች፣ ቢያንስ ግን አብሮነትና መድረክ (ኦፌኮን ሳይጨምር) እርስ በርስ ላለመፎካከር ተስማምተው ወደ ምርጫው ከገቡ፣ በጣም ባነሰ ግምት 55 በመቶ መቀመጫ አሸንፈው፣ የክልሉን ምክር ቤት ሊረከቡና ለፌደራሉ ፓርላማ 68 መቀመጫዎችን ሊያሸንፉ ይችላሉ። ቀሪውን 30 በመቶ  ወይም 37 መቀመጫዎች የብልጽግና ጎራ፣ እንዲሁም 15 በመቶ ወይም 18 መቀመጫዎች ደግሞ ብሔር ተኮር ጎራው ሊያሸንፍ ይችላል።" ሲሉ ተንብየዋል፤አቶ ልደቱ፡፡
 ይህ ውጤት ዋስትና የሚኖረው ግን ቢያንስ መድረክ በተለይም የእነ ፕሮፌሰር በየነ ኢሶዴፓና አብሮነት እርስ በርስ ላለመፎካከር መስማማት ላይ የሚደርሱ ከሆነ ነው ይላሉ፡፡ እንዲያውም አብዛኛዎቹ የአንድነት ተኮር ኀይሎች እርስ በርስ ላለመፎካከር መስማማት ላይ መድረስ የሚችሉ ከሆነ፣ የአንድነቱ ጎራ ውጤት ከ55 በመቶ ወደ 70 በመቶ የማደግ ዕድል ሊኖረው ይችላል። ከዚህ አንጻር መድረክ በተለይም ኢሶዴፓ የኀይል አሰላለፉን ለማስተካከል የሚወስደው አቋም የጨዋታውን ውጤት ቀያሪ /Game Changer/ ነው፤ ይላል ሰነዱ፡፡
"ከዚህ አጠቃላይ የምርጫ ውጤት ቅድመ ግምት ለመረዳት እንደምንችለው ሦስቱ የፖለቲካ ጎራዎች በተናጠል የፌደራል መንግሥት ለማቋቋም የሚያስችል ውጤት ሊያገኙ አይችሉም። ነገር ግን ከውጤት የቅደም ተከተል ደረጃ አንጻር፣ የአንድነት ተኮር ጎራው 45% ወይንም 223 የፓርላማ መቀመጫ በማሸነፍ አንደኛ ደረጃን፤ የብሔር ተኮር ጎራው 35% ወይንም 175 የፓርላማ መቀመጫ በማሸነፍ ሁለተኛ ደረጃን፤ የብልጽግና ተኮር ጎራው 20% ወይም 99 የፓርላማ መቀመጫ በማሸነፍ ሦስተኛ ደረጃን ይይዛሉ።" ሲል ግምቱን ያስቀምጣል፡፡
"የቅድመ ምርጫ ውጤት ግምቱ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ከፍና ዝቅ የማለት ዕድል ያለው ቢሆንም፣ የክልል ምክር ቤቶችን በማሸነፍ ረገድ የብልጽግና ተኮር ጎራ፣ አናሳ ሕዝብ ከሚኖርባቸው ክልሎች መካከል የተወሰኑትን ሊያሸንፍ የሚችልበት ዕድል መኖሩ አይካድም፤ ከትልልቆቹ ክልሎች ውስጥ ግን አንዱንም የማሸነፍ ግምት አልተሰጠውም። ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት ብልጽግና ፓርቲ ሀገሪቱ ውስጥ ካሉ ሁለት የፖለቲካ የኀይል አሰላለፍ መገለጫ አመለካከቶች ውስጥ አንዱንም የማይወክል፣ ሁለቱንም የአስተሳሰብ ማኅበራዊ መሠረቶች፣ በእወደድ ባይነት ስልት /Populism/ ለማስደሰት ወይንም ላለማስከፋት ሲል በወሰደው “አቋም የለሽ” የመሆን ምርጫ፣ ከሁለት ያጣ ወይም ከማኅበራዊ መሠረቱ የተነቀለ የፖለቲካ ጎራ በመሆኑ ምክንያት ነው።" ይላሉ፤አቶ ልደቱ፡፡     
 እንዲህ ዓይነቱን የምርጫ ውጤት ቅድመ ግምትና ትንተና ማቅረቤ፣ ሀገራችን በድኅረ ምርጫ 97 ወቅት የገጠማት ዓይነት ወይም ከዛ የባሰ የህልውና ቀውስ ውስጥ እንዳትገባ የማገዝ አዎንታዊ አስተዋእጾ ይኖረዋል በሚል እምነት ነው የሚሉት አቶ ልደቱ፤ የ97 ምርጫን አስመልክቶ በወቅቱ በቅንጅት ውስጥ አቅርቤው የነበረው ተመሳሳይ ‹‹የቅድመ ምርጫ ውጤት ግምትና ትንተና›› በኋላ በምርጫው ከመጣው ውጤት ብዙም ርቀት እንዳልነበረው ይገልጻሉ፡፡ ፡

አቶ ልደቱ አያሌው፤ "ሻሞ! “274” የሽግግር መንግሥት ጥያቄ ለሀገራችን ወቅታዊ፣ ጠቃሚና፣ ምትክ የለሽ መሆኑን የሚያሳይ የቅድመ ምርጫ ግምትና ትንተና" በሚል ያቀረቡት ሰነድ፤ በ26 ገጾች የተቀነበበ ነው፡፡
Read 14747 times