Monday, 18 May 2020 00:00

" ማን ያውጋ የነበረ ፤ ማን ያርዳ የቀበረ "

Written by  (ሻሎም ደሳለኝ)
Rate this item
(2 votes)

የስልጣኔ ምንጩ እውቀት ነው። ያወቀ ሰው ደግሞ ስልጡን ነው። እርግጥ ምሁራን የተባሉ ሁሉ አውቀዋልና ስልጡን ናቸው ማለት ነውር ቢሆንም።
"ማን ያውጋ የነበረ ፤ ማን ያርዳ የቀበረ" የሚል በሥነ ምግባር የሰለጠነ ማህበረሰባዊ አባባል አለን። ያለ ነገር አባባሏን አላነሳኋትም። ብሂሉን የሚጋፋ ድርጊት አብዝቼ ስላስተዋልኩ እንጂ።
በታሪክ ድርሳናት ላይ መጠዛጠዝ፣ ፈቅ በማይል ፖለቲካ መነካከስ፣ ሙያ እና ሙያተኛን ማራከስ የየዕለት ተግባራችን ከሆነ ሰነባብቷል።  
ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን "በእሳት ወይ አበባ" መድበሉ ውስጥ የተካተተ "ረሃብ ስንት ቀን ይፈጃል?" የሚል ግጥም አለው። ከርዕሱ ለመረዳት እንደሚቻለው ግጥሙ የሚያወሳው ረሃብን ነው። ስለ ረሃብ ብዙ ደራሲዎች ደርሰዋል። አንዳንዶቹ በምናብ ሌሎቹ በተግባር ተርበው ገጥመዋል።
በአንድ ወቅት ውጭ ሀገር ትምህርቱን በሚከታተልበት ወቅት፣ ረሃብ የቆነደደው ሰዓሊና ገጣሚ ገ/ክርስቶስ ደስታ፣ የተፈጠረበትን ስሜት በዚህ መልኩ አስፍሮ ነበር :-          

ወጡ ቀለም ሆኖ እንጀራው ብራና         
ይድረሰኝ ደብዳቤ ተርቤአለሁና         
ይሽተተኝ ቁሌቱ                             
የቅመም ሽንኩርቱ         
በርበሬው ይበተን ነፋስ ይዞት ይምጣ         
በዝናም ላኩልኝ ጠላውን ልጠጣ         
ልስከር በፊልተሩ!                             
ይረሳኝ ችግሩ . . .   

በዚህ ግጥሙ ውስጥ ገብሬ ነገረ ጉዳዩን የመግለፅና የመሳል ብቃቱ ጥግ መድረሱን ከመመስከር በላይ እኔን የሚገዛኝ በወቅቱ ደርሶበት የነበረው የረሀብ አድማስ ጥግታው ነው። "ምን ያክል ርሃብ ቢያንገላታው ነው እንዲህ የፃፈው?" ብሎ መብሰክሰክ ሚዛን ይደፋብኛል። ገጣሚው "ጠነነኝ- ጠኔ በረታብኝ" እያለስ ገለጣውን ከራቡ ፣ ስንኙን ከጥሙ አልቆ ማቆላመጥ ነውር አይሆንም?  
"የባለ ቅኔው ኑዛዜ" በሚል ርዕስ ፋሲካ ከበደ ባሳተመውና በሙሉጌታ ተስፋዬ የሕይወት ታሪክ ላይ በሚያጠነጥነው መጽሀፍ ውስጥ  ሙዚቀኛ ተፈራ ነጋሽ በአንድ ወቅት ሙሉጌታ ተስፋዬን ምሳ ጋብዞት ሲያበቃ፣ ስለ ድህነት የሚያትት የዘፈን ግጥም እንዲፅፍለት ላቀረበው ተማፅኖ ሙልጌታ እንዲህ ብሎ መልሶለት ነበር :-
 " ስለ ድህነት እንድጽፍልህ ከሆነ፣ ያን ሁሉ ምግብ ከመጋበዝህ በፊት አትነግረኝም ነበር። አሁን እንዲህ ቁንጣን እስኪይዘኝ ጠግቤ ስለ ድህነት በምን አውቃለሁ ብለህ ነው ?" ገጽ-94 ።
 "ህመም ከተሰማህ በሕይወት አለህ ማለት ነው ፤ የሰው ችግር ከተሰማህ ግን አንተ ሰው ነህ ማለት ነው" የሚል አባባል አለ፤ በሰው ጫማ ቆሞ የሰው ህመም መጋራት ትልቅ ጥበብ መሆኑን የሚዘክር። ለኔ ግን ይሄ የአሴምፕቶት ጫወታ ነው። "how Close?" የሚለውን ይመልስ ይሆናል እንጂ መሆንን አይተካም። ለዚህ ይመስለኛል ከምንግዜም ምርጥ የግጥም መድበል ውስጥ አንዱ በሆነው "እሳት ወይ አበባ" መድበል ውስጥ  "ርሃብ ስንት ቀን ይፈጃል?" የሚለው ሥራ ስሜቴን ኮርኩሮ አጢኖት እንድቸረው የጋበዘኝ።
ጋሽ ጸጋዬ በዚህ ግጥሙ ከላይ የጠቀስኩትን አይነት ስልጡን ማንነቱን አሳይቶበታል። ብስልነቱ ጎልቷል። ጠያቂነቱ ቀድሟል። በመጠየቁ ማወቁን አጠይቋል። ሊቅነቱ ተስተውሏል። ስላላየው በድፍረት ፣ ስላልሰማው በኩራት አያወራም። ይልቁንም ይጠይቃል። ባለጉዳዩን ያስቀድማል። በመሰለኝ አይወጠውጥም። ርሃብን አያውቀውምና የራበውን ሰው "ርሃብ ስንት ቀን ይፈጃል?" ብሎ ይጠይቃል።
.
ቆሽት-ሲቃው ሳያጣጥር ሰቀቀኑን ሳያጋግል
እስትንፋስ ስልምልም ሳትል
ቀጠሮ ይሰጣል ረሃብ? ለስንት ቀን ለስንት ያህል?
ስንት ሰዓት ነው የራቡ አቅሙ?
ለኔ ብጤማ ትርጉሙ
የሁለት ፊደል ድምፅ ነው ፥ 'ራብ' የሚሉት ከነስሙ
እንጂ የኔ ብጤውማ
የት አውቆት ጠባዩንማ
ብቻ ሲነገር ይሰማል
ይህንን ሁለት ፊደል ቃል . . .
ቃሉማ ያው በዘልማድ ይነገራል ይለፈፋል
ይተረካል ይዘከራል
ይደጋገማል ይተቻል
እንጂ እንኳን ጠባዩንና የራብ ዕድሜውን የት ያውቃል? . . .
ስንኞቹ የሚተርኩልን ያላወቀውን ሲጠይቅ፣ ያልገባውን "እንዴት ይሆን?" ሲል የተገኘን ሰው ነው።
እስቲ እናንተ ተናገሩ ተርባችሁ የምታውቁ
ከቸነፈር አምልጣችሁ እንደሆን ያስችላችሁ እንደሁ ጥቂት
ቀጠሮ ይሰጣል እልቂት?
ስንት መዓልት ስንት ለሊት?
እርግጥ ገጸ-ሰቡን በደራሲው ቦታ መተካት አግባብ ባይሆንም "እንዲህ ያለ ነገር ሳይዘራ አይበቅልም" ነውና ነገሩ ጋሽ ጸጋዬ ስንኙን በወፍ ዘራሽ ስሜት ከተበው ማለት ይተናነቀኛል ። ሌሊሳ ግርማ "እንግዲህ እንዲህ ከተሰማኝ ፤ እውነት ነው ማለት ነው" ይላል። እኔም ተዋስኩታ።  
ጋሽ ጸጋዬ መተናነስ (ማነስ አለማለቴን ልብ ይሏል) ግድ ብሎት እንጂ ዳዊት ሲደግም መፆሙ ፣ ፆሙ ረሃብ ምን እንደሆነ መጠቆሙ ቀረ እንድል አያስደፍረኝም። በፈቃድ መራብ ተገዶ ከመራብ መብለጡ ታውቆት እንጂ።   
ዓለም መንደር በሆነችበት፣ ቴክኖሎጂ ገመና በሚዘረግፍበት፣ ምስጢር ሁሉ ያደባባይ ፀሐይ በሚሞቅበት በዚህ ወቅት ከብዙ በጥቂቱ ፣ ከጥቅሉ በግርድፉ እያንዳንዱ ጉዳይ ላይ መረጃ ሳይኖረው የሚቀር ሰው ባይኖርም፣ "ከኔ ይልቅ ባለሙያው በምልኣት ነገረ ጉዳዩን ማብራራቱ ልክ ነው" ብሎ ማመን አግባብ ይመስለኛል ። መርዶ በቀበረ ፣ ወሬም በነበረ ሲተረክ ውብም ልክም ይሆናል። ያኔ ለጸጋዬ ገ/መድኅን ጠያቂ ስንኞች፣ የደበበ ሠይፉ ዓይነት ምላሽ የሚሰጡ ስንኞች አይጠፉም ባይ ነኝ። ጋሽ ደበበ "ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ" በሚል ግጥሙ ላይ ገጠሬ እንዲህ ያወጋል ከከተሜ :-  
የሕይወት ልብ በአውድማው ፥ በጓጥ በስርጓጉጡ
በአረሁ ላይ በገደሉ በፋልማው ላይ በዘብጡ
ለቅጽበት ሳይሰናከል ሲንር ሲመታ በቅጡ
ያሰማህ ይሆናል የከተሜ ሕልምህ ቅንጡ።
ግን ላንዳፍታ ነቅተህ ወርደህ ከከተሜ ህልም ዙፋንህ  
ፍቀድልኝ ወንድምዬ እዚህ ምን እንዳለ እኔ ልንገርህ
ዐለት ስር ሰዶ
ዐለት ወልዶ
እዚህ ዐለት
እዚያ ዐለት
የኮረብታው አናት - ዐለት
ዐለት
የላይ የታቹ መሠረት።
ቢያዩ ድንጋይ
ቢያሸቱ ድንጋይ
ጎንበስ ቢሉ ድንጋይ
ቀና ቢሉ ድንጋይ
ዋዕይ የሚያዘንብ ሰማይ።
ወንዞች ኩሬዎች
የውሃ ጥም እስረኞች
የሰው ያዕዋፍ በድን ታቅፈው
ያራዊት መቃብር ሆነው
ተኝተዋል ፤ ዐለት - ጎድናቸውን አግጠው።
.አልተርፍ አለ ሰው ለአሞራ
አልተርፍ አለ ለጥንብ አንሳ ለጆቢራ
ከላዩ መቅሰፍት ቸነፈር እያጓራ
ከሥሩ የድኝ እቶን እየደራ
.እንደው ብቻ በድቀቱ ታዛቢነት እንደታፈነ
እንደተከነ ፤ ---- እንደባከነ---- እንደተነነ ፤
ጥርኝ አፈር ያርገኝ ምኞት ሆነ። . . .
እንግዲህ እንደ ሌባ በሰው ኪስና በሰው ሙያ ገብቶ መዘላበድ ነውር የሚሆንበት ፤ መጠየቅ የሚቀድምበት ፤ መተናነስ የሚንሰራፋበት ጊዜ ያምጣልን ብዬ ከጸጋዬ እስከ ደቤ ያነሳሳሁበትን ጽሁፌን ቋጨሁ። መልካም ቀን።


Read 2229 times