Saturday, 16 May 2020 12:45

የሐኪሙ ሚስት ደብዳቤ

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(6 votes)

    ዐይኖችሽ ውስጥ የሚነዱት ጧፎች ልቤን ከሩቁ ያቀልጡትና በአጥንቴ ስሮች ልቆም ያቅተኛል፣ እንገዳገዳለሁ፤ የቀለጠው ልቤ እንደ ሎጥ ሚስት የጨው ዐምድ የሆነ ይመስለኛል፡፡ ፍቅሬ ልብሽ አበባ ነው፡፡ ንቡ ልቤ ቀለምሽን ሲያደንቅ፣ መዐዛሽን እንደ ጡጦ ሲጠባ ይቆያል፡፡ ድንኳኔ በሳቅ ፣ ዐይኔ በተስፋ እንዲሞላ፣ ዐይኖቼ ሰማይና ምድር የገጠሙበት አድማስ ላይ በትካዜ ከመጎለት የሚድኑት ባንቺ ነው፡፡
አንቺ ግን ያንን አበባ ልብ ብዬ እንዳላይ መግቢያ እልፍኙን እሾህ ነስንሰሽበታል፤ ኮስታራ ዐጸዱ ያስበረግጋል፡፡ ይሁንና ደም ረጭቼ እየቧጠጥኩም ቢሆን ልብሽን ፍለጋ መዳከር አላቋርጥም፡፡ ብዙ ጊዜ ደግሞ በእጆችሽ መጻሕፍት ይዘሽ ዐይሽና እቀናለሁ:: እነዚያ መጻሕፍት በዚያ ወርቅ ልብ ውስጥ የሚጨምሩት መዐዛ ያስቀናኛል:: ማን ያውቃል፣ ያ ልብ ከነቁንጅናው የኔ ይሆን ይሆናል፡፡ ‹‹ማን ስለሆንክ!›› ትዪኝ ይሆናል፡፡ ፍቅር አይተነበይም፡፡ ከዚህ ዐመድ ከተሞላ ዐለም ጀርባ ያለው የገነት ውበት ያለው እኔና አንቺ ልብ ውስጥ ነው፡፡ በፍጥሞ ደሴት ራእይ ያየው ዮሃንስ በግዞት ሆኖ ነው፡፡ አሁን በተዘጋው ደጅሽ ቆሜ የማወራሽ ሰው፣ ነገ ቤትሽ ውስጥ የምቆመው ምሰሶ ልሆን እችላለሁ፡፡ ሳቂ ያን ሳቅሽን፡፡ ትምህርት ቤት እያለን የምታፌዥውን ፌዝ አፊዢ፤ ያ ለኔ ሙዚቃዬ ነው፡፡
አሁን ግን ለጊዜው በላጤ ቤቴ፣ በራሴ ሰማይ የምታበሪ ኮከብ ነሽ፡፡ የወጣትነት ዜማዬ፣ ወደፊትም የትዝታዬ ኩል፣ የመዝሙሬ ግጥም አንቺ ነሽ፡፡ ሳስብሽ ይነዝረኛል፤ ስሰማሽ ያስደነግጠኛል፡፡ የልጅነት ጓደኛዬ የክፍሌ ተማሪ፣ የናፍቆቴ ጅማሬ ነሽ፡፡ የፍቅር መንገዴ ጠራጊ፣ የምደረበዳዋ ድምጽ!! ከደሞዝ በፊት ያገኘሁሽ ሀብቴ፡፡ ሳሮኔ!
የተወደድከው ባለቤቴ ኤፍሬም!...ዛሬ ይህን ኢ ሜል ስታየው ግር እንደሚልህ አስባለሁ፤ ምናልባትም በትዝታ ነቅለህ ወደ ወጣትነት ዘመናችን እንደምትነጉድ አልጠረጥርም፡፡ ደብዳቤህ አንድ የህክምና ሰው የጻፈው ነው ለማለት ምን ያህል እንደሚከብድ እየው፡፡
እኔ የቋንቋ መምህር ሆኜ እንኳ እንዳንተ አልጽፍም፤ እንዳንተ በዘይቤ ናዳ የሰው ልብ አልንድም፤ በጽጌረዳ ውበት የተፈጥሮን ገጾች አላሸበርቅም፡፡ በድሮው ደብዳቤህ የጀመርኩት ወደ አሁኑ ጉዳዬ ከመምጣቴ በፊት በትዝታ ዘመናችንን ልቆስቁሰው ብዬ ነው፡፡ መቸም እንደ ሩስያዊው ደራሲ ኢቫን ቱርጌኔቭ ዘመን፣ በደብዳቤ ውስጥ የሚሸት አበባ መላክ ባይቻልም፣ በቃላት የተሳሉ የትዝታ ክሮችን መምዘዝ ግን ማንም አይከለክለንም፡፡
ወድ ባለቤቴ አሁን አንተ ጦር ሜዳ እንዳለ ወታደር፣ እኔ ደግሞ እንደ ዘማች ሚስት ነን፡፡ አንተ ወረርሺኙን ስትዋጋ፣ እኔ ተማሪዎቼንና ልጃችንን ልረዳ በዚህ የታሪክ አጋጣሚ ቆሜያለሁ፡፡ ልጃችን ሆሜር አንተን እያሰበ የሚናገረው ይገርመኛል፡፡ ሀኪም ባይኖር ሰው ምን ይሆን ነበር!›› ይለኛል፡፡ ሀኪም ወትሮም ሕይወቱን ሰጥቶ የሚሰራ፤ ሌሎችን ለማዳን ራሱን አደጋ ውስጥ የሚጥል እንደሆነ ነገርኩት፡፡ ብዙ ሀኪሞች ለወገኖቻቸው ሲሉ ሞተዋል፡፡ በተላላፊ በሽታ ተጠቅተዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸውን ጥለው አልፈዋል፡፡ ግን ደግሞ ሀገራችን ሀኪም አታከብርም፡፡ እኛ ሀገር ፖለቲካችን ካድሬ ሲያነግስ የኖረ ነው፡፡ ፕሮፌሰሮች ተገድለው፣ የቀበሌ ገዳዮች የሚሾሙባት ሀገር ሆናም ነበር፡፡ ቢሆንም ያለፈውን ትተን፣ አሁን ልንለውጣት እንሰራለን፡፡ መጀመሪያ ግን አሁን ከፊታችን የተገተረውን ኮቪድ አስራ ዘጠኝ ተዋግተን እንለፍ፡፡ አንተ ወገኖችህን በመርዳት በርታ!! መከላከያ ሠራዊት ውስጥ ያለው ወንድሜ፣ የሀገር ጸጥታ በማስከበር እየሰራ ነው፡፡ እኔ ልጃችንን አስተምራለሁ፤ ተማሪዎቼን አስጠናለሁ፤ ራሴንና ጎረቤቶቼን እጠብቃለሁ፤ ደሆች ወገኖቼን ካለኝ በማካፈል ከሀገሬ ልጆች ጎን እቆማለሁ፡፡ ወደ ታሪክ መለስ ብለን ስናይ አያቴ ማይጨው ዘምቶ ሞቷል፡፡ እኔ ግን የጦር ግንባር ፍልሚያ የለብኝም፡፡ ነገር ግን ሕይወቴን ለስራዬ በመስጠት መልካም ታሪክ እደግማለሁ፡፡ ሁላችንም ሀገራችንን እንደምንወድ የምናሳየው በመሞት ብቻ አይደለም፡፡ በተሰማራንበት ቦታ ሁሉ በቅንነትና በእውነት ስንሰራ ነው፡፡
መከላከያ ሠራዊት ውስጥ ያለው ወንድሜ፣ ሀገር በማረጋጋት ተግባር ላይ ተሰማርቶ ሳየው እደነቃለሁ፡፡ አያታችን የዘራው ዘር መሆኑን አስባለሁ፡፡ ዐርበኛው አበበ አረጋይ ውስጥ የበቀለው የጎበና ዳጨ ዘር ነበረ፡፡ እንዲህ ሠንሠለቱ ይቀጥላል፡፡ ነገ ልጃችን ሆመርም ያንተን ዳና ይከተላል፡፡ አያቴ ለሀገር እንደ ሞተ ወንድሜም ለወገኖቹ ሰላም ለመሞት የተዘጋጀ ነው፡፡ በተለይ አሁን ሀገሪቱን ለማፍረስ ኢትዮጵያዊነትን አቅልለው ለጥፋት የተነሱ ክፉ ሰዎች በበዙበት ወቅት ብሄርና ሃይማኖት ሳይለይ ለሀገሩ ዘብ የቆመው መከላከያ ሰራዊታችን ምስጋና ይገባዋል፡፡ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ሆኖ በመቆም ጥፋትን ስለመከተ በታሪክ ሊዘከር ይገባል፡፡ ሀገር ያስተማረቻቸው ሰዎች በስልጣን ጥማት ሰክረው ለጥፋት ሲዘምቱ፣ የሀገር ደህንነት ከብሄር ግብግብ ትቀድማለች ያለውን ሰራዊት ሳስብ እኮራለሁ፡፡---እንዳንተ ደግሞ በኮሮና ወረርሽኝ የተጠቁ ወገኖቹን ለመርዳት ሕይወቱን ለአደጋ አጋልጦ ሌት ተቀን የሚተጋውን  የሕክምና ሰራዊት እልፍ ጊዜ አጨበጭብለታለሁ፤ ጭብጨባዬን የትውልድ መዝሙር ሆኖ ይቀጥላል:: አድማሳት የሚያስተጋቡት ብሄራዊ ኩራት ሆኖ ይደነቃል፡፡ ---ባሌ፣ አንዳንዴ በእንቅልፍ ልቤ አብረኸኝ ያለህ እየመሰለኝ፣ ጎኔን እዳብስና ሳጣህ ሆዴ ይባባል፡፡ ግን ምን ይደረጋል! --በክፉ ቀን ለሀገርና ለወገን ራስን  መስጠት፣ ከአባቶቻችንና ከእናቶቻችን  የተማርነው ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ ታሪካዊ ተጋድሎ ውስጥ ባሌ ተሳታፊ በመሆኑ ኩራቴ የትየለሌ ነው፡፡
ዐድዋ ዘመቻ ላይ እናቶቼ እንደ ዘመቱ እኔም የፈንታዬን እዚህ ዘመቻ ላይ አዋጣለሁ፡፡ እንደ ዐጼ ዮሃንስና እንደ ዐጼ ምኒልክ ነጋሪት ጎስሜ አዋጅ ባላስነግርም፣ ሁሉም ያገር ሰው ጉዳዩ እንደሚመለከተው መናገሬን ግን አልተውም፡፡ ፖለቲከኛው ሀገሩን ትቶ ለስልጣኑ ቢዘፍን ከባንዳ ለይቼ አላየውም፤ የዚህ ዐይነቱን ሰው ቅድም የጠቀስኩልህና አንተ የምታደንቃቸው ምሁር የዚህ ዐይነቶቹን ‹‹በሕይወቱ ጥረት የለውም፡፡ ከስልጣን በስተቀር:: በቀጥታም ሆነ በአቋራጭ በሚገባም ወይም በማይገባም እንደ ምንም ብሎ የፖለቲካ የገዢነት የአስተናባሪነት ሥልጣን እንዲኖረው ይጥራል፡፡›› ይላሉ፡፡ እኛ ከዚህ ወገን አይደለንም፡፡  ሀገርና ወገን ከሁሉ ይቀድማል፡፡
ያንተ ነገር የካድሬ ወሬ አወራሽብኝ፤ወይም ስብከትሽን ጀመርሽ እንደማትለኝ ተስፋ አለኝ፡፡ ያንተ ሰሞኑን የዐርበኞች ቀን ትውስታ ስላለብኝ ወደ ሀገር ፍቅርና ነጻነት ባደላ አትገረም፡፡ ትውልድ አቅም የሚያገኘው የቀደመው ካስቀመጠለት መልካም ተጋድሎ ነው፡፡ ሰሞኑን ያገሬ ዐርበኞች ተጋድሎ ውስጤ ላይ እየነደደ ነው፡፡ ዐማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ… ኢትዮጵያዊ ሆኖ ለሀገሩ ያልደማና ያልሞተ ማነው!!
እናንተ በሕክምናው ስትደክሙ፤ እኛም በከተማ ማድረግ ያለብን ነገር እንዳለ ታውቃለህ፡፡ መጠንቀቅ፣ ራሳችንን መጠበቅ አለብን፡፡ ይሁን እንጂ የሕክምና ባለሞያዎች ከሚነግሩን ይልቅ ፌስ ቡክ የሚያወራውን ይዘን ፖለቲካ የምንደልቅ ጥቂት አይደለንም:: ታክሲ ውስጥ እንኳ ጭምብል ለማድረግ ‹‹መብቴን አትንካ›› እያልን ከፖሊስ ጋር ግብግብ የምንፈጥር ጥቂት አይደለንም፡፡ የኛ ነገር ብዙ ይቀረዋል፡፡ ቢሆንም ከሰራን በቅርቡ እንለውጠዋለን፡፡ የፖለቲከኞቻችንን ነገር አላነሳብህም፡፡ ኮሮና ተረስቶ ዜማቸው ስልጣን  ሆኗል፡፡ ልካችን ይህን ያህል ነው፡፡
አንተ ግን አሁንም እንደ ዮሃንስ እስከ መስቀሉ እንደምትሄድ ተስፋ አደርጋለሁ:: እንደ ጲላጦስ በሀገር ጉዳይ እጃቸውን ታጥበው ከሚቆሙት ተርታ ስላልሆንክ እኮራብሃለሁ፡፡ ልብህ እንደ ናፖሊዮን ካርታ አለው፣ እንደ ሉተር ኪንግ ሕልም አለኝ የሚል፣እንደ ጋንዲ በምህረት የሚያምን፣ እንደ ቶሮው አዲስ ነገር የሚፈልግ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ለኮሮና መድሀኒቱ እንደዚህ ያለው ልብ ነው፡፡
አንተ በምጥ አልፈህ፣ የረገፉ ቅጠሎችን ሳይሆን፣ ለሀገርህ የፈካውን ጽጌረዳ አቀብላት፡፡ ሰው ትፈልጋለች፤ታማኝ ልጅ ትሻለች፡፡ ስለዚህ በታማኝነት ማማ፣ በቁርጠኝነት ዐጸድ ውስጥ ተገኝ፡፡ በክፉ ቀን ሀገርህን መታመን በታሪክ መዝገብ ውስጥ ለዘላለም መንገስ ነው፡፡ ከሃዲ ሆኖ ከመኖር ታማኝ ሆኖ መሞት በጣዕሙ እጅግ ይበልጣል፡፡ እንደ ይሁዳ አትካዳት፤ እንደ ጴጥሮስ አትሽሽ፡፡
እስራኤል በባቢሎን ምርኮ በወደቀ ጊዜ የጠላትም ዘፈን የናቁ፣ የአምላካቸውን ቃል ኪዳን የዘመሩ፣ የነበሩትን ያህል ታሪካቸውና ማንነታቸው ያበቃ መስሏቸው፣ ሕልማቸውን የጣሉ፣ በጠላቶቻቸው ዘፈን ልባቸው የወደቀ ብዙ ነበሩ፡፡ ግና ጥቂቱ ምኩራብ ላይ ተሰብስበው ቃል ኪዳናቸውን ጠብቀው ክፉውን ቀን አልፈዋል፡፡ እኛ ከከሃዲዎቹ ወገን አለመሆናችን አሁንም ያኮራኛል፡፡
እኔ ከተማሪዎቼ ዐይኖች የምለቅመው የታሪክ ጉድፍ የነገውን ትውልድ የቤት ስራ የሚያቃልል ይመስለኛል፡፡ በልባቸው ላይ የምጽፈውም የሀገሬ ሕልም እውን መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ እሸት ልቦች ላይ ታሪክ መጻፍ ትልቅ ሀውልት የመስራት ዕድል ነውና እጠቀምበታለሁ፡፡ አንተ ወገኖችህን እየረዳህ፣ ለራስህም እየተጠነቀቅህ እንድትቀጥልና እንድትበረታ እኔና ልጅህ አደራ እንላለን፡፡
አሊያ ግን አደባባይ የምታየው በቴሌቪዥን ባንዲራ ለብሶ የሚያላዝነው ሁሉ ለሀገሩ እንዳይመስልህ፣ ለሆዱ ነው:: አንዳንዱ ብር ይነጥቅበታል፤ ሌላው ስሙን ይሸጥበታል፡፡ ግብዝነትም አለበት፤ ጸሎቱም የታይታ ሊሆን ይችላል፡፡ አንተ  ዌልስ ብለህ የምትጠቅሰው ሰው “I hate whene the people pray on the screene” እንዳለውም ይሆናል፡፡ አንተ ግን እስከ ፍጻሜው ሂድ የሚለውን ቅዱስ ቃል ተከተል፡፡ የተማሪነት ቆፍጣናነትህ አሁንም ይቀጥል፡፡ አንተን ከፍቅር በቀር የሚያሸንፍህ እንደሌለ አውቃለሁና ጀግናዬ ጀግን፡፡ አንበሳዬ በርታ!!
ሀገር ሁሌም ሆድዋ ዝንጉርጉር ነው:: በእንባዋ ቀን ቆጥሮ መልካም ዘር ቢበቅልም እርሻው መሀል እንክርዳድ የሚዘሩ ተኩላዎችም አሉና ሕሊናህን ጠብቅ፡፡ ለሀገር መኖር፣ ለሀገር መሞት አንዳንዶች እንደሚሉት መበለጥ አይደለም፤ አያቶቻችን ባይሞቱ ሀገራችን አልነበረችም:: የምታደርገውን ሁሉ ስታደርግ ለምትወድደው ልጅህ በጎ ዘር እያስቀመጥክ እንደሆነ አስበህ ደስ እያለህ አድርገው፡፡ ለሕሊናህ ስትል በጎ ነገር አድርግ፤ ያን ደስታ ዳተኞች አያገኙትም፡፡ እጓለ ገብረዮሃንስ በመጽሐፋቸው አናክሳጎራንን ጠቅሰው፤ ‹‹የስነስርዐት ምንጩ ሕሊና ነው፡፡›› ይላሉ:: የኔ ጀግና በርታ!!
የተለመደ መዝሙርህን እየዘመርክ ስራህን ቀጥል፣ ሃኪሙ ወታደር በርታ!!
ተራመድ በርታ በርታ ጉዞህንም ፈጽም፣
ሕይወትህንም አድን፡፡
(ለማህጸን ሀኪሙ ለዶክተር ጌትነት ግዛውና ለሌሎች ሲሉ ሕይወታቸውን ላጡ፣ እርሱን ለመሰሉ ሐኪሞች መታሰቢያ!)

Read 2551 times