Print this page
Wednesday, 20 May 2020 00:00

ከኮቪድ-19 በኃላ፤ ጉርብትናና ወዳጅነት በኢትዮጵያ ስነ-ሰብዓዊ ምልከታ (Anthropological perspective)

Written by  ሮቤል ሙላት
Rate this item
(1 Vote)

በተለይ ከ2000 ዓ.ም በኃላ ተወራራሽ፣ ተደጋጋፊ እና ተካካቢ በሆነው የኢትዮጵያ የባህል ባላ ላይ በፍጥነትና በብዛት አያሌ ቅጠሎች እያቆጠቆጡበት ይገኛሉ፡፡ የቤተሰብ፣ ትምህርት ቤት፣ ሀይማኖት እና መንግስዊ ተቋማት ቅርጻቸው ብቻ ሳይሆን እድገታቸውና ይዘታቸውም እየተቀያየረ መጥቷል፡፡ ቅርብ የነበሩ እሴቶች እሳት እንደነካው ፌስታል ሲጨማደዱና ባዳ ሲሆኑ፤ ሩቅ ያሉ የሚመስሉ ትውፊቶች ደግሞ መጤነትን ተሻግረው ባለድርሻ ሆነው አርፈዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት መስፋፋት፤ የመሰረተ ልማት መጎልበት እና የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች መበልጸግ ደግሞ ለውጡ ድንገቴና አቅጣጫ አልባ አድርገውታል፡፡
ባህላዊና ማህበራዊ ህይወትን ከሚለውጡ አበይት ኩነቶች መካከል ቴክኖሎጂ፣ በሽታ፣ ድርቅ፣ ጦርነት፣ ስደት እና ሌሎች ተጠቃሽ ምክኒያቶች ናቸው (Stroma Cole, 2008)፡፡ ኢትዮጵያም ከላይ ለተጠቀሱት ገፊ ክስተቶች እንግዳ አይደለችም፡፡ ሀገሪቱ ባሳላፈችው ረጅም የታሪክ ሀዲድ ላይ ስሟ ከረሀብ፤ ከጦርነት እና ከጠኔ ጋር ሲነሳና ሲጣል፤ ሲቦካና ሲጋጋር ኖሯል፡፡ አሁን ደግሞ ኮቪድ (COVID-19) የተሰኘ ወረርሽኝ እያጠቃት ይገኛል፡፡ በሽታው ከ200 በላይ ሀገራትን አዳርሷል፤ ከ3.5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ህዝቦችን አልጋ ላይ አስተኝቷል፤ ከ300 ሺ በላይ ነፍሶችን ቀጥፏል (CNN, 12 May 2020)፡፡ ለበሽታው የተረጋገጠ ክትባትም ሆነ መድሀኒት ስላለተገኘለት የሟቾችና የኢኮኖሚ ኪሳሯው እንደሚቀጥል ይጠበቃል (WHO, 2020)፡፡ እጅን በየጊዘው መታጠብ፣ አለመጨባበጥ፣ አካላዊ ፈቀቅታን መጠበቅና ቤት ውስጥ መቀመጥ የህክምና ባለሙያዎች በሽታውን ለመከላከል ይረዳሉ ብለው ያስቀማጧቸው የመፍትሄ ሀሳቦች ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉና ጥብቅ ጉርብትናና አብሮ የመኖር ባህል ባዳበሩ ህዝቦች ላይ እንግዳ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ጽሁፍ በአለም የጤና ድርጅት ወረርሽኝ እንደሆነ ማረጋጋጫ የተሰጠለት ኮቪድ-19 በማህበራዊ ህይወት ላይ ስለሚያስከትለው ለውጥ ይዳስሳል፡፡
ከ'ህማመ ብድብድ' እስከ ኮረና
ጌታቸው ሀይሌ (ፕሮፌሰር) "ረሀብና ተስቦ በኢትዮጵያ" በተሰኘና ፲፲፱፻፹፩ ዓ.ም በታተመው ጥናታቸው ረሀብና ተስቦ  በኢትዮጵያ የጽሁፍ ታሪክ ውስጥ ከአስረኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት ጀምሮ እንደሰፈረ ይጠቅሳሉ፡፡ በየጊዜው የተነሱ የኢትዮጵያ ቅዱሳን ታሪክም በዘመናቸው ተስቦ (ህማመ ብድብድ) እና ረሀብ ተደጋግሞ ይነሳል ይላሉ፤
"በአጼ ዳዊት ዘመን (1375-1406 ዓ.ም) በመላው ኢትዮጵያ የተዘረጋ ተስቦ የተነሳ ይመስላል፡፡... ከእለታት ባንዱ ቀን ተስቦ በዓለም ላይ ከዳር እስከ ዳር (በአውሮፓ ጥቁር ሞት የተባለው ሳይሆን አይቀርም) ተለቀቀበትና ብዙዎች ሰዎች አለቁ፤ ተጨረሱ፡፡ በቤታቸው ለቅሶና እየየ ሆነ፡፡ በዚህ ሁኔታ ፫ ዓመት ቆየ"፡፡
"History of Epidemics in Ethiopia" የተሰኘ መጣጥፍን እኤአ በ2012 ለንበብ ያበቃው ክንፈ ገበየሁ (MD) በበኩሉ በአጼ ቴዎድሮስ ዘመን በተለይም በ1860 ከባድ የኮሌራ ወረርሽኝ በሀገሪቱ እንደተቀሰቀሰ ያስታውሳል፡፡ በተለምዶ የብርድ በሽታ ተብሎ የተጠቀሰው ይህ ኮሌራ ብዙ ህዝቦችን ከማፈናቀሉ ባሻገር ከመቶ ሺ በላይ ሰዎችን እንደገደለ ይታመናል፡፡ በወቅቱ የአጼ ቴዎድሮስ ሰራዊት በፈንግል ወረርሽን ማለቁን የተመለከተች አንዲት አልቃሽ የሚከተለውን ሙሾ እንዳወረደች ይነገራል፤
"በነጋሪትወ ሞት ተጥፎብዎ
የወጣው አይገባ ያለው አይቆይዎ"
ከዚህ ቀጥሎ በተለይም የአዲስ አበባ ህዝብን በብዛት ያጠቃውና ለህልፈት የዳረገው ወረርሽን በታሪክ "የህዳር በሽታ" ተብሎ የሚታወሰው ነው፡፡ የያኔው ታዳጊ በኃላም ንጉስ አጼ ኃይለ ስላሴ በ1911 ዓ.ም ስለተከሰተው ወረርሽኝ ጥቁር ትዝታ ነበራቸው (Richard Pankhurst, 2012)፡፡ ንጉሱ በህይወት ታሪክ ማስታወሻቸው ይህን ብለዋል፤
ከዚህ በኃላ ከህዳር ወር ፩ ጀምሮ እስከ ህዳር ፴ ቀን በአዲስ አበባና በሌላውም በኢትዮጵያ አውራጃ ሁሉ የጨነፈር (ግሪፕ) በሽታ ተስፋፍቶ ነበርና አዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከአስር ሺ የሚበዙ ሰዎች ሞቱ፡፡ እኔ ግን በብርቱ ከታመምኩ በኃላ በእግዚአብሔር ቸርነት ተረፍኩ፡፡
ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ እንደተነተኑት ጃንሆይ 'ግሪፕ' ያሉት ወረርሽኝ በዓለም ላይ ኢንፉሌንዛ ተብሎ የሚታወቅ ጉንፋን ሲሆን በወቅቱ ከ25 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ህይወት አሳጥቷል (ይህ አሀዝ በወቅቱ ከነበረው የአዲስ አበባ ጠቅላላ ህዝብ 1/5ኛ ማለት ነው)፡፡ በተጨማሪም በሀረርጌና አካባቢዋ በዚሁ ራስ በሚያዞር፣ በሚያስታውክና ደም በሚያስተፋ ወረርሽኝ አማካኝነት በቀን ከ80-120 ሰዎች ይሞቱ እንደ ነበር ራስ እምሩ ጽፈዋል፡፡ "በቶሎም ካንዱ ወደ አንዱ የሚተላለፍ በመሆኑ ብዙው ቤተሰብ እንዳለ እየተኛ አስተማሚው ብዙ ችግር ሆነ" (ዝኒከመሁ)፡፡   
የተለያዩ የታሪክና የህክምና ድርሳናት እንደሚጠቁሙት ካለፉት 50 ዓመታት ወዲህ የወባ እና የHIV AIDS ወረርሽኞች በኢትዮጵያ ሁለንታናዊ ለውጥ ላይ የራሳቸውን አሉታዊ አሻራ አስርፈዋል፡፡ የክስተቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዳፋ በተመለከተ ከተለያዩ የትምህርት አይነቶች በመነሳት ዘርፈ ብዙ ጥናቶች ተሰርተዋል (Helmut Kloos, 2001)፡፡ ይህ የኔ ምልከታ ግን ኮረና በጉርብትናና ወዳጅነት ባህል ላይ የሚያስከትለውን ለውጥ ወይም ሽግግር ለመተንተን ይሞክራል፡፡
ሙልጭልጩ ባህል
በዚህ ሁለንተናዊ ዓለም ውስጥ ያለ ለውጥ እንዳለ ቆሞ የሚገኝ ምንም ነገር የለም፡፡ ጊዜ ራሱ ከወንዝ ባልተለየ ሁኔታ ሳያቋርጥ በለውጥ እየፈሰሰ ይከንፋል ይላል ፓይታጎረስ (600ኛው ዓ.ዓ)፡፡ ቋሚ ወይም ዘላለማዊ የሆነ ባህልም ሆነ ማንንት የለም፡፡  የባህልን ምንነት ለመረዳት የእንግሊዛዊውን ስነ ሰብ (Anthropology) ተማራማሪ  ኢ. ቴይለር ትርጉም መፍቻ ማገላበጥ ግድ መሆኑን የመስኩ ባለሙያዎች ይስገነዝባሉ፡፡ Culture or civilization, taken in its wide ethnographic sense, is that complex whole which includes knowledge, belief, art, morals, law, custom, and any other capabilities and habits acquired by man as a member of society (Tylor, 1871). በቴይለር እምነት ባህል የአፈ-ታሪክ እና ሳይንሳዊ ዕውቀቱን፣ እምነትን፣ ስነ-ጥበብን፣ ሞራልን፣ ህግን እና ሌሎችን የህበረተሰቡን አጠቃላይ እሴቶች ያጠቃልላል፡፡ በተጨማሪም ዕለታዊ እንቅስቃሴዎቻችንን፣ ዝንባሌዎቻችንን፣ ህልሞቻችንን፣ አለባበሶቻችንን፣ ጭፈራዎቻችንን፣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎቻችንና ወዘተ የባህል አካል ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ጆ. ኩበር ደግሞ ባህልን በሁለት ይከፍለዋል፡፡ እነርሱም ቁሳዊና መንፈሳዊ በሚል፡፡ ቁሳዊ ባህል ሀውልቶችን፣ መጸሀፍቶችን፣ ቀደምት ቅርሶችንና ቁሳዊ ፍላጎታችንን ለማሟላት የምንገለገልባቸውን መሳርያዎች ሲይዝ፤ መንፈሳዊ ባህል ደግሞ የሀይማኖት፣ የፍልስፍና፣ የርዕዮት ዓለም እና ማህበራዊ ክንውኖችን የሚያካትት ነው፡፡ በተጨማሪም ባህል የሰው ልጅ ምክኒያታዊ ፍጡር እንዲሆን ያስቻሉት ወይም ከሌሎች ፍጡራን ለመለየት ያበቁትን ሙህራዊ፣ ስነምግባራዊ፣ አካላዊ እና ቴክኒካዊ እውቀቶችን የሚያጠቃልል ጽንሰ-ሀሳብ ነው፡፡
የስነ-ሰብ የጥናት ዘርፍ የባህል ለውጥን በሁለት ግዙፍ ዋርካዎች ከፍሎ ለማየት ይሞክራል፤ በቅርጽ/ተግባራት እና በተግባሪዎቹ (Dena Freeman, 2002)፡፡ በተያያዘም በባህል የለውጥ ፍሰት ውስጥ ሁለት ዋና ዋና ክስተቶች እንደሚከናወን E.K.Oke (1984) ያስረዳል፡፡ እነርሱም መቀበል እና መዋሀድ (Acculturation and Integration) ልንላቸው እንችላለን፡፡ አዲስ ባህልን በመቀበል ሂደት ውስጥ ሶስት የቅበላ ስነ-ስረዓቶች አሉ፡፡ የመጀመርያው መዋጥ (Assimilation) ይባላል፡፡ በሁለት የተለያ ባህሎች መስተጋብር መካከል የሀይል፣ የገንዘብ ወይም የሰው ቁጥር ወይም የዕውቀት አቅሙ ከፍተኛ የሆነ ማህበረሰብ ባህሉ ገዢ እና ተመራጭ ሲሆን የሚፈጠር ለውጥ ነው፡፡ ለምሳሌ በወ/ሮ ሀ እና በወ/ሮ ለ በተፈጠረ ማህበራዊ ግንኙነት  የወ/ሮ ለ ባህል በወ/ሮ ሀ ሲዋጥ ወይም ሲጠቃለል እንደ ማለት ነው፡፡
በሁለተኛነት የሚጠቀሰው የለውጥ ሂደት ቅይጥነት/ ድብልቅነት (Diffusion) ይባላል፡፡ እንደ ሴሪና ናንዳ ያሉ የማህበረሰብ ሳይንስ ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት የሰው ልጅ ለአዲስ ፈጠራ ባለው ጉጉነት ወይም ዝግጁነት ከራሱ የባህል ንፍቀ-ክበብ ውጭ ያለ አዲስ እሴት ሊፈጥር አለበለዚያ የተፈጠረ ሊቀበል ይችላል፡፡ ወዶም ይሁን እየተግደረደረ በሚቀበለው እንግዳ ባህል ላይ ከራሱ ማንነት ጋር አስታርቆ ሊያስኬደው ይችላል፡፡ ለምሳሌ በወ/ሮ ሀ እና በወ/ሮ ለ መካከል በተፈጠረ ማህበራዊ ግንኙነት ከሁለቱም የተውጣጣ አዲስ ባህል ወይም "ሐ" አይነቴነት ሲወለድ ማለት ነው፡፡  ንግድ፣ ቱሪዝም እና መሰል እንቅስቃሴዎች ለውህድ ማንነት ፈጠራ የጎላ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡
ብዝሀነት (Plurlism) በሶስተኛ ደረጃ የሚጠቀስ የባህል ለውጥ ሂደት ነው፡፡ ለምሳሌ በወ/ሮ ሀ እና በወ/ሮ ለ በተፈጠረ ማህበራዊ ግንኙነት ሁለቱም የየራሳቸውን ባህልና ማንነት ይዘው ሲቀጥሉ ብዝሀነት ይባላል፡፡ ይህ ሂደት ብዘሀ ቋንቋ፣ ብዘሀ ሀይማኖትንና እና ብዘሀ ትውፊት ባላቸው  ማህበረሰቦች ዘንድ ጤናማ ማህበራዊ ቁርኝት እንዲኖር ያስችላል፡፡ በተጨማሪም የባህል ልዩነትን እንደ ጸጋ እንጂ እንደ ስጋት ስለማያይ ለቀን ከቀን ማህበራዊ መስተጋብር ፣ ኢኮኖሚያዊ ቅልጥፍናና ሰላማዊ ፖለቲካዊ ፍክክሮች ቀና መንገድ ይፈጥራል (Richared Jenkins, 1995).   
ባይለይኝ ጣሰው (2019) በበኩሉ ሚልተን ጎርድንን በመጥቀስ የባህል የውህደት ሂደት በሶስት ዋና ዋና መንገዶች ወይም ደረጃዎች ይከናወናል ሲል ያስረዳል፡፡
አንዱ ባህላዊ ውህድት cultural assimilation ነው፡፡ ይህም የአንድ የህዝብ ቡድን በማንኛውም የአኗኗር ስልት ሁሉ በቋንቋ፣ በእምነት፣ ልማዳዊ አሰራሮች፣ ትውፊታዊ ደንቦች ወዘተ ሁሉ የሚከናወን ሂደት ነው፡፡ ሁለተኛውየማህበራዊ መዋቅር ውህደት ነው፡፡ ይህም በማህበራዊ ግንኙነት መርበቦች፣ በቡድኖች አደረጃጀት፣ በማህበራዊ የሙያና የስረ አከፋፈል ተዋረዶች እና ማየህበረሰብ መዋቅሮች መካከል የሚደረግ ውህደት፡፡ ሶስተኛው በጋብቻ አማካኝነት የሚከናወን ውህድት ነው"፡፡
በአጠቃላይ በጊዜና በቦታ ቅይይር አማካኝንት ባህል ይለወጣል፡፡ ምናልባት ለውጡ ፈጣን ወይም ቀርፋፋ ሊሆን እንደሚችል Stroma Cole, 2008፤ Ellis Cashmore, 1984፤ Ronald Inglehart and Christian Welzel, 2005 እና ሌሎችም ጽፈዋል፡፡
"በጨለማ የሰጡኝን በብርሃን እንዳስረክብ ፈጣረዬን እለምን ነበር"
ከሁለት አስርተ ዓመታት በፊት፡፡ አንድ የነበሩ ነገር ግን ፖለቲካ ሁለት ያደረጋቸው እናትና ልጅ ሀገሮች ተጣሉ፡፡ ጦርነትም ገጠሙና በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ህይወት ቀጠፉ፤ እንዲሁም የአያሌ ዜጎችን ሰላማዊ የዕለት ተለት ህይወት አመሰቃቀሉ፡፡ ማህበራዊ ኑሯቸው ከተገለባበጠባቸው እናቶች መካከል ወ/ሮ ሻሽቱ ንጉሤ እና ወ/ሮ ምግብ ተመስገን የሚታወሱ ናቸው፡፡ ሁለቱም የጎንድር ከተማ ነዋሪ ብቻ ሳይሆን ጎረቤታሞችም ነበር፡፡ ሰለምታ ከመለወወጥ ባሻገር ዕቃ መዋዋስ፣ በተለያዩ ማህበራዊ ተቋማት ውስጥ በጋራ መሳተፍ እንዲሁም ክፉና ደጉን አብሮ ማሳለፍ የሁልግዜ ልማዳቸው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል የነበረው ፖለቲካዊ ሁኔታ እነዚያን ወዳጆች ለያያቸው፡፡ ወ/ሮ ምግብ ሦስት ወልደው ያሳደጉበት፣ ከጎረቤቶቻቸው ጋ ደስታና ሀዘን ያዩበትን ቤት ጥሎ መሄድ ከባድ እንደነበር ይናገራሉ።  ወ/ሮ ምግብ ጎንደር ለ26 ዓመታት ያህል ኖረዋል፡፡ኢትዮጵያዊ አግብተው ወልደው ከብደዋል፡፡ በወቅቱ በነበረው ፖለቲካዊ ሁኔታ ኤርትራዊያን ወደ አገራችው ግቡ በተባለው መሠረት ቤት ንብረታቸውን ትተው ልጆቻቸውን ብቻ ይዘው አገራቸው ገቡ (ቢቢሲ, 2010)፡፡ ወቅቱ ጭንቅ ስለነበር ወ/ሮ ምግብ ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ነበርና ጥለው የወጡት እቃቸውን መልክ መልክ ማስያዝም የወ/ሮ ሻሽቱ ኃላፊነት ነበር፡፡ የቤት እቃዎቻቸው የተወሰኑት ተሸጠው አዲስ አበባ ለሚገኙት እህታቸው እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ ለቀረው ልጃቸው እንዲሰጥላቸው አደራ አሉ፤ ወ/ሮ ምግብ፡፡  ይህንን ለማድረግ ወ/ሮ ሻሺቱ አደራ ተቀበሉ፡፡
ሀያ ዓመታት ነጎዱ፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራም በ2011 ዓ.ም ታረቁ፡፡ ተለያተው የነበሩ እናትና ልጆችም ተገናኙ፡፡ ወ/ሮ ምግብም ለመጀመርያ ግዜ ወደ ጎንድር ተመለሱ፡፡ ቤታቸውን ትተው ሲሄዱ ተመልሼ አገኘው ይሆናል ብለው ያስቡ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ለቃላቸው ታማኝ የሆኑት፣ ቃላቸውን ጠብቀው ያቆዩት ወ/ሮ ሻሺቱ የወ/ሮ ምግብን ተስፋ አሳክተዋል።  ቤታቸው ሳይሸጥ አደራቸውን ጠብቀው በማቆየታቸው የተሰማቸውን ደስታ ወደር እንደሌለው ይናገራሉ፡፡ "በጨለማ የሰጡኝን በብርሃን እንዳስረክብ ፈጣረዬን እለምን ነበር" ብለዋል ወ/ሮ ሻሺቱ ለቢቢሲ፡፡
እንደዚ አይነት ታሪኮች በመላ ሀገሪቷ መንደሮች በብዛት  ይገኛሉ፡፡ ከግለኝነት ይልቅ በጋራ ጉዳዮች ላይ አብሮ መሳተፍ የተለመደ እሴት ነው፡፡ ከብቸኝነት ይልቅ ሰብሰብ ብሎ መጫወት ከልጅነት ይጀምራል፤ በወጣትነት ይጎለብታል፤ በእርጅና እድሜ ደግሞ ወደ ተቋምነት ተቀይሮ ይቀጥላል፡፡  በሀዘንና በደስታ ወቅት ሰዎችን የሚያቀራርቡ እንደ እቁብ፣ እድር፣ ቅሬ፣ ደቦ፣ ሰርግ፣ ወዳጃና መሰል ባህሎች በየብሄረሰቡ ሞልተዋል፡፡ በተለይም ጉርብትና ትልቅ ትኩረት ከሚሰጣቸው ማህበራዊ ትስስሮሽ መካከል ወሳኙ ነው፡፡
ጉርብትና ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ የቤተሰብ አባላት በቅርብት ወይም በተወሰነ ርቀት መካከል ተጎራብተው የሚኖሩበት ሁኔታ ነው፡፡ በአቅራቢያችን የሚኖሩ ግለሰቦች ሲወጡና ሲገቡ እየተመለከትን፤ መንገድ ላይ በአጋጣሚ እየተገናኘን ይሁን እንጂ የሚያስተሳስረን ምንም ገመድ እንደለሌ ከቆጥረን ጉርብትናችን እየጠፋ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለሆነም በጉርብትናው ዓለም ውስጥ ማህበራዊ  ግንኑነት ወይም ትስስር አስፈላጊ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ኮቪድ- 19 ይህን የቁርኝት መረብ/ክር ያላላዋል በጊዜ ሂደትም ይቀይረዋል፡፡ ይህን ለመረዳት የማህበራዊ ሳይንስ ሊቃውንት ሶስት ርዕዮቶችን አስቀምጠዋል፡፡ 1)- Symbolic interaction፣ ይህ አስተምህሮ ከቃልና ከንግግር ባሻገር በማናስተላልፋቸው የምልክት ሀሳቦችና ስሜቶች አብሮነትንና ማህበራዊነትን እናጠናክራለን ብሎ ያምናል Robert Alexnder, 1985)፡፡ በአሁኑ ወቅት በመጨባበጥ የሚካሄድ የሰለምታ ልውውጥ ለወረርሽኑ መተላለፊያ መንገድ ስለሆነ እንዲቀር የህክምና ባለሙያዎች አሳስበዋል፡፡ በመሆኑም ለመልካም ጉርብታና መሰረት የሆነውን እሴት እንዲተው ተደርጓል፡፡ 2) –Ethnomethodology፤ ይሄኛው በመሰረታዊነት ህብረተሰቡ በተጋራቸው እሴቶች የማህበራዊ ቅደም ተከተልነትላይ ያተኩራል፡፡ 3)-Dramaturgic sociology፤  ይዚህ እሰቤ  በህብረተሰቡ ተሳትፎና በመሪዎች አተገባበር ሂደት ላይ ስላለው ማህበራዊ ግንኙነታችን ያጠነጥናል ፡፡
በተያያዘም በጉርብትና አብረው በሚኖሩ ሰዎች መካከል የሚኖሩ ግንኝነቶች ጥብቅም ልልም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ምክኒያቱም የግንኙነቱ ታሪካዊ ዳራ፣ ደረጃና መጠኝ ከቦታ ቦታ ሊለያ ይችላል፡፡ ለምሳሌ የምርት መሳሪያዎች፣ የምግብ አዘገጃጀቶች፣ አለባበስ፣ ጌጣጌጦች እና መሰል እሴቶች ከአንዱ ወደ ሌላው የሚሰራጭበት ፍጥነትና ችሎታ ተጽዕኖ አለውና (ባይለይኝ ጣሰው, 2019)፡፡ በመሆኑም ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ፣ ቤት መቀመጥና ብቸኝንትን ማዘውትር ግላዊ የኑሮ ባህል እንዲዳብርና በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ያስችላል፡፡ ተከታዩ ትውልድ በበኩል ይህን ወረርሽኝ አመጣሽ አዲስ ልማድ ላይ ሀሳብ በመጨመር፣ ትርጉም በመስጠትና መሰረት በማስያዝ ተቋማዊ ያደርገዋል፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኃላም የተዳቀለ ወይም የተለወጠ ባህል ባለቤት ይኮናል፡፡ ስለዚህ ከTeories of social interaction በመነሳት የመጪው ግዚ ጉርብትና ስስ፣ ቀላልና በፍጥነት ተለዋዋጭ ይሆናል፡፡
በርግጥ በሩቁ በመጠያያቅና በመረዳዳት ጉርብትናን ከነ ሙሉ ክብሩ ለማስቀጠል የሚደረግ ጥረት ቢኖርም ወዳጅነትም ተመሳሳዩ ዕጣ ይገጥመዋል ብየ እገምታለሁ፡፡ ምክኒያቱም ወዳጅነትን ከሚያቀላጥፉትና ከሚያፋጥኑት እሴቶች መካከል ተጠቃሹ የሆነው ጉርብትና እየተሰበረ እና እየተቋረጠ በመጣ ቁጥር የወዳጅነት እድገት ይገታል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሀን ዋነኛ መወዳጃ መሳርያ ይሆናሉ፡፡ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ደግሞ የአካል ቅርርቦሽን ስለሚገድቡ ግንኙነቱ ቁሳዊ ወይም ወለፈንዴነት እንዲጫነው ያስገድዳሉ፡፡ በመጨረሻም በጉርብትና ላይ የቅርጽ ለውጥ ይፈጠራል፡፡
ስለዚህ ለውጡ አይቀሬ ከሆነ እንዴት እንቀበለው ወይም እንዴት እናስተናግደው የሚለውን ጥያቄ መመለስ አስፈላጊ ነው፡፡ በኔ እምነት የሚመለካታቸው አካላት ሁሉ በሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮርና መስራት ይገባቸዋል ብየ አስባለሁ፡፡ 1)- የጉርብትና ባህል ለውጥ አይቀሬ መሆኑን መረዳትና የወዳጅነት እጣም ተመሳሳይ መሆኑን መገንዘብ፡፡ ይሁን እንጂ ይህን እሴት የሚተካው አዲስ ልምድ ሀገር በቀል እንዲሆን ማስቻል፡፡ ለምሳሌ ወጣቶች የሚያከናውኑት አቅመ ደካሞችን የመርዳት ተግባር ከዘመቻ ጉድጉድ አላቆ ተቋማዊ ማድረግ፡፡ 2)- የቤተሰብ ኃላፊዎች ለልጆቸቸው እንዲሁም ታላላቆች ለታናናሾቻቸው ስለጉርብትናና አብሮ የመኖር ይትባህል የማሳተማርና የማስተግበር ርምጃዎችን መወሰድ አለባቸው፡፡
ግንቦት-2012

Read 6520 times