Print this page
Tuesday, 19 May 2020 00:00

ከፌስቡክ ገጾች

Written by  "አያልቅበት" – ኤፍሬም!!
Rate this item
(1 Vote)


ጋዜጠኛ፣ ተርጓሚና ደራሲ ነው – ኤፍሬም እንዳለ። አለቀ። ከዚህ ውጪ ስለ እሱ ግላዊ ህይወትና ማንነት፣ ጥረትና ልፋት በሕትመትና ብሮድካስት ሚዲያዎች ሲነገር ሰምቼ አላውቅም። የእሱም ፍላጎትም፣ ግድም አይመስለኝም አደባባይ መውጣቱ። ደም ለመመለስ ቤቱን አቃጥሎ የሸፈተ ሰው፣ መልኩን አይደለም ጥላውን ሳያሳይ ጫካና ጥሻን ተከልሎ ወደ ዒላማው ጥይቱን እንደሚልከው ሁሉ ፣ እሱም ካለበት ጥጋት ተሰትሮ በብዕር ከመተኮስ ውጪ በታይታ ሰውነቱ አይታወቅም።
ኤፍሬም ወደ ሰላሳ ለሚጠጉ ዓመታት – በእኔ ዕውቀት ከ"ፀደይ" መፅሄት ጀምሮ በተለያዩ ጋዜጦችና መፅሄቶች ላይ ምፀት - ለበስ ወጎችንና ጨዋታዎችን ሲያስኮመኩመን አሁን ድረስ አለ። ዘወትር ቅዳሜ ላለፉት አስራ ሰባት ዓመታት "ጨዋታዎቹን" የሚያስነብብባትን "አዲስ አድማስ" ጋዜጣን ባገላበጥኩና ፅሁፎቹን ባነበብኩ ቁጥር እጅጉን የምደመምበት ነገር ቢኖር የጨዋታዎቹ ለዛቸውን ጠብቀው መቆየታቸው፣ ዕይታዎቹና የሚያነሳቸው ጉዳዮች፣ እንዲሁም የብዕሩ ከዘመን ዘመን ሳትከሽፍ የኅብረተሰባችንን ጉዳዮች በራሱ በኅብረተሰቡ ወቅታዊው አስተሳሰብና አነጋገር እነሆ ማለቱ ነው። ትናንት አራዳ፣ ዛሬም አራዳ ነገም አራዳ እንደሆነ ስለ መዝለቁ ያሳብቃሉ – ለወጉ ማዋዣነት ጣል የሚያደርጋቸው አስቂኝ ቀልዶችና ገጠመኞች።
ኤፍሬም፤ በ"ፀደይ" መፅሄት "እንጨዋወት አምድ"፣ በ "Ethiopian Herald" ጋዜጣ "Between you and me" አምድ ላይ በአምደኝነት፣ በ"The Sun" ጋዜጣ ከአንጋፋዎቹ ጋዜጠኞች ያዕቆብ ወልደማርያምና ኤልያስ አወቀ ጋር በአዘጋጅነት፣ በ"ምዕራፍ" ጋዜጣ ከእነ ስብሐት ገብረእግዚአብሄር ጋር በመሆን በዋና አዘጋጅነት ፣ ካለፉት 17 ዓመታት ጀምሮ እስካሁን ደግሞ በ"አዲስ አድማስ" ጋዜጣ ላይ አምደኛ ነው።
መፅሀፍትን ለንባብ በማብቃቱም ረገድ፤ እጅግ ተነባቢና ተወዳጅ የነበረውን የሮበርት ሉድለምን መፅሀፍ "ፍንጭ" በሚል ርዕስ ለንባብ አብቅቷል። የቱርካዊውን አዚዝ ኔሲን "እራሴን አጠፋሁ" የተሰኘ መፅሀፍም በኤፍሬም እንዳለ ተተርጉሞ ለህትመት የበቃ ነው። እሱ ያዘጋጀውን "ቤርሙዳ ትርያንግል" የተባለ መፅሀፍም ከብዙ አመታት በፊት ማንበቤም ትዝ ይለኛል። "የዘመን ዱካ" የተሰኘ ሥራም አለው። በተለያዩ መፅሄቶችና "እፍታ" መፅሀፍ ላይ የወጡ የራሱንና ትርጉም አጫጭር ልቦለዶችን ለአንባቢያን አበርክቷል። "የጉራ ሊቅ"ን ያስታውሷል። "እንግሊዘኛን በቀላሉ" የተባለች ለእንግሊዘኛ መማሪያነት የምታገለግል በኪስ የምትያዝ ታዋቂ መፅሀፍም ነበረችው። ጋዜጣና መፅሄት ላይ ወጥተው የተነበቡ ስራዎቹንም በመፅሀፍ መልክ አሳትሟቸዋል።
በኢትዮዽያ ሬድዮ "ቅዳሜ መዝናኛ" እና በሸገር ሬድዮ "የጨዋታ" ፕሮግራም ላይ የተላለፉ ተከታታይ እና አጫጭር አዝናኝ ድራማዎችን በመድረስና በመተርጎም ለአድማጮች እንዲደርሱ አድርጓል። ተደንቆበታልም። "ስካይ ፕሮሞሽን" የሚል የማስታወቂያ ድርጅት አቋቁሞ እንቅስቃሴ ያደርግ እንደ ነበር አስታውሳለሁ – አሁን ይቀጥልበት አይቀጥልበት ባላውቅም።
አንዲት ሚጢጢ መፅሀፍ አበርክቶ ሰማይ ልንካ የሚል ፀሀፊ በሞላበት ሀገር ፣ ይህን ለሶስት አስርት ዓመታት ያህል ድምፁን አጥፍቶ ትልቅ ተግባር የከወነን ሰው አለማንሳት፣ አለማውሳት ትልቅ ሀፍረት ነው – ለሁሉም። ክብር ለሚገባው ሁሉ ክብር ይሁን፤ አበቃሁ !!!
ማሳሰቢያ:– ከኤፍሬም እንዳለ ሰብዕና፣ ሥራዎችና ጥረት አንፃር ይህ ልጥፍ ፅሁፍ 1% ያህል አይሰጠውም ከመቶው። ይሁን እንጂ ከእኔ በተሻለ ስለ እሱና ስራዎቹ የምታውቁ፣ በዚህች ቅንጭብ ፅሁፍ ላይ የታያችሁን ስህተት በእርማት፣ የቀረውን ደግሞ በአስተያየት ታሟሉታላችሁ ብዬ በማመን ነው እዚህ ያሰፈርኩት። ተሳትፎአችሁ ይጠበቃል !!!
(ከጀሚል ይርጋ ፌስቡክ)

የተምሳሌቶች ፋይዳ
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ጥንታዊ ታሪክ ያላቸውና የተለያየ ሕዝብ፣ ነገድ፣ ጎሳና ብሄር ያቀፉ ሐገሮች በአብዛኛው ማህበረሰባዊ መስተጋብራቸውን የሚያስጠብቁት ከቁሳዊ ነገሮች ይልቅ በምልክቶች፣ በአርማዎች፣ በመንፈሳዊ ብሂሎችና በተምሳሌቶች ነው፡፡ ሕዝቦች የጋራ የሆኑ ምልክቶቻቸውን ከመፍጠር ጀምሮ፣ የጀግንነት፣ የጽናት፣ የጥንካሬና የአንድነት መገለጫቸው በማድረግ፣ ግጥም ከመግጠም ጀምሮ ዘፈን እስከ መዝፈንና ቅኔ እስከ መቀኘት የሚያደርሳቸውም ተምሳሌቶቹ ከፍተኛ የሞራል ዋጋ ስላላቸው ነው፡፡
እስከ ዛሬ የምናቃቸው ምልክቶቹ፣ ምሳሌዎቹና አርማዎቹ በሕዝቦች ሕሊና ነፍስ ዘርተው ህልው የሆኑት፣ ዘመናችን በደረሰበት ዲሞክራሲያዊ የምርጫ ስርዓት ሳይሆን ከማይታዩና ከማይዳሰሱ ስነ-ልቦናዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ተሞክሮዎች በመነሳት ነው፡፡ በቅጡ ስናጤነውም፣ ሰንደቅ ዓላማን ጨምሮ የጋራ መግባባት የተደረሰባቸው ምልክቶች በዋዛ ፈዛዛና እንዲያው በአቦ ሰጡኝ አልነበረም፡፡ አብዛኞቹ የማይዳሰሱ ቅርሶች ናቸው፡፡ በጥልቅ የታሪክ ሂደት ውስጥ አልፈው፣ በከባድ የሕይወት መስዋእትነት ጭምር እየተዋጁ፣ ዘመናት ተሻግረው ዘመናትን እያሻገሩ ነው እዚህ የደረሱት፡፡
ዛሬ አካሄዱ ለየቅል ነው፡፡ ሕዝባዊ የሆኑ የቃል ኪዳን ምልክቶችና ተምሳሌቶችን መለወጥ፣ መከለስና መበረዝ ካስፈለገ ቁሳዊ የሆነን ቤተ መንግስት ከማደስ የጠለቀና የዳበረ ምክንያትና መግባባትን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ በቂ ምክንያት ይዞ በመነሳትና በስምምነት ምልክቶቹ በነባርነታቸው እንዲቀጥሉ ወይም በአዲስ እንዲተኩ  ማድረግ ተገቢ ነው። ያ ሳይሆን ቀርቶ፤ ተምሳሌቶች በዘፈቀደ ተተክተው የኔ ምልክት፣ የኔ ምሳሌና የኔ መገለጫ አይደሉም የሚል ስሜት ከተፈጠረ፣ ትልቁንና ዋነኛ ምሰሶ የሆነው ማህበራዊ መስተጋብራችንንና ራዕያቻችንን ሊሸረሽረውና ሊያከስመው ይችላል፡፡
ሕዝብ እንደዚህ ባሉ ጉዳዮች ላይ መነጋገሩ ተገቢ ነው፡፡ መሪ በመጣ ቁጥር አዳዲስ ምልክቶችንና ተምሳሌቶች ከመገንባትና ነባሩን ከማፍረስ ይልቅ ውይይትን በመጋበዝ፣ መስተጋብሮችን በጋራ አስጠብቆ ማስቀጠሉ ከፍተኛ ፋይዳ አለው፡፡ መርሳት የሌለብን ቁም ነገር በተምሳሌትና በምልክት የሃገር አንድነት የመጠበቁን ያህል፣ በተዛቡ ተምሳሌቶች መስተጋብሩ ሊፈርስ እንደሚችል ነው፡፡
(ከሙሼ ሰሙ ፌስቡክ፤ May 2)
***
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ምን ማድረግ አለባቸው?

 ሑሴን ከድር "ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ (ሚያዝያ 29 ቀን 2012) የሰጡት መግለጫ::" በሚል በፌስቡክ ገጹ ፖስት ያደረገውን በሚገባ ተመልክቸዋለሁ፡፡  የብልፅግና ፓርቲንና የመሪውን አቋም በሚገባ ያንጸባርቃል። የመከራከሪያ ሐሳቡ ጠንካራ ወይም አሳማኝ እንዲሆንም በሚገባ ጥረት ተደርጎበታል። ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትር መግለጫ ስለሆነ አገላብጠን ብናየው ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም። ከዚህ መግለጫ ጋር ተያያዥ የሆነ የተቃዋሚዎችን አቋምም  በቲቪ ተከታትያለሁ።  እነሱም አመለካከታቸውን ያለ አንዳች ገደብና ይሉኝታ እያቀረቡ ነው። ተቃዋሚዎች ያን ያህል ተጉዘው ህዝብን ለማሳመን ጥረት ማድረጋቸው ጥሩ ነው። ምርጫው በታሰበው ጊዜ ባይከናወንም፣ አቅማቸው ምን ያህል እንደሆነ  አሳይተውበታልና ይጠቅማል። ብልፅግና ፓርቲ ወደፊት የሚገጥመው ፈተና ቀላል እንደማይሆንም ያመለክታል።
እንግዲህ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊበራሊዝም ቀመስ መግለጫ ከመግባታችን በፊት የትና ከምን ተነስው እንዳሉት ጉዳዩን ቀስ በቀስ ማየት ይኖርብናልና፣ በቅድሚያ የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ እንመልከተው። ከሁሉ አስቀድሞ ከ1983 በፊት ወደነበረችው ኢትዮጵያ እንግባ።
እንደሚታወቀው ሁሉ በምሥራቅ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የነጻነት ንቅናቄ በኦጋዴንና በዓፋር በከረረ ሁኔታ ነበር። ነገሩ የዚያድባሬ እጅም አለበት እንጂ ዋናው ነጻ አውጭ (የዛሬው ሱማሊ) ኦጋዴን ነበር። ዛሬ ስለ ካራ ማራ ድል የሚያወሱ፣ የትግሉን አጠቃላይ ሁኔታ የማይገነዘቡ ሲሆኑ ለሱማሌዎች ግን ዛሬም ያልሻረ ቁስል ነው። የዓፋር ነጻነት ንቅናቄም እንደ ሱማሊው ተከፋፍሎ ማዕከላዊውን መንግሥት ይፋለም ነበር። በምዕራብ የቤንሻንጉልና ጉምዝ እንዲሁም የጋምቤላ ነበር። በሰሜን ኢትዮጵያ የትግራይና የኤርትራ ነጻ አውጭ ድርጅቶች ነበሩ። የኦሮሞ ነጻ አውጭ ድርጅቶች በብዛት ነበሩ።  በደቡብ የሲዳማ አንድነት ነቅናቄ ነበር።
የሽግግር መንግሥት በኋላም  መንግሥት ያቋቋሙት እነዚህ ናቸው። ብልፅግና ፓርቲ ይህን ተጨባጭ እውነታ ካላገናዘበ "በሬ ሆይ፣ በሬ ሆይ ሣሩን አየህና ገደሉን ሳታይ..." እንዲሉ እነዚህ አካላትን ረስቶ "ሐሳብ ያሸንፋል፤ ካላሸነፈም አርጩሜውም ካሮቱም ከኔ ጋር ነው።"  የሚል ከሆነ ከቅርብ ሩቅ የመንና ሶሪያ አሉና በበኩሌ "የአዳነችን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም" እላለሁ። ዛሬ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ተንቆ ነገ የብልፅግና ፓርቲ አሸነፍኩ ቢል የሚገጥመው ፈተና ሁለት ነው። አንድም መፈንቅለ መንግሥት፣ ካለበለዚያም "አሻፈረኝ ባዩ ቡድን" የሚያነሳው የእርስ በእርስ ጦርነት ነው። ጦርነቱ  ቢነሳ ደግሞ በድል አድራጊነት እወጣዋለሁ ወይ? ብሎ ከወዲሁ መጠየቅ ያስፈልጋል። መቼም አንድ ትራጂክ ሂሮ ተመክሮ አይመለስምና "ባመንኩበት እሄዳለሁ" ከተባለ የሚያስከፍለው ዋጋ አለ። ለመሆኑ ተጨባጭ ሁኔታዎችን አይቶ ነገሮችን ማስተካከል ሲቻል፣ ለምን "ባልኩት አይመልሰኝ" ይባላል?
ቀደም ሲል የተነሳው አንድ መሠረታዊ ነገር ብቻ ነው። ሌሎችም ባለፉት 30-50 ዓመታት ሲሠሯቸው የነበሩ ውስብስብ ጉዳዮች አሉ። እነዚህ ነገሮች ሊፈቱ የሚችሉት በመወያየትና ሆደ ሰፊ በመሆን ነው። እዚህ ላይ ብዙ ሰዎች የተሳሳተ ግምት እንዳላቸው ይገባኛል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን በመጀመሪያው ዓመት የስልጣን ዘመናቸው አሳይተውን፣ እኛም ዓለምም አጨብጭበንላቸዋለንና ምን ለማለት እንደፈለግሁ እንደሚረዱኝ አልጠራጠርም።
ከዚህ ሁሉ ተጨማሪ፣ ኮሮና ገታው እንጂ በክልሎች መካከል ወሰን ሊፈነዳ ተቃርቦ ነበር። ሲዳማ እራሷን ችላ ክልል እንደሆነችው ሁሉ ሌሎችም የክልልነት ጥያቄ ሲያነሱ የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ መነሳቱ ባልቀረም ነበር። ለምሳሌ በሲዳማና ወላይታ መካከል የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ ዝም ያለ ቢመስልም፣ ጊዜውን ጠብቆ መፈንዳቱ የሚቀር አይመስለኝም። ሌላውን ከዚህ ጋር ስንደምረው ችግሩ በአንድ ፓርቲ ሊፈታ የማይችል ግዙፍ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። ለጊዜው ለዘብ ያለ ቢመስልም የክልሎች ፍጥጫ በትግራይ፣ በአማራና በኦሮሚያ፣ በሱማሊና በኦሮሚያ ወዘተ  ባለው አይበቃም፣ እንዲያው "ሾላ ድፍን"  በሁሉም አለና አስጊነቱ እንደ ፍም ተዳፈነ/ተደበቀ እንጂ አልጠፋም። ይህ ክፉ ነቀርሳ የሆነ ሐቅ መሠረታዊ ችግራችን ሆኖ እያለ ጠቅጥቆ ለማለፍ መሞከር አደጋ ሊኖረው ይችላልና ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል።
  ከዚህ ጋር "በእንቅርት ላይ ደግፍ" እንዲሉ ኮሮና ተከስቷል።  ኮሮና ብሔራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ችግር ከመሆኑም በላይ የአገሪቱ አቅም የሚችለው አይደለም። ይልቁንም የሚያስከትለው የኢኮኖሚ ድቀት ዛሬ የፖለቲካ ቁማር የሚቆመርባቸው  በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውን ላይ ከፍተኛ እልቂት እንደሚያስከትል በበሳሎች እየተነገረ ነው።
 በጣም የሚያሳዝነው ግን ጉዳዩን ከሀገርና ከህዝብ ጥቅም አኳያ አይቶ ነገሩን ተቻችሎ ለማሳለፍ ከመሞከር ይልቅ ሁሉም የፖለቲካና የሃይማኖት ተቋማት በእብሪት ተወጥረው፣ ይዋጣልን የማለት ያህል ባህሪ ማሳየታቸው ነው። በኔ እምነትና በዚህ ዓይነት፣ "የኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያን ጥቅም ቅድሚያ ሰጥተው፣ ተቻችለውና ተመካክረው ለመሥራት ካልቻሉ፣ ሁሉም ለራሳቸው ግፍ የተሞላበት አገዛዝ፣ በፖለቲካ ፍትወት ተወጥረው ከመወራጨታቸው በስተቀር  ምርጫው ዛሬም ሆነ ነገ ቢካሄድ የጎላ ለውጥ የሚያመጡ አይመስለኝም። ካለፈው ሺ ዓመት ታሪካችን እንደምንረዳው ከሆነም አያመጡም። ሌላ ቢቀር ልዩነቶችን ለመፍታት እንኳን አይችሉም።
ለመሆኑ፣ አንድ ሰው የራሱን ትክክልነት ብዙ መረጃ እያቀረበ ስላስረዳ፣ የጠራና የተንጠራራ መስመር እንደሚያራምድ ስለገለፀና በጽሑፉ ስላሳረፈ፣ ነገር ግን በሌላው ዘንድ ትክክል ያልሆነበትን ካላወቀ፣ ሌላው ዝም ብሎ ጭፍን ሊቀበለው ይችላልን?
በኔ አስተያየት፣ ከሁሉም በላይ አገራችን ኢትዮጵያ፤ አሜሪካ ወይም  አውሮፓ አለመሆኗንና የዚያ የፖለቲካ አስተዳደር ሥርአት በቀጥታ መጥቶ በተግባር የማይተረጎም መሆኑን መገንዘብ ይገባል። አሁን ሀገራችን ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ተነስተን ስንመለከተው "በሐሳብ አሸናፊነትና በድምፅ ብልጫ ስልጣን ብቻ የሚታሰብ ከሆነ እጅግ ከፍተኛ ስህተት ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ነገሩ በአሜሪካ አስተማረሽ ወይም በቻይና አስተማረሽ የሚሄድ አይደለም። ስለሆነም የሀገሪቱን ታሪክ፣ ባህልና በዚያ ላይ የተመሠረተውን አመለካከት አካታች የሆነ አካሄድ ማየት ያስፈልጋል።
አዋቂ ለመሆንም እርሱ የሚቀበለውን ከራስ ወዳድነት የመነጨ አስተሳሰቡን ለማንጸባረቅ መቻሉ ላይ ሳይሆን ሌላው የማይቀበለው ምን እንደሆነ አውቆ የተጓዘ እንደሆነ ነው። ሌላውምኮ ተቃዋሚ እንዳለው ሁሉ ደጋፊ አለው። ስለዚህ "እምቢ፣ አይሻኝም፣ አልቀበልም" ቢል መልሱ ጦር መማዘዝ አይደለምን???  ውጤቱኮ "የፈሩት ይደርሳል፣ የጠሉት ይወርሳል" እንዲሉ ሊሆን ይችላል። ይህ እንደሚሆን አይታወቅም ይሆን እንዴ? ይህኮ ሩቅ ባልሆነ ጊዜ የሚከሰት እውነት እኮ ነው!
ሌላው ጎልቶና ገዝፎ የሚታየው የፖለቲካና የቲዮሎጂ በቀል ይመስለኛል። መነሻው ትላንት በስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ እንዲህ ያለ ጉዳት አድርሶብኛልና ልበቀለው፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ላዋርደው፣ ያለፈ ጥፋቱን እያነሳሁ ላሸማቀው ወዘተ ወዘተ  ሊሆን ይችላል። ይህ ከሆነ የፖለቲካ ብቀላ ወደ አምባገነኑ የሚያመራ ሲሆን በአምባገነንነትም ሊገለፅ የማይችል ማህበረሰብን መቅኖ የሚያሳጣ አደገኛ አስተሳሰብና የአገርን አንድነት ጨርቅ ላይ እንደፈሰሰ መርዝ የሚበታትን ነው።
ነገሩ በጣም ብዙ ነው። በኔ እምነት፣ ነገን ማየት ደግ ነው። ቢያንስ አደጋን ማስቀረት ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም። ስለዚህ፣ ለመንግሥት ያላደሩ ሽማግሌዎችን ሰብስቦ ማየት ቢቻልና አስታራቂ ሐሳብ ቢመጣ የተሻለ ይመስለኛል።
(ከተሾመ ብርሃኑ ፌስቡክ)

Read 3421 times