Sunday, 17 May 2020 00:00

የዐርበኞች ደም ቀለማት!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

ሳውል ኬ. ፓዶቨር የተባሉ ምሁር ስለ ቶማስ ጀፈርሰን ደብዳቤዎች የፖለቲካ፣ የማህበረሰብና ስነ-ልቡና በጻፉት መጽሐፍ ላይ ያሰፈሩት የምትደንቅ፣ሁሌ የምትቆረቁርና የምታሳዝን እውነት አለች፡፡ታዲያ ይህቺ ሀሳብ ሁሌም የምትነገር፣ግን ደግሞ ሁሌም የሰው ልጅ የሚሸነፍባት ጉድለቱ ትመስለኛለች፡፡አጥንት ውስጥ ታሳክካለች፡፡…ጀፈርሰን የሚለው እንዲህ ነው፡፡ "inspite of individual exceptions;and experience declares that man is the only animal which devoures his own kind;"በታሪክ የምናየው እውነት ይህ ነው፡፡ከተወሰኑ ሰዎች በስተቀር፣የሰው ልጆች የሕይወት ተሞክሮ ድምጹን ከፍ አድርጎ እንደሚነግረን፣የሰው ልጅ ከሌሎች ፍጥረታት በተለየ ሁኔታ ራሱን የሚያሳድድ፣ራሱን የሚበላ አውሬ ነው፡፡
ስለዚህም አንዱ አንዱን እረፍት እየነሳ፣አንዱ አንዱን እያጠፋ ብዙ ሺ አንጓዎች፣በርካታ ትውልዶች አልፈዋል፡፡ትልቁ ትንሹን ሲበላ ዘመን ተቆጥሯል፡፡ከዚህ መጠፋፋት አንዱ ጦርነት ነው፡፡ጦርነት ደግሞ አንዱ የሌላውን ለመንጠቅ ካለው ፍላጎትና ከሌላኛው ወገን ራስን ለመከላከል የሚደረግ ግጭት ነው፡፡ለዚህ ዋነኛ ማሳያ ደግሞ ሁለት ጊዜ የተደረጉት የዐለም ጦርነቶች ናቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በቁጥር በርካታ ጦርነቶች በየአካባቢው ተካሂደዋል፡፡ለዚህ ዐይነቱ ጦርነት ደግሞ እኛ ራሳችን ምስክሮች ነን፡፡በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ጦርነቶችን ስናካሄድ ኖረናል፡፡ምናልባትም ብዙዎቹ ጦርነቶች ጂኦ-ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ባለው የመሬት አቀማመጣችን ነው፣በምንገምትበት ሁኔታ በግብጽ፣በቱርክ፣በደርቡሽ፣በኢጣልያ፣በሶማሊያ ወዘተ በተደጋጋሚ ወረራ ተፈጽሞብን፣በድል አድራጊነት ተወጥተናል፡፡ይሁን እንጂ ለዚያ ሁሉ ድል ደምና ሕይወት ከፍለናል፡፡
ዛሬ ላነሳው የፈለግሁት ርዕሰ ጉዳይም ከዚሁ ደም ከመክፈል ጋር የተያያዘ ውድ ዋጋን የሚመለከት ይሆናል፡፡በተለይ ሰሞኑን ያከበርነውን የማይጨውን ጦርነት ተከትሎ፣ዐርበኞቻችን የከፈሉትን መስዋዕትነት ማስታወስና ገድላቸውን ከፍ ማድረግ ነው፡፡በተለይም ዛሬ ሰፊ ስፍራ የምሰጠው ብዙ የማይነገርላቸው ልጅ ኀይለማርያም ማሞ፣ ለሀገራችን ነጻነት የከፈሉትን ዋጋነው፡፡
ከዚያ በፊት ጸጋዬ ገብረመድህን ስለማይጨው ከተቀኛት ግጥም ጥቂት ስንኞችን ወስጄ የህመሙን ልክ ለማሳየት እፈልጋለሁ፡፡
ያገር ጎበዝ ያገር ወንድ
በነጭ ዐረመኔ ሞገድ፣
ያገር ሕጻን ያገር ወላድ
በእቶን የመርዝ እሳት እሳት ንዳድ፣
እንደ ፍካሬ ኢየሱስ ቃል
በፋሽስት ሲኦል ሲጣል፣…
ማይጨው እግዚኦ ላንቺ ቆሌ
አገር ውሀ ገባ አሞሌ
የሆነብሽ የእሳት ምፅዓት
የኘጭ አረመኔ መዓት
በሟች ብዕር ላይቀመር
የመቅሰፍትሽ ሲዖል ድንበር
‹‹በእግዚአብሔር በታሪክ››በቀር
በቁም ሮሮ ላይሠፈር
ላይመጠን ላይነገር፡፡

ይህ ማይጨው ላይ የወረደውን መዐት የሚያሳይ እንጉርጉሮ ነገር ነው፡፡ምናልባትም አልቃሻው ነቢይ የሚባለው ኤርምያስ ስለኢየሩሳሌም ሰቆቃ፣ በሰቆቃ ወ ኤርምያስ መጽሐፉ ከጻፈው ጋር ሊመሳሰል የሚችል ነው፡፡የባቢሎን መንግስት ህዝበ እስራኤልን እንዳስጨነቀ፣የጣልያን ፋሽስትም በገዛ ሃገራችን መጥቶ፣ በግፍ የጨፈጨፈንን ዘመን ሕመምና ጥዝጣዜ በትኩስ ስሜት፣ በነደደ ልብ፣ ባረረ አንጀት የጻፈው ይመስለኛል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ በዚያ የታሪክ ገጽ የተሻለ ገድል ለመጻፍ፣ለማይጨው ጦርነት እንደ ዐደዋው ጦርነት ከስነልቡና ጀምሮ፣በጦር መሳሪያ ሳይቀር በቂ ዝግጅት ስላላደረገችና ሃገራዊ አንድነትዋም ላልቶ ስለነበር ጦርነቱን ማሸነፍ አልቻለችም፡፡ይህ ሲባል ግን ሀገሪቱ የጀግና እጦት ነበረባት ማለት አይደለም፤አልነበረምም፡፡በአደባባይ ላይ እንደታየው በኋላ በአርበኝነት ጊዜ የውጭ ጠላትን ከራሱ መሳሪያ እየነጠቁ መፈናፈኛ ያሳጡት ዐርበኞች  ነበሯት፡፡ይሁን እንጂ ከጦርነቱ በፊት እንደ ራስ መኮንን የነቁና የአውሮፓውያንን ሸር ቀድመው የሚያጤኑ፣በሃገር ውስጥ ያሉ ችግሮችም አድገው ወደ ጦርነት ሳይደርሱ በእርቅ መፍታት የሚችሉ፣አሊያም እንደ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ (አባ መላ) ዐይነትብልህ ሰዎች አልነበሩም፡፡ያ ብቻ አይደለም፤የሰገሌ ጦርነት ላይ በተደረገው የእርስበርስ ጦርነት፣በርካታ የሀገር ጀግኖች ከሁለቱም ወገን አልቀዋል፤ያ አሳዛኝ የታሪካችን ፀፀት ነው፡፡ከዚህ ዐይነት ስሜታዊ ርምጃ በመታቀብ የሀገርን የውስጥ ጉዳይ ለነገ አሳድሮ ከውጭጠላት ጋር በመግጠም ዐጼ ዮሐንስ የተሻለ እርምጃ የወሰዱ ይመስለኛል፡፡በወቅቱ የሸዋ ንጉስ የነበሩት ምኒልክ ያለንጉሰ ነገስቱ ፍቃድ ግዛት እያሰፉ ሲሄዱ፣ከንጉስ ተክለሀይማኖትም በኩል ክፍተት ሲኖር ለጊዜው አቅም ላለማጣትና ለጠላት ቀዳዳ ላለመክፈት ጉዳዩን አሳድረው፣ ወደ ሌሎች የውጭ ጠላት ግንባሮች መሄዳቸው የተሻለ ብልሀት ነበር፡፡በንጉስ ተክለሀይማኖት ጸብ ጎጃም ላይ የሰሩትን ስሜታዊ ስራ ትተን፡፡
የማይጨው ጦርነት ድክመቶች መነሻቸው በአብዛኛው የእርስበርስ ግጭቱ ውጤቶች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡በሌላ በኩል፤ ንጉሱ ቀደም ሲል ዐጼ ዮሃንስ በእንግሊዞች የተታለሉትን ዐይነት ነገር ሲደግሙትወይም ተመሳሳይ ነገር ሲያደርጉ እናያለን፡፡በርካታ የታሪክ ጸሀፍት እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት አባል በመሆኗ በጠላት ስትወረር የሚታደጓት መስሏቸዋል፡፡ስለዚህም ጦርነቱ እንዳይጀመር ከፍተኛ ጥንቃቄና ልምምጥ የሚመስል አካሄድ ነበራቸው፡፡ሌላው ቀርቶ ወረራውን ተቃውመው ግጥሞች ጽፈው ለሕዝብ የበተኑትን ተስፋ ገብረስላሴን እስከማሰር ሄደዋል፡፡ልክ ዐጼ ዮሃንስ ራስ አሉላ ላይ እንዳደረጉት፡፡ይሁንና ጠላት የአርባ አመታት ዝግጅት ስለነበረውና ስለእኛ መዝረክረክ መረጃ ስለጠገበ ወደኋላ ማለት አልቃጣውም፡፡
በመሆኑም ጣልያን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ በመግባት የመጀመሪያው ጥይት ተተኮሰ፡፡የመጀመሪያውምሰው ሞተ፡፡አዶልፍ ፓክላር ጽፎት ተጫነ ገብሬ በተረጎመው መጽሐፍ፤ ‹‹ራስ ሥዩም ከጫካ ሳይወጡ የንጉሰ ነገስቱን መመሪያ ሲጠብቁ በመቶ ሺዎች የሚቆጠርበዘመናዊ መልኩ የሰለጠነና በታንኮች የሚደገፍ ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ጣሰ፤የመጀመሪያው የጣልያን ወታደር ወጣቱ መቶ አለቃ ሞርጋንቲኒ የኢትዮጵያን ድንበር መረብን ተሻግሮ፣ የኢትዮጵያን ድንበር ረገጠ፡፡ከጥቂት ውጊያ በኋላ በአንድ ኢትዮጵያዊ የገበሬ ወታደር ግንባሩን ተመትቶ ወደቀ››ይላል፡፡
ጦርነቱ በዚህ ጀግና ተጀምሮ፣እምነት በቁና ሲበጠር ደጃዝማች ኃይለስላሴ ጉግሳን የመሳሰሉት ሰነፎች መክዳት ጀመሩ፡፡ይሁን እንጂ በዚህ ድጥና ማጥ እነራስ ካሳ፣ እነ ራስ ሙሉጌታ፣ በዋናነት አቢቹን የመሰለ ጀግና የሚመራውና በሃፍቶም(ኤርትራ)፣በተስፋጽዮን(መቀሌ)፣በጋሹ(ጎጃም ዳሞት)በወርቁ (ሰላሌ)የሚመራው ጦር ተወልዶ ነበር፡፡
በጀግና ልብ እጦት ሳይሆን፣ ከላይ በተጠቀሱት የዝግጅትና የትጥቅ አለመመጣጠን ችግሮችና በአካባቢው ለጠላት በተገዙ ከሃዲዎች ምክንያት ጦርነቱ በጠላት ድል አድራጊነት ተደመደመ፡፡
ከድሉ በኋላ ግን እንደሌላው ሀገር ጦርነት ምዕራፉ አንገት በመድፋት አልተዘጋም፤ታሪክ በተገዢነት አልተቋጨም፡፡ ሌሎች የተስፋ ልጆች፣ሌሎች ቁጭት ያረገዙ ጎበዞች ከየጥሻው ብቅ ብቅ አሉ፡፡..በኢትዮጵያ ሰማይ ላይአዳዲስ ክዋክብት ተንቦገቦጉ፡፡
ኃይለማርያም ማሞ፤ ፈር ቀዳጁ የሸዋ ዐርበኛ
ኃይለማርያም ማሞ በዐጸደ ስጋ በነበረበት ዘመን በወገኖቹ ብቻ ሳይሆን በጠላቶቹ የተመሰከረለት ጀግና ነበር፡፡እንዲያውም ፋሽስት ገና አዲስ አበባ ከተማ ከመግባቱ በፊት መንገድ ላይ አሸምቆ በመጠበቅ በጥይት እየቆላ የተቀበለው እርሱ ነበር፡፡ከማይጨው ጦርነት ስብራት በኋላ ሞጆ መኖሪያ ቤቱ በትካዜ ተቀምጦ ነበር፡፡በኋላም ሰዎች ጠላት ወደ አዲስ አበባ እየመጣ መሆኑን ሹክ ሲሉት፣ በመትረየስ ሊቀበለው ጫጫ ሱኬ ሴራቤ የምትባል ቦታ ላይ አድፍጦ ጠበቀው፡፡ከዚያም በድንገት አደጋ በመጣል አምስት የጭነት ካሚዮኖች ሰባብሮ፣አንድ መቶ አርባ ወታደሮች ገድሎ፣ስድስት መትረየስና ልዩልዩ የህክምና ቁሳቁሶችን፣አንባሳትን ማርኮ ገባ፤የዐርበኝነቱ ታሪክ የዚያን ቀን ተጀመረ፡፡
ይህንን የሰማው ግራዚያኒ አንካሳና ፍርሃት የተቀላቀለበት መልዕክት ልኮለት ነበር፤ "…በወታደሮቻችን ላይ ያደረግኸውን በደል በይቅርታ አልፈነዋልና ወደ እኛ ግባ›› የሚል፡፡ ይህ ሃሳብ ለኃይለማርያም ማሞ ቀልድ ነበር፡፡ ይልቅስ ቁጭቱንና ቁጣውን ለመወጣት ልቡ ቆርጦ ስለነበር ኢትዮጵያዊ ወገኖቹን አሰባስቦ ጠላትን እያሳደደ መውቃቱን ተያያዘው፡፡በተለያዩ ግንባሮች የተጠቃው የጄነራል ግራዚያኒ ጦር በመጨረሻ በአራት ጄነራሎች የሚመራ ጦር፣ክልቤ በተባለው ጦርነት ሊዋጉ ለሚሄዱት ጀነራሎች፣ ግራዚያኒ የሚደንቅ ንግግር ነበር ያደረገው፡፡
‹‹በሕይወቴ ዘመን ብዙ ጀግኖች አጋጥመውኛል፤ነገር ግን ኃይለማርያምን የመሰለ አላየሁም፤ይልቁንም ከአባቶቹ ከእነአቶ አንዳርጋቸው፣እነደጃዝማች ኀይሌ አንዳርጋቸው ተላልፎ በደሙ የወረደለትን ጀግንነት የጊዜ ብዛት ሳያስረሳው ለዚሁ ለአሁኑ ጦርነት ላሳየው ጀብዱ ከልብ አደንቀዋለሁ፤ይህ ጀግና ድንገት እንኳ በእጃችን ቢወድቅ እጁን ስሜ ከመቀበልና በክብር ከጎኔ ከማስቀመጥ በቀር የውርደት ወይም የማጉላላት ሥራ ላልፈጽምበት በእግዚአብሄር ስም ቃል እገባለሁ‹፡፡››ነበር ያለው፡፡
የገዛ ወገኖቻቸውም ብዙ ጊዜ ስለኒሁ ጀግና ተቀኝተዋል፡፡አንዴ ቶኬ የሚባለው ቦታ ላይ ዐርበኞች ተቀምጠው ሳለ ጠላት ከእነባንዳው ማለፊያ አጥቶ በከበባ ውስጥ ቆየ፡፡ውጊያም ገጥመው ብዙ መሳሪያ ሰበሰቡ፡፡መሳሪያ መሰብሰብ የሁልጊዜ ስራቸው ነው፡፡እናም  አጋፋሪ ሞላልኝ የሚባል ዐርበኛ እንዲህ እያለ ሸለለ፡-
እሰይ የምስራች ሞላልን ጉደር፣
ያባጎፋን ቀኝ እጅ ቅደም ተሻገር፡፡
ተርቦ የነበር የፋሽስት ወገን፣
ቶኪ አፋፍ ላይ ቆየው ገበያው ጎፍን፣
አስቆርጦ ሔደ ሦስት መቶ ስድሳ ከሐድያን፡፡
ማጉም ለሰለሰ ሸማኔው ተቆጣ፣
አባ ጎፍን ኃይሌ መጠቅለያውመጣ፡፡
--ይኸኔ ዐርበኞች እንደ አንበሳ ደቦል እየተንጎማለሉ ፎከሩ፡፡
በዚህ ጊዜ ከእርሳቸው ጋር በየግንባሩ የሚሰለፉ፣የየራሳቸው ጦር ያላቸው በርካታ ዐርበኞች ነበሩ፡፡ከወጣቶቹም ስመ-ጥር የነበረው ልጅ ዐቢይ አበበ፣መቶ አለቃ ጀመረ ብሩ፣ልጅ ተኮላ ድልነሳው፣ከአዋቂዎቹም ባላምበራስ ዘውዴ አባ ፈርዳ፣ሌተና ኮሎኔል ነጋ ኃይለስላሴ፣አቶ መንግስቱ አድጎይ፣ደጃዝማች አውራሪስ ከእነልጆቻቸው፣ሻለቃ መስፍን ስለሺ፣ፊታውራሪ ዘውዱ አባኮራን፣ባላምባራስ አበበ አረጋይ፣ደጃዝማች እንቁስላሴ ባንትይዳኝ ከእነልጆቻቸው፣ተሰማ እርገጤ፣ወይዘሮ ፍቅርተ ኃይለስላሴ፣ልጅ ደስታ ሸዋርካብህ፣ደጃዝማች አበራና ሌሎችም በጅሩ፣በመርሃቤቴ፣በእንሳሮ፣በጅሩ፣በሞረት፣በላም ዋሻና በሌሎች በርካታ ግንባሮች ጠላትን መድረሻ አሳጥተውታል፡፡
የልጅ ኃይለማርያም መትረየስ ተኳሻቸው ይመሮ በሄዱበት ሁሉ ጠላትን እያግለበለበ የሚቀጣ ነበር፡፡ታዲያ አንዳንዴ ያገር ልጅ መስለው ጥቃት የሚፈጽሙ ባንዳዎች ስለነበሩ፣ዐርበኞች አይቀጡ ቅጣት ይቀጧቸዋል፡፡እንዲያውም ብዙ ጊዜ የውርደት ሞት ይሞታሉ፡፡አንዴ አኬማ ገዳና በዳሳ የተባሉ ሰው፣ ያፈር ጦር ይዘው ልጅ ኃይለማርያም ላይ አደጋ ጥለውባቸዋል፡፡በዚያን ጊዜ እሳቸውና ልጅ ደምሴ ሰጉ ቆስለው ነበር፡፡ቁስለኞቹንም ዐርበኞች ጉያማ ጠኔ ከሚባለው ርስታቸው ወስደው አስተኟቸው፡፡
ኃይለማርያም ከቆሰሉ በኋላ አንድ ቀን ከባላምበራስ ወልደሩፋኤል ጅፋሬ፣ልጅ ሁንዴ ቡልቶ፣ልጅ ገርቢ ቡልቶ፣ከበደ ከለሶ ሆነው ስምንት መቶ ጦር ካመጡ በኋላ አገኟቸው፡፡ከአለቃ ደመ ኢየሱስ ቤት መኩዳ ሩፋኤል እንደቆዩ፣ ድሬ ቀኛዝማች ቡልቶ ቤት ጠላት ሰፍሯል የሚል ወሬ ተሰማ፡፡ይሄኔ ኃይለማርያም "ባልጋ ተሸክማችሁ እዚያ አድርሱኝ፡፡››አሉ፡፡ዐመላቸውን የሚያውቁትም ዐርበኞች በአልጋ ተሸክመው ቆርቻ ቤኛ ለተባለ ሰው አደራ ብለው መትረየስ ከእነተኳሹ ትተውላቸው ሄዱ፡፡ከመድረሳቸው ሁለት ካፒቴኖች ገድለው፣የጦር ሜዳ ራዲዮና ሌሎችም የጦር መሳሪያዎች ማረኩ፡፡መሳሪያውም ለሃገሬው ሰዎች ተከፋፍሎ ለዐርበኝነት በቃ፡፡
ከባንዳዎቹ መካከልልኡል ራስ ኃይሉና ሌሎችም ነበሩ፡፡ከነዚህም ኦዳ ቆሪቻ አንዱ ነበር፡፡ኦዳ አምሳ አለቃ መንግስቱ ነዋይና ሻምበል ሙሉጌታ ቡሊ ከእነልጅ ኃይለማርያም ተለይተው ወደ ሌላ ስፍራ በሄዱ ጊዜ ወዳጅ መስለው አሳድረው መሳሪያቸውን ነጥቀው ስለነበር፣ዐርበኞች ኦዳና ከእነወንድሞቹ ማረኩት፡፡
በየስፍራው በሚደረጉ ጦርነቶች ጠላት መድፍና ተዋጊ ጄቶች ቢጠቀምም አልተቀመሱለትም፡፡የኢትዮጵያ ጀግኖች ቀድሞም ዝግጅት እንጂ ልብና ጀግንነት አላነሳቸውም፡፡በዐርበኝነቱ ዐመታትም ዋናው ችግር ባንዳ ነው፡፡ቁጥራቸው የማይዘለቅ ሰዎች ከጠላት ጎን ቆመው ስለነጻነት የሚዋደቁትን ያሳድዱ ነበር፡፡ከበደ አለማየሁ የተባለውም ባንዳ ቀደም ሲል ራስ ዳርጌን ይረብሽ የነበረ የደራው ባላባት የሀሰን ጉራራ ልጅ የታጠቁትን ዐርበኞች በጣም የሚያስቸግርና የገዛ የሀገሩን ልጆች ይዞ ለጠላት በመስጠት በስቅላት ያስቀጣ ነበረ፡፡በኋላ ንጉሱ ሲመለሱ ይቅርታ ተደርጎለት እንደ ሰው መኖሩ የሚደንቅ ታሪክ ነው፡፡
ገድላቸው ተነግሮ የማያልቀው ዐርበኛ ኃይለማርያም ማሞ ስለጀግንነታቸው ብዙ ስንኞች ተቋጥረዋል፡፡አንዴ ሞረትና እንሳሮ ላይ ጦርነት ተደርጎ የሀገሬው ሴቶች ሳይቀሩ በመጥረቢያ ተጋድለው በድሉ በተሳተፉበት ቀን ልጅ ኃይለማርያምና ባላምበራስ ዘውዴ አባ ፈርዳ ጠላትን በመትረየስ እያጨዱ ሲያሰጡትእንዲህ ተባለ፤
እንስራ ሲሰበር ይሉታል ገመሞ፣
ከነአሽከሩ ተኳሽ ኃይለማርያም ማሞ፡፡
ሴቶች ተሰብሰቡ ኑ ጠላ ቅመሱ፣
እንደ ጎፍን እናት እንድትጠነስሱ፡፡
ፋሽስት ተሰብስቦ ሲጫወት ገበጣ፣
ያባጎፍንን አሽከር ጅም አፍራሹ መጣ፡፡
ልጅ ኃይለማርያም ከባላምባራስ አበበ አረጋይና ሌሎች ጋር የጦር ዕቅድ በማውጣት፣በመመካከር ብዙ ጀብድ ፈጽመዋል፡፡ለጠላት የማይገኙ ምትሃት ሆነው አስጨንቀውታል፡፡ይሁንና በሕይወታቸው ሳሉ‹‹እኔ ኃይለማርያም ማሞ ግንባሬን ተመትቼ ነው የምሞተው››እንዳሉት፣በመጨረሻው ቀን ጠላት ሰባ ሁለት ሺህ ጦር ሰብስቦ በመጣበት ጦርነት፣የእርሳቸው ጦር መንገድ በዘጋበት ታላቅ ፍልሚያ፣ቀደም ብሎ በዐርበኝነት ዘመን አብሯቸው የቆየውና የሚወዱት በርሄ ሲሞትባቸው ቴዎድሮስ ገብርዬ ሲወድቅ እንዳዘነው አዘኑ፡፡ቢሆንም ጦርነቱ አላበቃም፤ ከፍተኛ ውጊያ ላይ ተጠምደው ፣መትረየሳቸው ግሎ ውሃ በጨርቅ እየነከሩ ጠላትን ሲያርከፈክፉት ቆዩ፡፡እናም በደረታቸው ተኝተው ከሶስት መቶ በላይ ጥይቶች ተኩሰው በዚያው ልክ ጠላት ጥለው፣ብድግ ብለው ሲመለከቱ ከጠላት የተተኮሰች ጥይት ግንባራቸውን አገኘቻቸውና ወደቁ፡፡
ይህ ወሬ ከተሰማ በኋላ ጠላት በደስታ ሰክሮ፣ጦርነቱ ያበቃ ያህል ቆጥሮ ከበሮ ደለቀ፡፡በመላው ሀገሪቱ ላሉት ዐርበኞች የልጅ ኃይለማርያምን መሞት በወረቀት አስጽፎ በአውሮፕላን አስበተነ፡፡ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ የጀግና ደም ጀግና እንደሚያበቅል ላላወቀው ጠላት፣ ያገር ልጆች በሚነድድ እሳት ውስጥ እየነደዱ ተዐምር አሳዩት፡፡ዐርበኝነቱ በባሰ ቁጭትና ቁርጠኝነት ቀጠለ፡፡
‹‹መተኮሱንማ ማንም ይተኩሳል፣
ኃይለማርያም ማሞ አንጀት ይበጥሳል፡፡››
ተብሎ የተዘመረላቸውም ስለሚገባቸው ነበር፡፡ዛሬም እኛ እኒህን ታላቅ ዐርበኛ በጀግንነታቸው እናስባቸዋለን፤እንኮራባቸዋለንም፡፡

Read 2419 times